በፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ፣ በኖቲንግሃምና በጎንደር ከተሞች ዐውደ ጥናቶች ተካሔዱ

ነሐሴ ፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም

በአሜሪካ፣ በአውሮፓና በጎንደር ማእከላት

IMG_4429

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ማኅበረ ቅዱሳን የአሜሪካ ማእከል በፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ልዩ ዐውደ ጥናት እንደሚያካሒድ ሐምሌ ፮ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም ባወጣነው ዘገባ ማስነበባችን ይታወሳል፡፡

በዚህ መሠረት ማእከሉ ከፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ እና የሴሜቲክና የአፍሮ እስያ ከፍተኛ ምርምርና ጥናት ተቋም (The Institute for Advanced Semitic Studies and Afro Asiatic Studies) ክፍል ጋር በመተባበር ባዘጋጀው መርሐ ግብር ‹‹የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዋጽዖ›› በሚል ርእስ ሐምሌ ፳፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም በፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ልዩ ዐውደ ጥናት ተካሒዷል።

በዐውደ ጥናቱ በጥናት አቅራቢነት የተሳተፉትን ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይስሐቅን ጨምሮ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መምህራንና ካህናት፣ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት፣ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች፣ የፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ጥሪ የተደረገላቸው የውጭ አገር ዜጎች ተገኝተዋል፡፡

በአማርኛ እና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች በተካሔደው በዚህ ዐውደ ጥናት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሰላምና ልማትን በማጠናከር፤ የተለያዩ የእምነት ተቋማትና የኅብረተሰብ ክፍሎች ተቻችለውና ተከባብረው ለዘመናት እንዲኖሩ በማስቻል፤ እንደዚሁም በሥነ ጽሑፍ፣ በቋንቋ፣ በዜማ ጥበብ እና ልዩ ልዩ ዘርፎች ለዓለም ያበረከተችውን አስተዋጽዖ የሚዳስሱ ዝግጅቶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።

full image
አንዳንድ የዐውደ ጥናቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ለዓለም የማስተዋወቁን ሥራ ማኅበሩ አጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው እንደዚህ ዓይነቱ የዓውደ ጥናት መርሐ ግብር ለቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይኾን በመላው ዓለም ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ኹሉ ትልቅ ርካታን እንደሚሰጥና የአገራችንን ታሪክ ለዓለም ለማስተዋወቅም ከፍተኛ ጥቅም እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

በመጨረሻም ለዐውደ ጥናቱ መሳካት ቦታ በማመቻቸት፣ ቁሳቁስ በማሟላትና አስተርጓሚ ባለሙያዎችን በመመደብ የፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ላደረገው ከፍተኛ ትብብር እንዲሁም ለጥናት አቅራቢዎችና ተሳታፊዎች የማኅበሩ ተወካይ ምስጋናቸውን አቅርበው ወደፊትም ይህን መሰል ዓውደ ጥናቶችን ማእከሉ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ካላቸው ዩኒቨርሲቲዎችና ተቋማት ጋር በተጠናከረ ኹኔታ እንደሚያካሒድ አስታውቀዋል፡፡

በተያያዘ ዜና የእንግሊዝ ንዑስ ማእከል ‹‹መዝሙሮቻችን ከየት ወዴት›› በሚል ርእስ ሐምሌ ፳፬ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም የኖቲንግሃምና የአቅራቢያ ከተሞች ካህናትና ምእመናን፣ የሰንበት ት/ቤት መዘምራንና የንዑስ ማእከሉ አባላት በተገኙበት በኖቲንግሃም ከተማ የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር ማካሔዱን የአውሮፓ ማእከል አስታውቋል።

M

የመርሐ ግብሩ ዋና ዓላማም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም እየታተሙ ገበያ ላይ የሚዉሉ የአማርኛ መዝሙራት ከያሬዳዊ ዜማ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ማጥናትና የመፍትሔ አቅጣጫዎችን ማመላከት ሲኾን በዕለቱ በሦስት ዋና ዋና አርእስት ላይ ያተኮሩ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል፡፡ በእያንዳንዱ ገለጻ ላይም በአራቱ ወንጌላውያን ስም የተሰየሙ የቡድን ውይይቶች ተካሒደዋል።

በመርሐ ግብሩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ዜማ፤ በአማርኛ መዝሙራት የይዘት ችግሮችና በቅዱስ ያሬድ ታሪክና ዜማዎቹ ላይ ያተኮረ ጥናታዊ ዘገባ በሊቀ ዲያቆናት ልዩ ወዳጅ፤ ‹‹የአማርኛ መዝሙራት በተለያዩ አዝማናት›› በሚል ርእስ በመጋቤ ሠናይ ሳምሶን ሰይፈ፤ ‹‹በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የወጡ መዝሙራት፣ የመናፍቃን መዝሙራት ተመሳሳይነትና ምን እናድርግ›› በሚል ርእስ በዲ/ን ዶ/ር አዳነ ካሣ ጥናታዊ ጽሑፎች ቀርበዋል።

