ሕንጸታ ቤታ

ሰኔ ፲፰ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

በሀገረ ቂሣርያ፣ ኬልቄዶንያ አውራጃ የመጀመሪያዋ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን የታነጸችበት ዕለት ሰኔ ፳ ‹‹ሕንጸታ ቤታ›› የተከበረ ነው፤ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያለ እንጨት፣ ያለ ጭቃና ያለ ውኀ በሦስት ድንጋዮች ቤተ ክርስቲያኗን ያነጸበት ዕለት ነውና፡፡

ሐዋርያው ጳውሎስና በርናባስ አሕዛብን ሰብከውና ብዙዎችን አሳምነው ከመለሱ በኋላ ሕዝቡ ቅዱስ ቊርባንን የሚቀበሉበት ቤተ ክርስቲያን ስላልነበረ በጸሎትና በሱባኤ ጌታችን ኢየሱስን እንዲማጸኑ ሕዝቡን አዘዙ፤ ጌታችንም በሱባኤው ፍጻሜ ላይ ለሐዋርያቱ ተገልጾ በመላው ሀገር እስከ ፊልጵስዩስ ድረስ በደመና ከሰበሰባቸው በኋላ ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ ‹‹ይህች ዕለት በእናቴ በማርያም ስም በአራቱ ማእዘነ ዓለም አብያተ ክርስቲያናት እንዲታነፁ የፈቀድኩባት ናት፡፡›› ከዚያም ጌታችን የቤተ ክርስቲያኗን ቦታና መሠረት ወስኖ ንዋየ ቅዱሳቷ፣ አልባሳቷንና መሠዊያዋን ካዘጋጀ በኋላ በዚያ ሥፍራ የነበሩትን ሦስት ድንጋዮች የተራራቁትን አቀራርቦ፣ ጥቃቅኑን ታላላቅ አድርጎ ቁመቱን በ፳፬፣ ወርዱን በ፲፪ ክንድ ለክቶ ለቅዱሳን ሐዋርያት ሰጣቸው፡፡

ከዚህም በኋላ እጁን በጴጥሮስ ራስ ላይ ጭኖ በአራቱ ማእዘነ ዓለም ውስጥ አርሳይሮስ (ሊቀ ጳጳሳት) ብሎ ሾመው፤ በዚያን ጊዜም ‹‹ለሐዋርያት አለቃ ጴጥሮስ ከጽንፍ እስከ ጽንፍ የጳጳሳት አለቃ ይሆን ዘንድ ይገባዋል! ይገባዋል! ይባዋል! እያሉ መላእክትና ምድራውያን ሦስት ጊዜ ተናገሩ፡፡ ኅብስት ሰማያዊ፣ ጽዋዕ ሰማያዊ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ወረደ፤ ጌታችንም፤ እመቤታችንን ታቦት፣ ሐዋርያትን ልዑካን አድርጎ፣ እርሱ ሠራዒ ካህን ሆኖ ቀድሶ ካቈረባቸው በኋላም የቅዳሴን ሥርዓት እንዲያከናውኑና ለሕዝቡ ቅዱስ ቊርባንን እንዲያቀብሏቸው አዘዛቸው፤ በመቀጠልም ለሐዋርያቱ እንዲህ አላቸው፤ ‹‹በዚህች ቀን የእጃቸውን ሥራ እንዳይሠሩ ሕዝቡን ሁሉ እዘዙአቸው፤›› ይህም የሆነው ሰኔ ፳፩ ቀን ነው፤ ጌታችንም ይህን ተናግሮ ወደ ሰማይ በታላቅ ክብር ዐረገ፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያትም በመላው ዓለም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም ቤተ ክርስቲያንን በእጃቸውም አነጹ፤ የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ቁመትም በነገሥታት ዘመን የነበሩ የ፳፬ቱ ነቢያትና የ፳፬ቱ ካህናተ ሰማይ አምሳል ሲሆን ወርዱ ደግሞ የ፲፪ቱ ሐዋርያት ምሳሌ ነው፡፡ ሦስቱ ድንጋዮች የሥላሴ አምሳል ሲሆኑ፣ ከታች አቀማመጣቸው ሦስት፣ ከላይ ሕንጻቸው አንድ መሆኑ የሥላሴን ሦስትነትና አንድነት ያመለክታል፡፡ የሠሩትም ሦስት ክፍል አድርገው ሲሆን ይህም የመጀመሪያው የታቦተ አዳም፣ ሁለተኛው የታቦተ ሙሴ፣ ሦስተኛው የታቦተ ኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነው፡፡ ዳግመኛም የሦስቱ ዓለማት ማለትም የመጀመሪያው የጽርሐ አርያም፣ ሁለተኛው የኢዮር፣ ሦስተኛው የጠፈር ምሳሌ ነው፡፡ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ የተሠራውም ጌታችን በዐረገ በ፲፱ኛው፣ እመቤታችን በዐረገች በ፬ኛው ዓመት ሰኔ ፳ ቀን ነው፡፡

