የአባቶች አንድነት ላይ የተሰጠ  የደስታ መግለጫ!

       

ቅዱስ ቂርቆስና ቅድስት ኢየሉጣ ከእቶነ እሳት በወጡበት በብሥራተ መልአክ በቅዱስ ገብርኤል የመታሰቢያ ዕለት የኢትዮጵያ አርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  አባቶች  አንድ ሆነዋል፡፡በዚህም የምእመናን ተስፋ ለምልሟል፡፡የጥል ግድግዳ ፈርሷል፡፡ይህ ታላቅ መንፈሳዊ ተግባር የተፈጸመበት ዕለት ለቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ የደስታ ዕለት ነው፡፡ይህ ዕለት ሰይጣን ቤተ ክርስቲያንን ለመዋጋት ጥይቱን የጨረሰበት፤ዝናሩን አራግፎ ባዶ እጁን የቀረበት ነው፡፡ዕለቱ የሰይጣን ጥርሱ የረገፈበትና የቤተ ክርስቲያን ብርሃን ለዓለም የተገለጠበት በመሆኑ የቤተ ክርስቲያን የምስራች ቀን ነው፡፡

ለዚህ ዕለት ደርሶ የተገኘውን ዕርቅ አይቶ የማይደሰት ቢኖር ዲያብሎስ ብቻ ነው፡፡ዕርቁ እውን እንዲሆን መለያየት እንዲወገድ፤የተፈጠረው ክፍተት መፍትሔ እንዲያገኝ ያደረገ እግዚአብሔር ይመስገን በማለት በቅን ልቡና የተቀበላችሁ ቅዱሳን ፓትርያርኮቻችን የፈረሰውን አንድነት በዘመነ ፕትርክናቸሁ ለመጠገን ፤የተለያየውን አንድ ለማድረግ፤የሻከረውን ለማለስለስ ያበቃችሁ እግዚአብሔር ይመስገን !

ከቅዱሳን አባቶቻችንና ከቅዱስ ሲኖዶስ የተቀበላችሁትን አደራ ከዳር ለማድረስ አንድ ጊዜ  አሜሪካ ሌላ ጊዜ ኢትዮጵያ በመመላለስ የደከማችሁ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና  በየአገሩ የምትገኙ የዕርቀ ሰላም ኮሚቴ አባላት እንኳን የድካማችሁን ፍሬ ለማየትና “ዕርቅ የሚያደርጉ ብፁዓን ናቸው፤ እነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይባላሉና” (በማቴ፭፥፱) የተባለው ተፈጽሞ ለማየት አበቃችሁ!

ዕርቁ ለቤተ ክርስቲያን፤ ለምእመናን አንድነት እንዲሁም ለሀገር ሰላም የሚኖረውን ጠቀሜታ ከፍተኛ መሆኑን ተመልክተው ለተግባራዊነቱ የሚችሉትን ሁሉ ላደረጉት ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስተር ለክቡር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ከፍተኛ ምስጋና ይገባቸዋል፡፡ በመጨረሻም ዕርቁ ተግባራዊ እንዲሆን በጾም በጸሎት እግዚአብሔርን ስትጠይቁ ለኖራችሁ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ፤መምህራን ፤ገዳማውያንና ምእመናን  እንኳን ይህን የአባቶችን የአንድነት ቀን ለማየት አበቃችሁ፤አበቃን በማለት ማኅበረ ቅዱሳን በራሱና በአባላቱ ስም ደስታውን ይገልጻል!

ይህ ደስታ የቤተ ክርስቲያን ታላቅ በዓል በመሆኑ ቤተ ክርስቲያናችን በምታደርግልን ጥሪ መሠረት ሁላችንም ምእመናን በአቀባበሉ ሥርዓት በመሳተፍ ፤የድርሻችንን እንድንወጣ ማኅበረ ቅዱሳን ጥሪያውን ያስተላልፋል፡፡

ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!

ሐምሌ 20 ቀን 2010 ዓ.ም