መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የእንኳን አደረሳችሁ ቃለ በረከት!

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

-በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣

-ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣

-የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣

-በሕመም ምክንት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤

-እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤት የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵውያት በሙሉ!

የዓመታትና የአዝማናት ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለአዲሱ ዓመት ለሁለት ሺህ ዐሥራ አምስት ዓመተ ምሕረት ዘመነ ሉቃስ በሰላም አደረሳችሁ !!

“ወዓመቲከኒ ለትውልደ ትውልድ፤ ዓመቶችህ ለልጅ ልጅ ናቸው” (መዝ. ፻፩፥፳፬)፡፡

ይህንን ቃለ እግዚአብሔር የተናገረው እግዚአብሔር በቅብዕ ቅዱስ አማካኝነት ሀብተ ትንቢት ወመዝሙር ያሳደረበት ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት ነው፤ የቃሉ መሠረተ ሐሳብም ዓመታት የእግዚአብሔር ስጦታ መሆናቸውን፣ እንደዚሁም የተሰጡት ለሰው ልጆች መሆናቸውን ይገልፃል፡፡ በእርግጥም ዓመታት ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች የተሰጡ ሀብቶች ናቸው፤ ዓመታት፣ ወራት፣ ዕለታት፣ ቀናት፣ ሰዓታት የሚያስፈልጉት ለሰው ልጅ እንጂ ለእግዚአብሔርና በመንፈሳዊ ዓለም ለሚገኙ ፍጡራን አይደለም፤ ምክንያቱም ሰው በደካማው ዓለም የሚኖር ደካማ ፍጡር ስለሆነ ለኑሮው ጊዜያት የግድ ያስፈልጉታል፤ በመንፈሳዊ ዓለም የሚገኙ ፍጡራን ግን፣ ድካም የሌለባቸው ትጉሃን ስለሆኑ፣ ዓመትም ቀንም ሰዓትም ወዘተ አያስፈልጋቸውም፤ የሰዓት መለኪያ ብርሃንም የላቸውም፤ ምክንያቱም ያሉበት ዓለም ሁሌም ብርሃን እንጂ ጨለማ ስለማይፈራረቀው፣ እንደዚሁም ተለዋዋጭ አየርም ሆነ ዕድሜ ስለሌላቸው ማለት ነው፤ ለሰው ግን የጊዜ መለኪያ የሚሆኑ ብርሃናትና አዝማናት ወዘተ የተመደቡለት ስለሆነ፣ በእነሱ እየተመራ ጊዜያትን ይለካል፤ ዓመታትን ወራትንና ቀናትን ወዘተ ይቈጥራል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፡-

ዓመታት ከእግዚአብሔር ለእኛ የተሰጡን ያለምክንያት አይደለም፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ሁሉ ክብርም ጥቅምም አለውና ልናከብረውና ልንጠቀምበት እንጂ፤ ሁላችንም እንደምንገነዘበው ጊዜ ትልቁና ቀዳሚው የሥራ መሣሪያ ነው፡፡ እህልን ዘርተን የዓመት ምግባችንን የምናገኘው ወርኃ ክረምት ስለተሰጠን ነው፤ ይህ ወቅት ባይኖር ኖሮ የእርሻ ሥራ ሠርተን ራሳችንን መመገብ እንደማንችል የምንስተው አይሆንም፡፡ ከዚህ አንጻር ዓመታትንና ወቅቶችን እንደ አመቺነታቸው እየተጠቀምን ልንሠራባቸው እግዚአብሔር አመቻችቶ ሰጥቶናል ማለት ነው፤ ስለዚህ በብሂለ አበው “ጊዜ ሳለ ሩጥ ….” እንደሚባለው ሁሉንም በጊዜው ጊዜ መሥራትና ተጠቃሚ መሆን ያስፈልጋል፡፡ ሰውም ሆነ ጊዜ ለሥራ የተፈጠሩበት ምክንያት መክበርም መዳንም ማግኘትም ማደግም መልማትም በሥራና በሥራ ብቻ የሚገኝ ከመሆኑ የተነሣ እንደሆነ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፤ “ብላዕ በሐፈ ገጽከ፤ በፊትህ ላብ እንጀራህን ብላ” የሚለው አምላካዊ ትእዛዝም ይህንን ይገልጻል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፡-

