“ለፀሐይም ቀንን አስገዛው፤ ጨረቃንና ከዋክብትንም ሌሊትን አስገዛቸው” (መዝ.፻፴፭፥፰‐፲)

                                                                 ዲያቆን ተስፋዬ ቻይ

ታኅሣሥ ፭፳፻፲፭ ዓመተ ምሕረት

‹‹የፀሐይን፣ የጨረቃን፣ የከዋክብትን ሥራቸውን ዕወቅ፤ ከሁሉ የሚደንቅ ክበባቸውን ከሁሉ የሚበልጥ ብርሃናቸውን ሁሉ ዕወቅ፤ በየወገናቸው የሚያበሩ የሚመላለሱ የእነዚህን የምሳሌያቸውን ሥራ ዕወቅ፤ ሁሉ ጊዜ እርስ በእርሳቸው እንደምንም እንደሚቀራረቡ ዳግመኛም እንደምንም እንደሚራራቁ ዕወቅ›› (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ ባስልዮስ ምዕራፍ ፴፭፥፲፯)

 

ፀሐይን፣ ጨረቃንና ክዋክብትን መቼ ከምንስ ፈጠራቸው?

የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ እግዚአብሔር ከዕለተ እሑድ እስከ ዕለተ ዐርብ ብዙውን አንድ እያልን ብንቆጥር ሃያ ሁለት ፍጥረታትን ፈጥሯል፤ ለፍጥረት ዐራተኛ በሆነው ማክሰኞ ማታ ለረቡዕ አጥቢያ ፀሐይን፣ ጨረቃና ክዋክብትን ፈጠረ፡፡ አክሲማሮስ የተባለው ቅዱስ መጽሐፍ ስለ ሥነ ፍጥረት በጥልቀት በሚገልጸው ክፍሉ ላይ ስለ ሦስቱ ብርሃናት አፈጣጠር እንዲህ ገልጾልናል፤  የፀሐይን ሰሌዳ ከእሳትና ከነፋስ አድርጎ ፈጠራቸው ትኩስነታቸው ከእሳት መፈጠራቸውን ነፋስነታቸው ከቦታ ቦታ መንቀሳቀሳቸውን ያስረዳል፤ የጨረቃና የከዋክብትን ሰሌዳ ከነፋስና ከውኃ ፈጠረ በነፋስነታቸው ይሄዳሉ፤ በውኃነታቸው ይቀዘቅዛሉ፡፡ እንዲህ አድርጎ ከፈጠራቸው በኋላ በዕለተ እሑድ ለይኩን ብርሃን ብሎ ከፈጠረው ብርሃን የስንዴ ቅንጣት ታህል ፀሐይን ቀብቶ ለቅዱሳን መላእክት አሳያቸው፤ ከዚያም አስፈራቻቸው፤ ለመላእክት ካስፈራች ለሰው ትከብዳለችና ከፍሎ ቀባት፡፡ ከሰባት እጅ ከፍሎ ሁለቱን ለጨረቃ፣ አንዱን ለከዋክብት፣ አራቱን ለፀሐይ ከፍሎ ቀባቸው፡፡ (መጽሐፈ አክሲማሮስ)

