ምዕዳነ አበው

በዲ/ን ኅሩይ ባየ እና በደረጀ ትዕዛዙ
 ሰኔ 17 ቀን 2003 ዓ.ም
/ምንጭ፦ ስምዐ ጽድቅ ጋዜጣ ከግንቦት1-15፣ 2003 ዓ.ም/ 
 
የቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት ጉባኤ ከግንቦት 10-16 ቀን 2003 ዓ.ም ሲካሔድ ቆይቶ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ተጠናቋል፡፡ ስለ ጉባኤው ሒደት አስተያየታቸውን እንዲሰጡን፤ ተሳታፊ ከነበሩት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ይመለከታቸዋል ብለን ያሰብናቸውን ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት አነጋግረን የዚህ ዕትም የአብርሃም ቤት እንግዳ አድርገናቸዋል፡፡

«ያሳለፍናቸው ውሳኔዎች በሥራ ላይ መዋል አለባቸው፡፡»

  የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል

ስምዐ ጽድቅ፡- የግንቦቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የርክበ ካህናት ጉባኤ ስለተወያየባቸው አጀንዳዎች ቢገልጹልን? 

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፡- ተወያይተን ውሳኔ ያሳለፍንባቸው አጀንዳዎች ወደ ዐሥራ ሦስት ይሆናሉ፡፡ የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ የጉባኤ መክፈቻ ንግግር፣ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ዓመታዊ የሥራ ክንውን፣ በቅርቡ ለጠቅላይ ቤተ ክህነት ሠራተኞች ስለተደረገው የደመወዝ ጭማሪ፣ የኢትዮጵያ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ፣ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ችግር፣ መንፈሳዊ ተቋማትን በተመለከተ፣ የልማት እና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ኤች አይ ቪ/ ኤድስ መከላከያና መቆጣጠሪያ መምሪያ ሥራ አፈጻጸም፣ ልማትን በተመለከተ፣ የስብከተ ወንጌል ጉዳይ፣ የሊቃነ ጳጳሳት ዝውውር፣ በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሓላፊ እና በማኅበረ ቅዱሳን የተፈጠረውን አለመግባባት በተመለከተ፣ የቀጣዩ ቋሚ ሲኖዶስ አባላት ምርጫና ልዩ ልዩ የሚሉ ናቸው፡፡
 
የደመወዝ ጥያቄን በተመለከተ ማስተካከያ አድርገናል፡፡ የሲዳማ ሀገረ ስብከት ችግር እንዲፈታ ተመድበው የነበሩት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ እና የሐዋሳ ደብረ ምሕረት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም አስተዳዳሪ እንዲነሡ ወስነናል፡፡ ለቀጣዩም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለሥራው ይስማማል ብለው ያመኑበትን ሥራ አስኪያጅ እንዲያቀርቡ እና በጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ትእዛዝ ሥራውን እንዲጀምሩ ወስነናል፡፡
ዝውውር የጠየቁ ሊቃነ ጳጳሳትም ለጥያቄያቸው ምላሽ አግኝተዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ቁልፍ የሆነው ስብከተ ወንጌል መሆኑ ይታመናል፡፡ በመሆኑም በስብከተ ወንጌል እንቅስቃሴ ቤተ ክርስቲያኒቱ የማታውቃቸው ሕገ ወጥ ሰባክያን እንዳይሰብኩ አግደናል፡፡ ሕገ ወጥ ሰባክያን ብቻ ሳይሆኑ ሕገ ወጥ ዘማርያንም በየትኛውም የስብከተ ወንጌል ዐውደ ምሕረት ቆመው እንዳያገለግሉ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

በሰንበት ት/ቤቶች ማደራጀ መምሪያ እና በማኅበረ ቅዱሳን መካከል ያለውን አለመግባባት ለመቅረፍ ከሊቃነ ጳጳሳት ሦስት አባቶች ከሊቃውንት ጉባኤ አራት ምሁራን ተመርጠው ጉዳዩን አጣርተው ለጥቅምት ሲኖዶስ እንዲያቀርቡ ኮሚቴዎችን ሰይመናል፡፡

ለቀጣዩ ስድስት ወራት የሚያገለግሉ ቋሚ የሲኖዶስ አባላትም ተመርጠው ሥራቸውን እንዲቀጥሉ አድርገናል፡፡ በተጨማሪም ከገጠሪቱ ክፍሎች ትምህርት ቤታቸውን ለቅቀው ወደ አዲስ አበባ እየፈለሱ የሚመጡ ሊቃውንት ባሉበት እንዲረጉ ለማስቻል በመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ እና በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት በኩል ችግሩ እንዲቀረፍ አቅጣጫ ሰጥተናል፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ስብከተ ወንጌል በተመለከተ ቀደም ብለው ሲገልጡልን ሕገ ወጥ ሰባክያን እና ዘማርያን ታግደዋል ብለውናል፡፡ ሕገ ወጥ ሰባክያን እና ዘማርያን ሲባል ምን ማለት ነው? ቅዱስ ሲኖዶስ ስለዚህ ጉዳይ ከዚህ ቀደም ወስኖ አልነበረም?

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፡- ሕገ ወጥ ሰባክያን እና ዘማርያን ማለት ቤተ ክርስቲያኒቱ ያላስተማረቻቸው የማታውቃቸው ያልተፈቀደላቸው ማለት ነው፡፡ እነዚህን ሕገ ወጥ ሰባኪያን እና ዘማርያን ባለፈው ጥቅምት ጉባኤ እንዲታገዱ ብለን መወሰናችን እርግጥ ነው፡፡ አሁን ግን ቅዱስ ሲኖዶስ ጥብቅ የሆነ ውሳኔ ነው ያስተላለፈው፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ሰባክያን እና ዘማርያን ሕጋውያን ናቸው ለማለት መሥፈርቱ ምንድን ነው?

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፡- ሕጋውያን ሰባኪያን እና ዘማርያን የምንላቸው በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ውስጥ የተካተቱ /የታቀፉ/ የአሠራር መዋቅርና መመሪያዋን የሚያከብሩ ማለታችን ነው፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- በጉባኤው የተወሰኑ ውሳኔዎች አፈጻጸማቸው እንዴት ይከናወናል?

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፡- ቅዱስ ሲኖዶስ ይሆናል ይጠቅማል እና ይበጃል ያለውን ነገር በሙሉ ወስኗል፡፡ ውሳኔውም በሚመለከታቸው አካላት ተግባራዊ መሆን አለበት፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- በጉባኤው ላይ የነበረው ውይይት ውጤታማ ነበር ማለት እንችላለን?

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፡- አዎ ውጤታማ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ በመጨረሻ መግለጽ የምፈልገው፤ የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት በሕገ ልቡና የነበረ በሕገ ኦሪት የጸና በሕገ ወንጌል በሐዋርያት፣ በሊቃውንት በጳጳሳት እና በካህናት እየተከናወነ ለዚህ ደርሷል፡፡ ከዘመነ መሳፍንት፣ ከዘመነ ነገሥት እና ከዘመነ አበው እየተወራረደ እስከ ዘመነ ሥጋዌ ዘልቆ ለዚህ ትውልድ የተላለፈ ባሕል፣ ሃይማኖት ቀኖና ትውፊት እና ዶግማ አለን፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዚህች ሀገር ታላቅ ድርሻ ያላት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ብዕር ቀርጻ፣ ቀለም በጥብጣ፣ ብራና ዳምጣ፣ የጽሕፈት መሣሪያ በሌለበት ጊዜ አሁን የምንገለገልበትን የብራና መጻሕፍት ጽፋ ታሪክ ጠብቃ ያኖረች ነች፡፡ ፊደልን አዘጋጅታ ሀ ሁ ብላ ያስተማረች ገንዘብ ሚኒስቴር ትምህርት ሚኒስቴር ሆና ያገለገለች ለትውልድ የዕውቀት እንጀራ ጋግራ ያሰናዳች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ የውጭ ወራሪ፣ የውስጥ መስሎ አዳሪ ጠላት በተነሣ ጊዜ ታቦት በራሷ፣ ቃጭል በጥርሷ ይዛ አዋጅ እየነገረች፣ ፍርሃት እንዳይመጣ እያበረታታች ድንኳን ተክላ ሥጋ ወደሙ ለሚገባው ሥጋ ወደሙ እየፈተተች እያቀረበች እያስተማረች እያጽናናች የታመመውን እያስታመመች የሞተውን እየቀበረች የሀገርን አንድነት ያስጠበቀች ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ከትናንት እስከ ዛሬ የዘለቀውን የቤተ ክርስቲያን ውለታ እንዘርዝረው ከተባለ ጊዜው አይበቃንም፡፡ ትውልዱም ይኼን ታሪክ አውቆ በማንነቱ ኮርቶ በሃይማኖት ጸንቶ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ሥርዓት ቀኖና እና ዶግማ እንዲጠብቅ አደራን አስተላልፋለሁ፡፡

 
ስምዐ ጽድቅ፡- ስለነበረን መልካም ቆይታ በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን፡፡

ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል፡- እናንተንም እግዚአብሔር ይጠብቃችሁ አገልግሎታችሁንም ይባርክ፡፡

«ጅራቱን አትልቀቅ ቀንዱን ትይዘዋለህ»
 

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የምዕራብ ትግራይ ሁመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ 

ስምዐ ጽድቅ፡- የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ ነበር ማለት ይቻላል?

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፡- ውይይቱ ቢያውልም፣ ቢያሰነብትም፣ ቢያከራክርም፣ ቢያዘገይም፣ ቢጎተትም ለቤተ ክርስቲያን ይጎዳሉ፣ ለምእመናን አይጠቅሙም፣ ለሀገር አይበጁም ያልናቸው ችግሮች ሁሉ እንዲቆሙ አድርገናል፡፡ ስለዚህ ውይይቱ ውጤታማ ነበር ማለት ይቻላል፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ስለ ስብከተ ወንጌል ምን የተወሰነ ነገር አለ?

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፡- ስብከተ ወንጌል የቤተ ክርስቲያኒቱ የጀርባ አጥንት ነው፡፡ በስብከተ ወንጌል ውስጥ የማይመለከታቸው አካላት ሰርገው ገብተው ጥንት የነበረውን ሥርዓታችንን እንዳያበላሹ ጥንቃቄ መደረግ አለበት፡፡ የቆየው ሥርዓታችን ተንዶ አዲስ ሥርዓት መተካት የለበትም፡፡ እነዚህን ሕገወጥ ሰባክያን በተመለከተ ባለፈው የጥቅምት ጉባኤ የተወሰነ ውሳኔ ነበር፡፡ አፈጻጸም ላይ ግን ተግባራዊ ሳይሆን ቆይቷል፡፡ ከአሁን በኋላ ግን በተግባር ላይ እንዲውል ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንኦት ወስኗል፡፡ «ጅራቱን አትልቀቅ ቀንዱን ትይዘዋለህ» እንደሚባለው ስብከተ ወንጌል ተዛብቷል፣ አብነት ት/ቤቶች ተዳክመዋል፣ ገዳማቱ ተቸግረዋል፡፡ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን እየጎነተሉን ነው እያልን፤ ከቀላል ወደ ከባድ፣ ከታች ወደ ላይ እየተጓዝን ነው፡፡ በዙሪያችን የሚታዩትን ችግሮችን በጋራ መቅረፍ አለብን፡፡ ሕገ ወጥ ሰባክያኑን በተመለከተ የተወሰነው ውሳኔ በመምሪያው ሊቀ ጳጳስ በኩል ተፈጻሚ እንደሚሆን ተስፋ አደርጋለሁ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- አጠቃላይ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ አፈጻጸም እንዴት ሊከናወን ይችላል?

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፡- የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥራዋን የምታንቀሳቅሰው በሕገ ቤተ ክርስቲያን እና በቃለ ዓዋዲው መሠረት ነው፡፡ በተለይ በአፈጻጸም እና በአሠራር በኩል ሙሉ በሙሉ የምታከናውነው በቃለ ዓዋዲው ነው፡፡ ቃለ ዓዋዲው የተመሠረተው በሦስት አካላት ነው፡፡ ሦስቱ አካላትም አንደኛ የካህናት ጉባኤ ሁለተኛ የምእመናን ጉባኤ ሦስተኛ የወጣቶች ጉባኤ በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነዚህ ሦስቱ ክፍሎች በመደማመጥ፣ በመቻቻል፣ በመወያየት በመናበብ እና በመተያየት ሥራቸውን ሙሉ በሙሉ ያካሒዱታል፡፡ ከታች እነዚህ አካላት ሆነው ከላይ ያለው የቤተ ክርስቲያኒቱ የሥልጣን አካል ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ምንጊዜም ቢሆን መመሪያ ነው የሚያስተላልፈው፡፡ የሚሠራውና የማይሠራውን የሚሆነውን እና የማይሆነውን ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔውን የሚያስተላልፈው ከላይ ለተገለጡት ሦስት አካላት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ከሕፃናት እስከ ዓዋቂ ከካህናት እስከ ምእመን የየራሳችን ድርሻ አለን ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ ገበሬው መገበሪያ ያቀርባል፡፡ ካህኑ ይረከበዋል፡፡ ሊቀ ጳጳሱ ይባርከዋል ለአገልግሎትም ይውላል፡፡ ሸማ ሠሪው ልብስ ይሠራል ለካህኑ ይሰጠዋል ሊቀ ጳጳሱ ይባርከውና ልብሱ ይቀደስበታል፡፡ አንጥረኛው መስቀል ይሠራል፡፡ ሠርቶም ለካህኑ ይሰጠዋል፡፡ ካህኑም ለሊቀ ጳጳሱ ያቀርበዋል ሊቀ ጳጳሱ ባርኮ እንዲባርክበት መልሶ ለካህኑ ይሰጠዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የተሟላ የሚሆነው ሁላችንም ተባብረን ስናገለግል ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ወስኖ ውሳኔውን በተግባር ፈጽሞ እንዲያሳያቸው የሚጠብቁ ሰዎች አሉ፡፡ ይኼ ግን ስሕተት ነው፡፡ የተወሰኑ ውሳኔዎችን መፈጸም እና ማስፈጸም የምእመናን ድርሻም እንደሆነ መታወቅ አለበት፡፡ የስሕተት ትምህርቶች ሲሰጡ፣ የቤተክርስቲያኒቱ ሥርዓት ወዳልተፈለገ ጎዳና ሲያዘነብሉ ምእመናን ዝም ማለት የለባቸውም፡፡ ከሊቃነ ጳጳሳትም ጀምሮ እስከ ምእመናን ድረስ የድርሻችንን ስንወጣ ቤተ ክርስቲያኒቱ በትክክል ትጓዛለች፡፡

ቅድስት ድንግል ማርያምን የሚነቅፉ፣ ቅዱሳን መላእክትን የሚቃወሙ፣ ቅዱሳኑን የሚተቹ ትምህርቶች በየዐውደ ምሕረቶቻችን ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ምእመናን ዝም ማለት የለባቸውም፡፡ ንስጥሮስ የክሕደት ትምህርት ሲሰጥ ሰምተው የማናውቀውን እንግዳ ትምህርት አንተ ከየት አመጣኸው? ብለው የተቃወሙት ምእመናን ናቸው፡፡ ስለዚህ የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተፈጻሚ የሚሆነው በካህናት እና በምእመናን ሲተገበር ነው፡፡ መሐንዲስ ፕላን ማውጣት እንጂ ግንብ መገንባት ላይጠበቅበት ይችላል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ያወጀውን አዋጅ የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ ለጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ያቀርቡታል፡፡ ከጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ በመሸኛ ይልኩታል፤ በዚህ መልኩ ይፈጸማል ማለት ነው፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- በቅርቡ የሐዋሳ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሆነው የተመደቡት ሊቀ ካህናት ጌታቸው ዶኒ ለመነሣታቸው ምክንያቱ ምንድን ነው?

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፡- በቃለ ዓዋዲው እና በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ ደንብ መሠረት የሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጆች የሚሾሙት በሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ አቅራቢነት በቅዱስ ፓትርያርኩ ፈቃድ በጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ፈቃድ በምእመናኑ ይሁንታ ሲያገኙ ነው፡፡ የሐዋሳው ሥራ አስኪያጅ ግን ሊቀጳጳሱ ስላልፈቀዱላቸውና ምእመናን መቃወማቸውን ቅዱስ ሲኖዶስ ስለተረዳ ሊነሡ ችለዋል፡፡ የማይሆን ነገር አይሆንም ማለት ነው፡፡ በግዴታ የሚሆን አንዳች ነገር የለም፡፡

ስምዐ ጽድቅ ፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልእክት ካለ?

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፡- ለቤተ ክርስቲያናችን ሁለንተናዊ ተልእኮ የሁላችንንም ትብብር ይጠይቃል፡፡ እርስ በእርሳችን በመተያየት በመደማመጥ አብረን ለመሥራት እንነሣ፡፡ ገብረ ማርያም ተብለን በስመ ጥምቀት መጠራት ብቻ ሳይሆን ለማርያም ምን አደረግሁ ብለን መጠየቅ አለብን፡፡ ሰይፈ ሚካኤል ከተባልን ለሚካኤል ምን አደረግሁ ማለት ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ የድርሻችንን ለመወጣት ጠንክረን እንሥራ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ስለ ሰጡን ማብራሪያ በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን፡፡

ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፡- እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ ሰላሙንም ያብዛላችሁ፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- አሜን ብፁዕ አባታችን፡፡

«ውሳኔዎቻችን ወረቀት ውጧቸው እንዳይቀሩ የሚያስተገብር አስፈጻሚ ያስፈልጋል»

 

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል የሲዳማ፣ ጊዲዮ አማሮና ቡርጂ አህጉረ ሰብከት ሊቀጳጳስስምዐ ጽድቅ፡- በሲኖዶሱ ጉባኤ ስለእርስዎ ሀገረ ስብከት ምን ተወሰነ? በውሳኔው መሠረት በሀገረ ስብከትዎ ምን ምን ተግባራት ለማከናወን ታስቧል?
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- ያው በሐዋሳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጵጵስናዬን ይዤ እንድቀጥል ተወስኗል፡፡ በፊትም የቆመ ነገር የለም፡፡ የእርስ በርስ ብጥብጥ ስለነበረ ቅዱስ አባታችን እዚህ ቆይ ስላሉኝ ትንሽ እዚህ ቆይቼ ነበረ፡፡ አሁንም ሥራችንን ከቀጠልን ልንሠራቸው ያሰብናቸው ነገሮች አሉ፡፡ የስብከተ ወንጌሉን አገልግሎት ቅድሚያ ሰጥተን፣ ካህናትን እያሠለጠንን ሕይወት ለዋጭ የሆነውን ትምህርተ ወንጌል ለማስፋፋት ነው የምንሠራው፡፡ ሁለተኛ ልማት ላይ እናተኩራለን፡፡ በቀበሌ ኪራይ ላይ ያለውን የሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ለማሠራት ዕቅድ አውጥተናል፡፡ ሦስተኛ የተጀመረ ማሠልጠኛ አለ፤ አዳሪ ተማሪዎችን ቁጥራቸውን በማሳደግ ጥራት ያለውን ትምህርት ለመስጠት አቅደናል፡፡ ከዚህ በተረፈ እርቅና ሰላምን በመስበክና በማስታረቅ ሰላም እንዲመጣ መጣር ዋናው ዕቅዳችን ነው፡፡ ይህን ከሁሉ ቀድመን የምንፈጽመው ይሆናል፡፡ ሰላም ከሌለ ምንም የለምና፡፡ ወንጌል ሰላም ነው፣ ትህትና ነው፣ አንድነት ነው፡፡ ቅዱስ ወንጌልን መሠረት ያደረገ ሰላምን ለመስበክ እንጥራለን፡፡ እርቅና ሰላሙ በተግባር መገለጥ ያለበት በመሆኑ ይህንኑ በስፋት እንገባበታለን፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ይህንን ለመፈፀም ከምእመናኑም ሆነ ከአገልጋዮች ምን ይጠበቃል ይላሉ?

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- ምእመናንና ካህናት ሁሌም ኅብረት መፍጠር አለባቸው፡፡ ካህናት በጸሎታቸው ምእመናን በገንዘባቸው በሙያቸው፣ በጉልበታቸው ልማትን ማፋጠን ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የተዘረዘሩትን የልማት ዕቅዶች እውን የምናደርገው ኅብረት፣ ፍቅርና አንድነት ሲኖር ነው፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያኒቱ የተመሠረተችው በምእመንና በካህናት ነው፡፡ ካህናት ስንል ብፁዓን አባቶችም በዛ ውስጥ አሉ፡፡ ስለዚህ ኅብረት እንዲኖር መጸለይ፣ መስማማት፣ መታረቅ ያስፈልጋል፡፡ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሁከት ስለነበረ ምንም ሳናለማ ነው የቆየነው፡፡ እርስ በእርስ መስማማቱ ጠፍቶ ነበር፡፡ እኔም ከተመደብኩ ጀምሮ ለማስታረቅ ብዙ ሞከርኩኝ ችግሩ እዛ አካባቢ ሳይሆን ከሌላ አካባቢ የተለኮሰ ስለሆነ በቀላል ሊበርድ አልቻለም፡፡ እዛ ብቻ ቢወሰን ኖሮ ያን ያህል አያስቸግርም ነበር፡፡ ዘርፍ ያለው፣ ሽቅብ ቀንድ ያለው፣ የሚያድግ፣ ቁልቁለትም አቀበትም ያለው ስለሆነ ብዙ አስቸጋሪ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ያ እንዲቀር ነው ጸሎታችን፡፡ ለዚህ ኅብረት ያስፈልጋል፤ ቤተ ክርስቲያናችን መለያየትን አትወድም፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ዐይኖችም እጆችም እግሮችም ሁሉም ሕዋሳት ተባብረው እንዲሠሩ አስተምሮናልና፣ ሳይንሱም ያዘናል፡፡ ይህን አንድነት እንድናገኝ እንጸልይ፡፡ ችግራችንን እንወቅ፣ ከባድ የሆነ አደጋ እንደከበበን ዐውቀን እንጠንቀቅ፣ ይህ አደጋ መለያየት መሆኑን ተገንዝበን እንንቃ፡፡ ስለዚህ መለያየታችንን በትዕግሥትና በእርቅ ማስወገድ ሐዋርያዊ ሥራ፣ ቤተ ክርስቲያናዊ ሥራ፣ ሕዝባዊ ሥራ መሥራት እንችላለን፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ በቀጣይ በአካባቢው ሰላም አንድነትና ሥርዓት ተጠብቆ እንዲሔድ ያስችላል የሚል እምነት አለዎት?

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና ሊቃውንት በቃለ ወንጌል ለማረጋጋት፣ ሰላም ለመስበክ ይሔዳሉ፡፡ እነርሱ ፈጽመው ከተመለሱ በኋላ ሥራችንን ለመቀጠል እንሔዳለን፡፡ ምእመናኑ ዘጠና ዘጠኝ በመቶ ከእኔ ጋር ናቸው፡፡ እነዛም ወንድሞቼ ልጆቼ ናቸው፡፡ አለመግባባት ነው እንጂ፡፡ ስለዚህ የአምላካችን ፈቃድ ከሆነ ሥራችንን እንቀጥላለን፡፡ እና ቅዱስ ሲኖዶስ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ሰላም፣ አንድነት እንዲሰፍን ጸሎቱም ሥራውም ስለሆነ የታሰበው ይፈጸማል ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ በደቡብ አካባቢ ትንሽ ስለሆንን ሌትም ቀንም እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ይፈልጋል፡፡ ይህ ፍላጎት እንዲሟላ እግዚአብሔር እንዲረዳን ከልብ እንጸልያለን፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- እርስዎ በቅዱስ ሲኖዶሱ አንጋፋ አባት እንደመሆንዎና በአገልግሎትም ረጅም ዘመን እንደ መቆየትዎ ከሕገ ቤተ ክርስቲያን አንጻር የሲኖዶሱን ውሳኔዎች አፈጻጸም ካለፉት ዓመታት ጋር እንዴት ያነጻጽሩታል? የሌሎች ሀገሮች ተሞክሮም ካለ ቢያካፍሉን?

ብፁዕ አቡነ ገብርኤል፡- «ሲኖዶስ» በኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሕግና ሥርዓት መሠረት የሐዋርያትን ሲኖዶስ ተከትሎ የሚሔድ ነው፡፡ ከሐዋርያት ጀምሮ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚመሰለው በመንፈስ ቅዱስ ነው፡፡ የመንፈስ ቅዱስ ውሳኔ ደግሞ ይግባኝ የለውም፡፡ ግን ሲኖዶስን የሚያጅቡ ፍቅር፣ ጸሎት፣ ሰላም፣ ትህትና፣ ይቅርታ ናቸው፡፡ እነዚህን ሁሉ ተላብሶ ወንጌል እንዲሰብክ የሚወስን ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያንን ዶግማዋን ሥርዓቷን የሚጠብቅ ነው፡፡ ምእመናን በጎቿን የሚጠብቅ፣ የሚያስጠብቅ ነው፡፡ በዚህ መሠረት ከቀደምት ጊዜያት ጀምሮ ውሳኔ ይወሰናል ነገር ግን ውሳኔን ማስፈፀም ላይ ችግር አለ፡፡ በጣም አስፈላጊ የሆኑ ውሳኔዎች ላይ አስፈጻሚ ያስፈልጋቸዋል፡፡ የሲኖዶሱን ውሳኔ ከፓትርያርኩ ጎን ሆኖ የሚያስፈልጽም አካል ያስፈልጋል፡፡

ውሳኔዎቻችን ወረቀት ውጧቸው እንዳይቀር በተግባር የሚያስፈጽም ታላቅ ኃይል የለንም፡፡ ከጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ ጋር ተባብረው የሚሠሩ ቢያንስ ዐሥራ ሁለት ሊቃነ ጳጳሳት ያሉበት አስፈጻሚ አካል ያስፈልጋል፡፡

የራሺያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ጠንካራ የሆነበት ምክንያት ከፓትርያርኩ ጋራ ዐሥራ ሦስት አባላት ያሉበት አስፈጻሚ በመኖሩ ነው፡፡ እኔ ዘጠኝ ዓመት እዛ ስቀመጥ ያየሁት ጠንካራ ነገር ይህ ነው፡፡ ምልዐተ ጉባኤው ወስኖ ሲሔድ እነዚህ አስፈጻሚዎች ተግባራዊ እንዲሆን ያደርጋሉ፡፡ እያንዳንዱ ውሳኔ አይባክንም፡፡ እንዲህ ዓይነት አሠራር በሲኖዶሳችን ሊኖር ይገባል፡፡ መወሰን ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ አፈጻጸሙን መከታተል ይገባል፡፡ መፈጸሙን ማረጋገጥ ይገባል፡፡ ከዚህ አንጻር ሲኖዶሳችን አስፈጻሚ ክፍል እንዲኖረው ይደረግ ነው የምለው፡፡ በሕገ ሲኖዶስ እየተመራ የሚሠራ ጠንካራ አስፈጻሚ ክፍል ቢያንስ መቋቋም አለበት፡፡ ብዙ ወስነን ጥቂቶቹ ብቻ ናቸው ተግባራዊ የሚሆኑት፡፡ ያ ስለሆነ ነው አስፈጻሚ ክፍል አስፈላጊ ነው የምለው፡፡

«ሁሉም የቤተክርስቲያን አካላት ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው»

 
የስብከተ ወንጌል እና ሐዋርያዊ ተልእኮ መምሪያ ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ማርቆስስምዐ ጽድቅ፡- በስብከተ ወንጌል ረገድ የዘንድሮው ግንቦት የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ውሳኔና ሐዋርያዊ ተልእኮ ምን ይመስላል? አፈጻጸሙስ ላይ ምን ታስቧል?

ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፡ በስብከተ ወንጌል አገልግሎት ላይ ያለው ችግር ውሎ ያደረ ውዝፍ በመሆኑ ለማስተካከል ጊዜ ይጠይቃል፡፡ መዋቅራዊ ሰንሰለቱን፣ ጠብቆ ማስቀጠል ግድ ይላል፡፡ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅና ውጪ የሚንቀሳቀሱ እና ጥልቀት የሌለው ትምህርት ያላቸው፤ ከገንዘብና ከጥቅም ጋር የተያያዘ ችግር ያለባቸው ናቸው ይህን ችግር እየፈጠሩ ያሉት፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ትኩረት እየሰጠ በመዋቅር ደረጃ አገልግሎቱ እንዲሰፋ እያደረገ ነው፡፡ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በዘርፉ አባት አስቀምጧል፡፡ የአንድ አባት /ሊቀ ጳጳስ/ ዓላማው ወንጌልን መስበክ ነው፡፡ ከጥንተ ስብከት ጀምሮ ወደ ዓለም ሒዱ ነው፡፡ ወንጌል ለሁሉም ነው፡፡ ድኅነት ስለሆነ፡፡ ከዚህ አንጻር ወደ ቤተ ክርስቲያናችን ስንመጣ አፈጻጸሙ ላይ ችግር አለ፡፡ ማእከላዊነቱን አለመጠበቅ አለ፡፡ አምና ተወስኖ ነበር የአፈጻጸም ችግር ስላለ አልተተገበረም፡፡ ዘንድሮም ያንኑ ውሳኔ በማንሳት በበለጠ መሥራት እንዳለብን ስምምነት ላይ ተደርሷል፡፡ ስብከተ ወንጌል መምሪያው ሳያውቀው፣ ቤተ ክርስቲያኒቱ ፈቃድ ያልሰጠቻቸው ሰባኪያን በየትኛውም ቦታ እንዳይንቀሳቀሱ ተብሎ ውሳኔ ተላልፏል፡፡ ይህንን መምሪያው፣ የየአህጉረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት የሌሎችም የእምነቱ ተከታዮች አፈጻጸሙ ላይ ትኩረት ሰጥተው /ሰጥተን/ በጋራ መሥራት አለብን፡፡ በሴርኩላር የሚተላለፈውን መመሪያ በየደረጃ መፈጸም ግድ ነው፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ከቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ውጪ የሚንቀሳቀሱ ሰባክያነ ወንጌል ላይ የተላለፈው ውሳኔ ተግባራዊ አለመሆኑ የሚያስከትለው ተፅዕኖ ምንድነው ይላሉ?

ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፡- ወንጌል ሰላም ነው፡፡ ትርጉሙ አንድነት ነው፡፡ ጉዳቱ በቤተ ክርስቲያን ትምህርት ያልዘለቁ፣ በመምህራን እግር ሥር ዕውቀትን ያልቀሰሙ እናስተምር ሲሉ ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ትክክለኛው ወንጌል፣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮ ወደ ምእመናን ይደርሳል ለማለት አይቻልም፡፡

አንዳንድ ማሠልጠኛ ገብተው በለብለብ ምኑንም ሳያውቁ እያቋረጡ እየወጡም ገበያው ሲመቻችላቸው ዕውቅና እያገኙ ሲሔዱ ዓውደ ምሕረቱን እንደራሳቸው ያደርጉታል፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡ ተስተካክሎ የሚያገለግል ብናገኝ እሰየው ነው፡፡ ሰው ያንሰናል እንጂ አይበዛብንም፡፡ ሁሉም የቤተ ክርስቲያን ልጆች ናቸው፡፡ ነገር ግን ከታች አጥቢያ ጀምሮ እስከ መንበረ ትርያርኩ ድረስ በመመሪያ የሚመጡ የሚወርዱ መሆን አለባቸው፡፡ ዋናው ተወስኗል፡፡ አፈጻጸሙ ላይ የሁሉም የቤተ ክርስቲያን አካላት ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው፡፡

ያለፈቃድ ሊሰብክ የሚወጣ ካለ መቃወም፣ መከልከል ይገባል፡፡ ይህ መምሪያው ብቻውን የሚወጣው አይደለም፡፡ ጥቃቅን ችግሮች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ ሃይማኖቱ ላይ መጠንከር ግን ይገባቸዋል፡፡ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና ሥርዓት መሠረት አሰረ ክህነት የሌለው ወንጌል አይሰብክም፡፡ ይህ ካልሆነ ከፕሮቴስታንቱ ምን ልዩነት አለን፡፡ አሁን የመጣ እንጂ ቢያንስ ዲቁና የሌለው እንዴት ይሰብካል? በማብቂያ ምን አድርጉ ሊል ነው? የወንጌል ማሰሪያው ንስሐ ግቡ፣ ሥጋውን ደሙን ተቀበሉ ነው፡፡ ያኔ ምእመኑን ምን ሊል ይችላል? ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን የማያውቅ፣ ቢያንስ ዲቁና የሌለው ሲያስተምር እናያለን ይህ ጊዜው ዝም ብሎ ያመጣው ነው እንጂ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሥርዓት አይደለም፡፡

ይህንን መምሪያው እያጣራ ነው፡፡ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን ጠብቀው ማኅበር መሥርተው ሲመጡ እንቀበላቸዋለን፤ መምህራኑ ግን ይህን ደረጃ ማለፍ ያለባቸው መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡ ይህ የመምሪያው ሓላፊነት ነው፡፡ የወጣቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣት ይበል የሚያሰኝ ነው፡፡ አካሔዱ ግን የመምሪያው ነው፡፡ መዝሙራቸው ሥርዓት መያዝ አለበት፡፡ ትምህርታቸው ሥርዓትን የጠበቀ መሆን አለበት፡፡ ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ነው፡፡ አፈጻጸሙ ጠቅላይ ጽ/ቤቱ፣ መምሪያው እና የየአህጉረ ስብከቶቹ ትብብር እና የምእመኑ እገዛ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅና ውጭ የሚንቀሳቀሱ ያመጡት ጉዳት ለተባለው ጤናማውን ምእመን እየበረዙ እየለያዩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ አደጋ መፍጠር ነው፡፡ ይህ ለቤተ ክርስቲያን፣ ለኅብረተሰቡም ሆነ ለመንግስት አደጋ ነው፡፡ ዛሬ በልማት እየተደረገ ያለውን ሩጫ ያደናቅፋል፡፡ ሕዝቡ ሰላም ሳይኖረው ልዩነት ካለ አደጋ ነው፡፡

ይህ ድርጊት በእምነት፣ በቀለም፣ በጎሳም አይደለም፡፡ አጠቃላይ የሰውን ልጅ ሰላም የሚነካ ነው፡፡ ስለዚህ የኛ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ትምህርት ሰላም ስለሆነ ይህንኑ ማስፈጸም ላይ መትጋት ነው፡፡ ሰላማዊውን ሕዝብ ሰላም የሚነሳ ከሆነ ይህ ሰይጣናዊ ስብከት ነው፡፡ ይህን ሕዝቡ ስለሚያውቀው እኛም እግዚአብሔር የፈቀደልንን ያህል ድርጊቱን ለማስቆም እንሔዳለን፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የተጠበቀውን ያህል ውጤታማ ነበር ማለት ይቻላል?

ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፡- ጥሩ ነበር፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሩ እድገት እያሳየ ነው፡፡ የአባታዊነትን ግዳጅ እየተወጣ ነው፡፡ ሥርዓተ ቤተክርስቲያን እንዲከበር እየጣረ ነው፡፡ በነገሮች መሰናክል አይጠፋም ነገር ግን በትዕግሥት ነጥቡን እያየን ነገሮች ሁሉ ዓላማቸውን ሳይስቱ ጉባኤው በጥሩ ግብ ላይ ነው የተደመደመው፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- የተሐድሶ መናፍቃን እንቅስቃሴ ላይ ምን የታሰበ አቅጣጫ አለ?

ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፡- ይህ ጉዳይ ሕጋውያን ሰባኪያን ካልሆኑት ጋር የሚገናኝ ጉዳይ ነው፡፡ ማንኛውም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ በሚሰጠው በየትኛውም ትምህርት አግባብ መስሎ ያልታየውን ተከታትሎ መረጃ መስጠት ይጠበቅበታል፡፡ ዛሬ ማእከላዊነት ስላልተጠበቀ ማንን ከማን መለየት አስቸግሯል፡፡ ማእከላዊነቱን በጠበቀ መልኩ ሁሉም ነገር ከአጥቢያ እስከ መንበረ ትርያርክ ሲኬድ ሁሉም ግልጽ ይሆናል፡፡ አንዳንዶች በየአጥቢያው ቤተ ክርስቲያን የግል ደጋፊ /ቲፎዞ/ ያበጃሉ፡፡ እነዚህ በገንዘብ፣ በጥቅም… ስለሚገቡ አጥቢያዎች የራሳቸውን ጥረት አድርገው በጥንቃቄ መለየት አለባቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት የመናፍቃን እንቅስቃሴ ይህ ነው አይባልም፤ እንደአሸን ፈልተዋል፡፡

በኑሮ እያሳበቡ አንዳንዶች መምህራንና መነኮሳት ጭምር ስም ለውጠው ወደ ሌላ ሔደዋል የሚባል ነገር ይሰማል፡፡ ሃይማኖት ደግሞ ከኑሮ ጋር አይያያዝም፡፡ ይህ እንዲቆም ሁሉም መትጋት አለበት፡፡ ስለዚህ መጠንከር ነው፡፡ በተለይ ብፁዓን አባቶች መጠንከር አለባቸው የሲኖዶስ ጥንካሬ ነው መፍትሔው፡፡ ነገሮችን አይቶ መዝኖ ይወስናል፡፡ አፈጻጸሙን ይከታተላል ያኔ መናፍቃን ይህን መንጋ ይወስዳሉ ብለን አንሰጋም፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- የቤተ ክርስቲያኒቱ ልዕልና እንዲከበር፣ ታሪኳ፣ ቅርሷ፣ ትምህርቷ ዶግማዋና ቀኖናዋ ተጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ ከምእመናንም ሆነ ከሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ምን ይበቃል?

ብፁዕ አቡነ ማርቆስ፡- ከታች እስከ ላይ የወንጌል መረብ እንዲዘረጋ በቀና መንፈስ ነገሮችን መመልከት ነው፡፡ ዘመኑን የዋጀ ትምህርት ለምእመናን ማድረስ ቤተ ክርስቲያን ሓላፊነት አለባት፡፡ ሕዝቡም መመሪያ ጠብቆ መገልገል አለበት፡፡ የጸሎት፣ የንስሐ ትምህርትን ማግኘት አለበት፡፡ ለዚህ ቀና መሆን ነው፡፡ በፍቅር በአንድነት ለአንድ ዓላማ መቆም ነው፡፡ እናት ቤተ ክርስቲያን ሁሉን ትይዛለች፤ የሕዝቡን ሥነ ምግባር፣ ሞራል፣ ሥርዓት ጠብቃ የኖረች ናት፡፡ ይህ አዲስ አይደለም፡፡ አሁን የመጣው ዕውቀት ሳይኖረው ሰባኪ ነኝ እያለ ሕዝቡን ማለያየት ሁከት መፍጠር ነው፡፡ የሚገባው ግን እውነተኛውን ወንጌል፣ የቅዱሳንን ታሪክ ገድላቸውን መስማት ነው፡፡ ይህ ትጥቅ ነው፡፡ ቅዱሳኑ እንዴት ሆነው እንደሞቱ፣ መከራን እንደተቀበሉ እንደሽንኩርት እንደድንች እንደተላጡ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ እንዲህ ሆነው ያለፉት ወንጀል ፈጽመው አይደለም ዓለምን ለማዳን ነው። ስለዚህ ብዙ ችግር የለም መዋቅር መጠበቅ ብቻ ነው፡፡ ሰፊ ክፍተት ስንፈጥር ነው ሌላው ያለአግባብ ውስጣችን የሚገባው፡፡

እስካሁን ያለፈው ሳያስጨንቀን ለወደፊቱ ተግቶ መሥራት ነው፡፡ ወንጌል በጥላቻ አይሰበክም፡፡ ፍቅርን ሰላምን ለማምጣት ትክክለኛው የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መጠበቅ ነው፡፡ ዋናው ለቤተ ክርስቲያን መኖር ነው፡፡ መኖር ማለት እናት ለልጇ አባትም ለልጁ እንደሚኖሩት ማለት ነው፡፡ የእነርሱ ተግባር አስፈላጊውን መስዋዕት ከፍሎ ልጅን ማሳደግ ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን ምእመናንም እንደዚያ መኖር አለባችሁ፡፡ ንስሐ መግባት፣ ሥጋውን ደሙን መቀበል፣ ጥላቻን ማስወገድ፣ እውነተኛ ሰባኪያንን አይዟችሁ ማለት ይገባል፡፡ አይሁድ «ትንሣኤው የለም» በማለት ወንጌል ረጭተዋል፤ ምእመናን ደግሞ «ወንጌል አለ ትንሣኤ አለ» በማለት ገንዘብ ማውጣት አለባቸው፡፡ ስለዚህ እርሱን ነው ለቤተ ክርስቲያን መኖር የምንለው፡፡ በተረፈ በጥላቻ የሚሆን ነገር የለም፤ በውይይት ግን ድል እናደርጋለን እግዚአብሔርም ይረዳናል፡፡

«ሌሎችን ለማምጣት እያሰብን ያሉትን እንዳናጣ መጠንቀቅ ይኖርብናል»

 ብፁዕ አቡነ ቀሌሜንጦስ/ ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሊቀ ጳጳስስምዐ ጽድቅ፡- የቅዱስ ሲኖዶስ የርክበ ካህናት ጉባኤ አጀማመርና አጨራረስ ምን ይመስል ነበር?
ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፡- ጥሩ ነው፤ መጨረሻው ሁሉም እንዲታይ ሆኖ ተካሒዷል፡፡ ውሳኔዎቹ ሁሉም ጥሩ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የጉባኤው አፈጻጸም ጥሩ ነው፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ከሰንበት ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ እና ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በተያያዘ የተነሡ አሳቦች እና ውሳኔዎች ምን ይመስሉ ነበር?

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፡ – አንዱ በአጀንዳነት የተያዘው ይኸው ነበር፡፡ በሁለቱም ወገን ችግሮችና ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ችግሩ ይታይ የሚለው የኛ አቋም ነበር፡፡ ለሁለቱም አካላት ደንብ የሰጠ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡ ማየትም የሚችለው ቅዱስ ሲኖዶስ በመሆኑ ችግሩ ተጠንቶ ይቅረብ ወደሚለው መደምደሚያ ላይ ተደርሷል፡፡ ውሳኔውም ይኸው ነው፡፡ በአሠራር ማለትም በአገልግሎትም ይሁን በግል ጉዳይ ችግሩ የት እንደሆነ አጥንቶ የሚያቀርብ አካል ተመርጧል፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- አጣሪው አካል ማነው? ማንን ማንን ያካትታል?

