በመ/ር ታዴዎስ መንግስቴ
የእግዚአብሔር ሰው የመሆን ምሥጢር በሰው አእምሮ አይደለም በመላእክት ኅሊናም ለመረዳት የማይቻል ረቂቅ፣ የማይመረመር ምሥጢር፣ የማይደረስበት ሩቅ፣ ዝም ብለው የሚያደንቁት ግሩም ነው። ሊቁ ቅዱስ ኤፍሬም ድንግል ማርያምን ባመሰገነበት ውዳሴው “ኦ ዝ መንክር ልደተ አምላክ እማርያም እምቅድስት ድንግል አግመረቶ ለቃል ኢቀደሞ ዘርዕ ለልደቱ፤ ልዩ ከሆነች ድንግል ማርያም ይህ የአምላክ መወለድ ምን ይደንቅ፣ ቃልን ወሰነችው ልደቱንም ዘር አልቀደመውም” (ውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ) በማለት በኅሊናው ላይ የተፈጠረውን አግራሞት ይገልጻል።
እንዲህ ያለው ልዩ ምሥጢር የተገለጸለትና የአንጾኪያ ሊቀ ጳጳሳት የነበረው ሊቁ ቅዱስ ሳዊሮስም “ወለዘወለዶ እግዚአብሔር አብ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ መንጸፈ አንስት፤ ወለደቶ ማርያም በሥጋ በምሥጢር ዘኢይትረከብ እንበለ ሩካቤ ተባዕት፤ እግዚአብሔር አብ በማይመረመር ምሥጢር ያለ እናት የወለደውን ማርያም በማይመረመር ምሥጢር ያለ ዘርዐ ብእሲ በሥጋ ወለደችው።” (ሃ.አበ. ዘሳዊሮስ ፹፭፥፴፯) በማለት የነገረ ሥጋዌውን ምሥጢር ከአእምሮ በላይ መሆን ያስረዳል። አምደ ሃይማኖት እየተባለ የሚጠራው ሊቁ ቅዱስ ቄርሎስም “ወልድ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማይመረመር ተዋሕዶ ሰው የሆነ አምላክ ነውና ቀዳማዊ ሲሆን ከዘመናት አስቀድሞ ከአብ የተወለደ ነው፤ ዳግመኛም ከድንግል በሥጋ የተወለደ ነው ተብሎ ስለ እርሱ እንዲህ ይነገራል።” በማለት ያስረዳል። (ሃ.አበ. ፸፫ ክፍል ፲፩ ቁ. ፬)
ለመሆኑ እግዚአብሔር ይህን ድንቅ ምሥጢር ለሰው ልጆች መግለጥና ሰው መሆን ለምን አስፈለገው? ብሎ መጠየቅ ይገባልና ምላሹ ዘርዘር ያለ ማብራሪያ የሚፈልግ ቢሆንም ከብዙ ምክንያቶች አንጻር ጥቂቶቹን እንመልክት፡-
እግዚአብሔር ሰውን ለማዳን ሰው ሆነ፡- በሥነ ፍትረት አባታችን አዳምን ጥንት እግዚአብሔር የእርሱን የባሕርይ አምላክነት፣ ገዢነት፤ ልጅነት ወዘተ በጸጋ አድሎት፣ ፍጥረቱን ሁሉ እንዲገዛ ፈቀደለት። ግን አታድርግ የተባለውን ሲያደርግ የተሰጠውን ጸጋ ሁሉ ተነጠቀ። ይህ የተነጠቀውን ጸጋ ይመለስለት ዘንድ እግዚአብሔር ወልድ ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው ሆነ። የሰው ልጅ ይድን ዘንድ አምላክ ሰው መሆኑን አስመልክቶ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ መጽሐፈ ምሥጢር በተሰኘ መጽሐፉ የሚከተለውን