በአሜሪካ ለአራተኛ ጊዜ ዐውደ ርእይ ተካሔደ

በአሜሪካ ማእከል

ነሐሴ ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

‹‹ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮዋን እንጠንቅቅ፤ ድርሻችንን እንወቅ›› በሚል ርእስ ማኅበረ ቅዱሳን ያዘጋጀው ፭ኛው ዙር ልዩ ዐውደ ርእይ በአሜሪካ አገር ለአራተኛ ጊዜ ለተመልካቾች ቀረበ፡፡

ዐውደ ርእዩ በአሜሪካ ማእከል በካሮላይና ግንኙነት ጣቢያ አስተባባሪነት ነሐሴ ፲፫ እና ፲፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም በሻርሎት ከተማ በሚገኘው የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አዳራሽ ቀርቦ በበርካታ ምእመናን ተጐብኝቷል፡፡

በመክፈቻ ሥርዓቱ ላይ የየአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ሰባክያነ ወንጌል፣ ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና በርካታ ምእመናን የተገኙ ሲኾን፣ በአባቶች ጸሎት ከተከተፈተ እና በግንኙነት ጣቢያው የእንኳን ደኅና መጣችሁ መልእክት ከተላለፈ በኋላ ዐውደ ርእዩ በሁለቱም ቀናት ለተመልካቾች ክፍት ኾኖ ቆይቷል፡፡

ከአባቶች ካህናትና ከአዋቂ ምእመናን በተጨማሪ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የሚግባቡ በርካታ ታዳጊ ሕፃናትና ወጣቶችም በዐውደ ርእዩ መሳተፋቸውን ግንኙነት ጣቢያው በሪፖርቱ አስረድቷል፡፡

እንደ ግንኙነት ጣቢያው ማብራሪያ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ይመለከተኛል የሚሉ ምእመናን እየተበራከቱ መምጣታቸውን የዐውደ ርእዩ ተመልካቾቹ ያቀርቧቸው ከነበሩ አስተያየቶች ለመረዳት ተችሏል፡፡ ይህም የዐውደ ርእዩ ዓላማ መሳካቱን እንደሚያመላክት በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡

ከዚሁ ዅሉ ጋርም የአንድ ለአንድ ድጋፍ በማድረግ የአብነት ተማሪዎችን ለመርዳትና ለማስተማር ቃል የገቡ ምእመናን እንደ ነበሩም ግንኙነት ጣቢያው ጨምሮ ገልጿል፡፡

በመርሐ ግብሩ ማጠቃለያ ዕለት ቃለ መጠይቅ የተደረገላቸው አንዳንድ ምእመናን በዐውደ ርእዩ በመሳተፋቸው ደስተኞች መኾናቸውን ገልጠው ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎቱን በአገር ውስጥ ብቻ ሳይገድብ ከኢትዮጵያ ውጪ ለሚኖሩ ምእመናንም ትምህርተ ወንጌል እንዲዳረስ የሚያደርገውን ጥረት አድንቀዋል፡፡ ይህ የማኅበሩ አገልግሎት ተጠናክሮ ሊቀጥል፣ ዐውደ ርእዩም በመላው ዓለም ሊዳረስ እንደሚገባው አስተያየት ሰጪዎቹ አሳስበዋል፡፡

በመጨረሻም ዐውደ ርእዩ በስኬት መጠናቀቁን ያስታወቀው የካሮላይና ግንኙነት ጣቢያ ጽ/ቤት እና የዝግጅት ኮሚቴው በልዩ ልዩ መንገድ አስተዋጽዖ ላደረጉ የቤተ ክርስቲያን አባቶች፤ ለአታላንታ ንዑስ ማእከልና ሰንበት ትምህርት ቤት አባላት፤ በተለይ ከአራት ሰዓታት በላይ ተጕዘው በትዕይንት ገላጭነት ለተሳተፉ ወንድሞች እና እኅቶች፤ እንደዚሁም ለበጎ አድራጊ ምእመናን በማኅበረ ቅዱሳን ስም ምስጋና አቅርቧል፡፡