ባልንጀራ

ክፍል አንድ

በእንዳለ ደምስስ

ባልንጀራ የሚለውን ቃል ደስታ ተክለ ወልድ በመዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው፡- “እኩያ፣ ባልደረባ፣ አቻ፣ አብሮ አደግ ጓደኛ፣ እንጀራ አቋራሽ” በ ማለት ሲተረጉሙት ባልንጀርነትን ደግሞ “እኩያነት፣ ባልደረብነት” በማለት ይፈቱታል፡፡

ባልንጀራ ክፉም ሆነ መልካም ነገር ሲገጥመን አብሮ የሚያዝንና የሚደሰት የልብ ወዳጅ፣ መልካሙን መንገድ የሚያሳይ፣ … ማለታችን ነው፡፡ ባልንጀርነት አብሮ በማደግ፣ አብሮ በመማር፣ አብሮ በመሥራት እንዲሁም በሙያ አጋርነት በመሳሰሉት ሁኔታዎች ሊፈጠር ይችላል፡፡ ይህ የባልንጀርነት ቁርኝት እየዳበረ የሚመጣ እንደመሆኑ መጠን በተለያዩ ምክንያቶችም ሊፈርስ ወይም ሊከስም ይችላል፡፡

ክፉ ባልንጀራ የሌላውን ሕይወት ያጨልማል፣ መልካምን ከማሰብና ከማድረግ ክፉ ሐሳቦችን ያመነጫል፣ ተግባራዊም ያደርጋል፡፡ አባቶችቻን ለዚህ ነው “ክፉ ባልንጀራ አይግጠምህ፤ ከክፉ ባልንጀራ ራቅ” እያሉ የሚመክሩት፡፡ ክፉ ባልንጀራ መልካም የሆነውን ወዳጁን ጠባይ ቀስ በቀስ በመለወጥ በሄደበት እንዲሄድ፣ በዋለበት እንዲውል፣ ከመልካም ቦታዎች ይልቅ ኃጢአትን ወደሚሠራባቸው ስፍራዎች ማለትም መንፈሳዊ ቦታዎችን አስጥሎ ወደ ጭፈራ ቤቶች፣ ዝሙት ወደሚሠራባቸውና ልዩ ልዩ ያልተገቡና በማኅበረሰቡም በእግዚአብሔርም የተጠሉ ተግባራት ወደሚከናወንባቸው ቦታዎች በመሄድ ጠፍተው እንዲቀሩ ምክንያት ይሆናል፡፡

ለዚህ እንደ ምሳሌ የሔዋንና የዲያብሎስ ወዳጅነት ማየት ይቻላል፡፡ ሰይጣን ከነበረው ክብር አምላክነትን በመሻቱ ምክንያት ከተጣለ በኋላ ለክፉ ሥራው ተባባሪ ለማግኘት በእባብ ላይ አድሮ ወደ ሔዋን ቀረበ፡፡ የአዳምና ሔዋን በገነት ውስጥ በተድላ በደስታ መኖር አበሳጭቶታል፡፡ እኔ ወድቄ ሌላው ለምን ይኖራል? በሚል በእባብ ላይ አድሮ ከሔዋን ጋር ባልንጀርነትን መሠረተ፡፡ እባብም ሴቲቱን “እግዚአብሔር በገነት ካለው ዛፍ ሁሉ አትብሉ ያላችሁ ለምንድነው?” አላት፡፡ ሴቲቱም “በገነት መካከል ካለው ከሚያፈራው ዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፤ እግዚአብሔር አለ “እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ፣ አትንኩትም” አለን በማለት አስረዳችው፡፡ (ዘፍ.፫፥፫)

በእባብ ላይ ያደረው ሰይጣንም “ሞትን አትሞቱም፤ ከእርሱ በበላችሁ ቀን ዐይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ፡፡” አላት፡፡ ሔዋንም እጅግ ለመብላት ጓጓች፤ ከዕፀ በለሱ ቀጥፋም ለአዳም ሰጠችው፤ ሁለቱም በመብላታቸው ዐይኞቻቸው ተከፈቱ፤ እግዚአብሔርንም አስቆጡት፤ ከገነት ወደ ምደረ ፋይድ ተጣሉ፡፡ ይህ ሁሉ ከክፉ ባልንጀራ ጋር ወዳጅነት መመሠረት ያስከተለው ጥፋት ነው፡፡

ባልንጀርነትን ከሚያበላሹ ነገሮች መካከል ጥቂቶቹን ብንመለከት፡-

መንፈሳዊ ሕይወት መዛል፡- በመንፈሳዊ ሕይወት ስንዝል ለሥጋዊ ፍላጎት ተላልፈን እንሰጣለን፡፡ ነፍሳችን በሥጋችን ላይ ትሠለጥናለች፡፡ በተለይ በወጣትነት ዘመናችን ስሜታዊነት ስለሚያይልብን ይህንንም ያንንም ለመሞከር በምናደረግው ጥረት ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወታችን ይጎዳል፡፡ በዚህ ወቅት መንፈሳውያን ወንድሞቻችንና አኅቶቻችንን ትተን ከማይመስሉን ጋር የሥጋን ሥራ ለመሥራት እንፈጥናል፡፡ ይህ ደግሞ በሕወታችን ውስጥ ከእግዚአብሔር ጋር እንኖራለን፣ እናሳካዋለንም ብለን ያሰብናቸው ነገሮች ሁሉ ከንቱ ሆነው ይቀራሉ፡፡ ቀድሞ የነበረንን ማንነት እያጣን መንፈሳዊነትን እርግፍ አድርገን እንድንተው ያደርገናል፡፡

ነገር ግን ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊ ሕይወታችንን ሊያጠናክሩልን፣ ብንወድቅ የሚያነሡንን፣ ብንደክም የሚያበረቱንን መልካም ወንድሞችና እኅቶችን መጠጋት ይገባል፡፡

የአቻ ግፊት፡- በብዙ ወጣቶች ዘንድ በተለይም በግቢ ጉባኤት ተማሪዎች ዘንድ ጎልተው ከሚታዩ ችግሮች አንዱ የአቻ ግፊት ነው፡፡ ከመንፈሳዊው ሕይወት እንድንወጣ ብልጭልጩን ዓለም እያሳዩ ከእግዚአብሔር እንድንለይ ከሚያደርጉን አቻዎቻችን መራቅ ተገቢ ነው፡፡ በአቻ ግፊት ምክንያት አዲስ ጠባይ እንድንይዝና ለማይገቡ ክፉ ጠባይት ተላልፈን እንዳንሰጥ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ “ሁሉን መርምሩ፤ መልካም የሆነው ያዙ” ተብለናልና፡፡ (፩ተሰ.፭፥፳፩)

በወጣትነት ዘመናችን በተለይም በግቢ ጉባኤ ሕይወታችን ውስጥ መልካም እየመሰሉን ከእግዚአብሔር አንድነት ከሚለዩን በዙሪያችን ካሉ ባልንጀሮቻችን መራቅ ይጠበቅብናል፡፡   ለመንፈሳዊ ሕይወታችን እንቅፋት የሆኑትን በመራቅ መንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችንን መከተል፣ መንፈሳዊ መጻሕፍትን በማንበብና ከመንፈሳዊ ሕይወታችን ሊያርቁን ከሚችሉ አካባቢዎች መራቅና ጊዜያችንን በአግባቡ በመምራት በአቻ ግፊት እንዳንወድቅ ይረዳናል፡፡

የሚጠቅመንና የሚጎዳንን መለየት፣ አባቶችን ማማከር፣ ወደ መልካም መንገድ ሊመሩን የሚችሉ አርአያ የምናደርጋቸውን ወንድሞችና እኅቶችን መከተል፣ ዘወትር በመንፈሳዊ ሕይወታችን በመትጋት የአቻ ግፊትን ተጽእኖ በመቋቋም በራስ መተማመንን ማጎልበት ይጠበቅብናል፡፡

ከላይ ከተመለከትናቸው ውጪ ክፉ ባልንጀርነት የሚፈጥረብን ተጽእኖ ቀላል አይደለም፡፡ በዚህም ምክንያት ክፉ ባልንጀርነት አለመተማመንን፣ ክፉ ጠባያት እንድንለምድ፣ ራስን ብቻ እንደንወድ፣ … ከመንፈሳዊነት እንድንወጣ ሊያደርገን ይችላል፡፡

ሀ. አለመተማመን፡-  በባልንጀሮች መካከል መልካሙን ግንኙነት ከማጠናከር ፋንታ የግል ጥቅምን በመሻት ወይም በባልንጀራ ላይ በመቅናትና የባልንጀራን የሆነን ሁሉ በመመኘት በሚፈጠሩ ያልተገቡ ጠባያትና ድርጊቶች ምክንያት ጤናማ የባልንጀርነት ግንኙነት ሊበላሽ ይችላል፡፡ ይህም በባልንጀሮች መካከል አለመተማመንን ይፈጥራል፡፡

ራስን ልዩ አድርጎ መቁጠር፣ በባልንጀራ ላይ የበላይ ሆኖ ለመታየት መጣር፣ ራስን ብቻ መውደድ፣ … ወዘተ በሁለቱ አካላት መካከል አለመተማንን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ሊያደርስ ይችላል፡፡ ይህም እስከ ጠላትነት ሊያደረስ የሚችል አካሄድ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ በሥነ ምግባር ያለመታነጽ፣ ከመንፈሳዊ ሕይወት ማፈንገጥና ለሥጋ ምኞትና ፍላጎት ብቻ ማደር በጎውን መንገድ እንዳናስብ መንገዱን ስለሚዘጋ ባልንጀራን ወደ ሥጋዊ አስተሳሳብና ድርጊት እንዲመራ በር ይከፍታል፡፡

ለ. ክፉ ጠባያትን ማስለመድ፡- በባልንጀሮች መካከል መልካም ጠባያት እንዳለ ሁሉ ክፉ የምንላቸው ጠባያትን ሊንጸባረቁ ይችላሉ፡፡ በተለይም የጓደኛ አመራረጣችንና አያያዛችን ወደማንፈልገው አካሄድ ሊመራን ይችላል።፡ ይህም ሕይወታችንን በመልካም ሥነ ምግባር እንዳንመራ እንቅፋት ይሆንብናል፡፡ ለመሆኑ ባልንጀራችን ማነው? በሕይወት፣ በባህል፣ በእምነት እንመስለዋለን? ውሎውን እንውላለን? በሃይማኖት አንድ ነን? የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ዶግማ፣ ቀኖና፣ ትውፊትና ሥርዓትን ይጠብቃል? እነዚህንና ሌሎችንም መመርመር ያስፈልጋል፡፡

ቤተ ክርስቲያንን አስጥሎ ለሥጋ ብቻ በማድላት ከጸሎት ይልቅ ሙዚቃን፣ ከመንፈሳዊ አገልግሎት ይልቅ ሥጋን ለመስደሰት የሚፈጥን ከሆነ ይህ ክፉ የክፉ ባልንጀራ ጠባይ ነውና መራቅ ያስፈልጋል፡፡ ሁል ጊዜ ከመልካም ይልቅ እግዚአብሔርንና አገልግሎትን የሚያስጥሉ ክፉ ጠባያትን የሚያስለምደን በመሆኑ ከዚህ ጋር ከመተባበር ልንቆጠብ ያስፈልጋል፡፡ ከማይመስሉን ጋር በክፉ መጠመድ አይገባም፡፡ ክፉ ባልንጀርነት መልካሙን አመል ያጠፋልና፡፡ (፩ቆሮ.፲፭፥፴፫)

ሐ. ራስን ብቻ መውደድ፡- ራሳችንን ብቻ የምንወድ ከሆነ ለሌላው ግድ አይኖረንም፡፡ ሁል ጊዜ ራሳችንን በማስቀደማችን ለሌሎች እንዳንኖር፣ ለባንጀሮቻችን ትኩረት እንዳንሰጥና ባልንጀሮቻችን እኛ በቀደድነው መንገድ ብቻ እንዲጓዙ ተጽእኖ እናሳድራለን፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ “እኔ ብቻ” አስተሳሰብን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጎለብት ስለሚያደርግ ከምናመልከው እግዚአብሔር ይለየናል፤ ወደ ክፋትም ይመራናል፡፡ ራሳችንን ብቻ በወደድን ቁጥር ለሌላው ክብር ለመስጠት እንቸገራለን፡፡ ስለዚህ ባልንጀራችን በተቸገረ ጊዜ ከአጠገቡ ከመቆም ይልቅ ውድቀቱ እንዲፋጠን ግፊት እናደርጋለን፡፡ በትምህርትም ይሁን በልዩ ልዩ ዕውቀት፣ በሀብት፣ … የሚበልጠን መስሎ ከተሰማን ከእርሱ ከመማር ይልቅ ለመጣል ጥረት እናደርጋለን፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ ከእግዚአብሔርም ከሰውም ሳንሆን እንድንቀር ያደርግናል፡፡

