መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

-ብፁዕ አቡነ ያሬድ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና
የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
– ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ
የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና
የምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
– ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
– የተከበራችሁ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የየመምሪያውና የየድርጅቱ ኃላፊዎች፣
– የየሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆችና ተወካዮች፣
– የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣
– ከልዩ ልዩ አህጉረ ዓለም የመጣችሁ፣ የጉባኤው ተሳታፊዎች፣
– በአጠቃላይ በዚህ ዓመታዊና ዓለም አቀፋዊ የሰበካ ጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባኤ ለመሳተፍ በክብር የተገኛችሁ ክቡራንና ክቡራት፣
እግዚአብሔር አምላክ በማይሰፈር ሀብተ ጸጋው ያለፈውን የሐዋርያዊ ተልእኮ ሥራችንን ባርኮና ቀድሶ ለአዲሱ ዓመት ስላደረሰንና ለዚህ ዓመታዊ ጉባኤ ስለሰበሰበን ስሙ የተመሰገነ ይሁን ፡፡
‹‹አድኅነነ እግዚኦ አምላክነ፤
ወአስተጋብኣነ እምኣሕዛብ፣
ከመ ንግነይ ለስምከ ቅዱስ፣
ወከመ ንትመካሕ በስብሐቲከ፤
አምላካችን እግዚአብሔር ሆይ አድነን፤ ቅዱስ ስምህን እናመሰግን ዘንድ፣ በምስጋናህም እንመካ ዘንድ ከአሕዛብ መካከል ሰብስበን›› (መዝ.105፡47)
የእስራኤል ንጉሥና ነቢይ የነበረው ቅዱስ ዳዊት ይህ ከዚህ በላይ የተገለፀውን ቃለ መዝሙር ለእግዚአብሔር ሲያቀርብ ዋና ግቡ እግዚአብሔርን ማመስገን እንደሆነ እንገነዘባለን፤ በገጸ ንባቡ እንደሚታየው የንጉሡ ጸሎት ሕዝቡን ከአሕዛብ መካከል እንዲሰበስባቸውና እንዲያድናቸው አምላኩ እግዚአብሔርን ይማጸናል ፡፡
ይህንን ጸሎት ለማቅረብ የፈለገበትም ምክንያት ሲገልጽ ሕዝቡ በአንድነት ሆነው እሱን እንዲያመሰግኑ፣ በምስጋናውም እንዲመኩ ሽቶ እንደሆነ ገልጿል፡፡
ሁኔታው ይህን የመሰለ ለሕዝብ የመቆርቆርና የማስተንተን መንፈስ ከአንድ የሕዝብ መሪና አስተናባሪ እንደሚጠበቅ ፍሬ ነገሩ ያሳያል፡፡
ከሁሉ በፊት ግን ለማመስገንም ሆነ ለማምለክ የሕዝቡ ደኅንነት እንደሚያስፈልግ፣ ደኅንነት ብቻም ሳይሆን አንድ ላይ መሰባሰብም ቅድሚያ የሚሰጠው እንደሆነ ልበ አምላክ ዳዊት ሳይገልፅ አላለፈም፡፡ በእርግጥም የሕዝቡ ደኅንነት ካልተጠበቀ፣ አንድ ላይ ተሰባስቦም በፍቅርና በኅብረት ካልተገኘ፣ ምስጋናም አምልኮም በአግባቡ ሊከናወን አይችልም፤ ቅዱስ ዳዊት የዚህን አስፈላጊነት በመንፈስ ቅዱስ ተገንዝቦ ነው ከአሕዛብ መካከል ሰብስበን፣ አድነንም፣ ከዚያም ስምህን እናመሰግናለን፤ በስምህም እንመካለን ብሎ የጸለየው ፡፡
ቅዱስ ዳዊት ለሚመራቸውና ለሚያስተዳድራቸው ሕዝበ እሥራኤል መጸለይ ብቻ ሳይሆን፣ የእነሱ ቤዛ ሆኖ እስከሞት ድረስ መሥዋዕት ለመሆን ‹‹ምንተ ገብሩ እሉ አባግዕ ዘአነ ኖላዊሆሙ ዳዕሙ ለትረድ እዴከ ላዕሌየ ወላዕለ ቤተ አቡየ›› ‹እረኛቸው ጠባቂያቸው የሆንኩላቸው እነኝህ በጎች ምን አደረጉ? እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ትሁን እንጂ› ብሎ አምላኩን የተማፀነ ንጉሥና ነቢይ እንደሆነም ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል ፡፡
– ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!
– ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፣
የቅዱስ ዳዊት መንፈሳዊ ተሐውኮና እስከ ቤዛነት የሚዘልቅ የመሪነት ብቃት ለሰው ልጆች በአጠቃላይ፣ በተለይም ለቤተ ክርስቲያን መሪዎች በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡
ዳዊት ይመራቸው የነበሩ ሕዝቦች መዳንና መሰባሰብ ያስፈልጋቸው እንደነበረ ሁሉ፣ ዛሬም መዳን፣ መሰባሰብ፣ አንድ መሆን የሚስፈልጋቸው ሕዝቦች አሉን፤ እነዚህ የምንመራቸው ሕዝቦች ቅዱስ ስሙን እንዲያመሰግኑና በስሙ አምነው እንዲኖሩ እኛ ስለእነሱ መዳን አዘውትረን መጸለይ አለብን፤ በአንድነት እንዲሰባሰቡም ማስተማርና መምከር፣ ማስታረቅና ማግባባት አለብን ፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስለሕዝቦች ሁለንተናዊ ደኅንነት መጸለይ፣ ማስተማርና መምከር ከእግዚአብሔር የተቀበለችው ዓቢይ ተልእኮ ከመሆኑ የተነሣ ዘወትር የምታከናውነው ተቀዳሚ ተግባርዋ ቢሆንም፣ በተለይም አሁን ባለንበት ወቅት በከፍተኛ ደረጃ በጸሎትና በማስተማር፣ በመምከርና በማስታረቅ ተግታ የምትሠራበት ጊዜ እንደሆነ እንገነዘባለን ፡፡
ዛሬ ሀገራችን በተስፋና በሥጋት መካከል ተወጥራ ያለችበት፣ የቤተ ክርስቲያናችን ማእከላዊ መዋቅርም በልዩ ልዩ ቡድኖች እየተፈተነ የሚገኝበት አሳሳቢ ወቅት ላይ ነን፡፡ በዚህ ፈታኝ ወቅት ቤተ ክርስቲያናችን ትዕግሥት ያልተለየው ጥበብና ብልሃት ተጠቅማ ልጆችዋን ወደ አንድነት ማሰባሰብ ከምንም በላይ ተቀዳሚ ተግባር አድርጋ መውሰድ ይጠበቅበታል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡራንና፣ ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፣ ቤተ ክርስቲያናችን ከእግዚአብሔር የተሰጣት የማስታረቅና የማስተማር፣ የመምከርና የማሰባሰብ ኃላፊነት የምታከናውነው አንዱን በማራቅ፣ ሌላውን በማቅረብ አንዱን በመደገፍ ሌላውን በመንቀፍ ሳይሆን ሁሉም ልጆችዋ ናቸውና በእኩልነት፣ በአንድነት፣ በፍቅርና በገለልተኝነት መሆን እንዳለበት መዘንጋት የለብንም፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን ከፖለቲካ ንክኪ ፍጹም ነጻ ሆና ሥራዋን እንድትቀጥል ማድረግ የሁላችንም የቤተ ክርስቲያን አመራሮች፣ አገልጋዮችና ሠራተኞች የውዴታ ግዴታ ነው፡፡ ሆኖም ስለሰው ልጆች ደኅንነትና እኩልነት፣ ሰላምና አንድነት የእግዚአብሔር ቃልን መሠረት አድርጋ በሰፊው የማስተማር ኃላፊነት እንዳለባት መርሳት የለብንም፡፡ በሀገራችን እየታየ ያለው ያለመግባባት መንፈስ በሁለት ምክንያቶች እንደሆነ ይታያል፤ ይኸውም በአንዱ ወገን የመለያየት ሥጋትን የሚከላከል ሲሆን በሌላ ወገን ደግሞ የእኩልነት እጦት ሥጋትን የሚከላከል ሆኖ ይስተዋላል፡፡ የግራና ቀኙ ሥጋት ለምን ይታሰባል ባይባልም መድኃኒት የሌለው ሥጋት ይመስል ይህን ያህል መጠራጠሩና መራራቁ ግን ተገቢ ሆኖ አይታይም፤ ምክንያቱም ሁሉም እንደሚያምንበት የዚህ ፍቱን መድኃኒት እኩልነትን ከአንድነት፣ አንድነትን ከእኩልነት ጋር አጣምሮ መያዝ እንደሆነ አያከራክርምና ነው፡፡ ኢትዮጵያውያንም ይህንን ሊዘነጉት አይገባም፤ ሕዝቡም በዚህ ላይ በሰፊው እንዲያስብበት ያስፈልጋል፡፡
• ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
• ክቡራንና ክቡራት የጉባኤው ተሳታፊዎች፤

