ዘወረደ

ትዕግሥት ሳዝነው

ከፍጥረት አልቆ በክብር ቢያበጀው፣

አዳም ክብር ሽቶ ክብሩን አቆሸሸው፣

ምንም ሳያጎድል ሁሉን ለእርሱ ሰጥቶ፣

ይቀመጥባት ዘንድ ገነትን ርስት አድርጎ፣

በውስጧ ያሉትን ፍጥረታትን ገዝቶ፣

አምላኩ ሲሾመው ጌታዋ አድርጎ፡፡

አንድ ሕግ ነበረ ለአምላክ ቃል የገባው፣

ከዛፎቹ ሁሉ አንዷን ዛፍ እንዲተው፣

እንዲህ ሲል አዘዘው፡፡

ክፉ እና ደጉን ከምታሳውቀው፡፣

ሞትን እንዳትሞት ከዚ’ች ዛፍ አትብላ፣

ከእርሷ በበላህ ቀን ትሞታለህና፣

ክብሩን ያላወቀ ማዕረጉን የረሣ፡፡

በተሰጠው ፍጥረት አዳም ተታለለ፣

ትእዛዝ እና ሕጉን የአምላኩን ቃል ጣሰ፡፡

 ዕፀ በለስ በልቶ አምላክ ይሆን ዘንድ፣

 በፍጥረት በእባብ ተታለለ ሳይወድ፣

በበላትም ቅፅበት ቆርጦ እንደወሰዳት፣

ክብርና ማዕረጉን አጥቶ ወረደ ከገነት፣

ሞትንም ሊቀምሳት መጣ ወደ መሬት፣

ትእዛዙን ተላልፎ አዳም ቢበድልም፣

ሕግን በመሻሩ በአዳም በደል ቢያዝንም፡፡

ንስሓን ሊሰጠው ይቅር ሊለው ወ’ዶ፣

ከሰማዩ ክብር ከዙፋኑ ወርዶ፣

ከፈጠረው ፍጥረት ከማርያም ተወልዶ፡፡

እርሱ በመውረዱ አዳም እንዲወጣ፣

አምላክ ሰው ሆነ ከእነክብሩ መጣ፣

አዳም የሻውን የአምላክነት ፀጋ፣

በአምላክ ሰው መሆን ከአምላኩ ተጠጋ፡፡

 የአዳም በደል ሊፍቅ የአዳም ቁስል ሊሽር፣

 አምላክ እንዲወርድ ቢያስገድደው ፍቅር፣

 እሱ ባላጠፋው ባልሠራው ኃጢያት፣

 በጅራፍ ተገርፎ በመስቀል ቢሰቅሉት፣

 አምላክ ነፍሱን ሰጥቶ የእርሱን ነፍስ አዳናት፡፡

 እኛም የአዳም ልጆች  ፍቅሩ ያልገባን፣

 አምላክ ይቅር ሲለን እኛ እየበደልን፣

ንስሓን ቢሰጠን በኃጢአት መኖር መርጠን፣

በዘር በጥላቻ በክፋታችን ደምቀን፣

ከተሰጠን ክብር ጌትነትም ወረድን፡፡

ወንድሙን ሊገድል ወዳጁን ሊከዳ፣

ሰው ከንቱ ሰው መና ይደክማል በጓዳ፡፡

ከተሰጠው ፍቅር ከተሰጠው ሕይወት፣

የክፋት አባቱ ዲያቢሎስ በልጦበት፣

 የዘር ጣዖት ሠርቶ ኖረ ሲሰግድለት፣

 ይህን በደል ዐይቶ ልቡናዬ ቢያዝን፣

 አምላክ ውረድና ቅጣን እንዳልለው፣

 እኔም ሰው ነኝና እንዳልቀጣ ፈራው፣

 ቂም በቀል ትዕቢት መለያየት ስመኝ፣

 በኃጢያት በክፋት በበደል ስጎበኝ፣

 አምላክ ዛሬም ውረድ ከበደሌ እጠበኝ፡፡

 የተሰጠኝ ፍቅር መጻሕፍትን ጥፎ፣

 ሐዋርያትን ሹሞ ሕግና ሥርዓትን፣

 ቀኖናን አትሞ ፃድቃን ሰማዕታትን፣

 መምህራንን ጠርቶ ትእዛዙን ሠራልን፡፡

 በደሙ አትሞ ከሕጉ የወጡት በግራው ሲቆሙ፣

 በሕጉ የፀኑት በቀኙ ሊቆሙ፣

ያኔ ሠርቶልናል ከሰማያት ወርዶ፣

ከፈጠራት ፍጥረት ከድንግል ተወልዶ።

ዘወረደ

ትርጕሙ ከሰማየ ሰማያት የወረደ ማለት ነው፡፡ ከሰማየ ሰማያት የወረደውን፣ ከድንግል ማርያም የተወለደውን አምላክ ለማመስገን ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ለመዘከር የሚጾም ጾም ነው፡፡ ጌታችን ጾመ ከማለት አስቀድሞ ከሰማየ ሰማያት መውረዱን ከድንግል ማርያም መወለዱን መናገር አስፈላጊ ነውና የመጀመሪያው ሳምንት “ዘወረደ” ተብሏል፡፡

አምላካችን አምስት ሺህ አምስት መቶው ዘመን ሲፈጸም ከእመቤታችን ከቅድስት ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን፣ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ከሆነ በኋላ ምልዓቱን ሳይለቅ በሰው አካል ተወስኖ ለሠለሳ ሦስት ዓመታት በዚህ ምድር ላይ ተመላልሶ ወንጌልንም አስተምሯል፡፡ ስለዚህ ወረደ” የሚለው ቃል እግዚአብሔር ሰው ሆኖ ያመለክተናል፡፡

ይህ የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት “ጾመ ሕርቃል” እየተባለም ይጠራል፡፡ ሕርቃል (ኤራቅሊዮስ) በ፮፻፲፬ ዓ.ም የነበረ የቤዛንታይን ንጉሥ ነው፡፡ ለክርስቲያኖች ባደረገው ርዳታ ምክንያት አንድ ሳምንት ጾመውለታል፡፡ አባቶቻችንም ይህንን ጾም ወዲህ አምጥተው በየዓመቱ ይጾሙት ነበር፡፡ ዛሬም ድረስ ጾመ ሕርቃል እየተባለ ይጠራል፡፡ (ሙሉ ታሪኩ በፍትሐ ነገሥት ትርጓሜ አንቀጽ ፲፭ ላይ ይገኛል፡፡)

በዚህም መሠረት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን የዐቢይ ጾም ሳምንታትን ከፋፍላ፣ ስያሜ ሰይማ ልጆቿን ታስተምራለች፡፡ በየሣምንቱም በዕለተ ሰንበት ከሚቀርቡት ምንባባት መካከል ከመልእክታት፣ ከግብረ ሐዋርያት፣ ከመዝሙር፣ ከወንጌል ዕለቱን የተመለከቱትን ትሰብካለች፡፡

 ምንባባት
ከቅዱስ ጳውሎስ መልእክታት፡- (ዕብ.፲፫÷፯-፮)

የእግዚአብሔርን ቃል የነገሩአችሁን መምህሮቻችሁን ዐስቡ፤ መልካም ጠባያቸውን አይታችሁ በእምነት ምሰሉአቸው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትናና ዛሬ እስከ ዘለዓለምም የሚኖር እርሱ ነውና፡፡ ሌላ ልዩ ትምህርት አታምጡ፤ ልባችሁ በመብል ያይደለ በጸጋ ቢጸና ይበልጣልና፤ በዚያ ይሄዱ የነበሩ እነዚያ አልተጠቀሙምና፡፡ ድንኳኒቱን ሲያገለግሉ የነበሩ ካህናት ከእርሱ ሊበሉ የማይቻላቸው መሠዊያ አለን፤ ሊቀ ካህናቱ የሚሠዉትን እንስሳ ደም ስለ ኀጢአት ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ያቀርብ ነበርና፤ ሥጋውንም ከሰፈር ውጭ ያቃጥሉት ነበር፡፡ ስለዚህም ኢየሱስ ሕዝቡን በደሙ ይቀድሳቸው ዘንድ ከከተማ ውጭ ተሰቀለ፡፡ አሁንም ተግዳሮቱን ተሸክመን÷ ወደ እርሱ ወደ ከተማው ውጭ እንውጣ፡፡ በዚህ የሚኖር ከተማ ያለን አይደለም የምትመጣውን እንሻለን እንጂ፡፡ በውኑ እንግዲህ በሰሙ አናምን ዘንድ የከንፈሮቻችን ፍሬ የሚሆን የምስጋና መሥዋዕትን በየጊዜው ለእግዚአብሔር ልናቀርብ አይገባንምን? ነገር ግን ለድሆች መራራትን÷ከእነርሱም ጋር መተባበርን አትርሱ፤ እንዲህ ያለው መሥዋዕት እግዚአብሔርን ደስ ያሰኘዋልና፡፡” (ዕብ. ፲፫÷፯-፮)

 (ያዕ. ÷፮-ፍጻ.)

“ነገር ግን ፈጣሪያችን የምትበልጠውን ጸጋ ይሰጣል፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል” ይላል፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔርን እሺ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት፤ ከእናንተም ይሸሻል፡፡ እግዚአብሔርን ቅረቡት፤ ይቀርባችሁማል፤ እናንተ ኃጥኣን እጆቻችሁን አንጹ፤ ሁለት ዐሳብም ያላችሁ እናንተ ልባችሁን አጥሩ፡፡ እዘኑና አልቅሱ፤ ሳቃችሁን ወደ ልቅሶ÷ ደስታችሁንም ወደ ኀዘን መልሱ፡፡ በእግዚአብሔር ፊት ራሳችሁን ዝቅ አድርጉ፤ እርሱም ከፍ ከፍ ያደርጋችኋል፡፡”

 ግብረ ሐዋርያት፡- (ሐዋ.÷፲፫ፍጻ.)

