ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለሚኒስትሮችና ለካቢኒ አባላት በሰጡት የወቅታዊ ጉዳይ ማብራሪያ አስመልክቶ ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ። ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም.
በእንተ ሢመተ ኤጲስ ቆጰሳት
በመ/ር እንዳልካቸው ንዋይ
ክህነት “ተክህነ” ከሚለው የግዕዝ ግሥ የወጣ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም አገለገለ ተሾመ መንፈሳዊ ሥልጣን ተቀበለ ማለት ነው፡፡በአጠቃላይ ዘይቤያዊ ትርጉሙ አገልግሎት ማለት ሲሆን በምሥጢር ለሹመት መመረጥን ያመለክታል፡፡
ካህን ማለትም በቁሙ ሲተረጎም ቄስ ጳጳስ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሕዝብ መሪ አስተማሪ መንፈሳዊ አባት ማለት ነው፡፡
ክህነት እግዚአብሔር ለሰው ከሰጠው ሀብት አንዱና ዋናው ነው፡፡ ክህነት ከእግዚአብሔር የሚገኝ ጸጋ መለኮታዊ ጥሪ እና ሰማያዊ ምርጫ ነው፡፡ ክህነት እንደ ምድራዊ ሹመት በዘፈቀደ የሚታደል አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ባወቀ ተመርጠው የሚሾሙበት ጸጋ እንጂ ሁሉ ገንዘብ የሚያደርገው ሥልጣን እንዳልሆነ ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ እንዲህ አለ
‹‹ ወደ ተራራም ወጣ ራሱም የወደዳቸውን ወደርሱ ጠራ ወደ እርሱም ሄዱ ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው ድዉዮችንም ሊፈወሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለቱን አደረገ›› (ማር.፫፡፲፭ )
የመጀመርያው ሰው አዳም ከእግዚአብሔር ከተሰጡት ፯ ሀብታት በአንዱ ሀብተ ክህነት ነው፡፡ ለዚህም ነው በገነት እያለ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቀርብ እንደነበር የተጻፈው ሕጉን ትእዛዙን አፍርሶ በሰይጣን በተታለለ ጊዜ ደሙን አእዋፍ ለምግቡ ከመጣለት ፍሬ ከስንዴ ጋር ቀላቅሎ መሥዋዕት አቀረበ ፡፡
እግዚአብሔርም ዓለም የሚድነው በአንተ ደም ሳይሆን በእኔ ደም ነው ብሎታል፡፡ይህ የክህነት አገልግሎት በሦስቱ ዘመናት ማለትም በዘመነ አበው በዘመነ ኦሪት በዘመነ ወንጌል የተለየ መልክና ሥርዓት ይዞ መጥቷል፡፡
በዘመነ አበው በአበው ዘንድ የክህነቱ ሥራ እየተሠራ ኖሯል፡፡በተራራ ላይ አበው መሥዋዕት እየሰው እግዚአብሔርን እያመለኩ ኖረዋል፡፡ በዘመነ ኦሪትም በምስክሩ ድንኳን በአሮን እና በአሮን ወገኖች ይፈጸም እንደነበር ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ በሐዲስ ኪዳን ግን ራሱ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ በላምና በበግ የነበረው መሥዋዕት በአማናዊው በግ በክርስቶስ ተተክቶ አምላካችን በሾማቸው በ12ቱ ሐዋርያት የሐዲስ ኪዳኑ የክህነት አገልግሎት ይቀጥላል፡፡
በሐዲስ ኪዳን ካሉት የክህነት ደረጃዎች አንዱ ኤጲስ ቆጶስነት ነው፡፡
ኤጲስ ቆጳስነት የአገልግሎቱ ስም ሲሆን ባለቤቱ ኤጲስ ቆጰስ ይባላል፡፡ኤጲስ ቆጶስነት ከፍተኛው የክህነት ደረጃ ነው፡፡ ትርጉሙም የበላይ ጠባቂ መምህር ማለት ነው፡፡በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ኤጲስ ቆጰስ የሚሾመው ከቆሞሳት መካከል በትምህርቱ በትሩፋቱ ልቆ የተገኘ አባት ነው፡፡ የሚመረጠውም በሲኖዶስ ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስ ስለ ጵጵስና ሲጽፍለት ለዚህ ከፍተኛ ማዕርግ የሚመረጠው አገልጋይ ሊያሟላቸው የሚገቡ ጉዳዮችን አብሮ ጽፎለታል፡፡እንዲህ ሲል እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል … (፩.ጢሞ ፫፡፩-፯)
