መልእክት

ከመጽሐፈ ስንክሳር

ጳጉሜን ፭ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ክርስቶስ በከበረ ደሙ የዋጃችሁ ሃይማኖታችሁ የቀና የተወደዳችሁ ምእመናን ሆይ ልዑል እግዚአብሔርን ልናመሰግነው ይገባናል። በይቅርታው ገናናነት በጎ የሆኑትን ሁሉ ስለሰጠን የልዕልናውን ምስጋና ጨምረን እጅግ ልናበዛ ይገባናል። እስከዚህች ዕለትና ሰዓት  አድርሶናልና።

ዳግመኛም ከበደላችንና ከክፉ ሥራዎቻችን ወደ ንስሐ እስከምንመለስ በእኛ ላይ ይታገሥ ዘንድ ከእኛ አስቀድሞ ብዙዎች አሕዛብን እንዳጠፋቸው ስለ ክፉ ሥራችን እንዳያጠፋን እግዚአብሔርን እንለምነው። እንግዲህም ከታካችነታችን ነቅተን ከወደቅንበት እንነሣ ስለ አለፈው በደላችንና ስለ ብዙ ኃጢአታችን በፊቱ ልናለቅስ ወደርሱም ልንጮህ ይገባናል።

በሕይወታችን ዘመን ሁሉ ከጠላችን ሰይጣን ወጥመድ ጠብቆ በቀናች ሃይማኖት ያጸናን ዘንድ በነፍስ በሥጋም ጤነኞች እንደሆን በቀናች ሃይማኖትና በበጎ ሥራ ሁሉ ጸንተን ደስ እንዳለን እንደ ዛሬው ለመጪው ዓመት ያደርሰን ዘንድ እንለምነው።

ከእኛም በሞት የተለዩትን በበጎ ዕረፍት እንዲያሳርፍልን፣ በሀገራችንም ጽጋብን በረከትን ይሰጥ ዘንድ፣ የተራቡም እንዲጠግቡ የምድራችንን ፍሬ ይባርክ ዘንድ፣ በሽተኞች ይፈወሱ ዘንድ፣ ሽማግሎዎችና አሮጊቶች፣ የሙት ልጆችም ይጠበቁ ዘንድ ለሀገራችንና ለዓለሙ ሁሉ ሰላም ይሁን!አሜን፡፡

ምንጭ፡ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ጳጉሜን