በግቢ ጉባኤያት ውስጥ የምንሳተፈው እርስ በእርስ ተደረዳድተን ስንሳተፍ አንዱ ያላወቀውን በማሳወቅ፣ በመረዳዳት መጓዝ እንጂ ሊበልጠኝ ይችላል በሚል ሰበብ በባልንጀራ ላይ ክፉ ማድረግን ልንጸየፍ ይገባል፡፡ ግቢ ጉባኤያት እግዚአብሔርን የምናውቅበት፣ በዕውቀት በጥበብ የምንበለጽግበትና መልካም ባልንጀርነትን የምንመሠረትበት ለሌሎችም አርአያ ሆነን የምንገኝበት መልካም አጋጠሚ መሆኑን በመረዳት ራስን ብቻ ከመውደድ አልፈን መንፈሳዊ ፍሬ ልናፈራ ይጠበቅብናል፡፡

ባልንጀራን መውደድ በረከትን ያሰጣል፤ ከእግዚአብሔርም ጋር ሕብረት እንድንፈጠር ይረዳናል፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አምላክ ሲሆን የእኛን ሥጋ ለብሷልና እኛን ያድነን ዘንድ በቀራንዮ አደባባይ በመስቀል ላይ ተሰቅሏል፡፡ ሰውን በመውደዱ እስከ ሞት ድረስም የታመነ ሆነ፡፡ “ስለ ወዳጆቹ ሕይወቱን አሳልፎ የሚሰጥ ሰው ያለ እንደሆነ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር የለም” እንዲል (ዮሐ.፲፭፥፲፫) ቅዱስ ዮሐንስ፡፡

ክፉ ባልንጀርነት በተመለከተ እነዚህን ከላይ የጠቀስናቸውን ነጥቦች አነሣን እንጂ ሌሎችንም ማንሣት ይቻላል፡፡

በተቃራኒው ራስን ከክፉ ባልንጀራ በማራቅ መልካም ባልንጀርነትን መመሥረትና በምግባር በሃይማኖት ታንጾ መኖር ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት እንድናጠናክር ያደርገናል፡፡

ይቆየን

መጻሕፍት ክርስቶስ ሰው እንደሆነ እንደሚነግሩን አምላክ እንደሆነም ይነግሩናል

 

  • የማይመረመር፣ የማይለወጥ ቃል ሥጋን ተዋሐደ፤ መለወጥ ይስማማው የነበረ ሥጋን የማይለወጥ አደረገው፡፡ ስለዚህም በተዋሐደው በመዋቲ አዳም ሥጋ ተገለጠ፡፡ (እልመስጦአግያ)
  • ከእመቤታችን ከቅድስት ደንግል ማርያም የተወለደው የእግዚአብሔር የባሕርይ ልጅ ነው፤ እርሱም የባሕርይ አምላክ ነው፤ መለኮት ቢያድርበት በጸጋ የከበረ አይደለም፡፡ ሥጋን በመንሣት ሰው የሆነ እርሱ ብቻ ነው፤ በመለኮት የእግዚአብሔር ልጅ ነው፣ አምላክ ነው፡፡ ወልድ አንድ ብቻ ነው፡፡ (ቅዱስ አትናቴዎስ)
  • በሰው ባሕርይ ሰው የሆነ እርሱ ነው፤ ከአብ የተወለደ፣ ከባሕር አምላክ የተገኘ የባሕርይ አምላክ የዘለዓለም ንጉሥ እርሱ ነው፡፡ (ሐዋርያት)
  • ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል በእመቤታችን በንጽሕት ድንግል ማርያም ማኅፀን አደረ፤ ስለ መለኮት ተዋሕዶ በዚህ በምንናገርም በወልድ ያለውን ነው፡፡ ስለ አብ ስለ መንፈስ ቅዱስ ሰው ለመሆን በድንግል ማኅፀን አደሩ አንልም፡፡ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ብቻ ከእርሷ ተወለደ እንላለን፡፡ (ቅዱስ አግናጥዮስ)
  • በቤተልሔም ተወለደ፣ በጨርቅ ተጠቀለለ፣ በበረት ተጣለ፤ ከብት ጠባቆች አዩት፣ መላእክት አመሰገኑት፣ ሰብአ ሰገል ሰገዱለት፡፡ (ቅዱስ ሄሬኔዎስ)
  • ከእመቤታችን ከንጽሕት ድንግል ማርያም ሥጋችንን ነሥቶ የተዋሐደው እርሱ ነው፤ ሥጋ ከመሆን በቀር ያለ መለየት ያለ መለወጥ ከአብ ጋር አንድ ነው፤ በሥጋም ያለመለይት ከእኛ ጋር አንድ ነው፡፡ (ቅዱስ ጎርጎርዮስ)
  • ከአብ የተወለደ፣ ከአብ ከመንፈስ ቅዱስ ጋር አንድ የሚሆን የእግዚአብሔር ቃል ሰው ሆነ፤ በመለኮቱ መዋረድ ሳይኖርበት በፈቃዱ ተዋርዶ የተገዥ ባሕርይን ተዋሐደ፡፡ ሰው ሆይ ሥጋ ያልነበረው እርሱ ለአንተ ብሎ ሥጋን ተዋሐደ፤ ሰው ሆይ በመለኮቱ የማይዳሠሥ የነበረ ነፍስና ሥጋን የተዋሐደ ቃል ለአንተ ብሎ ተዳሠሠ፤ በመለኮቱ ጥንት የሌለው እርሱ ጥንት ያለውን ፍጹም ሥጋን ተዋሐደ፡፡ (ቅዱስ አጢፎስ)
  • የከበሩ መጻሕፍት ክርስቶስ ሰው እንደሆነ እንደሚነግሩን አምላክም እንደሆነ እነርሱ እንዲሁ ይነግሩናል፡፡ ግዙፍ እንደሆነ እንደሚነግሩን ረቂቅም እንደሆነ፡፡ የእግዚአብሔር ቃልም እንደሆነ እርሱ ራሱም እግዚአብሔር እንደሆነ እንዲሁ ይነግሩናል፡፡ ከንጽሕት ድንግል ማርያም በኋላ ዘመን እንደተወለደ እንደሚነግሩን ቀድሞም ከአብ እንደተወለደ እንዲሁ ከአባት ያለ እናት፣ ከእናት ያለ አባት ለመወለድ መዠመሪያ እርሱ እንደሆነ ይነግሩናል፡፡ (ሄሬኔዎስ)
  • ከብርሃን የተገኘ ብርሃን፣ ከሕይወት የተገኘ ሕይወት ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው ልጁን ወደዚህ ዓለም ላከው፤ ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የእኛን ባሕርይ ይዋሐድ ዘንድ ጌትነቱንም ወደ ማወቅ ያደርሰን ዘንድ ነው፡፡ (ቅዱስ ጎርጎርዮስ)
  • እግዚአብሔር ቃል ወደዚህ ዓለም ይመጣ ዘንድ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ሥጋን ይዋሐድ ዘንድ ምን አተጋው? በጨርቅ ይጠቀለል፣ በበረት ይጣል ዘንድ ከሴት(ከድንግል) ጡት ወተትን ይጠባ ዘንድ በዮርዳኖስ ይጠመቅ ዘንድ ምን አተጋው? (ቅዱስ እለእስክንድሮስ)
  • ለመወለዱ ጥንት በሌለው አስቀድሞ ዓለም ሳይፈጠር በመለኮቱ ከአብ በተወለደ፣ ዳግመኛም እኛን ለመዳን በኋላ ዘመን ከቅድስት ድንግል ማርያም በተወለደ በእግዚአብሔር ልጅ እናምናለን፤ የቀኑ ቀጠሮ ሲደርስ እግዚአብሔር ልጁን ላከ፣ ከድንግልም ተወለደ፡፡ (ቅዱስ አትናቴዎስ)
  • ከሰው ባሕርይ ጋር አይመሳሰልም፣ ልደቱም እንደ ሰው ልደት አይደለምና ረቂቅ ምሥጢር ነው፤ አይመረመርም፡፡ (ቅዱስ ጎርጎርዮስ)

ምንጭ፡- ሃይማኖተ አበው

ይቆየን

እሰይ እሰይ እሰይ

በትዕግሥት ባሳዝነው

በድቅድቁ ሌሊት፣

በዕንባ ጸሎት ተጠምጄ፣

በአታላዩ ምላሶቹ ፤

በጠላቴ ተከድቼ።

ነጋ ጠባ ማዳንህን ስጠባበቅ፣

የመምጣትህን ዜና መውረጃህን ስናፍቅ።

ተወለድክልኝ የኔ ጌታ ፣

ሞቴን አንተ ልትሞት፣

መጣህልኝ የኔ ተስፋ ፣

ልታድነኝ ከዳግም ሞት፣

ወረድክልኝ የኔ አለኝታ።

ልትፈታኝ ከባርነት፣

የአብርሃም ደግነት፣

ላያነጣኝ ከኃጢአቴ፣

የሙሴ የዋህነት፤

ላያስፈታኝ ከእሥራቴ፣

የዳዊት ንግሥና ፤

ላይጠብቀኝ ከጠላቴ፣

የሰለሞን ጥበብ፤

ላያጥናናኝ ከሐዘኔ፣

የመልከ ጼዲቅ ክህነት፤

ላያስፈታኝ ከእሥራቴ፣

የአስቴር ጸሎት፤

ላያስጥለኝ ከገዳዬ፣

የመርዶኪዎስ ታማኝነት፤

ላያሰርዝ የአዋጅ ደብዳቤዬን፣

የኤሊያስ ግሳፄ፤

ላይመልሰው ክፉ ልቤን፣

የዮናስ ስብከት፤

ላያሽረው ሕመም ቁስሌን።

በአክአብ ደም ተለውሰው እጆቼ፣

የአቤል ደሙ በፊትህ ሁነውብኝ ከሳሾቼ፣

ነበር እኮ ሰዶምነት አመል ግብሬ፣

ቂም በቀልም መልክ ግንባሬ።

አመንዝራ፣ ሴሰኝነት መለያዬ፣

መለያየት፣ አድመኝነት መድመቂያዬ።

አልነበረም መልክህ መልኬ፤

ግብርህ ግብሬ፤

ስምህ መጠራዬ።

እና መጣህልኝ የኔ ጌታ፤

ልትፈታኝ ከእሥራቴ፤

ወረድክልኝ የኔ አለኝታ፣

ልታድነኝ ከዳግም ሞት፣

ተወለድክልኝ የኔ ተስፋ።

በሞቴ አንተ ልትሞት፣

ክፋት በደል ቢያቆሽሸኝ፣

ሕግን መሻር ባሪያ አድርጎኝ።

ጽድቄም ቢሆን የመርገም ጨርቅ፣

መሥዋቴ እዚሁ ቢደርቅ፣

ጾም ጸሎቴ በደል ባይፍቅ።

ዕንባ ሐዘኔ ባያስጥለኝ ከባርነት፤

ግብሬ ሆኖ መለያዬ፣

መውጫ አጥቼ ከመከራ፣

ስሜ ጠፍቶ በስምህ ላልጠራ።

መምጣትህን እየናፈኩ፣

ማዳንህን እየጠበኩ።

መጣህልኝ የኔ ጌታ፣

በሞቴ አንተ ልትሞት፣

ወረድክልኝ የኔ ተስፋ።

ልታድነኝ ከዳግም ሞት፣

ተወለድክልኝ የኔ አለኝታ፣

ልታወጣኝ ከባርነት።

እሰይ እሰይ እሰይ፤

ተወለደ የኔ ጌታ፣

ተጠመቀ የኔ አለኝታ።

እሰይ እሰይ እሰይ!!!

 

እንኳን ለጌታችን ለመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ልደት በሰላም አደረሳችሁ!

መልካም በዓል ይሁንላችሁ!!!

 

“እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል” (ሉቃ. ፪፥፲፩)

አንኳን ለጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ!

በእንዳለ ደምስስ

አውግስጦስ ቄሳር የሮም ገዥ፣ ሄሮድስ የይሁዳ ንጉሥ፣ በነበሩበት ወቅት በሀገረ እስራኤል በቤተ ልሔም የሰውን ልጅ ሕይወት ወደ ድኅነት ያሸጋገረ ታላቅ ነገር ተከሰተ፡፡ ይህንንም ክስተት ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ እንዲህ ይገልጸዋል፡፡ “እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው፡፡ ለእናንተም ምልክቱ እንዲህ ነው፡- ሕፃን አውራ ጣቱን ታስሮ፣ በጨርቅ ተጠቅልሎ በበረት ውስጥ ተኝቶ ታገኙታላችሁ፡፡” (ሉቃ. ፪፥፲፩)

ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ ወቅቱን በተመለከተ ሲገልጽ “በዚያም ወራት እንዲህ ሆነ፤ ሰው ሁሉ ይቆጠር ዘንድ ከአውግስጦስ ቄሣር ትእዛዝ ወጣ፡፡ … ዮሴፍም ከገሊላ አውራጃ ከናዝሬት ከተማ ወደ ይሁዳ ቤተ ልሔም ወደምትባለው ወደ ዳዊት ከተማ ወጣ፤ እርሱም ከዳዊት ሀገርና ከዘመዶቹ ወገን ነበርና፡፡ ፀንሳ ሳለች ከእጮኛው ከማርያም ጋር ይቆጠር ዘንድ ሄደ፡፡” (ማቴ. ፪፥፩-፭) በማለት ሂደቱን ይገልጻል፡፡

አዳም ትእዛዛትን በማፍረሱ ምክንያት ከገነት ከወጣ አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመን ሲፈፀም፣   በመንፈስ ቅዱስ ግብር በነቢያት ትንቢት፣ በመልአኩ በቅዱስ ገብርኤል ብስራት በኅቱም ድንግልና ተፀንሶ በኅቱም ድንግልና በቤተ ልሔም በከብቶች በረት ተወለዷልና ልደቱ ልዩ ነው፡፡ (ማቴ. ፩፥፲፯)፡፡

በዚያም (በቤተልሔም) የሚያርፉበት ቦታ አልነበረምና በከብቶች በረት እያሉ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርም የመውለጃዋ ወራት ደረሰ፡፡ የበኩር ልጅዋንም ወለደችው፤ አውራ ጣቱንም አሰረችው፣ በጨርቅም ጠቀለለችው፡፡ ወቅቱ የብርድ ወራት ነበርና ከብቶች በትንፋሻቸው አሟሟቁት፡፡ በዚህም በነቢይ “ድንግል ትፀንሳለች፣ ወንድ ልጅም ትወልዳለች” የተባለው (ኢሳ. ፯፥፲፬) ተፈፀመ፡፡

የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መወለድ በጨለማ የነበርነውን ወደ ብርሃን አወጣን፡፡ “በጨለማ የሄደ ሕዝብ ታላቅ ብርሃን አየ፤ በሞት ጥላና በጨለማ ሀገርም ለነበሩ ብርሃን ወጣላቸው” እንዲል፡፡ (ኢሳ. ፱፥፪) ዘመኑ ሲፈጸም አዳምና ልጆቹን ያድን ዘንድ፣ ሞትንም ይሽረው ዘንድ ወደዚህች ምድር ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ፣ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ በተዋሕዶ ተወለደ፡፡

ነቢየ እግዚአብሔር ኢሳይያስ የተበታተኑትን ሊሰበስብ፣ ተጣልተው የነበሩትን ሰውና እግዚአብሔር፣ ሰውና መላእክትን ያስታርቅ ዘንድ መምጣቱንም ሲገልጽ “ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና፤ አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል፤ ስሙም ድንቅ መካር፥ ኀያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል።” በማለት በትንቢት የተናገረው ደረሰ፡፡ (ኢሳ. ፱፥፮)

መዝሙረኛው ዳዊትም “እነሆ በኤፍራታ ሰማነው፤ ዛፍ በበዛበትም ቦታ አገኘነው፡፡ እንግዲህስ ወደ እግዚአብሔር ማደሪያዎች እንገባለን፤ የጌታችን እግሮቹ በሚቆሙበት ቦታ እንሰግዳለን” በማለት የጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ከአንድ ሺህ ዓመታት በፊት የተነበየው ትንቢት ጊዜው ሲደርስ በቤተ ልሔም በከብቶች በረት ተፈጸመ፡፡ (መዝ. ፻፴፩፥፮)

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በቤተ ልሔም ልጇን (ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ) በወለደች ጊዜ እንስሳት ትንፋሻቸውን ገበሩለት፤ “በሬ ገዢውን አህያም የጌታውን ጋጣ ዐወቀ፤ እስራኤል ግን አላወቁኝም፥ ሕዝቤም አላስተዋሉኝም።” (ኢሳ. ፩፥፫) እንዲል፡፡

የሰማይ መላእክት ልደቱን በቤተ ልሔም በጎችን ይጠብቁ ለነበሩት እረኞች የምሥራች ተናገሩ፡፡   “በዚያ ሀገር እረኞች ነበሩ፤ ሌሊቱንም ተግተው መንጋቸውን ይጠብቁ ነበር፡፡ እነሆም፥ የእግዚአብሔር መልአክ በአጠገባቸው ቆመ፤ የእግዚአብሔርም ብርሃን በዙሪያቸው አበራ፤ ታላቅ ፍርሃትንም ፈሩ፡፡ መልአኩም እንዲህ አላቸው፣ “እነሆ፣ ለእናንተና ለሕዝቡ ሁሉ ደስታ የሚሆን  ታላቅ የምሥራች እነግራችኋለሁና አትፍሩ፡፡ እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኽውም ቡሩክ ጌታ ክርስቶስ ነው፡፡ ይህም ምልክት ይሆንላችኋል፤ ሕፃን ተጠቅልሎ በግርግምም ተኝቶ ታገኛላችሁ።” (ሉቃ. ፪፥፰-፲፫) በጌታችን ልደትም መላእክት ከሰው ልጅ ጋር አብረው አመሰገኑ፡፡

መልካም እረኛ የሆነው ጌታ ልደቱ ከዘመኑ ታላላቅ ነገሥታት ይልቅ ቀድሞ ለእረኞች ደረሰ፡፡ (ዮሐ. ፲፥፲፩) እረኞቹ አመስግነውም አልቀሩም፡፡ “እንግዲህ እስከ ቤተ ልሔም ድረስ እንሂድ፤ እግዚአብሔርም የገለጠልንን ይህን የሆነውን ነገር እንይ” ተባባሉ። ፈጥነውም ወደ ቦታው ደርስው እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ከሕፃኑ፣ እንዲሁም ዮሴፍ ጋር በግርግም ተኝቶ አገኙት። አይተውም አደነቁ፤ ያዩትንም ፈጥነው ሄደው የምሥራቹን ለሌሎች ተናገሩ፡፡

ሰብዓ ሰገል (የጥበብ ሰዎች) በኮከብ እየተመሩ ቤተ ልሔም ደርሰው በታላቅ ምስጋና የነገሥታት ንጉሥ ነውና ወርቅ ለመንግሥቱ፣ ዕጣን ለክህነቱ፣ ከርቤንም ለሞቱ ገበሩለት፡፡ በነቢይ “የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የሳባና የዓረብ ነገሥታት እጅ መንሻን ያመጣሉ” እንደተባለ፡፡ (መዝ. ፸፩፥፲)

ሄሮድስና ኢየሩሳሌም ግን “ንጉሥ ተወለደ” ሲባሉ ደነገጡ፡፡ ሄሮድስም የካህናት አለቆችንና የሕዝቡን ጻፎች ሁሉ ሰብስቦ “ክርስቶስ በየት ይወለዳል?” ብሎ ጠየቃቸው፡፡ እነርሱም “በይሁዳ ክፍል ቤተ ልሔም ነው፤ በነቢይ እንዲህ ተብሎ ተጽፏልና፡፡ የይሁዳ ምድር አንቺ ቤተ ልሔም ከይሁዳ አለቆች ከቶ አታንሺም፤ ሕዝቤን እስራኤልን የሚጠብቅ ንጉሥ ከአንቺ ይወጣልና፡፡”  ከዚህም በኋላ ሄሮድስ ሰብአ ሰገልን በስውር ጠራቸው፤ ኮከቡ የታየበትንም ዘመን ከእነርሱ ተረዳ፡፡ “ሂዳችሁ የዚያን ሕፃን ነገር ርግጡን መርምሩ፤ ያገኛችሁትም እንደ ሆነ እኔም መጥቼ እሰግድለት ዘንድ በእኔ በኩል ተመልሳችሁ ንገሩኝ” ብሎ ወደ ቤተ ልሔም ሰደዳቸው። (ማቴ. ፪፥፬-፱) ሄሮድስ ይህን ያለው እንደ ቃሉ ሊሰግድለት ሳይሆን ሊገድለው አስቦ ነበር፡፡ የሩቆቹ ነገሥታት ሰብአ ሰገል ሰሙ፤ ሄሮድስ እና መሰሎቹ ግን ሲሰሙ ተረበሹ፡፡ እነሆ ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኅን ተወልዷልና፡፡ (ሉቃ. ፪፥፲፩)

ከልደቱ በረከት ረድኤት ያሳትፈን፡፡ አሜን፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ በዓለ ልደትን አስመልክቶ ለመንፈስ ቅዱስ ልጆቻቸው ያስተላለፉት መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣

ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣

የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣

በሕመም ምክንያት በየፀበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤

እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ፡-

በፍጹም ፍቅሩ እኛን ወደ ሰላም ለማምጣት በእኛ ሰውነት በዚህ ዓለም የተወለደው ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ልደቱ በደኅና አደረሳችሁ!

“ትእምርተ ሰላምነ ወልድ ተወልደ ለነ፡ የሰላማችን ሰንደቅ ዓላማ የሆነው ወልድ ወይም ወልደ እግዚአብሔር ኢየሱስ ክርስቶስ ለኛ ተወለደልን” (ድጓ ዘቅዱስ ያሬድ)

ዓለም ሁሉ በተለይም የክርስቲያኑ ዓለም በትክክል እንደሚያውቀው ቅዱስ መጽሐፍ በሰዎች የቋንቋ ዘይቤ የተጻፈ የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ በመንፈሳዊም ሆነ በዓለማዊ ርእዮት ቋንቋ የመልእክት ማስተላለፊያና መግባቢ መሳሪያ እንደሆነ ይታወቃል፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ መልእክቱን በዚህ መንገድ ለሰዎች ሲያስተላል ኖሮአል፤ የሚያስተላልፈውም መልእክት እንዲሁ ተሰምቶ እንዲቀር ሳይሆን እንዲታወቅ፣ እንዲታመን እንዲተገበርና ሰዎች እንዲጠቀሙበት ነው፤ ከሚፈለገው ጥቅም ለመድረስም ሰዎች መልእክቱን በሚገባ መረዳት የግድ ይሆናል፤ ሰዎች እንዲረዱት ደግሞ በቋንቋቸውና በባህላቸው ዘይቤ ሊነገራቸው ይገባል፤

በመሆኑም እግዚአብሔር ቃሉን በሰዎች ቋንቋ ባህላዊ ዘይቤ መልእክቱን ለዓለም ሲያስተላልፍ ኖሮአል ቤተክርስቲያንም ይህንን መሠረት አድርጋ የእግዚአብሔርን ቃል በሰው ቋንቋ ዘይቤ ታስተምራለች፤ ከዚህ አንጻር በሰው ልማዳዊ የዘይቤ ቋንቋ ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “የሰላም ሰንደቅ ዓላማ” የሚል ቅፅል ተሰጥቶታል፡ ምክንያቱም ንጉሥም ወታደርም ተራው ሕዝብም የሀገሩ ነጻነትና ክብር፤ አንድነትና ሉዓላዊነት ምልክት የሆነውን ሰንደቅ ዓላማ ተከትሎ ስራ ይሰራል ክብሩንም ይገልፃልና ነው፤ ተከተል አለቃህን ተመልከት ዓላማህን የሚለው ብሂልም ይህንን ያንፀባርቃል፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን

ምእመናንና ምእመናት!