ሊቀ ጳጳስ ባስልዮስም በዘመኑ በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ስም በታነጸው ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥዕል ለማሳል በመሻቱ ሠሌዳ ፈለገ፤ ከአንድ ባለጠጋ ዘንድ እንዳለም ሰምቶ እንዲሰጠው ቢያስልከብትም ባለጠጋው ግን ለልጆቹ እንደሆነና ከዚያም አልፎ በመድፈር በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቤተ ክርስቲያን ላይ የስድብ ቃል ተናገረ፤ በቅጽበትም ወድቆ ሞተ፤ በዚህን ጊዜ ልጆቹ በመፍራታቸው ሠሌዳውን ከብዙ ወርቅና ዕንቊ ጋር ወደ ቅዱስ ባስልዮስ ወሰዱለት፤ እርሱም ሠሌዳውን ወደ ሠዓሊው ወስዶ እንዲስልበት ሰጠው፤ ሆኖም ግን እመቤታችን ድንግል ማርያም በራእይ ተገልጻ ሥዕሏን በሠሌዳው እንዳይሥል ከለከለችው፤ ከዐመጸኛ እጅ የተገኘ ነበርና፡፡ የአንዱ በቀኝ የአንዱ በግራ የተሣለ የእመቤታችን ሥዕል ቀይ ሠሌዳ ያለበትንም ሥፍራ ነገረቸው፡፡

ቅዱስ ባስልዮስም እመቤታችን ወደ አመለከተችው ቦታ በመሄድ ሠሌዳውን አግኝቶ ወደ ቤተ ክርስቲያኗ አምጥቶ ሁለት ምሰሶዎች ከቤተ መቅደሱ ፊት ለፊት ካቆመ በኋላ ሥዕሏን በዚያ አስቀመጠ፡፡ እግዚአብሔር አምላክም በምሰሶዎቹ በታች የውኃ ምንጭ አፈለቀ፤ ድውያንም በእርሷ ይፈወሱ ነበር፡፡ ከእመቤታችንም ሥዕል በሽተኞች የሚፈውስ የዘይት ቅባት መፍሰስም ጀመረ፡፡

ነገር ግን አንዲት ሴት በፈለቀው ምንጭ ውኃ ስትታጠብ መላ ሰውነቷ በለምጽ ተሸፈነ፤ በዚህን ጊዜም ቅዱስ ባስልዮስ አስጠርቶ ምን እንደሆነች ጠየቃት፤ እርሷም የእኅቷን ባል እንደወደደችና እኅቷን በመርዝ ገድላ እንዳገባቸው ነገረቸው፤ ቅዱስ ባስልዮስም ታላላቅ ሦስት ኃጢአት በመሥራቷ ምንአልባት እግዚአብሔር ይቅር ይላት እንደሆነ ንስሓ እንድትገባ አዘዛት፤ ነገር ግን በዚያች ሰዓት ምድር ተሰንጥቃ ዋጠቻት፤ እርሷ ቤተ ክርስቲያንን ተዳፍራለችና፡፡
እኛም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ቤተ ክርስቲያንን በማክበርና ሥርዓቱን በመጠበቅ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ክብረ በዓል እናከብር ዘንድ ይገባል፡፡ ከበዓሉ በረከት ያሳትፈን፤ አሜን።

ምንጭ፤ መጽሐፈ ስንክሳር ዘወርኃ ሰኔ ፳ እና ፳፩ ቀን ገጽ ፬፻፴፫፣ ፬፻፵-፬፻፵፫፣መጽሐፈ ታሪክ ወግስ፣ መምህር አፈወርቅ ተክሌ፤ ፳፻፭ ዓ.ም፤ ገጽ ፫፻፵፱-፫፻፶፩