ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣ

ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ
ሐምሌ ፲፰ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! እንዴት አላችሁልን? እንኳን ለወርኃ ክረምቱ አደረሳችሁ! በእግዚአብሔር ቸርነት፣ የተዘራው እህል በቅሎ ምድር ድርቀቷ ተወግዶ በአረንጓዴ ለምለም የምታጌጥበት ወቅት ነው፡፡ ለምድር ዝናምን ሰጥቶ፣ በዝናብ አብቅሎ፣ በነፋስ አሳድጎና በፀሐይ አብስሎ ፍጥረታቱን የሚመግብ የእግዚአብሔር ቸርነቱን እያወሳን ለምስጋና የምንተጋበት ወቅት ነው፡፡ በዚህ የዕረፍት ጊዜያችን ለቀጣይ የትምህርት ዘመን እየተዘጋጀን ወደ ቤተ እግዚአብሔር በመሄድ በርትተን፣ ውለታውን እያሰብን ለጸሎት ለቅዳሴ መትጋት አለብን!

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ለዛሬ ያዘጋጀንላችሁ የሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስንና የእናቱ ቅድስት ኢየሉጣን ታሪክ ነው፡፡ በሦስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን በሮም ግዛት ክርስትና ቢስፋፋም በዚያው በጣዖት አምልኮ የተያዙ ብዙዎች ነበሩ፤ ይህም ለዘመኑ ክርስቲያኖች ፈታኝ ነበር፡፡ ይገርማችኋል ልጆች! ማንኛውም ክርስቲያን መሠረታዊ ፍላጎቶቹ እንዲሟሉለት ከፈለገ በጣዖት የሚያመልኩ ሰዎቸ ላቆሟቸው ጣዖቶች መንበርከክ (መስገድ) ግዴታው ነበር፡፡ ሰብአዊ መብቱን ከመገፈፉ ባሻገር ‹‹ተበድያለው›› ብሎ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ መብቱን የማስከበር ፍትሕ የማግኘት ዕድል አልነበረውም፡፡ በዚያ ላይ ደግሞ በየጊዜው ለክርስቲያኖች ፈታኝ የሆኑ አዋጆች ይወጣሉ፤ የክርስትናን ጎዳና ይበልጥ የሚያጠቡ ሕጎችም ዕለት ዕለት ይደነገጉ (ይወሰኑ) ነበር፡፡ ስለዚህም በወቅቱ የነበረ አንድ ክርስቲያን ሃይማኖቱን ከወደደ ይከሰሳል፤ እስከ መሰደድም ይደርሳል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! በዚህ አስጨናቂ ዘመን እግዚአብሔርን የሚያመልኩ በክርስትና ሃይማኖት የጸኑ ሕፃኑ ቅዱስ ቂርቆስ እና ቅድስት ኢየሉጣ የተባሉ ክርስቲያኖች ነበሩ፤ የዚህ ዘመን (የዘመነ ሰማዕታት) መልካም ፍሬዎች ናቸው፡፡ በዚህ በሮም ግዛት እለእስክድሮስ የተባለ ጨካኝ በጣዖት የሚያመልክ ንጉሥ ነበር፤ እናም ክርስቲያኖችን ጣዖት እንዲያመልኩ ያስገድዳቸው ጀመር፤ በዚህም የተነሣ ብዙዎች ጣዖትን ላለማምለክ ሀገር ጥለው ተሰደዱ፡፡ቅድስት ኢየሉጣም ባሏ በሕይወት ባለመኖሩ ከሕፃን ልጇ ቅዱስ ቂርቆስ ጋር ትኖር ነበር፡፡ ልጇ ቅዱስ ቂርቆስም ምንም እንኳን ገና ሦስት ዓመቱ ቢሆንም ነገረ ሃይማኖትንና ፍቅረ ክርስቶስን ታስተምረው ነበር፡፡ እለ ስክድሮስ ለጣዖት እንዲሰግዱ የክሕደት አዋጅን ሲያውጅ ቅድስቲቱ ለሕፃን ልጇ ራርታ ሽሽትን መረጠች፡፡ ሀብት ንብረቷን፣ ወገንና ርስቷንም ትታ ሕፃን ልጇን ተሸክማ ተሰደደች፡፡ መከራው ግን በሄደችበት አልተዋትም፡፡ እለስክንድሮስ ተከትሎ ባለችበት ቦታ አገኛት፡፡ ወታደሮች ልጇን ሳያገኙ እርሷን ብቻ ይዘው ወደ መኮንኑ አቀረቧት መኮንኑ፤ ‹‹ስምሽን ንገሪኝ›› ሲላት ‹‹ስሜ ክርስቲያን ነው›› አለችው፡፡ ‹‹ትክክለኛ ስምሽን ተናገሪ›› ቢላት ‹‹እውነተኛ ስሜ ክርስቲያን ነው፤ የዓለም መጠሪያ ስሜን ከፈለግህ ‹‹ኢየሉጣ ይባላል›› አለችው፡፡ እለእስክድሮስ የተባለ ጨካኝ በጣዖት የሚያመልክ ንጉሥ ‹‹ለጣዖት ልትሰግጂ ይገባል›› ባላት ጊዜ ‹‹እውነትን ይነግረን ዘንድ የሦስት ዓመት ሕፃን ልጄን ፈልገህ አምጣና ተረዳ›› አለችው፡፡ ንጉሡም ወታደሮቹን ፈልገው እንዲያመጡት ላካቸው፤ የሀገሩ ሰዎችም ልጆቻቸውን ስለ ደበቁ የተገኘው ቅዱስ ቂርቆስ ነበር፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱሱ ሕፃን በወታደሮች ተይዞ ሲቀርብ መልኩ ያበራ ነበርና መኮንኑ ‹‹ደስ የተሰኘህ ሕፃን እንዴት ነህ›› አለው፤ ቂርቆስም መልሶ ‹‹ትክክል ነህ! እኔ በጌታዬ ክርስቶስ ዘንድ ደስታ ይጠብቀኛል፡፡ አንተ ግን ወደ ገሃነም ትወርዳለህ›› በማለት ተናገረ፡፡ በሕፃኑ ድፍረት የደነገጠው መኮንኑ በብስጭት ‹‹እሺ ስምህን ንገረኝ›› ብሎ ጠየቀው፤ ያን ጊዜም ‹‹ከንጹሕ ምንጭ የተቀዳ ስሜ ክርስቲያን ነው፡፡ እናቴ የሰየመችኝ ግን ቂርቆስ ብላ ነው›› ሲል መለሰለት፡፡ ከዚያም እየደጋገመ ‹‹እኔ ክርስቲያን ነኝ›› ብሎ በመመሥከሩ መኮንኑ ቅዱስ ሕፃን ቂርቆስና እናቱ ቅድስት ኢየሉጣን እንዲያሠቃዪቸው ወታደሮቹን አዘዘ፡፡

