“ግቢ ጉባኤ ቤተ ክርስቲያን በወጣትነት ዘመናቸው ልጆቿን አቅፋ የያዘችበት ትልቁ ተቋም ነው” (ዐወቀ አበብሽ ከጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ)

ክፍል አንድ 

በእንዳለ ደምስስ

ዐወቀ አበብሽ ይባላል፡፡ በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስ በሜዲካል ላቦራቶሪ ትምህርት ዘርፍ   ተከታትሎ ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ በ፳፻፲፮ ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው ዋንጫና ሜዳልያ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡ ከትውልድ ቀዬው ጎጃም ወደ ጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ ሲመደብ ፍርሃት ነበረው፤ ነገር ግን ጠንክሮ በመማር፣ በግቢ ጉባኤያት ከመሣተፍ አልፎ በአገልግሎትም ከሚፋጠኑ ወንድሞች አንዱ ሆኖ አሳልፏል፡፡

የተወለደው ምሥራቅ ጎጃም ጎንቻ ሰውነቴ ወረዳ ውስጥ ነው፡፡ የሕፃንነት ዘመኑን የቤተሰቡን ከብቶች በመጠበቅ በእረኝነት የጀመረ ሲሆን ሕይወት ለአባቡሽ እንደማንኛውም የገጠር ተማሪ ከባድ ነበር፡፡ ገና በሕፃንነቱ ፊደል መቁጠር ቢጀምርም በኩራዝ (ላምባ) እያጠና በጠዋት ወደ ትምህርት ቤቱ ከሰፈሩ ልጆች ጋር እየሮጠ ይሄዳል፤ ሲመለስም እንዲሁ፡፡ ከትምህርት ቤቱ ርቀት የተነሣ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ርቀት እያስገደደው አራት ትምህርት ቤቶችን ቀያይሯል፡፡ ከአምስተኛ እስከ ስምንተኛ ያሉትን ክፍሎችም ከቦታ ቦታ መቀያየሩ ሳይበግረው የደረጃ ተማሪ እንደነበር ይገልጻል፡፡

የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም ከቤተሰቡ በመለየት ከጓደኞቹ ጋር ወደ ከተማ በመሄድ ቤት ተከራይቶ በባሕረ ጊዮርጊስ የመሰናዶ ት/ቤት ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ ዐወቀ ለትምህርት በነበረው ጠንካራ ፍቅር የተነሣ በሳምንት ወይም በሁለት ሳምንታት አንድ ጊዜ ወደ ቤተሰብ በመሄድ ለስንቅ የሚያስፈልገውን ጥሬ ምርት ይዞ በመመለስ አዘጋጅቶ መመገብን ለመደ፡፡

የዐሥራ ሁለተኛ ክፍል ውጤቱ ብዙም አስደሳች እንዳልነበረ የሚገልጸው ዐወቀ ዩኒቨርሲቲ ከገባ በኋላ ግን በቁርጠኝነት በመማር በአራት ዓመታት የትምህርት ቆይታው ፫.፱ አጠቃላይ ውጤት  ከዩኒቨርሲቲው ከፍተኛውን ነጥብ በማምጣት በእጅግ ከፍተኛ ማዕረግ ለመመረቅ በቅቷል፡፡

በቤተ ክርስቲያን ጋር የነበረውን ሕይወት በተመለከተም እንደማንኛውም ሕፃን በቤተሰቡ አማካይነት ቤተ ክርስቲያን ሄዶ ከመቁረብ ውጪ አብነት ትምህርትን ለመማር ጥረት አለማድረጉን ይናገራል፡፡ ነገር ግን የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ከጓደኞቹ ጋር ወደ ከተማ ሄዶ በመማር ላይ ሳለ ቤተ ክርስቲያን መሄድ፣ መጸለይ፣ የሠርክ ጉባኤ መሳተፍ ጀመረ፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታውም ግቢ ጉባኤ ውስጥ በመሳተፍ እንደተማረ፤ ይህም ስለ እምነቱ በሚገባ መረዳቱንና እንደ ዐቅሙ በሚችለው ሁሉ በአገልግሎት ሲሳተፍ እንደቆየም ነግሮናል፡፡

የዝግጅት ክፍላችንም በመማር ላይ ላሉትና ወደፊት ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ለሚማሩ ተማሪዎች ተሞክሮውን ያካፍል ዘንድ ጋብዘነዋል፤ ቀጥለን እናቅርበዋለን – መልካም ቆይታ፡፡

  • የልጅነት ዘመንህ እንዴት አለፈ? እስቲ ስለ ልጅነት ሕይወትህ አጫውተን፡፡

እንደማንኛውም ሕፃን ከሰፈር አብሮ አደግ ጓደኞቼ ጋር አፈር እየፈጨን፣ ኳስ እየተጫወትን ብናድግም ዋናው ሥራችን ግን እረኝነት ነበር፡፡ የገጠር ልጅ እንደ መሆኔ ከብቶቻችንን ማሰማራት፣ ወደ ወንዝ መውሰድና መመለስ፣ ለወላጆቼ በመላላክ ነው ያደግሁት፡፡

  • ለመማር በምታደርገው ጥረት ላይ የቤተሰቦችህ ድጋፍ ምን ይመስል ነበር?