“ከጥቂት ቀን በኋላም ንጉሥ አግሪጳና በር ኒቄ ወደ ቂሣርያ ወርደው ፊስጦስን ተገናኙት፡፡ተገናኙት፡፡በእርሱ ዘንድ ብዙ ቀን ከቈዩ በኋላ ፊስጦስ የጳውሎስን ነገር ለንጉሡ ነገረው፤ እንዲህም አለው÷ “ፊልክስ በእስር ቤት ትቶት የሄደ አንድ እስረኛ ሰው በእዚህ አለ፡፡ በኢየሩሳሌም ሳለሁም ሊቃነ ካህናትና የአይሁድ ሽማግሌዎች ወደ እኔ መጥተው እንድፈርድበት ማለዱኝ፡፡ አኔም፡- ተከሳሹ በከሳሾቹ ፊት ሳይቆም÷ ለተከሰሰበትም ምላሽ ይሰጥ ዘንድ ፋንታ ሳያገኝ ማንም ቢሆን አሳልፎ መስጠት የሮማውያን ሕግ አይደለም ብየ መለስሁላቸው፡፡ ከዚህም በኋላ፤ በዚሁ በተሰበሰቡ ጊዜ ሳልዘገይ በማለዳ በፍርድ ወንበር ተቀምጬ÷ ያን ሰው እንዲያመጡት አዘዝሁ፡፡ የከሰሱትም በቆሙ ጊዜ÷ እኔ እንደ አሰብሁት በከሰሱት ክስ የሠራው ምንም ነገር የለም፡፡ ስለ ሃይማኖታቸው ከሆነው ክርክርና ስለ ሞተው÷ ጳውሎስ ግን ሕያው ነው ስለሚለው ሰው ስለ ኢየሱስ ከሆነው ክርክር በቀር፤ ስለ ክርክራቸውም የማደርገውን አጥቼ ጳውሎስን ወደ ኢየሩሳሌም ሄደህ በዚያ ልትከራከር ትወዳለህን? አልሁት፡፡” አግሪጳም ፊስጦስን÷ “እኔም ያን ሰው ልሰማው እወደለሁ” አለው፤ ፊስጦስም÷ “እንግደያስ ነገ ትሰማዋለህ …” አለው፡፡

ምስባክ፡- (መዝ. ፪፥፲፩)
“ተቀነዩ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ወተሐሠዩ ሎቱ በረዓድ።አጽንዕዋ ለጥበብ ከመ ኢይትመዐፅ እግዚአብሔር፤ ለእግዚአብሔር በፍርሃት ተገዙ፥ በረዓድም ደስ ይበላችሁ። ጥበብን አጽኑአት፤ እግዚአብሔር እንዳይቆጣ።”

ወንጌል፡- (ዮሐ.÷፳፬ )
ጌታችን ኢየሱስም መልሶ÷ “አንተ የእስራኤል መምህራቸው ነህ፤ ነገር ግን አንዴት ይህን አታውቅም?” አለው፡፡ እውነት እውነት እልሃለሁ፤ የምናውቀውን እንናገራለን፤ ያየነውንም እንመሰክራለን፤ ነገር ግን ምስክርነታችንን አትቀበሉንም፡፡ በምድር ያለውን ስነግራችሁ እንዴት ታምኑኛላችሁን? ከሰማይ ከወረደው የሰው ልጅ በቀር ወደ ሰማይ የወጣ የለም፤ እርሱም በሰማይ የሚኖረው ነው፡፡ ሙሴ በምድረ በዳ እባቡን እንደ ሰቀለው የሰው ልጅ እንዲሁ ይሰቀል ዘንድ አለው፡፡ ያመነበት ሁሉ ለዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ አንጂ ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና፡፡ ዓለም በእርሱ ይድን ዘንድ ነው እንጂ በዓለም አንዲፈርድ እግዚአአብሔር ልጁን ወደዚህ ዓለም አልላከውምና፡፡ በእርሱ ያመነ አይፈረድበትም፤ በእርሱ ያላመነ ግን ፈጽሞ ተፈርዶበታል፤ በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም አላመነምና፡፡ ፍርዱም ይህ ነው፤ ብርሃን ወደ ዓለም መጥቶአልና፤ ሰውም ሥራው ክፉ ስለሆነ ከብርሃን ይልቅ ጨለማን መርጦአልና፡፡ ሥራው ክፉ የሆነ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፤ ክፉም ስለሆነ ሥራው እንዳይገለጥበት ወደብርሃን አይመጣም፡፡ አውነትን የሚሠራ ግን ሥራው ይገለጥ ዘንድ ወደ ብርሃን ይመጣል፤ ስለ እግዚአብሔር ብሎ ይሠራልና፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ይሁዳ ምድር ሄደ፤ በዚያም እያጠመቀ አብሮአቸው ተቀመጠ፡፡ ዮሐንስም በዮርዳኖስ ማዶ በሳሌም አቅራቢያ በሄኖን ያጠምቅ ነበር፤ በዚያ ብዙ ውኃ ነበርና፤ ብዙ ሰዎችም ወደ እርሱ እየመጡ ያጠምቃቸው ነበር፡፡ ዮሐንስ ገና ወደ ወኅኒ ቤት አልገባም ነበርና፡፡”
ቅዳሴ
ዘእግዚእነ

ይቆየን፡፡

“ለግቢ ጉባኤ ትምህርቴ የመደበኛው ትምህርቴን ያህል ትኩረት ስሰጠው ነበር፡፡” (ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ)

ክፍል ሦስት                                           

በእንዳለ ደምስስ

ጉባኤ ቃና፡- በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ቆይታዎ ግቢ ጉባኤ ውስጥ በመሳተፍዎ አጋጠሞኛል የሚሉት ችግር ከነበረ ቢገልጹልን?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- እኔ በግቢ ጉባኤ ውስጥ በመሳተፌ ገጠመኝ የምለው ችግር የለም፡፡ እንዲያውም ራሴን እንደ ዕድለኛ ነበር የምቆጥረው፡፡ በግቢ ጉባኤ ውስጥ በመሳተፌ በርካታ ጥቅሞችን ነው ያገኘሁት፡፡ ከመምህራኖቼ፣ ከጓደኞቼ፣ እንዲሁም ከማኅበረሰቡ ጋር የነበረኝ ግንኙነት በጣም ጠንካራና ጤናማ ነበር፡፡ በጣም የሚገርምህ ኅብረተሰቡ ራሱ ተማሪውን ይንከባከባል፣ ያቀርብሃል፤ ስለዚህ እንደ ችግር የማነሳው ገጠመኝ የለኝም ማለት እችላለሁ፡፡ ለዚህም በቅርበት ራስን መግለጥና በቅንነት መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያን ልጅነታችን ስለሌሎች ሕይወት እንጨነቅ ነበርና ያለንን ለመስጠት ወደ ኋላ አለማለት ያስፈልጋል፡፡

መንፈሳዊ ሕይወታችን መደበኛ ትምህርታችንን በአግባቡ እንድንከታተል፣ ዓላማ እንዲኖረን፣ ጠንቃቃ እንድንሆን ስለሚያደርገን ተጠቃሚዎች ነን፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ሌሎች ውጫዊ ነገሮች እንዳይረብሹንና መንፈሳዊ ሕይወታችንን ሊያጨናግፉ ከሚችሉ ነገሮች እንድንርቅ አድርጎናል፡፡

በአገልግሎት ላይ ግን አንዳንድ ይገጥሙን የነበሩ ችግሮች ነበሩ፡፡ እንደ ምሳሌ ባነሳ፡- አንዳንድ ተማሪዎች ወደ ቤተ ክርስቲያን መቅረብ ባለመቻላቸው እኛም አጥብቀን ባለመከታተላችን ሃይማኖታቸውን የቀየሩበት ሁኔታ ነበር፡፡ ያሳዝኑኛል፡፡ ከዚህ ውጪ አብረውን ይማሩ የነበሩ ወንድሞቻችን በተለያዩ የጤና እክሎች ምክንያት ያረፉ ልጆች ነበሩ፡፡ ይህ በጣም አሳዛኝ ነገር እንጂ እንደ ችግር የሚነሣ ጉዳይ አይደለም፡፡ ሌላው አንድ ወቅት ሕመም ገጥሞኝ ለሕክምና ወደ አዲስ አበባ መጥቼ ነበር፡፡ ነገር ግን ጠንክሬ እማር ስለነበር ከትምህርት ክፍሉ ከሁሉም ተማሪ የእኔ ውጤት ነበር ከፍተኛው፡፡ ስለዚህ እንደ ችግር ከምቆጥራቸው ይልቅ እንደ መልካም ነገር የምቆጥራቸው ነገሮች ይበዙብኛል፡፡

ጉባኤ ቃና፡- በርካታ ተመራቂዎች ሲመረቁ የሰጡትን ሜዳልያ ምክንያት አድርገው እርስዎን እንደ አርአያ ይቆጥራሉ፡፡ እነርሱም ከፍተኛ ውጤት አመጣለሁ፣ ሜዳልያዬንም እንደ ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ ለማኅበረ ቅዱሳን እሰጣለሁ ብለው ይጀምራሉ፣ ሲፈጽሙም ቃላቸውን ጠብቀው ሲሰጡ እንመለከታለን፡፡ ለመሆኑ ያኔ እንዴት ሊያስቡትና ሜዳልያዎን ሊሰጡ ቻሉ? ምክንያትዎ ምን ነበር?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡-  ገና ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ስንገባ ከአቀባበል ጀምሮ የተደረገልን እንክብካቤ፣ ምክራቸው፣ በተለይም ጠንካራ ተማሪዎች እንድንሆን፣ ጊዜያችንን በአግባቡ እንድንጠቀም፣ ጎበዝ ተማሪ እንድንሆን፣ ይህንን ማድረጋችን ለራሳችንም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን እንደሚጠቅም፣ በአገልግሎትም እንድንሳተፍ ይመክሩን ነበር፡፡ እኛም ይህንን እንደ መመሪያ ወስደን የምናወጣውን የጊዜ አጠቃቀም ተግባራዊ እያደረግን ውጤታማ ሆነን ለመውጣት ረድቶናል፡፡

የመጀመሪያ ዓመት የመጀመሪያ ሴሚስተር ላይ ፈተና እንደጨረስን በዕለቱ ነበር ከጓደኞቼ ጋር አዲስ አበባ የመጣሁት፡፡ ስለ ውጤት የምጨነቅበት ጊዜ አልነበረም ቤተሰብ ይናፍቅሃል፣ ዕረፍት ትፈልጋለህ፡፡ የዕረፍት ጊዜያችንን ጨርሰን ስንመለስ ቀጥታ ያመራነው ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ነበር፡፡ አንድ በግቢ ጉባኤ ውስጥ ያገለግል የነበረ ወንድማችን የእኔን ውጤት ቀደም ብሎ ሰምቶ ስለነበር በደስታ ነው የተቀበለኝ፡፡ “እንኳን ደስ ያለህ! ከሁሉም ተማሪ የአንተ ውጤት ከፍተኛ ነው፡፡ ጎበዝ! በርታ! እንዲህ ዓይነት ተማሪ ነው የምንፈልገው” ብሎ አበረታታኝ፡፡

ከእኔ ይልቅ እርሱ የነበረው የደስታ ስሜት እስከ ዛሬ አይረሳኝም፡፡ ወዲያውኑ ነው “እኔ ለወንድሞቼ ብዬ የተለየ የሠራሁት ነገር የለም፡፡ በእርግጥ ጠንክሬ ተምሬያለሁ፡፡ የእኔ ውጤት ወንድሞቼን እንዲህ የሚያስደስታቸው ከሆነ በዚሁ ጥረቴ እቀጥላለሁ፤ ስጨርስም ሜዳልያዬን ለእነርሱ ነው የምሰጠው” ብዬ ቃል ገባሁ፡፡ እግዚአብሔርም ረድቶኝ የትምህርት ክፍሌንና የዩኒቨርሲቲው አጠቃላይ አሸናፊ ሆኜ ጨረስኩ፡፡ በገባሁት ቃል መሠረትም በ፲፱፻፺፬ ዓ.ም ማኅበረ ቅዱሳን ጠቅላላ ጉባኤውን ሲያካሂድ በጉባኤው ላይ ተገኝቼ ሜዳልያዬን ሰጠሁ፡፡

ጉባኤ ቃና፡-  እርስዎ የሰጡት ሜዳልያ ለበርካታ ተማሪዎች ውጤታማነት መነሳሳትን ፈጥሯል ማለት ይቻላል፡፡ ሜዳልያቸውንም እያመጡ ለማኅበረ ቅዱሳን በየዓመቱ ያበረክታሉና ይህንን ሲመለከቱ ምን ይሰማዎታል?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- እኔ ለማኅበረ ቅዱሳን ሜዳልያውን የሰጠሁት ሌሎችን ለማነሳሳት ብዬ አልነበረም፡፡ ለወንድሞቼ ደስታ ስል ነበር ይህንን ያደረግሁት፡፡ ነገር ግን በሂደት ለሌሎች መነሳሳትና ውጤታማነት አስተዋጽኦ አድርጎ ከሆነ መልካም ነው፡፡ እኔም በዚህ ደስተኛ ነኝ፡፡

ጉባኤ ቃና፡- በርካታ ተማሪዎች የአብነት ትምህርት ተምረው የዲቁና ማዕረግን ተቀብለው ይወጣሉ፡፡ እርስዎ ይህ ዕድል ገጥሞዎት ነበር? 