ልጆች! ከዚህ በኋላ በእነርሱ ላይ የተፈጸመባቸው ግፍ እና የደረሰባቸው መከራ እጅግ አስከፊና የሚዘገንን ነው:: መኮንኑ በትልቅ በርሜል ውኃ አስፈልቶ ከዚያም ውስጥ ኬሚካል በውስጡ ጨመረ፤ በዚህን ጊዜ ቅድስት ኢየሉጣ የልጇን ነገር አስባ በውስጧ ፍርሃት አደረ፤ ሆኖም ግን በዚህን ጊዜ ሕፃን ቂርቆስ በእምነቱ ጽኑ ስለነበር በመከራው ብዛት አልፈራም፡፡ ይገርማችኋል እንዲያውም የእናቱን ጭንቀትና ለእርሱ ስትፈራ ሲመለከት ‹‹እናቴ ሆይ ከብረቱ ጋን ትልቅነት የተነሣ አትፍሪ! ድንጋጤም አይደርብሽ! አናንያን፣ አዛርያንና ሚሳኤልን ከእቶን እሳት ያዳነ እኛንም ያድነናል፤ ሶስናን ከኃጢአተኞች እጅ ያዳናት፣ ዳንኤልን ከአንበሳ ጉድጓድ ያወጣ እኛንም ያድነናል›› አላት፤ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ፤ የዚያን ጊዜ እናቱ ተጽናናች፤ በረታችም፤ ፍርሃት ተወገደላት፤ ስለ እምነታቸው መስክረው ከፈላው የብረት ጋን ውስጥ ጨመሯቸው፤ በዚህን ጊዜ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ከሰማይ ወረደና በብረቱ ጋን የፈላውን ውኃ እንደ ውርጭ ውኃ አቀዘቀዘው፤ ኬሚካል ተጨምሮበት ሰውነታቸውን እንዲበጣጥሰው የተዘጋጀውን አቀዝቅዞ ውኃ አደረገው፤ ከመከራም አዳናቸው፡፡ እናቱም ለልጇ ‹‹እኔ የወለድኩህ እናትህ ነኝ፤ አንተ ደግሞ በእምነት ጽናትህ በመንግሥተ ሰማያት አባት ሆንከኝ›› አለችው፤ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ፤