የወላጆቼ ድጋፍ ነው ዛሬ ውጤታማ ለመሆን ያበቃኝ፡፡ በትምህርቴ እንድበረታና ውጤታማ እንድሆን በሚችሉት ሁሉ ደግፈውኛል፤ የቤት ኪራይ እየከፈሉ፣ የሚያስፈልገኝን የትምህርት መሣሪያዎችን እየገዙልኝ፣ ቀለቤን ሁሉ ችለው ነው ያስተማሩኝ፡፡

ዘጠነኛና ዐሥረኛ ክፍል ልጅነትም ስላለኝ፣ ከቤተሰብም ተለይቼ ስለማላውቅ ቤተሰቦቼ ስለሚናፍቁኝ በየዐሥራ አምስት ቀን እየሄድኩ እጠይቃቸው ነበር፡፡ እነርሱም ስንቅ የሚሆነኝን ጥሬ ቋጥረው ይልኩኝ ነበር፡፡ ዐሥራ አንድ እና ዐሥራ ሁለተኛ ክፍል ግን ትምህርቱም እየጠነከረ ስለመጣ ትኩረት መስጠት ስላላብኝ ብዙም አልመላለስም ነበር፡፡

  • ወደ ዩኒቨርሲቲ ከገባህ በኋላ ጠንክሮ ለመማር ያደረግኸውን ጥረት ብታካፍለን?

የሄድኩት ወደማላውቀው ቦታ ነው፡፡ ብቀጥልም ባልቀጥልም ሄጄ ማየት አለብኝ ብዬ ነው የሄድኩት፡፡ ነገር ግን ወደ ኋላ ማለት ወደፊት ዋጋ እንደሚያስከፍለኝ ስለተረዳሁ ዕድልን ለመጠቀም ወሰንኩ፡፡ ለጊዜው ሙቀቱ በጣም አስቸግሮኝ ነበር፤ ውስጤ ፍርሃት የነበረ ቢሆንም ወንድሞችና እኅቶች ተቀብለው በጥሩ ሁኔታ ነው ያስተናገዱን፡፡ በግቢ ጉባኤ አቀባበል መርሐ ግብር ላይም ለእኛ የሚጠቅመንን ምክር በመስጠት አበረታቱን፡፡ ለራሴም አንድ ቃል ገባሁ፡- “እዚህ ድረስ ከመጣሁ አይቀር በጥሩ ውጤት መመረቅ አለብኝ፡፡” ብዬ ወሰንኩ፡፡ መደበኛ ትምህርቴን መማር፣ ማጥናት፣ ቤተ ክርስቲያን መሄድ፣ ግቢ ጉባኤ በሚኖረው መርሐ ግብር መሳተፍ ብቻ ነበር ሥራዬ፡፡ ይህንን ደግሞ በተግባር ላይ ለማዋል ጊዜ አልፈጀብኝም፡፡

የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመት (ሴሚስተር) ውጤቴ ፫.፱ ነበር፡፡ ከዚህ የተሻለ ውጤት ለማምጣትም ራሴን አሳመንኩት፡፡ ነገር ግን ኮቪድ ገብቶ ስለነበር የትምህርት ሂደቱን ስለገታው ወደ ቤተሰብ ነው የሄድኩት፡፡ ትምህርት ሲጀመርም ቀጥታ ሕክምና ለማጥናት የሚያስችለኝ ውጤት ቢሆንም ስድስትና ሰባት ዓመት አልቆይም ብዬ ሜዲካል ላቦራቶሪ ለማጥናት ወሰንኩኝ፡፡

ጅግጅጋ የተመደብኩት እኔ ብቻ ሳይሆን ከእኔ ጋር የነበረው ጓደኛዬ ጭምር ስለነበር ሁለታችንም ጥሩ ውጤት ለማምጣት የምንችለውን ሁሉ አድርገናል፡፡ ተመሳሳይ አቋም ስለነበረን ሁለታችንም በጥሩ ውጤት ነው የጨረስነው፡፡ የግቢ ጉባኤ ወንድሞችና እኅቶች በምክርም በማበረታታት ስለሚያግዙን በራሳችን ላይ ጫና እንዳንፈጥር ጥረት አድርገናል፡፡

ነገር ግን ወደ መጨረሻዎቹ ዓመታት ትምህርቱ እየከበደ ስለሚመጣ ሊሆን ይችላል ብዙም አይጎበኙንም ነበር፡፡ ካሉት ግቢዎች አንጻር የመርሐ ግብር መደራረብ፣ ትምህርትና የጥናት፣ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎችን ለመቆጣጠር፣ ለመምከርና ለመስተማር የጊዜ እጥረት ሊገጥማቸው እንደሚችል ቢታወቅም ክትትል ያስፈልጋቸዋልና ይህንን ክፍተት ለመሙላት መጣር ይገባል፡፡

  • በአገልግሎት ደረጃ የነበረህ ተሳትፎ ብታብራራልን?