የሰበካ ጉባኤ ዓላማ ካህናትን ምእመናንና ወጣቶችን በአንድ ሕጋዊ መዋቅር አደራጅቶ ሃይማኖትን ማስተማር ማስፋፋትና ማስጠበቅ እንደዚሁም የቤተ ክርስቲያን ሀብትና ንብረትን በቅዱስ ሲኖዶስ ማእከላዊ አስተዳደር በሕግና በሥርዐት እየተቆጣጠሩ ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ማዋል ነው፤ ከዚህ ውጭ መቼም፣ የትም ቢሆን የቤተ ክርስቲያናችን መዋቅር ተጠብቆ በስሟ የሚሰበሰብ ሀብትና ንብረት ሁሉ በእሷ ዕውቅናና ጥበቃ ሥር ሆኖ የማይከናወን አሠራረር ሥር እየሰደደ ከሄደ፣ የቤተ ክርስቲያን አንድነት ፈተና ላይ መውደቁ አይቀሬ ነው፡፡ ይህ በቤተ ክርስቲያናችን እያቆጠቆጠ የመጣው የሀብት ሽሚያ ክፉ መንፈስ አንዱ ሌላውን እየወለደ ሄዶ ዛሬ የራሳችን ቤተ ክህነት እናቋቁማለን እስከማለት ተደርሶአል፡፡