ይነግረናል። “ባለመድኃኒቱ በድውዮች ሴት ልጅ አደረ፣ ከእርሷም ምድራዊት ሥጋን ተዋሐደ ለድውዮችም ፈውስ በሚሆን ገንዘብ ከመለኮቱ ጋር ገንዘብ አደረገው። ባለመድኃኒት ከሰማየ ሰማያት መጥቷልና የፈውስ እንጨትም በዳዊት ቤት ተገኘ። መለኮት ከሥጋ ጋር ሳይዋሐድ ፈውስ እንደማይሆን ባለመድኃኒቱ ዐወቀ። ስለዚህ ራሱን ሰው ለመሆን ሰጠ።” (መጽሐፈ ምሥጢር ፳፥፯) ሁሉን የሚያድን አምላክ ለሰው ልጅ መድኃኒት ያደረገው ራሱ ሰው መሆንን ነበር።
ጎርጎርዮስ ገባሬ ተአምራት “እስመ አሕዛብ አፍቀሩ አርአያ ወአምሳለ እምዕፀው ዘፀረብዎ ፀረብት ወበእንተዝ ኮነ ሥጋ ወልድከ፤ አሕዛብ የለዘበ ድንጋይ የተጠረበ እንጨት እያመለኩ የሚታይ አምላክ እንጂ የማይታይ አምላክ ማምለክ አልፈለጉም በዚህም ልጅህ ሥጋን ተዋሐደ” (ሃይ.አበው ዘጎርጎርዮስ ፲፭፥፮) በማለት አምላክ ሰው የሆነበትን ምክንያት ያስረዳል። ስለዚህ አምላክ ሰው የሆነው የሰው ልጅ የማያየውን፣ በእምነት ብቻ የሚከተለውንና የሚያመልከውን አምላክ ማምለክ ስላልቻለ ግዙፍ አምላክ ለግዙፍ አስተሳሰባችን የሚመች ሆኖ መጣ።
፫. አምላክ ሰው መሆን ለምን አስፈለገው የሚለውን ስንመለከት ዲያብሎስ አዳምና ሔዋንን ሲያስታቸው በእባብ ላይ አድሮ ነው። ዲያብሎስ በእባብ አድሮ አዳምንና ሔዋንን እንዳሳተ እግዚአብሔር ወልድም በሥጋ ተገልጦ ዲያብሎስን ድል ያደርግና አዳምን ነጻ ያወጣ ዘንድ አምላክ ሰው ሆነ፡፡ “ወበከመ ተሀብአ ሰይጣን በጕህሉት ውስተ ሥጋ ከይሲ ከማሁ ኮነ ድኅነትነ በተሠውሮተ ቃለ እግዚአብሔር በዘመድነ፤ ሰይጣን በተንኮሉ በሥጋ ከይሲ እንደ ተሠወረ ድኅነታችንም ቃለ እግዚአብሔር በሥጋችን በማደሩ ተፈጸመልን።” (መቅድመ ወንጌል) የእኛ ድኅነት በዚህ መንገድ ይሆን ዘንድ ፈቅዷልና አምላክ ሰው ሆነ።
በሌላ መንገድ ሰው መሆን ለምን አስፈለገው የሚለውን ቅዱስ ቄርሎስና አረጋዊ መንፈሳዊ የተባበሩበት “በሕፃን አምሳል ተገለጠ አንተን ሕፃን ያደርግህ ዘንድ” የሚለው ነው። ቅዱስ ጎርጎርዮስም “እግዚአብሔርም አለ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር” (ዘፍ. ፩፥፳፮) ያለውን ይጠቅስና “የሰው ልጅ ሁሉ እግዚአብሔርን መስሎ ተፈጥሮ ነበር። ነገር ግን አትብላ የተባለውን ዕፀ በለስ ሲበላ እግዚአብሔርን መምሰሉ ተበላሸ፣ መነሻ ግብራችን ከእኛ ተለይቶን ነበር። ስለዚህ ያ እግዚአብሔርን የመሰለበት ተፈጥሮ ሲበላሽ ራሱ እግዚአብሔር ሰውን መሰለ” በማለት ያብራራል።
