‹‹ለምን ትመታኛለህ?›› – ካለፈው የቀጠለ

በዲያቆን ሄኖክ ኃይሌ

ሚያዝያ ፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

ጌታችን መጻጕዕን ‹‹ተነሣና አልጋህን ተሸክመህ ሒድ›› ብሎ ሲነግረው ወዲውኑ ድኖ አልጋውን ተሸክሞ ሔደ፡፡ ከዚህ ላይ አባታችን ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳለው የዚህን በሽተኛ እምነት እናደንቃለን፡፡ ራሱን መሸከም የማይችለው መጻጕዕ ‹‹ተነሣና አልጋህን ተሸከም›› ሲባል አልሳቀም፡፡ ‹‹እንዴት አድርጌ ነው ደግሞ አልጋ የምሸከመው?›› ብሎ አልጠየቀም፡፡ በፍጹም እምነት ተነሣና ተሸክሞ ሔደ፡፡ የሠላሳ ስምንት ዓመት ጓደኛውን፣ ሰው ሳይኖረው አብራው የኖረችውን፣ የተሸከመችውን ባለ ውለታ የኾነችዋን አልጋ ተሸከማት አለው – ተሸክሞ ሔደ፡፡

አንድ ሰው እንኳን ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ይቅርና ለሠላሳ ስምንት ቀናት እንኳን ቢታመም እንደ ተሻለው ተነሥቶ አልጋ አይሸከምም፡፡ እስከሚያገግም ድረስ በደንብ መንቀሳቀስ አይችልም፡፡ ራሱን ያዞረዋል፤ ይደክመዋል፡፡ የቀረ ሕመም አያጣውም፡፡ መጻጕዕ ግን የተፈወሰው ያለ ተረፈ ደዌ (ያለ ቀሪ በሽታ) ነበር፡፡ ጌታችንም ወዲያው ተነሥቶ አልጋውን እንዲሸከም አዘዘው፡፡ መምህር ኤስድሮስ እንደ ተረጐሙት መጻጕዕ የብረት አልጋውን ተሸክሞ እየሔደ የጌታን ጽንዐ ተአምራት አሳየ፡፡

ጌታችንም ከዚያ በሽታ ያዳነው በነጻ መኾኑን በሚያሳይ ኹኔታ ያችን አንዲት ንብረቱንም ‹‹ተሸክመህ ሒድ›› አለው፡፡ መጻጕዕ የተሸከመችህን አልጋ ተሸከም ተባለ፡፡ እግዚአብሔር የተሸከሙንን እንድንሸከም የሚፈልግ አምላክ ነው፡፡ ውለታ ሳንረሳ የተሸከሙንን ወላጆቻችንን የተሸከመችንን ቤተ ክርስቲያንን፣ የተሸከመችንን አገራችንን እንድንሸከም ይፈልጋል፡፡ አንድ ሊቅም ‹‹ዓለም እንደዚህ ናት፤ እናት ዓለም አልጋ መጻጕዕን ‹እንደ ተሸከምሁህ ተሸከመኝ› አለችው›› ሲሉ አመሥጥረውታል (ዝክረ ሊቃውንት 2)፡፡

ከዚህ ላይ ጌታችን ቤተ ሳይዳ ከመጣ አይቀር ዅሉንም በሽተኞች መፈወስ ሲችል ለምን አንዱን ብቻ ፈውሶ መሔዱ ጥያቄ ሊኾንብን ይችላል፡፡ ጥያቄ የሚያስነሣው ሌላው ጉዳይ ደግሞ ሊቃውንቱ እንደ ጻፉት የቤተ ሳይዳው መጠመቂያ ፈውስ ከዚያ በኋላ ብዙም አለመቆየቱ ነው፡፡ የመልአኩም መውረድ ቆሞአል፡፡ ከዚያ በኋላ በሰባ ዓመተ ምሕረትም ኢየሩሳሌም መቅደስዋ ፈርሶአል፤ ተመሰቃቅላለች፡፡ ወንጌላዊው ዮሐንስም ‹‹በኢየሩሳሌምም በበጎች በር አጠገብ በዕብራይስጥ ‹ቤተ ሳይዳ› የምትባል አንዲት መጠመቂያ ነበረች፤ አምስትም መመላለሻ ነበረባት፤›› ብሎ በኃላፊ ጊዜ ግስ (past perfect tense) ነው የተናገረላት (ዮሐ. ፭፥፪)፡፡

ታዲያ ጌታችን እንዲህ መኾኑን እያወቀ ምነው መጻጕዕን ብቻ ፈውሶት ሔደ? ቢባል የፈወሰው እርሱን ብቻ አይደለም፡፡ እርሱን በሥጋ ቢፈውሰውም ተአምራቱን አይተው በማመናቸው በነፍሳቸው የተፈወሱ ይበዛሉ፡፡ ‹‹ሕሙማነ ሥጋን በተአምራት ሕሙማነ ነፍስን በትምህርት እየፈወሰ›› እንዲሉ አበው፡፡ በዚያ ሥፍራ በሥጋ ታመው በነፍሳቸው አምነው የዳኑ ብዙዎች ናቸው፡፡ የጌታችንና የእርሱ አካል የኾነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዋነኛ ሥራዋ ነፍስን መፈወስ እንጂ ሥጋዊ በሽታን መፈወስ ብቻ አይደለም፡፡ ለዚህ ነው እንጂ ጌታችን ሰው ኾኖ ይህችን ምድር በእግሩ ሲረግጥ በሽታ እንዳይኖር ያደርግ የነበረው፡፡

ቅዱስ ባስልዮስ ‹‹በመስቀል ላይ በቈሰልኸው ቍስል ከኃጢአቴ ቍስል አድነኝ›› ብሎ እንደ ጸለየ እኛም የዘወትር ልመናችን ለሚከፋው ለነፍሳችን በሽታ ነው፡፡ የጌታችን ወደ ምድር መምጣት ዋነኛ ዓላማም ለነፍሳችን ድኅነትን ለመስጠት ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ለሥጋ አልመጣም ማለት አይደለም፡፡ ጌታችን ‹‹ኃጢአተኞችን ለንስሐ ልጠራ መጣሁ እንጂ ጻድቃን ልጠራ አልመጣሁም … ከእስራኤል ቤት በቀር ለአሕዛብ አልተላክሁም›› ሲል መናገሩ ለጻድቃን አይገደኝም፤ ለአሕዛብ አላስብም ለማለት እንዳልኾነ ዅሉ፣ ለነፍስ ድኅነት ቅድሚያ ሰጥቶአል ማለትም ለሥጋ አይገደውም ማለት አይደለም፡፡

በመጻጕዕ ታሪክ ውስጥ የምንማራቸው ብዙ ነጥቦች ቢኖሩም ሁለት ነገሮችን ብቻ እናንሣና ይህችን አጭር ጽሑፍ እንግታ፤ ይህ ሰው ተፈውሶ አልጋውን ተሸክሞ ሲሔድ ሰንበት ለሰው ድኅነት እንደ ተፈጠረች ያልተረዱ አይሁድ በቍጣ ነደዱ፡፡ ‹‹ሰንበት ነው፤ አልጋህን ልትሸከም አልተፈቀደልህም፤›› አሉት፡፡ አስተውሉ! ይህ ሰው በቤተ ሳይዳ ሠላሳ ስምንት ዓመታት ሙሉ ሲማቅቅ እንደኖረ የሰውን ገመና አዋቂ ነን ባዮቹ አይሁድ ይቅሩና ቤተ ሳይዳን የረገጠ ሰው ዅሉ ያውቃል፡፡ ለሠላሳ ስምንት ዓመታት ወደዚያች የመጠመቂያ ሥፍራ ሲሔዱ፣ ያም ባይኾን በጎች ታጥበው ተመርጠው በሚገቡበት የበጎች በር ሲያልፉ ይህን በሽተኛ በአልጋው ተጣብቆ ሳያዩት አይቀሩም፡፡

አሁን ግን ከአልጋው ተነሥቶ የተሸከመችውን አልጋ ተሸክሞ በአደባባይ ሲያዩት የጠየቁትን ጥያቄ ተመልከቱ፤ ‹‹እንኳን ለዚህ አበቃህ! ዛሬ የእግዚአብሔር መልአክ ወደ ውኃው ወረደ ማለት ነው? እሰይ ልፋትህን ቈጠረልህ!›› ያለው ሰው የለም፡፡ የተናገሩት አንድ ዐረፍተ ነገር ብቻ ነው፤ ‹‹ሰንበት ነው አልጋህን ልትሸከም አልተፈቀደልህም›› የሚል ብቻ፡፡ በአይሁድ ዘንድ መጻጕዕ ድኖ ሠላሳ ስምንት ዓመት የተኛበትን አልጋ ተሸክሞ ከመሔዱ ይልቅ ሰንበትን መሻሩ የሚያስደንቅ ትልቅ ዜና ነው፡፡ መጻጕዕም ‹‹ያዳነኝ ያ ሰው አልጋህን ተሸከም አለኝ›› አላቸው፡፡ እነርሱም ‹‹አልጋህን ተሸክመህ ሒድ ያለህ ሰው ማን ነው?›› ብለው ጠየቁት፡፡ እነዚህ ሰዎች ይህን በሽተኛ ፈጽሞ አያውቁትም ነበር ቢባል ‹‹ያዳነኝ ሰው›› ሲላቸው ‹‹ከምንድን ነው የምትድነው? ምን ኾነህ ነበር? ከየት ነው የመጣኸው?›› ይሉ ነበር፡፡

