‹‹ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እናንተ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ ክርስቶስ በፍቅር ተመላለሱ›› (ኤፌ. ፭፥፪)

በወልድ ውሉድ፤ በክርስቶስ ክርስቲያን የሆንን ሰዎች ሁሉ ከክርስቶስ ጋር ያለን ግንኙነት በሃይማኖት እውቀት ላይ ብቻ የተመሠረተ ሳይሆን በተግባር በሚገለጥ ፍቅርም ጭምር መሆኑን መረዳት ይገባል፡፡ ክርስቲያንነታችን ቁንጽል ወይም ጎደሎ ሆኖ ያለ ፍሬ እንዳይቀርና የተሟላ እንዲሆን የሚያደርገው ከእምነት ጋር የክርስቶስን የፍቅር ሥራ በጎነትን፣ ትሕትናውንና ትዕግሥቱን ሁሉ እርሱን አብነት በማድረግ፤ እርሱ ባለፈበት መንገድ ሁሉ በእግር ሳይሆን በግብር ተከትለን በመሄድ ነው፡፡ የክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መምጣት በጥቅሉ ሲገለጽ አንደኛ ለቤዛነት፤ ሁለተኛ ለአርአያነት በመሆኑ ሁለቱም በእኛ ላይ ተፈጻሚነት ሊኖራቸው የሚችለው የመጀመሪያውን በእምነት ስንቀበለው ሁለተኛውን ደግሞ ክርስቶስን መስለን እንደ እርሱ በመኖር ፍቅር በተግባር ስንተረጒመው መሆኑን ተረድተን ሁለቱንም በአንድነት መያዝ አለብን፡፡ ነገር ግን በአንዳንድ ወገኖች እንደምናየው የእምነትን ነገር ብቻ ጠብቆ ሌላውን ማጣጣል ከክርስቶስ ይለየናል እንጂ አንድ አያደርገንም፡፡ ‹‹እንግዲህ እንደ ተወደ ልጆች እግዚአብሔርን የምትከተሉ ሁኑ፥ ክርስቶስም ደግሞ እንደ ወደዳችሁ ለእግዚአብሔርም የመዓዛ ሽታ የሚሆንን መባንና መሥዋዕትን አድርጎ ስለ እንናተ ራሱን አሳልፎ እንደሰጠ ክርስቶስ በፍቅር ተመላለሱ›› ተብሏልና፡፡ (ኤፌ. ፭፥፩-፭፤ የትምህርተ ሃይማኖት መቅድም)

የእግዚአብሔር ልጆች እንሆን ዘንድ አምላኮተ እግዚአብሔርን መፈጸም ይጠበቅብናል፡፡ በመጽሐፍም አባቶቻችን በብሉይ ኪዳን ፍየል፣ በግ፣ ወይፈን፣ ርግብን መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ሲያቀርቡ እሳት ከሰማይ ወርዳ መሥዋዕቱን ትበላላቸው እንደነበር ይገልጻል፡፡ መሥዋዕታቸውንም እሳት መብላቱ እግዚአብሔር ለመቀበሉ ማረጋገጫ ነበረች፡፡ እነርሱም በዚህ ከእግዚአብሔር ጋር ታርቀው ይኖሩ ነበር፡፡ ቅዱስ አባታችን ዮሐንስ አፈወርቅ ይህን ሲተረጉም ‹‹መሥዋዕት ማለት አንተ ሰው ዛሬ በግ፣ ፍየል፣ ወይፈን ወይም ርግብ የምታርድ አይምሰልህ፤ ራሱን ሠውቷልና፡፡ ከአንተ የሚፈልገው መሥዋዕት ምንድነው ካልከኝ ራስህን መሥዋዕት አድርገህ ማቀረብ ነው፤ ክህነት የማያስፈልጋት መሥዋዕት ማለት ይህች ናት›› ብሏል፡፡ መሥዋዕት የሚቀርብበት መረብረቢያው፣ መጸፍጸፊያው፣ ድንጋዩ፣ ጉልቻው፣ እንጨቱ፣ እና ማገዶው ደግሞ ምሕረትና ርኅራኄ ነው፡፡ ፍቅር፣ ትዕግሥት፣ ትሕትና፣ የዋህነት እና ንጽሕና የመሥዋዕት መረብረቢያዎች ናቸው፡፡ ጸሎት፣ ስግደት፣ ምጽዋት እና ቸርነት መሥዋዕት ሲሆኑ የሚቀርቡበት ምድጃ ትዕግሥትና ትሕትና ነው፡፡  (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)

አንዳንድ ጊዜ ግን ትዕግሥት ትዕቢትን ያመጣል፤ ‹‹እኔ ይገርማችኋል ብዙ አልበሳጨም፤ ብዙም አይከፋኝም፤ ምንም መስሎ አይታየኝም›› የሚል ሰው አጋጥሞን ይሆናል፡፡ ራሱን ጥሩ  አድርጎ ይቆጥራልና ነው፡፡ ሆኖም ለትዕግሥት ትሕትና ያስፈልገዋል፤ ያለበለዚያ ግን ትዕቢት ሕይወታችን በውስጡ ያድራል፡፡ ትዕግሥተኛ ብንሆን እንኳን እንዳልታገሥን ሊሰማን ይገባል፡፡  በትዳር ውስጥም በሚገጥሙን  ፈታናዎች ሁሉ ፈጽመን መታገሥ እንጂ መፋታት የለብንም፡፡ ለጊዜው የከበደንን ነገር ስንማረር እስከ መጨረሻው በትዕግሥት ከጠበቅነው ውጤቱ ያማረ፤ የጣፈጠ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም አባቶቻችን እንደሚሉት ትዕግሥት መራራ ብትሆንም ፍሬዋ ግን ጣፋጭ ነው፡፡ ሁልጊዜ የእግዚአብሔርን ትዕግሥት አርአያ እያደረግን ለሕይወታችን፣ ለቅድስና ሕይወታችን እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን ሁሉ በትዕግሥት ማለፍ ታላቅ የክርስቲያናዊ ሕይወት ብስለት መለኪያ ነው፡፡ በዚህ ዘመን ሴትን አይቶ ማለፍ፤ ወንድን አይቶ ማለፍ፤ ምግብን አይቶ ማለፍ፤ ብርን አይቶ ማለፍ ከባድ እየሆነ መጥቷል፤ ይሁን እጂ ይህን ፈተና ለማለፍ ትዕግሥት ገንዘብ ማድረግና በጸሎት መጽናት ያስፈልጋል፡፡

ትዕግሥትን ገንዘብ የማያደርጉ ሰዎች ጸሎት ይሰለቻቸዋል ወይም ይመራቸዋል፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ ከፈጣሪ መልስ ያጡ ይመስላቸዋል፡፡ ‹‹የጻድቅ ሰው ጸሎት ከአፉ ወደ ጆሮው ነው፤ ጥያቄውን በአፉ ከማቅረቡ መልሱ በጆሮው ይደርሳል›› እንደሚባለው ጥያቄያቸው፣ ልመናቸውና ጸሎታቸው በአንድ ጀምበር ምላሽ እንዲያገኙ ይፈልጋሉ፡፡ ይሁን እንጂ ብዙዎች የሚለምኑትን አያውቁም፤ ከዚያ ባሻገር ደግሞ ከእግዚአብሔር ጋር በጸሎት ለመነጋገር ንጽሐ ልቡና ያስፈልጋል፡፡ ንጽሐ ልቡናና ፈሪሀ እግዚአብሔር ካለው ማንኛውም የጸሎት ሰው ለእግዚአብሔር ቅርብ ነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ እንደ ኤልያስ ሰማይን መለጎም፤ እንደ ኢያሱ ባሕርን መክፈል፤ እንደ ዳንኤል የአንበሶችን አፍ መዝጋት… ይችላል፡፡  ስለዚህ ለእግዚአብሔር የጸሎታችንን ጥያቄ ስናቀርብ ትዕግሥት፣ ቅንነት፣ የዋሃት፣ ፈሪሀ እግዚአብሔርና ትሕትና መሥዋዕታችን ናቸውና እነዚህን ገንዘብ ማድረግ አለብን፤ ልባችን ደግሞ መሠዊያችን በመሆኑ ከበቀል፣ ከቂም፣ ከትምክሀት፣ ከትዕቢት እና ከክፋ ሥራ ሁሉ ንጹሕ ሊሆን ይገባል፡፡ ያን ጊዜ  እግዚአብሔር እኛ ከጠየቅነው ይልቅ አብዝቶ የልቡናችን መሻት ይፈጽምልናል፡፡

መሥዋዕቱን ሚበላው እሳቱ ደግሞ ፍቅረ እግዚአብሔር ነው፡፡ በፍቅረ ንዋይ እና በዝሙት፤ ከመቃጠል በፍቅረ እግዚአብሔር መቃጠል ይሻላል፡፡ እነዚህ መቃጠሎች ወደ ጽድቅ ይመሩናል፤ ያደርሱናልም፡፡ ብዙ ጊዜ መንፈሳዊ አገልግሎት፣ ቅዳሴ፣ ዐሥራት በኵራት መሥጠት ኃጢአትን መናዘዝ፣ የትዳር ሕይወታችን የሚሰለቸን ውስጣችንን የገንዘብ እንጂ የእግዚአብሔር ፍቅር ስለማያቃጥለን ነው፡፡ በዘወትር ጸሎታችን ላይ ይእቲ መንግሥት የተባለችው መንግሥተ ሰማያት ኃይል የምንላት ደግሞ ሰውን ወደ እሳት የምትወስድ፤ በበርሃ በዱር በገደል፣ በዋሻውና በፍርኩታው የምታንከራትት፤ አካልን ለእሳት የምትሰጥ፣ ስለሃይማኖት፣ ስለክርስቶስ ፍቅር ‹‹አንገቴን ለስለት፤ ደረቴን ለውጋት፤ እግሬን ለእግር ብረት፤ ዓይኔን ለፍላት እሳጣለሁ›› በማለት እስከፍጹም መሥዋዕት የምታደርስና በክርስቶስ ፍጹም ፍቅር የምትማርክ የፍቅር ኃይል አላት፤ ነገር ግን እኛ እንደዚህ ዓይነት ፍቅር ስለሌለን ሁሉ ነገር ይሰለቸናል፡፡  (ጾመ ድጓ)

የገንዘብ፤ የሥልጣን ወይንም የውበት ፍቅር ሊያቃጥለን አይገባም፤ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለውበት እንዲህ ብሏል ‹‹ወዳጄ ውበት ማለት ምን እንደሆነ ልንገርህ? አንተ ውብ በምትለው ሰውነትህ ውስጥ የተበሉ፤ የተጠጡ ጭማቂዎች በላይ ሲፈሱ ነው፡፡ በአንተ ውስጥ ያሉትን እነዚህን በላስቲክ አስቀምጬ ባሳይህ ትጸየፈዋለህ፤ የላይኛው በቆዳ ተለጉሞ እንጂ ትርጒም የለውም፡፡ የሚተላ እና የሚበሰብስብ ሰውነት ለሰው ልጅ ምን ያኮራዋል? እንዲህ ባለው በዝሙት እና በመጎምጀት ጥማት አትንደድ፤ በእግዚአብሔር ፍቅር ንደድ!››  መንፈስ ቅዱስ በእሳት ተመስሎ መውረዱ ልጆቹን በፍቅሩ እሳትነት ያነዳቸውልና ነው፡፡ እናንተም በእሳት ትጠመቃላችሁ የተባለው በፍቅሩ ስለሚያፈላ፤ ልቡናዬ በመንፈስ ቅዱስ ፈላና ምሥጢር አወጣ የሚባለውም ይህን ጊዜ ነው፤ ስለዚህ ቅዱስ ጳውሎስ በእግዚአብሔር ፍቅር  ነደደ፡፡ (ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፤ ቅዱስ ቄርሎስ)

ቅዱስ አፈወርቅም ‹‹ቅትሎ ለሥጋከ፤ ሥጋህን ግደለው፤ ይበቃሀል በለው፤ ፍላጎቱን ግታው፤ እስከመቼ እየሳሳህ ትኖራለህ፤ እጅህን ግታው›› በማለት አስተምሯል፡፡ ‹‹ቀኝ እጅህም ብታሰናክልህ፥ ቈርጠህ ከአንተ ጣላት›› እንደተባለውም እጃችን አልመጸውትም ብትል እና ዓይናችን ዝሙት ብትመኝ እንቢ ልንል ይገባል፤ እግራችን ቆሜ አላስቀደስም ብትለን እስኪ ትቆረጪ እንደሆነ አይሻለሁ ብለን አስቀድሰን እስክንጨርስ ልንቆምባት ያስፈልጋል፡፡ የሰውነትን ፈቃድ በመግታት የልቡናችንንም ፍላጎት በመተው ነፍሳችን እናድናታለን፡፡ (ማቴ. ፭፥፴)

አምልኮተ እግዚአብሔር እንፈጽም ዘንድ የፈጣሪያችን እርዳታ አይለየን፤ አሜን!

ምንጭ፤ ‹‹የትምህርተ ሃይማኖት መቅድም›› በሊቀ ጉባኤ አባ አበራ በቀለ፤ ጾመ ድጓ