የማይነቀፍ
ከፍተኛው የቤተ ክርሰቲያን መዓርግ ስለሆነ የእግዚአብሔርም እንደ ራሴ ቤተ ክርስቲያንንም የሚጠብቅ ነውና ለዚህ ሹመት የሚመረጠው አገልጋይ የሚነቀፍ ጠባይ ሊኖረው አይገባም፡፡
ድንግል መነኮስ የሆነ
ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ለጢሞቴዎስ ኤጲስ ቆጶስ የአንዲት ሚስት ባል እንዲሆን ጽፎለታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም ይህን ሲተረጉም ሐዋርያው ይህንን ትእዛዝ እንደ ግድ መስፈርት አድርጎ አላስቀመጠውም ነገር ግን ከአንድ በላይ ሚስት ያገቡትን ከዚህ ሹመት ለማገድ ነው፡፡
ይህንንም ማድረጉ በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ጊዜያት በመሥፈርቱ ልክ የሚሆን ሰው ስላልነበረ በጊዜው ከነበሩት ሰዎች የተሻለ ቅድስናና ንጽሕና የያዙትን ለመምረጥ ነው፡፡ የድንግልና የገዳማዊ ሕይወት ከተጀመረ በኋላ ግን ከደናግል መነኮሳት መካከል ተመርጦ ይሾማል፡፡ ብሏል በቤተ ክርስቲያናችንም በ325 ዓም በኒቅያ ጉባኤ ከአገልግሎቱ ትልቅነት የተነሳ ጳጳስ ድንግላዊ እንዲሆን ተወስኗል፡፡
ልበኛ
ስለአገልግሎቱ ጥንቁቅና ንቁ መሆን አለበት ቤተ ክርሰቲያንን የሚያይበት ብዙ አይኖች ያሉት የትናንቱን የዛሬውንና የነገውን አርቆ ማየት የሚችል መሆን አለበት፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም አንድ ጳጳስ አንድ ጦርን ከሚመራ የጦር መኮንን በላይ ጥንቁቅ መሆን አለበት፡፡
ራሱን የሚገዛ
ራስን መግዛት ትልቁ የኦርቶዶክሳዊነት መለኪያ ነው፡፡ ሐዋርያውም በመልእክቱ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ በማለት ገልጾታል፡(ገላ ፭፡፳፫) ራስን መግዛት ለአንድ ምዕመን በጣም አስፈላጊ ከሆነ ለምዕመናን ጠባቂማ እጅጉን አስፈላጊ ይሆናል ፡፡ ራሱን የገዛ ዓለምን መግዛት ይችላል አዳም በገነት ሲኖር ራሱን በመግዛቱ ፍጥረታት በመላ ተገዙለት ራሱን መግዛት ቢሳነው ግን ፍጥረታት በመላ ጠላት ሁነው ተነሱበት፡፡ አምላክም ሰው የሆነው ሰውን ራሱን መግዛት ወደሚችልበት መዓርግ ለመመለስ እና ከራሱ ጋር አስታርቆ ፍጥረት ሁሉ እንዲወዳጀው ለማድረግ ነው፡፡
እንደሚገባው የሚሠራ
የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ እንደመሆኑ ሊሠራ የሚገባውን ሥራ ሐዋርያት በሲኖዶስ ሠለስቱ ምዕትም በፍትሐ ነገሥት እንዲሠራ የተናገሩትን በትጋት በአግባቡ የሚሠራ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከመዓርጉ የተነሳ ሊሠራ የማይገባውን ከማድረግ መከልከል ይኖርበታል ምክንያቱም ምዕመናን አብነት እንዳያጡ እርሱም የማይገባ ሥራ ሠርተዉ እንደተቀጡ እንደ ናዳብና አብዩድ እንዳይቀሰፍ መጠንቀቅ ይገባዋል (ዘሌ.፲፡፩)
ገንዘብ የማይወድ
የአንድ አባት ገንዘቡ ቤተ ክርስቲያንና ምዕመናን ናቸው፡፡ ጌታም ለቅዱስ ጴጥሮስ አደራ ጠብቅ ብሎ የሠጠው ገንዘብ በጎች ጠቦቶችና ግልገሎች ናቸው፡፡ማለትም ከታናሽ እስከ ታላቅ ያሉ ምዕመናንን መጠበቅ ዋናው ተግባሩ እንደሆነ ያሳያል ( ዮሐ.፳፩፡፲፭-፲፯) ከላይ በተወሰነ መልኩ ያየናቸው የአንድ ኤጲስ ቆጶስ መገለጫዎች ሲሆኑ የሚሾምበትን ሥርዓት ተመልክተን የጽሑፋችን ሐሳብ እንቋጫለን፡፡