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡-  አዎ፡፡ ግቢ ጉባኤ ከገባሁ በኋላ ነው የአብነት ትምህርት የተማርኩትና ዲቁና እስከመቀበል የደረስኩት፡፡ በጣም ጠንካራ ጉባኤ ቤት ነበር፡፡ መምህራችንም በጣም ትጉህ ነበሩ፡፡ ወንበር ዘርግተው ከማስተማር በተጨማሪ ተማሪዎቻቸውን ሁሉ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ይዘው ገብተው ማኅሌት ያስቆሙናል፣ ከአገልግሎት ጋር እንድንተዋወቅ፣ በሄድንበት ሁሉ ቤተ ክርስቲያንን ከማገልገል ወደ ኋላ እንዳንል ይመክሩናል፡፡ ወርኀዊ በዓላት ይሁን ዓመታዊ በዓላት ከኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን አልፈን አጎራባች አጥቢያዎች ድረስ ይዘውን እየሄዱ ማኅሌት እንድንቆም ያደርጉናል፣ በብዛት መኅሌት ላይ የምገኘው የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች   ነበርን፡፡ በተለይም የሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ማኅሌት ከተማው ውስጥ ካሉት ሁሉ ደማቁ ነበር፡፡

ጉባኤ ቃና፡- ቤተሰብ ልጆቻቸውን ወደ ከፍተኛ ትምህርት ሲልኩ ግቢ ጉባኤ ውስጥ እንዲሳተፉ የሚያበረታቱ እንዳሉ ሁሉ ጊዜያችሁን ይሻማባችኋል፤ ወደ ግቢ ጉባኤ እንዳትገቡ እያሉም የሚያስጠነቅቁ ወላጆች አሉና ከተሞክሮዎ ተነስተው ለወላጆች ምን ይመክራሉ?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡– ግቢ ጉባኤ እንዳይገቡ የሚያደርጉ ወላጆች ግቢ ጉባኤን ካለመረዳት የመነጨ ነው፡፡ ከቤተሰቦቻቸውም ጋር አብረው እየኖሩ ሰንበት ትምህርት ቤት አትሂድ የሚል ወላጅም ያጋጥምሃል፡፡ ግንዛቤ ከማጣት ነው ያልተገባ ፍርድ የሚሰጡት፡፡ ኦርቶዶክሳዊ ሆኖ ልጆቹን ቤተ ክርስቲያን አትሂድ የሚል ወላጅ ስለ እምነቱ ያለውን ግንዛቤ በትክክል ተረድቷል የሚል ግምት የለኝም፡፡ ነገር ግን ወላጆች አንዳንድ ከሚያይዋቸውና ከሚሰሟቸው አሉታዊ መረጃዎች የተነሳ ሰንበት ትምህርት ቤትን ወይም ግቢ ጉባኤያትን የሚስሉበት መንገድ ትክክል ካለመሆን የመነጨ ነው፡፡

በትክክል ግቢ ጉባኤን ወይም ሰንበት ትምህርት ቤትን የሚያውቅ ወላጅ ግን እንዲህ አይልም፡፡ እንዲያውም ዘመኑ ከሚያመጣቸው አንዳንድ ያልተገቡ ድርጊቶችና መረጃዎች የተነሳ ልጆቻቸው እንዳይበላሹባቸው ስለሚሰጉ ወደ ግቢ ጉባኤና ሰንበት ትምህርት ቤት የሚልኩ በርካታ ናቸው፡፡ ወላጆች ልጆቻቸውን ማድመጥ፣ መንገድ መምራት፣ ትክክለኛውን መስመር ይዘው እንዲያድጉ የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ለልጆቻቸው የሚበጃቸውን የማሳየት፣ ከልጆች በተሻለ ስለ ጉዳዩ ከፍ ያለ ግንዛቤው ያላቸው እንዲሆኑ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ወደ ሰንበት ትምህርት ቤት የሚሄዱ ልጆች በአብዛኞቹ በተመሳሳይ የዕድሜ ክልልና ተመሳሳይ አስተሳሰብ ያላቸው ናቸው፡፡ ነገር ግን አካባቢያቸውም ሆነ ወላጆቻቸው በተበታተነ ሁኔታ ውስጥ ስለሚገኙ እኩል ግንዛቤ መፍጠር አይቻልም፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ግን ወላጆችን አሰባስቦ ማስተማር የሚቻልበት ጉባኤ ሊፈጠር ያስፈልጋል፡፡ ይህ ጉባኤ ቤተ ክርስቲያን ቢኖራት ኖሮ አሁን የምናያቸው ችግሮች አይፈጠሩም ነበር፡፡ የሀገር መሠረቱ ወላጆቻችን ናቸው፡፡ ለምሳሌ የእኔ እናት ዘመናዊ ትምህርት የተማረች አይደለችም፣ ነገር ግን ሀገሯን የምትወድ፣ ዘወትር ቤተ ክርስቲያን የምትሳለም፣ እኛንም ወደ ቤተ ክርስቲያን እንድንሄድ ግፊት የምታደርግ እናት ናት፡፡ በእርሷ አቅም ልትነግረን፣ ልታሳየን የፈለገችውን ነገር ነፍጋ አላሳደገችንም፡፡ ቤተ ክርስቲያን እንድንሄድ፣ ጥሩ ዜጎች እንድንሆን የከፈለችው ዋጋ አለና በእኛ እርሷም ደስተኛ ናት፡፡

ትምህርት ቤት ገብቶ የወጣውና ፊደል የቆጠረው፣ ዲግሪ፣ ዶክትሬት አለኝ የሚለው ወላጅ ግን ለልጁ ምንድነው የሚመኝለት? ምን እንዲሆንልት ነው የሚፈልገው? ለዚያ የሚመጥን ሥራ ከወላጆች ይጠበቃል ማለት ነው፡፡ ግቢ ጉባኤ አትሂዱ ሳይሆን ሂዱ ግን ስትሄዱ ይህንን አድርጉ፣ ይህንን ደግሞ አታድርጉ ብሎ ለይቶ ሊመክር፣ ሊከታተል ይገባዋል ወላጅ፡፡ ግቢ ጉባኤ እንዳይሄዱ ቢፈልጉ እንኳን ቤተ ክርስቲያን ሂዱ ብለው ልጆቻቸው ከእግዚአብሔር ጋር ያላቸውን ግንኙነት እንዲያጠናክሩ መርዳት አለባቸው፡፡ ወላጆች በማያውቁት ነገር ላይ የማይገባ ሐሳብ ባይሰጡም መልካም ነው፡፡ አሁን ደግሞ ጊዜው እየከፋ ነው የመጣው፡፡ ሁሉም የማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ሆኗል፣ ሁሉም አስተያየት ሰጪ ነው፡፡ ይህ ተገቢ አይደለም፡፡ ያላለፉበትን መንገድ ልምድ ካላቸው ሰዎች ቢጠይቁ፣ ከልጆቻቸው ጋር ቢመካከሩ መልካም ነው፡፡

ማኅበረ ቅዱሳን ብዙ የአገልግሎት መስኮች ላይ ስለተሰማራ እዚህ ላይ እንደሚቸገር ይገባኛል፡፡ እኔም የአገልግሎቱ አካል ስለሆንኩ በቅርብ የምረዳው ነው፡፡ ወላጆች ላይ መሥራት ሀገርና ቤተ ክርስቲያን ላይ መሥራት ማለት ነው፡፡ በተለይ አሁን በእኛ ዕድሜ ላይ ያሉ ወላጆች ላይ ቢሠራ ልጆቻቸውን እንዴት መያዝ እንደሚችሉ ማስተማር ልጆቻችን ኮሌጅ ሲገቡ አይቸገሩም፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተኮትኩተው የማደግ ዕድሉን ስለሚያገኙ ኮሌጅ ሲገቡ ሁሉንም ዐውቀውና ተረድተው ይገባሉ፡፡ በዚህ መልኩ ከሄድን ለውጥ ሊመጣ ችላል ብዬ አስባለሁ፡፡

ጉባኤ ቃና፡- የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ተመርቀው ከወጡ በኋላ ብዙዎቹ ከአገልግሎት ይርቃሉ፡፡ ሕይወት ከምረቃ በኋላ እንዴት መሆን አለበት ይላሉ?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- ይህንን በሁለት መንገድ ልንመለከተው እንችላለን፡፡ ግቢ ጉባኤ ውስጥ ያስተማርናቸው ሁሉ አገልጋይ እንዲሆኑ መመኘት መልካም ቢሆንም በቅድሚያ ጥሩ ምእመን ሆኖ መገኘት አለበት፡፡ ስለዚህ ሁሉም አገልጋይ መሆን አይችልም፡፡ ጥሩ ምእመን መሆን ከቻለ ልጆቹን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ እንዲያድጉ የሚያደርግ ከሆነ አላገለገለም ልንለው አንችልም፡፡ ጥሩ ምእመን ጥሩ አገልጋይ ነው፡፡ የሰበካ ጉባኤ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እኛም ባሉበት አጥቢያ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ነው የምንመክራቸው፡፡ ስለዚህ አስተምሯልና ግዴታ ማኅበረ ቅዱሳን ውስጥ መግባት አለባቸው ልንል አንችልም፡፡ ካገኘነው የጣነውን መቁጠር ልማድ ስለሆነብን እንጂ ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤ ውስጥ ያስተማራቸው ሁሉ ጠፍተዋል ማለት አይደለም፡፡ ጥሩ ጥሩ ምእመናንን ማፍራታችንም ማሰብ አለብን፡፡ ሌላው ከምረቃ በኋላ የቤተሰብ ኃላፊ መሆን፣ ቤተሰብ የማስተዳደርና የተለያዩ ሥራዎችን መሥራት፣ ልጆችን መንከባከብ፣ ማኅበራዊ ኃላፊነት ሁሉ ስለሚሻሙት ሁሉም በአባልነት ያገልግል ማለት አይቻልም፡፡

ጉባኤ ቃና፡-  ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤያት ላይ የሚሰጠውን አገልግሎት ከማጠናከር አንጻር ሊያከናውናቸው ወይም ሊያሻሽላቸው ይገባል የሚሏቸው ጉዳዮችን ቢገልጹልን?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- ማኅበረ ቅዱሳን በርካታ የአገልግሎት ዘርፎች ውስጥ ውጤታማ አገልግሎት እያከናወነ እንዳለ ሁላችንም የምንረዳው ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን የነገዋን ኢትዮጵያንና ቤተ ክርስቲያንን የሚጠቅምና የሚታደግ ትውልድ ለመፍጠር ወላጆች ላይ መሥራት አለበት እላለሁ፡፡ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎቻችን በዕረፍት ጊዜያቸው ከመላው ቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲመካከሩ ማድረግ ያለውን ክፍተት እንዲሞላ ያደርገዋል፡፡

