በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናችኋለን ቆላ.1፥19

ጥር 9/2004 ዓ.ም

በዓላት ቤተ ክርስቲያን አገልግሎቷን ከምትፈጽምባቸው ሥርዓቶች መካከል እንደ አንዱ ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡ በበዓላት ምእመናን ረድኤት በረከት ከማግኘታቸው ባለፈ ቤተ ክርስቲያን የምትሰጣቸውን አገልግሎቶች የሚቀበሉባቸው መንፈሳዊ መድረኮች ናቸው፡፡ በበዓላቱ መምህራን ትምህርተ ወንጌልን ለምእመናን ያደርሳሉ፡፡ በበዓላት አከባበር ሥርዓት ውስጥ ምእመናን በቤታቸው፤ በአካባቢያቸውና በአደባባይ ሁሉም በጋራ በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነትና ጌትነት፣ ለሰውም ያደረገውን የማዳን ሥራ የሚመሰክሩበት፣ በቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ላይ ያላቸውን ጽናት ለየትኛውም ወገን ያለሀፍረት የሚገልጹበት የአገልግሎት ዕድል ነው፡፡

ጌታችን “በሰው ፊት የሚመሰክርልኝን እኔም በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ” /ሉቃ.12፥8/ ያለውን ቃሉን በማክበርና በመጠበቅ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በአዋጅና በአደባባይ የምታከብራቸው ማራኪ በዓላት አሏት፡፡ እነዚህ በዓላት በዓይነታቸው ሁሉንም የክርስቲያን ቤተሰብ በየመዓርጉ፣ በየጸጋው እንደየ አቅሙ የሚያሳትፉ በመሆናቸው ደማቅ ናቸው፡፡ በተለይ የጌታችን የመድኀኒትችን የኢየሱስ ክርስቶስን ሥራ፣ ተአምራትና የማዳን ነገር የሚዘክሩትን በዓላት /በዓለ ልደት፣ ጥምቀት፣ ስቅለት፣ ትንሣኤ፣ መስቀል/ ዐበይት ሆነው ይከበራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ የበዓላት ቀን ቀመር መሠረትም ብሔራዊ በዓላት እንዲሆኑ በሕግ ተመዝግበው የሚታወቁና ደምቀው የሚከበሩ ናቸው፡፡

እነዚህ ወንጌልን መሠረት ያደረጉ የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዐበይት በዓላት በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ውስጥና በምእመናን ልብ ከፍ ያለ ቦታ ተሰጥቷቸው መገኘቱ ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ሁሉ ለስብከተ ወንጌል የሰጠችውን የማያቋርጥ ትኩረት ይመሰክራል፡፡ ይህ ለቤተ ክርስቲያን ሕይወቷም አገልግሎቷም ነውና፡፡ እንዲህም ሆኖ እስከዚህ ዘመን ደርሷል፡፡

የዚህ ዘመን የቤተ ክርስቲያን ትውልድም እነዚህን ዐበይት የጌታችንን በዓላት ከጊዜ ጊዜ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የማክበር ዝንባሌው164149_1457139283455_1682564302_893573_395312_n እያደገ ነው፡፡ ወንጌል በተግባር እየተሰበከ ነው፡፡ ይህም መናፍቃን እኛን ኦርቶዶክሳውያንን ወንጌልን እንደማንሰብክ አድርገው በሚያሙበት ነገር የበለጠ እንዲያፍሩ አገልግሎቱም የበለጠ እንዲሰፋ አድርጓል፡፡ በተለይ በዓለ ጥምቀትን የመሰሉ የአደባባይ በዓላት በየጊዜው እየደመቁ በአከባበር ሥርዓታቸውም ከባህላዊ ይዘታቸው ይልቅ ፍጹም ሃይማኖታዊ መልክ እየያዙ እንዲመጡ እየተደረገ ነው፡፡ ወደፊትም እነዚህ በዓላት በቅዱስ ወንጌል ያለንን እምነት በሰዎች ሁሉ ፊት የምንሰብክባቸው ዓውደ ምሕረቶቻችን ሆነው ደምቀው መከበር እንዳለባቸው ማኅበረ ቅዱሳን የጸና አቋም አለው፡፡ ለዚህም ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም በቤቱና በአደባባይም ሁሉ በዚህ በረከት በሚገኝበት አገልግሎት መሳተፍ ይጠበቅበታል፡፡ በፍጹም ሰላም፣ ሃይማኖታዊ /መንፈሳዊ/ ፍቅር የጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሥራና ትምህርቱን፣ ሰውንም የወደደበትን ታላቅ ፍቅር፣ በሰው ሁሉ ፊት በመመስከር በደስታ እንዲያከብሩ ልናነሣሣቸው ይገባል፡፡