ወደ አገልግሎት የገባሁት ቆይቼ ቢሆንም በልማት ክፍል ውስጥ አገልግያለሁ፡፡ ብዙ ጊዜ እየተማሩ ግቢ ጉባኤ መሳተፍን አክብደው የሚያዩ ተማሪዎች አሉ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ ጊዜያችንን አብቃቅተን የቤተ ክርስቲያንን ትምህርትም መማር እንችላለን፡፡ እኔ ከመደበኛው ትምህርቴ ውጪ ቤተ ክርስቲያንና ግቢ ጉባኤ ውስጥ ነው ሳሳልፍ የነበረው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሄጄ እጸልያለሁ፣ ግቢ ጉባኤ ውስጥ ደግሞ በልማት ክፍል ውስጥ ስብሰባ ሲኖር እንዲሁም የምናከናውናቸው ተግባራት ሲኖሩ እሳተፋለሁ፡፡ ኮርስን በተመለከተ እሑድ እሑድ የሚሰጥ በመሆኑ ከቅዳሴ በኋላ እማራለሁ፡፡

በአገልግሎት መሳተፌ ጠቅሞኛል እንጂ ምንም ያሳጣኝ ነገር የለም፡፡ ቁርጠኛ እንድንሆን ሰዓታችንን በአግባቡ እንድንጠቀም ያደርገናልና እኔ በዚህ ተጠቅሜአለሁ፡፡

ይቆየን፡፡

“ለግቢ ጉባኤ ትምህርቴ የመደበኛው ትምህርቴን ያህል ትኩረት ስሰጠው ነበር፡፡” (ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ)

ክፍል ሁለት                                          

በእንዳለ ደምስስ

ጉባኤ ቃና፡- በርካታ ተማሪዎች መደበኛ ትምህርቱንና የግቢ ጉባኤ ትምህርትን አጣጥሞ ለመቀጠል የጊዜ እጥረት ሊገጥመን ይችላል የሚል ስጋት ያድርባቸዋል፡፡ የእርስዎን ተሞክሮ ቢያካፍሉን?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- አንድ ሰው ሊያደርገው የሚገባውን ነገር አስቦና አምኖበት የሚያደርግ ከሆነ በምንም ነገር ሊቸገር አይችልም፡፡ ችግር እንኳን ቢገጥመው ተቋቁሞት ያልፈዋል እንጂ ላመነበት ነገር ወደ ኋላ ማለት የለበትም፡፡ መደበኛውም ሆነ የግቢ ጉባኤ ትምህርቱ በጣም የተለያዩ ነገሮች ናቸው ለእኔ፡፡ የመደበኛው የትምህርት ሰዓቴን በአግባቡ ነው የምጠቀመው፡፡ በዚህ ጊዜ ወደ አገልግሎት አልሄድም፡፡ ሁለቱንም የየራሳቸው ሰዓት መድቤ ነው የማከናውነው፡፡ ለመንፈሳዊው ትምህርት እንዲሁም ለአገልግሎት በመደብኩት ሰዓት በምንም ምክንያት ወደ መደበኛው ትምህርቴ አላተኩርም፡፡ ሁለቱ ተጋጭተውብኝ አያውቁም፡፡ ተማሪዎች ስሕተት ውስጥ የሚገቡት ሁሉንም ነገር በአንድ ጊዜ ለማከናወን መሞከራቸው ነው፡፡ በተለይ የዚህ ዘመን ትውልድ ሁሉም ነገር ያምረዋል፡፡ ፊልም ማየቱ፣ መንፈሳዊ ትምህርቱ፣ ኳስ ጨዋታው፣ ከጓደኖች ጋር በሳቅ በጨዋታ ማሳለፍ፣ በመደበኛ ትምህርቱ ውጤታማ መሆንን … ያምታቱታል፡፡ ለእያንዳንዱ ነገር ጊዜ አይመድቡለትም፡፡ ይህ ደግሞ የሚሆነው ጥርት ያለ  ግብ ስለሌላቸው ነው፡፡

