‹‹መኑ ውእቱ ገብር ኄር፤ ታማኝ አገልጋይ ማነው?››

በመ/ ምስጢረ ሥላሴ ማናየ

መጋቢት ፲፮ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስያሜ የዐቢይ ጾም ስድስተኛው እሑድ ወይም ሳምንት ‹ገብር ኄር› ይባላል፡፡ ሰያሜውን የሰጠውም ኢትዮጵያዊ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ነው፡፡ ከአምስቱ መጻሕፍቶቹ አንዱ በኾነው ጾመ ድጓ መጽሐፍ ሳምንቱን የዐቢይ ጾም ሳምንታት ስያሜዎች ከነሥርዓተ ማኅሌቱ አዘጋጅቷል፡፡ ስለዚህ በስድስተኛው የዐቢይ ጾም ሳምንት ከዋዜማው ቅዳሜ ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን የሚዘመረው ዝማሬ፣ የሚሰበከው ስብከት፣ የሚሰጠው ትምህርት ገብር ኄርን የሚያወሳ ነው ማለት ስለ ታማኝ አገልጋይ የሚያስረዳ ነው፡፡ በማቴዎስ ወንጌል ፳፭፥፲፬-፳፭ የተገለጸውና በዕለቱ የሚነበበው ወንጌል የሚነግረንም ይህንኑ ትምህርት ነው፡፡

አንድ ባዕለ ጸጋ ሰው ባሪያዎችን ጠርቶ ለአንዱ አምስት መክሊት ሰጠው፣ ሁለት መክሊት የሰጠውም አለ፣ አንድ መክሊትም የሰጠው አለ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደሩቅ አገር ሔደ፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለውም ወጥቶ ወርዶ ሌላ አምስት አትርፎ ዐሥር አደረገ፡፡ ሁለት የተቀበለውም አትርፎ አራት አደረገ፡፡ አንድ የተቀበለው ግን መሬቱን ቆፍሮ በሻሽ ጠቅልሎ የጌታውን መክሊት ቀበራት፡፡ ከብዙ ጊዜ በኋላ ጌታቸው መጥቶ ተቆጣጠራቸው፡፡ አምስት መክሊት የተቀበለው ቀርቦ ‹‹ጌታዬ አምስት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ አምስት አተረፍኩ›› አለው፡፡ ‹‹ገብር ኄር ወምዕመን ዘበውሁድ ምእምነ ኮንከ ዲበ ብዙህ እሰይመከ ባእ ውስተ ፍሥሐሁ ለእግዚእከ፤ አንተ ታማኝ ባሪያ! በጥቂቱ ታምነሃልበብዙ እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡ ሁለት የተቀበለውም ቀርቦ ‹‹ጌታዬ ሁለት መክሊት ሰጥተኸኝ ነበር እነሆ ወጥቼ ወርጄ ሌላ ሁለት አትርፌ አራት አድርጌአለሁ፤›› ብሎ መክሊቱን አቀረበ፡፡ ጌታውም፡- ‹‹አንተ ታማኝ በጎ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃልበብዙ እሾምሃለሁ፡፡ ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አለው፡፡

አንድ መክሊት የተቀበለው ግን ‹‹ጌታዬ፣ አንተ ክፉና ጨካኝ፤ ካልዘራህበት የምታጭድ፤ ካልበተንህበት የምትሰበስብ፤ እንደ ኾንክ ስለ አወቅሁ መሬቱን ቆፍሬ ቀበርኋት እነኋት መክሊትህ›› አለው፡፡ ‹‹አንተ ሰነፍ ባሪያ! መክሊቴን በጊዜ ልትሰጠኝ በተገባህ ነበር፡፡ እኔም ወጥቶ ወርዶ ለሚያተርፍ በሰጠሁት ነበር፤›› አለና ‹‹ኑ፤ የዚህን ሐኬተኛ መክሊት ውሰዱና ዐሥር መክሊት ላለው ስጡት፡፡ላለው ይሰጡታል ይጨመርለታል ለሌለው ግን ያለውን ይቀሙታል›፡፡ ንዑ ይህን ሰነፍና ሐኬተኛ ባርያ እጅ እግሩን አሥራችሁ ጽኑ ጨለማ ወደ አለበት ውሰዱት! ጩኸትና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ጨምሩት!›› የሚል ፍርድ ወሰነበት፡፡