እዚህ ላይ ሁለት መመሳሰሎች ይታያሉ። የመጀመሪያው “እግዚአብሔር ሰውን በአርአያውና በአምሳሉ ፈጠረው” እና “ሰው እግዚአብሔርን መሰለ” ሁለተኛው ግን የአምላክ ሰው መሆን ራሱ አምላክ ሰውን ሆኖ መጣ ማለት ነው። ቅዱስ ሳዊሮስ “ቀዳሚሰ ወሀበነ አርአያሁ ክብርተ ወደኃሪሰ ነሥአ ሥጋነ ህሥርተ፤ በመጀመሪያ ክብርት የሆነች አርአያውን ሰጠን፤ በኋላ ግን የእኛን የጎሰቆለ ባሕርያችንን ከኃጢአት ንጹሕ አድርጎ ገንዘቡ አደረገ።” በማለት ያስረዳል። ስለዚህ ለእኛ ሁለተኛ ልደት ይሰጠን ዘንድ እርሱ ሁለተኛ ተወለደ፤ እርሱ ሁለተኛ ባይወለድ እኛም ሁለተኛ አንወለድም ነበር። እርሱ ፈራሽ በሆነ ሥጋ ተወልዶ እኛ ዘለዓለማዊ የሆነ ልደትን እንድንወለድ አደረገ። እንዲሁም እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለው ፍጹም ፍቅር ይታወቅ ዘንድ ሰው ሆነ። ፍቅሩ ድንቅ ይሆን ዘንድ ከሚራብ፣ ከሚጠማ፣ ከሚታመም፣ ከሚሞት ሥጋ ጋር ተዋሐደና ረሀብ፣ ጥም፣ ሕማም፣ ሞት ወዘተ. የማይስማማውን ዲያብሎስን ድል አደረገው።
እግዚአብሔር ለሰው ልጅ ያለውን ፍጹም ፍቅር በቅዱስ ወንጌልም “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘለዓለም ሕይወትን እንዲያገኝ እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ቤዛ አድርጎ እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲህ ወዶታልና” (ዮሐ. ፫፥፲፮) ተብሎ እንደ ተገለጸው እንዲሁ መውደዱን ይገልጽልን ዘንድ ዋጋ ከፈለልን። ስለ ወደደን ተወለደልን፣ ስለ ወደደን ተገረፈልን፣ ስለ ወደደን ተሰቀለልን፣ ዋጋ ከፍሎ መውደድና ዋጋ ሳይከፍሉ መውደድ የተለያየ ስለ ሆነ እጅግ የሚያስደንቅ ዋጋ ከፈለልን። ይህን በተመለከተ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው “ፍቅር ሰሀቦ ለወልድ ኀያል እመንበሩ ወአብጽሖ እስከ ለሞት፤ ኀያል ወልድን ፍቅር ከዙፋኑ ሳበው እስከ ሞትም አደረሰው” (ቅዳሴ ማርያም) በማለት እንደ ገለጸው የጽንዐ ፍቅሩ መገለጫ ይሆን ዘንድ የማይሞት መለኮት ከሚሞት ሥጋ ጋር ተዋሐደ፤ የማይራበው መለኮት በሚራብ ሥጋ ተራበ፣ የማይሞተው መለኮት በሚሞት ሥጋ ሞተ።
ይህም ብቻ አይደለም ሰው የመሆኑ ምክንያት። ቅዱስ ቄርሎስ “ወረደ ከመ ያዕርገነ ለነ ኀበ ሀገሩ አርያማዊ ኀበ ሀሎ አቡሁ፤ የባሕርይ አባቱ ካለበት ሰማያዊ ሀገሩ ያገባን ዘንድ እርሱ ወደ እኛ ወረደ” (ሃይ. አበው) በማለት ተናገረ። ይህን ደግሞ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ስብከቱ “ልባችሁ አይደንግጥ በእግዚአብሔር እመኑ፤ በእኔም እመኑ። በአባቴ ቤት ብዙ ማደሪያና ማረፊያ አለ” (ዮሐ. ፲፬፥፩) በማለት ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ነገራቸው ሰማያዊውን ርስት ያወርሰን ዘንድ ሰው ሆነ። በዚህ ክፍል “አምላክ ሰው ሆኖ ያደረጋቸውን የማዳን ሥራዎች ሁሉ ሰው ሳይሆን ማድረግ አይችልም ነበር ወይ?” ለሚለው ጥያቄ መልሱ “ይችላል” ነው። ነገር ግን ከላይ በዘረዘርናቸው ምክንያቶች ሰው ሆነ እንዳልን ሁሉ ለመጨረሻ አርአያነቱን ሊያድለን ሰው ሆነ። አርአያነት በተግባር የሚገለጽ ነው። መለኮት የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚቸገር፣ የሚታመም፣ የሚሞት ባሕርይ የለውም። በቅዱስ ወንጌልም “ቀንበሬን በላያችሁ ላይ ተሸከሙ፤ ከእኔም ተማሩ፤ እኔ የዋህ ነኝና፤ ልቤም ትሑት ነውና ለነፍሳችሁም ዕረፍትን ታገኛላችሁ።” (ማቴ. ፲፩፥፳፱) እንዳለን እኛ እንድንጠቀምበት የምንሠራውን ሁሉ አስቀድሞ እርሱ ፈጽሞልናል። ስለዚህ ጹሞ “ጹሙ” ፣ ተርቦ “ተራቡ ፣ ተሰዶ “ተሰደዱ” ፣ ተገርፎ “ተገረፉ” ለማለት የሚራብ፣ የሚጠማ፣ የሚሰደድ፣ የሚገረፍ፣ የሚሞት ሥጋ ያስፈልገው ስለ ነበር አምላክ ሰው ሆነ።
ውድ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች በክርስቶስ መወለድ የሰው ልጅ ካገኛቸው ጸጋዎች አንዱ ከመላእክት ጋር በአንድነት እግዚአብሔርን ማመስገን መቻል ነው። ሊቁ ቅዱስ አትናቴዎስ በሃይማኖተ አበው “ወረሰዮ ድልወ ይትቀነይ ሎቱ ወይትለአኮ ከመ መላእክት እንዘ ሀሎ ውስተ ምድር በምግባር ሠናይ ወበሃይማኖት ርትዕት ዘሥላሴ ቅድስት፤ በዚህ ዓለም ሳለ በበጎ ምግባር ሥላሴንም በማመን እንደ መላእክት ያገለግለው ዘንድ ለእርሱም ይገዛለት ዘንድ የበቃ አደረገው” “ሃ.አበ. ፳፰፥፴፭) በማለት እንደገለጸው ሰውና መላእክት ዋናው የተፈጠሩለት ዓላማ እግዚአብሔርን አመስግነው ክብሩን ወርሰው ለመኖር ነው። ስለዚህ መላእክት ከሰው ጋር ማመስገን ቻሉ።
ይህን በተመለከተ በቅዱስ ወንጌል “ድንገትም ከዚያ መልአክ ጋር ብዙ የሰማይ ሠራዊት እግዚአብሔርን እያመሰገኑ መጡ፤ ክብር ለእግዚአብሔር በሰማያት ሰላምም በምድር ለሰው ልጅም በጎ ፈቃድ ሆነ ይሉ ነበር” (ሉቃ. ፪፥፲፫-፲፬) ተብሎ መላእክት በክርስቶስ ልደት ከሰው ልጅ ጋር ያመሰገኑት ምስጋና ተመዝግቦልን እናገኛለን። ሊቁ ቅዱስ ያሬድም “ዮም አሐደ መርኤተ ኮኑ መላእክት ወሰብእ ከመ ይሰብሕዎ ለክርስቶስ በቃለ አሚን፤ ዛሬ መላእክትና ሰው ሃይማኖታዊት በሆነች ቃል ክርስቶስን ያመሰግኑት ዘንድ አንድ ሆኑ።” (ድጓ ዘፋሲካ) በማለት አስረዳን። ስለዚህ ከሊቁ አገላለጽ የምንረዳው በብዙ መንገድ የተገለጸውና መጻሕፍት አምልተውና አስፍተው የሚነግሩን የሰው ልጅ ከመላእክት ጋር ማመስገናቸውን ነው።
ከዚሁ ጋር ተያይዞ ይህንን የከበረ ክርስቲያናዊ በዓል ስናከብር በኅሊናችን አስቀድሞ ሊመጣልን የሚገባው ነገር ቢኖር የድኅነታችን ምክንያት፣ የባሕርያችን መመኪያ፣ የዕርገታችን መሰላል፣ የከፍታችን ጉልላት፣ የክብራችን ጌጥ፣ የንጽሕናችን መሠረት የሆነችውን እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን ማመስገን ነው። ይህን አስመልክቶ አባ ጊዮርጊስ ዘጋሥጫ “ሰብእ ወእንስሳ ወኵሉ ዘሥጋ ያስተበፅዑኪ እስመ ለዘይሴስዮሙ በሐሊበ አጥባትኪ ሐፀንኪዮ፤ ሰው እንስሳና ሥጋዊ ፍጥረት ሁሉ ያመሰግኑሻል። የሚመግባቸውን በጡትሽ ወተት አሳድገሽዋልና” (አርጋኖን ዘሰኑይ) በማለት ቅድስት ድንግል ማርያምን ፍጥረታት ሁሉ እንደሚያመሰግኗት ከገለጸ በኋላ ለምን እንደሚያመሰግኗት ምክንያቱን ሲያብራራ ደግሞ ፍጥረታትን ሁሉ የሚመግበውን አምላክ ጡቷን አጥብታ በማሳደጓ እንደሆነ ያስረዳል።
የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ልደት ስናከብር ይህ አስደናቂ ወቅት ልባችንን በደስታ ይሞላል። የልደት በዓል ከአንድ ቀን በላይ ነው። ይህም የእግዚአብሔርን ወሰን የለሽ ፍቅር ማስታወሻ ነው፤ እጅግ ጥልቅ የሆነ ፍቅሩ፣ አንድ ልጁን ልኮ እኛን እንዲቤዠን ምክንያት የሆነበትን ምሥጢር የምንረዳበት ዕለት ነው። ታላቁ ቅዱስ አትናቴዎስ እንደተናገረው፣ “ሰው አምላክ ይሆን ዘንድ እግዚአብሔር ሰው ሆነ” (በእንተ ተሠግዎተ ቃል፣ ፶፬)። ይህ ጥልቅ የሆነ የመገለጥ ምሥጢር እግዚአብሔር ወደ እርሱ እንድንቀርብ እና በፍቅሩ ሊለውጠን ምን ያህል እንደፈለገ ያሳየናል።
በቤተልሔም የክርስቶስ የልደት ታሪክ በታሪክ ውስጥ ያለ ክስተት ብቻ አይደለም፤ የእምነታችን መሠረት እና የክርስትና ሕይወታችን ልብ ነው። በግርግም የተወለደው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ትሕትና፣ ስለ ትሕትና ኃይል እና ለእግዚአብሔር ፈቃድ መፈጸም ዝግጁ የሆነን የልብ ውበት ያስተምረናል። የተወለደውን አዳኝ ለማየት የቸኮሉት እረኞች፣ ክርስቶስን አጥብቆ በመሻትና በማግኘት የምንጎናጸፈውን ፍጹም ደስታ ያስታውሱናል፣ ጥበበኞች (ሰብአ ሰገል) ደግሞ ንጉሥ ክርስቶስን በሙሉ ልባችን የመፈለግን አስፈላጊነት ያሳዩናል። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘእንዚናዙ ይህን ሲያስረዳ “ክርስቶስ ተወልዷልና እናክብረው! ክርስቶስ ከሰማይ መጥቷልና እናግኘው!” ብሏል (ትምህርት ፴፰፡ በእንተ አስተርእዮቱ)።
