Sebe

ሕንፃ ሰብእ ወይስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ይቀድማል?

ታኅሣሥ 16/2004 ዓ.ም

ትርጉም፡- በዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

 

Sebe

“የጌታን ቤት በወርቅ ወይም በብር ባለማስጌጣቸው ከጌታ ዘንድ በሰዎች ላይ የሚመጣ አንዳች ቅጣት የለም”


ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ በማቴ.14፥23 ያለውን ንባብ በተረጎመበት ድርሳኑ ከሰው የሚቀርብላቸው ከንቱ ውዳሴን ሽተው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን ሲያስጌጡ የሚታዩ ነገር ግን እንደ አልዓዛር ከደጃቸው የወደቀውን ተርቦና ታርዞ አልባሽና አጉራሽ ሽቶ ያለውን ደሃ ገላምጠው የሚያልፉትን ሰዎች ይገሥፃል፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ዘመን አንዳንድ ባለጠጎች ደሃ ወገናቸውን ዘንግተው ከእግዚአብሔር ዋጋ የሚያገኙ መስሎአቸው ቤተ ክርስቲያንን የወርቅና የብር ማከማቻና መመስገኛቸው አድርገዋት ነበር፡፡ ይህ ጥፋት በአሁኑ ጊዜ መልኩን ቀይሮ በሕንፃ ኮሚቴ ሰበብ ምዕመኑን ዘርፎ የራሳን ሀብት ማከማቸት በአደባባይ የሚሰማና የሚታይ ምሥጢር  እየሆነ ነው፡፡ እነዚህን በዮሐንስ አፈወርቅ ዘመን ከተነሡት ጋር ስናነጻጽራቸው እነዚያ ከእነዚህ በጣም ተሸለው እናገኛቸዋል፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እነዚያን እንዴት ብሎ እንደሚወቅሳቸው እንመልከትና በዚህ ዘመን የሚፈጸመው ዐይን ያወጣ ዘረፋ ምን ያህል አስከፊ ቅጣትን ሊያመጣ እንደሚችል እናስተውለው፡፡

… ሰው ወላጆቻቸውን በሞት ያጡ ሕፃናትንንና ረዳት ያጡ ባልቴቶችን ከልብስ አራቁቶ በወርቅ የተለበጠ ጽዋ ለቤተ ክርስቲያን በማበርከቱ ብቻ የሚድን እንዳይመስለው ይጠንቀቅ፡፡ የጌታን ማዕድ ማክበር ከፈለግህ ስለእርሷ የተሠዋላትን ነፍስህን ከወርቅ ይልቅ ንጹሕ በማድረግ በእርሱ ፊት መባዕ አድርገህ አቅርባት፡፡ ነፍስህ በኃጢአት ረክሳና ጎስቁላ አንተ ለእርሱ የወርቅ ጽዋ በማግባትህ አንዳች የምታገኘው በረከት ያለ አይምሰልህ፡፡ ስለዚህም በወርቅ የተሠሩ ንዋያተ ቅድሳትን መስጠት የእኛ ተቀዳሚ ተግባር አይሁን፡፡ ነገር ግን የምናደርገውን ሁሉ በቅንነት እናድርግ እንዲህ ከሆነ ከእግዚአብሔር የምናገኘው ዋጋ ታላቅ ይሆንልናል፡፡ ሥራችንን በቅንነት መሥራታችን ከወርቅ ይልቅ እጅግ የከበረ ዋጋ አለው፤ እንዲህ በማድረጋችንም ከቅጣት እናመልጣለን፡፡

 

ቤተ ክርስቲያን የወርቅና የብር ማምረቻ /ፋብሪካ/ ወይም ማከማቻ አይደለችም፡፡ ነገር ግን የመላእክት ጉባኤ እንጂ፡፡ ስለዚህም የነፍሳችንን ቅድስና እንያዝ አምላካችንም ከእኛ የሚፈልገው ይኼንኑ ነው፡፡ ስጦታችን ከነፍሳችን ይልቅ አይከብርም፡፡

 

 

ጌታችን ከሐዋርያት ጋር በማዕድ በተቀመጠ ጊዜ ሥጋውን በብር ዳሕል ደሙንም በወርቅ ጽዋ አድርጎ አልነበረም ያቀረበላቸው፡፡ ነገር ግን በማዕዱ የነበሩት ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ እጅግ የከበሩና ማዕዱም ታላቅ ነበር፡፡ ምክንያቱም ማዕዱ ሲቀርብ ሐዋርያት በመንፈስ ነበሩና፡፡ ለጌታችን ቅዱስ ሥጋና ደም ተገቢውን ክብር መስጠት ትሻለህን? አስቀድመህ ደሃ ወገንህን አስበው፥ መግበው፥ አልብሰው፥ የሚገባውን ሁሉ አድርግለት፡፡ እንዲህ ስል ቅዱስ ሥጋውን አታክብረው ማለቴ አለመሆኑን ልትረዳኝ ይገባሃል፡፡ አንተ በዚህ ማዕድ ቅዱስ ሥጋውን በሐር ጨርቅ በመክደንህ ያከበርከው ይመስልሃል፡፡ ነገር ግን ይህን አካል /ቅዱስ ሥጋውን/ በሌላ መንገድ አራቁተኸዋል፤ ለብርድም አጋልጠኸዋል፡፡ጌታችን ኅብስቱን አንሥቶ “ይህ ሥጋዬ ነው” ሲለን “ስራብ አላበላችሁኝም ስጠማ አላጠጣችሁኝም” ያለው አካሉን አይደለምን? ስለዚህም ጌታችን “እውነት እላችኋለሁ ከሁሉ ከሚያንሱት ከእነዚህ ለአንዱ ስላላደረጋችሁ ለእኔም አላደረጋችሁትም” በማለትም ጨምሮ አስተማረን፡፡

