የ፳፻፲፯ ዓ.ም ፵፫ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ዓለም አቀፍ መደበኛ ጉባኤ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ

የ፳፻፲፯ ዓ.ም ፵፫ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ዓለም አቀፍ መደበኛ ጉባኤ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ

፵፫ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ዓለም አቀፍ መደበኛ ጉባኤ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ጠቅላይ ቤተ ከህነት አዲሱ አዳራሽ ከጥቅምት ፮ – ፲ ቀን ፳፻፲፯ ዓ.ም በማካሄድ ፳ ዋና ዋና ነጥቦችን ያካተተ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቀቀ፡፡ የአቋም መግለጫውን እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የ፵፫ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ዓለም አቀፍ መደበኛ ጉባኤ የአቋም መግለጫ

“ትውልደ ትውልድ ይንእዱ ምግባሪከ ወይዜንዉ ኃይለከ፤ የልጅ ልጅ ሥራህን ይናገራሉ፤ ያመሰግናሉ፣ ከሃሊነትህን ይናገራሉ ያስተምራሉ፡፡” (መዝ. ፻፵፬፥፬)

፩. በጉባኤው መክፈቻ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ያስተላለፉፉልንን ቃለ ምዕዳንና ቃለ ቡራኬ ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ተቀብሎታል፣ ለተግባራዊነቱ ቃል ይገባል፡፡

፪. ብፁዕ አቡነ አብርሃም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የባሕር ዳርና የሰሜን ጎጃም አህጉረ ሰብከት ሊቀ ጳጳስ ያስተላለፉልንን አባታዊ መልእክት ጉባኤው በሙሉ ድምጽ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል እንገባለን፡፡

፫. በብዙ የሀገራችን ክፍል ባለው የሰላም እጦት የተፈጠሩት ዘርፈ ብዙ ችግሮች ምክንያት የካህናት፣ የመነኮሳትና የምእመናን ሞትና ስደት በጥብቅ እያወገዝን በዚህ ታሪክ የማይረሳው በምድር ወንጀል፣ በመንፈሳዊው ዓለምና በሰማይ ኃጥያት የሆነ እኩይ ተግባር የተሰማራችሁ ሁሉ ወደ ርኃራኄ ልብ እንድተመለሱ ጉባኤው በአጽንኦት ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

፬. የሰላም ዕጦት ጉዳይ ምንም እንኳ ዓለም አቀፍ ቢሆንም ሀገራችንም በተከሰተው ግጭትና ጦርነት ምክንያት ሰላም ካጣች ሰንብታለች፣ ስለሆነም ቅዱስ ሲኖዶስ በዓለም የሚደነቅ፣ ለሀገር ተገን የሚሆን አስደነቂ ውሳኔ እንደሚወስን ተስፋችን ጽኑ ነው፣ ጸሎታችንም ነው፤ የአገልጋዮች እንባ የሚታበስበት፣ ለነገ ታሪክ የትውልድ ተወቃሽ ከመሆን ይልቅ፤ የሰላምና እርቅ ምሳሌ የምንሆንበት ከፍተኛ የሰላም ሥራ ልዩ የሆነ የሰላም ኮሚቴ ተቋቁሞ ዘላቂ ሰላምን ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የሚያመጣ ሥራ እንዲሠራ ጉባኤው ያሳስባል፡፡

፭. የዚህን ዓለም ተድላ ንቀው፣ ዳዋ ለብሰው ጤዛ ልሰው በገዳም ተወስነው ድምጸ አራዊቱን ግርማ ሌሊቱን ታግሰው ለመላው የሰው ዘር የሚጸልዩ ይህን ይደግፋሉ ያንን ይቃወማሉ የማይባሉ ገዳማውያን መነኮሳት ከየበዓታቸው ተጎትተው ወጥተው የተገደሉበት ሁኔታ በሀገራችን መከሰቱ ጉባኤውን እጅግ አሳዝኖታል፤ ይህ ጉዳይ ቀጣይነቱ እየታየ ስለሆነ የሚመለከታቸው ሁሉ ተገቢውን የሕግ ሥራ በመሥራት የሰው ልጅ ከአምላክ የተሰጠውን የመኖር መብት፣ የእምነት ነፃነት፣ የመዘዋር ተፈጥሯዊና ሰብዓዊ መብት በሀገራች እንዲከበር ያሳስባል፡፡

፮. በታሪካችን ያላየነው ከአባቶቻችን ያልሰማነው በመጻሕፍት ያላነበብነው ከኢትዮጵያ ባሕልና ሥነ ልቡና ውጪ በሆነ መንገድ ሰዎችን ለገንዘብ ሲባል ማገት በተለይም ፊትና ኋላ፣ ግራና ቀኝ፣ እሳትና ውኃ ያለዩ ሕጻናት በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው፣ ወጣቶችና አረጋውያን ሳይቀር እያተገቱ የሚሰቃዩበትና የሚደፈሩበት ሁኔታ የገጠመንን ፈተና ክብደቱን የሚያሳይ መሆኑ ይህ ጉዳይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መፍትሔ እንዲበጅለት ጉባኤው ጥሪውን ያቀርባል፡፡

፯. ጥላቻና የጥፋት ቅስቀሳዎች፣ በዜጎች መካከል አለመተማመንና መለያየት፣ ለሀገር አንድነትና የሕዝብ አብሮነት ጠንቅ፣ ለወደፊቱ አስጊ የሆኑ እንቅስቃሴዎች የበዙበት፣ የትውልዱ የወደፊት በሰላምና በተረጋጋ ሁኔታ የመኖር ዋስትና እየጠፋ፣ በርካታ ወጣቶች በስደትና በመፈናቀል ላይ ያሉበት ሁኔታ በመኖሩ የጥላች ንግግር፣ ዘለፋና ያልተገባ ትችትና መናናቅ ማንንም የማያንጽ ክፉ ትምህርት፣ ለሀገርም፣ ለሕዝብም የማይጠቅም ሁሉንም የሚያጠፋ ስለሆነ በእንዲህ ያለ ተግባር መገናኛ ብዙኃን በመጠቀም የተሰማራችሁ፣ ሁሉ በሚያፋቅርና በሚያዋድድ ተግባር እንድትሰማሩ ጉባኤው ጥሪውን ያቀርባል፣ ቅዱስ ሲኖዶስም ለዚሁ ትኩረት ሰጥቶ መመሪያና ውሳኔ ያወጣ ዘንድ በአጽንኦት እንጠይቃለን፡፡

፰. በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ ፳ በእንተ ሰማዕታት የጌታችንን ትምህርት መሠረት በማድረግ በተሠራው ቀኖና ካህናትና ምእመናን ሰማዕትነትን የተቀበሉበትን ቀን መዘከርና ማክበር፣ የከበረ አጽማቸውን በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን በክብር ማስቀመጥ፣ ቤተሰቦቻቸውንና በእነሱ ሥራ ይተዳደሩ የነበሩ የሰማዕታት ቤተሰብ በሚል መርዳት የተደነገገ ቀኖና ነው፤ ይህን በማድረግ የሰማዕትነት ዋጋን እናገኛለን፣ ቤተ ክርስቲያነን እናጸናለን፤ በዚህ ቀኖና መሠረትና ከሰብዓዊ ርኅራሄ በመነሣት በሰማዕትነት የተለዩን ወገኖች መታሰቢያቸው እንዲደረግ፣ ቤተሰቦቻቸውና ጉዳተኞችን ወላጆቻውን ያጡ የካህነትና የምእመንና ጨቅላ ሕጻናትና ያልደረሱ ልጆች፣ ያለጧሪ የቀሩ አረጋውያን የቤተ ክርስቲያንን እንክብካቤ በጥብቅ ይፈልጋሉ፤ ለዚህ መፍትሔ እንዲሆን በውጭና በሀገር ውስጥ ያሉ አህጉረ ሰብከት ያካተተ አስቸኳይ ዓለም አቀፍ ግብረ ኃይል እንዲቋቋም ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ እንዲሰጥበት እያሳሰብን ለተግባራዊነቱም ሁላችንም ቃል እንገባለን፡፡

፱. በአንዳንድ አካባቢዎች ሕግንና የአምልኮ ነፃነት ሰብዓዊ መብትን በመጣስ የመስቀል ደመራና የባሕረ ጥምቀት ቦታ መወሰድ ሃይማኖታዊ አለባበስና መስቀል መያዝን በመከልከል የአንገት ማዕተብን መበጠስ፣ በኦርቶዶክሳውያን ላይ እንግልትና ወከባ መፍጠር አሳዛኝ በመሆኑ ድገርጊቱን አጥብቀን እየተቃወመን በቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ ውይይት እንዲደረግበት ጉባኤው ያሳስባል፡፡

፲. ቤተ ክርስቲያን እንኳንስ ተናግራ ሰማች ሲባል የሚያስደነግጥ ግርማና መታፈር፣ መከበርና መወደድ የነበራት በመሠረተችው ሀገር የምትሳደድበት፣ የመሪዎቿ አባቶች ጥሪ የማይከበርበት፣ የሰላም ጥሪ ድምጽዋ የማይሰመባት፣ ምክንያቱ ምን እንደሆነ በመፈተሸ ክብርና ልዕልናዋ እንዲመለስ በቅዱስ ሲኖዶስ ቀርቦ ውይይትና ጥልቅ ምክክር እንዲደረግ መፍትሔም እንዲፈለግለት ጉባኤ ያሳስባል፡፡

፲፩. ሙስና፣ ዘረኝነት፣ ጎሠኝነት፣ ቡድነኝነት፣ አድሎዓዊነትና ግለኝት በተመለከተ በጋራ በአንድ ድምጽ በመነሣት ይህንን ክብረ ነክና አጋላጭ፣ ለቤተ ክርስቲያን እድገትና ለሐዋርያዊ ተልእኮ እንቅፋት፣ የቤተ ክርስቲያን ማንነት ለሌላቸው ግለሰቦች መደበቂያ፣ በጥቂት ግለሰቦች በደልና ጥፋት በንጽሕና በቅድስና የሚያገለግሉ፣ ካህናትንና ሠራተኞችን የሚያሳፍሩ፣ ምእመናንን የሚያሸማቅቁ በመሆናቸው እነዚህን ክፉ ደዌያት ስም አጠራራቸውን ከቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ለማስወገድ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ በጥናትና በቁርጠኝነት ላይ የተመሠረተ፣ የጥፋት በራቸውን በዘላቂነት የሚዘጋ ሥልት እንዲቀይስ ጉባኤው ያሳስባል፡፡