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፡- ከአባቶችና ከሊቃውንት የተውጣጣ ነው፡፡ ሦስት ሊቃነ ጳጳሳት ማለትም፤ አቡነ ገሪማ፣ አቡነ ሕዝቅኤል፣ አቡነ ማርቆስ እንዲሁም መልአከ ታቦር ተሾመ ዘሪሁን፣ ቀሲስ ዶ/ር ምክረ ሥላሴ ገ/አማኑኤል፣ መልዐከ ምሕረት ዓምደ ብርሃን፣ ከሊቃውንት ጉባኤ፣ ከሕግ ክፍል አቶ ይስሐቅ ናቸው፡፡ ከአሁን ጀምሮ ሥራቸውን ይጀምራሉ ማለት ነው፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- በሁለቱም ወገን ያለው ችግር መንሥኤ ምን ይሆናል ብለው ያስባሉ?

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፡- በውጭ ሰፍቶ የምናየው ችግር ውስጡ ገብተን ብናየው ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ ክፍተት ግን አለ፡፡ ምናልባት የአሠራር ወይንም የአፈጻጸም ችግር ጉዳዩን እንዲጎላ አድርጎታል ብዬ አስባለሁ፡፡ ከሁለቱም ወገን ስሕተቱ የት ነው የሚለውን ለመለየት የጥናቱ ውጤት ወሳኝ ነው፡፡ ማን ምንድነው? ደንቡስ ምን ይላል? የሚለው በአጥኚዎች ተፈትሾ ለምልዐተ ጉባኤው ሲቀርብ ውሳኔ ይሰጥበታል፡፡ ዝርዝር ችግሮቻቸው ምንድናቸው የሚለውን አሁን ማወቅ አይቻልም መንሥኤውንም እንዲሁ የአጥኚዎቹ ሥራ ነው፡፡ ለሚቀጥለው ጥቅምት የጥናቱ ውጤት ይታያል ማለት ነው፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- ኮሚቴ መዋቀሩና ጥናት መካሔዱ ለችግሩ መፍትሔ ያመጣል ብለው ያስባሉ?

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፡- አዎ ያመጣል ጉዳዩ ሰፋ እያለ ሲሔድ ሁለቱንም አካላት የሚያወዛግባቸው ነገር ግልጥ እያለ ይሔዳል፡፡ ጉባኤውም የጥናት ውጤቱን ተከትሎ የሚሰጠው ውሳኔ መፍትሔን ያመጣል ብዬ አምናለሁ፡፡ ከሕግ ስሕተትም ካለ እየታረመ፣ ማስጠንቀቂያም እየተሰጠ ችግሮች እየወጡ መወያየት የሚቻልበትን ሁኔታ መፍጠር ይገባል፡፡ ማመንም ማሳመንም ይገባል፡፡ ይህ የአሠራር ሒደት ነው፡፡ ስለዚህ ማደራጃ መምሪያው ዋናው ሥራው ወጣቱ ላይ ነው፡፡ አይደለም ያሉትን እና የተያዙትን ሌሎችንም ወጣቶች ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ መሳብ ይገባዋል፡፡ ካሉት ጋራ ውዝግብ ከመፍጠር አገልግሎት ላይ ትኩረት ማድረግ የተሻለ ነው፡፡ ተገቢው ነገር ደንብና ሥርዓት ተከብሮ በመነጋገር ጥቃቅን ችግሮችን መፍታትና ወጣቱን መያዝ የሚገባ ነው፡፡ ሌሎችን ለማምጣት እያሰብን ያሉትን እንዳናጣ መጠንቀቅ ይኖርብናል፡፡ ይህንን ቀላል ጉዳይ ተነጋግረን መፍታት ካልቻልን ሑከት ፈጣሪዎች እኛው ነን ማለት ነው፡፡ ይህ በጣም ለልማት እንቅፋት መሆን ማለት ነው፡፡ እኛ መርዳት እና ለሰላም አስተዋጽኦ ማድረግ ሲገባን እንዲህ ውዝግብ ውስጥ መግባቱ አግባብ አይደለም፡፡ ዓለም እየሮጠ ነው፡፡ ሕዝቡን በሰላምና በፍቅር አሰልፈን መጓዝ አለብን፡ ዋናው ትኩረታችን ወጣቱ ነው፡፡ እነርሱ ላይ መሥራት አለብን ይህ የተደራጀው ኃይል ለሀገርም ለቤተ ክርስቲያንም ጠቃሚ ኃይል ነው፡፡ በአእምሮው፣ በገንዘቡ፣ በጉልበቱ ሀገሩን እና ቤተ ክርስቲያንን የሚያለማውን ወጣት ማገዝ ይገባል፡፡ መምራት ይገባል፡፡ እነርሱ ዘንድ ጥፋት ካለ በእኛ ምክርና ግሳጼ ይታረማሉ ብለን እናምናለን፡፡

ስምዐ ጽድቅ፡- በመጨረሻ የሚያስተላልፉት መልእክት አለ?

ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ፡- ሰላም ለሁሉም ወሳኝ ነው፡፡ ሰላም ብለን ስንናገር ቀላል ነው፡፡ ወደ ሥራው ስንገባ ያደክማል፡፡ ሰው ራሱን ለሰላም ማዘጋጀት አለበት፡፡ ስለዚህ ሁለቱም አካላት ለዚህ ተገዢ መሆን አለባቸው፡፡ ደንቡ ሥርዓቱ ሊገዛቸው ይገባል፡፡ ለዚህ መቻቻል መከባበር ይገባል፣ የግል ጉዳይ የለም ሁሉም የሚሠራው ለቤተ ክርስቲያኒቱ ነው፡፡ አጀንዳችን ሁሉ ቤተ ክርስቲያን መሆን አለበት፡፡ ሰላም ካለ ለመደመጥም፣ ለማዳመጥም ለመምራትም ለመመራትም ይበጃል፡፡ የሁለቱም ወገን ሓላፊዎች ለዚህ ተገዢ መሆን አለባቸው፡፡ ያለ ኘሮግራም የሚሠራ ነገር ሁሉ ዋጋ የለውም፡፡ ሁሉም በፕሮግራም መመራት አለባቸው፡፡ ሁለቱም በመመሪያ እና በሕግ ቢመሩ ክብር አላቸው፣ ተወዳጅነት አላቸው፣ ውጤታማ ሥራም ይሠራል፣ ግንኙነታቸውም ይጠብቃል፡፡