‹‹ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ›› (ዘፀ.፲፥፲፰)

ቀሲስ ከፍያለው ጥላሁን

ሰኔ ፳፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ጸሎት እግዚአብሔር አምላክን እንድንማጸን የሚረዳን ኃይል ነው፡፡ በተለያዩ ችግርና መከራም ሆነ በባርነት ውስጥ ያሉ ሰዎች በጸሎት አምላካቸውን በመማጸን መፍትሔም ያገኛሉ፤ ለዚህም ምሳሌ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እንመልከት፡፡

በቀደመው ዘመን ንጉሡ ፈርዖን የተወለደ ወንድ ሁሉ እንዲገደል ዐዋጅ አወጣ፤ እግዚአብሔርም በቸርነቱ የአዋላጆቹን ልብ በማራራት ነቢዩ ሙሴ የእስራኤል ሕዝብ መሪ ሆኖ ከግብፅ ያወጣቸው ዘንድ ስለፈቀደ በድብቅ ተወለደ፤ እናቱም ሦስት ወር ከደበቀችው በኋላ የወንድና የሴት ሕፃናት ድምጽ ሲያለቅሱ ስለሚለይ በድምጽ ለይተው እንዳይገድሉባት የደንገል ሳጥን አዘጋጅታ፣ ዝፍትና ቅጥራን ለቅልቃ በውስጡ ልጇን ካስተኛችው በኋላ ወደ ወንዝ ዳር ወስዳ በቄጠማ ውስጥ አስቀመጠችው፤ የሙሴ እኅት ማርያም ደግሞ እንጨት የምትለቅም መስላ ወንድሟን ትጠብቅ ነበር፡፡ (ዘፀ. ፪፥፪-፬)

ከዚህም በኋላ የንጉሡ ፈርዖን ልጅ ወደ ወንዝ ስትወርድ ሣጥኑን በቀጤማ ውስጥ ባየችው ጊዜ ደንገጥሮችዋን ልካ ሣጥኑን አስመጣችው፡፡ ሲከፍቱት በውስጡ ሕፃን አገኙ፤ እርሷም ሙሴን የሚያሳድግላት አጥታ ስትጨነቅ እኅቱ ሕፃኑን ጡት የምታጠባ ሴት ለማምጣት እንዲትፈቅድላት ከጠየቀቻት በኋላ የሙሴን እናት ወደ እርሷ አመጣችላት፡፡ እናቱም ልጇ ሙሴን ጡት ማጥባት ብቻ ሳይሆን ስለ ወገኖቹ ታሪክና ስለተቀበሉት መከራ እያስተማረች በቤተ መንግሥት አሳደገችው፡፡ ሙሴም በቤተ መንግሥት ይደግ እንጂ የወገኖቹን ሥቃይ ዘወትር ይሰማ ስለነበር የፈርዖን የልጅ ልጅ እንዳይባል በእምነት እንቢ አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ኑሮ ሲመቻችልን ቤተ ክርስቲያንን ሀገርን እና ወገንን እንዳንረሳ ከሙሴ ታሪክ መማር ያስፈልጋል፡፡

እስራኤላውያንን ‹‹በብርቱ ሥራም ያስጨንቋቸው ዘንድ የሠራተኞች አለቆችን ሾሙባቸው›› እንደተባለው ሙሴ ካደገ በኋላ እስራኤላውያን ከመከራ እንዲወጡ ምክንያት ሆናቸው፡፡ እርሱ ሕዝቡን እየመራ ወደ ምድረ ርስት ሲጓዝ ከፊቱ የኤርትራ ባሕር ተንጣሎ ተመለከተ፤ ከበስተኋላ ደግሞ ፈርዖን ጦር አሰልፎ ጎራዴ መዞ መጣበት፤ ሙሴ ግን አስቀድሞ እንዲህ ብሎ ጸልዮ ነበር፤ ‹‹አንተ ከእኛ ጋር ካልወጣህስ፥ ከዚህ አታውጣን፡፡›› (ዘፀ.፩፥፲፩፣ ፴፫፥፲፭)

ሰዎች በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥመንን ችግርና ፈተና ለማለፍ እንዲሁም ከቅኝ አገዛዝ እስር ለመውጣት እግዚአብሔርን መማጸን ያስፈልጋል፡፡ የእስራኤል ሕዝብም በኤርትራ ባሕርና በንጉሡ ጦር ሠራዊት መካከል ከባድ ፈተና አጋጠማቸው፡፡ በዚህም ጊዜ በሙሴ ላይ ጮኹ፤ በግብፅ የነገረህ ስላልኖረ በምድረ በዳ እንሞት ዘንድ አወጣኸንን? ከግብፅ ታወጣን ዘንድ ይህ ያደረግህብን ምንድን ነው? በምድረ በዳ ከምንሞት ብንገዛላቸው ይሻላልና። ተወን፥ ለግብፃውያን እንገዛ ብለን በግብፅ ሳለን ያልንህ ቃል ይህ አይደለምን? አሉት። ሙሴም መልሶ እንዲህ አላቸው፤ ‹‹አትፍሩ፥ ዛሬ የምታዩአቸውን ግብፃውያንን ለዘላለም አታዩአቸውምና ቁሙ፥ ዛሬ ለእናንተ የሚያደርጋትን የእግዚአብሔርን ማዳን እዩ። እግዚአብሔር ስለ እናንተ ይዋጋል፥ እናንተም ዝም ትላላችሁ።›› (ዘፀ. ፲፬፥፲፩-፲፬)