፲፪. በአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት እስከ አሁን ቤተ ክርስቲያን በፈረሱባት ሕንፃዎችና ቤቶች ምትክ ቦታ በመስጠት ጉዳቷን ለመቀነሰ የተደረገውን ጥረት ጉባኤው እያደነቀ፤ በተሰጡት ይዞታዎች ላይ በአጭር ጊዜ ግንባታውን በማካሄድ የአባቶችቻንን አሻራ መልሶ በመትከል፣ ይዞታውን ማስከበርና የተቋረጠውን ገቢ ማስቀጠል እንዲቻል ብርቱ ጥረት እንዲደረግ ጉባኤው እያሳሰበ፤ የኮሪደር ልማት የተባለው ጉዳይ በሌሎች የክልል ከተሞችም እየተስፋፋ ስለሆነ በቀጣይ ለሚነሡ የይዞታ ጥያቄዎች ለሚከሰቱ ችግሮች ከወዲሁ ዝግጅት እንዲደረግ፡፡

፲፫. አዳዲስ አማኞችን አሳምኖ ለሥላሴ ልጅነት ማብቃት፣ የአዳዲስ አብያተ ክርስቲያናት መተከል፣ መታነጽና መባረክ የታየው ስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልእኮ እመርታ ሁሉን ያስደሰተ በመሆኑ ከዚህ በበለጠ አጠናክረን ለመሥራት ቃል እንገባን፡፡

፲፬. የቅዱስ ባኮስ የቅድስና ዕውቅና ቤተ ክርስቲያን በታሪኳ ስትዘግበው የቆየ ቢሆንም ጽላት ተቀርፆ እንዲከበር መደረጉ አስደሳች ሲሆን ለሀገር በረከት፣ ለትውልድ የመንፈሳዊ ሕይወት አርአያ፣ ለቅድስና ፍኖት የሆኑ ነገርግን የማይታወቁ የሌሎች ኢትዮጵያውያንን ቅዱሳን ታሪክና ገድል በማጥናት እንዲዘከሩ እንዲደረግ ጉባኤው ያሳስባል፡፡

፲፭. በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ የተከፈቱ መንፈሳውያን ኮሌጆችና የካህናት ማሠልጠኛዎችም በአጥጋቢ ሁኔታ ሥራ መጀመራቸው፣ በዚህ ዘርፍ በእጥፍ እየጨመረ የመጣው ዕድገትና ውጤት ጉባኤው ያደነቀ ሲሆን ወደ ሥራ ለመግባት በሂደት ላይ ያሉት በርካታ መንፈሳዊ ኮሌጆች እየተስፋፉ ያሉ የአብነት ትምህርት ቤቶች፣ ዘመናዊ የትምህርት ተቋማት በአጠቃላይ ሁሉም ትምህርትን የሚመለከት ጉዳይ በትምህርት ኮሚሽን ተቋቁሞ ጥናት በማድረግ እንዲስፋፉ ጉባኤው ያሳስባል፡፡

፲፮. በሰላም መታጣትና በቀኖና ጥሰት ምክንያት መላው ወለጋ አህጉረ ስብከት ለበርካታ ወራት ከማእከሉ ጋር ያለው ግንኙነት ተቋርጦ ከቆየ በኋላ በቅርቡ በሀገረ ሰብከቱ ሊቀ ጳጳስ ወደ መዋቅር መመለሳቸው ጉባኤውን በእጅጉ አስደስቷል፤ ስለሆነም ቀሪ ሥራዎች ተጠናቀው የቤተ ክርስቲያን መዋቅር እንዲጠበቅ፣ በሌሎችም አካባቢዎች ለተፈጠሩት የመዋቅር ጥሰቶች ቀኖናዊ መፍትሔ እንዲበጅለት ጉባኤ ያሳስባል፡፡

፲፯. ሐዋርያዊትና የክርስቶስ አገልጋይ የሆነች ቤተ ክርስቲያን ቋንቋን በማክበር ታገለግልበታለች እንጅ በቋንቋም አትገደብም፤ ስለዚህ በልዩ ልዩ ቋንቋዎች ሐዋርያዊ ተልእኮ መፈጸሟ እንደተጠበቀ ሆኖ ለወደፊት የሁሉም መዓረገ ክህነት ሢመት፣ በየደረጃው ያሉ የአስተዳደር ሥራ የኀላፊነት ምደባዎች፣ መሠረት እምነትን፣ ቀኖና ቤተክርስቲያንን፣ ዕውቀትና ሙያዊ ብቃትን ብቻ መሠረት ያደረገ ይሆን ዘንድ ጉባኤው በጥብቅ ያሳስባል፡፡

፲፰. ሰበካ ጉባኤን ማጠናከር፣ ሰንበት ትምህርት ቤትን ማደራጀት፣ አብነት ትምህርት ቤቶች ማጎልበትና ማስፋፋት፣ ሕጎችና ደንቦችን በማዘጋጀት የተደረገውን ጥረት የሚያስመሰግን ሆኖ አሁን ወቅቱን የጠበቁ ሕጎችና ደንቦችን በማውጣት ሁሉም እንዲሠራበት ማድረግን፣ መልካም አስተዳደርን ማስፈን፣ የራስ አገዝ ልማትን ማሳደግና በገቢ ራስን መቻል፣ በጸደቀው የዐሥር ዓመቱ መሪ ዕቅድ መሥራት የቤተ ክርስቲያናችን ዓይነተኛ ተልእኮ በመሆኑ በሚሰጠው መመሪያ መሠረት ለመፈጸም ቃል እንገባለን፡፡

፲፱. የቤተ ክርስቲያናችን የውጭ ሀገር አገልግሎት እየሰፋና እያደገ መምጣቱ በጉልህ የሚታይ ሲሆን ይህ እድገትና አደረጃጀት እንዲጠናከር፤ በተጨማሪም ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተሳትፎ የበለጠ እንዲያድግ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሠራ ጉባኤው ያሳስባል፡፡

፳. ከውይይትና ከብፁዓን አበው መልእክቶች እንደተሰጠው መመሪያ የቤተ ክርስቲያንን ልዕልና ለመመለስ፣ ለሀገራንችን ሰላምና ደኅንነት ለሰው ልጆች ሁሉ መልካም ግንኙነት የጋራ ጸሎት በኅብረት ይደረግ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ እንዲሰጥበት ጉባኤ በአክብሮት ይጠይቃል፡፡

በመጨረሻም እስከ ዛሬ ስንሰበሰብበት ከነበረው መቃረቢያ አዳራሽ ወጥተን ይህ ዛሬ የተገኘንበት አዳራሽ በአጭር ጊዜ አሁን ባለበት ደረጃ እንዲህ ጸድቶና ተውቦ የ፵፫ኛውን አጠቃላይ ጉበኤ እንዲከናወንበት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ አመራር መስጠታቸው ቁርጠኝነት ካለ ብዙ መሥራት እንደሚቻል ያሳየ፣ የሥራ ክትትልና አፈጻጸም አድናቆታችንን በመግለጽ ሐዋርያው እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖርና እንዳለው የአዳራሹ ቀሪው ሥራ ተጠናቆ በቅርቡ እንደሚመረቅ ተስፋችንን እንገልጻለን፡፡

ይህ ጉባኤ በተሳካ ሁኔታ እንዲፈጸም ያደረጉ በቅዱስነታቸው አባታዊ ርእሰ መንበርነት፣ በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ በሳልና የተረጋጋ አመራር ሁሉም መርሐ ግብሮች በተያዘላቸው ሰዓትና ጊዜ ተጠናቀው እንዲፈጸሙ የመሩንን አባቶች በረከታችሁ ይድረሰን እያልን፡፡

የጉባኤው ዋና አዘጋጅ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ ዋና ኀላፊና መላው ሠራተኞች፣ ሁሉም ተባባሪ አካላት በገንዘብም በጉልበትም ትብብር ያደረጉ ሁሉ በአጠቃላይ ጉባኤው አመስግኗል፡፡

ከሁሉም በላይ ለዚህ ለ፵፫ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ዓለም አቀፍ መደበኛ ጉባኤ ያደረሰንና ያስፈጸመን የአባቶቻችን አምላክ ልዑል እግዚአሔር ምስጋና ይግባው አሜን፡፡ ሎቱ ስብሐት ወባርኰት ወጥበብ፣ ወአኰቴት፣ ወኃይል ወጽንዕ ለአምላክነ ለዓለመ ዓለም፤ አሜን!

አዲስ ዓመት እና ግቢ ጉባኤያት

ጥቅምት ፳፱ ቀን ፳፪፲፯ ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ከሰጣቸው በረከቶች መካከል ጊዜአቸውን ጠብቀው የሚፈራረቁ ወቅቶች ይገኙበታል፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ” (መዝ. ፷፬፥፲፩) እንዲል የበጋውን፣ የበልጉንና ክረምቱን ወቅቶች አፈራርቆ መጸው  ደግሞ ምድር በአረንጓዴና በልዩ ልዩ አበባዎች በምትደምቅበት በመስከረም ወር ሰዎችም የእግዚአብሔርን ቸርነት አድንቀውና አዲስ ተስፋን ሰንቀው “እንኳን አደረሳችሁ” በማለት ዓመቱ የተባረከ እንዲሆን የሚመኙበት ጊዜ ነው፡፡

አዲስ ዓመት ላይ ሆነን እግዚአብሔር በሰጠንና ባሳለፍነው ዓመት ምን ዐቅደን ነበር? የትኛውን አሳካን? የትኛውስ ቀረን? በሂደት ላይ ያሉትስ የትኞቹ ናቸው? በአዲሱ ዓመት ደግሞ ከደካማ ጎናችን ተምረን ራሳችንን ፈትሸን ያላጠናቀቅናቸው ዕቅዶቻችንን ጨምረን አዲስ ዕቅድ ለማውጣት ጥረት ማድረግ በብዙዎቻችን ዘንድ የተለመደ ተግባር ነው፡፡

አንዱን ስናሳካ ሌላውን መመኘት ሰዋዊ ባሕርይ እንደመሆኑ መጠን የተመኘናቸውን ሁሉ ማሳካት አንችልም፡፡ “ነገር ግን ሁሉን በአግባብና በሥርዓት አድርጉ” (፩ኛቆሮ. ፲፬፥፵) እንደተባለ ልናከናውናቸው የምንችላቸው ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ዐቅደን ለመፈጸም አቅማችንን ሁሉ መጠቀም ይገባል፡፡