አሁን ባለንበት ነባራዊ ሁኔታ የግቢ ጉባኤ አገልግሎት ማስተባበሪያ ውስጥ ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ስለሆነ አጠናክሮ መቀጠል፣ መጻሕፍትን በአግባቡ ለተማሪዎች ተደራሽ ማድረግ፣ ቴክኖሎጂን ተጠቅመን የገጽ ለገጽ ትምህርቶችን ማሠራጨት፣ የተለያዩ መተግበሪያዎችን   ማበልጸግ፣ በሞባይል ስልኮቻቸው ተከታታይ ትምህርቶችን በድምጽ ወይም በጽሑፍ የሚያገኙበት ሁኔታ መፍጠር፣ የግቢ ጉባኤያት ኅብረትን ማጠናከር ያስፈልጋል፡፡ በተጨማሪም ከግቢ ጉባኤ ከወጡ በኋላ በሥነ ምግባር የታነጹና በተመረቁበት ሙያ በብቃት አገልግሎት የሚሰጡ፣ ሁል ጊዜ ራሳቸውን ለማሻሻል የሚተጉ እንዲሆኑ መንገዱን ማመላከት ያስፈልጋል፡፡ ለደረስንበት ደረጃ እግዚአብሔርን ማመስገን፣ ላልደረስንበት ደግሞ በሥራ ላይ የታገዘ ትጋት ሊኖር ይገባል፡፡

አሁን ተመርቀው የሚወጡ ልጆች የሚቀጥለውን የሕይወት ምዕራፍ አንድ ብለው የሚጀምሩበት ነው፡፡ በተሠማሩበት የሥራ መስክ ጠንካራና የሚመሰገኑ ባለሙያዎች እንዲሆኑ እመክራለሁ፡፡   እንደ እከሌ ተብለው እንደ ምሳሌ ሊጠቀሱ የሚችሉ መሆን አለባቸው፡፡ በምንም ነገር ውስጥ ጠንክረው ሳይሠሩ በአቋራጭ የሚገኝ ነገር የለምና እዚህ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሊሠሩበት ይገባል፡፡

ጉባኤ ቃና፡- ለነበረን ቆይታ በእግዚአብሔር ስም እናመሰግናለን፡፡

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

“ለግቢ ጉባኤ ትምህርቴ የመደበኛው ትምህርቴን ያህል ትኩረት ስሰጠው ነበር፡፡” (ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ)

ክፍል አንድ                                             

በእንዳለ ደምስስ

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ በ፲፱፻፹፯ ዓ.ም ከኮልፌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ፲፪ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ፬ ነጥብ በማምጣት በ፲፱፻፹፰-፲፱፻፺፬ ዓ.ም በጅማ ዩኒቨርስቲ የሕክምና ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በሰባት ዓመታት የሕክምና ትምህርት ቆይታቸው ከትምህርት ክፍሉ እና ከአጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው ተመራቂዎች በከፍተኛ ማዕረግ የሜዳልያ ተሸላሚ በመሆን የሕክምና ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ባስመዘገቡት ውጤት መሠረትም በዩኒቨርሲቲው ለሁለት ዓመታት በመምህርነት ተመድበው አገልግለዋል፡፡

ለሰባት ዓመታት በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ በየዓመቱ ዩኒቨርሰቲው የሚያዘጋጃቸውን ሽልማቶች በተደጋጋሚ ለመቀበል ችለዋል፡፡ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው በቆዩባቸው ጊዜያት በግቢ ጉባኤ ውስጥ በንቃት ከሚሳተፉ ወንድሞችና እኅቶች መካከል ነበሩ፡፡

ፕ/ር እንግዳ በሙያቸው በተለያዩ ሆስፒታሎች ውስጥ ያገለገሉና በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሆስፒታል ውስጥ በሚገኘው የሕክምና ኮሌጅ ውስጥ በኃላፊነትና በመምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በሙያቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦም ከተለያዩ ተቋማት ሽልማቶችን ለማግኘት የቻሉ ባለሙያ ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት የካቲት ፲ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የማኔጅመንት ቦርድ የዶ/ር እንግዳ አበበን መረጃዎች ከገመገመ በኋላ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰጥቷል፡፡ ፕሮፌሰር እንግዳ አበበ ገላን የሕክምና ዲግሪያቸውን (MD) ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ፣ የቀዶ ሕክምና ስፔሻሊቲ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቀዶ ሕክምና እንዲሁም የሰብ-ስፔሻሊቲ ዲግሪያቸውን በኩላሊት ንቅለ ተከላ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የሕክምና ኮሌጅ ያገኙ ሲሆን፤ የተለያዩ አጫጭር የሞያ ሥልጠናዎችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር መከታተላቸውን የሕክምና ኮሌጁ አስታውቋል፡፡

ፕሮፌሰር እንግዳ አበበ ገላን በግላቸውና ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር ከ፵ በላይ በምርምር የተደገፉ ጥናታዊ ፅሁፎችን በታወቁ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ መጽሔቶች ላይ ለኅትመት አብቅተዋል፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሕክምና ኮሌጅ በሚገኘው የሕክምና ትምህርት ቤት ውስጥ የቀዶ ሕክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ወደ ቃለ ምልልሳችን ከመግባታችን በፊት አብረዋቸው የሚሠሩ ባለሙያዎች ስለ ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ የሰጡትን የምስክርነት ቃል በጥቂቱ እነሆ፡-

“እጅግ በጣም ታታሪ እና ትሁት ስለሆነው ፕ/ር እንግዳ አበበ ሳወራ በኩራት ነው፡፡ ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል የሚሄድ ሁሉ ያውቀዋል፡፡ ጠዋት ታካሚዎችን ስንጎበኝ ለአንድ ቀን የተኛ ታካሚ እንኳን በእርሱ መታየት ይፈልጋል፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚማሩ ተማሪዎች ሁሉ እንደ እርሱ መሆን ይፈልጋሉ፡፡ በሆስፒታል ውስጥ በሚሠሩ ሰዎች ሁሉ የተከበረ ነው፡፡ የቀዶ ጥገና ፕሮፌሰርና የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሐኪም የሆነው ፕ/ር እንግዳ አበበ ለእኛ ልዩ አርአያችን ነው፡፡” (ዶ/ር ፍራኦል)

“በእርሱ መማር መቻሌ ታላቅ ዕድል ነው፡፡ ሰው አክባሪ፣ ትሁት፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ነው፡፡”(ምሕረት ተዘራ)

“የተባረኩ እጆች፣ የሚደንቅ ዕውቀት ያለው ሰው ነው፡፡ ከእርሱ ጋር ቀዶ ጥገና ከገባህ የሚያሳስብህ አይኖርም፡፡”(ቶሌ ካን ያደቴ)

“በሀገራችን ካሉ ምርጥ የቀዶ ጥገና ሐኪሞች አንዱ ነው፡፡ ትህትናው፣ ዕውቀቱ እና ታማኝነቱ ሁሉም ተስማምተው ስለ እርሱ መልካምነት እንዲያወሩ አድርጎታል፡፡”(አዲስ ዓለም ገንታ)

“ፕ/ር እንግዳ እጅግ የምትደነቅ ትሁት እና ሥራ ወዳድ ሰው ነህ፡፡ አብሬህ በመሥራቴ ዕድለኛ እንደሆንኩ ይሰማኛል፡፡” (ቤላ ሮማን)

“እርሱ በጣም የሚደንቅና ታላቅ ሰብእና ያለው ሰርጀን ነው፤ በጣም ትሁት፣ ታታሪና ጠንካራ ሠራተኛ እንዲሁም ለታካሚዎች አክብሮት የሚሰጥ ሰው ነው፡፡ እርሱን በቃላት መግለጽ አይቻልም፡፡ በእርሱ በመማሬ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡” (አያንቱ ተስፋዬ)

ከላይ የቀረበው ምሥክርነት “Hakim 2011 Nominee” በተሰኝ ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ሲሆን ከዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ ጋር በሕክምናው ዘርፍ የሠሩ እና የተማሩ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ለመሆኑ ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ ማን ናቸው? በየጊዜው የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን ታሳቢ በማድረግ በምናሳትማቸው የጉባኤ ቃና መጽሔት እትሞቻችን በግቢ ጉባኤያት ውስጥ ያለፉና የሕይወት ተሞክሯቸው ሌሎችን ያስተምራል ያልናቸውን ወንድሞችና እኅቶችን በቃና እንግዳ ዓምዳችን እናቀርባለን፡ እኛም በዚህ ዝግጅታችንም የግቢ ጉባኤ ቆይታቸውን መሠረት አድርገን ከሕይወት ተሞክሯቸው ያካፍሉን ዘንድ ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበን እንግዳችን አድርገናቸዋል፡፡ መልካም ቆይታ ይሁንላችሁ፡፡

ጉባኤ ቃና፡- ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከመግባትዎ በፊት ለቤተ ክርስቲያን የነበረዎትን ቅርበት ቢገልጹልን?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- ተወልጄ ያደግሁት አዲስ አበባ ነው፡፡ ልጅ ሆኜ እንደማንኛውም ሕፃን እናቴ ወደ ቤተ ክርስቲያን ትወስደኝና ታስቆርበኝ ነበር፡፡ በዕድሜ ከፍ ስል ከሌላ ጊዜ በተለየ ሁኔታ የፍልሰታ ለማርያም ጾምን በጉጉት እጠብቀው ስለነበር ከሰፈር ጓደኞቼ ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ እቆርብ ነበር፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ስከታተልም ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን የረቡዕ ሠርክ እና እሑድ ከቅዳሴ በኋላ ልዩ ጉባኤ በየዐሥራ አምስት ቀኑ ይካሄድ ስለነበር ያለማቋረጥ እሳተፍ ነበር፡፡ በሠርክ ጉባኤም እየተገኘሁ በመማር ስለ እምነቴና ስለ ቤተ ክርስቲያን ለማወቅ ጥረት ከማድረግ ወደ ኋላ አላልኩም፡፡ በተለይም በወቅቱ ያስተምሩን የነበሩት መምህራን በዘመኑ ላለነው ወጣቶችና ኦርቶዶክሳውያን አርአያ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ከልጅነቴ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንን ለማወቅና ስለ እምነቴ ለመረዳት የቻልኩትን አድርጌያለሁ ማለት እችላለሁ፡፡ ይህም በወጣትነት ዘመኔ ራሴን እንድገዛና በፈሪሃ እግዚአብሔር እንድታነጽ አድርጎኛል፡፡

ጉባኤ ቃና፡- የከፍተኛ ትምህርትን ለመከታተል ከቤተሰብ ርቆ መሄድ እንዴት ይገልጹታል?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- ከቤተሰብ መራቅ በራሱ አስፈሪ ያደርገዋል፡፡ ለአንዲት ቀን ከቤተሰብ ተለይቶ የማያውቅ ተማሪ በአንድ ጊዜ ወደተመደበበት ለመሄድ ሲታሰብ ከራስ አልፎ ቤተሰብ ውስጥ የሚፈጥረው ስጋት ቀላል አይደለም፡፡ በቤተሰብ በኩል ምክሮችና መመሪያዎች ይበዙብሃል፤ “እንዲህ አድርግ፣ እንዲህ ደግሞ አታደርግ” ትባላለህ፡፡ በዚህ ላይ ወጣትነት በራሱ አዲስ ነገር ለማየትና ለመሞከር ፍጥነት የሚታይበት ጊዜ ነው፡፡ ለተወሰኑ ቀናት አካባቢውን ለማጥናትና ለመልመድ ሲባል ቁጥብነት በተማሪው ዘንድ ይታያል፡፡