ጌታችን በመድኅንነቱ የሁላችን የሰላም ሰንደቅ ዓላማ በመሆኑ መምህራችን ቅዱስ ያሬድ የሰላማችን ሰንደቅ ዓላማ የሆነ ልጅ ተወለደልን ብሎ ይገልፀዋል፤ ጌታችን በዛሬው ዕለት በቤተልሔም ሰውነታችንን ሰውነት አድርጎ መወለዱ ራሱ የሰላም ማሳያ ምልክት ነው፤ ምክንያቱም ሳይወደን አይቀርበንም፤ አይዋሐደንምና ነው፤ በልደቱ ዕለት “ለዕጓለ እመሕያው ሠምሮ የሰው ልጅን ወደደው” ተብሎ በቅዱሳን መላእክት የተዘመረበትም ምክንያት ይኸው ነው፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ጌታችን የተዋሐደው ሰውነት የወዳጁ አልነበረም የጠላቱ እንጂ፤ ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን ሲገልፅ “ጠላቶቹ ሳለን እግዚአብሔር በልጁ ሞት ታረቀን” ይላልና ነው፡ በዚህ ዓለም የኖረውም ከሚያሳድዱት፣ ከሚከሱት፤ ስሙን ከሚያጠፉና ሊገዱሉት ከሚከጅሉ ጋር እንጂ ከወዳጆቹ ጋር ብቻ አልነበረም፤ እሱ ግን ሁሉንም በፍቅር ይቀበል ነበረ፤ ይፈውስና ያድን ነበረ፤ ያስተምርም ነበረ፤ ለሁሉም ስርየተ ኃጢአትን ሰጠ ለጠላቶቹም ጸለየ፤ ጌታችን በዚህ ሁሉ ለኛ አርእያና የተግባር መምህር በመሆኑ የሰላም ሰንደቅ ዓላማችን ነው፡፡

ምእመናንና ምእመናት

ዓለም በጌታችን ዕለተ ልደት የተዘመረውን ሰማያዊውን የሰላም መዝሙር መዘመር ከጀመረች እነሆ ዛሬ ድፍን ሁለት ሺሕ ዐሥራ ስድስት ዓመት ሆነ፤ የሰላሙ መዝሙር ዛሬም በመላው ዓለም በሚገኙ ክርስቲያኖች ይዘመራል፤ ይሁን እንጂ በዚህ ዓለም ሰላም ሰፍኖ እየታየ አይደለም፤ ይህ ለምን ሆነ ቢባል ደምበኛ መልስ ሊሆን የሚችለው እግዚአብሔርን አለማመንና አለመፍራት ያመጣው ችግር ነው የሚል ነው፤ ምክንያቱም ሃይማኖትና ፈሪሐ እግዚአብሔር ከሌለ ፍትሕ ይጐድላል፣ ፍትሕ ከጐደለ ብሶት ይፈጠራል፣ ብሶት ካለ ሰላም ሊኖር አይችልም፤ በሁሉም

የዓለማችን ክፍል ሃይማኖትና ፈሪሐ እግዚብሔር እየተዘነጋ በመሄዱ ቀውሱ ተባብሶ ይታያል፤ የሰው ልጅ ኑሮ በየትም ይሁን በየት በስጋት የተሞላ ሆኖአል፤ የሚወራው ሁሉ ስለ ግጭት ስለአየር ብክለት ስለ ረኃብና እልቂት ሆኖአል፤ ዓለም የጉልበተኞችና የባለ ሀብቶች ብቻ እንድትሆን የተፈጠረች እስክትመስል ድረስ ከባድ የፍትሕ መዛባት አጋጥሞአታል፤ የዝቅተኛው ማኅበረሰብ ሰብአዊ መብት ተዘንግቶአል፣ ከዚህ አኳያ ዓለም በዚህ እስከ ቀጠለች ድረስ ሰላም የማግኘቷ ዕድል በጣም አጠራጣሪ ነው፡ የክርስቶስ ልደት ያስተማረን ግን እንደዚህ አልነበረም፡፡

ጌታችን የተወለደው በተዋበና ምቹ በሆነ የሀብታም ቤት ሳይሆን በከብቶች በረት ነበረ፤ የተገለጠውም ለባለሥልጣኖች ሳይሆን ዝቅተኞች ለሚባሉ እረኞች ነበረ፤ ልዑላኑ ሰማያውያንና ትሑታኑ ምድራውያን በአንድነት አገናኝቶ ስለ ሰላም በጋራ እንዲዘምሩ አደረገ፤ አሳዳጅ ሳይሆን ተሳዳጅ ሆኖ በግብጽ አገር በመንከራተት አደገ፤ ይህን ሁሉ ያደረገው እኛ እሱን እያየን እንደ ሰንደቅ ዓላማ እንድንከተለው ነበር፤ ጌታችን ከባለሥልጣናቱና ከባለሀብቶቹ ይልቅ በድሆቹ ደረጃ የተወለደው ለድሆቹና ለዝቅተኞቹ ትኩረት እንድንሰጥ ለማስተማር ነው፤ የእኛ ድርጊት ግን ግልባጩ ሆኖ እየተስተዋለ ነው፡፡

እጅግ የሚያሳዝነው ደግሞ ክርስቲያን ነኝ ብሎ፤ በስመ እግዚአብሔር ተሰይሞ፤ መስቀልን በአንገቱ ተሸክሞ የእሱ መሰል በሆነው ወይም መስቀል በተሸከመው ወንድሙ እና እኅቱ እንዲሁም በመሰል ፍጡር ላይ ያለ ርኅራኄ ሲጨክን መታየቱ ነው፡ እንዲህ እየሆነ እንዴት ሰላም ይምጣ? እግዚአብሔርስ እንዴት በረከቱ ይሰጣል? ይህ እጅግ በጣም ሊታሰብበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን

ምእመናንና ምእመናት!

እኛ ኢትዮጵያውያን ከእንዲህ ዓይነቱ የሃይማኖትና የሞራል ዝቅጠት በአስቸኳይ መውጣት አለብን፤ ጠቡ፤ መለያየቱ፣ መጨካከኑ፤ ለኔ ለኔ መባባሉ ከረምንበት፤ ሆኖም ያመጣልን ነገር ቢኖር ሁለንተናዊ ውድመት ብቻ ነው፡ ያስገኘልን ትርፍ ይህ መሆኑ እያወቅን በዚሁ ልንቀጥል አይገባም፡ ሰው ችግሩን በልቡ እያወቀ በዓይኑ እያየ እንዴት ገደል ውስጥ ይገባል? ዕርቅና ይቅርታ ማንን ጐዳ? ሰላምና አንድነት ማንን አከሰረ? ሰበብ አስባብ እየተፈለገ በሆነውም ባልሆነውም ከመተላለቅ ለምን ኢትዮጵያ የሁላችን ናት ብለን በእኩልነትና በስምምነት መኖር አቃተን?

ሦስት ሺሕ ዘመናት አብረው የኖሩ ሕዝቦች እንዴት ችግራቸውን በጠባይና በብልሐት ማስወገድ አቃታቸው? ይህ ከቶ ሊሆን አይገባም፤ ሁላችንም ሰክን ብለን እናስብ፤ ለሁሉም የማሰቢያና የመመካከሪያ ጊዜ ፈጥረን ችግሩን በስፍሐ አእምሮ እንፍታው፡ ችግርን በምክክርና በይቅርታ መፍታት አማራጭ የሌለው ጥበብ ነው፤ የሃይማኖት መሪዎች፤ የሀገር ሽማግሌዎች፤ ምሁራንና ልኂቃን በዚህ ተግተን ልንሰራ ይገባል፤ መንግሥትና የፓለቲካ ፓርቲዎችም ለዚህ የበኩላቸውን ድጋፍ ያድርጉ፤ በዚህም ሰላማችንን እንመልስ፡፡

በመጨረሻም

በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በተከሠተው የድርቅና የሰው ሰራሽ ምክንያት በችግር ላይ የወደቁ ወገኖች በርካታ ናቸው በመሆኑም የወገን ደራሽ ወገን ነውና ሁሉም ካለው ብቻ ሳይሆን የቀን ቍርሱን ለተቸገሩ ወገኖች እንዲለግስና በመተጋገዝ ረኃቡን እንድንከላከለው ጥሪያችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የልደት በዓል ያድርግልን

እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!! ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!! አሜን።

አባ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አዲስ አበባኢትዮጵያ

 

በዓለ ክብሩ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታኅሣሥ ፲፱ ቀን ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ከእግዚአብሔር ተልኮ ሠለስቱ ደቂቅን (አናንያ፣ አዛርያ እና ሚሳኤል) ከነደደ እሳት ያዳነበትን መታሰቢያ በዓል በድምቀት ታከብራለች፡፡

ቅዱስ ገብርኤል አብሣሪ መልአክ እንደሆነ ሁሉ ምእመናን እግዚአብሔርን በማምለካቸው ምክንያት ከአላውያን ገዢዎች ከሚደርስባቸው መከራም የሚታደጋቸው መልአክ ነው፡፡ የፋርስ ንጉሥ የነበረው ናብከደነፆር እግዚአብሔር አምላክ ምድሪቱን እና ሕዝቡን ያስተዳድር ዘንድ ቢፈቅድለት በትዕቢት ተሞልቶ “በኃይሌ አደርጋለሁ፣ በማስተዋል ጥበቤም የአሕዛብን ድንበሮች አርቃለሁ፣ ሀብታቸውንም እዘርፋለሁ፣ የሚቀመጡባቸውንም ከተሞች አናውጣለሁ፣ በእጄም ዓለምን ሁሉ እንደ ወፍ ቤት እሰበስባለሁ፣ እንደ ተተወ እንቁላልም እወስዳቸዋለሁ፤ ከእኔም የሚያመልጥ የለም፤ የሚቃወመኝም የለም” ብሎ በመታበይ የወርቅ ጣዖትን አሠርቶ በባቢሎን አውራጃ ቁመቱ ስድሳ ክንድ፣ ወርዱም ስድስት ክንድ የሆነ የወርቅ ምስል አሠርቶ በዱራ ሜዳ ላይ አቆመው፡፡ (ኢሳ. ፲፥፲፫-፲፬፤ ዳን.፫፥፩)፡፡

መኳንንትንና ሹሞቹን እንዲሁም ሕዝቡን አስጠርቶ በዐዋጅ ነጋሪ “ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው ለወርቁ ምስል ስገዱ፤ ወድቆም የማይሰግድ በዚያን ጊዜ በሚነድ እሳት እቶን ውስጥ ይጣላል” ሲል ዐዋጅ አስነገረ፡፡ ይህን ዐዋጅ የሰሙ የንጉሥ ሹማምንት ሁሉ ተደፍተው ለወርቁ ምስል ሰገዱ፡፡ ነገር ግን በመካከላቸው አናንያ፣ አዛርያ እና ሚሳኤል ንጉሡ ላቆመው ምስል አልሰገዱም፡፡

ነገር ሠሪዎችም ይህንን ወሬ ለንጉሥ ባደረሱ ጊዜ ንጉሡ እጅግ ተቆጥቶ ካስጠራቸው በኋላ “… አምላኬን አለማምለካችሁ ላቆምሁትም ለወርቁ ምስል አለመስገዳችሁ እውነት ነውን?” ሲል ጠየቃቸው፡፡

አናንያ፣ አዛርያ እና ሚሳኤል ግን በንጉሡ ፊት ቆመው “ንጉሥ ሆይ፥ እኛ የምናመልከው አምላክ በሰማይ አለ፡፡ ከሚነድደው ከእቶኑ እሳት ያድነን ዘንድ ይችላል፤ ከእጅህም ያድነናል፡፡ ንጉሥ ሆይ! ይህም ባይሆን አማልእክትህን እንዳናመልክ ላቆምኸውም ለወርቁ ምስል እንዳንሰግድ ዕወቅ” አሉት፡፡ (ዳን.፫፥፬፫-፲፰)፡፡

የንጉሥ ናቡከደነፆር ቁጣ ከፊት ይልቅ እጅግ ነደደ፤ እሳቱንም ሰባት እጥፍ እንዲያቀጣጥሉና እነዚህን ሦስት ብላቴኖች እጅና እግራቸውን አስረው ከእቶን እሳት ውስጥ እንዲጨምሩአቸው አዘዘ፤ ጋሻ ጃግሬዎቹም ፈጥነው ወደሚነደው እሳት ጨመሯቸው፡፡ እግዚአብሔርም የሦስቱን ወጣቶች የእምነት ጽናት ተመለከተ፡፡ በፊቱ የሚቆመውን ባለሟሉን የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤልንም ከመጣባቸው መከራ ይታደጋቸው ዘንድ ላከላቸው፡፡ ቅዱስ ገብርኤልም ከእስራታቸው ፈታቸው፤ እሳቱንም እንደ ውኃ አቀዘቀዘው፡፡ ሠለስቱ ደቂቅም ከተጣሉበት ሆነው መልአኩን ልኮ ከዚህ እቶን እሳት ያዳናቸውን አምላክ አመሰገኑት፡፡

ንጉሡ ናብከደነፆርም ሠለስቱ ደቂቅ እሳቱ አንዳች ጉዳት ሳያደርስባቸው በእሳት ውስጥ ሲመላለሱ ተመለከተ፡፡ “እነሆ እኔ የተፈቱ በእሳቱም መካከል የሚመላለሱ አራት ሰዎችን በዚያ አያለሁ ምንም የነካቸው የለም፤ የአራተኛውም መልክ የእግዚአብሔርን ልጅ ይመስላል” ብሎ ፊቱን ጸፍቶ አፉንም ከፍቶ እንዲናገር አደረገው፡፡ ሠለስቱ ደቂቅ በእሳቱ ውስጥ ሆነው እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ ሰማቸው፡፡ መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም ከነደደው እሳት አዳናቸው፡፡ (ዳን. ፫፥፳፬-፳፮)

ናብከደነፆር የተደረገውን ተአምር ተመልክቶ ወደ እሳቱ በመቅረብ ለሦስቱ ብላቴኖች  “እናንተ የልዑል አምላክ ባሪያዎች ሲድራቅ፣ ሚሳቅንና አብደናጎም ኑ ውጡ” ብሎ ተናገራቸው፡፡ (ዳን.፫፥፳፮) እነርሱም እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ወጡ፡፡ መሳፍንቱና ሹማምቶችም የሚያመልኩት አምላካቸው ቅዱስ እግዚአብሔር የሚነደው እሳት ሰውነታቸውን ሳይበላ፣ የራሳቸውም ጸጉር ሳይነካ፣ የእሳቱም ሽታ በላያቸው እንዳልነበረ አዩ፡፡ ንጉሡ ናቡከደነፆርም በሠለስቱ ደቅቅ ፊት ለእግዚአብሔር ሰገደ፡፡ እግዚአብሔርንም እያመሰገነ ሕዝቡን ሁሉ የብላቴኖቹ ሠለስቱ ደቂቅን አምላክ እንዲያመልኩ፤ አናመልክም በሚሉትና የስደብን ነገር በሚናገሩት ላይ ከፍተኛ ቅጣት እንደሚደርስባቸው ዐዋጅ አስነገረ፡፡ ሚሳቅን፣ ሲድራቅና አብደናጎምንም በባቢሎን አውራጃ ውስጥ ሾማቸው፡፡ ከፍ ከፍም አደረጋቸው፡፡

ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ልጆቿን ከእነዚህ ብላቴኖች የእምነት ፍሬ ተምረው፣ የመልአኩ ቅዱስ ገብርኤልንም ተራዳኢነት ተረድተው እግዚአብሔርን በማምለክ እንዲጸኑ ታኅሣሥ ፲፱ ቀንን ትዘክራለች፤ በታላቅ ድምቀትም ታከብረዋለች፡፡

የመላእክት አለቃ የቅዱስ ገብርኤል ምልጃና ተራዳኢነት አይለየን፤ ለዘለዓለሙ አሜን፡፡

በሁለት ወገን የተሳላችሁ ሁኑ!

ዲ/ን ስንታየሁ አለማየሁ

ሰው በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠረ፣ ነገር ግን ከሁሉ የሚልቅ ዕፁብ ድንቅ ፍጥረት ነው። ከአፈር መፈጠሩ ሲታይ “ታስበው ዘንድ ሰው ምንድነው?” ፤ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል መፈጠሩ ሲታይ ደግሞ “ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አሳነስኸው፤ የክብርና የምስጋና ዘውድ ጫንህለት፥ በእጆችህም ሥራ ላይ ሾምኸው” ማለቱ የእግዚአብሔርን ቸርነት ሁሉን በአግባቡና በሥዓቱ ፈጥሮ የሚገዛ አምላክ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡ (ዕብ. ፪፥፮-፯)

እግዚአብሔር ሰውን በዚህ በሚያስደንቅ ሁኔታ ከ፬ቱ ባሕርያተ ሥጋ (ከአፈር፣ ከነፋስ፣ ከእሳትና ከውኃ) እና ከ ፫ቱ ባሕርያተ ነፍስ (ሕያዊት፣ ለባዊት፣ ነባቢት) ፈጥሮ ፍጥረትን ሁሉ እንዲጠብቅ፣ እንዲገዛ አድርጓል። የሥጋ ባሕርያት እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ቢሆኑም እንኳ በሰው ላይ ተስማምተውና ጸንተው የፈጣሪን ከሀሊነት አሳይተዋል ። ስለዚህም የሰው ልጅ ስንል የነፍስ እና የሥጋ ተዋሕዶ ማለታችን ነው። የሥጋንና የነፍስን ሚዛን አስማምቶና ከኃጢአት ርቆ የሚኖር ሰው እርሱ በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ነው።

በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ በሁለቱም በኩል መሥራትና የታለመለትን ውጤት ማስገኘት ይችላል።  ማለትም መቁረጥ ከሆነ መቁረጥ፣ መጥረብ ከሆነ መጥረብ… ፤ እንዲሁ ሰው ነፍሱንና ሥጋውን በእግዚአብሔር ቃል፣ በመልካም ምግባርና ሃይማኖት በመጠበቅ ከገለጠ እርሱ በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ነው። ምክንያቱም በእምነት የተገለጠ ክርስትና ነፍሳትን ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ያደርሳልና።

ነፍሳችን ከእግዚአብሔር ከተቀበለችው አንዱ ጸጋ ዐዋቂነት ነው። በእምነት በጎ ሥራን ለመሥራት ዕውቀት ያስፈልጋል። በእምነት፣ በዕውቀትና በጥበብ እንደ ባለ አእምሮ ከተመላለስን ለዓለም ምሳሌ ሆነን በክብር በጨለማው ውስጥ እናበራለን። ነገር ግን ዕውቀታችንና ጥበባችን ከእግዚአብሔር ከለየን፤ እግዚአብሔር በሐዋርያው ላይ አድሮ እንደ ነገረን “እግዚአብሔርን ለማወቅ ባልወደዱ መጠን እንዲሁ እግዚአብሔር ይህን የማይገባውን ይሠሩ ዘንድ ሰነፍ አእምሮን ሰጣቸው” እንዲል ይገሥጸናል። (ሮሜ. ፩፥፳፰)

በሁለት በኩል መሳል ለምን ያስፈልጋል?

በሁለት በኩል መሳል የሥጋን ባሕርይ ለነፍስ በማስገዛት የእግዘብሔርን ስም በመቀደስ ክብሩን እንዲወርስ ያደርጋል። ሰዎች በሁለት በኩል መሳላቸው ከራስ አልፈው ለሌሎች ነፍስ መዳን ምክንያት ይሆናሉ። እንዴት ቢሉ፡- የእግዚአብሔርን ቃል በማስተማር፣ በመምከር፣   በማሳመን ብዙዎችን ከገቢረ ኃጢአት ወደ ገቢረ ጽድቅ ይመልሳሉ። ሃይማኖትንና ምግባርን አስተባብረው በርትተው በመሥራትም የተራበ ያበላሉ፣ የተጠማ ያጠጣሉ፣ የታረዘ ያለብሳሉ፣ አልፎ ተርፎም ለብዙዎች አርአያ ይሆናሉ፡፡ ለዚህ ነው ታላቁ አባት ብፁዕ አቡነ ሺኖዳ “ለራሱ ብቻ የኖረ ሰው አልኖረም ማለት ነው” ያሉት። ሰው በሕይወቱ የእግዚአብሔርን ቃል ከመማር በተጨማሪ የዓለምን ፍልስፍናና ዕውቀት ማወቅ ተገቢ ነው። እንዲህ ሲሆን ለሁሉም በሚገባው ቋንቋ ነገረ እግዚአብሔር አስተምሮ ለመንግሥቱ ያቀርባልና።

“እግዚአብሔር የለም” በሚሉ ሰዎች ፊት እግዚአብሔር መኖሩን እነርሱ በደረሱበት የዕውቀት ልክ ገልጦ ሲመሰክር “ስለዚህ በሰው ፊት ለሚመሰክርልኝ ሁሉ እኔ ደግሞ በሰማያት በአባቴ ፊት እመሰክርለታለሁ” የሚለውን ሽልማት ይጎናጸፋል፡፡ (ማቴ. ፲፥፴፪) በመንግሥቱም እንደ ፀሐይ ደምቆ ያበራል። ሰዎች በመንፈሳዊም ሆነ ዓለማዊ ሕይወታቸው በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ሲሆኑ ተልእኳቸው በስኬት ይታጀባል፤ ከራሳቸው አልፎ ወደ ሌሎችም ይሻገራል። ለዚህ ነው “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ” የተባለው ። (ማቴ. ፭፥፲፫)

ጨው ከራሱ አልፎ ለሌላው ጣዕም ይሰጣል፤ አልጫውንም ያጣፍጣል። በሁለት ወገን የተሳለ ሰውም በምግባሩና በሃይማኖቱ ለሌላው የሕይወት መዓዛ ይሆናል “በሚድኑትና በሚጠፉት ዘንድ ለእግዚአብሔር የክርስቶስ መዓዛ ነንና፤ የሞት መዓዛ የሚገባቸው ለሞት፤ የሕይወት መዓዛ የሚገባቸውም ለሕይወት ናቸው” (፪ኛቆሮ ፪፥፲፭) እንዲል። የምድር ጨው (Nacl) የተገነባው ከሁለት መሠረታዊ ንጥረ ነገሮች ማለትም ከሶዲየም(Na) እና ክሎሪን(Cl) ሲሆን ሁለቱም ለብቻቸው  ለሰው ልጅ ጸር ናቸው። ነገር ግን ሁለቱ አንድ ሲሆኑ ከራስ አልፈው ለሌላ ጣዕም ይሆናሉ። ሰውም መንፈሳዊውን እና ዓለማዊው ሕይወቱን አዋሕዶ ሲገኝ በሁለት በኩል የተሳለ ሰይፍ ይሆናል፡፡ ከራሱ አልፎ በሥጋም በነፍስም ለሌላው ይጠቅማል።  ከሁሉም በላይ እግዚአብሔርን በመፍራት የሕሊናውን ሚዛን ይጠብቃል፡፡ ምክንያቱም “የጥበብ ሁሉ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው”ና፡፡ (መዝ.፻፲፩፥፲)

መንፈሳዊ አገልግሎትን ከትምህርት ጋር እንዴት ማጣጣም ይቻላል?

መንፈሳዊ አገልግሎት በእግዚአብሔር ለተለየ አገልግሎት መመረጥ እንደ መሆኑ መጠን ከትምህርት፣ ከመደበኛ ሥራችን እና ሌሎች ማኅበራዊ ሕይወታችን ጋር አጣጥሞ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ ለአገልግሎት መጠራታችንን ከተረዳን ከሌሎች ተግባራቶቻችን ጋር በጊዜ ለክተንና አስማምተን በዕቅድ ራሳችንን መምራት ይገባል፡፡ “… አሁንም በፊቱ ትቆሙና ታገለግሉት ዘንድ አገልጋዮቹም ትሆኑ ዘንድ እግዚአብሔር መርጧችኋልና ቸል አትበሉ” ሲል እግዚአብሔር በነቢዩ ሕዝቅያስ ላይ አድሮ እንደተናገረ፡፡ (፪ኛ ዜና. ፳፱፥፩-፲፩፤ ማቴ. ፱፥፱) መመረጥ መልካም እንደሆነ ሁሉ ለተመረጡበት አገልግሎት ታምኖ መገኘትና ማገልገል ከአንድ መንፈሳዊ አገልጋይ ይጠበቃል፡፡ ነገር ግን አገልግሎታችን ፍሬ እንዲያፈራ ሌሎች ከምናከናውናቸው ተግባራት ጋር ማስማማት ግድ ይላል፡፡

መንፈሳዊ አገልግሎት የሚከናወነው በእግዚአብሔር ፈቃድ ነው፡፡ አገልግሎቱ የመንፈስ ቅዱስ እንጂ የሰው አለመሆኑን ማመን ተገቢ ነው። በሰው ጥበብ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ረዳትነት፣ ዕውቀትና ብቃት ብቻ የሚከናወን አይደለም፡፡ የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስንጠይቅ መንፈሳዊው አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ለሕይወታችን ለሚያስፈልጉን ነገሮች ሁሉ መቃናት ወሳኝ ነው፡፡ “ካለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም” ብሎናልና፡፡ (ዮሐ. ፲፭፥፭) ስለዚህ የምናከናውናቸውን ተግባራት በጊዜ ለክተንና መድበን ሁሉንም በአግባቡና በሥርዓት ማስኬድ ይጠበቅብናል፡፡ በተለይም ወጣቶች ይህንን ከተረዱ በመልካም አገልግሎታቸው እና ልዩ ልዩ ተግባራት  ለሌሎች አርአያ መሆን እንችላሉ፡፡

ወጣትንነትን ስንመለከት የእሳትነት ዘመን እንደ መሆኑ መጠን ስሜታዊነት ጎልቶ የሚታይበት ጊዜ ነው፡፡ በተለይም በግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ውስጥ አገልግሎትን ከመደበኛ ትምህርት ጋር አጣጥሞ መጓዝ ላይ በርካታ ችግሮች ይስተዋላሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ራስን በዕቅድ አለመምራት ነው፡፡ ዕቅድ ሲታቀድ ደግሞ በጊዜ ተለክቶ በመሆኑ ለተግባራዊነቱ ቁርጠኛ መሆንን ይጠይቃል፡፡ በተለይም በበርካታ ወጣቶች ላይ የሚታየውን ስሜታዊነት ማረቅ የሚቻለውና ለተጠሩለት አገልግሎት እንዲሁም ለመደበኛ ትምህርት አስፈላጊውን ጊዜ ሲሰጡ   ነው፡፡

በመጀመሪያ የሚያስፈልጉትንና የማያስፈልጉትን መለየት ይገባል። ቀጥሎም አሁን

ከሚያስፈልገው በመነሣት ሁሉንም በቅደም ተከተል መዘርዘር ያስፈልጋል፡፡ ምክንያቱም፡-  ጊዜ የሚባል በጣም ውድ የእግዚአብሔር ስጦታ አለና። ጊዜ በአግባቡ ከተጠቀምንበት ወርቅ ነው፡፡ ለሁሉም ጊዜው አለውና “ለሁሉ ዘመን አለው፤ ከፀሐይ በታችም   ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው፡፡” (መክ. ፫፥፩) እንዲል ጠቢቡ፡፡ ጊዜ የለኝም! ነገ አገለግላለሁ!  ነገ እሠራለሁ! ማለት ለተጠሩለት አገልግሎት ታማኝ ሆኖ አለመገኘትን ያመለክታልና ምክንያት ከመደርደር ይልቅ በተገቢ ጊዜና ሰዓት ተገቢውን አገልግልሎት መፈጸም ይገባል፡፡ በምንም ጊዜና ሁኔታ ውስጥ ብንሆን እንኳን ሁሉን በተገቢው መንገድ አቀናጅተን እንሠራለን፤ እናገለግላለን፡፡ በሐዋርያው ቃልም እንዲህ እንላለን” … አገልግሎት ስላለን አንታክትም” (፪ቆሮ. ፬፥፩)፡፡

እዚህ ላይ ቆም ብለን ራሳችንን አንድ ነገር እንጠይቅ፡- ጊዜ የሚያንሰኝ ለምንድነው? ለትምህርቴስ? ለአገልግሎቴ ለጓደኞቼ የምሰጠው ጊዜ ምን ያህል ነው? ለቤተሰቦቼስ? ለማኅበራዊ ሚዲያስ? … በአጠቃላይ ምን ምን እያከነወንኩ ነው ጊዜዬን የምጨርሰው? በእውኑ ለአገልግሎት ጊዜ የለኝምን? እነዚህን ጥያቄዎች መመለስ ያስፈልጋል፡፡ ከመለስን

የሚጠቅመንና የሚጎዳንን ከለየን በኋላ ሁሉን በጊዜው እንሥራ፤ “የሚሻለውን ሥራ

እንድትመረምሩና እንድትፈትኑ ክርስቶስ በሚመጣበት ቀን ያለ እንቅፋት ቅዱሳን ትሆኑ   ዘንድ” (ፊል.1፩፥፲) እንዲል፡፡ የሚጠቅመንን ማድረግ ስንጀምር ዕለት ዕለት ያለመታከት

በአግባቡ ካጠናን የሚጠበቅብንን ሁሉ በሰዓቱ ካከናወንን ጊዜ በምንም ሁኔታ ሊያጥረን

አይችልም። በተለይም ደግሞ ተማሪዎች   አንዱ ለእግዚአብሔር የምናቀርበው አሥራታችን

ጊዜ ነው። በዚህ ታምነን ከተገኘን ለነፍሳችን ስንቅ ለሥጋችን ስኬትን እናገኛለን።

በሚገባ ጊዜያችንን ተጠቅመን ትምህርታችንን ከተማርንና እርሱን ካገለገልን በማያልቅ በረከት ይባርከናል፤ በሁለት ወገን የተሳልን ሰይፎች ሆነንም እንወጣለን፡፡

አምላከ ቅዱሳን ለተጠራንበት አገልግሎት ታምነን በሥጋም በነፍስም ተባርከን ስሙን ለመቀደስ መንግሥቱንም ለመውረስ ያብቃን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

በኣታ ለማርያም

ታኅሣሥ ሦስት በዚህች ቀን አምላክን የወለደች እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ሦስት ዓመት ሲሆናት ወደ ቤተ መቅደስ የገባችበት ነው፡፡ እርሷ ለእግዚአብሔር የስእለት ልጅ ነበረችና፡፡

እናቷ ቅድስት ሐና ልጅ የሌላት ስለሆነች በቤተ እግዚአብሔር ውስጥ ከሴቶች ተለይታ ርቃ ትኖር ነበር፡፡ ሽማግሌ ከሆነ ከኢያቄም ከባሏ ጋርም እጅግ የምታዝን ሆነች፡፡ እግዚአብሔርም ሐዘናቸውን ሰማ፤ ቅድስት ሐናም እንዲህ ብላ ለእግዚአብሔር ተሳለች፡፡ “የሰጠኸኝን ፍሬ ለእግዚአብሔር አገልጋይ አደርገዋለሁ፡፡”

ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምንም በወለደቻት ጊዜ ሦስት ዓመት በቤቷ ውስጥ አሳደገቻት፡፡ ከዚህም በኋላ ከደናግል ትኖር ዘንድ ወደ ቤተ መቅደስ ወሰደቻት፡፡ ካህኑ ዘካርያስም ስለ ምግቧ በመጨነቁ ሕዝቡን ሰብስቦ ሳለ መልአኩ ፋኑኤል ኅብስት ሰማያዊ ጽዋዕ ይዞ ከሰማይ ወረደ፤ ዘካርያስ ለእርሱ የመጣ ሀብት መስሎት ታጥቆ እጅ ነሥቶ ቢቆም ወደ ላይ ራቀበት፡፡ ከስምዖን ጀምሮ በዚያ የተሰበሰቡት ሰዎችም በተራ ቢሞክሩ በተመሳሳይ ወደ ላይ ራቀባቸው፡፡ ምን አልባት ለእንግዶች የመጣ ሀብት እንደሆነ ብለው ሐና እና ኢያቄም እንዲቀርቡ አደረጓቸው፤ ለእነርሱም ራቀባቸው፤ ዘካርያስም ሐናን እግዚአብሔር የሚያደርገውን የሚያውቅ የለምና ልጅቷን ትተሸ ወደዚህ ነይ ባላት ጊዜ ቅድስት ድንግል ማርያም ድክ ድክ እያለች እናቷን ስትከተል መልአኩ ፋኑኤል ወደ እርሷ ቀርቦ አንድ ክንፉን አንጥፎ አንድ ክንፉን ጋርዶ መግቧት ዐረገ፤ ሊቀ ካህናቱም ሕዝቡም የምግቧ ነገር ከተያዘልን በቤት እግዚአብሔር ትኑር ብለው አስገቧት፤ ይህም ታኅሣሥ ፫ ቀን ነበር፡፡

በቤተ መቅደስም ምግቧን ከመላእክት እየተቀበለች አሥራ ሁለት ዓመት ኖረች፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ ወደ ዓለም መጥቶ ከእርሷ ሥጋን እስከነሣ ድረስ፡፡

ከሴቶች ሁሉ የተመረጠች ይህቺ ናት፤ በቤተ መቅደስም በመኖር አሥራ ሁለት ዓመት ሲፈጸምላት እርሷ ለእግዚአብሔር የተሰጠች የስእለት ልጅ ናትና ለሚጠብቃት ይሰጧት ዘንድ ካህናት እርስ በእርሳቸው ተማከሩ፡፡ በሴቶች ላይ የሚደርስ በእርሷ ላይም ይደርስባታል ብለው ስለፈሩ በቤተ መቅደስ ውስጥ ይተዋት ዘንድ ለእነርሱ ትክክል መስሎ አልታያቸውም፡፡ ስለዚህም ሊጠብቃት ለሚገባው በእርሷ ላይ እጮ ለያኖሩ ወደዱ፡፡

ከዚህም አስቀድሞ ሊቀ ካህናት ዘካርያስ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን “ልጄ ማርያም ሆይ አንቺ እንዳደግሽና ለአካለ መጠን እንደደረስሽ ዕወቂ፤ ልትታጨ ትወጃለሽን? እግዚአብሔርን የሚፈራ መልካም የሆነ የተባረከ ጎልማሳ እንፈልግልሽን? ወይም በሕይወትሽ ዘመን ሁሉ በቤተ መቅደስ ተቀምጠሽ እግዚአብሔርን ልታገለግዪው የምትሺ ከሆነ በሴቶች ላይ የሚደርሰው በሚደርስብሽ ወራት ወደ ቤተ መቅደስ ደጅ ከመግባት ትጠበቂ ዘንድ በኦሪቱ የተፈጸመውን የርግማን ሥርዓት በአንቺ ላይ እንሠራለን” አላት፡፡

ቅድስት ድንግል እመቤታችን ማርያምም “እነሆ እኔ የእግዚአብሔር አገልጋዩ በፊታችሁ ነኝ፤ አባትና እናት የሉኝም፤ ስሙ ቡሩክ ምስጉን ከሆነ ከእግዚአብሔር በታች ከእናትና አባት ፈንታ እናንት ናችሁና የእግዚአብሔር ትእዛዝ እንደምታውቁ አድርጉ” ብላ መለሰች፡፡

ካህናቱና ማኅበሩም ሁሉ ዘካርያስን ወደ ቤተ መቅደስ ገብተህ ስለዚህች ብላቴና ማርያም ወደ እግዚአብሔር ጸልይ አሉት፡፡ ዘካርያስም ገብቶ ሲጸልይ በዚያን ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ ተገለጠለትና እንዲህ አለው፡- “ዘካርያስ ሆይ ወጥተህ ከዳዊት ወገን ሚስቶቻቸው የሞቱባቸውን ሁሉ ወንዶች ሰብስብ፤ የእያንዳንዱንም በትር ከስሙ ጋር ውሰድ፡፡ ወደ ቤተ መቅደስም በምሽት ገብተህ ወደ እግዚአብሔር ጸልይበት፡፡ በነጋ ጊዜም በትሮቻቸውን አውጣ፡፡ እግዚአብሔርም በበትሩ ላይ ምልክት ለገለጠልህ ለዚያ ሰው ማርያምን ተቀብሎ ሊጠብቃት ይገባዋል፡፡”

ካህኑ ዘካርያስም ወጥቶ አንድነት ለተሰበሰቡት ሕዝብ የእግዚአብሔር መልአክ የነገረውን ነገራቸው፡፡ በዚያንም ጊዜ “ከዳዊት ወገን ጎልማሳም ቢሆን ሽማግሌም ቢሆን ሚስቱ የሞተችበት ሁሉ በኢየሩሳሌም ወደ አለ ቤተ መቅደስ ይሂድ” እያሉ ዐዋጅን ዙረው የሚናገሩ በእስራኤል አገር ሁሉ ላከ፡፡

ከዳዊት ወገን የሆነ ጠራቢው ዮሴፍም በሰማ ጊዜ በትሩን ይዞ ከናዝሬት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፡፡ ካህኑ ዘካርያስም የሁሉንም በትሮች ተቀብሎ ስማቸውን በላያቸው ጻፈ፡፡ ቁጥራቸውም አንድ ሺህ ዘጠኝ መቶ ሰማንያ አምስት በትሮችን ወደ ቤተ መቅደስ አስገብቶ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፡፡ እንዲሁም ሰዎች ሁሉ ከቤተ መቅደስ ውጪ ቆመው ይጸልዩ ነበር፡፡ ዘካርያስም ጸሎቱን በፈጸመ ጊዜ በማግስቱ  ለእያንዳንዱ በትራቸውን አውጥቶ ሰጠ፡፡ ጠራቢው ዮሴፍም በትሩን ሊቀበል በቀረበ ጊዜ የዮሴፍ በትር አብባና አፍርታ ተገኘች፡፡ ከበትሩም ጫፍ ላይ ኦ ዮሴፍ ወልደ ዳዊት ዕቀባ ለማርያም ፍኅርትከ፤ ዮሴፍ ሆይ እጮኛህ ማርያምን ጠብቃት” የሚል ጽሑፍ አገኙ፤ ርግብም እየበረረች መጥታ በአረጋዊው ዮሴፍ ራስ ላይ አርፋለች፤ ካህናቱና ሕዝቡም ሁሉ አይተው እጅግ አደነቁ፤ ምስጉን የሆነ እግዚአብሔርምን አመሰገኑት፡፡

ዘካርያስም ዮሴፍን “ዮሴፍ ሆይ ከእግዚአብሔር የታዘዘ መልአክ እንደተናገረ ድንግል ማርያምን ወደ ቤትህ ወስደህ ጠብቃት” አለው፡፡ የሴፍም ቅድስት ድንግል ማርያምን ከካህናት እጅ ተቀበላት፣ በእርሱም ዘንድ ኖረች፡፡ ከዚህም በኋላ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ገብርኤል ስለ እግዚአብሔር ልጅ ከእርሷ ሰው ሁኖ ስለመወለዱ በዮሴፍ ቤት አበሠራት፡፡

ከእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ቃል ኪዳንና በረከት ያሳትፈን፡፡ አሜን፡፡

ምንጭ፡- ስንክሳር ታኅሣሥ ፫ ቀን

ወጣትነት እና እጮኝነት

በዲ/ን ኢያሱ መስፍን

 ክፍል ሦስት

የእጮኝነት ጊዜ

ተገቢውን ዝግጅት እና ጥንቃቄ አድርጎ እጮኛውን የመረጠ ሰው እስከሚያገባበት ቀን ድረስ እጮኛ መሆኑ የሚሰጠው ብዙ የተለየ መብት አይኖርም። የትዳር ተስፋ ያላቸው ከመሆኑ ባሻገር ከልብ ጓደኛና፣ የተለየ አካላዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው ለእጮኛሞች አይፈቀድም። ከጋብቻ በፊት የሚደረግ ሩካቤ ዝሙት ነው። ሩካቤ ሳይፈጸም ጾታዊ ደስታን ለማግኘት የሚፈጸሙ እንደ መሳሳም፣ መተቃቀፍ፣ መነካካት ያሉ ድርጊቶች መጽሐፍ ቅዱስ መዳራት ብሎ የሚጠራቸውና ያልተፈቀዱ የኃጢአት ሥራዎች ናቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ይዞ መማማል፣ በንስሓ አባቶች ፊት ቃል መገባባት፣ ያለ ቤተ ክርስቲያን ዕውቅና አብሮ ሄዶ መቁረብ፣ ያለ ቤተ ክርስቲያን ዕውቅና ቀለበት መተሳሰር እና የመሳሰሉት ድርጊቶች እጮኛሞች አካላዊ ግንኙነት እንዲኖራቸው መብት የሚሰጡ አይደሉም። መሓላ በራሱ ኃጢአት ከመሆኑም በተጨማሪ (ማቴ 5፡34) ጋብቻን ሊተካ የሚችል አይደለም። አንዳንድ ንስሓ አባቶች ልጆቻቸው አንዳቸው ሌላኛውን እንዳይበድሉ በማሰብ እርሳቸው ባሉበት ቃል እንዲገባቡ የሚያደርጉ ሲሆን ይህ የማይበረታታ እና ብዙ ችግር ይዞ ሊመጣ የሚችል ድርጊት ነው። አንደኛ ይህንን ቃል እንደ ጋብቻ ቆጥረው ወደ ሩካቤ የሚገቡ ጥንዶች ይኖራሉ፡፡

እንዲሁም እጮኝነት የትውውቅ ጊዜ እንደመሆኑ የእጮኞቻቸውን ክፉ አልያም ሊሻሻል የማይችል እና ከነርሱ ፈቃድ ጋር የማይሄድ ነገር ያዩ ሰዎች ሐሳባቸውን እንዳይቀይሩና ተገቢውን ጥንቃቄ እንዳያደርጉ የገቡት ቃል የሚያስጨንቅ እስራት ይሆንባቸዋል። ይህን እና ይህን የመሰለውን ፈተና ይዞ ስለሚመጣ ቤተ ክርስቲያን በሠርጋችን ዕለት ቃል እስክታስገባን ድረስ እንደዚህ ዓይነት ቃል ኪዳኖች ውስጥ ላለመግባት መጠንቀቅ ያስፈልጋል። በንስሓ አባቶች ግፊት የምንገባ ከሆነ ያ ቃል ኪዳን አጋራችንን ላለመበደል እና ክፉ ላለማድረግ የገባነው እንጂ የጋብቻ እንዳልሆነ ማወቅ ያስፈልጋል። ከትዳር በፊት ሩካቤን እና አብሮ መኖርን የሚያበረታቱ ንስሓ አባቶችንም እንቢ ማለት ነውር አይደለም። ቤተ ክርስቲያን በሰው እና በእግዚአብሔር ፊት ዐውጃ፣ ተገቢውን ጸሎት አድርጋ በጋራ እስካላቆረበችን ድረስ ተስማምቶ መቁረብ፣ በአንድ ቀን መቁረብ እንጂ አብሮ መቁረብ ሊባል አይችልም። የዚያን ቀን ከእኛ ጋር ተሰልፈው ከቆረቡት ሰዎች የተለየ አንዳንች ኅብረት አይኖረንም ስለዚህ ይህም ጋብቻን የሚተካ ድርጊት አይደለም።  ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በሰርጉ ቀን በቅብዓ ሜሮን አክብራ ከምታደርገው ቀለበት ውጪ  ሌላ የቀለበት ሥርዓት የላትም፡፡ ስለዚህ በግል አልያም ቤተሰብ ባለበት የሚደረግ ቀለበት የመደራረግ ሥርዓት መንፈሳዊውን ጋብቻ የሚተካ ስላልሆነ የተለየ መብት አይሰጥም።

ስለዚህ ኦርቶዶክሳውያን ወጣቶች በዝሙት ፈተና ወድቀው እግዚአብሔርን እንዳያሳዝኑ ለዚህ ፈተና ከሚዳርጉ ሁኔታዎች ራሳቸውን አርቀው ከዝሙት በመሸሸ (1ቆሮ 6፣18) አካላቸውን እና ሐሳባቸውን በመቀደስ፣ በጋራ ቃለ እግዚአብሔርን በመማር፣ ምክረ ካህን በመቀበል፣ የንስሓ እና የቅዱስ ቁርባን ሕይወትን በመለማመድ የእጮኝነት ጊዜያቸውን ሊያሳልፉ ይገባል።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ወጣትነት እና እጮኝነት

በዲ/ን ኢያሱ መስፍን

 ክፍል ሁለት

እጮኝነት ከማን ጋር?

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ጥያቄ የምትሰጠውን መልስ አለመረዳት በሥጋም በነፍስም ብዙ ዋጋ የሚያስከፍል ስሕተት ውስጥ ሊያስገባ ይችላል። የትዳር አጋር አልያም እጮኛ ለመምረጥ የሃይማኖት አንድነት፣ ዝምድና፣ ዕድሜ፣ ወዘተ ያሉት  ቅድሚያ የምንሰጣቸው መሥፈርቶች በመሆናቸው ትልቅ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ያስቀደምናቸው መሥፈርቶች ጊዜያዊ እና ሥጋዊ ብቻ ከሆኑ ግን የጋብቻን መንፈሳዊ ዓላማ ለማሳካት እንቅፋት ከመሆናቸውም ባሻገር እስከ ፍጽሜ የሚጸና ጥምረት ለመፍጠርም አዳጋች ይሆናሉ። ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ልጆቿ ቅድሚያ እንዲሰጧቸው አጥብቃ ከምታዝዛቸው መሥፈርቶች መካከል ሃይማኖት እና መንፈሳዊ ሕይወት የመጀመሪያዎቹ ናቸው።

በብሉይ ኪዳንም ሆነ በሐዲስ ኪዳን በሃይማኖት ከማይመስሉን ሰዎች ጋር በትዳር መጣመር የተነቀፈ ምግባር ነው፡፡ አብርሃም ለልጁ ይስሐቅ ሚስትን ፍለጋ ሎሌውን ሲልክ ከአሕዛብ እና ከከነዓናውያን እንዳያጋባው አስምሎ እግዚአብሔርን ከሚያውቁ ከዘመዶቹ አገር ሚስት እንዲያመጣለት የላከው በዚሁ ምክንያት ነው። (ዘፍ 24) እንዲህ ዓይነት ታሪኮችን በመጽሐፍ ቅዱስ ማግኘት የተለመደ ነው። በሐዲስ ኪዳን ያለን አማኞችም ከማይመስሉን ሰዎች ጋር የሚኖረንን ግንኙነት በተመለከተ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል። “ከማያምኑ ጋር በማይሆን አካሔድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዐመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለውና?” (2ቆሮ6፡14)። እስከ ሕይወት ፍጻሜ ከሚቀጥል በመንፈስ ብቻ ሳይሆን በአካል አንድ ከሚያደርግ ከጋብቻ በላይ ልንጠነቀቅለት የሚገባ አካሔድ ወይም ጉዞ ምን አለ?

ብዙዎች ለዚህ ስሑት ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃ አድርገው የሚያቀርቡት አንድ ጥቅስ አለ፡፡ ይህም ቅዱስ ጳውሎስ “ሌሎችንም እኔ እላለሁ ጌታ አይደለም፣ ከወንድሞች ወገን ያላመነች ሚስት ያለችው ቢኖር እርስዋም ከእርሱ ጋር ልትቀመጥ ብትስማማ አይተዋት…” የሚለው ነው፡፡ (1ቆሮ. ፯፥፲፪) የገዛ ፈቃዱን ለማስፈጸም ሳይሆን የእግዚአብሔርን ቃል በእውነት ለመረዳት ለሚያስብ ሰው ይህ ኃይለ ቃል ካላመኑ ሰዎች ጋር ለመጋባት መብት የሚሰጥ አይደለም። ቅዱስ ጳውሎስ “የማታምን ሴት ለማግባት የፈለገ ሰው ቢኖር” ብሎ አላስተማረም፤ ይልቁንም  ክርስትና ባልተስፋፋበት በዚያ ዘመን ተጋብተው ከሚኖሩ መካከል ባል ወይ ሚስት በወንጌሉ ቢያምኑ የትዳር አጋሬ አላመነም ብለው የገነቡትን ቤት እንዳያፈርሱ ልጆች እንዳይበተኑ እና ክርስትና የጸብ እና የመለያየት ምክንያት እንዳይሆን የተሰጠ ትእዛዝ ነው። መልእክቱ አግብተው የሚኖሩትን እንጂ ገና ያላገቡትን አይመለከትም።

ሐዋርያው ዝቅ ብሎ ይህ ያላመነ አጋር ለማመን አልያም ከክርስቲያን አጋሩ ጋር አብሮ ለመኖር ፈቃደኛ ባይሆን መተው ወይም መፍታት እንደሚቻል በመናገር ጌታችን ከዝሙት ውጭ አትፋቱ ብሎ ካስቀመጠው ሥርዓት በተጨማሪ የሃይማኖት ልዩነት ሌላ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል ገልጿል። እጮኛ የሚይዝ ኦርቶዶክሳዊ ወጣት እየመረጠ ያለው የትዳር አጋሩን በመሆኑ እና ከጋብቻ ውጪም እጮኛ የሚያዝበት ሌላ አንዳች ዓላማ ስለማይኖረው እስካልተጋባን ምን ችግር አለው ሊል አይችልም።

ከማያምኑ ጋር ብንጋባ ችግሩ ምንድን ነው?

ቅዱሳት መጻሕፍት እንዳዘዙን ቢቻለንስ ከሰው ሁሉ ጋር በሰላም ልንኖር ይገባናል (ሮሜ. ፲፪፥፲፰)። ይህ ማለት ግን ጥላቻን እና አለመግባባትን ማስወገድ መቻል ማለት እንጂ ትዳርን በሚያህል የተቀደሰ ትስስር ወስጥ መግባት ማለት አይደለም። የተቀደሰውን ለውሾች እንዳንሰጥ ጌታችን አስጠንቅቆናል (ማቴ 7፡6)። በክርስቶስ ኢየሱስ ደም የከበረ ከውኃ እና ከመንፈስ ተወልዶ የሥላሴን ልጅነት ያገኘ እና የእግዚአብሔር መቅደስ ተብሎ የተጠራ ሰውነታችን የተቀደሰ አይደለምን?  ይህንን ሳናስተውል ቀርተን በእምነት የማይመስለን እጮኛ ብንይዝ ከሚገጥሙን እንከኖች መካከል የተወሰኑትን እናንሣ።

. የትዳርን ዓላማ ማሳካት አንችልም

ክርስቲያኖች ወደ ምንኩስናም ሆነ ወደ ጋብቻ የሚገቡበት ዓላማ አንድ ዓይነት ነው። እርሱም ቅድስና! የድንግልናን ሕይወት የመረጠ ሰው ራስን መግዛትን ገንዘብ አድርጎ ፍትወታቱን ለፈቃደ ነፍሱ አስገዝቶ ለመኖር እንደሚችል አምኖና ወስኖ ነው። የዚህ ጉዞ ዓላማውም ኃጢአትን አሸንፎ በምድር መላእክትን መስሎ መኖር ነው። በሌላ በኩል ራስን መግዛትን እና ድንግልናን መጠበቅን ገንዘብ ማድረግ ያልቻለ ሰው ስለ ዝሙት ጠንቅ እንዲያገባ ተፈቅዶለታል (1ቆሮ 7፡2)። የዚህም ሰው ጉዞ በዝሙት ተፈትኖ ሳይወድቅ በትዳር ንጽሕናውን ጠብቆ የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ ነው። ስለዚህም የትዳር አንዱ ዓላማ መረዳዳት ነው። መረዳዳት ማለትም ብዙዎች እንደሚያስቡት በሥራ እና በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በዋናነት በመንፈሳዊ ሕይወት ነው። ጠቢቡ ሰሎሞን “አንድ ብቻ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል ቢወድቁ አንዱ ሁለተኛውን ያነሣዋልና” (መክ 4፡9) እንዳለ አንዱ ወድቆ ከእግዚአብሔር መንግሥት እንዳይርቅ ሌላኛው አጋዥ ሊሆነው፣ ቢዝል ሊያበረታው፣ ተስፋ ቢቆርጥ ሊያጽናናው ይችላልና ተረዳድተው እና ተደጋግፈው የእግዚአብሔርን መንግሥት መውረስ የትዳር ዋነኛ ዓላማ ነው። ለዚህም ነው ምዕራባውያን ሊቃውንት “the goal of marriage is not happiness; it is holiness” “የጋብቻ ግቡ ደስታ፣ ተድላ አይደለም ቅድስና ነው” የሚሉት።

የማያምን የትዳር አጋር ያለው ሰው ይህንን ዓላማ ሊያሳካ አይቻለውም። ከማያምን ሰው ጋር ተረዳድቶ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት በጋራ መግባት የማይሆን ነገር ነው ምክንያቱም ጌታችን እንዳለ “የማያምን ሰው በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል” (ዮሐ 3፡18)። ከማያምኑ ጋር መኖር ለመንፈሳዊ ዝለት መንስኤ እንጂ መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ ጋብቻችን እንኳ እጅግ መልካም ቢሆን ከተድላ ሥጋ ያለፈ ለነፍሳችን የሚረባ ነገር አይኖረውም። ክርስቲያኖች ደግሞ እንኳን እንዲህ ያለውን ትልቅ ነገር ቀርቶ ጥቃቅኑን ጉዳይ እንኳ የእግዚአብሔርን ፍቅር እያሰብን ለእርሱ እንድናደርገው ታዝዘናል። “መብላትም ቢሆን መጠጣትም ቢሆን ማንኛውንም ነገር ስታደርጉ ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” (1ቆሮ 10፡31) እንዳለ።

. በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ያለው ኦርቶዶክሳዊ ጋብቻ መፈጸም አንችልም

ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን ልጆቿን በእግዚአብሔር እና በሰዎች ፊት በክብር የምትድርበት ሥርዓተ ተክሊል የሚባል የጋብቻ ሥርዓት አላት። ለደናግል በሚደረገው የተክሊል ጋብቻም ሆነ ለመዓስባን (ደግመው ለሚያገቡ አልያም ድንግልናቸውን ላጡ) ሰዎች በምታደርገው የመዓስባን ጋብቻ (የቁርባን ጋብቻ) መሳተፍ የሚችሉት ምሥጢራተ ቤተክርስቲያንን መፈጸም የተፈቀደላቸው፣ ልጅነትን ያገኙ ክርስቲያኖች ብቻ ናቸው። እግዚአብሔር አምላክ የሚቀበለው ጋብቻ እርሱ ምስክር ሆኖ የተጠራበትን ቅዱስ ጳውሎስ “ሁሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” እንዳለ እርሱ የሚከብርበትን ጋብቻ ብቻ ነው።

የሰው ልጅ የእግዚአብሔር መንፈስ አልያም የጠላት ዲያብሎስ መንፈስ ያድርበታል። እስራኤል የያዕቆብ አምላክ፣ የእግዚአብሔር ማደሪያ (ሐዋ.፯፥፲፮) እንደ ተባሉ ሁሉ ባቢሎናውያን ደግሞ የአጋንንት ማደሪያ ተብለው ተጠርተዋል (ራእ. ፲፰፥፪)። እያንዳንዱ ሰው የሚያድርበትን መንፈስ የሚመርጠው ራሱ ነው። እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስን የሚያቀርብ ሥራ እና ምግባር ያለው ሰው የእግዚአብሔር ማደሪያ ይሆናል፡፡ ሐሳቡን እና ድርጊቱን ያልቀደሰ ሰው ደግሞ ለጠላት ማደሪያነት እንደ ተወለወለ ቤት ራሱን ያዘጋጃል (ሉቃ. ፲፩፥፳፭)። በሠርጋችን ቀን የሚኖረን ምግባር በዕለቱ የምንጠራውን የክብር እንግዳ የሚጋብዝ ነው። ወዳጄ ሆይ! በሰርግዎት ቀን የትኛው መንፈስ እንዲገኝ ይሆን የሚፈልጉት? ማንም ጤነኛ አእምሮ ያለው ክርስቲያን ከእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ ውጭ ሌላ መልስ እንደሌለው ግልጥ ነው። እግዚአብሔር በማይከብርበት ብዙ መብላት፣ ብዙ መጠጣት፣ ዘፈን፣ ጭፈራ፣ መዳራት እና የመሳሰሉት ኃጢአቶች ባሉበት ቦታ እግዚአብሔር በረድኤት አይገኝም። ኃጢአት የደስታው ምንጭ የሆነለት ዲያብሎስ ግን ሳይጠራ የሚመጣበት ዓለሙ ነው። እነዚህ ሁሉ ኃጢአቶች ባይኖሩ እንኳ ስለ እግዚአብሔር ክብር እንደ እርሱ ፈቃድ አልተደረገምና እግዚአብሔር አይገኝበትም።

በተቃራኒው ቤተ ክርስቲያን በአምልኮተ እግዚአብሔር በሚደረግ ጋብቻ ላይ ጌታችን እንደ ቃና ዘገሊላ ቤት ይገኝበታል። ዛሬም ሠርጉ በሚደረግበት ቤተ ክርስቲያን በሚፈጸመው ቅዳሴ ላይ የጌታችን እውነተኛ ሥጋው እና ደሙን በቤተ ክርስቲያን  ይቀበላሉ፡፡ በዚህ የቅዳሴ ጸሎት ቅዱሳንም በሠርጋችን ይገኛሉ። ንጉሣቸው ባለበት ሁሉ የማይታጡ ሠራዊተ መላእክት ባሉበት መሞሸር የማይፈልግ ማነው? ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን በመሰለ ጋብቻ እንዳንከብር ከምትከለክልባቸው ምክንያቶች አንዱ ከማያምኑ ጋር የሚደረግ ጋብቻ ነው።

. በልጆች አስተዳደግ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አለው 

ከላይ የዘረዘርናቸው መንፈሳዊ ጉዳዮች አያሳስቡኝም የሚል እንኳ ቢኖር የተለያየ እምነት ያላቸው ሰዎች የሚፈጽሙት ጋብቻ ይዞት የሚመጣው ማኅበራዊ ቀውስ ብዙ ነው። ከእነዚህም ወስጥ የልጆች አስተዳደግ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። ወላጆች ልጆቻቸውን ወደየራሳቸው እምነት ለመሳብ የሚያደርጉት ጥረት የልጆችን አእምሮ በብዙ መልኩ የሚጎዳ ሲሆን ይህንን ጉዳት ለመሸሽ ልጆችን ወደ እምነት ተቋማት አለመውሰድ ደግሞ የባሰ ፈጣሪን የማያውቁ እና ከአምልኮተ እግዚአብሔር የራቁ ሆነው እንዲያድጉ ያደርጋል። ሌላኛው ወላጅ ባይቃወምና ልጆች አማኝ ሆነው ቢያድጉ እንኳ ከወላጆቻቸው አንዱ ለእግዚአብሔር መንግሥት ያልታጨ ለዘላለም ፍርድ የተጋለጠ መሆኑን እያሰቡ እንዲኖሩ ይገደዳሉ።

እነዚህና መሰል ጉዳዮች በእምነት ከማይመስሉን ሰዎች ጋር በዚህ መልኩ መጠመድ እንደማይገባን የሚያሳስቡ ናቸው። ከዚህም ባሻገር በአንድ ሃይማኖት ጥላ ሥር መጠለል ብቻውን በትዳር ለመጣመር በቂ ምክንያት አይደለም። ምንም እንኳ በእምነት የሚመስሉንን ሰዎች እንዳናገባ ክልከላ ባይኖርብንም መምህራችን ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለ የተፈቀዱልን ነገሮች ሁሉ የሚጠቅሙን እና የሚያንጹን አይደሉም (፩ቆሮ. ፮፥፲፪ እና ፩ቆሮ. ፲፥፳፫)። ዓላማቸው ከዓላማችን፣ ፈቃዳቸው ከፈቃዳችን መግጠሙን ማስተዋል ያስፈልጋል። በሃይማኖት እንመሳሰላለን ካልን በኋላ አንዳችን ለፈቃደ እግዚአብሔር መገዛትን ስንሻ፣ ሌላኛው ይህ የማያሳስበው ከሆነ ግንኙነቱ ዘላቂነት የሌለው ቢዘልቅም አንዱን አካል አልያም ሁለቱንም የሚጎዳ መሆኑ አይቀርም። ስለሆነምወደ ትዳር ከመግባት በፊት ከሃይማኖት ባሻገር መንፈሳዊ ሕይወታችን ተቀራራቢ ደረጃ ላይ መሆኑን እና እርስ በርስ መደጋገፍ መቻላችንን ማወቅ ይገባል። መደጋገፍ አልን እንጂ መደገፍ ብቻ አላልንም። እለውጠዋለሁ፣ አሻሽላታለሁ ተብሎ ወደ ጾታዊ ግንኙነት መግባት ትዕቢትንም ጭምር የሚያሳይ ነው።

መተው የምንፈልገውን ኃጢአት ለመተው፣ መልመድ የምንፈልገውን በጎ ምግባር ለመልመድ ራሳችንን ማሻሻል እና መለወጥ ያልቻልን ሰዎች ሌላ ሰው እለውጣለሁ ብሎ ማሰብ ከትዕቢት ውጭ ምን ሊሆን ይችላል? ስለዚህ ከእኛ ጋር ተቀራራቢ፣ ከተቻለም የተሻለ መንፈሳዊ ሕይወት ያለውን ሰው መምረጥ ያስፈልጋል። ብዙዎች ሰዎችን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ በማግኘታቸው ብቻ መንፈሳዊ ሰዎች እንደሆኑ አስበው ሳይጠነቀቁ ወደዚህ ሕይወት ይገባሉ ከዚያም ነገሮች እንዳሰቡት ባልሆኑላቸው ጊዜ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉት ሰዎች ሁሉ እንደዚያ እንደሆኑ በማሰብ መንፈሳዊ ሕይወትን እና ቤተ ክርስቲያንን ይሸሻሉ። ሐኪም ቤት ውስጥ የተገኘ ታማሚ ሁሉ ተሽሎት እንደማይወጣ እንዲሁም ቤተክርስቲያን ወስጥ ያገኘናቸው ሰዎች ሁሉ ከድካማቸው የተፈወሱ አይደሉምና መጠንቀቅ ያስፈልጋል።

ይቆየን