ነገር ግን መዳኑን ማየት አልፈለጉም እንጂ ማን እንደ ኾነ ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ እስኪ ጥያቄና መልሱ ውስጥ ያለውን ሽሽት እንመልከት፤ ‹‹ያዳነኝ ሰው አልጋህን ተሸከም አለኝ›› ለሚለው ምላሽ ተከታዩ ጥያቄ ‹‹ማን ነው ያዳነህ?›› የሚል መኾን ነበረበት፡፡ እነርሱ ግን የጌታን የማዳን ሥራ ላለመስማት ጆሮአቸውን ደፍነው ‹‹አልጋህን ተሸከም ያለህ ማን ነው?›› አሉ፡፡ እንግዲህ የማዳኑን ሥራ እያዩ ከማመን ይልቅ መከራከር፣ ከማድነቅ ይልቅ የትችት ሰበብ መፈለግ ጌታን የሰቀሉ የአይሁድ ጠባይ ነው፡፡

የመጨረሻው ቁም ነገር መጻጕዕ ከዚህ በኋላ ወደ አይሁድ ሔዶ ጌታን መክሰሱና ለጌታ ሞት የመማከራቸው ምክንያት መኾኑ ነው፡፡ ይህ ሰው ‹‹ከዚህ የሚብስ እንዳይገጥምህ ደግመህ ኃጢአትን አትሥራ›› ብሎ ጌታ ቢያሳስበውም አልሰማም፡፡ ጌታ በተያዘበት በምሴተ ሐሙስ ለሊቀ ካህናቱ አግዞ ጌታችንን በጥፊ መታው፡፡ ጌታችንም ‹‹ክፉ ተናግሬ እንደ ኾነ ስለ ክፉ መስክር፤ መልካም ተናግሬ ከኾነ ግን ስለምን ትመታኛለህ?›› አለው (ዮሐ.፲፰፥፳፫)፡፡ ጌታችን ‹‹‹አልጋህን ተሸክመህ ሒድ› ከማለት በቀር ክፉ ቃል ተናግሬህ ከኾነ መስክርብኝ፤ የተናገርኩህ መልካም ኾኖ ሳለ ስለ ምን ትመታኛለህ?›› ማለቱ ነበር፡፡

በማግስቱ ያ ዅሉ ጅራፍና ግርፋት በጌታችን ላይ ሲደርስበት አንድም ጊዜ ‹‹ለምን ትመታኛለህ?›› ብሎ አልተናገረም፡፡ የመጻጕዕ ጥፊ ይህን ያህል ዘልቆ የተሰማው ለምንድር ነው? ለዚህም የመጀመሪያው ምክንያት ከቤተ ሳይዳ ከበጎች በር ጋር የተያያዘ ምሥጢር አለው፡፡ ጌታችን የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ ነው፡፡ በበጎች በር አልፎ የመጣውም ንጹሐ ባሕርይ እንደ ኾነ ለማስረዳት ነበር፡፡ ለዚህም ንጽሕናው ዋነኛው ምስክር ፈውስን የሰጠው ይህ በሽተኛ ነበር፤ እሱ ግን መታው፡፡ ‹‹በቤተ ሳይዳ ክፉ ቃል ተናግሬህ ከነበር መስክርብኝ›› ማለቱ ‹‹ነውር የሌለብኝ፣ ለመሥዋዕት የተዘጋጀሁ በግ ነኝ ለምን ትመታኛለህ?›› ሲል ነው፡፡ ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ከሮማውያን ግርፋት በላይ ለጌታ ዘልቆ የሚሰማው ባዳነው ሰው መመታቱ ስለ ኾነ ነው፡፡

ውድ አንባብያን! መጻጕዕ ከሠላሳ ስምንት ዓመታት በሽታ ብቻ ዳነ፤ እኛ ግን የዳንነው ከአምስት ሺህ አምስት መቶ ዓመታት በሽታ ነው፡፡ ጌታችን እኛን ያስነሣን ከሲኦል አልጋ ነው፡፡ በሰሙነ ሕማማት ያን ዅሉ መከራ ዝም ብሎ የተቀበለ ጌታ መጻጕዕ በጥፊ በመታው ጊዜ ግን ‹‹ለምን ትመታኛለህ?›› ሲል ጠየቆታል፡፡ ከሌላው ሰው ይልቅ የእኛ ከዘለዓለም ሞት ያዳነን ክርስቲያኖች ዱላ ለእግዚአብሔር ይሰማዋልና፡፡ ይህም ዱላ ኃጢአታችን ነው፡፡ እናም እግዚአብሔር ዛሬም ድረስ እያንዳንዳችንን ይጠይቀናል – ‹‹ለምን ትመታኛለህ?›› እያለ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