እግዚአብሔር አምላክ ያለመታከት ሠርተን ራሳችንን በራሳችን የምናስተዳድርባት በሀብትና በጊዜ የተዋበች ምድር አስረክቦናል፤ ምድሪቱንም ለእኛ በሚመች አኳኋን አበጅተን እንድንጠቀምባት የሚያስችል አእምሮና ጉልበትም ከጤና ጋር ሰጥቶናል፤ ሐቁ ይህ ከሆነ ታድያ ለምንድን ነው በምድራችን ስጋትና ጭንቀት፤ ረኃብና እርዛት፣ የሀብት እጥረትና የእርስ በርስ ግጭት በስፋት የሚታየው የሚለውን ጥያቄ ሰው ሁሉ በጥልቀት ሊያጤነው ይገባል፡፡ እግዚአብሔር የሰጠን ምድር አሁንም ለፍጡራን የሚበቃ የተትረፈረፈ ሀብት ያለጥርጥር አላት፣ የአጠቃቀም ጉዳይ ካልሆነ በቀር ሀብት የሌለው የምድር አካባቢ ፈጽሞ የለም፡፡ ይህም ከሆነ ሁሉም ወደ ሥራና ሥራ ብቻ ተሠማርቶ ጥረቱን ከቀጠለ የሚያጣው ነገር የለም ማለት ነው፣ ሰው ጤና ዕውቀትና ሰላም ካለው ሀብታም ነው፤ ምክንያቱም እነዚህ ከተሟሉለት ሌላው ሁሉ እግዚአብሔር ከሰጠው ምድር ሠርቶ የሚያገኘው ነው፡፡ ሰላም ከሌለ ግን ነገሩ ሁሉ ጨለማ ይሆንበታል፤ አካላዊና አእምሮአዊ ጤናውም ይደፈርስና ሳያጣ ያጣ ወደ መሆን ይቀየራል፡፡ ዛሬ በሀገራችንም ሆነ በዓለማችን እየተከሠተ ያለው ሐቅ ይኸው ነው፡፡

ይህ የሰላም እጦት በሀገራችን በኢትዮጵያ በርከት ላሉ ዓመታት እየተደጋገመ በመከሠቱ፣ በዚህ ጠንቅ ሕዝባችን ሳያጣ ያጣ ሆኖአል፤ ኢትዮጵያን በመሰለች ለምና ምድራዊት ገነት ተቀምጠን፣ በዓለም ውስጥ የድህነት ተምሳሌት ሆነን መገኘታችን፣ የሁላችንም ኅሊና ሊኰረኲረው ይገባል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት

በአዲሱ ዓመት ለኢትዮጵያውያን ልጆቻችንና ወገኖቻችን ሁሉ በአጽንዖት የምንመክረው ዓቢይ ምክር በግጭት ችግሮቻችንን መፍታት በፍጹም አንችልም፤ በመራራቅም ማደግ አንችልም፤ በተለያየን ቊጥር ድህነታችንን ከማስቀጠልና ደካሞች ከመሆን በቀር የምናገኘው አንዳች ፋይዳ የለም፤ እውነቱ ይህ ከሆነ ከገባንበት ያላስፈላጊ ግጭት በፍጥነት ወጥተን ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት ወደሚያስችል ወደ ምክክርና ውይይት እንግባ፤ አዲሱ ዓመት እውነተኛ አዲስ ዓመት ሊሆን የሚችለው ይህንን ያደረግን እንደሆነ ነው፡፡ አሮጌውን አስተሳሰብ እንዳለ ተሸክመን ለመቀጠል እየዳዳን ከሆነ አዲስ ዓመት ማለቱ የአፍና የጆሮ ቀለብ ከመሆን በቀር የሚሰጠን አንዳች ትርጉም የለም፡፡ ስለሆነም አዲሱን ዓመት አዲስ የሆነ የሰላምና የዕርቅ የስምምነትና የአንድነት የይቅርታና የምሕረት የፍትሕና የእኩልነት መርሕ አንግበን ፍጹም ሰላምን ለማንገሥ በቊርጥ ማሰብና መነሣሣት አለብን፣ ይህንንም ለማሳካት በአንድ አዳራሽ፣ በአንድ ጠረጴዛ ተገናኝተን ችግሮቻችንን በውይይትና በምክክር እንድንፈታ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም

አዲሱ ዓመት የሰላም የፍቅር የበረከት የዕድገት የሃይማኖትና የልማት ዓመት እንዲሆንልን ወደ እግዚአብሔር በመጸለይና በብሩህ ተስፋ እንድንቀበለው መልእክታችንን በድጋሚ በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር መልካም አዲስ ዓመት ያድርግልን !

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ !!

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን !!!

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ

ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት

መስከረም ፩ ቀን ፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

አዲስ አበባ፤ ኢትዮጵያ፡፡