አስደናቂው የድንግል ማርያም ሞትና ትንሣኤ
ነሐሴ ፲፭ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም
በዲያቆን ታደለ ፈንታው
በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ የጌታ ልደቱና ጥምቀቱ፣ ሞቱ፣ ትንሣኤው፣ ዕርገቱና ዳግመኛ መምጣቱ በነገረ ድኅነት ትምህርታችን እጅግ ጠቃሚ የኾኑ ምሥጢራት ናቸው፡፡ ቤተልሔም የሥጋዌውን ምሥጢር ሲያሳይ ዮርዳኖስ ቀዳማዊ ልደቱን ያሳያል፡፡ የመጀመርያው የእኛ ባሕርይ ሲኾን ሁለተኛው የጌታ የራሱ የባሕርይ ገንዘቡ የኾነ ነው፡፡ እርሱ የሰው ልጅ ኾነ፤ እኛ ደግሞ የእግዚአብሔር ልጆች ኾንን፡፡ ይህ ኹሉ የተደረገው ከድንግል ማርያም በነሳው ሥጋ ነው፡፡ እርሱ የእኛን ተፈጠሮ ገንዘቡ ስላደረገ፤ እኛ ደግሞ የእርሱን ቅድስና ገንዘብ በማድረግ የመንግሥቱ ተካፋዮች ለመኾን በቃን፡፡ በእርሷ ምክንያት የእኛ የኾነው ኹሉ የእግዚአብሔር፤ የእግዚአብሔር የኾነው የእኛ ኾኗል፡፡ ስለዚህም እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ እናደርገዋለን፤ ለዚህ ክብር በቅታ ያከበረችንን፣ ከእግዚአብሔር ጋር ያዛመደችንን እመቤታችንንም እናከብራታለን፡፡
እርስዋ ከኪሩቤል ትበልጣለች፤ ከሱራፌልም ትከብራለች፡፡ ጌታችን የሱራፌልን፣ የኪሩቤልን ባሕርይ ባሕርዩ አላደረገም፡፡ የመላእክትንም ባሕርይ እንደዚሁ፤ የእርሷን አካል ባሕርዩ አደረገ እንጂ፡፡ የእኛ መንፈሳዊ ልደት የተገኘው ጌታ በሥጋ ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደው ልደት ነው፡፡ የቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን አምላክና የሰው ልጆች የተገናኙበት፤ አምላክና ሰው የተዋሐዱበት መካነ ምሕረት ነው፡፡ እግዚአብሔር ዙፋኑን ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀናት የዘረጋበት መካነ ሰላም ነው፡፡ የእግዚአብሔር ዙፋን ፍጹም በማይናወጥና ጸጥታ በነገሠበት ሥፍራ የሚዘረጋ የክብር ዙፋን ነው፡፡ ይህም ዙፋን የቅድስት ድንግል ማርያም ማኅፀን ነው፡፡
ድንግል ማርያም በአባት በእናቷ ቤት ሦስት ዓመት፤ በቤተ መቅደስ ዐሥራ ሁለት ዓመት፤ ከልጇ ጋር ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር፤ ከጌታችን ስቅለት በኋላ ደግሞ ዐሥራ አምስት ዓመታት በምድር ኖራለች፡፡ ጌታን የፀነሰችበትን ወራት ስንጨምር በዚህ ዓለም በሥጋ የቆየችበት ጊዜ ስድሳ አራት ዓመት ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ አርጋኖን ድርሰቱ ‹‹ከሚያሰጥመው ባሕር ሞገድ የተነሣ የማትነቀነቅ፣ መልኅቆቿም በሦስቱ ሥላሴ ገመድ የተሸረቡ ናቸው ይህቺ ደግሞ ከነፋሳት ኃይል የተነሣ የማትናወጥ በጭንጫ ላይ ያለች የዕንቈ ባሕርይ ምሰሶ ናት፤ እርሷን የተጠጋ መውደቅ መሰናከል የለበትም›› የሚላት እመቤታችን ሞት አይቀርምና እርሷም እንደሰው የምትሞትበት ጊዜ ደርሶ ጥር ሃያ አንድ ቀን ከዚህ ዓለም ውጣ ውረድ ዐርፋለች፡፡ እግዚአብሔር አያደላምና /ሮሜ.፪፥፲፩/፡፡
ቅድስት ድንግል ማርያም የኃያሉ እግዚአብሔር እናቱ፣ መቅደሱ፣ ታቦቱ፣ መንበሩ ኾና እያለ ሞትን መቅመሷ በራሱ የሚያስገርም ምሥጢር ነው፡፡ የዚህ ከኅሊናት ኹሉ በላይ የኾነው የእመቤታችን ዕረፍትም እንዲህ ተብሎ ተገልጿል፤ ‹‹ለምንት ይዜኃር ኃያል በኃይሉ ወባዕል በብዝኃ ብዕሉ ኢያድለወ ሞተ ክርስቶስ ለሥጋ አባሉ ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኵሉ፡፡ ኃይለኛ በኃይሉ ለምን ይታጀራል? ባለ ጸጋም በሀብቱ ብዛት፡፡ ክርስቶስ ለአካሉ አላደላም፡፡ ሞትስ ለሟች ይገባዋል፤ የእመቤታችን የቅድስት ማርያም ሞት ግን አስደናቂ ነው›› /መጽሐፈ ዚቅ/፡፡
ጠቢቡ ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ ‹‹ወዳጄ ሆይ ተነሺ፤ ውበቴ ሆይ ነይ፡፡ እነሆ ክረምት አለፈ፤ ዝናሙም አልፎ ሔደ፡፡ አበቦች በምድር ላይ ተገለጡ፤ የዜማም ጊዜ ደረሰ፡፡ የቍርዬም ቃል በምድር ላይ ተሰማ፤›› /መኃ.፪፥፲-፲፬/፡፡ ይህ ትንቢት የዚህ ዓለም ድካሟ ኹሉ መፈጸሙን ያስረዳል፡፡ ልጇን ይዛ ከአገር ወደ አገር በረሀብና ጥም የተንከራተተችበት ጊዜ አሁን አለፈ፡፡ ታናሽ ብላቴና ሳለች ልጇን አዝላ በግብጽ በረሃ የተቀበለችው መከራ ኹሉ ፍጻሜ አገኘ፡፡ ከእግረ መስቀል ሥር ወድቃ የልጇን የቈሰለ ገላ እየተመለከተች የደረሰባት ልብ የሚሰነጥቅ ኀዘን ወደ ደስታ ተለወጠ፡፡ ‹‹በነፍሷ ሰይፍ ያልፋል›› ተብሎ የተነገረው ልብ የሚሰነጥቅ መከራ እንደ ነቢዩ ቃል ትንቢት የሚቀጥልበት ጊዜ ተፈጸመ፡፡
የቤተ ክርስቲያን ትውፊት የድንግል ማርያም ሞት በሚከተሉት ምክንያቶች እንደ ኾነ ያስረዳል፤ የመጀመሪያው ‹‹ለመለኮት ማደርያ ለመኾን የበቃችው ኃይል አርያማዊት ብትኾን ነው እንጂ እንደ ምድራዊት ሴትማ እንደምን ሰማይና ምድር የማይችለውን አምላክ ልትሸከመው ይቻላታል?›› የሚሉ ወገኖች ነበሩና እግዚአብሔር ወልድ የተዋሐደው የሰው ልጆችን ሥጋ መኾኑን ለማጠየቅ ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲያስረዳ ‹‹እንግዲህ ልጆቹ በሥጋና በደም ስለሚካፈሉ፣ እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር፣ ይኸውም ዲያብሎስ ነው፡፡ በሕይወታቸው ኹሉ ስለሞት ፍርሃት በባርነት ይታሠሩ የነበሩትን ኹሉ ነጻ እንዲያወጣ፣ በሥጋና በደም እንዲሁ ተካፈለ፡፡ የአብርሃምን ዘር ይዟል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም›› አለ /ዕብ.፪፥፲፬-፲፭/፡፡ በዚህም ድንግል ማርያም የአዳም ዘር መኾኗ ታወቀ፡፡ ሁለተኛው ቅዱስ ያሬድ እንደተናገረው ጌታችን በፍርዱ አድልዎ የሌለበት መኾኑ ይታወቅ ዘንድ ነው፡፡ ሥጋ የለበሰ ኹሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ የግድ ነውና፡፡
እመቤታችን ባረፈች ጊዜ ሐዋርያት ሊቀብሯት ሲሹም ከአይሁድ ክፋት የተነሣ ልጇ ሌላ ክብርን ደረበላት፡፡ ከጌቴሴማኒ ሥጋዋ ተነጥቆ በገነት በዕፀ ሕይወት ሥር እስከ ነሐሴ ዐሥራ ስድስት ቀን ለሁለት መቶ አምስት ቀናት ቆይታለች፡፡ ልጇ ወዳጇ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን በሥልጣኑ እንዳሸነፈ የልጇ መለኮታዊ ኃይል ሞትን አሸንፋ እንድትነሣ አደረጋት፡፡ ጠቢቡ ሰሎሞን ስለ ትንሣኤዋ የተናገረው ቃል ተፈጸመ፡፡ ሊቁ ‹‹ለዛቲ ብእሲት ሠረቀ ላዕሌሃ ብዕለ ጸጋሁ ለአብ ወአግዓዛ እምእኩይ ውስተ ሠናይ እሞት ውስተ ሕይወት፤ በድንግል ማርያም ላይ የአብ የባለጸግነቱ ብዛት ተገለጠ፡፡ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከክፉ ዓለም ወደ በጎ ዓለም አሸጋግሯታልና›› ሲል የተነጋረውም ይኼንን ምሥጢር የሚገልጽ ነው፡፡
ለአምላካችን ለልዑል እግዚአብሔር ክብር ምስጋና ይግባውና ከሞት ወጥመድ በላይ እንኳን የኾነ ሌላ ኃይል አለ፤ ይኼውም ሞት ፈጽሞ ሊያሸንፈውና ሊገዳደረው የማይችል የእግዚአብሔር መለኮታዊ ኃይል ነው፡፡ ሕያው የኾነው እግዚአብሔር የሕያዋን አምላክ ነውና ሞት ሊያሸንፈው፣ ሊደርስበትም የማይችለውን ሕይወት ይሰጣል፡፡ ይህንን እርሱ የሚሰጠውን ሕይወት ሰይጣን በእጁ ሊነካው ከቶውንም አይችልም፡፡ ከሞት ሥልጣንና ኃይል በላይ የኾነው ይኸው የእግዚአብሔር መለኮታዊ ሥልጣን የድንግል ማርያምን ሥጋ ለፍርድ እስከሚመጣበት ጊዜ ድረስ በመቃብር ውስጥ ተጠብቆ እንዲቆይ፤ ፈርሶና በስብሶ በምድር ላይ እንዲቀር አላደረገም፡፡ ከሙታን መካከል ተለይታ ተነሥታለች፡፡ እንድትነሣም ያደረገ የእግዚአብሔር ኃይል ነው እንጂ በራሷ ሥልጣን የተነሣች አይደለችም፡፡ መንፈስ ቅዱስ በድንግልና ፀንሳ በድንግልና መውለዷን በትንቢት እንዳናገረ ትንሣኤዋንም በትንቢት ሲያናግር ኖሯልና ይህ ታላቅ ምሥጢር በቅዱስ ዳዊት አንደበት ‹‹ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ አንተ ወታቦተ መቅደስከ፤ አቤቱ ወደ ዕረፍትህ ተነሥ፤ አንተና የመቅደስህ ታቦትም›› ተብሎ ተገልጿል /መዝ.፻፴፩፥፰/፡፡
ቅዱስ ዳዊት በዚህ የትንቢት ክፍል ትንሣኤዋን አስረድቷል፡፡ ታቦት የጽላቱ ማደሪያ ነው፡፡ በታቦቱ ውስጥ የሚያድረው በእግዚአብሔር ጣቶች የተጻፈው ሕጉ ነው፡፡ ይህ እግዚአብሔር ያከበረው ነገር ኾኖ ሊመጣ ላለው ነገር ማሳያ ነው፡፡ እውነተኛዋ ታቦት ማርያም ናት፡፡ ሙሴ በተቀበለው ታቦት ውስጥ ያለው ጽላት በውስጡ የያዘው ሕጉን ነው፤ በድንግል ማርያም ላይ ያደረው ግን የሕጉ ባለቤት ነውና፡፡ ከፍጡራን ከፍ ከፍ የማለቷ ድንቅ ምሥጢርም ይህ ነውና፡፡ የእመቤታችን ትምክህቷም፣ ትውክልቷም ጌታ እግዚአብሔር እንደ ኾነ ወንጌላውያኑ በመንፈስ ቅዱስ ተቃኝተው መስክረውላታል፡፡ እርሷም ‹‹ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች፤ መንፈሴም በአምላኬ፣ በመድኃኒቴ ሐሤትን ታደርጋለች›› በማለት ተናግራለች /ሉቃ.፩፥፵፯/፡፡
እመቤታችን ባለችበት ሥፍራ የሕይወት ትንሣኤ ያላቸው ሰዎች ይኾኑ ዘንድ አስቀድማ ከሙታን ተለይታ በመነሣት የተጠበቀልን ተስፋ ማሳያ ኾነችን፡፡ ከእንግዲህ በኋላ ልጇ ሲንገላታ፣ ሲሰደድ፣ ሲገረፍ፣ ሲሰቀል፣ ሲቸነከር ያየችበት ዓለም አለፈ፡፡ አሁን የልጇን ልዕልና ከሚያደንቁ ጋር ታደንቃለች፤ ከፍ ከፍ ከሚያደርጉት ጋር ታከብረዋለች፡፡ ይኸውም ከገቡ የማይወጡበት፤ ኀዘን፣ መከራ፣ ችግር የሌለበት ሰማያዊ አገር ነው፡፡ በእግዚአብሔር መንግሥት ስደት፣ መከራ፣ ኀዘን፣ ሰቆቃ፣ መገፋት፣ መግፋትም የለም፡፡ ቅዱሳን ሩጫቸውን ጨርሰው የድል አክሊልን የሚቀዳጁበት ሥፍራ ነው፡፡ በዚህም ከፍጡራን ኹሉ ከፍ ባለ በታላቅ ክብርና ጸጋ ለዘለዓለም እንደምትኖር እናምናለን፡፡ ልመናዋ፣ ክብሯ፣ ፍቅሯ፣ አማላጅነቷ፣ የልጇም ቸርነት በኹላችን ላይ አድሮ ይኑር፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡
ምንጭ፡– ሐመር ፲፰ኛ ዓመት፣ ቍጥር ፭