‹‹ለችግረኛና ለምስኪን የሚያስቡ ብፁዓን ናቸው›› (መዝ. ፵፥፩)

ነሐሴ ፲፱ ቀን ፳፻፲፫ ዓ.ም

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ዓለም በሥጋ ብእሲ ተገልጦ በኖረበት ዘመነ ሥጋዌ የተለያዩ ችግሮች ያሉባቸውና በክፉ ደዌ የተያዙ ሰዎች በእርሱ እንደተፈወሱ መጽሐፍ ቅዱስ ቀዳሚ ምስክር ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜም ቤተ ክርስቲያን ተጠግተው በጸበል ኃይል የሚፈወሱ፣ የዕለት ጉርሻቸውን በምእመናን ርዳታ የሚያገኙ ነዳያን በርካታ ናቸው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ችግረኞችን እንዴት መርዳት እንደሚቻል ታስተምራለች፡፡

ሰዎች በቅን ልቡና ተነሣሥተው ችግረኞችን መርዳት ይችሉ ዘንድ እነማንን መርዳት እንዳለባቸው ማወቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ችግረኞችን ለይተን ማወቅ ካልቻልን የሚለምኑ ሁሉ ችግረኞች እየመሰሉን ርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ነዳያን ተገቢውን ርዳታ ላናደርግላቸው እንችላለን፡፡ ለዚህም መስፈርት አድርገን የምናስቀምጣቸው መሠረታዊ ነገሮች ምግብ፣ አልባሳትና መጠለያ ያልተሟላላቸውን ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የጤና እክል ያለባቸው፣ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ የተያዙና ባለባቸው ችግር የተነሣ ሠርተው መብላት ያልቻሉ፣ አልባሽ አጉራሽ ቤተሰብም ሆነ ዘመድ የሌላቸውንም ችግረኞች እንላቸዋለን፡፡ በተጓዳኝ ረዳት ያጡ፣ ጠዋሪና ቀባሪ የሌላቸው አረጋውያን፣ ወላጅ አልባ ሕፃናት፣ በተለያዩ ምክንያቶች ቤት ንብረታቸውን አጥተው ከቀዬያቸው የተፈናቀሉትንም መርዳት ያስፈልጋል፡፡

ነዳያንን መርዳት በእግዚአብሔር ዘንድ ሰማያዊ ዋጋ ከማስገኘቱም በላይ ምድራዊ ሀብትና በረከትም ያስገኛል፤ በመጽሐፍ ቅዱስም ‹‹ስጡ ይሰጣችሁማል፤ በምትሠፍሩበት መስፈሪያ ተመልሶ ይሠፈርላችኋልና›› ተብሎ እንደተጻፈ ለችግረኞች የሚመጸውት ሰው በምድርም በሰማይም ዋጋውን ከእግዚአብሔር ያገኛል፡፡ (ሉቃ.፮፥፴፰)

ከዚህም ጋር ተያይዞ መስጠት ለሰዎች ደስታን ይሰጣል፤ ነገር ግን አብዛኛዎቻችን ደስታ ከመቀበል ወይም ከማግኘት ብቻ የሚገኝ ይመስለናል፡፡  ‹‹ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፁዕ ነው››  እንዲል፤ (ሐዋ.፳፥፴፭)

ባለጸጎች ሠርተው መኖር ለሚችሉት ወይም ብድራትን ለሚመልሱ ከመርዳት ይልቅ ምንም ሌላቸው ምስኪኖች ቢረዱ ደስታና ክብርን ያገኛሉ፡፡ ስለዚህም በቅዱስ ሉቃስ ‹‹ግብዣ በምታደርግበት ጊዜ ድሆችን፥ጦም አዳሪዎችን አካል ጉዳተኞችን ጥራ፤ የሚመልሱት ብድራት የላቸውምና ብፁዕ ትሆናለህ፤ በጻድቃን ትንሣኤ ይመልሱልሃልና›› የሚል ተጽፎ እናገኛለን፡፡ (ሉቃ. ፲፬፥፲፫)

ነዳያንም ለችግራቸው የሚደርስላቸው እንደሌለ በሚያስቡበት ወቅት ተስፋ በመቁረጥ ወደ ሕገ ወጥ ልመናና ከዚያም አልፈው ወደ ስርቆት ሊገቡ ይችላሉ፤ ልመና እንደ ገቢ ማመንጫ በሚቆጠርበት በዚህ ወቅት መረዳት ያለባቸውን ነዳያንን ለይተን አስፈላጊውን ርዳታ ካላደረግን ልፋታችን ከንቱ ከመሆኑም በተጨማሪ በጎ ምግባር ብለን ያሰብነው እርምጃችን ተገቢ ላልሆነ ተግባር ይውልብናል፡፡ ከእንደዚህ ዓይነቱ ተግባር ለመታደግ ችግረኞችን የመለየት ኃላፊነት የእኛ እንደሆነ አምነን ልንቀበል ይገባል፡፡

ርዳታችንን በተገቢውም መንገድ ለማከናወንም በቀዳሚነት ችግረኞችን የመለየቱን ተግባር አስቀድመን ከዚያም አስፈላጊውን ርዳታ ልናደርግላቸው ይገባል፤ ይህም ሲባል አካል ጉዳት ያለባቸውን ሙሉ አካል ከሆኑት፣ ሠርተው መኖር የሚችሉትን ከማይችሉት፣ በተለያዩ በሽታና ደዌ የተያዙትን በመለየት የሚያስፈልጋቸውንም ርዳታ በመረዳት የምንችለውን ማድረግ እንዲሁም እነርሱን መርዳት ለሚፈልጉ ባለጸጎችም ወይም ተቋማት በማገናኛነት እንዲረዱ ማድረግ ይቻላል፡፡

አምላካችን እግዚአብሔርም ‹‹ድኃና ችግረኛ የሆነውን ምንደኛ ከወንድሞችህ ወይም በምድርህ በሀገርህ ደጅ ውስጥ ከሚቀመጡት መጻኞች ቢሆን አታስጨንቀው›› ብሎ እንደተናገረው የእነርሱን ችግር በመረዳት መፍትሔ ልንሰጣቸው ይገባል እንጂ ወደ አልተገባ መንገድ እንዲሄዱ መንሥኤ ልንሆን አይገባም፡፡ የእነርሱ መቸገርና ወንጀል መፈጸም የእኛም ድክመትና ስሕተት መሆኑን በመረዳት ተጠያቂ ለሚያደርጉን ተግባራትም በሙሉ ኃላፊነት መውሰድ አለብን፡፡ ምክንያቱም ችግረኞቹ የሚረዳቸው በማጣታቸው የተነሣ የእነርሱ ወንበደኝነት ስርቆትንና ወንጀልን በማስፋፋቱ የማኅበራዊና ልማታዊ ቀውስ አስከትሏል፡፡ ከዚህም ባሻገር ተግባሩም በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ መሆኑን በቀዳሚነት መዘንጋት የለብንም፡፡(ዘዳ.፳፬፥፲፬)

የአካል ጉድለት የሌለባቸው ችግረኞች ሠርተው መኖር ያለመቻላቸው የማኅበረሰቡም ኃላፊነት በመሆኑ እነርሱን መርዳት ከእኛ ይጠበቃል፤ በሌላ በኩል ደግሞ አልፎ አልፎ የአካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች እንኳን ሠርተው የዕለት ጉርሻቸውን ለሟሟላት የቻሉም ስለመኖራቸው የታወቀ ነው፡፡ ስለዚህም ልመናን እንደ ቀዳሚ አማራጭ መጠቀም የለብንም፡፡ በጉልበታቸውም ሆነ በሞያቸው እንዲሁም ዕውቀታቸው ሀገሪቱንና ማኅበረሰቡን ሊረዱ የሚችሉ ብዙ ድብቅ ሀብቶች ሊኖሩ ይችላሉና ቸል አንበል፡፡ በተለይም በክርስቶስ ክርስቲያን የተባልን የእግዚአብሔር ልጆች በፍቅር አንድ እንድንሆን ካለን ነገር ሁሉ ለሌለው ልናካፍልና ችግረኞችን ልንረዳ ይገባል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር