ልደቱ ለቅዱስ ማርቆስ

ጥቅምት ፴ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም

ቅዱስ ማርቆስ ትውልዱ ዕብራዊ ነው፤ ቤተሰቦቹ ግን ይኖሩ የነበሩት በሰሜን አፍሪካ ሲረኒካ  (ቀሬና) በተባለችውና በዛሬዋ ሊቢያ ምዕራባዊ ጠረፍ በተቆረቆረችው ደማቅ ነበር፡፡ ነገር ግን የሰሜን አፍሪካ  ዘላን ጎሳዎች የሆኑት በርበሮች በየጊዜው በከተማዋ ጥቃት እየነሰዘሩ ሀብት ንብረታቸውን እየዘረፉ ስላስቸሯቸው እናቱ ማርያምና አባቱ አርስጦቡሎስ ወደ ትውልድ ሀገራቸው ኢየሩሳሌም በመመለስ ቤት ሠርተው ተቀመጡ፡፡

የማርቆስ እናት ማርያም ባውፍልያ ቤቷን ለክርስቲያኖች መሰብሰቢያነት የሰጠች ደግ ሴት ነበረች፡፡ ጌታችንም የመጀመሪያውን የሐዲስ ኪዳን ቁርባን ለሐዋርያት ያቆረባቸው በእርሷ ቤት የላይኛው ፎቅ ላይ ነበር፡፡ በበዓለ ኀምሳም መንፈስ ቅዱስ ለሐዋርያት የወረደላቸው በእርሷ ቤት ተሰብስበው ሲጸልዩ ነው፡፡

በርናባስ ለቅዱስ ማርቆስ አጎቱ ነው፡፡ የቅዱስ ማርቆስ አባት አርስጦብሎስና በርናባስ በእናት የሚገናኙ ወንድማማቾች ናቸው፡፡ የእነርሱን እኅት ደግሞ ቅዱስ ጵጥሮስ ስላገባት ቅዱስ ማርቆስ አክስቱን ለመጠየቅ ሲሔድ ከቅዱስ ጵጥሮስ ጋር ተዋወቁ፡፡

ቅዱስ ማርቆስ ገና በልጅነቱ ኢየሩሳሌም ለመኖር በመታደሉ በዚያን ዘመን ይሰጥ የነበረውን መንፈሳዊ ትምህርት የማግኘት ዕድል ገጥሞታል፡፡ የላቲን የግሪክና የዕብራይስጥ ቋንቋዎችን አሳምሮ ያውቅ ነበር፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በይሁዳ አውራጃዎች እየተዘዋወረ ሲያስምር ማርቆስ ገና ሕፃን ነበር፡፡ በምሴተ ኀሙስ ለሐዋርያት (ወደ ከተማ ሂዱ፤በማድጋ ውኃ የተሸከመ ሰው ታገኛላችሁ፤ ተከተሉትም) በማለት ፈሲካን ሊያዘጋጁለት የመረጠውን ቤተ እንዲያሳያቸው የጠቆማቸው ወጣት ቅዱስ ማርቆስን መሆኑ የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት ይመሰክራሉ፡፡ (ማር.፲፬፥፲፫)

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ቀራንዮ በሚጓዝበት ዕለት ቅዱስ ማርቆስ ዕርቃኑን በነጠላው ሸፍኖ ይከተለው ነበር፡፡ ነገር ግን አይሁድ ሊይዙት ባሰቡ ጊዜ ጨርቁን ጥሎ ራቁቱን ሸሽቷል፡፡ ይህም በዚያ ጊዜ ገና ልጅ እንደነበር ያመለክታል፡፡ (ማር.፲፫፥፶)

ከበዓሉ በረከት ያካፍለን፤ አሜን፡፡

ምንጭ፤ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ቁጥር ፩ ገጽ ፻፪-፻፫