እኔ የተመደብኩት ጅማ ዩኒቨርሲቲ ነበር፡፡ እንደማንኛውም ተማሪ ፍርሃት ይኖራል፡፡ ነገር ግን ብዙ አልተቸገርኩም፡፡ ከእኛ ቀድመው ወደ ዩኒቨርሲቲው የገቡና የግቢ ጉባኤ ተሳታፊ የነበሩ ወንድሞችና እኅቶች አውቶቡስ ተራ ሄደው ነው የተቀበሉን፡፡ ቦርሳችንን ተሸክመው እየተንከባከቡ እግራችንን በሽሚያ አጥበው፣ አስመዘግበውን፣ ማደሪያ ክፍላችን ድረስ ወስደው ነው ያስገቡን፡፡ በዚህ እንክብካቤ ውስጥ ፍርሃት ይጠፋል፡፡ በጣም ደስ የሚል አቀባበል ነበር፡፡ አንዳንዶች ቶሎ ለመልመድ ቢቸገሩም በአብዛኛው ግን ቶሎ ይለምዳል፡፡ ስለዚህ እኔ አልተቸገርኩም ማለት እችላለሁ፡፡

ጉባኤ ቃና፡- ግቢ ጉባኤ ውስጥ መሳተፍ እንዴት ጀመሩ?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- ቀድሞ መርካቶ ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ሠርክ ላይ ይሰጥ የነበረው የወንጌል ትምህርትና አገልግሎት በጣም ረድቶኛል፡፡ በተለይ በወቅቱ ያገለግሉ የነበሩ መምህራን እግር ሥር ቁጭ ብለን እንማር ስለነበር እኔም አንድ ቀን ወደ አገልግሎት እንደምገባና እንደ እነርሱ ባይሆንም የአቅሜን አበረክታለሁ የሚል ሕልም ነበረኝ፡፡ በወቅቱ በሚያገለግሉ ወንድሞቻችን ላይ በጣም መንፈሳዊ ቅናት እቀና ነበር፡፡ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ስገባ የነበረው ግቢ ጉባኤ በጣም ጠንካራና የተደራጀ ነበር፡፡ አስተባባሪዎቹም የሚመጣውን ተማሪ የሚንከባከቡበት መንገድ አስደሳች ስለነበር ገብተን መንፈሳዊውን ማዕድ ለመካፈል አልተቸገርንም፡፡ ቤተ ክርስቲያን መሄድ የምትፈልጉ ኑ እናሳያችሁ እያሉም ይወስዱን ስለነበር እኔም ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ ለመግባት ችያለሁ፡፡  እኛን ለማቅረብና ግቢ ጉባኤ ውስጥ እንድንማር የሚያደርጉት ጥረት፣ በዚያውም እንደ አቅማችን በአገልግሎት እንድንሳተፍ ያበረታቱን ነበር:: የመጀመሪያ ዓመት ላይ በግቢ ጉባኤው አማካይነት ይሰጥ የነበረውን መንፈሳዊ ትምህርት በመማር ነው ያሳለፍኩት፡፡ መምህራኖቻችንም ቤተ ክርስቲያንን እንድንወድ፣ የጸሎት ሕይወት እንዲኖረን፣ ጊዜያችንን አጣጥመን ውጤታማ ሆነን እንድንወጣ ዘወትር ይመክሩን ነበር፡፡

ይቆየን

“ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፣ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኵሉ” (ድጓ ዘአስተርእዮ ማርያም)

በእንዳለ ደምስስ

አስተርእዮ ቃሉ አስተርአየ፤ ታየ፣ ተገለጠ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የተገኘ ቃል ሲሆን መታየት፣ መገለጥ ማለት ነው። ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስን ነሥቶ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማሕፀኗ አድሮ የተወለደበት (በሥጋ የተገለጠበት)፣ አንድነት፣ ሦስትነቱም የተገለጠበት ወቅት በመሆኑ ከልደት በዓል እስከ ጥር መጨረሻ ዘመነ አስተርእዮ በመባል ይታወቃል። የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በዓለ ዕረፍትም በዘመነ አስተርእዮ ውስጥ ስለሚውልና ስለሚከበር “አስተርእዮ ማርያም” ተብሏል።

ታላቁ የቤተ ክርስቲያናችን አባት ቅዱስ ያሬድም በእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞት እጅግ ተደንቆ “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፣ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኲሉ፤ ሞት ለማንኛውም ሰው ሁሉ የተገባና የማይቀር ነው፣ የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል” በማለት ገልጾታል።(ድጓ ዘአስተርእዮ ማርያም)፡፡

የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞትና ትንሣኤ እንዴት ነው ቢሉ፤ ቅዱሳን አባቶቻችን ነገረ ማርያም በተሰኘው የምስጋና መጽሐፍ በስፋት ይተርኩታል፡-

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በስልሣ አራት ዓመቷ ከዚህ ዓለም ዐርፋለች፡፡ እንደምን ነው ቢሉ ሦስት ዓመት ከወላጆቿ ከሐና እና ከኢያቄም፣ ዐሥራ ሁለት ዓመት በቤተ መቅደስ ሐርና ወርቅ አስማምታ ስትፈትል ኑራለች፡፡ በዐሥራ አምስት ዓመቷ ከቤተ መቅደስ ወጥታም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በግብረ መንፈስ ቅዱስ ፀንሳ፣ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኗ አድሮ ተወልዷል፡፡ ሠላሳ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከልጇ ከወዳጇ ከጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ጋር ከሀገር ሀገር፣ ረሃቡንና ጥሙን ታግሳ እስከ ዕለተ ስቅለቱ አብራው ኑራለች፡፡ በስቅለቱ ጊዜም እጅግ ይወደው ከነበረው ከወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ጋር በመስቀሉ ሥር ተገኝታለችና እናቱን ለቅዱስ ዮሐንስ አደራ ሰጥቷታል፡፡ ለቅዱስ ዮሐንስ ብቻ ሳይሆን በእርሱ በኩል ለክርስቲያኖች ሁሉ ተሰጥታናለች፡፡ በቅዱስ ዮሐንስ ቤትም ዐሥራ አምስት ዓመታትን ኖራለች፡፡ እነዚህን ስንደምር ለስልሣ አራት ዓመታት በዚህ ምድር ላይ እንደኖረች እንረዳለን፡፡

ስልሣ አራት ዓመት በዚህ ዓለም ኖራም ጥር ፳፩ ቀን በዕለተ እሑድ ጌታ እልፍ አዕላፋት መላእክቱን አስከትሎ መጥቶ “እናቴ ሆይ ከዚህ ዓለም ድካም ላሳርፍሽ መጣሁ” አላት።  እርሷም “ልጄ ሰማይና ምድር የማይወስኑህ፣ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በማኅፀኔ ተሸክሜ፣ በድንግልና ወልጄህ እሞታለሁን?” አለችው። ወደ ሲኦል ወስዶም በሲኦል የሚሠቃዩ ነፍሳትን አሳይቶ “እናቴ ሆይ ሞትሽ ለእነዚህ ሁሉ ነፍሳት ቤዛ ይሆንላቸዋል” አላት። እርሷም በሲኦል ያሉትን ነፍሳት ሥቃይ ከተመለከተች በኋላ አዝና “ይሁን” አለችው። ቅዱስ ሥጋዋን ከቅዱስ ነፍሷ ለይቶ ነፍሷን በመላእክት ዝማሬ በይባቤ ወደ ሰማይ አሳረጋት። ደቀ መዛሙርቱንም ከያሉበት በደመና ጠቅሶ ካለችበት አድርሶ “የእመቤታችሁን ሥጋዋን በክብር አሳርፉ” አላቸው። (ተአምረ ማርያም)፡፡

ሐዋርያት በአጎበር አድርገው ወደ ጌቴ ሰማኒ ይዘው ሲሄዱ አይሁድ በምቀኝነት ተነሣስተው ቀድሞ ልጇ ተነሣ፣ ዐረገ እያሉ ሲያውኩን ይኖራሉ አሁን ደግሞ እርሷን ተነሣች፣ ዐረገች እያሉ ሊያውኩን አይደለምን? በእሳት እናቃጥላታለን ብለው ተነሡ። ታውፋንያ የሚባል አይሁዳዊ በትዕቢት ተራምዶ አጎበሩን ጨበጠው። ጌታችንም መልአኩን ልኮ በሰይፍ እጁን ቆረጠው፣ ከአጎበሩም ተንጠልጥሎ ቀረ። ታውፋንያ የደረሰበትን ተመልከቶ በድያለሁ ማሪኝ ብሎ ቢማጸናት እጁ ተመልሶለታል። ከዚህም በኋላ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከደቀ መዛሙርቱ ቅዱስ ዮሐንስን አስከትሎ በደመና ነጥቆ፣ ከገነት ወስዶ ከዕፀ ሕይወት ሥር አኖራት።

ቅዱስ ዮሐንስ ሲመለስም ደቀ መዛሙርቱ በአንድነት ሆነው “እንደምን ሆነች?” አሉት፡፡ እርሱም “ከገነት ከዕፀ ሕይወት ሥር አለች” አላቸው፡፡ ደቀ መዛሙርቱም ቅዱስ ዮሐንስ የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ዕርገት አይቶ እኛ ሳናይ ብለው በነሐሴ መባቻ ጾም ጀመሩ፡፡ ሁለት ሱባኤ ሲፈጸምም እሑድ አምጥቶ ሰጥቷቸው ቀብረዋታል፡፡ በሶስተኛው ቀን ማክሰኞ ከመ ትንሣኤ ወልዳ፣ እንደ ልጇ ተነሥታለች።

በዚህ ጊዜ ቅዱስ ቶማስ አልነበረምና ደመና ጠቅሶ ከሀገረ ስብከቱ ሲመጣ ስታርግ አገኛት “ቀድሞ የልጅሽን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁ፣ ዛሬ ደግሞ የአንቺን ትንሣኤ ሳላይ ቀረሁን?” ብሎ ከሐዘኑ የተነሣ ከደመናው ላይ ወደ መሬት ሊወድቅ ወደደ፡፡ እመቤታችንም “አይዞህ አትዘን እነርሱ ትንሣኤዬንና ዕርገቴን አላዩም አንተ ግን አይተሃልና ተነሣች፣ ዐረገች ብለህ ንገራቸው” ብላ የያዘችውን ሰበን ሰጥታ ሰደደችው። ከዚህ በኋላ ሄዶ ሐዋርያት በተሰበሰቡበት “የእመቤታችን ነገር እንደምን ሆነ?” አላቸው፡፡ “አግኝተን ቀበርናት” አሉት፡፡ “ሞት በጥር፣ በነሐሴ መቃብር? ተዉ ይህ ነገር አይመስለኝም” አላቸው። ቅዱስ ጴጥሮስ “አንተ ሁል ጊዜ ልማድህ ነው፣ አንተ ብቻ ተጠራጥረህ አትቀርም ሰውን ሁሉ ስታጠራጥር ትኖራልህ” ብሎ ተቆጥቶ ወደ መቃብሯ ሄደው ቢከፍቱት የእመቤታችንን ሥጋ አጡት፡፡ ሁሉም ደንግጠው በቆሙበት ሐዋርያው ቶማስም አታምኑኝም ብዬ እንጂ “እመቤታችንስ ተነሣች፣ ዐረገች” አላቸው፡፡ የያዘውንም ሰበን ሰጥቷቸው ለበረከት ተካፍለውታል። በዓመቱ ሐዋርያት “ቅዱስ ቶማስ ትንሣኤሽንና ዕርገትሽን አይቶ እኛ ሳናይ” ብለው ነሐሴ አንድ ቀን ጾም ጀመሩ፡፡ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በ፲፮ኛው ቀን እመቤታችንን መንበር አድርጎ፣ ቅዱስ ጴጥሮስን ካህን፣ ሊቀ ዲያቆናት ቅዱስ እስጢፋኖስን ሠራዒ ዲያቆን አድርጎ በዚያው ላይ ቀድሶ አቁርቧቸዋል። ቤተ ክርስቲያንም ይህንን መታሰቢያ አድርጋ በየዓመቱ ታከብረዋለች። ቅዱስ ያሬድ በዚህ ተደንቆም “ሞትሰ ለመዋቲ ይደሉ፣ ሞታ ለማርያም የዐጽብ ለኵሉ፤ ሞት ለማንኛውም ሰው ሁሉ የተገባና የማይቀር ነው፣ የማርያም ሞት ግን ሁሉን ያስደንቃል” በማለት ተናገረ፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሞታ እንደማትቀር፣ እንደምትነሣና እንደምታርግ ጠቢቡ ሰሎሞንም ምሥጢር ተገልጦለት ሲናገር “ወዳጄ ሆይ ተነሺ፣ መልካምዋ ርግቤ ሆይ ነዪ” በማለት ተናግሯል፡፡(መኃ.፪. ፲)፡፡ ምንም እንኳን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ነፍስ፣ ንጽሐ ልቡናን አስተባብራ የያዘች ብትሆንም የሥጋ ሞት ለማንም እንደማይቀር ሲያስረዳም “ርግብየ ተንሥኢ ወንዒ፣ ርግቤ ሆይ ተነሺ፣ ነዪ” አለ፡፡

