ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ የእሳት ቃጠሎ ደረሰበት

በዲያቆን ኤፍሬም የኔሰው

ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም

sebeta

የተቃጠለው ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ወለልና የሕንጻው ቍሳቍስ በከፊል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሰበታ ወረዳ ቤተ ክህነት የሚገኘውና በጥር ወር ፳፻፮ ዓ.ም የተመሠረተው የሰበታ ዋታ ምዕራፈ ቅዱሳን አቡነ አረጋዊ እና በዓታ ለማርያም ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ታኅሣሥ ፳፬ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ከጠዋቱ ፪ ሰዓት ከ፴ ደቂቃ አካባቢ የእሳት ቃጠሎ ደረሰበት፡፡

ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ በቆርቆሮና በኮምፖርሳቶ ከመታነጹ በተጨማሪ ቃጠሎው የደረሰው ካህናቱ አገልግሎታቸውን ፈጽመው ከቤተ ክርስቲያን ከወጡ በኋላ መኾኑ ጉዳቱን የከፋ አድርጎታል፡፡

የቃጠሎው መንሥኤ እስካሁን በግልጽ እንዳልታወቀና በቃጠሎውም ከጽላቶቹ በስተቀር ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ሙሉ በሙሉ እንደ ወደመ የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መልአከ ሕይወት ሐዋዝ ተስፋ ለማኅበረ ቅዱሳን ሚድያ ክፍል አስታውቀዋል፡፡ እንደ አስተዳዳሪው ገለጻ ከአምስት መቶ ሺሕ ሰማንያ ብር በላይ የሚገመቱ ንዋያተ ቅድሳት በቃጠሎው ወድመዋል፡፡

sebeta-copy

በቃጠሎው የወደሙ ንዋያተ ቅደሳት በከፊል

የማኅበረ ቅዱሳን ጋዜጠኞች ቦታው ድረስ በመሔድ እንደ ተመለከትነው ታኅሣሥ ፳፭ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም ረፋድ ላይ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በደብሩ ተገኝተው ማኅበረ ካህናቱንና ሕዝበ ክርስቲያኑን አጽናንተዋል፤ የደብሩን ይዞታ የሚያስከብርና ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን የሚያስገነባ የልማት ኰሚቴም አስመርጠዋል፡፡ እንደዚሁም የሰበታ ወረዳ ቤተ ክህነት ሠራተኞች፣ የየአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናትና ማኅበረ ምእመናን ለሕንጻው ማሠሪያና ለንዋያተ ቅድሳት መግዣ የሚኾን ገንዘብ በማሰባሰብ ለልማት ኰሚቴው አበርክተዋል፡፡

አቡነ ሳዊሮስ

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ

ብፁዕነታቸው በዕለቱ ቃለ ምዕዳን ሲሰጡ የልማት ኰሚቴው ከሐሜት በጸዳ መልኩ የማያድግምና ዘላቂ የኾነ ሥራ መሥራት እንደሚጠበቅበት ተናግረዋል፡፡ አያይዘውም ለሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ ብቻ ሳይኾን ለሃይማኖታችን መጠበቅና ለምእመናን አንድነትም ዘብ መቆም ይገባዋል ብለዋል፡፡

‹‹ይህ ዅሉ የደረሰው በእኛ ኀጢአት ነው›› ያሉት ብፁዕነታቸው የደብሩ አገልጋይ ካህናትና የአካባቢው ምእመናን ጥላቻንና መለያየትን በማስወገድ፤ ከኀጢአት በመራቅ፤ በፍቅር፣ በሰላምና በአንድነት በመኾን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በቅንነት እንዲያገለግሉ አባታዊ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ በቃለ ምዕዳናቸው ማጠቃለያም በደብሩ ላይ የደረሰውን የእሳት ቃጠሎ ከማጥፋት ጀምሮ መቃኞ ቤት በመሥራትና በሌላም ልዩ ልዩ መንገድ ድጋፍና ትብብር ያደረጉትን ምእመናንና በአካባቢው የሚኖሩ የእስልምና እምነት ተከታዮችን አመስግነዋል፡፡

መቃኞ

በአካባቢው ነዋሪዎች ትብብር የታነጸው መቃኞ ቤት

በቤተ ክርስቲያኑ ላይ የደረሰውን የቃጠሎ አደጋ ሰበካ ጉባኤው ለፖሊስ ሪፖርት እንዳደረገና በቃጠሎው ዕለትም የሰበታ ወረዳ ኮማንድ ፖስት፣ የጸጥታ ዘርፍ ሠራተኞችና ሌሎችም የመንግሥት ባለሥልጣናት እንደ ተገኙ የተናገሩት አስተዳዳሪው የቃጠሎው መንሥኤ እስኪጣራ ድረስም የደብሩ ሰሞነኛ ካህናትና የጥበቃ ሠራተኞች በሕግ ከለላ ሥር ይገኛሉ ብለዋል፡፡

አማንያንም ኾኑ ኢአማንያን የአካባቢው ነዋሪዎች በጋራ በመረባረብ ለታቦተ ሕጉ መቀመጫ የሚኾን ጊዜያዊ መቃኞ ቤት ማነጻቸውን ያስታወቁት የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ እንደ ገና ታድሶ አገልግሎት ይሰጥ ዘንድም የመላው ሕዝበ ክርስቲያን ድጋፍና ርዳታ አይለየን ሲሉ በቤተ ክርስቲያን ስም ጥሪያቸውን ያቀርባሉ፡፡