ሕይወት ተገለጠ አይተንማል

 የካቲት 3 ቀን 2006 ዓ.ም.

ዲ/ን ታደለ ፈንታው

ስለሕይወት ቃል ከመጀመሪያ የነበረውንና የሰማነውን በዓይኖቻችንም ያየነውን የተመለከትነውም እጆቻችንም የዳሰሱትን እናወራለን፡፡ ሕይወትም ተገለጠ አይተንማል፡፡እንመሰክራለንም፡፡/1ኛ ዮሐ 1፡1/

ቅዱስ ዮሐንስ በቀዳማይ መልእክቱ ለዓለም የሚያስተዋውቀው ሕይወት ዓለም የማያውቀው አስቀድሞ ከእግዚአብሔር አብ ዘንድ የነበረ በኋለኛው ዘመን ሰው ይሆን ዘንድ ሥጋን ተዋሕዶ በምድር ላይ ይመላለስ ዘንድ የወደደ፣ ከአብ ዘንድ የነበረውን፣ ለእኛም የተገለጠውን ሕይወት ነው፡፡ አስቀድሞ በወንጌሉ ይህንን ሕይወት ‹‹ በመጀመሪያ ቃል ነበረ፤ ቃልም በእግዚአብሔር ዘንድ ነበረ ቃልም እግዚአብሔር ነበረ፤ ሁሉ በእርሱ ሆነ ከሆነው አንዳች ስንኳ ያለእርሱ አልሆነም/ዮሐ 1፡1/ በማለት የገለጠው ነው፡፡

ወንጌላዊው ከመጀመሪያ የነበረውን ሲል እያስተማረን ያለው ቀዳማዊ ቃል ዘመን የማይቆጠርለት መሆኑንና በየዘመናቱ የሰራው ታላቅ ሥራ መገለጡን የሚያመለክት ነው፡፡ እርሱ ከባህርይ አባቱ ከእግዚአብሔር አብ ጋር ህልው ሆኖ የሚኖር ነው፡፡ አይቀዳደሙም፣ ወደኋላ አይሆኑም፡፡ አብን መስሎ አብን አክሎ የተወለደ ነው፡፡ በኅላዌ ፣በአገዛዝ፣ በመለኮት፣ በአገዛዝ፣ በመለኮት፣ ከባሕርይ አባቱ ጋር የተካከለ ነው፡፡

እርሱ ዘላለማዊ ቃል ነው የሚለው በመጀመሪያ ቃል ነበረ በማለት በወንጌሉአስቀድሞ ገልጦታል፡፡ነገር ገን ዓይኖቻችን የተመለከቱት የሚለው ቃል የሚያመለክተው የጌታን መገለጥ ነው፡፡ እጆቻችን የዳሰሱትንም የሚለው ቃል ተመሳሳይ እሳቤን ይይዛል፡፡ አካላዊ ቃል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተገልጦ ስጋን ተዋሕዶ ባይታይ ኑሮ የሰው ልጆች ባልተመለከቱት አብረውት ባልበሉ ባልጠጡም ነበር፡፡ ስለጌታ የሚኖረን እውቀት፣ ስለሃይማኖታችን የሚኖረንም መረዳት በማየት ላይ የሚቆም አይደለም፡፡ የሚመሰከርም ነው እንጂ፡፡ ምስክርነት የሚለው ቃል ሰማእትነትን የሚያመለክት ነው፡፡ አይተንማል ስለዚህ በስምህ ልንሰደድ ፣ልንገረፍ፣ ወደ ወኅኒ ልንጋዝ፣ ልንሰደድ አስፈላጊም ሆኖ ሲገኝ ልንሞት ተዘጋጅተናል ማለት ነው፡፡ ሰማእታት በእውነት ምስክርነታቸው የተቀበሉት መከራ ብዙ ነው፡፡ ምስክርነታቸውም ለሰሙትና ላዩት ቃል ነው፡፡ ምስክርነት በቃል ፣ በኑሮ/በሕይወት/ በሥራ፣ የሚገለጥ ነው፡፡ የክርስቲያኖች ምስክርነት የሚሰሙአቸውን ወጎኖች ያስቆጣቸዋል፤ ይህንን ሁኔታ ተከትሎ የእውነት ምስክር የሚሆን ክርስቲያን ፍጻሜ ሰማእትነት ነው፡፤ ሰዎች ስለእረሱ ይመሰክሩ ዘንድ እግዚአብሄር ፈቃደ ነው፡፡ ስለዚህም ነው መድኃኒታችን ‹‹ በሰው ፊት የሚመሰክርልኝን በሰማይ አባቴና በመላእክቱ ፊት እመሰክርለታለሁ በሰው ሁሉ ፊት የሚክደኝን በሰማይ አባቴና በመላእክቱ ፊት እክደዋለሁ በማለት የተናገረው፡፡››

ከጌታ መገለጥ አስቀድሞ ሰው ልጅ ይኖር የነበረው ከእግዚአብሔር ቁጣ በታች ሆኖ በመርገም ነበር፡፡ እግዚአብሔርን ተግተው ይፈልጉ ያገለግሉ የነበሩ ነቢያት ይህንን ሁኔታ ‹‹ጽድቃችን እንደመርገም ጨርቅ ነው/ኢሳ 64፡6/ በማለት የተናገሩለት ነው፡፡ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር አሕዛብን እርሱን ተመራምረው የሚረዱበትን መንገድ ሳያመለክት እንዲሁ አልተዋቸውም ነበር፡፡ ነገር ግን በዚህየፈጣሪን ሀልወቆት በሚገልተው መንገድ ተጉዘው ወደ እውነተኛው አምላክ መድረስ ሳይቻላቸው ቀርቷል፡፡ እግዚአብሄር ሀልዎቱ የተገለጠበትን ድንቅ ሥራውን የሚመሰክርበትን ዓለም በኃጢአት አቆሸሹት፡፡ ራሳቸውንም በደለኛ አደረጉ፡፡ የእግዚአብሔርም ቁጣ የሚገባቸው ሆኑ፡፡ የአሕዛብም ጣዖት ማምለክ እግዚአብሄርን አስቆጣው፡፡ ምክንያቱም ከፈጣቲ ይልቅ ፍጡርን ፍጡርንም የሚያስተውን አጋንንትን ለማምለክ ፈቅደዋልና፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ጥቁር የኃጢአት መልክ እንደሚከተለው ይገልጠዋል፡- ‹‹እግዚአብሔር ስለገለጠላቸው ስለ እግዚአብሄር ሊታወቅ የሚቻለው በእነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና፡፡ የማይታየው ባህርይ እርሱም የዘላለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ጀምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ሆኖ ይታያልና፤ ስለዚህም እግዚአብሔርነቱን እያወቁ እንደ እግዚአብሔርነቱ ባላከበሩት መጠን ስላላመሰገኑትም የሚያመካኙት አጡ፤ ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱዎች ሆኑ፤ የማያሥተውለውም ልባቸው ጨለመ፡፡ ጥበበቦች ነን ሲሉ ደንቆሮዎች ሆኑ፤የማይጠፋውንም የእግዚአብሔር ክብር በሚጠፋ ሰውና በወፎች አራት እግር ባላቸው በሚንቀሳቀሱትም መልክ ለወጡ፡፡/ሮሜ 1፡18-27/

አይሁድ የነበሩበት ሁኔታ ከአሕዛብ እምብዛም የተሻለ አልነበረም፡፡ አይሁድ ከአሕዛብ የሚለዩበት ምቹ ሁኔታዎች ነበሩአቸው፡፡ በብሉይ ዘምን በተለያየ ጌዜ የተደረገው መገለጥ፣ ሕጉ፣ ነቢያት ቀዱሳት መጻሕፍት ነበሩአቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ ነገሮች በደላቸውን ከማብዛት ውጪ አንዳች የጠቀሙአቸው ነገር አልነበረም፡፡ አሕዛብ ጣዖት በማምለክ ወጥመድ ሲያዙ ሕጉ ግን ሊመጣ ስላው ክርስቶስ ይናገር እንደነበረ አላስተዋሉም፡፡ አሕዛብ ጣዖት በማምለክ ወጥመድ ሲያዙ አይሁድ የሕጉን ነጠላ ትርጓሜ ፊደልን በማምለክ ተያዙ፡፡ ሕጉ ግን ይመጣ ስላለው ክርስቶስ ይናገር እንደነበረ አላስተዋሉም እንደመሰላቸው ተረጎሙት እንጂ፡፡ በብሉይ ኪዳን የነበሩ ቅዱሳን ሕጉን ባለና በሌለ ጉልበታቸው በመፈጸም ወደ ቅድስናና ፍጹምነት ለመድረስ ይጣጣሩ ነበር፡፡ ይህ ሰውኛ ጥረት በሕግም እንዲገኝ ይፈለግ የነበረው ጽድቅ ሰዎች ስለራሳቸው የነበረቸው አመለካከት እንዲዛባ፣ ራሳቸውን ከፍ አድርገው እንዲመለከቱ‹‹ ጌታ ሆይ እኔን እንደቀራጩ ስላላደረግኸኝ አመሰግንሃለሁ›› እንዲሉ አድርጓቸዋል፡፡