በተአምረ ማርያም መግቢያ ስለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ክብርና ቅድስና የተጠቀሰውን በማስከተል ጽሑፋችንን እናጠቃልል፡- “እንደ እመቤታችን እንደ ማርያም የአብ ማረፊያ የሆነ ማነው? እንደ እመቤታችን እንደ ማርያም የወልድስ ማደሪያ የሆነ ማነው? እንደ እመቤታችን ማርያም የመንፈስ ቅዱስ ቤት የሆነ ማነው? ለሰው ኃጢአት ሳይሠራ መኖር ይቻለዋልን? ከአራቱ ባሕሪያት ከተፈጠረ ሰው ከእመቤታችን በቀር እሳትን የተሸከመ፣ ኃጢአትንም ያልሠራ የለም፤ እመቤታችን ማርያም ከመላእክት ይልቅ ንጽሕት ናት፣ እመቤታችን ማርያም ከሴቶች ሁሉ ትበልጣለች፡፡ የእመቤታችን ማርያም ሐሳብ እንደ አምላክ ሐሳብ ነው፡፡ የእመቤታችን ማርያም መልኳ እንደ አምላክ መልክ ነው፣ የአምላክን መልክ ይመስላል፡፡ እመቤታችን ማርያም ንጽሕት በመሆንዋ አምላክን እንዲያድርባት አደረገችው፡፡ እመቤታችን ማርያም ለአምላክ የደስታ ማደሪያ ሆነችው፡፡ እመቤታችን ማርያም አምላክን በድንግልና ወለደችው፡፡ እመቤታችን ማርያም በነቢያት ትነገር ነበር፡፡ እመቤታችን ማርያም በሐዋርያትም ትነገር ነበር፡፡ እመቤታችን ማርያም በፍጥረት አንደበት ትመሰገናለች፣ የቤተ ክርስቲያን ልጆች አክብሯት ለእኛ ለኃጥኣን መድኃኒታችን ስለሆነች፡፡ በጎ አገልግሎትም ለሚያገለግሉት ዋጋውን ትሰጠዋለች፣ ሳትጠራጠሩ በፍጹም ልቡናችሁ እመኑባት እሷ መድኃኒታችን ናትና፡፡ በሥዕሏ ፊት ስገዱ ለሥዕሏም ያልሰገደ ግን ከቆመበት ቦታ ይጥፋ፣ ስም አጠራሩም አይታወቅ፡፡ (ተአምረ ማርያም መግቢያ)፡፡

ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በረከት ረድኤት ያሳትፈን፡፡ አሜን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡

ቃና ዘገሊላ

እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ በጥምቀት በዓል ማግስት ጥር ፲፪ ቀን የቃና ዘገሊላ በዓል ይከበራል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና ዘገሊላ በተደረገ ሠርግ ቤት ያደረገውን ተአምር በማሰብ በዓልን ታደርጋለች፡፡ በዓሉ ቃና ዘገሊላ የሚል ስያሜ ያገኘው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ክፍል ቃና በተባለችው ቦታ በፈፀመው ተአምር መነሻነት ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃና በዶኪማስ ቤተ በተደረገ ሠርግ እመቤታችን ለሠርገኞቹ ዘመድ ነበረችና ከእናቱ ከድንግል ማርያም እንዲሁም መምህርን ጠርቶ ደቀ መዛሙርቱን መተው ሥርዓት ስላልሆነ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ተገኝቷል፡፡ በሠርጉ ቤትም ሥርዓቱ እየተከናወነ ሳለ የተዘጋጀው የወይን ጠጅ አለቀባቸው፡፡ ይህን የተገነዘቡት ዶኪማስና አስተናባሪዎቹ ተደናግጠው ሳለ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የወይን ጠጁ ማለቁን ተረድታ ጭንቀታቸውን ወደሚያቀልለው ልጇ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ዘንድ ቀርባ “ልጄ የወይን ጠጅ አልቆባቸዋል” አለችው፡፡ እርሱም መልሶ አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት፡፡ ይህም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሚውልበትና ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለሰው ልጆች ሁሉ ለዘለዓለም ድኅነት ያድል ዘንድ ጊዜው አለመድረሱን ሲያመለክት ነው፡፡ እመቤታችንም ለአገልጋዮቹ የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው፡፡ በቦታው የነበሩትን ስድስት ጋኖች ውኃ ሞልተው እንዲያመጡ አዘዘቻቸው፡፡ እያንዳንዱም ጋን ሁለት ወይም ሦስት እንስራ ይይዙ ነበር፡፡ አስተናባሪዎቹም ውኃውን በጋኖቹ ሞልተው አቀረቡለት፣ ውኃውንም ወደ ወይን ለወጠው፡፡  እነርሱም እየቀዱ ለታዳሚዎች አቀረቡ፡፡

ታዳሚዎቹም በወይን ጠጁ ልዩ ጣዕም ተደንቀው ሙሽራውን ጠርተው ሰው ሁሉ መልካሙን የወይን ጠጅ አስቀድሞ ያጠጣል፤ ከጠገቡ በኋላም ተርታውንም ያመጣል፤ አንተ ግን መልካሙን የወይን ጠጅ እስከአሁን አቆየህ አሉት፡፡ ጌታችን ኢየሱስም በቃና ዘገሊላ ያደረገው የተአምራት መጀመሪያ ይህ ነው፤ ክብሩንም ገለጠ፤ ደቀ መዛሙርትም አመኑበት፡፡ (ዮሐ.፪፥፩፲፩)

የቃና ዘገሊላ ጥንተ ነገሩ ወይም ታሪኩ የተፈፀመው በሌላ ጊዜ ቢሆንም አባቶቻችን የውኃን በዓል ከውኃ በዓል ጋር ለማክበር ብለው ወደ ጥር ፲፪ አምጥተውታል፡፡ ይህም ውኃ ወደ ወይን የተለወጠበትን በዓል ከጌታ ጥምቀት በዓል ጋር ለማስተሣሠር በማሰብ ነው፡፡ በመሆኑም የቃና ዘገሊላ በዓል ጥር ፲፪ ቀን ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በድምቀት ታከብረዋለች፡፡

እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሣይነግሯት በልብ ያለውን የምታውቅ እናት ናትና የሠርጉ አስተናባሪዎች ይህ ጎደለ ሳይሏት የልቡናቸውን ሐዘን ተመልክታ ከልጇ ከወዳጇ አማልዳ የጎደላቸውን ሞልታለች፤ ያስጨነቃቸውንም አርቃለች፤ ለችግራቸውም ደርሳላቸዋለች፡፡ ሳይነግሯት የልቡናን አይታ ካማለደች ስሟን ጠርተው ለሚለምኗት ሁሉ እመቤታችን ትደርሳለችና ዘወትር ወደ እርሷ እንጸልይ ዘንድ ይገባል፡፡   

ከእናታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤት በረከት ያሳትፈን፡፡ አሜን!

“ባሕር አየች፣ ሸሸችም” (መዝ. ፻፲፫፥፫)

በዲ/ን አሻግሬ አምጤ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከገሊላ ተነሥቶ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ፣ በዮሐንስ እጅ በተጠመቀ ጊዜ ባሕር ሸሸች፣ ዮረዳስም ወደ ኋላ ተመልሷል፡፡ ጌታችን ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ የወረደው በጥምቀቱ ክብር ሊያገኝበት፣ የጎደለው ነገር ኖሮ ሊመላበት ሳይሆን እኛም ከውኃ እና ከመንፈስ ቅዱስ ተወልደን ልጅነትን እንድናገኝ፣ በኃጢአት ምክንያት ጎድሎብን የነበረው እንዲሞላልን፣ አጥተነው የነበረው ልጅነት እንዲመለስልን ነው፡፡

ሊቁ ቅዱስ ያሬድ በድጓው “አጥምቀኒ በማይ ከመ ይትቀደስ ማይ በማእከለ ሰማይ” በማለት የዘመረው ጌታችን ወደ ዮርዳኖስ የወረደው በአንጻረ ዮርዳኖስ ውኃዎችን ሁሉ ለመባረክ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ረግቶ የሚኖር ውኃ በማዕበል ሲመታ እንደሚጠራ ሁሉ የሰው ልጅ ከአምላኩ በመጣላቱ ውኃ የሞት ምክንያት ሆኖ ስለነበር ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በውኃ በመጠመቁ የሕይወት መድኅን አድርጎ ባሕርይውን ሳይሆን ግብሩን ለወጠው፡፡

የጌታችን ጥምቀት ልጅነት ያገኘንበት ቢሆንም በየዓመቱ ወንዝ ዳር ወርደን የምንጠመቀው ግን   ልጅነትን ለማግኘት ሳይሆን የተከፈለልንን ዋጋ ለማስታወስ ነው፡፡ በየዓመቱ የሚከበረው የጥምቀት በዓል እና በውኃ መረጨታችን በረከት ለማግኘት፣ ትውፊቱን ለማስቀጠል እና የተከፈለልንን ውለታ ለማስታወስ የምንፈጽመው ነው፡፡

የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት የሥላሴ አንድነትና ልዩ ሦስትነት የተገለጠበት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት በተመለከተ በተለያዩ መንገዶችና ሁኔታዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ተገልጾ እናገኘዋለን፡፡ ይህም ታላቅ ምሥጢር በይፋ ከተገለጠባቸው መንገዶች አንዱ የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ጥምቀት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእደ ዮሐንስ፣ በማእከለ ዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ አብ በደመና ሆኖ ተገልጧል፤ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ተቀምጧል፡፡ ይህንንም ቅዱስ ወንጌል “ጌታችን ኢየሱስም ወዲያው ከውኃው ወጣ፡፡ እነሆ ሰማይ ተከፈተ፤ የእግዚአብሔርም መንፈስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ አየ፡፡ እነሆም ‘በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው’ የሚል ድምፅ ከሰማይ መጣ” በማለት የረገልጸዋል፡፡ በዚህም የእግዚአብሔርን አንድነትና ሦስትነት እንረዳለን፡፡ (ማቴ.፫፥፲፮-፲፯)