ከዚህ አንጻር በዚህ ጽሑፍ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ላይ ትኩረት እናደርጋለን፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመማር ላይ የሚገኙና አዲስ ወደ ግቢዎች የሚገቡ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ትምህርትን ፍለጋ ከቤተሰብ መራቃቸውን በመገንዘብ ለትምህርታቸው ትኩረት እንደሚሰጡ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን እንዴት ማጥናት? መቼ ወደ ቤተ ክርስቲያን መሄድ? ኮርስ መቼ መማር፣ በተመደቡበት የአገልግሎት ክፍል ስብሰባ፣ አገልግሎት እንዴት በተቀናጀና በዕቅድ በተመራ መንገድ ማከናወን እንዳለባቸው ባለመረዳት ችግር ውስጥ ይገባሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ውጤት ርቋቸው ሕይወታቸው ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ሲያመራባቸው ይታያል፡፡ ይህንን ችግር ለማስወገድና ውጤታማ ሆኖ ለመውጣት ዕቅድ አስፈላጊ ነው የምንለውም ለዚህ ነው፡፡

በዕቅዶቻቸው ውስጥ ትምህርታቸው ላይ የሚወስዱት ጊዜን፣ የሚያጠኑበት፣ መንፈሳዊ ትምህርት የሚማሩበትና የጸሎት፣ እንዲሁም ከጓደኞቻቸው ጋር መረጃ የሚለዋወጡበት፣ ጊዜ መመደብና በዕቅዳቸው ውስጥ ማካተት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት እነዚህን ዕቅዶች ተግባራዊ ለማድረግ ቀጥሎ ያሉትን ነጥቦች መዘንጋት አይገባም፡-

፩. እግዚአብሔርን አጋዥ ማድረግ፡-

ከሁሉም ነገር በፊት ውጤታማ ሆነው ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም እንዲገቡ ያበቃቸውን አምላካቸውን ማመስገን፣ ከእርሱም ጋር ያላቸውን ቁርኝት ማጥበቅ የዕቅዳቸው አካል ሊሆን ይገባል፡፡ “እኔ የወይን ግንድ ነኝ፤ ቅርንጫፎቹም እናንተ ናችሁ፤ በእኔ የሚኖር እኔም በእርሱ፤ ብዙ ፍሬ የሚያፈራ እርሱ ነው፤ ያለ እኔ ምንም ማድረግ አትችሉምና” ተብሎ እንደተጻፈ ያለ እግዚአብሔር ፈቃድ ምንም ሊያደርጉ እንደማይችሉ በመረዳት ሁል ጊዜ እግዚአብሔርን ማስቀደም፣ እንደ ፈቃዱም መመላለስ ይጠበቅባቸዋል፡፡ (ዮሐ. ፲፭፥፭) በትምህርታቸውም በአገልግሎታችውም ከመታከት ርቀው እግዚአብሔር በጎ ምኞታቸውንና ጥረታችውን እንዲባርክላቸው ዘወትር ሌሊት ኪዳን በማድረስ፣ ማታም በአገልግሎት በመሳተፍ ከዓላማው ሳይናወጡ መጸለይ ያስፈልጋል፡፡ “እግዚአብሔር ቅርብ ነው፤ በምንም አትጨነቁ፤ ነገር ግን በሁሉ ነገር ጸልዩ፣ ማልዱም፤ እያመሰገናችሁም ልመናችሁን ለእግዚአብሔር ግለጡ” እንዲል   (ፊል. ፬፥፮)፡፡    

፪. ለትምህርታቸው ትኩረት መስጠት፡-

ወደ ከፍተኛ ትምህርት ለመግባታቸው ምክንያቱ ትምህርታቸው ላይ ትኩረት አድርገው ውጤታማ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ ከውጤት በኋላም ወላጅ ከእቅፉ ነጥሎ የሚልካቸው ነገ ራሳቸውን ችለው ቤተሰብን፣ ሀገርንና ቤተ ክርስቲያንን በጉልበታቸው፣ በዕውቀታቸውና በገንዘባቸው እንደሚደግፉ፣ በጎደለው በኩልም በመቆም ጎደሎን ይሞላሉ፣ ቀጥሎም የራሳቸውን ሕይወት ይመራሉ በሚል በጎ ሐሳብ ነው፡፡ ስለዚህ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የገቡበት ዋነኛ ዓላማ ጊዜአቸውን ለትምህርታቸው ቅድሚያ በመስጠት ውጤታማ ሆነው መገኘታቸው ነው፡፡ በግቢ ቆይታቸውም ክፍል ውስጥ መገኘት፣ በማስተዋል ትምህርታቸውን መከታተል፣ የሚሰጣቸውን የክፍል፣ የቤት ወይም የቡድን ሥራ ንቁ ተሳታፊዎች ሆነው በጥራት በመሥራት ለሌሎች አርአያ መሆን ይጠበቅባቸዋል፡፡

፪. የጥናት ጊዜን መመደብ፡-  

አንድ ተማሪ በየትኛውም የትምህርት ደረጃ ላይ ይገኝ የጥናት ጊዜ ሊኖረው ይገባል፡፡ በቀን ውስጥ ለጥናት የሚሆን ጊዜ መመደብ፣ ለዚያም ታማኝ በመሆን ከሌሎች ጉዳዮች በመራቅ የመደበውን ሰዓት በአግባቡ መጠቀም ያስፈልጋል፡፡ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ እስካለ ድረስ ማጥናት ግዴታው መሆኑን፣ ይህንንም በሥርዓትና በኃላፊነት መወጣት እንዳለበት ራሱን ማሳመን አለበት፡፡ እርሱ ጥናቱን አጠናቅቆ ሌሎች ጉዳዮችን ለማከናወን በሚዘጋጅበት ጊዜ ሌሎች ጓደኞቹ የራሳቸውን ጉዳዮች አጠናቀው መጥተው እናጥና ስላሉት፣ ወይም እንዝናና ቢሉት በይሉኝታ ታስሮ ከዐቀዳቸው ዕቅዶች ውጪ ማከናወን ወይም መጓዝ የለበትም፡፡ ለመደበው ጊዜና ላቀደው ዕቅድ ታማኝ መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ ለጥናት ልዩ ትኩረት በመስጠት ጊዜውን በአግባቡ መጠቀም ይገባል፡፡

፫. የጸሎት ጊዜ፡-

ክርስቲያን ከጸሎት የተለየ ሕይወት ሊኖረው አይገባም፡፡ በተለይም በግቢ ጉባኤ ውስጥ የሚሳተፉ ወንድሞችና እኅቶች በጸሎት የታገዘ ሕይወት ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በላከው መልእክቱ “በጸሎትና በምልጃ ሁሉ ዘወትር በመንፈስ ጸልዩ፤ ከዚህም ጋር ስለ ቅዱሳን ሁሉ ለመጸለይ ሁል ጊዜ ትጉ” በማለት ክርስቲያን ጸሎት መጸለይ እንደሚገባው ይናገራል፡፡ በጋራም ሆነ በግል ጸሎት ላይ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በመገኘት መንፈሳዊ ሕይወትን ማሳደግ ያስፈልጋል፡፡ (ኤፌ. ፮፥፲፰)   

ጸሎት በንጽሕና ሆነን ከእግዚአብሔር ጋር የምንገናኝበት መንፈሳዊ የሕይወት መንገድ ነው፡፡ ያለ ጸሎት መንፈሳዊ ሰው መሆን፣ በአገልግሎት መትጋት፣ መንፈሳዊ ፍሬዎችንም ማፍራት አይቻልም፡፡ ከጸሎት የተለየ ሕይወት የአጋንንትና የሠራዊቱ ማኅደር እስከ መሆን ያደርሳልና ዘወትር በጸሎት መትጋት ከአንድ ክርስቲያን ይጠበቃል፡፡

በግቢ ጉባኤ ውስጥ ትምህርታቸውን የሚከታተሉ ወጣቶችም ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት የጸሎት ጊዜ በመመደብ የሚገጥማቸውን ፈተና ሁሉ እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ በተጋድሎ ሊጸኑ ይገባል፡፡ ይህም በሥጋም በነፍስም ተረጋግተው ውጤታማ ሕይወት እንዲመሩ ያስችላቸዋል፡፡

፬. ለመንፈሳዊ አገልግሎት ጊዜ መስጠት፡-

አንድ በግቢ ጉባኤ ውስጥ የሚሳተፍ ተማሪ ለትምህርቱ ቅድሚያ ከሰጠ፣ የጥናት ጊዜውን መድቦ ተግባራዊ ካደረገ፣ ለጸሎት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ከተጋ ቀሪው በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ በመሳተፍ በተሰጠው ጸጋ ማገልገል ነው፡፡ አገልግሎትን በግቢ ውስጥ በአገልግሎት ላይ ልምድ ካካበቱ ወንድሞች ጋር በመሆን ከእነርሱም በመማርና ልምድ በመቅሰም ክርስቲያናዊ ግዴታውን መወጣትይገባዋል፡፡

ብዙውን ጊዜ በአንዳንድ የግቢ ጉባኤ ወንድሞችና እኅቶች ችግር ሆኖ የሚታየው ጊዜአቸውን ሁሉ ለአገልግሎት በማዋል በትምህርታቸው ሲደክሙ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ይህ የሚመነጨውም ጊዜአቸውን በአግባቡ ዐቅደው ባለመጠቀማቸው ምክንያት ስለሆነ በትምህርት ጊዜ ለትምህርታቸው፣ በጥናት ጊዜም ጥናታቸውን፣ በአገልግሎት ጊዜም አገልግሎታቸው ላይ ትኩረት በማድረግ ሳይጨናነቁ ሁሉንም አጣጥመው መጓዝ ይገባቸዋል፡፡

በአጠቃላይ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ውጤታማ ሆነው ለመውጣት በዕቅድ መመራትን ልምድ እንዲያደርጉና ለዐቀዱት ዕቅድ ደግሞ ታማኝ ሆነው በመገኘት ወደ ተግባር በመለወጥ በሥጋም በነፍስም ሊያተርፉ ይገባል፡፡ በዚህ አዲስ ዓመትም ካለፈው ስሕተት በመማር ስኬታማ የትምህርት ዘመንን ለማሳለፍ ዕቅድ በማውጣትና ተግባራዊ በማድረግ ሊጓዙ ይገባል፡፡ ከላይ የጠቀስናቸው ነጥቦች ከብዙ በጥቂቱ ቢሆኑም እነዚህን ተግባራዊ በማድረግ ስኬታማ ሆነው መውጣት ይችላሉና፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ግሸን ደብረ ከርቤ

‹‹ግሸን ማርያም›› በወሎ ክፍለ ሀገር በአምባሰል አውራጃ ውስጥ የምትገኝ ደብር ናት፤ ይህች ደብር በሐይቅና በመቅደላ፣ በደላንታ፣ በየጁ መካከልና በበሸሎ ወንዝ አዋሳኝ የምትገኝ አንድ መግቢያ በር ብቻ ያላት ዙሪያውን በገደል የተከከበች አምባ ናት፡፡

በ፲፩ኛው ክፍለ ዘመን ዐፄ ላሊበላ ከቋጥኝ ድንጋይ ፈልፍለው ‹‹እግዚአብሔር አብ›› የተሰኘ ቤተ ክርስቲያን በዚሁ ቦታ ሲያሠሩ ‹‹ደብረ እግዚአብሔር›› ተብላ ተሰየመች። ብዙም ሳይቆይ ‹‹ደብረ ነገሥት›› ተባለች። ከዚያም የሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ሲመሠረት ሐይቅ ‹‹ደብረ ነጎድጓድ›› ተብሎ ሲሰየም ግሸን የሐይቅ ግዛት በመሆኗ ‹‹ደብረ ነጎድጓድ›› ተብላለች፡፡

በ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ በዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት የክርስቶስ ግማደ መስቀሉ ግሸን ገብቶ ሲቀመጥ ‹‹ደብረ ከርቤ›› ተብላ ተሰየመች፡፡ ከዐፄ ድልናአድ ዘመን ፰፻፹፮ዓ.ም እስከ ፲፩ኛው ክፍለ ዘመን በአሁኑ ስያሜ ‹‹ደብረ ከርቤ›› በመባል ትታወቅ ነበር። በዚህ ጊዜ የነበረው የቤተ ክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መምህረ እስራኤል ዘደብረ ከርቤ ይባል ነበር። በመጨረሻም ከደብረ ከርቤ ግሸን ማርያም የሚል ስያሜ አገኘች፡፡

ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ግማደ መስቀሉን ይዘው እየገሰገስገሱ ስለመጡ በግዕዙ ‹‹ገሰ›› ወይም በአማርኛው ‹‹ገሰገሰ›› የሚለው ቃል ለቦታው ስያሜ ሆነ። በዘመናት ሂደት ገስ ወደ ግሸን የሚለው ስያሜ ተዛወረ፤ አካባቢው በዚህ ስም ታወቀ።

በዚያችም አምባ ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ታላቅ ቤተ መቅደስ ሠርተው መስቀሉንና ሌሎች ንዋየ ቅድሳቱን በየማዕረጋቸው የክብር ቦታ መድበው አስቀመጧቸው፤ ዘመኑም በ፲፬ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው፡፡

ከእስክንድርያ ሀገር ከመስቀሉ ጋር በልዩ ልዩ ሣጥን ተቆልፈው የመጡትም ንዋየ ቅዱሳት ጌታችን መድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዕለተ ዓርብ ለብሶት የነበረው ቀይ ልብስ ከሮም የመጣ ከለሜዳ፣ ከአፍርጌ ሀገር የመጣው ሐሞት የጠጣበት ሰፍነጉ፣ የቅዱስ ዮሐንስ የሳለው የኲርዓተ ርዕሱ ስዕል፣ ቅዱስ ሉቃስ የሳለው የእመቤታችን ሥዕል፣ የበርካታ ቅዱሳን አጽምና በኢየሩሳሌም ውስጥ ከልዩ ልዩ ቅዱሳት መካናት የተቆነጠረ የመሬት አፈር፣ የዮርዳኖስ ውኃ እና በግብጽ ውስጥ ከሚገኙት ታላላቅ ገዳማት የተቆነጠረ አፈር ናቸው፡፡

የእነዚህን ንዋየ ቅዱሳት ዝርዝር ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለግሸን ካህናት መስከረም ፳፩ ቀን ፩፻፬፻፵ ዓ.ም. በጽሑፍ በመዘርዘር ገለጹ፡፡

በዚያም ዘመን የነበሩት የኢትዮጵያ ጳጳሳት አባ ሚካኤልና አባ ገብርኤል የተባሉ ከንጉሡ ከዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ጋር ሆነው የምሕረት ቃል ኪዳን ለመቀበል በዚህች በግሸን ደብር ሱባዔ ገብተዋል፡፡ በሱባዔአቸውም መጨረሻ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ተገልጾ ‹‹ይህች ቦታ እኔ ተወልጄ ያደኩባትን ኢየሩሳሌምን ትሁን፤ የተሰቀልኩባትን ቀራንዮን ትሁን፤ የተቀበርኩባትንም ጎልጎታን ትሁን፤ በዚህች ቦታ እየመጣ የሚማፀነውን ሁሉ ቸርነቴ ትጎበኘዋለች፤ ጠለ ምሕረቴም አይለይባትም›› አላቸው፡፡

ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብም በዚያ ለተገኙት ምእመናን ሁሉ በጽሑፍ ካሰሙ በኋላ ጠቅላላ የግማደ መስቀሉንና የሌሎቹን ታሪካውያን ንዋየ ቅዱሳትንም ዝርዝር ታሪክ የያዘውን መጽሐፈ ‹‹ጤፉት›› ብለው ሰይመው ድንጋጌውን ሁሉ በመዘርዘር ለ ‹‹ግሸን እግዚአብሔር አብ›› ሰጡ፡፡

ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብም በዚህ ብቻ ሳይወሰኑ ዕሌኒ የተሰኘችው ንግሥት በእመቤታችን ማርያም ስም ቤተ መቅደስ እንድትሠራ አዘው፤ የእመቤታችን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ከእግዚአብሔር አብ ቤተ ክርስቲያን አጠገብ አሣንጻ ጥር ፳፩ ቀን ቅዳሴ ቤቱ ተከበረ፡፡ ይህችን ደብር ‹‹ደብረ ከርቤ›› ብለው በመሰየም ‹‹እንኳንስ ሰው የሠገረ ቆቅ፣ የበረረ ወፍ እንዳይገደል ዳሯ እሳት መሐሏ ገነት ትሁን›› ብለው ደንብና ሥርዓት በ ‹‹መጽሐፈ ጤፉት›› ውስጥ አጽፈዋል፡፡

በዚህ ምክንያት በየጊዜው የነገሡ የኢትዮጵያ ነገሥታት፣ ጳጳሳት፣ መሳፍንትና መኳንንት ልዩ ልዩ ንዋየ ቅድሳትንና መጻሕፍትን፣ የወርቅንና የብር ጻሕል ጽዋን፣ መስቀልን እና የመሳሰሉትን ስጦታ አበርክተዋል።

ግማደ መስቀሉ ከእስክንድርያ ስናር የገባው መስከረም ፲ ቀን ቢሆንም ኢትዮጵያ ‹‹ግሸን አምባ›› የገባበት፣ መቅደስ ተሠርቶ ቅዳሴ ቤቱ የተከበረውና ዐፄ ዘርዐ ያዕቆብ ለመላው ኢትዮጵያ በጽሑፍ በመዘርዘር የገለጹበትም መስከረም ፳፩ ቀን ነው፡፡ ይህን ዕለትም በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል፤ ምእመናንም በግሸን ማርያም ለመገኘት ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ይሄዳሉ፡፡ ኃጢአታቸውን ለካህን ተናዘው፣ ንስሓ ገብተው በዚህ ዕለት ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ በመሔድ የሚጸልዩና የሚማጸኑ ሁሉ እስከ ሰባት ትውልድ ድረስ የምሕረት ቃል ኪዳን እንደሚያገኙም ‹‹ጤፉት›› በተባለችው መጽሐፍ ተጠቅሷል፡፡

ቅዱስ መስቀል

እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን፡፡

መስቀል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰው ልጆችን ኃጢአት ያስወግድ ዘንድ በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ መሰቀሉን፣ ተጣልተው የነበሩትን ሰባቱ መስተፃርራን (ሰውና እግዚአብሔርን፣ መላእክትና ሰውን፣ ነፍስና ሥጋን፣ ሕዝብና አሕዛብን) ያስታረቀበት ነው፡፡ በቀራንዮ “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም“ (ዮሐ. ፲፭፥፲፫) እንዲል፡፡ በዚህም የመዳን ምልክት መሆኑ የተረጋገጠበት በክርስቶስ ደም የተቀደሰ፣ የጠብ ግድግዳን ያፈረሰ፣ ቅድስናና ክብር ያለው የአበው ተስፋ የተፈጸመበት፣ ሰው ከውድቀቱ መነሣቱን የተበሰረበት ነው፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ታላቅ ክብር ይሰጠዋል፡፡ የመስቀል በዓልም ከጌታችን ንዑሳን በዓላት አንዱ ሲሆን በየዓመቱ መስከረም ፲፯ ቀን ይከበራል፡፡ በዋዜማውም ደመራ በመደመር፣ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውነተ ቤተ ክርስቲያን መምህራን፣ ካህናትና ዲያቆናት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራን እንዲሁም ምእመናን ጋር በመሆን በአደባባይ በጸሎት፣ በትምህርትና በዝማሬ በድምቀት ታከብረዋለች፡፡

የደመራው መደመር ምክንያትም ስንመለከት፡- ጌታችን መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል አይሁድ በምቀኝነት ተነሣስተው ከሦስት መቶ ዓመታት በላይ ሰውረው ቀብረውት ስለነበር የእግዚአብሔር ጊዜ ሲደርስና ፈቃዱ ሲሆን ቦታው የተገኘበትን ቀን በቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ በዓል ሆኖ ይከበራል፡፡ በ፫፻፳፮ ዓ.ም የንጉሥ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ፣ ኪራኮስ በተባለ አንድ የታሪክ አዋቂና ሽማግሌ ጠቋሚነት ደመራ አስደምራ በዕጣን ጢስ ተመርታ ጢሱ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ማመልከቱን በማሰብ ቤተ ክርስቲያናችን መስከረም ፲፮ ቀን የደመራ በዓልን ታከብራለች፡፡

ንግሥት ዕሌኒ በጭሱ ምልክትነት መስቀሉ ያረፈበትን ቦታ ካረጋገጠች በኋላ መስቀሉን ለማውጣት መስከረም ፲፯ ቀን በማስጀመር ለሰባት ወራት ያህል በማስቆፈር በመጋቢት ፲ ቀን እንዳስወጣቸው ታሪክ ይነግረናል፡፡ ዛሬ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ዘንድ ደመራ የሚደመረውም ይህንን ታሪክ ተከትሎ እንደሆነ ሊቃውንቱና ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡

ቅድስት ዕሌኒ በምልክቱ መሠረት ተራራውን ስታስቆፍር የተገኙት ሦስት መስቀሎች ናቸው፡፡ የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን መስቀል ሁለት ወንበዴዎች ከተሰቀሉበት መስቀል ለመለየትም ባደረገችው ጥረት የጌታችን መስቀል ድውያንን ፈውሷል፣ አንካሳ አበርትቷል፣ ጎባጣን አቅንቷል፣ የዕውራንን ዐይን አብርቷል፡፡

ስለ መስቀሉ ስናነሣ በዘመነ ብሉይ የመባረኪያ ምልክት እንደነበረ በመጽሐፍ ቅዱስ ተጠቅሶ እናገኛለን፡፡ ያዕቆብ በሚሞትበት ጊዜ የዮሴፍን ልጆች እያንዳንዳቸውን በእምነት ባርካቸው” እንዲል፡፡ በተጨማሪም ዮሴፍ አባቱ ያዕቆብ ልጆቹን ይባርክለት ዘንድ ባቀረባቸው ጊዜ “የሴፍም ሁለቱን ልጆቹን ወሰደ፤ ኤፍሬምንም በቀኙ፣ ምናሴንም በግራው አቆማቸው፤ ወደ አባቱም አቀረባቸው፡፡ እስራኤልም ቀኝ እጁን ዘርግቶ በኤፍሬም ራስ ላይ አኖረ፣ እርሱም ታናሽ ነበረ፤ ግራውንም በምናሴ ላይ አኖረ፤ እጆቹንም አስተላለፈ። ያዕቆብም ባረካቸው” ይላል፡፡ (ዘፍ. ፵፰፥፲፩፤ ዕብ. ፲፩፥፳፪)

መስቀል በብሉይ ኪዳን ለወንጀለኞች መቅጫነት አገልግሏል፣ በመስቀል የተመሰለው የሙሴ በትርም ባሕር ከፍሏል፣ ጠላት አስጥሟል፣ መና አውርዷል፣ ደመና ጋርዷል፣ ውኃ ከዐለት አፍልቋል፣ በግብፃውያን ላይ ድንቅ ድንቅ ተአምራትን አድርጓል፡፡

በሐዲስ ኪዳንም አይሁድ ወንጀለኞችን የሚቀጡት በውግራት፣ በእሳት ማቃጠል ቢሆንም በመስቀልም ይቀጡ ነበር፡፡ ከፍተኛ ወንጀል የፈጸሙ ሰዎች አይገረፉም፤ በመስቀል ይቀጡ ነበር፡፡ ከተገረፉ ደግሞ አይሰቀሉም፡፡ (ዘዳ. ፳፩፥፳፩-፳፫) በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ግን ከሕጋቸው ውጭ ገርፈውታልም ሰቅለውታል፡፡

የቅዱስ መስቀሉ በረከት ይደርብን፡፡ አሜን፡፡

ተቀጸል ጽጌ

ርእሰ ዐውደ ዓመት

እንኳን ከዘመነ ዮሐንስ ወደ ዘመነ ማቴዎስ በሰላም አሸጋገረን፡፡ መልካም አዲስ ዓመት!

በኢትዮጵያውያን ዘመን አቆጣጠር የመስከረም ወር የወራት ሁሉ መጀመሪያ ነው፡፡ ይህ ወር ዘመን መለወጫ፣ ዕንቁጣጣሽ፣ ቅዱስ ዮሐንስ እየተባለ ይጠራል፡፡ ገበሬው በክረምቱ ወራት መሬቱን አልስልሶ፣ ዘሩንም ዘርቶ ምድሪቱም አደራዋን ለመመለስ በልምላሜ የምታጌጥበት ወር ነው፡፡ በዚህም ምክንያት እንስሳት ለምለሙን ሣር ግጠው፣ የጠራውን ውኃ ጠጥተው ረክተው፣ አምረው የሚታዩበት የልምላሜ ወር ነው። ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ምድርን ጐበኘሃት አጠጣሃትም፥ ብልጥግናዋንም እጅግ አበዛህ፤ የእግዚአብሔርን ወንዝ ውኃን የተመላ ነው፤ ምግባቸውን አዘጋጀህ እንዲሁ ታሰናዳለህና። ትልምዋን ታረካለህ፥ ቦይዋንም ታስተካክላለህ፤ በነጠብጣብ ታለሰልሳታለህ፥ ቡቃያዋንም ትባርካለህ። በቸርነትህ ዓመትን ታቀዳጃለህ፥ ምድረ በዳውም ስብን ይጠግባል። የምድረ በዳ ተራሮች ይረካሉ፥ ኮረብቶችም በደስታ ይታጠቃሉ። ማሰማርያዎች መንጎችን ለበሱ፥ ሸለቆችም በእህል ተሸፈኑ፤ በደስታ ይጮኻሉ ይዘምራሉም” እንዲል። (መዝ. ፷፬፥፱-፲፫)

ቅዱስ ዮሐንስ

ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችንም ዓመታትን በቸርነቱ ለሚያቀዳጅ ለእግዚአብሔር ምስጋና ለማቅረብ የአዲሱን ዓመት መጀመሪያ ወይም ርእሰ ዐውደ ዓመት “ቅዱስ ዮሐንስ” በሚል ስያሜ ስታከብረው ኖራለች፣ ትኖራለችም። ይህም ሊሆን የቻለበት ምክንያት የመጥምቁ ዮሐንስ ተግባር ለዘመነ ወንጌል በር ወይም መነሻ ሆኖ መገኘቱና የቤተ ክርስቲያን አበው የበዓላትን ድንጋጌ በወሰኑበት ጊዜ የመጥምቁ ዮሐንስ መታሰቢያ በዓል የኢትዮጵያ ርእሰ ዐውደ ዓመት በሚሆን መስከረም አንድ ቀን እንዲከበር በየዓመቱ የዘመኑ መጀመሪያ በእርሱ ስም እንዲጠራ በመደንገጋቸው ነው። (ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ)፡፡  መጽሐፈ ስንክሳር የዓመቱን መጀመሪያ የሆነውን መስከረምን ሲያትት “ይህ የመስከረም ወር የተባረከ ነው፤ እርሱም የግብጽና የኢትዮጵያ ዓመቶች መጀመሪያ ነው” በማለት ያስረዳል። 

የዘመን መለወጫ

ብርሃናት (ፀሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት) የዓመት ዑደታቸውን በጳጉሜ ወር ጨርሰው በመስከረም ወር ስለሚጀምሩ ይህ ቀን የዘመን መለወጫ ተብሎ ይጠራል። ሌሊቱ ከቀኑ ጋር ይተካከላል፡፡ ዓመቱን ጠንቅቀው ቢቆጥሩ ፫፫፷፬ ቀናት ይሆናል፡፡ መጽሐፈ ሄኖክ ይህን ሲገልጽ “ሌሊቱም ከቀኑ ጋራ ይተካከላል፡፡ ዓመቱም ጠንቅቆ ቢቆጥሩት ሦስት መቶ ስልሳ አራት ቀን ይሆናል፡፡ (ሄኖ. ፳፮፥፻፬) ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስም አዲሱን ዓመት በተመለከተ ሲገልጽ “ዘመናችንን እንደ ቀድሞ አድስ” (ሰ.ኤር. ፭፥፳፩) በማለት በኃጢአት የወደቅን በንስሓ ተነሥተን፣ የቀማን መልሰን፣ በአዲስ ሰውነትና በአዲስ አስተሳሰብ ከእግዚአብሔር ጋር እርቅ የምንፈጽምበት፣ በሕይወታችንም እንድንለወጥና እንድታደስ ይመክረናል፡፡

ዕንቁጣጣሽ 

ከሁለት አበይት ምክንያት መጠሪያ እንደሆነ ሊቃውንት ይናገራሉ፤ የመጀመሪያው ምክንያት የኖኅ ልጅ ካም ከወንድሞቹ ጋር ምድርን ሲከፋፈሉ በዕጣ አፍሪካ ስትደርሰው መጀመሪያ ያረፈው ኢትዮጵያ ላይ በመስከረም ወር ሲሆን በዚህ ጊዜ የምድሩንና የአበቦቹን ማማር አይቶ ደስ ብሎት”ዕንቁ ዕጣ ወጣሽል” ሲል ይህችን ወቅት እንቁጣጣሽ ብሏታል። ሁለተኛው ንጉሡ ሰሎሞን ለንግሥት ሳባ “ዕንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንልሽ” ሲል እጅግ በጣም የከበረ ዕንቁ ያበረከተላት በዚህ በመስከረም ወር ስለነበር፤ ከዚህ በመነሣት መስከረም አንድን እንቁጣጣሽ በሚለው ስያሜ እንደሚጠራ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ያስተምራሉ።  

በአጠቃላይ ዘመን መለወጫ ከላይ ባየናቸው የተለያየ ስያሜ ይጠራ እንጂ ዘመኑ አዲስ እየተባለ ቢጠራም አዲስ መሆን ያለበት ወርና ወቅቱ ብቻ ሳይሆን የእኛ የክርስቲያኖች ሕይወት ነው፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ወንድሞች ሆይ ሰውነታችሁን ለእግዚአብሔር ሕያውና ቅዱስ ደስ የሚያሰንም መስዋዕት አድርጋችሁ ታቀርቡ ዘንድ በእግዚአብሔር ርኅራኄ እማልዳችኋለሁ” እያለ በመዋዕለ ሥጋዌው ያስተምር ነበር፡፡ አዲስ ዓመት ሲመጣ በኃጢአት፣ በተንኮል፣ በክፋት የቆሸሸው ሰውነታችን በንስሓ፣ በቅዱስ ቊርባን፣ በመልካም ተግባር አዲስ ልናደርገው ይገባናል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

የግቢ ጉባኤ የደረጃ ሦስት ተተኪ መምህራን ሥልጠና ተጠናቀቀ

የማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማሰተባበሪያ ከሃያ ማእከላት ለተውጣጡ ፴፱ መምህራን የደረጃ ሦስት ሥልጠናን ከነሐሴ ፳፯ እስከ ጳጉሜን ፫ ቀን ፳፻፲፮ ዓ.ም ድረስ በመስጠት በሠርተፍኬት አስመረቀ፡፡

ሥልጠናው በሰባት የትምህርት ዓይነቶች ማለትም፡- ትምህርተ ሃይማኖት፥ አንጻራዊ ትምህርተ ሃይማኖት፥ ነገረ ድኅነት፥ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፥ የአንድምታ ወንጌል አጠናን ስልት፥ ነገረ አበው፥ አርአያነት ያለው የመምህራን ሕይወት በሚሉ ርእሰ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ሲሆኑ በቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በአገልግሎት በሚታወቁ መምህራን ተሰጥቷቸዋል፡፡ በተጨማሪም በማኅበረ ቅዱሳን ዋና ፀሐፊ ከሠልጣኞች የማኅበሩን አገልግሎት በተመለከተ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ሰፋ ያለ ማብራሪያ በመስጠት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን የማገልግል ተልእኮአቸውን እንዲወጡ በአደራ ጭምር መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

መልአከ ታቦር ኃይለ ኢየሱስ ፋንታሁን “አርአያነት ያለው የመምህራን ሕይወት” በሚል ርእስ  ማንበብን ገንዘብ እንዲያደርጉ፣ የአባቶችን ፍኖት ተከትለው እንዲጓዙ፣ በሥነ ምግባር ታንጸው የሚገጥማቸውን ፈተና በጽናት በማለፍ የተጣለባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ሰፋ ባለ ሁኔታ በምክርና በተግሣጽ ላይ ያተኮረ ሕይወት ተኮር ትምህርት ተሰጥቷቸዋል፡፡

ከሠልጣኞቹ መካከል ከመቱ ማእከል የመጡት ዲ/ን ዘመኑ ለማ ሥልጠናውን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት “ከአቀባበል ጀምሮ በመምህራኑ የተሰጠን ሥልጠና ከዚህ በፊት የነበረንን ዕውቀት የሚያሳድግ፣ እንዲሁም ያለንን የአገልግሎት ትጋት ከፍ የሚያደርግ ነው” ብለዋል፡፡ “ዕውቀትና ትግባር ተኮር ትምህርት ነው የተሰጠን፡፡ ያለብንን የዕውቀት ክፍተት ለመሙላትና በተሻለ አቅም እንድናገለግል የሚያግዘን ሥልጠና ነው” ያሉት ደግሞ ከአርሲ ግቢ ጉባኤ የመጡት ዲ/ን ቢንያም አስናቀ ናቸው፡፡

ሥልጠናውን ከተሳተፉት ውስጥ በሥልጠናው በመሳተፋቸው ያገኙትን ሲገልጹም “በመምሀራኑ የተሰጠን ሥልጠና ወደፊት አቅማችንን በማንበብ እንድናሳድግ የሚያደርገን ነው፡፡ ዕይታችንን የሚያሰፋ ሥልጠና ነውና የወሰድነው ወደፊትም ተጠናክሮ ቢቀጥል” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡፡፡

በመጨረሻም ሥልጠናውን ካጠናቀቁ በኋላ የምሥክር ወረቀት የተሰጣቸው ሲሆን የማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ዋና ኃላፊ የሆኑት አቶ አበበ በዳዳ ለሠልጣኞቹ መምህራን መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡ “ማኅበረ ቅዱሳን ከተሰጡት ኃላፊነቶች ውስጥ ዋነኛው የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ማስተማር ነው፡፡ እናንተም ይህንን ኃላፊነት እንድትሸከሙ ነው ሥልጠናውን የወሰዳችሁት፡፡ በዚህም መሠረት ለትውልዱ አርአያ የሚሆኑ ኦርቶዶክሳውያንን ማፍራት እንድትችሉ በንባብ ራሳችሁን በማሳደግ ለአግልግሎት እንድትፋጠኑ አደራ እንላለን” ብለዋል፡፡

የደረጃ ሦስት የተተኪ መምህራን ሥልጠና ሲሰጥ ይህ ለሦስተኛ ጊዜ ሲሆን ወደፊትም የሚቀጥል መሆኑን አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል፡፡  

ወርኃ ጳጉሜን

ወርኃ ጳጉሜን

የጳጕሜን ወር አሥራ ሦስተኛዋ ወር በማለት እንጠራታለን፡፡ አሥራ ሁለቱ ወራት እያንዳንዳቸው ሠላሳ ቀናት ያሏቸው ሲሆን የጳጕሜን ወር ግን ያሏት አምስት (በዘመነ ማቴዎስ፣ በዘመነ ማርቆስ፣ በዘመነ ሉቃስ) እና በየአራት ዓመቱ በዘመነ ዮሐንስ ደግሞ ስድስት ቀናትን ትይዛለች፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን አስትምህሮም የጳጕሜን ወር የዓመት ተጨማሪ ወር ትባላለች፡፡   

ጳጕሜን “ኤፓጉሜኔ” ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን ትርጉሙም “ጭማሪ” ማለት ነው፡፡ በግእዝ “ወሰከ፤ ጨመረ” ከሚለው የግእዝ ግስ የወጣ ተውሳክ (ተጨማሪ) ማለት ነው፡፡ (አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ መዝገበ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገብ ቃላት፤ ገጽ ፱፻፭)

የጳጕሜን ወር በየዓመቱ የክረምትን ወር አሳልፈን ወደ ጸደይ ወቅት የምንሸጋገርባት እንደሆነች ሁሉ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጳጕሜን ወር የዓለም ፍጻሜ መታሰቢያ ተደርጋም ትታሰባለች፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢያሱስ ክርስቶስ ይህቺን ምድር ያሳልፋት ዘንድ በክበበ ትስብዕት፣ በግርማ መለኮት በቅዱሳን መላእክት ታጅቦ የሚመጣበት፣ የዓለም መከራና ችግር እንዲሁም ሥቃይ የሚያበቃበት መሆኑን የርስት መንግሥተ ሰማያት ማሳያ ናት ጳጕሜን፡፡

ወደ አዲስ ዘመን ስንሸጋገር አዲስ ተስፋና በጎ ምኞትም ይዘን “ኑ የአባቴ ብሩካን ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ” የሚባሉባት እንደ መሆኑ ጳጕሜን ወር አዲሱን ዓመት ለመቀበል የምንዘጋጅበት ጊዜ ነው፡፡ (ማቴ. ፳፭፥፴፬) በዚህች በተሰጠን የጭማሪ ወር ተጠቅመን ለነፍሳችን ድኅነት የሚሆነን ስንቅ በመያዝ አዲሱን ዘመን ልንቀበል ያስፈልጋል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደ ገዳመ ቆሮንቶስ በፈቃዱ በሄደ ጊዜ ከቆመ ሳይቀመጥ፣ ከዘረጋ ሳያጥፍ ለአርባ ቀንና ሌሊት በዲያብሎስ ቢፈተንም ዲያብሎስን ድል ነሥቶ ከፊቱ አሰወግዶታል፡፡ ከጾሙም በኋላ የሥራው መጀመሪያ ያደረገው በኢየሩሳሌም እየተዘዋወረ አስተምሯል፣ ድውያንን ፈውሷል፣ ለምጻሙን አንጽቷል፣ ሺባውን ተርትሯል፣ የተራቡትን አብልቷል፣ የተጠሙትንም አጠጥቷል፣ ልዩ ልዩ ተአምራትንም አድርጓል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ቅዱሳን ሐዋርያትን ከኢየሩሳሌም እንዳይወጡ አስጠንቅቋቸው ለአርባ ቀናት መጽሐፈ ኪዳንን እያስተማራቸው ቆይቷል፡፡ ከዚያም “ሂዱና አሕዛብን በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስም እያስተማራችኋቸውና   እያጠመቃችኋቸው ክርስቲያን አድርጓቸው” ብሏቸዋል፡፡ ሀገረ ስብከታቸውን ተከፋፍለው ለአገልግሎት ከመሰማራታቸው በፊት ግን መምህራቸውን አብነት አድርገው በጾም በጸሎት ተወስነው ቆተዋል፡፡ ይህንንም ጾም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት አንዱ አድርጋ ሥርዓት ሠርታለች፡፡ የአገልግሎት መጀመሪያ በጾም ጸሎት መወሰን፣ ፈቃደ እግዚአብሔርን መጠየቅ ዋጋ ያሰጣልና ኦርቶዶክሳውያን ምእመናን ይህንን የጳጉሜን ወር በፈቃድ ጾም ተወስነው ዓመቱ በሃይማኖት የሚጸኑበት፣ በጎ ሐሳባቸው ይፈጸም ዘንድ የሚተጉበት ይሆን ዘንድ ይጾሙታል፡፡    

እኛም አዲሱን ዓመት ከመቀበላችን በፊት የበደልን ንስሓ ገብተን፣ ዓመቱን ሙሉ አቅደናቸው ያልሠራናቸውን ሥራዎች ዕቅድ የምናወጣበት፣ ከሁሉም በላይ መንፈሳዊ ሕይወታችንን በማጠንከር ከእግዚአብሔር ጋር እርቅ የምንፈጽምበት ጊዜ መሆኑን ተረድተን በአዲስ ማንነትና ሰውነት ታድሰን አዲሱን ዓመት ለመቀበል መዘጋጀት ይጠበቅብናል፡፡

ወርኃ ጳጉሜን የዮዲት ጾም ተብሎም በቤተ ክርስቲያናችን ይጠራል፡፡ ዮዲት በጾምና በጸሎት ተወስና በሕገ እግዚአብሔር በምትኖርበት ጊዜ በእርሷና በሕዝቡ ላይ የመጣውን መከራና ችግር አምላክ እንዲፈታላት የያዘችው ሱባኤ ከእግዚብሔር ዘንድ ምላሽና መፍትሔ እንዳሰጣት ሁሉ እኛም የችግራችን ቋጠሮ እንዲፈታልንና ካለንበት የመከራ አረንቋ አውጥቶ ወደ በጎ ዘመን እንዲያሸጋግረን ተስፋ በማድረግ ልንጾም እና በጸሎት ልንማጸን ይገባል፡፡    

እምነት ኃይልን ታደርጋለችና አምላካችን እግዚአብሔር ችግራችን እንደሚፈታልን በማመን በጾምና በጸሎት ብትንጋ ምላሽ እናገኛለን፡፡ በጾምና በጸሎት የተጋችው ዮዲት ጠላቶቿን ድል ማድረግ እንደምትችል በማመን ካሉበት ድረስ በመሄድ የተፈጥሮ ውበቷን ተጠቅማ አሸንፋለች፡፡

ከዚያ ሁሉ አስቀድማ ግን ማድረግ ስላሰበችው ነገር የአምላኳን ርዳት በሱባኤ ጠይቃ ስለነበር ያለ ምንም ፍራቻ ለምታምንበት ነገር ሽንፈትም ሆነ ውድቀትን ሳታሳብ ያለ ጥርጣሬ ጠላቷን ተጋፍጣ አሸንፋዋለች፡፡ በዚህም ከራሷ አልፎ ለሀገሯ ሕዝብ መዳንና የሀገር ሰላም መገኛ ሆናለች፡፡ እኛም ይህን ያለ ጥርጣሬ በማመን በዚህ በከፋ ወቅት በአንድነት ሆነን አምላካችን እንለምን፤ ኅብረት ጥንካሬ ነውና፡፡ የተሰጠንን የጊዜ ጭማሪ በመጠቀምም በጾም ተወስነን አብዝተን እንማጸን፡፡ እንደ ዮዲት ማቅ ለብሰን፣ አመድ ነስንሰንና ድንጋይ ተንተርሰን አብዝተን ልንጾምና ልንጸልይ ይገባል፡፡ ከመከራና ሥቃይ እንዲሰውረን፣ የእርስ በእርሱን ጦርነት እንዲገታልን፣ ያጣነውን ሰላም፣ ፍቅርና አንድነትን እንዲመልስልን መጸለይና መጾም ያስፈልጋል፡፡

የግቢ ጉባኤደረጃ ሦስት ተተኪ መምህራን ሥልጠና ተጀመረ

የማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማሰተባበሪያ ከየማእከላት ለተውጣጡ 45 መምህራን የደረጃ ሦስት ሥልጠናን ከነሐሴ 28 እስከ ጳጉሜን 2 ቀን 2016 ዓ.ም ድረሰ በመስጠት ላይ ይገኛል። በዚህ ሥልጠናም:- ትምህርተ ሃይማኖት፥ አንጻራዊ ትምህርተ ሃይማኖት፥ ነገረ ድኅነት፥ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፥ የአንድምተ ወንጌል አጠናን ስልት፥ ነገረ አበው፥ አርአያነት ያለው የመምህራን ሕይወት እና ሌሎችም ርእሰ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ሥልጠናው እየተሰጠ ይገኛል።

ወጣትነትና ታማኝ አገልጋይነት

ወጣትነትና ታማኝ አገልጋይነት

በዲ/ን ወልደ ቂርቆስ ደሳለኝ

ክፍል ሦስት

በወጣቶች አገልግሎት ላይ የሚታዩ ክፍተቶች

እስከ አሁን የተመለከትናቸው አራት መሠረታዊ ነጥቦች ወጣቶች ወደ መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይቀርቡና ከቤተ ክርስቲያን እንዲሸሹ እያደረጉ ያሉ እንቅፋቶችን ነበር፡፡ ነገር ግን እነዚህ እንቅፋቶች በእግዚአብሔር ቸርነት፣ በደጋግ ካህናትና መምህራነ ወንጌል አበረታችነት ተቋቁመው ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን በተሰጣቸው ጸጋ ለማገልገል በደጇ የሚመላለሱ ወጣቶች ብዙዎች ናቸው፡፡ በወጣትነት (በጉብዝና ወራት) ፈጣሪን እያሰቡ በቤተ ክርስቲያን እቅፍ ተከልሎ ማለፍ፣ በመንፈሳዊም ይሁን በሥጋዊ ሕይወታችን ከውድቀትና ከኃጢአት ተጠበቀን ለራሳችን፣ ለቤተሰባችን፣ ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገራችን ጠቃሚዎች ከመሆን አልፈን ለሰማያዊ ክብር እንበቃ ዘንድ በትጋት ለማገልገል መሠረት የምንጥልበት ወቅት ነው፡፡

ይህ ማለት ግን በቁርጠኝነት ወደ ቤተ ክርስቲያን ከቀረቡ በኋላ ፈተና የለም ማለት አይደለም፡፡ በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ያሉ ወጣቶችም ብዙ ፈታኝና አስቸጋሪ ሁኔታዎች እየገጠሟቸው እንመለከታለን፡፡ ከዚህ በታች አጠር ባለ መንገድ በዘመናችን በወጣቶች መንፈሳዊ አገልግሎት ላይ እየታዩ ያሉ ፈታኝ ጉዳዮችን (ችግሮችን) እንመለከታለን፡፡

የልምድ ተመላላሽ መሆን

አገልግሎት መቼም ቢሆን መንግሥተ ሰማያትን (ሰማያዊ ሕይወትን) ዕሴት ያደረገ ግብ ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም ወደ እግዚአብሔር ቤት መመላለሳችን በዓላማ የታጠረ፣ በዕቅድ የተወጠነ መሆኑ ቀርቶ እንዲሁ በዘልማድ ብቻ ከሆነ ለራሳችንም፣ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንም የማንጠቅም ከንቱዎች መሆናችን እሙን ነው፡፡ ብዙ ወጣቶች ወደ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ወደ መንፈሳውያን ማኅበራት ለምን እንደሚሄዱ እንኳን ግራ እስኪገባቸው ድረስ ያለ ዓለማ በዘልማድ ይመላለሳሉ፡፡ ግብና ዓላማ የሌለው አገልጋይ ለመንፈሳዊ ሱታፌና ፈተናን ድል ለማድረግ የነቃና የተዘጋጀ ይሆን ዘንድ ፈጽሞ አይቻለውም፡፡ ከዚያ ይልቅ “በራድ ወይም ትኩስ ብትሆንስ መልካም ነበር፤ እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልሆንህ ከአፌ ልተፋህ ነው” (ራእ. ፫፥፲፭-፲፮) እየተባለ በመኖርና ባለመኖር መካከል እንደባከነ ዘመኑን ይጨርሳል፡፡

ስለዚህ እኛ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልጆች በትምህርት፣ በሥራ፣ ብሎም በማኅበራዊ ሕይወታችንም “እግዚአብሔር ቢፈቅድ ብንኖር ይህን ወይም ያን እናደርጋለን” እያልን ምን ለማድረግ፣ ምን ለመሥራት፣ መቼና እስከ መቼ በምን ያህል ፍጥነት የሚለውን ጥያቄ በንቃት እያሰብን ከዘልማዳዊ ምልልስ መውጣት አለብን፡፡ (ያዕ. ፬፥፲፭)፡፡ ነገር ግን አገልጋዮች በተለይም ወጣቶች የትንሣኤ ልቡና ንቃተ ኅሊና ሳይኖራቸው እንዲሁ ከተመላለሱ ከማትርፍ ይልቅ ይጎዳሉ፡ በዚህም “ስለ በረከት ፈንታ መርገምን፣ ስለሥርየተ ኃጢአት ፈንታ ገሃነመ እሳትን ይቀበላል” እንዲል ሥርዓተ ቅዳሴአችን ልፋትና ድካማችን ለውድቀት ይሆንብናል፡፡

መንፈሳዊነት የሌለበት ስሜታዊ አገልገሎት

በእርግጥ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተቆርቁሮ በእልህ፣ በመንፈሳዊ ወኔና በስሜት “የቤትህ ቅናት በልቶኛልና፣ የሚሰድቡህም ስድብ በላዬ ወድቋልና” (መዝ. ፷፰፧፱) ብሎ ለመንፈሳዊ አገልግሎት በቁርጠኝነት መነሣት የተገባ በጎ ተግባር ነው፡፡ አንድ መንፈሳዊ አገልጋይ ከዓለማውያን ሠራተኞች የሚለየው ከመንፈሳዊ ስሜትና ቁጭት ጋር መንፈሳዊ ብስለትና ፈቃደ እግዚአብሔርን አስተባብሮ መጓዝ ሲችል ነው፡፡

በዘመናችን ብዙ ወጣቶች ልቡናቸውን በቃለ እግዚአብሔር ሳይሰብሩ በሥጋዊ አስተሳሰብ፣ በእልህ፣ በቁጣና በስሜት ብቻ ለአገልግሎት ሲመላለሱ ይስተዋላል፡፡ በዚህም ምክንያት በመንፈሳዊ አገልግሎት ላይ ጠብ፣ ክርክርና ንትርክ ሲበዛ እንመለከታለን፡፡ ማንኛውም መንፈሳዊ አገልግሎት ግቡን የሚመታውና ውጤታማ የሚሆነው አገልግሎቱን የሚፈጽመው ሰው መንፈሳዊ ብስለትን ሲጎናጸፍ ብቻ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በሥጋዊ አስተሳሰብ መንፈሳዊ ጉዳይን ለማራመድ መሞከር ከንቱ ድካም ነው፡፡

ወደ ቤተ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ብስለት ሳይሆን በሥጋዊ ስሜት ብቻ የምንመላለስ ከሆነ ድካማችን ለፍሬ የማይበቃ ነው የሚሆነው፡፡ ከዚያም አልፎ ስኬትን በሥጋ ሚዛን እየመዘንን በቀላሉ ተስፋ የምንቆርጥና ችኩሎች ሆነን ከምናለማው ይልቅ የምናጠፋው የሚገዝፍ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ታማኝ አገልጋይ ተብለን በጌታችን እንመሰገን ዘንድ ራሳችንን ከስሜታዊነት አላቅቀን በፍጹም መንፈሳዊ ትዕግሥትና ትሕትና በእግዚአብሔር ቤት በቀናነት ልንመላለስ ይገባል፡፡ ይህንን ስናደርግ ነው እንደ ጎልያድ የገዘፈውን የዓለም ፈተና እንደ ነቢዩ ዳዊት “እኔ ግን ዛሬ በተገዳዳርኸው በእስራኤል ጭፍሮች አምላክ ስም በሠራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ስም እመጣብሃለሁ” (፩ሳሙ. ፲፯፥፵፭) በማለት ድልን የምንጎናጸፈው፡፡

ራስን ማታለል (ለራስ ኅሊና መዋሸት)

አቡሃ ለሐሰት፣ የሐሰት አባት የተባለ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስ “ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም እንደምትሆኑ መልካምንና ክፉን እንደምታውቁ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ” (ዘፍ. ፫፥፬) ብሎ ሔዋንን በማታለል ሐሰትን እንደ ጀመረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል፡፡ መዋሸት በሁለት መንገድ ሊፈጸም ይችላል፡፡ በቀዳሚነት በተለመደው መንገድ አንድ ሰው ለሌላ ሁለተኛ ወገን እውነትን አዛብቶ፣ አልያም ያለተደረገውን ተደረገ ብሎ ቢናገርበት የሚፈጸመው ሲሆን፣ በሌላ በኩል ግን አንድ ሰው ይህንኑ ጉዳይ ሌላ ሁለተኛ አካል ሳያስፈልግ ከራሱ ጋር ሊፈጽመው ይችላል፡፡ ራስን መዋሸት ወይም ማታለል ማለት እውነታውን እያወቁ ከኅሊና መደበቅ ማለት ነው፡፡ በዘመናችን ብዙ ወጣቶች በመንፈሳዊ አገልግሎት ራሳቸውን ሲያታልሉ ይስተዋላል፡፡

አበ ብዙኃን የተባለው አባታችን አብርሃም ያስጨነቀውና እውነትን ወደ መምርመር የወሰደው ኅሊናውን ማታለልና ለራሱ መዋሸት ከባድ ስለሆነበት ነው፡፡ ከእንጨት ተጠርቦ የተሠራውን ጣዖት ምስል ፈጣሪ፣ መጋቢ፣ አምላክ፣ ወዘተ ነው ብሎ አምኖ ለመቀበልና ለኅሊናው ውሸትን ይነግር ዘንድ አልቻለም፡፡ በዚህም የተነሣ “የፀሐይ አምላክ ተናገረኝ” በማለት በትጋት አምላኩን ፈልጎ አገኘ፡፡ ነገር ግን የሰው ልጅ ራሱን እያታለለ ከእውነት ሲሸሽ በጉልህ ይስተዋላል፡፡ በርእሳችን መነሻ ያነሣነውን የመክሊቱን ምሳሌ መለስ ብለን ብንመለከት ያ ሰነፍና ልግመኛ አገልጋይ (ገብር ሐካይ) ኅሊናው ሥራ፣ ድከም፣ መክሊትህን አትቅበር እያለ እንዳይወቅሰው ለራሱ ማታለያ ይሆነው ዘንድ ምክንያት አስቀምጦ ነበር፡፡ ይኸውም “አቤቱ አንተ ካልዘራህበት የምታጭድ፣ ካልበተንህበትም የምትሰበስብ እንደሆንህ አውቃለሁ” የሚል ነው፡፡ ይህም ምክንያት ለስንፍናው ማደላደያ ያቀረበው የሐሰት ማስረጃ እንደሆነ ከጌታው ምላሽ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ “ጌታውም መልሶ አለው፤ አንተ ክፉና ሰነፍ አገልጋይ እኔ ካልዘራሁበት የማጭድ፣ ካልበተንሁበት የምሰበስብ ጨካኝ ሰው እንደሆንሁ ታውቃለህን?” በማለት የተሰጠውን መክሊት በታማኝነት ሳይጠቀምበት በመቅረቱ ለቅጣት እንደተዳረገ እንመለከታለን፡፡ (ማቴ. ፳፭፥፳፬-፳፮)፡፡

ብዙ ወጣቶች ለመንፈሳዊ አገልግሎት ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመጡ በኋላ ቅዱሳት መጻሕፍት የመዘገቡትን፣ አበው ሊቃውንት የሚያስተምሩትን ከመሥራትና የሕይወታቸው መመሪያ ከማድረግ ይልቅ “እናንተ ሰነፎች የገላትያ ሰዎች ሆይ፤ ለዐይን በሚታየው እውነት እንዳታምኑ ማን አታለላችሁ?’ (ገላ. ፫፥፩) እንዳለ ከእውነት ርቀው ራሳቸውን በማታለል ለፈቃደ ሥጋቸው አድልተው ፈቃደ ነፍሳቸውን የሚያከስም ተግባርና አካሄድ ላይ ይጠመዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ነው በመንፈሳዊው ዐውደ ምሕረት በአገልግሎት ስም ዓለማዊ ጭፈራ በሚመስል አላስፈላጊ እንቅስቃሴ ዋና አጋፋሪዎች የሆኑ ብዙ አገልጋዮችን የምንታዘበው፡፡ በዚህም ራስን በማታለል ኩነኔውን ጽድቅ፣ የጽድቁን ሥራ ልማዳዊ አድርጎ የማሰብ አባዜ የተነሣ በሥርዓተ ዑደቱ በዝማሬና እልልታ የቤተ ክርስቲያን ቅጽር በምእመናን ተሞልቶ በሥርዓተ ቅዳሴውና በምሥጢረ ቁርባን ግን በጣት የሚቆጠሩ ምእመናን ብቻ የምንመለከተው፡፡ በዚህ ራስን የማታለል ልማድ ምክንያት ለመላው ምእመናን በዐዋጅ ቤተ ክርስቲያን ያስቀመጠቻቸውን ሰባቱ አጽዋማት እንኳን ያለ ምንም መነሻ ይህ የአረጋውያን፣ ይህ ደግሞ የካህናት፣ ይህኛው የሕፃናት የሚል ያልተገባ ክፍፍል ሲያደርጉ እንመለከታለን፡፡ ሌሎችም ከቤተ ክርስቲያን ሳይርቁ ከጾም፣ ከጸሎትና ከስግደት ርቀው የጠፋውን ድሪም ሆነዋል፡፡

ድክመቶቻችንን በሌሎች እያሳበብን በደላችንን አምነን ለንስሓ ሳንዘጋጅ፣ የሌሎችን ሕይወት በመንፈሳዊ አገልግሎት ለመሥራት የምንጥር፣ በምድራዊ ታይታና ከንቱ ውዳሴ ብቻ እየተመራን እግዚአብሔርን ሳይሆን ሰዎችን ብቻ በሚያስደስት የይሰሙላና ከንቱ አገልግሎት የምንጠመድ ሆነን እንቀራለን፡፡ ስለሆነም ራስን ከማታለል ተቆጥበን፣ ድካማችንን እያሰብን ሥርየተ ኃጢአትን ለማግኘት ወደ አበው ሊቃውንትና ወደ መምህራነ ንስሓ ቀርበን በደላችንን በመናዘዝ ለመለወጥ እየተጋን የምናገለግል ከሆነ ያኔ ትጉህና ታማኝ አገልጋይ እንሆናለን፤ አገልግሎታችንም “በውኃ ፈሳሾች ዳር እንደተተከለች፣ ፍሬዋን በየጊዜዋ እንደምትሰጥ፣ ቅጠልዋም እንደማረግፍ ዛፍ ይሆናል” (መዝ. ፩፥፫)

የአገልግሎት ጸጋን ለይቶ አለማወቅ

ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ “መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆን ስጦታው ልዩ ልዩ ነው፡፡ ጌታም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፡፡ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አሠራር አለ፡፡ ለሁሉም ጌታ እየረዳ በዕድሉ እንደሚገባውና እንደሚጠቅመው ለእያንዳንዱ በግልጥ ይሰጠዋል፡፡” (፩ቆሮ. ፲፪፥፬-፲፩) እንዲል የምናገለግለው ለአንድ ሰማያዊ ዓለማ ቢሆንም ያንን የምናደርግበት ልዩ ልዩ ጸጋ ከእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ተሰጥቶናል፡፡ የሰው ልጅ በተሰጠው ጸጋና መክሊት እግዚአብሔርን ያገለገለ እንደሆነ አገልግሎቱ ሠላሳ፣ ሥሳና መቶ ያማረ ፍሬ ያፈራ ዘንድ ጊዜ አይወስድበትም፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን በብዙ ወጣቶች አገልግሎት ላይ የሚስተዋለው ፈተናና ተግዳሮት ይኸው የመንፈሳዊ አገልግሎት ጸጋን ለይቶ አለማወቅ ችግር ነው፡፡

አንዳንድ ወጣቶች በዐውደ ምሕረት ላይ በኵራት ቁመው ድምጽ ማጉያውን ጨብጠው ለስብከተ ወንጌል ካልተሰማሩ ያገለገሉ አይመስላቸውም፡፡ ሌሎቹም እንዲሁ መንፈሳዊ አገልግሎት ዝማሬ ከመዘመር ጋር ብቻ ሁኖ ይታያቸዋል፡፡ በዚህ ጸጋን ለይቶ አለማወቅ ድካም ብዙ ወጣቶች ከሌሎች በሚደርስባቸው ተግሣፅና ነቀፋ በመሸማቀቅ እንደ ሎጥ ሚስት (ዘፍ. ፲፱፥፪) ወደ ኋላ ሲመለከቱ በዓለም እየቀለጡ ቀርተዋል፡፡ ወጣትና ታማኝ አገልጋይ ሆነን አትርፈን እንገኝ ዘንድ ከንቱ ውዳሴንና እየኝ ማለትን ብሎም ምድራዊ ክብርን ትተን አንተ ሰይጣን ከፊቴ ወግድ ብለን አሽቀንጥረን በመጣል በተሰጠን ጸጋ በተለያየ የአገልግሎት ዘርፍ ተግተን በመሳተፍ በሰማይ ያለ መዝገባችንን ልናካብት ይገባል፡፡

ማጠቃለያ

ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ጎልማሳ መንገዱን በምን ያቀናል፤ ቃልህን በመጠበቅ ነው” (መዝ. ፲፰፥፱) እንዳለ የቃሉን ወተት በትጋት እየተመገበ ስሜቱን በቅዱስ መንፈስ እየገዛ በእውነትና ለእውነት በመመላለስ የሚተጋ ወጣት አገልጋይ ለመሆን እንበቃ ዘንድ ከሁሉም በፊት ከላይ የተጠቀሱትን ክፍተቶች እንደ ሰንኮፍ አውልቀን እንጣል፡፡ ስለሆነም በጉብዝናችን ወራት ፈጣሪን በማሰብ እናልፍ ዘንድ አገልግሎት ለምርጫ የምናስቀምጠው ጉዳይ ሳይሆን መንፈሳዊ ግዴታ እንደሆነ ልብ ልንለው ይገባል፡፡ “በጎ ነገር ማድረግን የሚያውቅ፣ የማይሠራትም ኃጢአት ትሆንበታለች” (ያዕ. ፬፥፲፯) እንደተባለ በመንፈሳዊ አገልግሎት አለመሳተፍ ኃጢአት ነው፡፡ ከጥፋት ለመዳን ብሎም በዘለዓለማዊ ፍሥሐ ስሙን ለመቀደስ፣ ዘለዓለማዊ ክብርን ለመውረስ “የኢየሩሳሌምን ጥፋት አታሳየን” (ኤር. ፱፥፩-፴) እያልን ለአገልግሎት ዛሬ እንነሣ፣ የመዳን ቀን አሁን ነውና፡፡ ይህንንም በትጋት እንዳንፈጽም እንቅፋት የሚሆኑንን ፈተናዎች ሁሉ በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብና መምህራንን በመጠየቅ አስወግደን፣ ራሳችንን በመንፈሳዊ አገልግሎት አትግተን፣ የኋላውን እየተውን ወደፊት እንገሰግስ ዘንድ የአበው ቅዱሳን ረድኤት አይለየን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር