የ፳፻፲ ዓ.ም የጥቅምት ወር ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤን መጀመር አስመልክቶ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሰጡት ሙሉ ቃለ ምዕዳን 

ጥቅምት ፲፫ ቀን ፳፻፲ ዓ.ም

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ

መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ

አሐዱ አምላክ አሜን

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ወኤጲስ ቆጶሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

እግዚአብሔር አምላካችን በተለመደው ቸርነቱ ከየመንበረ ጵጵስናችን በሰላም አሰባስቦ በዚህ ዓቢይ ዓመታዊ ስብሰባ ተገኝተን ስለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አንድነት፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በስሙ እንድንመካከር ለፈቀደልን ለእርሱ ፍጹም ምስጋና ከአምልኮት ጋር እናቀርባለን፡፡

እናንተም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት እንኳን በደኅና መጣችሁ፤ እንኳንም ለዚህ ሐዋርያዊና ቀኖናዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ዓመታዊ ጉባኤ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!!

‹‹ወዘንተ ባህቱ አእምር ከመ በደኃሪ መዋዕል ይመጽኣ ዓመታት እኩያት ወይከውኑ ሰብእ መፍቀርያነ ርእሶሙ፤ ነገር ግን በኋኞቹ ዓመታት ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱበት ክፉ ዘመን እንደሚመጣ ዕወቅ›› (፪ ጢሞ ፫፥፩)

ይህ መልእክት ቅዱስ ጳውሎስ ለሚወደው ደቀመዝሙሩ ለጢሞቴዎስ ያስተላለፈው ምክር አዘል መልእክት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደሚታወቀው ዓይነቱ፣ ስልቱና መጠኑ ይለያይ እንደሆነ ነው እንጂ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከፈተና ተለይታ አታውቅም፤ ይሁን እንጂ ወደመጨረሻው ዘመን አካባቢ የሚሆነው መከራ ግን ከሁሉ የባሰ እንደሚሆን በቅዱሳት መጻሕፍት በተደጋጋሚ የተገለፀ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ቅዱስ ጳውሎስ ተማሪውን ጢሞቴዎስን ሊያስገነዝበው የፈለገው ነገር በመጨረሻ ዘመን የሚከሠተውን ፈተና ምእመናን አውቀው ጥንቃቄ ያደርጉ ዘንድ እንዲያስተምር ነው፡፡ ለወደፊት የሚሆውን ነገር አስቀድሞ የማሳወቅና ወዳጆቹን የማስጠበቅ ኩነት ከጥንት ጀምሮ የነበረ የእግዚአብሔር አሠራር ነው፡፡ በዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ለተከታዩ ትውልድ ስለመጨረሻው ዘመን ሁናቴ የማሳወቅ ሥራን ሲሠራ እናስተውላለን፡፡

በተጠቀሰው ክፍለ ምንባብ ላይ የመጨረሻው ዘመን ገጽታ ምን እንደሚመስል በዝርዝር ተገልጾአል፤ ይዘቱን ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው በመጨረሻው ዘመን አካባቢ ነገሩ ሁሉ የተመሰቃቀለ እንጂ አንዳች የሚያስደስት ነገር እንደሌለው ነው፤ በተለይም በጥቅሱ ላይ እንደሚታየው የመጨረሻው ዘመን “ሰዎች ከምንም በላይ ራሳቸውን የሚወዱበት ጊዜ” መሆኑ ተነግሮአል፤ ይህ ዓይነቱ አመለካከት ቃለ ቅዱስ ወንጌልን ሙሉ በሙሉ የሚጻረር ነው፡፡

ጌታችን ለተከታዮቹ ያስተማረው “የኔ ሊሆን የሚወድ ሁሉ ራሱን ይካድ” የሚል ነው፡፡ ይህም ማለት የኋለኛው ትውልድ ራስን የሚወድ ከሆነ፣ ጌታ የሚያዘው ደግሞ ራስን መውደድ ሳይሆን ራስን መካድ ከሆነ ነገሩ “ሆድና ጀርባ” ሆኖአል ማለት ነው፤ ከዚህ አንጻር የዘመናችን ክሥተት በዚህ ፈተና ላይ ያለ እንደሆነ በግልፅ ማየት ይቻላል፡፡

ዛሬ የመንፈስ እናታቸው ብቻ ሳትሆን የማንነታቸውና የታሪካቸው ጭምር ማኅደር ከሆነች እናት ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እያፈተለኩና እየኮበለሉ የሚገኙት በርካታ ወገኖች ራስን ከመውደድ የተነሣ ካልሆነ በቀር ሌላ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡ ክርስቶስ ሌላ አዲስ ክርስቲያን የፈጠረ ይመስል ክርስቲያን የሆነውን ሰው በተለያየ አባባል ወደሌላ የክርስቲያን ጎራ እንዲኮበልል መጣጣር አስኮብላዩም ኮብላዩም ራስን ከመውደድ የተነሣ የሚያደርጉት ነው እንጂ አንዳች የሚጨበጥ ክርስቲያናዊ ትርጉም የለውም፡፡

ራስን በመውደድ የሚታወቀው የዘመናችን ባህርየ ሰብእ በዚህ ብቻ ሳይወሰን በትምህርትም፣ በሐሳብም፣ በአስተያየትም፣ በሥራም፣ ወዘተ የሚገለጸው ራስን ከፍ ከፍ የማድረግና የኔ ከሁሉ ይበልጣል እያሉ ሌላውን የማንኳሰስ አባዜ የሃይማኖት መዓዛ ምግባርን እየበከለው ይገኛል፡፡ ከዚህም የተነሣ የእኔ አውቅልሃለሁ ባይነት ዝንባሌ ሥር እየሰደደ ትሕትናና ፈሪሀ እግዚአብሔር የራቀው ትውልድ እየተበራከተ ይገኛል፡፡

ዛሬ እንደትናንቱ አበው ባሉት እንመራ፣ እንታዘዝ፣ አበውን እናዳምጥ የሚል ትውልድ ሳይሆን ከእናንተ ይልቅ እኛ እናውቃለንና እኛ የምንላችሁን ተቀበሉ በማለት ወደ ላይ አንጋጦ የሚናገር፣ ራስ ወዳድ የሆነ፣ መታዘዝን የሚጠላ ከሃይማኖታዊነት ይልቅ አመክንዮዋዊነትን የሚያመልክ ትውልድ እየመጣ ነው፡፡ ይህ ራስ ወዳድ አስተሳሰብ የሚመነጨው ዘመኑ ያፈራው የሥነ ልቡና ፍልስፍና እንጂ፣ ራሱን በመንፈስ ደሀ አድርጎና ሌላው ከእሱ እንደሚሻል አድርጎ ከሚያስተምር፣ በመንፈሰ እግዚአብሔር ከተጻፈው ከቅዱስ መጽሐፍ የመነጨ አይደለም፡፡

ቤተ ክርስቲያን ደግሞ መመሪያዋ በመንፈሰ እግዚአብሔር የተጻፈ ቅዱስ መጽሐፍ እንጂ በሰዎች ውሱን ጥበብ የተቀነባበረ ሰው ሠራሽ ፍልስፍናና ዘመን አመጣሽ ስልት አይደለም፡፡ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን ስትጠብቀው የኖረች ለወደፊትም የምትጠብቀው በመንፈሰ እግዚአብሔር በታጀበ ጥበብና ስልት እንጂ ከፍልስፍና ብቻ የተገኘ የተውሶ ዕውቀት ሊሆን አይችልምና ሁሉም ሊያስብበት ይገባል፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ለሁለት ሺሕ ዓመታት ያህል በአንድነትና በጥንካሬ ጠብቆ ያቆየ ጥበብ ኦርቶዶክሳዊና ሲኖዶሳዊ የሆነ የውሉደ ክህነት አመራር ጥበብ እንጂ የምዕራባውያንና የሉተራውያን ምክር ቤታዊና ዘመን አመጣሽ ፍልስፍና አይደለም፡፡ የቤተ ክርስቲያናችን መርሕ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ዛሬ የምናያት አንዲት ሐዋርያዊትና ኃያል ቤተ ክርስቲያን ሳትሆን የተበታተነች የደከመችና መዓዛ ሐዋርያት የሌላትና የተለያት ቤተ ክርስቲያን ነበር የምናየው፡፡

ይሁን እንጂ አባቶቻችን ካህናት መሪዎች፣ ሕዝቡ ተመሪ ሆኖ በአንድ የእዝ ሰንሰለት እየተደማመጠ ካህኑ ተናገረ ማለት እግዚአብሔር ተናገረ ማለት ነው በሚል ቅንና ትሕትና የተመላ ታዛዥነት እንደዚሁም በውሉደ ክህነት አመራር ሰጪነት የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት እስከዛሬ ድረስ ተጠብቆ ቆይቷል፡፡

አሁን ግን ይህ ቀርቶ በአባቶች ላይ ተደራቢ አመራር ሰጪ፣ በአባቶች ላይ የስድብ ናዳ አውራጅ ትውልድ መበራከቱን ካየንና ከሰማን ውለን አድረናል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ከጎናችን ሳይሆኑ ከጎናችሁ አለን የሚሉ ወገኖችም ስለድርጊቱ አፍራሽነት በተመለከተ አንድ ቀንስንኳ የተቃውሞ ሐሳብ አለመሰንዘራቸው በስተጀርባው እነርሱራሳቸው ያሉበት እንደሆነ የሚያመላክት መስሎ አሳይቶባቸዋል፡፡

አሁን ዋናው ጥያቄ፣ ይህ ራስ ወዳድ አመለካከት ተቀብሎ የሚመጣውን ጥፋት ማስተናገድ ይሻላል? ወይስ ራስን መካድ የሚለውን የጌታ ትምህርት አሥርፆ ነገሮች ሁሉ በንሥሐ ወደነበሩበት መመለስ፣ ምርጫውን ለዚህ ዓቢይ ጉባኤ አቅርበነዋል፡፡

በሌላ በኩል ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተልእኮ በሚገባ ለማከናወን ግልፅነትንና ታማኝነትን በማረጋገጥ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ለነገ የማይባል የቤተ ክርስቲያናችን ዓቢይ አጀንዳ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ የቤተ ክርስቲያናችንን ዙሪያ መለስ ምጣኔ ሀብት በሚገባ ለመያዝና ለማሳደግ እንዲሁም የሰው ኃይላችንን በአግባቡ ለመጠቀም የዘመኑን አሠራር መከተል የግድ ያስፈልገናል፡፡

ሌላው በሀገራችን እየተመዘገበ ያለውን የልማትና የዕድገት ግንባታ በአስተማማኝ ለማስቀጠል የሕዝቡ አንድነትና ሰላም መረጋገጥ ወሳኝነት አለው፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን ከሆነ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም እናት ሆና ሕዝቡን በማስተማር ያስመዘገበችው ጉልህ ታሪክ ዛሬም ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ሁላችንም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ኃላፊነታችንን እንድንወጣ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም

ይህ ቅዱስ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንኳርና ዓበይት ጉዳዮችን በጥልቀት በመመርመርና በማጥናት ለቤተ ክርስቲያናችን ሊጠቅሙ የሚችሉ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ጉባኤው እንዲቀጥል እያሳሰብን እነሆ ዓመታዊው የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መከፈቱን በእግዚአብሔር ስም እናበስራለን፡፡

እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ፤ ይቀድስ፡፡

ሀገራችንንም ይባርክ፤ ይቀድስ፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡

አባ ማትያስ ቀዳማዊ፣

ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፣

ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት፣

ጥቅምት ፲፪ ቀን ፳፻ወ፲ ዓ.ም፤

አዲስ አበባ ኢትዮጵያ፡፡