በአንጻሩ በሕጉ ጥላ ሥር የነበሩ ጉድለታቸውን የተገነዘቡ ወገኖች መራራ የሆነ የኃዘን ስሜት ተሰምቶአቸው ‹‹ እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ፣ ለዚህ ሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? በማለት ጩኸታቸውን አሰምተዋል፡፡ /ሮሜ 7፡24/ አሁን እየጠናገርነው ላለው ነገር ማሳያ ምሁረ ኦረት ከነበረው ለአባቶቹ ወግና ሥርዓት ይጠነቀቅ ከነበረው የቀድሞው ሳውል የኋለኛው ብርሃና ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ የበለጠ ምስክር ሊሆን የሚቻለው ወገን የለም፡፡ ኢክርስቲያናዊ ከሆነው ወግና ልማድ ወጥቶ ክርስቲያናዊ በሆነው መስመር ለመጓዝ ቅዱስ ጳውሎስ የራሱን የሕይወት ተሞክሮ ይነግረናል፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ የተደረገ ለውጥ ሥሩን ዘልቆ መሰረቱን ነክቶ የተደረገ ክርስቲያናዊ ለውጥ ነበር፡፡ ካለፈው ወጉና ልማዱ ፈጽሞ የሌው ነው አዲስ የሆነ የሕይወት ፍልስፍና የኑሮ መስመርም እንዲከተል ያደረገው ነው፡፡ ሕይወትና ሞት በማነጻጸር ሊገለጥ የሚችል ለውጥ ነው፡፡ ወደ ክርስቶስ ሞት ይገባ ዘንድ ሞቱንም በሚመስል ሞት ይተባበር ዘንድ እንዳደረገ ክርስቲያኖችም አስቀድመው ከሚገዙለት ዓለም ወጥተው ለዓለም ሊሞቱ ይገባቸዋል፡፡ ሞቱን በሚመስል ሞት ይተባበሩ ዘንድ ይህ ነገር አስፈላጊ ነው፡፡ ከክርስቶስ ገር መሞትም መቀበርም መነሳትም የሚቻለው በዚህ መንገድ ነው፡፡/ሮሜ 6፡2-8፣ ገላ 2፡20፣ቆላ 3፡3/ ከክርስቶስ ጋር የሚነሳው አዲሱ ሰው የሚወለደው በዚህ መንገድ ነው፡፡ እርሱም ክርስቲያን የሚለውን ስም የተሸከመና ከሥምም በላይ የሆነውን ስም ገንዘብ የሚያደርግ ነው ፡፡ የጌታ መገለጥ ዓላማው ይህ ሁኔታ ይፈጸም ዘንደ ነው፡፡

በክርስቶስ መገለጥ አዲስ ስምን ገንዘብ ያደረገው መንፈሳዊው ሰው የራሱ የሆነ ግላዊና ዓለማዊ ጠባያትን አስወግዶ ባህርይውን ከክርስቶስ ባህርይ ጋር ማስማማት የሚያስችለውን የመንፈስ ማሰሪያ ገንዘብ ለማድረግ የሚታገል መላ ዘመኑን በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ የሚመላለስ የእግዚአብሔርንም እውነጠኛ ፍቅሩ በልቡናውቋጥሮ የሚመላለስ ነው፡፡

 

