የሕማማት ሣምንት ሐሙስ ስያሜዎች

በሰሙነ ሕማማት ውስጥ ማለትም ከሰኞ አስከ ቅዳሜ 6 ቀናት ያሉ ሲሆን በተለይ ዕለተ ሐሙስ በተለያዩ ስያሜዎች ትታወቃለች፡፡ የተወሰኑትንም ለማየት ያህል ፡-

ጸሎተ ሐሙስ፡- የዓለም መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ሥጋን የተዋሐደ አምላክ መሆኑን ለመግለጥና ለአርአያነት ጠላቶቹ መጥተው አስኪይዙት ድረስ ሲጸልይ ያደረበት ነውና ጸሎተ ሐሙስ ተባለ፡፡ማቴ 26 ፡1

ሕፅበተ እግር፡- ጌታችን በዚህ እለት የደቀ መዛሙርቱን እግር በፍጹም ትሕትና ዝቅ ብሎ አጥቧል፡፡ ይህም የሚያሳየው የዓለምን ሁሉ ኃጢአት ለማጠብ የመጣ መሆኑን ነው፡፡ ይህንኑ ለመዘከርም ዕለቱ ‹‹ሕፅበተ እግር›› ይባላል፡፡ ይህን ለማስታወስ ዛሬም ከቅዱስ ፓተርያርኩ ጀምሮ ካህናት ሊቃነ ካህናት የደብር አስተዳዳሪዎች፤ በዕለቱ የተገኙትን ምእመናንን እግራቸውን በወይንና በወይራ ቅጠል ያጥባሉ፡፡

የምስጢር ቀን፡- ከሰባቱ ምሥጢራት አንዱ በዚህ ዕለት ተመሥርቷል፡፡ ይኸውም ‹‹ሲበሉም ኢየሱስ እንጀራን አንሥቶ ባረከ ቈርሶም ለደቀ መዛሙርቱ ሰጠና ይህ ስለ እናንተ በመስቀል ላይ የሚቆረሰው ሥጋዬ ነው፤ እንካችሁ፥ ብሉ፡፡ ጽዋውንም አንስቶ አመሰገነ፣ ይህ ስለ እናንተ ነገ በመስቀል የሚፈርስ የሐዲስ ኪዳን ደሜ ነው፥ ከእርሱም ጠጡ›› (ማቴ.26፡26) በማለት እኛ ከእርሱ ጋር፣ እርሱም ከእኛ ጋር አንድ የምንሆንበትን ምሥጥር ከጠላት ዲያብሎስ ሰውሮ ለደቀ መዛሙርቱ የገለጠበት ቀን በመሆኑ የተሰጠ ሥያሜ ነው፡፡ ይህንኑ አብነት በማድረግም በዚህ ዕለት ክርስቲያን የሆነ ሁሉ በንስሐ ታጥቦ ቅዱስ ሥጋውንና ክቡር ደሙን ለመቀበል ይዘጋጃል፡፡

የሐዲስ ኪዳን ሐሙስ፡- ዕለቱ በዚህ ስያሜ የተጠራበት ምክንያት በዘመነ ኦሪት በእንስሳት ደም የሚቀርበው መሥዋዕት ማብቃቱን ገልጦ ለድኅነተ ዓለም ራሱን የተወደደ መሥዋዕት አድርጎ ያቀረበበት ዕለት በመሆኑ ነው፡፡ ‹‹ይህ ጽዋ ስለ እናንተ በሚፈሰው በደሜ የሚሆን ሐዲስ ኪዳን ነው፤ ከእርሱ ጠጡ›› በማለቱ ይታወቃል፡፡ ሉቃ.22፡20

የነጻነት ሐሙስ፡- የሰው ልጅ ለኃጢአትና ለዲያብሎስ ባሪያ ሆኖ መኖር ማብቃቱ፣ ያጣውን ክብር መልሶ ማግኘቱ የተረጋገጠበት ቀን ስለሆነ ነው፡፡ ጌታችን ስለ ሰው ልጅ ነጻነት ሲናገር ‹‹ከእንግዲህ ወዲህ ባሮች አልላችሁም ባርያ ጌታው የሚደርገውን አያውቅምና፡፡ ወዳጆች ግን ብያችኋለሁ›› (ዮሐ.15፡15) በማለት ከባርነት ወጥተን ልጆች የተባልንበት፣ ባርነት ርቆ ከእግዚአብሔር ጋር የተወዳጀንበት፣ ታርቀን አንድ የሆንበት፣  ፍቅር አንድነት ልጅነት የታወጀበት፣ ወደ ቀደመው ክብራችን የተመለሰንበት ዕለት በመሆኑ የነጻነት ቀን ይባላል፡፡

በአጠቃላይ ከዕለተ ሐሙስ በትሕትና ራስን ዝቅ ዝቅ በማድረግ ከትዕቢትም መጠበቅን፣ ፍቅርን፣ አንድነትን፣ በጎነትን፣ ለሰዎች ድኅነት መልካም ማድረግን፣ ትዕግስትን፣ በአገልግሎት ላይም በጾም በጸሎት እና በንሰሐ ሕይወትን መምራት፣ መተሳሰብንና ለሎችም መኖር እንዳለብን እንማራለን፡፡ ቀኑን አስበን ከቀኑም በረከትን እንድናገኝበት በዓሉንም ለሕይወት፣ ለድኅነት እና ለበረከት እንዲያደርግልን የእርሱ መልካም ፈቃድ ይሁንልን አሜን ፡፡

ምንጭ ፡- ስምዐ ተዋሕዶ ልዩ እትም ዘሰሙነ ሕማማት ከሚያዝያ 1-15 ቀን 2004 ዓ/ም

ሰሚ ያጣው የሕፃናት ጩኸት

በዲ/ን ታደለ ሲሳይ

ቀኑ ወረፋውን ለጨለማው ለመልቀቅ በማመናታት ላይ ያለ ይመስላል፡፡ የአዲስ አበባ ምድርም የፀሐይን ብርሃን በሰው ሠራሽ ብርሃን ለመተካት ፓውዛዎቿን ስልም ቁልጭ እያደረገች ነው፡፡ ሁሉም በየፊናው እየተሯሯጠ ነው፡፡ ጠዋት ሥራ የገባው ወደ ቤቱ ለመመለስ፣ ማታ የሚሠራው ደግሞ በአዲስ መንፈስ ለመሥራት ጥድፊያ ላይ ነው፡፡

ከዐዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ተነሥቼ በድካም የዛለ ሰውነቴን ለማሳረፍ ወደ ቤቴ እያመራሁ ነው፡፡ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ፊት ለፊት ዋናውን አስፓልት አቋርጬ ቀጥታ በድባብ መናፈሻ አድርጌ የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ግቢን ትቼ ወደ ታች ስታጠፍ በርቀት የሚስረቀረቅ የሕፃናት ኅብረ ድምፅ ሰማሁ፡፡ ምን እንደሚሉ አይሰማም፤ የድምፃቸው ጣዕመ ዜማ ግን ልብን ሰርስሮ ይገባል፡፡

Read more

በፍቅር መኖር

…በመ/ር ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ…

በክርስቲያናዊ ሕይወት ለመኖር የወሰነ ሰው ሰውን ሁሉ ሊወድ ይገባል፡፡ ፍቅር ሲባል ፍትወታዊ የጾታ ፍቅር ሳይሆን ሁሉንም ሰው ሳይለያዩ መውደድ ነው፡፡ ለዚህ ነው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሕግጋት ሁሉ ፍቅርን ያስበለጠው፡፡ (ዮሐ. 15፥12) ቅዱስ ጳውሎስ ይህንን ሲጠቅስ በሰዎችና በመላእክት ልሳን ብናገር ፍቅር ግን ከሌለኝ እንደሚጮኽ  ናስ ወይም እንደሚንሿሿ ጸናጽል ሆኛለሁ፤ ትንቢትም ቢኖረኝ ምሥጢርንም ሁሉና ዕውቀትን  ሁሉ ባውቅ ተራሮችንም እስካፈርስ ድረስ እምነት ቢኖረኝ ፍቅር ግን ከሌለኝ ከንቱ ነኝ፤ ድሆችን ልመግብ ያለኝን ሁሉ ባካፍል ሥጋዬንም ለእሳት መቃጠል፤ አሳልፌ ብሰጥ ፍቅር ግን ከሌለኝ ምንም አይጠቅመኝም፡፡ ፍቅር ይታገሣል፤ ቸርነትም ያደርጋል፤ ፍቅር አይቀናም፤ ፍቅር አይመካም፤ አይታበይም፤ የማይገባውን አያደርግም…(1ኛ ቆሮ. 13፥1) በማለት አስረድቷል፡፡

Read more