ማኅበረ ቅዱሳን ለሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ 90 ሺሕ ብር የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ

ጥቅምት 3 ቀን 2006 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

sewasew 1

ማኅበረ ቅዱሳን ለአንጋፋውና የሊቃውንት መፍለቂያ ለሆነው የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ 90 ሺሕ ብር የሚያወጡ ኮምፒዩተሮች፤ ፕሪንተሮችና መጻሕፍት ጥቅምት 1 ቀን 2007 ዓ.ም. ለኮሌጁ ደቀመዛሙርት አገልግሎት እንዲውል ድጋፍ አደረገ፡፡

ማኅበሩ ከኮሌጁ በቀረበለት ጥያቄ መሠረት የኮሌጁን ደቀመዛሙርት እውቀት ለማሳደግ የሚያስችሉ ግምታቸው 90 ሺሕ ብር የሚደርሱ 12 ኮምፒተሮች፤ 2 ፕሪንተሮች፤ እንዲሁም ማኅበረ ቅዱሳን በአማርኛና በኦሮምኛ ቋንቋዎች ያሳተማቸውን 184 መጻሕፍት በኮሌጁ አዳራሽ ርክክብ አድርጓል፡፡

በርክክቡ ሥነ ሥርዓት ላይ በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ሓላፊና የኮሌጁ ዋና ዲን ሊቀ ማእምራን ፋንታሁን ሙጬ ማኅበሩ ያደረገውን ድጋፍ አስመልከቶ ሲገልጹ “ኮሌጁ በርካታ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንን ያፈራ ነው፡፡ ዛሬም sewasew 2በማፍራት ላይ ቢገኝም በርካታ ችግሮች አሉበት፡፤ በዚህም መሠረት ደቀዛሙርቱ ከዘመኑ የቴክኖሎጂ ሽግግር ጋር ለማገናኘትና ከኢንተርኔት አጠቃቀም አንጻር ያለባቸውን ክፍተት ለመፍታት ለማኅበረ ቅዱሳን ባቀረብነው ጥያቄ መሠረት የኮምፒዩተሮችና የመጻሕፍት ድጋፍ በማድረጉ በመላው የኮሌጁ ማኅበረሰብና ደቀመዛሙርት ስም ምስጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ ማኅበሩ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነቱ እሰየሠጠ ካለው አገልግሎት አንጻር ወደፊት ተጨማሪ ድጋፎችንም እንደሚያደርግልን ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሐፊ አቶ ተስፋዬ ቢሆነኝ በበኩላቸው ኮምፒዩተሮችና መጻሕፍቱን ካስረከቡ በኋላ እንደገለጹት “ማኅበሩ ከኮሌጁ በተጠየቀው መሠረት ማድረግ ከሚችለው ውስጥ ትንሹን ነው ያደረገው፡፡ ወደፊትም ኮሌጁ በሚያስፈልገው፤ ማኅበሩ ደግሞ በሚችለው መጠን ድጋፍ ያደርጋል” ብለዋል፡፡

በኮሌጁ ውስጥ ከሚገኙት ሊቃውንት መካከል መምህር ሃይማኖት ኃይለ ማርያም ማኅበሩ ባደረገው ድጋፍ በሰጡት አስተያየት “የእግዚአብሔርን ለእግዚአብሔር ማድረግ መልካም ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ልጆች በመሆናቸው የቤተ ክርስቲያንን ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ነው የሰጡት፡፡ ሌሎችም ማኅበሩን አርአያ አድርገው ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል” በማለት ገልጸዋል፡፡

በኮሌጁ መምህራን የተዘጋጁ መጻሕፍትም ለማኅበረ ቅዱሳን ቤተ መጻሕፍት አገልግሎት እንዲውሉ በመምህራኑ አቅራቢነት፤ በኮሌጁ ዲን አማካይነት ለማኅበረ ቅዱሳን ተበርክቷል፡: