“ልጄ ሆይ ከእንግዲህ አባቴ ነህ!”

ዲያቆን ሰሎሞን እንየው

ሐምሌ ፲፰፤፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

ሕፃኑ ቂርቆስ ገና የሦስት ዓመት ብላቴና ሳለ እናቱ ኢየሉጣ ከሮሜ አገር የኪልቂያ አውራጃ ከሆነች ጠርሴስ ወደ ምትባል አገር ይዛው ሸሸች። በዚያም የሸሸችውን መኮንን እለእስክንድሮስን አገኘችው። መኮንኑም ኢየሉጣን አጥብቆ መረመራት። “ስምሽ ማን ነው? አገርሽ ከወዴት ነው?” አላት። እርሷም “ስሜ ክርስቲያን ነው” በማለት መለሰችለት።

የቤተ ክርስቲያን ልጆች አስተዋላችሁን? ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ “ዳግመኛ የተወለዳችሁት ከሚጠፋ ዘር አይደለም፥ በሕያውና ለዘለዓለም በሚኖር በእግዚአብሔር ቃል ከማይጠፋ ዘር ነው እንጂ” እንዳለ ከማይጠፋ ዘር ተወልደን በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን እኛ ዛሬም ስማችን ከግብራችን ጋር ሊስማማ ይገባዋል። መኮንኑም ተበሳጭቶ “ጽኑ ሥቃይ በላይሽ ሳይመጣ ተነሥተሽ መሥዋዕትን ለአማልክት አቅርቢ” አላት። በልጇ ሙሉ እምነት ያላት ኢየሉጣም “እውነቱን መረዳት ከፈለግህ የሦስት ዓመት ሕፃን ልጅ አለኝ፤ እርሱን ጠይቅ” አለችው። መኮንኑም ሕፃኑ ቂርቆስን አስመጣው።

መኮንኑም ቅዱስ ቂርቆስ መልኩ የሚያምርና ደም ግባት ያለው ለሕፃን እንደሆነ ባየ ጊዜ “ደስ የምትል ደስተኛ ሕፃን ሰላምታ ይገባሃል” አለው። ሕፃኑ ቂርቆስም “እኔን ደስተኛ ማለትህ እውነት ተናገርክ፤ ለአንተ ግን ደስታ የለህም” አለው። “ሰላም ለገጽከ ዘይጸድል ወይበርህ ምስብዒተ እደ እምጸዳለ ፀሐይ ወወርኅ ሕፃን ቂርቆስ ዘለዓለም ፍሡሕ፤ለዓለም ደስተኛ የሆንክ ሕፃን ቂርቆስ ሆይ ከጨረቃና ከፀሐይ ፀዳል ይልቅ ሰባት እጅ ፈጽሞ ለሚበራው ፊትህ ሰላምታ ይገባል” እንዲል፤ (መልክአ ቂርቆስ) ይህን ሕፃን ደስ ያሰኘ ምንድን ነው? እንደኛ ሀብት ንብረት አግኝቶ ይሆንን? ቅዱስ ጳውሎስ በፊልጵስዩስ መልእክቱ ስለ ደስታ ብዙ አስተምሮአል፤ በመልእክቱም “በጌታ ሁልጊዜ ደስ ይበላችሁ፤ ደግሜ እላለሁ፤ ደስ ይበላችሁ” በማለት መከራው ሥቃዩ ለሚበዛባቸው የፊልጵስዩስ ሰዎች ሁሉ ነገር በጌታ ደስ እንዲላቸው ይነግራቸው ነበር። (ፊል.፬፥፮) እናም ይህ ሕፃን ለአምላኩ ሲል መከራ እንደሚደርስበት እያወቀ እጅግ ደስተኛ ነበር።

ክርስቲያኖች አንድ ነገር ልጠይቃችሁ? ቅዱስ ጳውሎስ የፊልጵስዩስ መልእክቱን የጻፈው በእስር ቤት ውስጥ እጁና እግሩ በሰንሰለት ታስሮ ነው። እኛ ብንሆንስ ምን የሚል መልእክት የምንልክ ይመስላችኋላል? ታስረን ሊጠይቁን ለመጡ ሰዎች ምን እንላቸው ይሆን? “ምግቡ አልተመቸኝም፤ ሥቃዩ ከበደኝ፤ ያለ ጥፋቴ ነው የታሠርኩት፤ ምንም አላጠፋሁም፤ እኔ ስለእናንተ ታስሬ እናንተ ግን ዝም አላችሁኝ” እያልን የምንጽፍ አይመስላችሁምን? ቅዱስ ጳውሎስ ግን እንዲህ አላለም፤ መከራንና ሥቃይን በመቀበሉ እርሱ በጌታ ደስ እያለው ይህን መልእክት ጽፏል።

ሕፃኑ ቂርቆስ በንጉሡ ፊት ደስታን ተመልቶ ቆሞ ደስተኛ የሆነበት ምሥጢር ምን ይደንቅ ምን ይረቅ? ወደ እሳቱ ወደ ስለቱ ሊጣል ሲል ደስ የሚሰኝ ሕፃን ከወዴት ይገኛል? እስኪ ጥያቄ ልጠይቃችሁ? እናንተ ወደ ፈላ ውኃ ልትጣሉ ነው ብትባሉ የሚታያችሁ ምንድን ነው? ውስጣችሁስ ምን ዓይነት ስሜት ይሰማው ይሆን? ይህ ሕፃን ግን በፈላው ውኃ ውስጥ የሚታየው ከፈላው ውኃ ሲጣል ሊቀበሉት የተዘረጉት የእግዚአብሔር አገልጋይ የቅዱስ ገብርኤል እጆች ነበሩ። መኮንኑም “ስምህ ማን ነው?” የሚል ጥያቄ ሲጠይቀው እንዲህ አለ፤ “እኔ ክርስቲያን ነኝ” አለ፤ ምን ዓይነት መታደል ነው! ስማችን ለጠፋብን ለእኛስ ይህ ነገር ምን ይሆን? እኛ የምንመካበት ስምስ ምን ጥቅም አለው? አሁንም ቂርቆስ “እኔ ክርስቲያን ነኝ” እያለ የክርስቶስን ስም የተሸከመ ክርስቲያን መሆኑን መሰከረ። ክርስቲያኖች ሆይ፥ ስማችን ይከሰናልና ከስማችን ወቀሳ እንድን ዘንድ የክርስትና ሥራ እንሠራ ዘንድ እለምናችኋለሁ።

ከዚህ በኋላ መኮንኑ አፈረና ጽኑ ሥቃይ ሊያሠቃያቸው ወድዶ እንደ ክረምት ነጎድጓድ ድምፅ ወደ ሚያስተጋባው የፈላ ውኃ እንዲጥሏቸው አዘዘ፤ ያን ጊዜ እናቱ ፈራች፤  ሕፃኑ ግን ለእናቱ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ እንዲህም አላት፤ “እናቴ ሆይ አትፍሪ! ጨክኝ፤ አናንያ አዛርያ ሚሳኤልን ያዳነ አምላክ እኛንም ያድነናል” አላት። እናቱ ቀና ብላ ብትመለከት ለቅዱሳን ሰማዕታት የተዘጋጁትን የብርሃን ማደርያቸውን ተመለከተች፤ ደስም ተሰኝታ እንዲህ አለች፤ “ልጄ ሆይ ከእንግዲህ አባቴ ነህ፤ እኔም ልጅህ ነኝ፤ አንተን የወለድኩባት ቀን የተባረከች ናት፡፡” ክርስቲያኖች ዛሬ እናቱ ስትመጸውት ልጁ የሚሰርቅ፣ አባቱ ቤተ ክርስቲያንና ሀገር ሲሠራ እርሱ የሚያፈርስ ስንት ልጅ አለ? ቂርቆስ ግን እንዲህ አይደለም፤ ለእናቱ አባት የሚሆን የታመነ ልጅ ነው እንጅ። ወላጆች ሆይ! ልጆቻችሁን እንደ ቅድስት ኢየሉጣ ምግብ ብቻ ሳይሆን ቃለ እግዚአብሔርም እየመገባችሁ አሳድጉአቸው። ስለ ሥጋቸው ድኅነት እንደምትጨነቁ ሁሉ ነፍሳቸው እንዳትጠወልግና እንዳትከሳ ተንከባከቡአቸው። የመከራ ቀን መዳኛ ይሆኑአችኋልና።

ሕፃኑ ከእናቱ ጋር ወደ ፈላው እሳት ተጣለ። ያን ጊዜ የአካላዊ ቃልን ሰው የመሆን የምሥራች የተናገረ፣ የይቅርታና የቸርነት አማላጅ፣ ነቢያት በትንቢታቸው “ይወርዳል ይወለዳል” የተናገሩት፣ ትንቢታቸው መፈጸሙንም የምሥራች ቃል በመናገር ለዓለሙ ሁሉ ደስታ የሆነ፣ የጨለማ አበጋዝ በሚሆን በሰይጣን ተንኮል ከእፉኝት መርዝ የሚከፋ በሰው ልቡና ውስጥ አድሮ የነበረውን የኀዘን ስሜት ያጠፋ፣ በሰይጣን የተንኮል ቃል በዓለም ላይ የተዘረጋው የጨለማ መጋረጃ በምሥራች ቃል በዓለሙ ሁሉ የሕይወት ብርሃን ያበራ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ጋኑ ውስጥ በገቡ ጊዜ የውኃውን ፍላት እንደ ንጋት ውርጭ አቀዘቀዘው፤ ይህም በከበረች በሐምሌ ፲፱ ቀን ነበር፡፡

ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን፤ የቅዱስ ገብርኤል አማላጅነትና ተረዳኢነት አይለየን፤ በቅዱስ ቂርቆስና በቅድስት ኢየሉጣ ጸሎት ይማረን፤ በረከታቸው ይድረሰን፤ ለዘለዓለሙ አሜን!!!

ምንጭ፦ ስንክሳር ዘወርኃ ጥርና ዘወርኀ ሐምሌ እና ድርሳነ ገብርኤል