ባዕለ ጸጋ የተባለው ጌታ ነው፡፡ መክሊት የተባለው ልዩ ልዩ የአገልግሎት ጸጋ ነው፡፡ ያተረፉት በሚገባ በታማኝነት ያገለገሉ ቅዱሳን ሰዎች ናቸው መክሊቱን የቀበረው ደግሞ በታማኝነት በተሰጠው ጸጋ ማገልገል ሲገባው ያላገለገለ ነው፡፡ ጌታቸው ሊቆጣጠራቸው መጣ ማለት ጌታችን በዕለተ ምጽአት ለዅሉም በሠራው ምግባር መጠን ዋጋ ለመስጠት እንደሚመጣ ያሳየናል፡፡ ያገለገሉትን ‹‹ወደ ጌታህ ደስታ ግባ!›› አላቸው ማለት ታማኝ አገልጋዮች መንግሥተ ሰማያትን ይወርሳሉና፡፡ ሰነፉ አገልጋይ ወደ ጨለማና ጥርስ ማፋጨት ወዳለበት ቦታ መወርወሩም ኀጥአን ወደ ሲኦል መግባታቸውን የሚያሳይ ነው፡፡

ከላይ ያነሳነው የቅዱስ ወንጌል ቃል፡- ‹‹ታማኝ አገልጋይ ማነው?›› ይላል፡፡ ይህ እያንዳንዱ በአርአያ እግዚአብሔር የተፈጠረ የሰው ልጅ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ አምላካዊ ጥያቄ ምላሽ መስጠት ከሰው ልጆች ይጠበቃል፡፡ ከዚህ ቀጥለን በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪካቸው ከተመዘገበላቸው ታማኝ አገልጋዮች መካከል ሦስቱን ጠቅሰን ከእነርሱ ሕይወት እንድንማር የሚያነሣሣ መጠነኛ ትምህርት እናቀርባለን፤

ሙሴ

ሊቀ ነቢያት ሙሴ ታማኝ አገልጋይ መኾኑን ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፤ ‹‹በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ ወይም በሕልም አናግረዋለሁ፡፡ ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም እርሱ በቤቴ ዅሉ የታመነ ነው፤›› እንዲል (ዘኍ.፲፪፥፮)፡፡ ይህ የፍጡር ቃል ሳይኾን በፈጣሪው የተሰጠ ምስክርነት ነው፡፡ በውኑ በዘመናችን እንኳን ፈጣሪ ፍጡራን ታማኝነቱን የሚመሰክሩለት አጋልጋይ ይኖር ይኾን? እንጃ! የሙሴን ታማኝ አገልጋይነት በረኃ፣ ስደት፣ መከራ፣ የፈርዖን ግርማ እና ቁጣ አልበገረውም፡፡ ዐርባ ዓመት ስለ ወንድሞቹ በመሰደድ ዐርባ ዓመት ደግሞ የተሰደደላቸው ወንድሞቹን በመምራት፣ ባሕር በመክፈል፣ ጠላት በመግደል፣ መና በማውረድ፣ ደመና በመጋረድ ውኃ ከዓለት አፍልቆ በማጠጣት መከራውን ከወገኖቹ ጋር በመቀበል የቀኑን ኃሩር፣ የሌሊቱን ቁር (ብርድ) ታግሦ በታማኝነት አገልግሏል፡፡ ታማኝነቱም እስከ ሞት ድረስ ነበር፡፡