ይህ ጥያቄ ሊመጣ የቻለው እውነት ቤተ ክርስቲያን የቤተ ክህነት ጽ/ቤት ያላቋቋመችበት አካባቢ በኢትዮጵያ ኖሮ ነውን? ክርስቲያን ልጆችዋ በሚሰሙት ቋንቋ እንዳይማሩስ እውነት ከልክላ ነውን? መከልከል ቀርቶ መጽሐፉን አስተርጉማና አሳትማ ሳታሠራጭ ቀርታ ነውን? ይህ ሁሉ ፍጹም ሐሰት ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ በስተጀርባ ያለው ሐቅ ሌላ ነው፤ ከቤተ ክርስቲያን ማእከላዊ የፋይናንስ እይታ ውጭ በቤተ ክርስቲያን ስም የደለቡ ቡድኖች መኖራቸው ስለሚታወቅ፣ እኛም በተመሳሳይ የተለየ ቤተ ክህነት አቋቁመን ሀብት እናድልብ ነው ጥያቄው፤ ይህ አዝማሚያ የቤተ ክርስቲያንን ምጣኔ ሀብት የሚያሽመደምድ፣ አንድነትዋንም የሚፈታተን ስለሆነ ሁሉም ወገኖች ለኛ ማለትን ያቁሙና ለቤተ ክርስቲያናችን የሚለውን ቅን መርህ ይከተሉ፤ ሁሉም በአንዲት የቤተ ክርስቲያን ማእከላዊ መዋቅር ሥር ሆነው ጥያቄአቸውን በተገቢውና በሕጋዊ መንገድ ማቅረብ ይችላሉ፤ ከቅን አመለካከትና ከተቈርቋሪነት የሚመነጭ፣ ለቤተ ክርስያን ጠቃሚ የሆነ፣ ሕግና ሥርዓትን የተከተለ፣ መዋቅሩን የጠበቀ ጥያቄ ከምእመናን ካለ አባቶች ለማስተናገድ ዝግጁ የማንሆንበት ምክንያት የለም ፡፡

ከዚህ ውጭ ግን ከሚያስተዛዝበን በስተቀር የጊዜ ጉዳይ እንጂ አያዛልቅም፣ ቅዱስ ሲኖዶስም እግዚአብሔር በዳዊት አድሮ እንደተናገረው ሕዝቡን ለመሰብሰብ እንጂ በተለያዩ አደናጋሪ አባባሎች ሕዝቡን በቡድን ሊከፋፍል አልተፈጠረምና ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ስሕተት እንዳይፈጸም እንጠንቀቅ፣ የሰበካ ጉባኤ ዓላማና ተልእኮም ሊሳካ የሚችለው በቤተ ክርስቲያን ስም የሚሰበሰበው ማናቸውም ሀብትና ንብረት ቤተ ክርስቲያኒቱ በምታውቀውና በምታጸድቀው፣ እንደዚሁም ማእከላዊ አሠራሩን ጠብቆ በሚፈጸም መንፈሳዊና ማኅበራዊ፣ ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ፣ ኢኮኖሚያዊና አስተዳደራዊ አሠራር እንጂ፤ የቤተ ክርስቲያንን ሀብት ለመሻማት ጓጉተው በየጊዜውና በየአካባቢው በሚፈጠሩ የልዩ ልዩ ቡድኖች አስመሳይ የእናውቅላችኋለን ስብከት አይደለም፡፡ ስለሆነም ይህ ዓቢይ ጉባኤ ጉዳዩን በአጽንዖት እንዲያጤነው ወቅታዊና አባታዊ መልእክታችን ነው፡፡

በመጨረሻም

ይህ ዓቢይ ጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት የሚያስጠብቅ፣ የሀብትዋና የንብረትዋ ማእከላዊ አስተዳደርን የሚያስከብር ነውና የሀገራችን ሰላምና ልማት፣ የሕዝባችን እኩልነትና አንድነት እንደዚሁም የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነትና የሀብቷና የንብረቷ ተጠቃሚነት እውን የሚያደርግ ዓቢይና ላዕላዊ ጉባኤ እንደመሆኑ መጠን፣ እነዚህን ተግባራት በማረምና ሥርዐት በማስያዝ ረገድ በበጀት ዓመቱ ጠንክሮ እንዲሠራ በማሳሰብ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፤ ዓመታዊውንና ዓለም አቀፉን የሰበካ ጠቅላላ መንፈሳዊ ጉባኤ መከፈቱንም በዚሁ እናበሥራለን ፡፡ መልካም የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አሜን
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
ጥቅምት 5 ቀን 2012 ዓመተ ምሕረት
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