በዚህ የተቀደሰ ወቅት፣ የገና በዓል ምን ማለት እንደሆነ እንድታስቡ ያስፈልጋል። ጊዜው የስጦታ እና የመብል የመጠጥ ብቻ ሳይሆን ልባችሁን ለእግዚአብሔር ፍቅር እና ጸጋ ለመክፈት የተሰጠን ዕድል ነው። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ “በዓሉን ዝም ብለን አናክብር ይልቁንም በዓሉን በመንፈሳዊ ተግባራት ለማክበር እንትጋ” (Homily on the Nativity of Christ) በማለት ያሳስበናል። ይህ ወቅት እምነታችን የሚጠነክርበት እና ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር በተግባር የሚገለጽበት ወቅት ይሁን።
የተወደዳችሁ የግቢ ጉባኤት ተማሪዎች የጌታ ልደት በረከት ተካፋዮች፣ እናንተ በእግዚአብሔር ፊት ውድ እንደሆናችሁ አስታውሱ። ይህ ሲሆን በቤተልሔም የተወለደው ያው ጌታ በልባችሁ ይኖራል። በዓለም ላይ የእርሱ ብርሃን ትሆኑ ዘንድ ተጠርታችኋል። በደግነታችሁ፣ በመታዘዛችሁ እና ለሌሎች ፍቅር በመስጠታችሁ በማንነታችሁ የክርስቶስን ክብር ታንጸባርቃላችሁ። መላእክት በምድር ላይ ሰላምን እንዳወጁ ሁሉ እናንተም በዙሪያችሁ ላሉ ሰዎች ሰላምና ደስታን ልታመጡ ይገባችኋል። ታላቁ ቅዱስ ባስልዮስ በአንድ ወቅት “ዛፍ በፍሬው ይታወቃል፤ ሰውም በሥራው ። መልካም ሥራ መቼም አይጠፋም።” ( Homily on Psalm 1) እንዳለው በዚህ ሰሞን ይበልጥ ተግባራችሁ የክርስቶስን ፍቅር ማሳየት እንዲችል መጣር ያስፈልጋል።
በአጠቃላይ በዓል የደስታ ዕለት ያለፈን ነገር እያስታወስን የምንደሰትበትና የተደረገልንን ነገር እያስታወስን እግዚአብሔርን የምናመሰግንምበት ዕለት ነው። በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓልም እንዲሁ ሰዎች እየተጠራሩ ይበላሉ፤ ይጠጣሉ፤ ዘመድ ከዘመድ ይጠያየቃሉ፡፡ ይሁን እንጂ የዘመድ መጠያየቂያ ከመሆን ባሻገር ድሆችንና ጦም አዳሪዎችን፣ ዕውሮችን፣ እጅና እግር የሌላቸውን ብድር መመለስ የማይችሉትን እንዳንዘነጋ መዘንጋት ብቻ ሳይሆን ብድር መመለስ ከሚችሉት ከዘመዶቻችንና ከባለጸጎች ይልቅ ቅድሚያ ሰጥተን እንድናበላቸውና እንድናጠጣቸው ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አስተምሮናል፡፡ (ሉቃ ፲፬) በተማርነው ትምህርት ተጠቅመን፣ ከባለጸጎችና ከዘመዶቻችን ይልቅ ድሆችንና ጦም አዳሪዎችን፣ ዕውሮችን፣ እጅና እግር የሌላቸውን አስበናቸው የተቻለንንም አድርገንላቸው የበዓሉን በረከት እንዲያድለን እግዚአብሔር ይፍቀድልን አሜን፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ ወለወላዲቱ ድንግል፤ ወለመስቀሉ ክቡር።