ማኅበረ ቅዱሳን 26ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን ሊያከብር ነው

በማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኙነት እና የትብብር አገልግሎት ማስተባበሪያ

ሚያዝያ ፳፫ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን 26ኛ ዓመት የምሥረታ በዓሉን በመንፈሳዊ ሥርዓት ሊያከብር መኾኑ ተገለጠ፡፡

ማኅበሩ ሚያዝያ 28 ቀን 2010 ዓ.ም፣ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ አዲስ አበባ ከተማ ከመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም አጠገብ በሚገኘው ሕንጻ፣ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን በዓለ ልደትና ማኅበሩ የተመሠረተበትን 26ኛ ዓመት የምሥረታ ቀን በመንፈሳዊ ሥርዓት እንደሚያከብር ከማኅበሩ የሕዝብ ግንኙነትና የትብብር አግልግሎት ማስተባበርያ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን የሕዝብ ግንኙነትና የትብብር አገልግሎት ማስተባበሪያ ሓላፊ፣ አቶ ደመላሽ አሰፋ እንዳስታወቁት በማኅበረ ቅዱሳን የምሥረታ ቀን መታሰቢያ በዓል አከባበር ላይ፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፣ ተጋባዥ እንግዶችን ጨምሮ በርካታ ሕዝበ ክርስቲያንና የማኅበሩ አባላት ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በዕለቱ የእንኳን በደኅና መጣችሁ መልእክት፣ እንደዚሁም ትምህርተ ወንጌል እና መዝሙር እንደሚቀርብ አቶ ደመላሽ አስታውቀዋል፡፡ የዕለቱ መርሐ ግብርም ከቀኑ 11፡00 ሰዓት እንደሚጠናቀቅ ሓላፊው አያይዘው ገልጸዋል፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን፣ ከቅዱስ ሲኖዶስ በተሰጠው ሕጋዊ ዕውቅና መሠረት ላለፉት 26 ዓመታት በርካታ መንፈሳዊውያን ተግባራትን ለቤተ ክርስቲያን ሲያከናውን መቆየቱና አሁንም አገልግሎት በመስጠት ላይ መኾኑ ይታወቃል፡፡