ዓለማየሁ ገብሩ
ትውፊት ማለት አወፈየ ከሚለው የግእዝ ግሥ የመጣ ሲሆን ውርስ፣ ቅብብል ተብሎ ይተረጎማል፡፡ ትውፊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ትምህርቶቿን ጠንቅቃ ከያዘችበት እና ልጆቿንም ከምትመራባቸው ሦስቱ የመሠረተ እምነት ምንጮች ውስጥ አንደኛው ነው፡፡ የቤተ ክርስቲያን መሠረተ እምነት ተብለው የሚጠቀሱት፡- ዶግማ፣ ቀኖና እና ትውፊት ሲሆኑ እነዚህ መሠረቶች ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ሳትለወጥና ሳትበረዝ እንደ ደመቀች ከትውልድ ወደ ትውልድ እንድትተላለፍ አድርገዋታል፡፡
ለቤት መቆም ብቻ ሳይሆን ቤቱ ዕድሜ እንዲኖረውም የሚያደርገው የመሠረቱ ጥንካሬ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ትውፊት አንድ ሰው ከእርሱ በፊት ከነበረው ማኅበረሰብ የሚቀበለውና የሚወርሰው እምነት፣ ባህል፣ የአኗኗር ዘይቤ፣ …ወዘተ ሲሆን ሒደቱም በዚህ ሳያበቃ እርሱም በተራው ለተተኪው የሚያስተላልፈው ነው፡፡
ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ ስለ ትውፊት እንዲህ በማለት ማብራሪያ ይሰጣሉ፡-“ትውፊት በቃል ወይም በጽሑፍ ወይም በተግባር እንቅስቃሴ ከአንዱ ወደ ሌላው የሚተላለፍ ታሪክ፣ ትምህርት፣ ባህል፣ ወግና ሥርዓት ነው፡፡ ትውፊት በተጨባጭ በትክክል የተፈጸመ እንጂ ተረት አይደለም፡፡ ከሕገ ልቡና ወደ ሕገ ኦሪት፣ ከሕገ ኦሪት ወደ ሕገ ወንጌል፣ በቅብብሎሽ የመጣ የተወረሰና ለተከታዩ ትውልድ የተላለፈ ነው፡፡ ትውፊት ልማደ ሀገርን ሕገ እግዚአብሔርን ባህለ ሃይማኖትን ሁሉ የሚያጠቃልልና እንደ መንፈሳዊ ሕግ ሆኖ ሊያዝ የሚችል ነው፡፡” ይላሉ (ሊቀ ካህናት ክንፈ ገብርኤል አልታዬ፤ ፈለገ ጥበብ መጽሔት ፪ኛ ዓመት ቁጥር ፲፭/፲፱፻፺፪ ዓ.ም. ገጽ ፲፭)
ትውፊት ከትውልድ ወደ ትውልድ በሦስት መንገዶች የሚተላለፍ ሲሆን፤ እነርሱም፡- የሚዳሰስ፣ የማይዳሰስ እና በቃል ይተላለፋሉ፡፡
ሀ. በሚዳሰስ መንገድ የሚተላለፍ ትውፊት፡-
በሚዳሰስ መንገድ የሚተላለፍ ትውፊት በሆነ ዘመን ተሠርተው አገልግሎት የሚሰጡ አብያተ ክርስቲያናት፣ ንዋየተ ቅድሳት እና ቅዱሳት መጻሕፍትን የመሳሰሉት ቅርጻቸውንና ይዘታቸውን ሳይለውጡ ከትውልድ ወደ ትውልድ ተጠብቀው የሚተላለፉበት የትውፊት መተላለፊያ መንገድ ነው፡፡ እነዚህ ንዋያተ ቅዱሳት በክብር እየተጠበቁ ወደ ቀጣይ ትውልድ ይሸጋገራሉ፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን በትውፊት ምክንያት የሚነቅፉና ትውፊት አያስፈልግም መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ የሚሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ በትውፊት ያለንበት ዘመን መድረሱን ይዘነጋሉ፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ መቼ መዘጋጀት ጀመረ? ከሚለው አንስቶ መቼ አሁን ያለበትን ቅርጽ ያዘ እስከሚለው ድረስ ያለውን ብንመረምር ከአንዱ ወደ አንዱ እየተላለፈ በትውፊታዊ መንገድ ቀድሞ የተጻፉትን በመቀበል በየዘመናቱ የሚጻፉትንም ደግሞ በማካተት አሁን ያለበትን መልክ ይዞ እኛ ጋር እንደደረሰ መዘንጋት የለብንም፡፡
ለ. በማይዳሰስ መንገድ የሚተላለፍ ትውፊት፡-
ርእያዊ ትውፊት ሲባል የተለያዩ ባህሎች አከባበር፣ የተለያዩ መንፈሳዊ መዝሙራት ወይም ወረብ አቀራረብ እንዲሁም መንፈሳዊ አለባበስና አመጋገብ የመሳሰሉ በማየት የምንወርሳቸው ወይም የምንቀበላቸው የትውፊት ዓይነቶች ናቸው፡፡ ለዚህ ጥሩ ማሳያ የሚሆነው በሕገ ልቡና ዘመን የአሥራት በኲራት አቀራረብ ሕግ ሆኖ ለሙሴ ከመነገሩ በፊት አበ ብዙኃን አብርሃም፣ ልጁ ይስሐቅና ያዕቆብ ያቀርቡ ነበር፡፡ የመሥዋዕትንም አቀራረብ በማየትና በመስማት ከልጅ ልጅ እየተቀባበሉ ሲገለገሉበት ነበር፡፡
ሊቀ ነቢያት ሙሴ አሥርቱን ትእዛዛት ከመቀበሉ በፊት ቅዱስ ዮሴፍ ዝሙት ኃጢአት እንደሆነና ከዚያም ሲሸሽ የዝሙት ኃጢአት እግዚአብሔርን የሚያሳዝን ኃጢአት መሆኑን ዐውቆ ራሱን ሲጠብቅ እናየዋለን (ዘፍ.፴፱፤፱)፡፡ ሕግ ሳይሰጥ ከየት ዐወቀው ከተባለ ከአባቶቹ በማየትና በመስማት የተማራቸው ነገር ስላለ ነው፡፡ እስራኤላውያን የፋሲካል በዓል አከባበር አሁን ድረስ ጥንታዊ ባህሉን ጠብቀው ያከብራሉ፡፡ በዓል አከባበሩ ተጽፎላቸው ሳይሆን በማየት ብቻ ከአንዱ ትውልድ ወደ አንዱ ትውልድ እየተላለፈ የመጣ ስለሆነ ነው፡፡
በአጠቃላይ ትውፊት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ወጥ ሥርዓት እንዲኖራት የሚረዳ ሲሆን ከዚህ ትውፊታዊ ሥርዓት የሚወጡትን ደግሞ ለይተን እንድናውቅበት ይረዳናል፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለን “ዳሩ ግን ማንም ሊከራከር ቢፈቅድ እኛ ወይም የእግዚአብሔር አብያተ ክርስቲያናት እንዲህ ያለ ልማድ የለንም ” (፩ቆሮ.፲፩፤፲፮) በማለት ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ውጪ ካሉ ተቋማት እንድንጠበቅ እንዲሁም ሥርዓት፣ ወግ፣ ባህል ከሌላቸው አካላት ጋር መለየታችንን በጉልህ የሚያሳየን መሠረተ እምነት ነው ትውፊት፡፡
ሐ. ቃላዊ ትውፊት፡-
ቅዱስ ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች ሲያስተምር “አሁንም ወንድሞቻችን ሆይ ጸንታችሁ ቁሙ፤ በቃላችንም ቢሆን ወይም በመልእክታችን ያስተማርናችሁንና የሠራንላችሁን ሥርዓት ያዙ፡፡” (፪ተሰ.፪፥፲፭) ይላል፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከጻፈልን ፲፬ቱ መልእክት በተጨማሪ በቃል የሰበከውንም እንድንይዝ ይመክረናል፡፡ እንደሚታወቀው የክርስቶስ ቤተሰብ የተባሉት ከዋለበት ውለው፣ ካደረበትም አድረው ከጌታችን እግር ሥር ቁጭ ብለው ከተማሩት ከአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ሁለቱ ቅዱስ ማቴዎስና ቅዱስ ዮሐንስ እንዲሁም ከሰባ ሁለቱ አርድእት ደግሞ ቅዱስ ማርቆስና ቅዱስ ሉቃስ ብቻ ናቸው ወንጌልን የጻፉልን፡፡
የተቀሩት ሐዋርያትና አርድዕት የእግዚአብሔርን ቃል አላስተማሩም? አልሰበኩም? አልጻፉም ማለት ነው? አይደለም፡፡ ይህ የሚያሳየው ከላይ ባነሣነው የቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት መሠረት ባይጽፉም ወንጌል መስበካቸውን አንጠራጠርምና በቃል የሰበኩትንም እንድንይዝ ተነግሮናል፡፡ ለዚህም ነው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳን ሐዋርያት በቃል የሰበኩትን የእነሱ ተከታይ የሆኑና ደቀ መዛሙርቶቻቸው ጽፈው ያስተላለፉትን የምትቀበለው፡፡
ኦርቶዶክሳዊ ቃላዊ ትውፊት ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሐዋርያት ያስተማራቸውን፣ ሐዋርያትም ለተከታዮቻቸው ያስተላለፉትን እየተቀባበሉ እዚህ እኛ ዘመን ላይ ደርሷል፡፡ “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠሁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለሁና” (፩ቆሮ.፲፩፥፳፫) እንዲል ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡፡
ቃላዊ ትውፊት ከጥንት ጀምሮ በቤተ ክርስቲያን በኩል ቃል በቃል ሲነገር የመጣ በቃልም በጽሑፍም ከአበው ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የኖረና የሚኖር ነው፡፡ በቅዱሳት መጻሕፍት ያልተጻፉትን ከአበው ቃል በቃል የተላለፉትን የእምነት፣ የሥርዓት፣ የትምህርትና የታሪክ ውርሶች የሚቀርብበት ነው፡፡
ቅዱሳን ሐዋርያት በቃላዊ ትውፊት አማካይነት በወንጌል ያልተጻፈውን የጌታችን ትምህርት ጌታችን የተናገረው ብለው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሲጽፉ እናያለን፡፡ ለምሳሌ “ከሚቀበል ይልቅ የሚሰጥ ብፀዕ ነው፤ ያለውንም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ቃል ዐስቡ፡፡” (ሐዋ.፳፥፴፭) ይላል፡፡ ወንጌላዊው ቅዱስ ሉቃስ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አለ ያለውን ቃል በአራቱም ወንጌል ውስጥ ተጽፎ አናገኘውም፡፡ ከየት አመጣው ብንል ጌታችን ሲያስተምር የሰማውን እንደጻፈ መረዳት ቀላል ነው፡፡
ጌታችንስ በወንጌል ከተጻፉት ውጪ ሌላ ቃል አላስተማረም ብሎ ማሰብ ሞኝነት አይደለምን? ወንጌላውያኑስ ጌታ የተናገረው ሁሉን ጽፈዋል ብሎ ማመኑ አይከብድምን? ስለዚህ አራቱ ወንጌላውያን ያልጻፉት ወይም ያልመዘገቡት የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርቶች መኖራቸውን መገንዘብ ይገባል፡፡ ለምሳሌ፡- ተረፈ ወንጌል የሚባሉት እንደ ተአምረ ኢየሱስ፣ ድርሳነ ማኅጠዊ ባሉት ተጽፏ፡፡ ለዚህም ነው ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ “ኢየሱስም በዚህ መጽሐፍ ያልተጻፈ ሌላ ብዙ ምልክት በደቀ መዛሙርቱ ፊት አደረገ” (ዮሐ.፳፥፴) ያለው፡፡
በተጨማሪም ቅዱስ ጳውሎስ “የታያቸውም እንዲህ ግሩም ነበር፤ ሙሴም እንኳን እኔ ፈርቻለሁ ደንግጫለሁም” ብሎ ጽፎልን እናገኛለን (ዕብ.፲፪፥፳፩)፡፡ ነገር ግን ሊቀ ነቢያት ሙሴ አለ ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ የጻፈልንን ቃል ሙሴ በየትኛውም መጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ውስጥ ጽፎት አናገኝም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ከየት አመጣው? ካልን በቃል በተላለፈ ትምህርት አግኝቶት ነው፡፡
በተመሳሳይ ቅዱስ ጳውሎስ ሙሴን ስለተቃወሙትና ስለተከራከሩት ሁለቱ ጠንቋዮች ሲናገር የጠንቋዮቹን መጠሪያ ስም “ኢያኔስና ኢያንበሬስም ሙሴን እንደተቃወሙት” በማለት ይጠቅሳል፡፡ (፪ጢሞ.፫፥፰)፡፡ ይህ ታሪክ በተመዘገበበት በኦሪት ዘጸ. ፯፥፲፩ ላይም ሆነ በሌላ የኦሪት መጽሐፍት ላይ የእነዚህ ሁለት ጠንቋዮች ስም የተገለጸበት ቦታ የለም፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ግን ከነስማቸውን ጠቅሶ ይነግረናል፡፡ ከየት አምጥቶት ስማቸውን ጻፈ ብንል በቃላዊ ትውፊት በተላለፈ ትምህርት መሆኑን እንረዳለን፡፡
የሐዋርያትን የቃል ስብከት በተመለከተ የሚናገሩት ቃል የእግዚአብሔርን ቃል እንጂ ከራሳቸው አመንጭተው እንዳልሆነ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲነግረን እንዲህ ይላል፡፡ “ስለዚህም የመልእክትን ቃል እርሱም የእግዚአብሔር ቃል ከእኛ በተቀበላችሁት ጊዜ በእውነት እንዳለ በእናንተ በምታምኑ ደግሞ እንደሚሠራ እንደ እግዚአብሔር ቃል እንጂ እንደ ሰው ቃል አድርጋችሁ ስላልተቀበላችሁት እኛ ደግሞ እግዚአብሔርን ሳናቋርጥ እናመሰግናለን” (፩ተሰ. ፪፤፲፫)፡፡