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ብዙ ቃል ኪዳን ገባላቸው፤ ‹‹እኔን መከተል የሚወድ ራሱን ይናቅ፤ መስቀሌንም ተሸክሞ ይከተለኝ›› ያለውን አማናዊ ቃል ሰምተው ለሙሽራው ለክርስቶስ ፍቅር ራሳቸውን አሳልፈው ሰጡ፡፡ (ማቴ.፲፮፥፳፬) ስለዚህ እኛም አምላክን ያከበሩ ቅዱሳንን እናከብራቸዋለን፤ ፈለጋቸውን እንከተላለን፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹እኔ ክርስቶስን እንደ ምመስል እናንተም እኔን ምሰሉ›› በማለት እንደመከረን ቅዱሳን ሰማዕታትን በእምነት በምግባር ልንመስላቸው ይገባል፤ (፩ኛ ቆሮ. ፲፮፥፩) ከቅዱስ ቂርቆስና ከቅድስት ኢየሉጣ ታሪክ ብዙ ነገር እንማራለን! በሥነ ምግባር የታነጽንና እምነታችን የጸና ልጆች ሆነን ማደግ አለብን፡፡ ቅዱስ ቂርቆስ እናቱ የምታስተምረውን የክርስትና ትምህርት በደንብ ያደምጥ ነበር፤ መከራ በገጠማቸው ጊዜ ከእርሱ ቀድመው እንደነበሩት ቅዱሳን ሰማዕታት በእምነት መጽናት እንዳለበት ተረዳ፤ እናቱንም በእምነትና በጸሎት አጸናት፤ አያችሁ ልጆች! የተማረውን ትምህርት ሳይረሳ በሕይወቱ ተገበረው፤ የሃይማኖት ጽናትን ለእናቱ አስተማረ፤ እኛም እንደ ቅዱስ ቂርቆስ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ከእኛ በፊት የነበሩ ክርስቲያኖች እንዴት ይኖሩ እንደነበረ ጠይቀን በመረዳት እንደነርሱ ልንሆን ይገባል፡፡

ውድ የእግዚአብሔር ልጆች! ከቅዱስ ቂርቆስ ምን እንማራለን? ለወላጅ እየታዘዙ ማደግ፣ ከአባቶች የምንማራቸውን በሕይወታችን መተግበር፣ ያወቅነውን ለሌሎች ማሳወቅ፣ ሰዎችን በጸሎት መርዳት፣ ስለ እውነት መመሥከርን፤ እንማራለን !

የቅዱስ ቂርቆስና የቅድስት ኢየሉጣ አምላካ በረከቱን ያድለን አሜን!!! ቸር ይግጠመን ይቆየን!!!

ስብሐት ለእግዚአብሔር
ወለወላዲቱ ድንግል
ወለመስቀሉ ክቡር አሜን!!!