ድሆች ወገኖቻችን ለመኖር የሚያስችላቸውን መሠረታዊ የሆኑ ፍላጎቶቻቸውን ሁሉ ልናደርግላቸው ይገባናል፡፡ ይህን ማድረግ ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባን ግዴታችን ነው፡፡ በዚህ መልክ ክርስቶስ ኢየሱስ ከእኛ እንደሚሻው በመሆን ሕይወታችንን ቅዱስ በማድረግ ወደ ማዕዱ እንቅረብ፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እግሩን ሊያጥበው በቀረበ ጊዜ ቅዱስ ጴጥሮስ “እግሬን በአንተ ልታጠብ አይገባኝም” በማለት ተከላክሎት ነበር፡፡ ነገር ግን ቅዱስ ጴጥሮስ የእርሱ መከላከል ከአክብሮት ይልቅ ታላቅ በረከትን ሊያሳጣው የሚችል መከላከል እንደሆነ አልተረዳም ነበር፡፡ ቢሆንም ከጌታ ዘንድ “ካላጠብሁህ ከእኔ ጋር ዕድል የለህም” የሚለውን ቃል ሲሰማ እርሱ ያሰበው ነገር ተገቢ እንዳልነበረ ተረዳ፡፡ እንዲሁ እኛም እንደታዘዝነው ለድሆች ወገኖቻችን ቸርነትን እናድርግ፤ እርሱን ማክበራችንም የሚረጋገጠው በፍቅረ ቢጽ እንጂ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያንን በማስጌጥ አይደለም፡፡ እግዚአብሔር በወርቅ ሳይሆን ከወርቅ ይልቅ ንጽሕት በሆነች ነፍስ ደስ ይሰኛልና፡፡ እንዲህ ስል ግን ስጦታዎችን ወደ እግዚአብሔር ቤት እንዳታምጡ ማለቴ እንዳልሆነ ልትረዱኝ እፈልጋለሁ፡፡ ነገር ግን ከስጦታዎቻችሁ በፊት ትእዛዙን መፈጸም ይቀድማል፡፡

በእርግጥ በተሰበረ ልብ ሆናችሁ ስጦታዎችን ወደ እግዚአብሔር ቤት ብታመጡ እርሱ አይባርካችሁም እያልኩ አይደለም ፡፡ ነገር ግን ድሆችን ከረዳችሁ በኋላ ስጦታን ለእርሱ ብታቀርቡ ታላቅ ዋጋን ታገኛለችሁ፡፡  በዚያኛው ስጦታ አቅራቢው ብቻ ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ በዚህኛው ግን ቸርነትን የተደረገለት ወገንም ተጠቃሚ ይሆናል፡፡ አንድም የወርቅና የብር ዕቃን ስጦታዎች ማድረጋችን ከሰዎች ምስጋናን ለማግኘት ብለን የፈጸምነው ሊሆን ይችላል፡፡ በእርግጥም ደሃ ወገንህ ተርቦና ተጠምቶ እንዲሁም ታርዞ አንተ እንዲህ ማድረግህ ከዚህ ውጪ ሌላ ምክንያት የለውም፡፡ ደሃው ወገንህ በርሃብ እየማቀቀ አንተ የጌታን የማዕድ ጠረጴዛ በወርቅና በብር እቃዎች ብትሞላው ምንድን ነው ጥቅምህ? ነገር ግን አስቀድመህ ደሃውን አብላው አጠጣው እንዲሁም አልብሰው፡፡ በመቀጠል የጌታን ማዕድ (መንበሩን) በፈለግኸው መልክ በወርቅም ይሁን በብር አስጊጠው፡፡

ለድሃ ወገንህ ለጥሙ ጠብታ ታክል ቀዝቃዛ ውኃ እንኳ ሳትሰጠው የወርቅ ጽዋን ስጦታ አድርገህ ለእግዚአብሔር ታመጣለታለህን? እንዲህ ማድረግህ ጌታን ያስደስተዋልን? አካሉን የሚሸፍንበትን እራፊ ጨርቅ ለደሃ ወገንህ ነፍገኸው፣ መንበሩን በወርቅ ግምጃ ጨርቅ በማስጌጥህ ከጌታ ዘንድ የረባ ዋጋ አገኛለሁ ብለህ ታስባለህን? እንዲህ በማድረግ ጌታ አምላክህን በስጦታህ ልትሸነግለው ትፈልጋለህን? በዚህስ ድርጊትህ በአንተ ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ አይነድምን? ወገንህ አካሉን የሚሸፍንበት እራፊ ጨርቅ አጥቶ በብርድ እየተጠበሰና በመንገድ ዳር ወድቆ የወገን ያለህ እያለ አንተ የቤተ ክርስቲያን ዐምዶች በወርቅ በመለበጥህ ጌታ በአንተ ደስ የሚለው ይመስልሃልን? ይህል ከባድ ኃጢአት አይደለምን?… ኦ እግዚኦ አድኅነነ እም ዘከመ ዝ ምግባር አኩይ!!