ፀሐይን ከቀባት አራት እጅ አንዱን አንሥቶ ለሰማይና (ጠፈር) ለደመናት ቀባቸው፤ ለፀሐይ ሦስት እጅ ቀረላት፡፡ ቅዱሳን መላእክትም የፀሐይን መሞቅና የጨረቃን ድምቀት አይተው አድንቀው እልል እያሉ አመሰገኑት፡፡ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም፤ ቅዱስ አትናቴዎስ ስለ ደንቅ ሥራው እንዲህ ይመሰክርልናል፡፡ ‹‹.እርሱ እንደወደደ ፈጠረ፤ እርሱ እንደ ወደደ ጥረቱ በጎ ሥራ ልንሠራ ወደ እርሱ አቀረበን፤ ለወዳጆቹ ለአንዱም ለአንዱም መስጠት የሚገባው እንደመሆኑ እንደ ቸርነቱ እርሱ እንደ ወደደ ሥራውን ገለጠ፤ እንደምን ሆነ? በምን ሥራ ተደረገ? ብለን አንመርምር? የፈጠረ እርሱ ነውና ዕውቀትን ሁሉ ለእግዚአብሔር እንተው እንጂ…››‹‹.. (ሃይማኖተ አበው ዘቅዱስ አትናቴዎስ ፳፰፥፵) እኛም እንደ ቅዱሳኑ  ድንቅ ሥራውን ከማድነቅ ውጪ በጥቂቱ አስተሳሰባችን መርምረን ልንደርስበት አይቻለንም? በእምነት ብቻ እንቀበለዋለን፤ ቅዱስ ጳውሎስ ለዕብራውያን ምእመናን በላከው መልእክቱ ‹‹…ዓለም በእግዚአብሔር ቃል እንደተፈጠረ፥ የሚታየውም ነገር ከማይታየው እንዳልሆነ በእምነት እናስተውላለን›› በማለት የተናገረው ለዚህ ነው፡፡ (ዕብ.፲፩፥፫)

ቅዱስ ኤጲፋንዮስም እግዚአብሔር የፍጥረታት ፈጣሪ መሆኑን ሲመሰክር እንዲህ ይላል፤ ‹‹…ሁሉ ከእርሱ ነው፤ ሁሉም ስለ እርሱ ነው፤ ሁሉም የእርሱ ነው፤ ሰማይ በእርሱ ነው፤ ከሰማያት በላይ ያለ ሰማይም የእርሱ ነው፤ የአርያም ስፋት የክብሩ ዙፋን ነው፤ የምድርም ስፋት የእግሩ መመላለሻ ናት፤ ፀሐይ የእርሱ ነው፤ ጨረቃም ከእርሱ ነው፤ ክዋክብትም የእጁ ሥራ ናቸው፤ ደመናት መልእክተኞቹ ነፋሳትም ሠረገላዎቹ ናቸው፤ እሳትም የቤቱ ግርግዳ ነው፡፡ (ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ)

ፀሐይን፤ ጨረቃንና ክዋክብትን ለምነ ፈጠራቸው? እስከ መቼ ይቆያሉ?

በዕለተ ረቡዕ በዐራተኛ ቀን እግዚአብሔር ፀሐይን፣ ጨረቃን፣ ከዋክብትን ዘመናትን ለመቁጠር ጊዜያትን ለመስፈር ዕድሜን ለመለካት ፈጥሯቸዋል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወልደ ነጎድጓድ የእግዚአብሔርን ቅድመ ዓለም መኖር በገለጠበት ጸሎተ ቅዳሴው ይህንኑ እንዲህ ገልጦልናል፡፡ ‹‹…ፀሐይ የመዓልትን ርዝመት ሳይገዛ ጨረቃም የሌሊትን ርዝመት ሳይገዛ በባሕርዩ የነበረ ነው…›› ፀሐይን በቀን እንድታበራ አደረጋት፤ ጨረቃንና ከዋክብትን ደግሞ በሌሊት አሠለጠናቸው፤ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊትም በመዝሙሩ እንዲህ መስክሯል፡፡ ‹‹.. ለፀሐይ ቀንን ያስገዛ ..…ለጨረቃና ለከዋክብትም ሌሊትን አስገዛቸው …›› (መዝ.፻፴፭፥፰-፱) እነዚህ ብርሃናት (ፀሐይ ጨረቃ ከዋክብት) ለሰው ልጅ ያገለግሉ ዘንድ በጠፈር (በሰማይ) ሆነው እንዲያበሩለት ተፈጥረዋል፡፡

እግዚአብሔር የፈጠራቸው ሊጠቀምባቸው አይደለም፤ ለሰው ልጆች እና በምድር ላሉ ፍጥረታት እንጂ፤ በሠለስቱ ምዕት ጸሎተ ቅዳሴ ‹‹..ፀሐይና ጨረቃን በፈጠረም ጊዜ እንደ ጨለመበት ሰው ሊያበሩለት አይደለም፡፡ ከእርሱ ብርሃን የስንዴ ቅንጣት ታህል ሰጣቸው እንጂ ስለዚህም በሰው ላይ አበሩ፡፡….›› በማለት የተናገሩት ለዚህ ነው፡፡ (ቅዳሴ ዘሠልስቱ ምዕት)

አገልግሎታቸውም እግዚአብሔር ዳግመኛ ለፍርድ ወደዚህ ምድር እስኪመጣ ድረስ ነው፤ ጌታችን ለቅዱሳን ሐዋርያት ስለ ዳግም ምጽአቱ ባስተማረው ትምህርቱ አስቀድሞም በነቢያቱ ገልጿል፡፡ ‹‹…ከዚያች ወራትም መከራ በኋላ ወዲያው ፀሐይ ይጨልማል፤ ጨረቃም ብርሃንዋን አትሰጥም፤ ከዋክብትም ከሰማይ ይወድቃሉ፤ የሰማይም ኃይላት ይናወጣሉ::(ማቴ.፳፬፥፳፱፣ ኢሳ.፲፫፥፲፣ ሕዝ.፴፪፥፯)

ቅዱስ አትናቴዎስም በጸሎተ ቅዳሴው ቁጥር ፷፱ እንዲህ ያስረዳናል፤ ‹‹ዳግመኛ ይህች ዕለት በምትሰለጥንበት ጊዜ አዲስ ሥራ አዲስ ነገርም ይሆናል፤ ያን ጊዜ የፀሐይና የጨረቃ ጸዳል ክረምት ወይም በጋ የለም፡፡››

እነዚህ ድንቅ የዕለተ ረዕቡዕ ፍጥረታት አንዳቸው ከአንዳቸው  በክብር ይበላለጣሉ፤ ፀሐይ በክብር ከሁሉ ትልቃለች፤ ጨረቃ ደግሞ ከከዋክብት፤ ከዋክብትም እያንዳንዳቸው አንዱ ከአንዱ እንዲሁ፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ምእመናን በላከው መልእክቱ እንዲህ ይገልጸዋል፤ ‹‹…የፀሐይ ክብሩ አንድ ነው፤ የጨረቃም ክብሩ ሌላ ነው፤ የከዋክብትም ክብር ሌላ ነው፤ በክብር አንዱ ኮከብ ከሌላው ኮከብ ይለያል…፡፡›› (፩ቆሮ.፲፭፥፵፩)

እግዚአብሔር ፀሐይን ከእሳትና ከነፋስ ፈጥሯታል፤ በእሳትነቷ ታቃጥላለች፤ ታበራለች፤ በነፋስነቷ ትንቀሳቀሳለች፤ ፀሐይ ከምሥራቅ ወጥታ በመዐልት ስታበራ ቆይታ በምዕራብ ትጠልቃለች፤ ነቢዩ ክቡር ዳዊት የፍጥረታት ጌታ ስሙ በሁሉ የተመሰገነ መሆኑን በገለጸበት ምስናው እንዲህ ገልጿል ‹‹…የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ተናገረ፤ ከፀሐይም መውጪያ ጀምሮ እስከ መግቢያዋ ድረስ ምድርን ጠራት …›› (መዝ.፵፱፥፩) ጨረቃና ክዋክብት ከውኃ እና ከነፋስ ተፈጥረዋል፡፡ በውኃነታቸው ይቀዘቅዛሉ፤ በነፋስነታቸው ይንቀሳቀሳሉ፡፡

ሰዓቱን ከዕለት፣ መዓልቱን ከሌሊት፣ ዓመቱን ከዘመን ለመለየት ፀሐይንና ጨረቃን ከዋክብትን ሹሞአቸዋል፡፡ ፀሐይ መግቦቷን ዓመት እስከ ዓመት ገዛች፤ ጨረቃን ሌሊቱን ዓመት እስከ ዓመት ገዛች፡፡ ከዋክብት በዐራት የከዋክብት አለቃ፤ (ምልክኤል፣ ሕልመልሜሌክ፣ ናርኤል፣ምልኤል)  አመካኝነት ዓመቱን ለዐራት ከፍለው ክረምት፣ ሐጋይ፣ መጸው፣ ጸደይ በማለት ፺፩ ቀን ፺፩  ቀን ይገዛሉ፡፡ (መጽሐፈ አክሲማሮስ)

ከመጋቢት ፳፭ ጀምሮ እስከ ሰኔ ፳፭ ያለውን ምልክኤል ይመግባል፤ ወቅቱም ጸደይ ይባላል፤ በዚህ ወቅት በጸደይ ሠልጥኖ የባጀ ዋዕይ ወደታች ተቀብሮ የነበረ ቁር ወደ ላይ ሲል ከላይ ሙቀቱ ከታች ጠሉ ሲሰማት ምድር ትለሰልሳለች፤ የዘሩባትን ሁሉ ታበቅላለች፡፡

ከሰኔ ፳፭ እስከ መስከረም ፳፭ ቀን ድረስ ያለውን ሕልመልሚሊክ ይመግባል፤ ወቅቱም ክረምት ይባላል፡፡ በዚህም በክረምቱ ሠልጥኖ የነበረ ዋዕይ ፈጽሞ ሲጠፋ ተቀብሮ የነበረው ቁር ሲወጣ ከውኃው ብዛት ከምንጩ ጽናት የተነሣ ምድር እፈርስ እፈርስ እናድ እናድ ትላለች፤ ከዚህም በኋላ ጌታ ደመና ገልጦ ፀሐይ አውጥቶ ምድርን ያረጋታል፤ ያጸናታል፡፡

ከመስከረም ፳፭ እስከ ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ያለውን ናርኤል ይመግባል፤ ወቅቱም መጸው ይባላል፤ በዚህ መጸው ሠልጥኖ የከረመው ቁር ወደ ታች ተቀብሮ የከረመ ዋዕይ ወደ ላይ ሲወጣ ከታች ሙቀቱ ከላይ ጠሉ ሲሰማቸው አዝርአት አትክልት ያድጋሉ፤ ይገዝፋሉ፤ ያብባሉ፤ ያፈራሉ፡፡

ከታኅሣሥ  ፳፭ እስከ መጋቢት  ፳፭ ቀን ያለውን ምልኤል ይመግባል፤ ወቅቱም  ሐገይ (በጋ) ይባላል፡፡ በዚህም ሐጋይ ሠልጥኖ የቆየው ቁር ፈጽሞ ተቀብሮ የከረመ ዋዕይ ጽናት የተነሣ አዝርዕት አትክልት ይደርቃሉ፤ ታጭደው ተወቅተው በጎተራ በሪቅ ይገባሉ፡፡

ፀሐይና ጨረቃ ክዋክብትን ከፈጠራቸው በኋላ የተፈጥሮ ዑደታቸውን ጠብቀው እንዲያበሩ እንዲፈራረቁ ጠባቂ መላእክትም ሾሞላቸዋል፤ ቅዱሳን መላእክት ወደ እነርሱ እንደሚላኩ ሲያስረግጥልን እግዚአብሔርን ባመሰገነበት ምስጋናው ቅዱስ ጎርጎርዮስ በቅዳሴው እንዲህ ይለናል፡፡ ‹‹…ለእርሱ ብቻ እንሰግድለት ዘንድ ኑ! በአየር ላይ የምትወጡ ሁላችሁ የመላእክት ሠራዊት ወደ ፀሐይና ወደ ጨረቃ ወደ ከዋክብትም የምትላኩ ወደ ባሕርና ወደ ቀላያትም የምትወጡ….›› በማለት ይናገራል፡፡ (ቅዳሴ ቅዱስ ጎርጎርዮስ ገጽ ፻፴፬)

ከሰው ልጅ ሕይወት ጋር ያላቸው ምሳሌነታቸው ምንድን ነው?

ፀሐይን በቀን ጨረቃን ከዋክብትን በሌሊት አሠለጠናቸው፤ ፀሐይን በቀን ብቻ ያደረጋት ከዋዕዩ ብዛት የተነሣ በሙቀቷ ፍጥረት እንዳይጎዳ በመዓልት ብቻ እንድታበራ አደረገ፤ ጨረቃንና ከዋክብትን በሌሊት ማሰልጠኑ ከውርጭ ብዛት ከቁር ጽናት የተነሣ ፍጥረት እንዳይኮማተር በማለት ነው፡፡

የዕለተ ረቡዕ ፍጥረታት ለምእመናን ሕይወት ምሳሌ ናቸው፤ ምእመናን በመልካም ሥራቸውና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ጥንካሬ በገድል ትሩፋታቸው ጽናት አንዳቸው ከአንዳቸው መላላቅ (መበላለጥ) እንዳለ ምሳሌ ናቸው፡፡ ቅዱሳን ሰማዕታት እንደየ ሥራቸው ባለ ፴ ፣ባለ ፷ ፣ባለ ፻ ፍሬ ይሆናሉ፡፡ ‹‹…አንዱም መቶ፣ አንዱም ስድሳ፣ አንዱም ሠላሳ ፍሬ ሰጠ..›› (ማቴ.፲፫፥፰) እንዲል ቅዱስ ወንጌል፡፡ እግዚአብሔር ‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ …›› በማለት ፈለጉን ተከትለው፣ ሕጉን አክብረውና ትእዛዙን ፈጽመው ለሚኖሩ በማይታበል ቃሉ በገባው ቃል ኪዳን መሠረት ከባሕርይ ቅድስናው በጸጋ ይሰጣል። (ዘሌ.፲፱፥፪)

ለቅድስና ሕይወት ለመብቃት ሦስት ደረጃዎች አሉ፤ ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ነፍስ፣ ንጽሐ ልቡና ናቸው፡፡ ሰዎች በሃይማኖታችን ጽናት በምግባራችን መጎልበት ንጽሐ ሥጋ ላይ ስንደርስ ከበደል በሥጋችን ስንነጻ ባለ ፴ ፍሬ፣ በነፍሳችን ንጹሕ ስንሆን ባለ ፷ ፍሬ፣ በልቡናችን ንጹሕ ስንሆን ባለ ፻ ፍሬ አፍርተን በክብር ባለቤት ዘንድ ክብርን እንጎናጸፋለን፡፡ በዕለተ ረዕቡ የተፈጠሩት ከዋክብት በክብር እንዲበላለጡ ቅዱሳንም በተጋድሏቸው ልክ በክብር ይገለጣሉ፤ ጌታችን ስለ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ክብር ሲገልጥ ‹‹…እውነት እላችኋለሁ ከሴቶች ከተወለዱት መካከል ከመጥምቁ ዮሐንስ የሚበልጥ አልተነሣም..፡፡›› እንዳለው ቅዱሳን ፣ ሰማዕታት በዘመናቸው በገጠማቸው ተጋድሎ ክብራቸው ይላላቃል፤ (ማቴ.፲፩፥.፲፩) በንጽሐ ሥጋ ማዕረግ  ከጽማዌ፣ ከልባዌ፣ ከጣዕመ ዝማሬ የደረሱ ባለ ፴፣ በንጽሐ ነፍስ ከሑሰት፣ ከፍቅር፣ ከአንብዕ፣ ከኩነኔ የደረሱ ባለ ፷፣ በንጽሐ ልቡና ማዕረግ ንጻሬ መላእክት፣ ከዊነ እሳት፣ ነጽሮተ ሥሉስ ቅዱስ ክብር ደርሰው ባለ ፻ የተባሉ አሉ፡፡ ‹‹ልበ ንጹሐን ብፁዓን ናቸው፤ እግዚአብሔርን ያዩታልና…›› እንዲል፤ (ማቴ.፭፥፰) ፀሐይ ለጻድቃን ምሳሌ ናት፤ ፀሐይ ሁል ጊዜ ሙሉ ናት፤ ጻድቃንም በምግባራቸው በሃይማኖታቸው ሙሉ ናቸው፡፡ ‹‹.. ጨረቃ የኃጥእን ምሳሌ ናት፤ ጨረቃ አንዴ ሙሉ አንዴ ጎዶሎ ትሆናለች፤ ኃጥአንም በምግባር በሃይማታቸው ሲሞሉ ሲጎድሉ ይኖራሉ፡፡ እንዲሁም  ፀሐይ በኃጥኣን ትመሰላለች፤ ፀሐይ ሁል ጊዜ ምሉዕ እንደሆነች ኃጥአንም በክፋት ሥራቸው ሁሉም ሙሉ እንደሆኑ ሳይለወጡ የመኖራቸው ጨረቃ በጻድቃን ትመሰላለች፤ ጨረቃ ጎድላ አትቀርም፤ ትሞላለች፤ ጻድቃንም በኃጢአት ከጽድቅ ሥራ ቢጎድሉም በንስሓ መልሰው ሙሉ ይሆናሉ፡፡ (መጽሐፈ አክሲማሮስ) ‹‹ ..ጻድቅ ሰባት ጊዜ ይወድቃል ይነሣልም..›› (ምሳ.፳፬፥፲፮)

መዓልት የመንግሥተ ሰማያት ምሳሌ በመዓልት ብዙ ደስታ ይገኛል፤ እንደዚሁም ሁሉ ጻድቃን በመንግሥተ ሰማያት ብዙ ክብር ብዙ ጸጋ ያገኛሉ፡፡ ‹‹…ብሩሃት ከዋክብት የምትመስሉ ሁላችሁ ምእመናን ሆይ ለእናንተ ክብር ይገባል ..›› እንዲል፤ (ቅዱስ አትናቴዎስ) በዳግም ምጽአት በመልካም ሥራ አጊጠን ‹‹እናንተ የአባቴ ብሩካን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥቴን ውረሱ›› የሚለውን የሕይወት ቃል ሰምተን፣ እንደ ፀሐይ አብርተን፣ እንደ ጨረቃ ደምቀን፣ እንደ ከዋክብት አሸብርቀን እንገኝ ዘንድ እንደ ፀሐይ በምግባር ሙሉ እንሆን ዘንድ በሕጉ እንመራ፤ (ማቴ.፳፭፥፴፬) ከበደል ሥራ እንራቅ፤ በጽቅ ጎዳና እንመላለስ፤ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ሁል ጊዜ ወደላይ እንደግ በጾም፣ በጸሎት፣ በትሩፋት ሥራ እንድመቅ፡፡

ሌሊት የገሃነመ እሳት ምሳሌ ነው፤ በሌሊት ብዙ መከራ ይገኝበታል፤ እንደዚሁም ሁሉ ኃጥኣን በገሃነመ እሳት ብዙ ሥቃይና መከራ ያገኛቸዋል፡፡ በበደል መኖርና ከጽድቅ መለየት በሰማይ ብቻ ሳይሆን በምድርም ሕይወትን ያቀጭጫል፤ የኑሮን ጣዕም ያመራል፤ ጎዳናን ያጨልማል፤ በክርስትና ሕይወት ስንኖር ከጨለማ ሥራ ልንለይ ይገባል፡፡ ጨረቃ ጎዶሎ እንደምትሆነው ከጽድቅ ሥራ ልንጎድል አይገባም፤ ‹‹..በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን አውቃለሁ፡፡ በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም በሆነ ነበር፡፡ እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንክ ከአፌ ልተፋህ ነው …›› በማለት አምላካችን ተናግሯል፡፡ (ራእ.፫፥፲፭-፲፮) ከምግባር ሕይወት ጎድለን እንዳንተፋ ከመንግሥተ ሰማያት አፋኣ እንዳንሆን ስለበደላችን ንስሓን ገብተን በጥሩ ሥነ በምግባር በቀና በሃይማኖት እንጽና ዘንድ ቅዱስ ፈቃዱ ይሁንልን፡፡

ይቆየን!

ስብሐት ለእግዚአብሔር

ወለወላዲቱ ድንግል

ወለመስቀሉ ክቡር!