ወቅቱን የዋጀ አገልግሎት ከመስጠት አንጻር ደግሞ ከዚህ ቀደም ከነበረው አገልግሎታቸው በበለጠ ትጋት የሚፈለግባቸው ሊቃውንቱና ካህናቱ ናቸው፡፡ ሊቃውንቱና ካህናቱ የበዓላት አገልግሎታችን ሥርዓቱን ጠብቆ በቅልጥፍና እንዲካሔድ ሥምረትም እንዲኖረው ከምእመናን በኩል ያለውን ተነሣሽነት ያገናዘበ ተሳትፎ ልናደርግ ይገባል፡፡ ዞሮ ዞሮ የበዓሉ ማእከል በካህናቱ የሚሰጠው አገልግሎት በመሆኑ በየአጥቢያው ባሉ ማኅበረ ካህናት ምክክር ሊደረግበትም ይገባል፡፡ በበዓላቱ የምንሰጠውን የወንጌል አገልግሎት ሁሉ ምእመናን አውቀው በእምነት አሜን፣ በደስታም እልል እንዲሉ ተርጉመን ምስጢሩን ማስረዳት ይገባናል፡፡ የተቀደሰውን ቅዳሴ፣ የተቆመውን ቁመት፣ የተነበበውን ወንጌል፣ የተሰበከውን ምስባክ፣ የቀረበውን ወረብ ቃሉን ተርጉመን ምስጢሩን ተንትነን ስንነግራቸው የምእመናን ተሳትፎ ይጨምራል፡፡ የአገልግሎቱ ፍቅር የበለጠ ያድርባቸዋል፡፡

164149_1457139483460_1682564302_893577_6995263_nያነሣነውን ታቦት ክብርና ምስጢር፣ የጥምቀተ ባሕሩን ምንነት፣ በዚህም ላይ ቅድስት ወንጌል ያላትን ኀይል ማሳየት ይጠበቅብናል፡፡ ይህ ሲሆን ምእመናን ለካህናት አባቶች ያላቸው የልጅነት መንፈስ ካህናት አባቶችም ለምእመናን ያላቸው የአባትነት መንፈስ ይጨምራል፡፡ በፍቅርና በአገልግሎታችን የበለጠ ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እንስባቸዋለን፡፡ በዓላትን ለማየት ብቻ የሚታደሙ የውጭና የሀገር ውስጥ ተመልካቾችን ወደ ድኅነት እንጠራለን፡፡

በየበዓላቱ ጉባኤያትን በማዘጋጀት፣ በአደባባይ ዝማሬን በማቅረብ፣ ምእመናንን በመቀስቀስ ታላቅ ድርሻ ያላቸው ሰንበት ትምህርት ቤቶችም የበዓላት አገልግሎቱ ምሰሶና ማገር መሆናቸውን የበለጠ ሊጠብቁ ይገባል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በምታከብራቸው የጌታችን ዐበይት በዓላት ያለውን አጠቃላይ የምእመናንን ተሳትፎ የመምራት በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን መሠረትም ቅርጽ የያዘ እንዲሆን የበለጠ መትጋት ይጠበቅባቸዋል፡፡ የዝማሬያችን ጣዕም የአለባበሳችን ድምቀት፣ የዝማሬ ሥርዓታችን ስባት፣ በትሕትናና በፍቅር በመመላለሳችን፣ አንድነታችንና መተሳሰባችን በበዓላቱ ወንጌልን የምንሰብክበትን ክርስቲያናዊ አገልግሎት የበለጠ ያፈካዋል፡፡

ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያቱ በዓለሙ ሁሉ “ምስክሮቼ ትሆናላችሁ” /የሐ.ሥ.1፥9/ ያለውን ቃሉን እያሰብን የበዓላቱን መለከት ልንነፋ ይገባል፡፡ /2ሳሙ.6፥1/ በዓላቱን በማድመቅ ዋጋ እንደሚያገኙ በማመን የሚተጉ፣ እግዚአብሔር በጊዜው ጊዜ ያነሣሣቸውን የየአጥቢያውን ወጣቶችም ለአገልግሎታችን እንደተሰጠን እንደ አንድ ጸጋ ተቀብለን ልንጠቀምባቸው ይገባል፡፡

ምእመናንንም ከበዓላቱ ጋር ተያይዘው የሚዘወተሩ ሌሎች ደባል ሥጋዊ ክንውኖች ሳያዘናጓቸው ሃይማኖታዊ በዓላቱ ለወንጌል አገልግሎት ያላቸውን ድርሻ ማስጠበቅ ይገባቸዋል፡፡ በተለይም ባህላዊ ገጽታ ተላብሰው በበዓላቱ የጎንዮሽ የበቀሉ የሰይጣን ማዘናጊያዎችን ፈር ማስያዝ አለብን፡፡ በዓላችን ቅዱስ ወንጌልን የምንመሰክርበት ነው ካልን የትኛውም ዓይነት የሥጋ /የኀጢአት/ ሥራ ተደባልቆ እንዳይሠለጥንበት ደረጃ በደረጃ ከቤተሰቦቻችን ጀምረን በማስተማር ወደ ፍጹም ክርስቲያናዊ ባህል ማድረስ አለብን፡፡ በዓላቱ ለእግዚአብሔር የተቀደሱ ቀናት ናቸው፡፡ ስለዚህ በስካር፣ በዝሙት፣ በመዳራት፣ በዘፈን፣ በአምልኮ ባዕድ በማመንዘር፣ በጠብ በክርክር ወዘተ ሳይሆን እግዚአብሔርን ደስ በሚያሰኝ ፈሪሐ እግዚአብሔር ባለበት በትሑት መንፈስ በፍቅርና በደስታ በምስጋናም ማክበርን ጠብቀን ሌሎችንም ልናስተምር ይገባል፡፡

በበዓላቱ ሕፃናት፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞችም ያለ ምንም ችግር በበዓላቱ እንዲሳተፉ ምቹ ሁኔታ መፍጠርም ይገባል፡፡ በዓላት በባህሪያቸው ደስ ብሎን የምናመሰግንባቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም ምስኪኖችን በማጽናናት በመደገፍ ከበዓሉ የክርስቲያን ወገን የሚገኘውን ደስታ ሁሉ ተሳታፊ ሆነው አምላካችንን እንዲያመሰግኑ እናግዛቸው፡፡ በዓሉን የክርስቲያን ወገን የሚያገኘውን ደስታ ሁሉ ተሳታፊ ሆነው አምላካችንን እንዲያመሰግኑ እናግዛቸው፡፡ በዓሉን የክርስቲያን ወገን የሚያገኘውን ደስታ ሁሉ ተሳታፊ ሆነው አምላካችንን እንዲያመሰግኑ እናግዛቸው፡፡ በዓሉን ለመድኀኒታችን ክብር ለእኛም በረከት እንዲሆን ብለን እስከ ጠበቅነው ድረስ ታናናሾችን መቀበልና ማክበር እርሱን መቀበልና ማክበር መሆኑን የነገረንን ቃሉን ማሰብ ተገቢ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ሐዋርያው “በነገር ሁሉ ደስ ልታሰኙ ለጌታ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እንለምናችኋለን” እንዳለው በዓላት ማንንም ሳናሳዝን ለሁሉም ወገን ሐሴትን የምንሞላበት እንዲሆኑ ያስፈልጋል፡፡ ይህንንም ስናደርግ ጌታችን ደስ በሚሰኝበት የወንጌል ቃሉን በማሰብ፣ በመመስከር ሊሆን ይገባል እንላለን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፡- ሐመር 19ኛ ዓመት ቁጥር 8 ታኅሣሥ 2004 ዓ.ም