ሕገ ወጥ ልመናን የሚያስፋፉ ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ተጠቆመ፡፡

ጥር 26 ቀን 2006 ዓ.ም.

በቅርቡ በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት በቤተ ክርስቲያን ዕድሳት ስም ፈቃድ ሳይሰጣቸው በየዐደባባዩና በአልባሌ ቦታዎች ልመናን የሚያስፋፉ ሕገ ወጥ ግለሰቦች ላይ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ተጠቆመ፡፡

የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ እንዳስታወቁት በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ላይ ለሚደርሰው ተፈጥሮአዊና ሰው ሠራሽ አደጋ እንዲሁም አዲስ ለሚታነፁ አብያተ ክርስቲያናት ለማሠሪያ የሚሆን ገንዘብ ምእመናንንና በጐ አድራጊዎችን ለመጠየቅ የሚያስችል ፳፬ አንቀጾች ያሉት ደንብና መመሪያ ተዘጋጅቷል፡፡ ደንቡና መመሪያው ለሁለት ዓመት የሚያገለግል ሲሆን ከሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ጥያቄ ሲቀርብ ፈቃድ ይሰጣል፡፡

ይሁንና ይኼን አጋጣሚ በመጠቀም ሕገ ወጥ ልመና የሚፈጽሙ ግለሰቦች ከተሰጠው ፈቃድ ውጪ ጊዜ ያለፈበትን የፈቃድ ደብዳቤ በመያዝ በየዐደባባዩ ሥዕለ አድኅኖ በማስቀመጥና ምንጣፍ በማንጠፍ ይለምናሉ፡፡ ድምፅ ማጉያ በመጠቀም በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም መጻሕፍት፣ ካሴትና ሲዲ ግዙ በማለት ምእመናንን ያውካሉ፡፡ እነዚህን ግለሰቦች ሕግ አስከባሪው አካል እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለሁሉም ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን በቁጥር 435/11686/06 በቀን 08/02/2006 ዓ.ም የተጻፈ ደብዳቤ ተላልፏል፡፡

የዕቅድና ልማት መምሪያ ሓላፊ የሆኑት አቶ እስክንድር ገ/ክርስቶስ በቁጥር 10273/11686/2005 በቀን 24/11/2005 ለፌደራል ፖሊስ ከሚሽንና ለአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን በጻፉት ደብዳቤ ያለ አግባብ በየመንገዱ የሚለምኑ አካላት ሕዝበ ክርስቲያኑን ግራ ከማጋባት በተጨማሪ ለጸጥታ አስከባሪዎች ችግር እየፈጠሩ መሆናቸው ከፖሊስና ከጸጥታ አካላት እየተገለጸ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

የከተማውን ሕዝብ በድምፅ ማጉያ እየረበሹ በቤተ ክርስቲያን ስም የሚነግዱትን ሕገ ወጦች እርምጃ እንዲወሰድባቸው እንጠይቃለን በማለት አቶ እስክንድር ተናግረዋል፡፡

ለቤተ ክርስቲያን ግንባታ ፈቃድ የሚሰጠው ለሁለት ዓመት ሲሆን የሚሰበሰበው ገንዘብ ሕጋዊ በሆነ ደረሰኝ በሞዴል 30 ገቢ ይደረጋል፡፡ የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤትም በተሰጠው ፈቃድ መሠረት የተሰበሰበው ገንዘብ በትክክል አገልግሎት ላይ መዋሉን እየተቆጣጠረ እንዲሠራና የቤተ ክርስቲያኑ ሥራ ሲጠናቀቅ ለዕቅድና ልማት መምሪያው እንደሚያሳውቅ ሕገ ደንቡ እንደሚገልጽ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በጎዳና ላይ ልመና እንዲካሔድ ቤተ ክርስቲያን ፈቃድ አትሰጥም፤ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ሥዕለ ቅዱሳንና ልዩ ልዩ ንዋያተ ቅድሳት በመያዝ በየጐዳናው የሚለምኑ ወገ ኖችን በሕግ ለመጠየቅ ከፌደራልና ከክልል ፖሊስ ጋር እየሠራን እንገኛለን ሲሉ አቶ እስክንድር አመልክተዋል፡፡

በልመና ላይ የተሠማሩት ካህናት ሳይሆኑ ካህን መስለው የሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች መሆናቸውን የጠቀሱት አቶ እስክንድር ወደፊት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ለመሥራት መታቀዱን ገልጠዋል፡፡

 

  • ምንጭ፡- ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ 21ኛ ዓመት ቁጥር 8 2006 ዓ.ም.