የዮርዳኖስ ውኃ ፈርታ ወደ ኋላዋ መመለሷ ሰማይና ምድር መሸከም የማይቻላቸውን እኔ እንዴት እችለዋለሁ? ብላ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ጌታችን ለዚህ ክብር ስለመረጣት ደስታዋን መቋቋም ተስኗት ወደ ኋላዋ ተመልሳ፣ ለዝማሬ አሸብሽባለች፡፡ ነቢዩ ዳዊት “ባሕር አየች ሸሸችም ፤ ዮርዳኖስም ወደ ኋላው ተመለሰ” በማለት የዘመረው ለዚህ ነው፡፡ (መዝ. ፻፲፫፥፫)

የዕዳ ደብዳቤያችንን ለመደምሰስ እንዲሁም ትሕትናንን ለማስተማር (አርአያ ሊሆነን)  በዮርዳሰኖስ ወንዝ ተጠመቀ፡፡  ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እግዚአብሔርንም የመምስል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፡፡ በሥጋ የተገለጠ፣ በመንፈስ የጸደቀ፣ ለመላእክት የታየ፣ በአሕዛብ የተሰበከ፣ በዓለም የታመነ፣ በክብር ያረገ» (፩ኛ. ጢሞ. ፫፥፲፮) በማለት የተናገረለት ጌታ ወደ ዮርዳኖስ ሄዶ በዮሐንስ እጅ መጠመቁን ትውፊት አድርገው ታቦታት ከመንበራቸው ተነሥተው ወንዝ ዳር አድረው ውኃውን ባርከው ይመለሳሉ፡፡ በዚህም መሠረት “በዓለ ጥምቀት የሚከበረው ከወንዝ ዳር ነው፡፡ ወንዝ ከሌለ ግን ክብ ቅርጽ ባለው ነገር ውስጥ ውኃ ይዘጋጃል፡፡ በከተራ ከማደሪያቸው የሚወጡ ታቦታት በወንዝ ወይም በተዘጋጀ የውኃ አካባቢ ያድራሉ፡፡ ይህም ክርስቶስ ለመጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ የመውረዱ ምሳሌ ነው፡፡ እያንዳንዱ ቤተ ክርስቲያን የሚመሰለው በገሊላ ነው፡፡ ታቦታቱ የሚያድሩባቸው ሁሉ በዮርዳኖስ ይመሰላሉ፡፡

ጌታችን ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ በመሄዱ በአንጻረ ዮርዳኖስ ውኃዎች ሁሉ እንደተባረኩ፣ ታቦታትም መንበረ ክብራቸውን ለቀው ወንዝ ዳር አድረው ውኃውንም፣ አካባቢውንም ባርከው ወደ መጡበት ይመለሳሉ፡፡ በዓሉን የምናከብረውም ይህን ትውፊት አድርገን በረከት እናገኝ ዘንድ ነው፡፡

በዐፄ ገብረ መስቀል ዘመን ታቦታት ጥር ፲፩ ቀን ከመንበራቸው ወጥተው በዕለቱ ተመልሰው እንዲገቡ ሥርዓት ተሠርቶ ነበር፡፡ በቅዱስ ላልይበላ ዘመን ደግሞ በከተራ ዕለት ወይም በዋዜማው ከመንበራቸው ወጥተው ጥምቀተ ባሕር ከሚፈጸምበት ቦታ አድረው በማግስቱ ይመለሱ ነበር፡፡ በዐፄ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ደግሞ ሁሉም አካባቢ በረከት እንዲያገኝ ወይም እንዲባረክ ታቦታት በሄዱበት መንገድ እንዳይመለሱ የሚል ሥርዓት ተሠራ፡፡ ይህም በዓሉን ለማክበር በመሄዳችን ከመንበራቸው ወጥተው ወንዝ ዳር አድረው በሚመለሱ ታቦታት የምንባረክ መሆኑን ያስረዳል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ጾመ ጋድ(ገሃድ)

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ካሏት ሰባቱ የአዋጅ አጽዋማት መካከል አንዱ ጾመ ጋድ(ገሃድ) ነው፡፡ ገሃድ ማለት ለውጥ(ምትክ) ወይም ልዋጭ፤ እንዲሁም ግልጥ፣ ተገላጭ በማለት ይተረጎማል፡፡ ይህንንም ደስታ ተክለ ወልድ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ጋድ(ገሃድ) እንዲህ ይተረጉሙታል፡- “ገና፣ የጥምቀት ከተራ (የልደትና የጥምቀት ዋዜማ) እንደ ዐርብ ረቡዕ እና ፍልሰታ፣ እንደ ሑዳዴ የሚጾም፡፡ ትርጓሜው የሚገለጥ፣ ተገላጭ፣ ግልጥ ማለት ነው፡፡ ጌታችን እንደ ሰውነቱ በአጭር ቁመት፣ በጠባብ ደረት ተወስኖ መታየቱን ያስረዳል” (ደስታ ተክለ ወልድ መዝገበ ቃላት፤ ገጽ ፪፻፴፪)፡፡

ጥር ፲ የሚነበበው ስንክሳር በጥምቀት ዋዜማ መጾም እንደሚገባ ሲገልጽ፡- “በዚች ዕለት ምንም መብልን ሳይቀምሱ ምእመናን ሁሉ እስከ ምሽት ይጾሙ ዘንድ ከእኛ አስቀድመው የነበሩ ታላላቅ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን መምህራን ሥርዓትን ሠሩ፤ በምሽትም ቢሆን በታላቁ ጾም ከሚበላው በቀር ጥሉላትን አይቅመሱ፡፡ በዚህች ዕለት ምእመናን እስከ ምሽት እንዲጾሙት ያዘዙበት ምክንያት ይህ ነው፡- የልደትና የጥምቀት በዓል በረቡዕ ወይም በዐርብ ቀን ቢውል በበዓለ ሃምሳ የሚበላውን የጥሉላት መብል በጥዋት በመብላት ምእመናን ሁሉ በዓሉን እንዲያከብሩ አባቶቻችን ሐዋርያት አዝዘዋል፡፡ እሊህ ሁለቱ የእግዚአብሔር ታላላቅ በዓሎቹ ናቸውና፡፡”

ይህም ማለት ልደት እና ጥምቀት ረቡዕና ዐርብ ከዋሉ በዋዜማው ማክሰኞና ሐሙስ ይጾማሉ። ረቡዕና ዐርብ ምንም እንኳን የጾም ቀናት ቢሆኑም የፍስክ ቀን ሆነው ይከበራሉ። የልደት እና የጥምቀት በዓል እሑድ ቢውሉ በዋዜማው ቅዳሜ የጥሉላት ምግብ አይበላም። እንዲሁም ልደት እና ጥምቀት ሰኞ ቢውሉ እሑድ ጥሉላት አይበላም። እንደ ሌሎች የአጽማዋት ቀናት እህልና ውኃ ግን አይጾሙም።

ፍትሐ ነገሥት ስለ ጾም ሲገልጽ፡- “ጾምስ በሕግ ውስጥ በታወቀው ጊዜ የሰው ከምግብ መከልከል ነው፤ በደሉን ለማስተሥረይ ዋጋውንም ለማብዛት እርሱን ወዶ ሕግን ለሠራለት እየታዘዘ የፈቲውን ኃይል ያደክም ዘንድ ለነባቢት ነፍሱም ትታዘዝ ዘንድ” በማለት ይተረጉመዋል፡፡ በዚህ ጊዜ መጾም እንደሚገባም ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዓት ሠርታለች፡፡ (ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው፣ አንቀጽ ፲፭፥፭፻፷፬)

ጾም ወደ እግዚአብሔር የምታደርስ የነፍስ ምግብ ናትና ሥጋችንን ለነፍሳችን አስገዝተን ጾምን በመቀደስ የበረከቱ ተሳታፊዎች ያደርገን ዘንድ የአምላካችን እግዚአብሔር ፈቃድ ይሁን አሜን፡፡

በዓለ ግዝረት

እግዚአብሔር የግዝረት ሥርዓትን ለአበ ብዙኀን አብርሃም የሰጠው የቃል ኪዳን ምልክት ነው። እግዚአብሔርም አብርሃምን አለው፡- “አንተ ደግሞ ቃል ኪዳኔን ትጠብቃለህ፤ አንተ፣ ከአንተም በኋላ ዘርህ በትውልዳቸው፡፡ በእኔና በአንተ መካከል፣ ከአንተም በኋላ በዘርህ መካከል የምትጠብቋት ቃል ኪዳኔ ይህች ናት፤ ከእናንተ ወንድ ሁሉ ይገረዝ፡፡ የሰውነታችሁን ቊልፈት ትገረዛላችሁ፤ በእኔና በእናንተ መካከል ላለውም ቃል ኪዳን ምልክት ይሆናል” በማለት ቃል ኪዳንን አኖረ፡፡ (ዘፍ.፲፯፥፯-፲፬) በሊቀ ነቢያት ሙሴ ዘመንም ግዝረት የእስራኤል ሕዝብ ምልክት ነበር። እግዚአብሔርም ሙሴንና አሮንን አላቸው፡- ”ይህ የፋሲካ ሕግ ነው፤ ከእርሱ ባዕድ ሰው አይብላ፡፡ አገልጋይ ወይም በብር የተገዛ ቢኖር ከተገረዘ በኋላ ያን ጊዜ ከእርሱ ይብላ” (ዘፀ. ፲፪፥፵፫)

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ግዝረትን በተመለከተ “ኦሪትንም ብትፈጽም ግዝረት ትጠቅምሃለች፤ ኦሪትን ባትፈጽም ግን ግዝረትህ አለመገዘርህ ትሆንብሃለች፡፡ አንተ ሳትገዘር ብትኖር ኦሪትንም ብትጠብቅ አለመገዘርህ መገረዝ ትሆንልሃለች፡፡” (ሮሜ. ፪፥፳፭) በማለት ለሮሜ ክርስቲያኖች በላከው መልእክቱ ጽፎላቸዋል፡፡ ይህም የሥጋን ሸለፈት መገረዝ ሳይሆን የልብ መለወጥና በእግዚአብሔር ማመን፣ ሕጉንም መፈጸም እንደሆነ ያመለክተናል፡፡ ይህንንም ሲያጸና “የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መጠበቅ ነው እንጂ መገዘርም አይጠቅምም፤ አለመገረዝም አይጎዳም፡፡” (ቆሮ.፪፥፲፱) እንዲል፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ኦሪትና ነቢያትን ልሽራቸው የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽማቸው እንጂ ልሽራቸው አልመጣሁም፡፡” እንዳለ (ማቴ.፭፥፲፯) እርሱ ራሱ ይገረዝ ዘንድ ሥርዓቱንም ለመፈጸም ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ በስምንተኛው ቀን ወደ ቤተ መቅደስ በወሰደችው ጊዜ ተገርዞ ተገኝቷል እንጂ በፍጡራን እጅ አልተገረዘም። የገራዡ ምላጭም በገራዡ እጅ እንዳለ ውኃ ሆኖ ተገኝቷል (መጽሐፈ ስንክሳር ጥር ስድስት)። ይህም በመለኮታዊ ኃይሉ ነው።

በዚህም ምክንያት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን የጌታችን የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የግዝረት በዓል በየዓመቱ ጥር ፮ ቀን ታከብራለች (መጽሐፈ ስንክሳር ጥር ስድስት)። ስሙም ገና በሥጋ ሳይፀነስ የእግዚአብሔር መልአክ ባወጣለት ስም “ኢየሱስ” ተብሎ ተጠራ፡፡ (ሉቃ. ፪፥፳፩-፳፬)

ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በኅቱም ድንግልና ተጸንሶ በኅቱም ድንግል መወለዱ እንደማይመረመር ሁሉ ግዝረቱም አይመረመርም፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተዘጋ ቤት ሐዋርያት ተሰብስበው ባሉበት ገብቶ እንደወጣ ሁሉ እርሱ በሚያውቀው ረቂቅ ጥበብ ከሥጋው ምንም ምን ሳይቈረጥ፣ ምንም ደም ሳይፈሰው ተገርዞ ተገኝቷል፡፡

ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት ሲሆን ይህ ስም የወጣለት በተወለደ በስምንተኛው ቀን ነው፡፡ ይህም በኦሪቱ ሥርዓት መሠረት ወንድ ልጅ በተወለደ በስምንት ቀን ከተገረዘ በኋላ ስም የማውጣት ልማድ አለና የኦሪትን ሕግ ለመፈጽም ይገረዝ ዘንድ ሄደ፡፡ ““ኦሪትና ነቢያትን ልሽራቸው የመጣሁ አይምሰላችሁ፤ ልፈጽማቸው እንጂ ልሽራቸው አልመጣሁም፡፡” እንዲል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ባልንጀራ

በእንዳለ ደምስስ

ክፍል ሁለት

መልካም ባልንጀርነት

ሰዎች በሚኖራቸው የእርስ በእርስ መስተጋብር መልካም ባልንጀርነትን ሊመሠርቱ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል የነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት እና የነቢዩ ናታን ግንኙነትን ማንሣት እንችላለን፡፡

ነቢዩ ዳዊት የወዳጁንና የጦር አበጋዙ ኦርዮን ሚስት “የባልንጀራህን ሚስት፣ የባልንጀራህን ቤት አትመኝ” (ዘጸ.፳፥፲፯) የሚለውን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመተላለፍ ቤርሳቤህን በማስነወሩና እርሷም በማርገዟ ኦርዮንን ማስገደል አማራጭ አድርጎ ወሰደው፡፡ ጦር ሜዳ ሳለም አስገደለው፡፡ እግዚአብሔርም በዝምታ አላለፈውም፡፡ ይገስጸው ዘንድ ባልንጀራውን ነቢዩ ናታንን ላከበት።

ነቢዩ ናታንም እኔ ስለ ባልንጀራዬ ምን አገባኝ ሳይል ብልሃት በተሞላበት መንገድ በምሳሌ አስረድቶ ስለ ጥፋቱ ነግሮ በንስሓ እንዲመለስ የድርሻውን ተወጣ፡፡ ይህ የመልካም ባልንጀርነት ውጤት ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ እንዲህ ይላል፡፡ “ልቡ ንጸህ የሆነ፣ እጆቹም የነጹ፣ በነፍሱ ላይ ከንቱ ያልወሰደ፤ ለባልንጀራውም በሽንገላ ያልማለ፣ እርሱ ከእግዚአብሔር ዘንድ በረከትን ይቀበላል” ይላል፡፡ (መዝ.፳፫፥፬)

መልካም ባልንጀርነትን ሊያጠነክሩ የሚችሉ ዋና ዋና ጉዳዮች መካከል ጥቂቶቹን እንመለከት፡

ሀ.  ማመንና መታመን፡- በቅርባችን ያሉትን እናትና አባታችን፣ ቤተሰቦቻንን፣ ጓደኞቻችንን፣ ወይም በጎ ነገር ያደረጉልንን ልናምን እንችላለን፡፡ ነገር ግን ከሁሉም በፊት እግዚአብሔርን ማመን ቅድሚያ የምንሰጠው ጉዳይ   ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ሰዎች በላከው መልእክቱ “በእርሱም እጸና ዘንድ ዛሬ የኦሪት ጽድቅ ሳይኖረኝ ክርስቶስን በማመን ከእግዚአብሔር የሚገኝ ጽድቅ አለኝ እንጂ፡፡” (ፊልጵ. ፫፥፱) በማለት እግዚአብሔርን ማመን ቅድሚያ ልንሰጠው የሚገባ መሆኑን ይገልጻል፡፡

ቅዱስ ጳውሎስ ማመን ብቻ ሳይሆን መታመንም እንደሚያስፈልግ ሲያመለክት ደግሞ “የተጠራህለትንና በብዙ ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘለዓለምን ሕይወት ለመቀበል መልካሙን የሃይማኖት ገድል ተጋደል” (ጢሞ. ፮፥፲፪) ሲል ደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስን እንዳሳሰበው ላመኑት ነገር ታምኖ መገኘትን አስፈላጊነት ያሳየናል፡፡ በዚህም መሠረት መልካም ባልንጀርነትን ለመመሥረት ጓደኛን ማመን፣ እንዲሁም ራስም ታምኖ መገኘት ይገባል፡፡ በዚህ ረገድ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን ችግር ማንሣት ያስፈልጋል፡፡

 የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከቤተሰብ መራቃቸው፣ ራሳቸውን እንዲመሩ ነጻነትም ስለሚሰማቸው ጓደኛ ለመያዝ የሚያደርጉት ጥረት ላይ ክፍተቶች ይታያሉ፡፡ ከመንፈሳዊነት ይልቅ ሥጋዊውን በማሰብና በማድረግ ለተጠሩለት ዓላማ ታምነው መገኘት ይሳናቸዋል፡፡ ስለዚህ ጓደኛዬ ማነው? ሊሉ ይገባል፡፡ በሃይማኖት የሚመስላቸውን፣ ለአገልግሎት የሚያበረታቸው፣ ምሳሌም የሚሆናቸው፣ በትምህርታቸውም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ሊደጋገፉ የሚችሉ መሳዮቻቸውን መምረጥ ይገባቸዋል፡፡ ብዙዎች ውጤት አልባ ሆነው የሚቀሩት ለሥጋዊ ፍላጎታቸው በማድላት በሚፈጽሙት ያልተጋባ ድርጊት ከዓላማቸው ሲሰናከሉ እንመለከታለንና ጥንቃቄ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ የሚያምኑትና እነርሱም ሊታመኑለት የሚችሉትን ባልንጀራ መያዝ ያስፈልጋል፡፡

ለ. ራስን አሳልፎ መስጠት፡- መልካም ባልንጀርነት ራስን አሳልፎ እስከ መስጠት የሚደርስ ነው፡፡ ባልንጀራህ በሚደርስበት ችግር ተካፋይ በመሆን ቢወድቅ ማንሣትን፣ ቢቸገር የችግሩ ተካፋይ መሆንን፣ ሁል ጊዜም መልካምን መመኘት ይጠይቃል፡፡

ባልንጀርነትን ለማጽናት ማመንና መታመን እንደሚገባ ሁሉ ባልንጀራ በተቸገረ ጊዜ ከጎኑ በመሆን ደስታውንም ሆነ   ችግሩን መካፈል ይገባል፡፡ ይህንንም ችግር ለመፍታት በሚደረግ ጥረት ውስጥ ስለ ባልንጀራ/ጓደኛ ራስን አሳልፎ እስከ መስጠት የሚደርስ እንኳ ቢሆን መከፈል ያለበትን መሥዋዕትነት መክፈል የመልካም ባልንጀርነት መገለጫ ነው፡፡

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ ላይ አድሮ “ቸር ጠባቂ እኔ ነኝ፤ ቸር ጠባቂ ስለ በጎቹ ነፍሱ አሳልፎ ይሰጣል” በማለት እንደተናገረው ጌታችን የአዳምና የልጆቹን በደል ተሸክሞ በመስቀል ላይ ራሱን አሳልፎ በመስጠት በመስቀል ላይ ውሏል፡፡ (ዮሐ.፲፥፲፩) የሰውን ልጆች ነጻ ያወጣ ዘንድ ነፍሱን እስከመስጠት ታማነ፤ ቤዛም ሆነ፡፡ ስለ ሌሎች ራስን አሳልፎ መስጠትን ከጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንማራለን፡፡ “እንደ ሰውም ሆኖ ራሱን አዋረደ፤ ለሞት እስከ መድረስም ታዘዘ” በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ጽፏል፡፡ (ፊልጵ.፪፥፰)፡፡ መልካም ባልንጀራም ስለ ወዳጁ እስከ ሞት ድረስ እንኳ ቢሆን የታመነ ሊሆን  ይገባዋል፡፡ “ነፍሱን ስለ ወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም” (ዮሐ.፲፭፥፲፫) እንዲል፡፡

መልካምን ማድረግ፡- የባልንጀርነት መገለጫ ከሆኑት ውስጥ አንዱ ለባልንጀራ መልካምን ማድረግ ነው፡፡ “መልካም ሰው ከልቡ መዝገብ መልካም ነገርን ያወጣል”ና (ማቴ.፲፪፥፴፭) በማለት እንደገለጸው ሁል ጊዜ ስለ ባልንጀራ መጸለይ፣ በችግሩም ጊዜ አብሮ መቆምን፣ በሰላሙም ጊዜ አለመለየት፣ ከባልንጀራም ጋር መሆን ይገባል፡፡ በዚህም የእግዚአብሔርን በረከት ይገኛል፡፡ “ሰላምን እተውላችኋለሁ፤ ሰላሙንም እሰጣችኋላሁ፣ እኔ የምሰጣችሁ ዓለም እንደሚሰጠው አይደለም፤ ልባችሁ አይደንግጥ፣ አትፍሩም” ይለናል፡፡ (ዮሐ. ፲፬፥፳፯)

ትእዛዛትን መጠበቅ፡- ከስድስቱ ትእዛዛተ ወንጌል አንዱ “ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ” የሚል ነው፡፡ ባልንጀራን እንደ ራስ መውደድ ስንል ከልብ በመነጨ ፍቅር ተመሥርተን ውጣ ውረዱን፣ ደሰታም ሆነ ሐዘኑን መጋራትን ያመለክታል፡፡ ከመቀበል ይልቅ መስጠት ላይ ትኩረት ያደረጋል ባልንጀርነት፡፡

ትእዛዛትን መጠበቅ ከቻልን ከእግዚአብሔርም ከሰውም ጋር ያለን ግንኙነት የጠበቀ ይሆናል፡፡ በዚህም ምክንያት ከክፉ እንርቃለን፡፡ “ደግ ሰው ከመልካም ልቡ መልካም ነገርን ያወጣል” እንዲል፡፡ (ማቴ.፲፪፥፴፫) ባልንጀራን ወደ ትክክለኛው መንገድ መምራት የመልካም ባልንጀርነት መገለጫ ነው፡፡ ትእዛዛትን የሚጠብቅ ሰው በባልንጀራው ላይ ክፉ ነገርም አያደርግም፡፡

በአጠቃላይ በሃይማኖት፣ በምግባር ታንጾ የሚኖር ሰው ለባልንጀራው ፍቅር ይኖረዋል፡፡ በባልንጀራው ላይ ክፉም አያደርግም፤ ሁል ጊዜ በባልንጀራው ደስታ እርሱም ይደሰታል እንጂ፡፡ ሌላውን መውደድ ስንችል እንግዚአብሔርን እንወዳለን፤ እርሱም ይወደናል፡፡ “… ባልንጀራህንም እንደ ራስህ መውደድ ከመባና ከመሥዋዕት ሁሉ ይበልጣል” ነው የተባልነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች በጻፈላቸው መልእከቱ “ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋል” (፩ቆሮ. ፲፭፥፴፫) ብሎ እንደተናገረው ከክፉ ባልንጀራ ርቀን፣ ክፉ የሆነውንና ከባልንጀራችን የወረስነው ክፉ ዐመል አስወግደን መልካምን እያደረገን እንኖር ዘንድ ይገባል፡፡

የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ተራዳኢነት አይለየን፡፡ አሜን፡፡