‹‹ሙሴም ወደ እግዚብሔር ተመልሶወዮ እኒህ ሕዝብ ታላቅ ኃጢአት ሠርተዋል፡፡ ለራሳቸውም የወርቅ አማልክት አድርገዋል፡፡ አሁን ይህን ኀጢአታቸውን ይቅር በላቸው፤ ያለዚያ ግን ከጻፍከው መጽሐፍ እባክህ ደምስሰኝ? ከባለሟልነትህ አውጣኝ?›› ተብሎ ተጽፏል (ዘፀ.፴፪፥፴፩)፡፡ ታማኝ አገልጋይ የሚባለው እንደ ሙሴ ‹‹እኔ ልሙት ሌሎች ይዳኑ›› የሚል ሰው ነው፡፡ አሁን የምናየው ግን ፈጽሞ ከዚህ የተለየ ነው፡፡ ‹‹ሰዎች ይሙቱ፤ እኔ ልኑር፡፡ ሰዎች ጦም ይደሩ፤ እኔ ልብላ፡፡ ሰዎች ይራቆቱ፤ እኔ ልልበስ፡፡ ሰዎች ይዘኑ፤ እኔ ልደሰት›› ነው፡፡ ይህም ታማኝ አገልጋይ ያለ መኾን መገለጫ ነው፡፡ ታማኝ አገልጋይ ለሚያገለግላቸው ሰዎች ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥ እንጂ የራሱን ጥቅም የሚያስቀድም አይደለም፡፡

ዛሬ በዓለማችን የምንመለከተው ድርጊት ግን ‹‹ጩኸት ለአሞራ መብል ለጅግራ›› የሚባለውን ዓይነት ነው፡፡ በታማኝ አገልጋዮች ድካም የሚሸለሙ፤ ታማኝ አገልጋዮች በሠሩት ሪፖርት የሚያቀርቡ፤ ባልሠሩት ሥራ የሚወደሱ፤ ከጥቅሙ እንጂ ከድካሙ መካፈል የማይሹ ጥቂቶች አይደሉም፡፡ እንቅፋት የሚመታው እግርን ነው፡፡ አክሊል የሚቀዳጀው ግን ራስ ነው፡፡ ታማኝ አገልጋይ ማለት እንደራስ አክሊል ዘውድ የሚጸፋ ብቻ ሳይኾን እንደ እግር እንቅፋቱን፣ እሾኹን፣ ውጣ ውረዱን፣ መከራውንና ድካሙን የሚቀበል ነው፡፡ በጥቅም ጊዜ ለራሱ በአካፋ የሚዝቅ፤ ሌሎች በጭልፋ የሚቆነጥር አይደለም፡፡ ሙሴ ባሕር የከፈለው፣ መና ያወረደው ደመና የጋረደው ውኃ ያፈለቀው ለራሱ አልነበረም፤ ለሚመራቸው ሕዝብ ነበር እንጂ፡፡ ታማኝ አገልጋይ ያሰኘውም ይኸው ነው፡፡ በዚህ ከብሮበታል፤ ተመስግኖበታልም፡፡

ዳዊት

ነቢዩ ዳዊት ዘመነ መሳፍንት አልፎ ዘመነ ነገሥት ሲተካ እስራኤልን በንጉሥነት እንዲመራ እግዚአብሔር ከበግ ጥበቃ የመረጠው ንጉሥ ነው፡፡ እርሱም በተሰጠው ሥልጣን ሳይታበይ በታማኝነት ሕዝበ እስራኤልን መርቷል፡፡ እግዚአብሔር ለሙሴ እንደ መሰከረው ዅሉ ስለ ለዳዊትም መስክሮለታል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር እንደ ልቡ የኾነ ሰው መርጧልናየዘይቱን ቀንድ ሞልተህ በልጆቹ መካከል ለእኔ ንጉሥ አዘጋጅቻለሁና ወደ እሴይ ወደ ቤተ ልሔም እልክሃለሁ፤›› ተብሎ እንደ ተጻፈ (፩ሳሙ. ፲፫፥፲፫፤ ፲፮፥፪)፡፡

