hitsanat

ልዩ የሕፃናት መርሐ ግብር ተዘጋጀ

ሐምሌ 10 ቀን 2004 ዓ.ም.

በፍጹም ዓለማየሁ

hitsanat

በ12 የአዲስ አበባ ሰንበት ትምህርት ቤቶች የጋራ ጥምረት እና በአፍሪካ ኅብረት ደብረ ምሕረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል ሰንበት ትምህርት ቤት አዘጋጅነት ለሕፃናት የሚሆን መርሐ ግብር ተዘጋጅቷል፡፡ መርሐ ግብሩ ከሐምሌ 12-15/2004 ዓ.ም. ለአራት ቀናት የሚካሄድ ሲሆን በሦስቱ የመጀመሪያ ቀናት “ዝክረ ቅዱሳን ሕፃናት በልሣነ ሕፃናት” በሚል መሪ ቃል በአስተናጋጅ ሰንበት ትምህርት ቤት ሕፃናት የተዘጋጀ ዐውደ ርዕይ ይቀርባል፡፡ ከመርሐ ግብሩ አስተባባሪዎች እንደተረዳነው ሐሙስ ሐምሌ 12 ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት የሚከፈተው ይህ ዐውደ ርዕይ የሕፃናቱን የእደ ጥበብ ውጤቶች ጨምሮ 8 ክፍሎች ይኖሩታል፡፡

በተጨማሪም በመርሐ ግብሩ ማጠናቀቂያ ሐምሌ 15 ዕለተ እሑድ ከቀኑ 6፡00 ጀምሮ በሚካሄደው “ዝክረ ቅዱስ ቂርቆስ ወሕፃናት” በተሰኘው የሕፃናት ጉባኤ፣ በመርሐ ግብሩ ተሳታፊ የሰንበት ትምህርት ቤቶች ሕፃናት የተዘጋጀ ወረብ፣ መንፈሳዊ ቅኔ፣ የኪነ ጥበብ ፍሬዎች በተጨማሪም በሕፃናቱ የተዘጋጀ ስለ ቅዱስ ቂርቆስ ተራኪ የሆነ ፊልም የሚቀርብ ሲሆን በሥዕል የተደገፈ የሕፃናት መጽሐፍ በዕለቱ ይመረቃል፡፡ በዕለቱም ቅዱሳን ሊቃነ ጳጳሳትና የደብር አስተዳዳሪዎች እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በዕለቱም ሕፃናት ልጆችዎን ይዘው በመርሐ ግብሩ ላይ እንዲገኙ የመርሐ ግብሩ አስተባባሪዎች ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