ሥርዓተ ሢመተ ኤጲስ ቆጳሳት
ኤጲስ ቆጶስ ከ፶ ዓመት በታች እንዳይሾም ተከልክሏል ‹‹ወዘኢኮነ ሕይወቱ ሕፁፀ እም ፶ ዓመት›› ፍት.ነገ አን ፭/ ዲድ .፬
ብሉይና ሐዲስ የተማረ
የሚሾመውም በሚሾምበት ሀገር በምእመናን ምርጫና በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ (ፓትርያርኩ) ፈቃድ ነው፡፡ካህናቱና ሕዝቡ እንዲሾምላቸው ኤጲስ ቆጶስ የሚሆነውን ቆሞስ መርጠው ሲያቀርቡ ስለ ደግነቱና ትሩፋቱ ስለንጽሕናውና ከነውር የራቀ ስለመሆኑ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሦስት ጊዜ እየመላለሰ ማረጋጋጫ ይጠይቃቸዋል፡፡ ሕዝቡም አረጋግጠው የሚገባው ነው ብለው ሦስት ጊዜ መልስ ይሰጣሉ በሦስተኛው ሕዝቡ መልስ ሲሰጡ እጃቸዋን አንስተዉ ይገባዋል እያሉ ያጨበጭባሉ፡፡
ደግነቱ ያልታወቀ አይሾምም
ሲሾም ካህናቱም ሕዝቡም በሙሉ ተገኝተዉ እየመሰከሩለት ነው የሚሾመው ‹‹ወኩሎሙ ሰብእ ይንበሩ በእንተ ተሠይሞቱ ሕዝብኒ ወካህናት እንዘ ስምዐ ይከውኑ ሎቱ›› በአንድ ዘመን በአንድ ወንበር ሁለት ሰዎች ፓትርያርክ ሆነው አይሾሙም፡፡
-ርእሰ ሊቃነ ጳጶሳት ሲሾም ሊቃነ ጳጳሳት ኤጲስ ቆጰሳት ይገኛሉ፡፡ይህ ሹመት ያለ ኤጲስ ቆጶሳት ጉባኤ አይደረግም (ፍት.መን አን.፬ ) ሊቀ ጳጳሳቱ ወይም ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የታመመ እንደሆነ እስከሚድን የታሠረ እንደሆነ እስከ ሚፈታ ይጠበቃል ሹመቱ ለሌላ አይሰጥም፡፡ (ፍት.መን. አን 4)
በአጠቃላይ ከብዙ በጥቂቱ ሥርዓተ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ይህን ይመስላል፡፡አሁን በአለንበት ጊዜ ግን እነዚህን ሥርዓታት ባለመከተል ከሐዋርያት ሲኖዶስ እና ከፍትሐ ነገሥት ትምህርት ውጭ ኤጲስ ቆጶሳትን ሾምን የሚሉ አካላት እየመጡ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ይህን ትምህርት በማወቅ ክፉውን ከደጉ ሃይማኖቱን ከክህደት ጽድቁን ከኃጢአት ሥርዓቱን ሥርዓት ካልሆነው በመለየት በአባቶቻችን ትምህርት መጽናት ይገባል፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት የወላዲተ አምላክ አማላጅነት የቅዱሳን ጸሎት ይርዳን፡፡
ምንጭ ፡ፍትሐ ነገሥትና
-ድዲስቅልያ
ከቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት የተላለፈ መልእክት
የሚዛን ቴፒ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ቢሮ መታሸጉ ተገለጸ።
የሰሜን አሜሪካ ካህናት ማኅበር መግለጫ
ከርእሰ አድባራት ዱባይ ሻርጃ አጅማን ቅድስት ማርያም ወቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት የተሰጠ ወቅታዊ ማሳሰቢያ።
ከርእሰ አድባራት ዱባይ ሻርጃ አጅማን ቅድስት ማርያም ወቅዱስ ያሬድ ቤተ ክርስቲያን ሰበካ ጉባኤ ጽ/ቤት የተሰጠ ወቅታዊ ማሳሰቢያ።
ከምሁር የኢየሱስ ገዳም የተሰጠ የአቋም መግለጫ፡፡
የገዳማችን የበላይ ጠባቂ መስሎ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነትን ለመናድና ምእመናንን ለማወናበድ የታቀደውን ሴራ ስለመቃወም ከምሁር የኢየሱስ ገዳም የተሰጠ የአቋም መግለጫ፡፡
ከነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር የተሰጠ መግለጫ
ኢ-ቀኖናዊ በሆነ መልኩ የተፈጸመውን ”ሲመተ ኤጲስ ቆጶሳት” አስመልክቶ ከነገረ መለኮት ምሩቃን ማኅበር የተሰጠ መግለጫ