በመዝሙረ ዳዊትም ‹‹ወረከብክዎ ለዳዊት ገብርየ ወቀባዕክዎ ቅብዐ ቅዱስ፤ ባሪያዬ ዳዊትን አገኘሁት የተቀደሰ ዘይትንም ቀባሁት›› ተብሎ ተነግሮለታል (መዝ. ፹፰፥፳)፡፡ ይህንንም አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ በመጽሐፈ ሰዓታት ድርሰቱ፡- ‹‹ረከብክዎ ለዳዊት ገብርየ ብእሴ ምእመነ ዘከመ ልብየ፤ አገልጋዬ ዳዊትን እንደ ልቤ የታመነ ሰውን አገኘሁት›› ሲል ተርጕሞታል፡፡ ንጉሥ ዳዊት ከመንገሡ በፊት የተገኘው በታማኝነት ነበር፡፡ ከነገሠ በኋላም ታማኝ ነበር፡፡ አሁን በዚህ ዓለም የምንኖር እኛ ግን በድኅነት ታማኝ እንኾንና ሀብት፣ ሹመት፣ ሥልጣን ሲመጣ ታማኝነትን እናጣለን፤ እንዲያውም ታማኝነትን እንንቀዋለን፡፡ መስረቅ ጀግንነት ይመስለናል፡፡ መዋሸት ሥልጣኔ ይኾንልናል፡፡

ዳዊት ሳይሾም በጎቹን በመጠበቅ ታማኝ ነበር፡፡ በጎቹን የሚነጥቅ ተኩላ አንበሳ ቢመጣ በኋላው ተከትሎ ነብሩን በጡጫ፣ አንበሳውን በእርግጫ ብሎ በጎቹን ያስጥል ነበር፡፡ ‹‹እኔ ባሪያህ የአባቴን በጎች ስጠብቅ አንበሳ ወይም ድብ ይመጣ ነበር፡፡ ከመንጋውም ጠቦት ይወስድ ነበር፡፡ በኋላውም እከተለውና እመታው ነበር፤ ከአፉም አስጥለው ነበር፡፡ በተነሣብኝም ጊዜ ጉሮሮውን አንቄ እመታውና እገድለው ነበር፡፡ ይህም ፍልስጥኤማዊ ከነዚያ እንደ አንዱ ይኾናል፤ እንግዲህ እገድለው ዘንድ፤ ከእስራኤል ተግዳሮትን አስወግድ ዘንድ ዛሬ አልሔድምን? የሕያው አምላክ ጭፍሮችን ይገዳደር ዘንድ ይህ ቆላፍ ምንድን ነው? ከአንበሳና ከድብ ያስጣለኝ እግዚአብሔር ከዚህ ያልተገረዘ ፍልስጥኤማዊ እጅ ያስጥለኛል!›› በማለት እርሱ እንደ ተናገረው (፩ኛሳሙ.፲፯፥፴፬)፡፡

ዛሬም ቢኾን በእስራኤል ዘነፍስ በምእመናን ላይ የሚገዳደሩ ብዙ ፍልስኤማውያን ተሰልፈዋል፡፡ እነዚህን ድል የሚነሣ፤ በጎቹን ምእመናን ከተኩላ፣ ከአንበሳና፣ ከድብ አፍ የሚታደግ ታማኝ አገልጋይ ማነው? ከምእመናን ተግዳሮት የሚያርቅ ፈጣሪዬ ከመከራ ያድነኛል ብሎ የሚታመን የኢ አማንያን ብዛት የማያስፈራው ማን ነው? ከትንሽነቱ እስከ ታላቅነቱ የታመነ አገልጋይ ማነው? ለተሾመበት ሓላፊነት ታማኝ ማነው? አሁንም ዓለማችን ከሥጋውያን ባለ ሥልጣናትም ኾነ ከመንፈሳውያን መሪዎች የምትሻው ታማኝ ሰው ነው፡፡ በሙስና ያልተዘፈቀ፤ ጉቦ አይኑን ያላጨለመበት፤ ለመንጋው አርአያና ምሳሌ የሚኾን ሰው፤ ታማኝ አገልጋይ ማለት እርሱ ነው፡፡ በመሐላ የተቀበለውን የአገልግሎት ሓላፊነት የማይዘነጋ ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ ሰባኪ፣ መምህር፣ ሐኪም፣ ዳኛ፣ ነጋዴ፣ ተማሪ፣ ወታደር፣ የቤት ሠራተኛ፣ የቢሮ ሠራተኛ ታማኝ መኾን አለበት፡፡