Publication1

የመጀመሪያዉ ዙር የግንዛቤ ማስጨበጫ መርሐ ግብር በጥር ወር ፳፻፰ ዓ.ም በበዓለ ጥምቀት ዋዜማ በበርሚንግሃም ከተማ ተዘጋጅቶ የነበረ ሲኾን በኖቲንግሃም ከተማ የተዘጋጀው ይህ መርሐ ግብር ሁለተኛው ዙር መኾኑን ከእንግሊዝ ንዑስ ማእከል የተላከልን መረጃ ያመለክታል።

በጉባኤው ላይ የተገኙ ምእመናን በማጠቃለያዉ ላይ በሰጡት አስተያየት መሠረትም በ፳፻፱ ዓ.ም ሦስተኛ ዙር መርሐ ግብር በለንደን ከተማ ለማካሔድ ዕቅድ መያዙንም ንዑስ ማእከሉ ጨምሮ ገልጾልናል።

በመጨረሻም የአዉሮፓ ማእከል ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል፤ የእንግሊዝ ንዑስ ማእከል አባላት፤ የልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት አገልጋይ ካህናትና ምእመናን ለመርሐ ግብሩ መሳካት ላበረከቱት ልዩ ልዩ አስተዋጽዖ ንዑስ ማእከሉ በእግዚአብሔር ስም ከፍ ያለ ምስጋና አቅርቧል።

በተመሳሳይ የአገር ውስጥ ዜና የጎንደር ማእከል ሙያ አገልግሎት ክፍል ከሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት እና ከጎንደር ከተማ አስተዳደር ባህል እና ቱሪዝም መምሪያ ጋር በመተባበር በጎንደር ከተማ ሲኒማ አዳራሽ ሐምሌ ፩ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም የዐውደ ጥናት መርሐ ግብር ማካሔዱን የጎንደር ማእከል ዘግቧል፡፡

ማእከሉ ለዝግጅት ክፍላችን እንዳስታወቀው በዐውደ ጥናቱ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እና የማኅበሩ አባላት የተገኙ ሲኾን የዐውደ ጥናቱ ዓላማም መልካም እና መልካም ያልኾኑ ጉዳዮችን በመመርመር ለቤተ ክርስቲያን ውስጣዊ እና ውጫዊ ችግሮች መፍትሔዎችን ለመጠቆም መኾኑን የጎንደር ማእከል የሙያ አገልግሎት ክፍል ሰብሳቢ ዶ/ር አገኘሁ ተስፋ ተናግረዋል፡፡

ጥናት እና ምርምር ለቤተ ክርስቲያን ያለውን ፋይዳ የተመለከተ ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ዶ/ር መሠረት ካሤ ጥናትና ምርምር የጎደለውን ለመሙላት፣ የተበተነውን ለመሰብሰብ፣ የተጎዳውን ለመጠገን፣ የጠፋውን ለመፈለግ፣ የተቀበረውን ለማውጣት ዓይነተኛ መንገድ መኾኑን ገልጸው ‹‹የአገራችን የኪነ ጥበብ፣ የሕግ፣ የዘመን አቈጣጠር፣ የባህል እና የማኅበራዊ ሕይወት ዕውቀቶች እና ተግባራዊ ልምምዶች በቀደሙት የቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የተቀመሩ የምርምር ውጤቶች ናቸው›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ሌላኛዋ ጥናት አቅራቢ ወ/ሪት መሠረት ሐሰን ደግሞ ‹‹ሉላዊነት በባህል እና በእምነት ላይ ያለው ተጽዕኖ›› በሚለው ጥናታቸው በአገራችን በኢትዮጵያ እየተለመዱ የመጡት ከትዳር አጋር ውጭ ጾታዊ ግንኙነት መፈጸም፣ ግብረ ሰዶም፣ ሥርዓት ያጣ አለባበስ፣ ወዘተ የመሳሰሉት ተግባራት የሴኪዩላር ሂዩማኒዝም ምልክቶች መኾናውን አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ማርሸት ግርማይ በበኩላቸው ‹‹Rethinking Ethiopian Educational System from the Ethiopian Orthodox Church፤ የኢትጵያን ሥርዓተ ትምህርት ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ትምህርት አንጻር እንደገና ማየት›› በሚል ርእስ ባቀረቡት ጥናታቸው ዘመናዊው ትምህርት ከቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ትምህርት ተሞክሮ መውሰድ እንደሚገባው ጠቁመዋል፡፡

የጎንደር ማእከልም ለጥናቱ መሳካት ልዩ ልዩ አስተዋጽዖ ያበረከቱትንና ጥናት አቅራቢዎችን በእግዚአብሔር ስም አመስግኗል፡፡

ከየማእከላቱ የደረሱን ዘገባዎች እንዳስታወሱት ኹሉም ዐውደ ጥናቶች በአባቶች ጸሎት ተጀምረው በአባቶች ጸሎት ተፈጽመዋል፡፡