ክርስቲያናዊ ሕይወት ከክርስቶስ ጋር መቀበር ነውና ከዓለምና ከኃጢአት መለየትን ይጠይቃል፡፡/ኤፌ 2፡13/ ይህ ከዓለምና ከኃጢአት መለየት በክርስቶስ የመስቀል ላይ የማዳን ሥራ የተገለጠ ነው፡፡ ‹‹አይዞአችሁ እኔ ዓለሙን አሸንፌዋለሁ››በሚለው እውነተኛ የአዋጅ ቃልም የታጀበ ነው፡፡ አማናዊ የሆነ የአዋጅ ቃልም ነው፡፡ በነፍሳችን መልሕቅ ልዩ ሥፍራ ያለው ነው፡፡ ክርስቲያኖች ክርስቶስን ይለብሱታል፡፡ በመድረክ ላይ የሚጫወት ተዋናይ መድረኩን እንዲያደምቅለት በመድረክ ላይ ሳለ የሚለብሰው ከመድረክ ሲለይ የሚያውቀው የትወና ልብስ ዓይነት አይደለም፡፡ በመሰዊያው ፊት ለፊት ክርስቶስን ወክሎ የክርስቶስ ወኪል እንደሆነው ካህን ነው እንጂ፡፡ ካህኑ ክርስቶስን ወክሎ እንደሚናገር ክርስቶስን የለበሰ ክርስቲያንም በእርሱ የክርስቶስ ሕይወት ይታያል፡፡ በመውጣቱ፣ በመግባቱ፣ በኑሮው፣ በድካሙ የሚታየው መልክ ሕያው የሆነ የክርስቶስ መልክ እንጂ አስቀያሚ የሀኖነ ዓለማዊ ሰው መልክ አይደለም፡፡

በዚህ ሁኔታ ክርስቲያናዊ ሕይወትን ስንመለከተው ተራ የሆነው የዕለት ዕለት የዚህ ዓለም ኑረሮአችን አላፊ ጠፊ የማይጠቀም ሆኖ እንመለከተዋለን፡፡ በዚህ ዓለም የምናደርገው ስጋዊ ሩጫም አንድ ቀን በሞት ፍጻሜውን እንደሚያገኝ እንረዳለን፡፡ ቅዱሳን የዚህ ዓለም ኑሮ ቀናት እየገፉ በሄዱ ቁጥር የማይጠቅም እንደነበረ ተገንዝበዋል፡፡ ይህንም ሁኔታ ለማሰወገድ ጠንካራ ጦርነት ላይ ነበሩ ከዓይን አምሮትን ከሥጋ ፍላጎት ጋር ተዋግተዋል፡፡ ታግለውም አሸንፈዋል፡፡ ይህን ዓለም ተዋግተው ወደ ውጭ በገፉት መጠን በልብ ውስጥ ወዳለው ወደ ተሰወረው የልብ ሰው ይመለከቱ ዘንድ እግዚአብሔር ረድቶአቸዋል፡፡ የቅዱሳን ሕይወትና ሥነ ምግባር የተቀረጸው በልባቸው ላይ በነገሰው በክርስቶስ አማካኝነት ነው፡፡

ከቅዱሳን አንዱ እንዲህ ይላል፡- እግዚአብሄርን በሕይዎታችን ሲሰራ እንመልከተው፡፡ ለሥራው መልስ በመስጠት ምስክር እንሁን፡፡ ክርስቲያናዊ ሃይማኖትንና ምግባርን ይዘን እንገኝ፡፡ የክርስቶስን መልክ ለብሰን ስለእርሱም ዕለት ዕለት የምንሞት ብንሆን በነፍሳችን ተጠቃሚዎች ነን፡፡ በማየትና በማመን መካከል የገዘፈ ልዩነት አለ፡፡ በተግባር የምንኖረው ሕይወት ሰዎች ካልኖሩበት ትርጉሙን ላይረዱት ይችላሉ፡፡ ብዙ ምስጢራትን የምንገነዘባቸው በእምነት ሕይወት በማደግ እንጂበቃላት የመይገለጡ፣ ከቃላትም የመግለጥ አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮች አሉ፡፡ ቃላት የማያውቁትን ነገር ማስረዳት አይቻላቸውምና፡፡ ወደ እርሱ መቅረብ ማንም ወገን የማይቻለው እውነተኛ ብርሃን ዘመዶቹ ሊያደርገን በወደደ ጊዜ በሥጋ ተገለጠ፡፡ ይህም መልካም በመሆኑ ምክንያት እንጂ በጽድቅ ሥራችን የተነሣ አይደለም፡፡ ይህን ሁኔታ አውቀን ከፊታችን ያለውን ሩጫ በእምነት መሮጥ ይቻለን ዘንድ አምላካችን ይርዳን፡፡