መንጋው በክህደት ሲጠፋ ዝም ብሎ የሚያይ ጳጳስ፣ ቄስ፣ ዲያቆን፣ መምህር፣ ሰባኪ፣ ታማኝ አይደለም፡፡ ታማሚው እየተሰቃየ የሚዝናና ሐኪም ታማኝ አይደለም፡፡ ፍርድ የሚያጎድል፤ ድሆችን የሚበድል፤ ለደሃ አደጎች የማይፈርድ ዳኛ ታማኝ አገልጋይ አይደለም፡፡ ቅቤ በሙዝ እና በድንች ቀላቅሎ፣ በርበሬ በሸክላ አፈር ጨምሮ፣ ሌሎችን አጭበርብሮ የሚሸጥ ነጋዴ ታማኝ አገልጋይ አይደለም፡፡ እየነገደ ያለው በሰው ሕይወት መኾኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ ዅሉም እንደየአቅሙ በተሰጠው የአገልግሎት ዘርፍ ታማኝ መኾን አለበት፡፡

ዮሴፍ

ዮሴፍ ለወንድሞቹ ምግባቸውን ተሸክሞ የእርሱ ስንቅ ቢያልቅ የወንድሞቹን ስንቅ ያልበላ በትንሹ የታመነ ሰው ነበር፡፡ ወንድሞቹ ሸጠውት በቤተ ጲጥፋራ በሚያገለግልበት ጊዜም ታማኝ ነበር፡፡ ታማኝነቱ በጲጥፋራ ቤት ጌታ አድርጎታል፡፡ ‹‹ዮሴፍ ተሸጠአገልጋይም ኾነ፡፡ እግሮቹ በእግር ብረት ሰለሰሉ፡፡ ሰውነቱም ከብረት አመለጠች፡፡ ቃሉ ሳይደርስ የእግዚአብሔር ቃል ፈተነው፡፡ ንጉሥ ላከ፤ ፈታውም የሕዝብ አለቃ አድርጎ ሾመው፡፡ የቤቱም ጌታ አደረገው፡፡ በገንዘቡ ዅሉ ላይ ገዢ አደረገው፡፡ አለቆቹን እንደ እርሱ ይገሥፅ ዘንድ፤ ሽማግሌዎችን እንደ እርሱ ጥበበኞች ያደርጋቸው ዘንድ፤›› ተብሎ እንደ ተነገረለት (መዝ.፻፬፥፲፯)፡፡

በዚህ ኹኔታ የነበረው ዮሴፍ የጌታው ሚስት ሲወጣ ባቱን፣ ሲገባ ደረቱን እያየች ዐይኗን ጣለችበት፤ በዝሙት አይን ተመለከተችው፡፡ ‹‹ከእኔ ጋር ተኛ›› እያለችም በየቀኑ አስቸገረችው፡፡ እርሱ ግን ‹‹እምቢ›› አላት፡፡ ለጌታው ሚስትም፡- ‹‹እነሆ ጌታዬ በቤቱ ያለውን ዅሉ ለእኔ በእጄ አስረክቦኛል፡፡ በቤቱ ያለውን ምንም የሚያውቀው የለም፡፡ በዚህ ቤት ከእኔ የሚበልጥ ሰው የለም፡፡ ሚስቱ ስለ ኾንሽ ከአንቺ በቀር ያልሰጠኝ ነገር የለም፡፡ እንዴት ይህን ትልቅ ክፉ ነገር አደርጋለሁ? እንዴትስ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአትን እሠራለሁ?›› በማለት የዝሙት ጥያቄዋን ውድቅ አደረገባት (ዘፍ.፴፱፥፯)፡፡

በዮሴፍ ታማኝነት የጌታው ቤት ተባርኳል፡፡ ሀብቱ በዝቷል፡፡ በታማኝነቱ በቤቱ ያለውን ዅሉ ተረክቦ ነበር፡፡ የቀረበለት ፈተና ግን ከባድ ነበር፤ ኾኖም ግን በታማኝነቱ ለማለፍ ችሏል፡፡ ዮሴፍ በታማኝ አገልጋይነቱ በመጣበት መከራ ቢታሰርም እንኳን ያለ ሹመት አላደረም፤ የእስረኞች አለቃ ነበር፡፡ ከእስር ቤት ሲወጣም ግብጽን በሙሉ መርቷል፡፡ በግብጻውያን ላይ ተሾሟል፤ በጥቂቱ ታምኗልና፡፡ ‹‹በጥቂቱ የታመነ በብዙ ይሾማል›› እንዲል (ማቴ.፳፭፥፳፬)፡፡ዛሬ በእየአንዳንዱ ጓዳ እንደ እሳት የሚያቃጥሉ አገልጋዮች ናቸው ያሉት፡፡ ልጅ በፈላ ውኃ የሚቀቅሉ ናቸው የሚበዙት፡፡ እንኳን በዅሉ ገንዘብ ለመሾም በጥቃቅን ዕቃዎች እንኳን የሚታመን ሰው ጠፍቷል፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ፡- ‹‹አቤቱ አድነኝ፤ ደግ ሰው አልቋልና፡፡ ከሰው ልጆችም መተማመን ጎድሏልና፤›› በማለት እንደ ተናገረው በመካከላችን መተማመን የለም (መዝ.፲፩፥፩)፡፡

እናም ከእነዚህ ሦስት ታማኝ አገልጋዮች (ሙሴ፣ ዳዊት እና ዮሴፍ) ሕይወት ዅሉም የሰው ልጅ ታማኝ አገልጋይነት የሚያሰጠውን ክብርና ጸጋ ተመልክቶ በታማኝነት ማገልገል ይገባዋል፡፡ ታማኝ መኾን መጀመሪያ የሚጠቅመው ራስን ነው፤ ከዚያ በኋላ ለአገር፣ ለወገን፣ ለቤተ ክርስቲያን፣ ላመኑትም ላላመኑትም ዅሉ ጠቃሚ ይኾናል፡፡ በመጨረሻም የጽድቅ አክሊልን ይቀዳጃል፤ መንግሥተ ሰማያትን ያወርሳል፡፡ ታማኝነት በሰውም፣ በእግዚአብሔርም ፊት ያስከብራልና፡፡ ጻድቃን፣ ሰማዕታት ቅዱሳን በታማኝነት በማገልገላቸው ፈጣሪአቸውን ደስ አሰኝተው ከብረዋል፡፡

በሓላፊው ገንዘብ ያልታመኑት እነይሁዳ፣ ሐናንያ እና ሰጲራ የደረሰባቸውን ጉዳት አይተናል፡፡ አካን ወልደ ከርሚንም ተመሳሳይ ቅጣት ደርሶበታል (ሐዋ.፭፥፩-፳፭)፡፡ ስለ ኾነም ዅሉም በተሰማራበት የአገልግሎት መስክ ታማኝ አገልጋይ ኾኖ ‹‹አንተ በጎ ታማኝ አገልጋይ በጥቂቱ ታምነሃል፤ በብዙ እሾምሀለሁ፤›› የሚለውን የጌታውን የምስጋና ቃል ለመስማት ተዘጋጅቶ መጠበቅ ይገባዋል፡፡ መልካም አገልግሎት አገልግለን፣ በእግዚአብሔር ‹አግብርት ኄራን፤ ታማኝ አገልጋዮች› እንድንባል፤ መንግሥቱንም እንድንወርስ አምላካችን ይርዳን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