እኛም በዚህ ጊዜ በሀገር፣ በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በሕዝብ ላይ መከራ ሲደርስ እንዴት  እንወጣዋለን ብለን እንጨነቃለን፡፡ ነገር ግን ችግራችንን ሁሉ መፍትሔ ላለው ለእግዚአብሔር ብንሰጥ መልስ እናገኛለን፤ ሙሴም እንዳለው በጸሎት አምላካችንን ከመከራና ካለብን ሀገራዊም ሆነ ማኅበራዊ ችግር እንዲያወጣን ዝም ብለን  በትዕግሥት በመጠበቅ አለብን፡፡ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ የእግዚአብሔር ሰዎች ትልቁ ጋሻ መከታቸው እንዲሁም ኃይላቸው ጸሎት ነውና፡፡ ለዚህም ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ መልእክቱ እንዲህ ብሏል፤ ‹‹በምንም አትጨነቁ፤ ነገር ግን በሁሉ ነገር ጸልዩ፤ ማልዱም፤ እያመሰገናችሁም  ልመናችሁን ለእግዚአብሔር ግለጡ፡፡›› (ፊል.፬፥፮)

በውስጥም በውጭም፣ በጥቂትም በብዙም፣ በሚታይም በማይታይም ነገር ሁሉ በመጸለይና በቅድስት ድንግል ማርይም፣ ቅዱሳን መላእክት፣ ነቢያት፣ ሐዋርያት፣ ጻድቃን፣ ሰማዕታት ምልጃ በመማጸን ከምስጋና ጋር ፈተናችንን፣ ስደታችን፣ መታረዛችንን ማለፍና ሞትን መጋፈጥ ይቻላልና በጸሎት መትጋት አለብን፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስም እግዚአብሔር አምላካችን ‹‹እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት›› ብሎናል፡፡ (፩ጴጥ.፭፥፯)

የሙሴ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር በደረሰ ጊዜም ባሕረ ኤርትራን በበትሩ ይከፍል ዘንድ ተቻለው፤ ቅዱሳን የነፍሳቸው ቅድስና ለሥጋቸው፣ ለጥላቸው፣ ለልብሳቸው፣ ተርፎ በማቋሚያቸውም ተአምር ይሠራሉ፡፡ ሙሴም ባሕሩን ከፈለው፤ ከ፭፻፼ (ከአምስት መቶ ሺህ) በላይ የሚሆነው ሕዝበ እስራኤልም እንደ የብስ ባሕሩን ተረግጠው ተሻገረ፡፡ ፈርዖንና ሠራዊቱ ግን እስራኤልን ለመያዝ ወደ ባሕሩ በሚገቡበት ጊዜ ዳግመኛ እግዚአብሔር ሙሴ በባሕሩ ላይ በትሩን እንዲዘረጋ አዘዘው፤ ባሕሩም ወደ ነበረበት ሥፍራ ተመልሶ መፍሰስ ጀመረ፤  ወደ ባሕሩ የገቡትን የፈርዖንንም ሠራዊት ሁሉ አጠፋቸው፡፡ (ዘፀ.፲፬፥፳፩-፳፰)

በሰው ላይ ግፍ የሚሠሩ፣ በደል የሚፈጽሙ፣ በምድርም በሰማይም የሥራቸውን እንደሚያገኑ ከፈርዖንና ከሠራዊቱ ታሪክ መረዳት እንችላለን፡፡ የተወለደው ወንድ ሁሉ እንዲገደል በማድረጉ ሕዝበ እስራኤልን ለመከራና ሥቃይ ስለዳረግም እርሱና ሠራዊቶቹ በሙሉ በውኃ ውስጥ ሰጥመው ሞቱ፡፡ እስራኤላውያንም ውኃ እንደ ግድግዳ ሆኖላቸው ከተሻገሩና ጠላቶቻቸው ፈርዖንና ሠራዊቱ ከሞቱ በኋላ የሙሴ እኅት ማርያም ከበሮዋን አንሥታ ‹‹ባሕሩን ለከፈለ፣ ጠላት ላሰጠመ፣ ከጠላት ለታደጋቸው አምላክ ምስጋና ይገባል›› በማለት ዘመረችለት፡፡

ከዚህም በኋላ እስራኤላውያን ጉዞአቸውን ቀጠሉ፤ እግዚአብሔርም ከዐለት ላይ ውኃ እያፈለቀ እና ከሰማይ መና እያወረደ በመመገብ ምድረ ርስት እንዲገቡ አደረጋቸው፡፡ እስራኤል ከመከራ የዳኑበት ዋናው መሳሪያ ጸሎት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ እኛም መከራ ሲመጣብን ተግተን መጸለይ አለብን፡፡ አማናዊው ሙሴ መድኃኔዓለም የኃጢአትን ባሕር ከፍሎ ወደ ቀደመ ቦታችን ለመመለስ በሥጋ ማርያም ተገለጠ፤ መጸለይ የማይገባው አምላክ በጌቴሴማኔ ተገኝቶ እንደጸለየ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሷል፡፡ እኛም በፈተና ሰዓት በጸሎት እንድንጸና በጸሎት ወደ እርሱ እንድንመለከት ራሱ ጸልዮ እንዳንጸልይ አስተማረን፡፡

ሐዋርያትም በአንድ ልብ ሆነው ጸልየዋል፤ እኛ በክርስቶስ ክርስቲያን በወልድ ውሉድ ተሰኝተን፣ ወንድ በ፵ ቀን ሴት በ፹ ቀን በማሕፀነ ዮርዳኖስ ከመንፈስ ቅዱስ ብንጸልይም  በአንድ ልብ መጸለይ አቅቶናል፡፡ ሁላችን ስንጸልይ አባታችን ሆይ እንጂ አባቴ ሆይ ብለን አንጸልይም፤  የሁላችን አባት አንድ እግዚአብሔር እንደሆነ ሁሉ እኛም ልጆቹ አንድ መሆናችን በዚህ መረዳት አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህም አንድ ልብ ልንሆን ሲገባ ነገር ግን መለያየት በዝቷል፡፡ ጸሎታችንም መልስ እንዳያገኝ ከሚያደርጉብን ነገሮች መካከል አንዱ በአንድነት አለመጸለያችን ነው፡፡ እስራኤል ዘሥጋ ከሙሴ ጋር ወደ እግዚአብሔር እንደ ጮኹና እግዚአብሔርም ሰምቶ እንዳዳናቸው ሁሉ እኛም ለቅዱሳኑ፣ ለጻቃኑና ለሰማዕታቱ ብሎ በአሁኑ ጊዜ በውስጥም በውጭም፣ በአንድም በሌላም ፈተና ላይ ያለች ኢትዮጵያን እንዲሁም ቤተ ክርስቲያንን እንዲታደግልን በአንድነት ወደ እግዚአብሔር መጮህ አለብን፡፡

በዘመነ ሐዋርያት ጌታችን ኢየሱስ ሐዋርያትን የሚበላ እንዳላቸው ሲጠይቃቸው ሌሊቱን በሙሉ ሲደክሙ ቢያድሩም አንድም ዓሣ ማጥመድ እንዳልቻሉ ነገሩት፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ፈቃድ በጸሎት አልጠየቁም ነበርና፡፡ ከሁሉ አስቀድሞ እግዚአብሔርን በጸሎት መጠየቅ አስፈላጊ ነው፡፡  በዚህ ጊዜም ለረጅም ዓመታት ተምረው ሥራ ያጡ ሰዎች አሉ፤ ለፍተውም ስኬታማ ያልሆኑም በርካቶች ናቸው፤ በትዕግሥት በጸሎት ሊጠይቁት ይገባል፡፡ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር የለምና፡፡ አባቶቻችን በጦርነትም ሆነ በመንፈሳዊ ተጋድሎ ድልን የተቀዳጁት እግዚአብሔርን በጸሎት እየጠየቁና ኃይልህን አሳድርብን እያሉ ስለወጡ ነው፡፡ ስለዚህ ሐዋርያትም ጌታችን ኢየሱስ መረባቸውን በታንኳዩቱ በስተቀኝ በኩል እንዲጥሉት ካዘዛቸው በኋላ በአንድ ጊዜ ፻፶ (መቶ ኀምሳ) ዓሣዎችን አጥምደዋል፡፡ ይህም የሆነው ለመታዘዝ ፈቃደኞች ስለሆኑ ነው፡፡ (ዮሐ. ፳፩፥፭-፮)

ሰማያዊውን አምላክ ስናመልክና እርሱን በጸሎት ስንጠይቅ ሁሉም ነገር ይስተካከላል፡፡ በአንድም በሌላም መንገድ በሀገር፣ በሕዝብ፣ በቤተ ክርስቲያን ላይ ፈተና ሲመጣ መጮህ ያለብን ወደ እግዚአብሔር ነው፡፡ እግዚአብሔር ጸሎታችንን ሰምቶ መዓቱን በምሕረት፣ ቊጣውን በትዕግሥት እንዲመልስልን የእኛ አካሄድ ከገንዘብና ከዕውቀት፣ ከዘር ወይንም ከሥልጣን ጋር ሳይሆን ከእግዚአብሔር ጋር መሆን አለበት፤ መጨረሻችን እንዲያሳምርልን  የአምላካችን ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፤ አሜን፡፡