በእርግጥ መጀመሪያ ሰው መሆን ይቀድማል፡፡ እኔ እውነተኛ ሰው መሆን እፈልጋለሁ፡፡ የትምህርቴ ግብ ደግሞ ጥሩ ተማሪ፣ ጥሩ ሐኪም መሆን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ማንነቴን የሚያንጽልኝ የግቢ ጉባኤ አገልግሎትና መደበኛው ትምህርቴ ናቸው የሚል እምነት በውስጤ አሳድሬያለሁ፡፡ የግቢ ጉባኤ ትምህርቴን የመደበኛው ትምህርቴን ያህል ትኩረት የምሰጠው ጉዳይ ነው ምናልባትም ሳላስበልጠው አልቀርም፡፡ ያ ማለት ሁለቱን አምታታለሁ ማለት አይደለም፡፡ ስለዚህ ቤተ ክርስቲያን ሄዶ መማርን፣ መጸለይን፣ ማገልገልን እንደ መደበኛ ትምህርቴ ዋጋ ሰጥቼዋለሁ፡፡ በትምህርቴ ደግሞ ድርድር አላውቅም፡፡ የዕረፍት ጊዜ የሚባል ነገር ኖሮኝ አያውቅም፡፡ ለእኔ መደበኛ ትምህርቴ ላይ ካልሆንኩ ቤተ ክርስቲያን ነኝ ማለት ነው፡፡ አለበለዚያ ከቤተሰቦቼ ጋር ነው የምሆነው፡፡ ስለዚህ ተማሪዎች የወደፊት ግባቸውን ማሰብና ለዚያም የሚገባቸውን መሥዋዕትነት መክፈል ይገባቸዋል፡፡

ጉባኤ ቃና፡-  በከፍተኛ ትምህርት ተቋም ውስጥ በእናንተ ዘመንና አሁን ያለውን ትውልድ የአገልግሎት ትጋት በማነጻጸር ቢገልጹልን?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- ድሮ በነበረው ሁኔታ ዛሬ ላይ ያሉት የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች እንዲያልፉ አይጠበቅባቸውም፤ በትናንት መለካት የለባቸውም፡፡ ቀድሞ የነበረውና አሁን ያለው የአገልግሎት መንፈስ የተለያየ ነው፡፡ እኛ ግቢ ጉባኤ ስንገባ የጅማ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በደሳሳ መቃኞ ውስጥ ነበረች፤ አዳራሽ አልነበረንም፡፡ ከእኛ በፊት ገብተው የነበሩ ታላላቅ ወንድሞቻችን እኛን ለማስተማርና የተቀናጀ አገልግሎት ለመስጠት ይሰበሰቡባት የነበረችው ቤት አነስተኛ ስትሆን የከብቶች እዳሪ እየለቀለቁና እያጸዱ ይጠቀሙበት ነበር፡፡ እኛ ደግሞ መማሪያ አዳራሽ ያስፈልገናል አልን፡፡ ስለዚህ ቅድሚያ ሰጥተን አዳራሽ መሥራት ወደሚለው ስላዘነበልን አዳራሹን ለመሥራት ቻልን፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ የአጥቢያው ምእመናንን ጨምረን በማስተባበር ቤተ ክርስቲያኑን ለምን አንሠራም ብለን ተነሣሣን፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የእናታችን ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያንን ለማሠራት በቃን፡፡ አሁን ያሉት ተማሪዎች ግን ይህ ሁሉ አይጠበቅባቸውም፡፡ ሊገጥማቸው የሚችለው ችግር ከእነርሱ በፊት በነበሩ ወንድሞች ተፈትቶ ስለሚያገኙት በቀላሉ አገልግሎት ማግኘት ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የቀድሞው አገልግሎት በርካታ ውጣ ውረድ ይበዛበት ነበር፡፡

በዚህ ዘመን የሚጠበቅባቸው ነገር ቢኖር መንፈሳዊ ሕይወታቸው ላይ መሥራትና ዓለሙን አሸንፈው በትምህርታቸውም በመንፈሳዊ ሕይወታቸውም ውጤታማ ሆነው እንዲወጡና ሙሉ ሰው እንዲሆኑ ነው፡፡ ሁሉም ነገር የተሟላላቸው ስለሆነ የተዘጋጀ ምግብን አንስቶ የመጉረስ ያህል ነው፡፡ አዳራሽ፣ ወይም ቤተ ክርሰቲያን እንሥራ አይሉም የተዘጋጀውን መንፈሳዊ ማዕድ ላይ መሳተፍ ብቻ ነው የሚጠበቅባቸው፡፡

በእኛ ዘመን ከነበርንበት ግቢ ቢያንስ እስከ ፻፶ ኪሎ ሜትር ድረስ በእግራችን እየተጓዝን በዙሪያው ያሉትን አብያተ ክርስቲያናት እናገለግል ነበር፡፡ ከእኛ በፊት የነበሩት ወንድሞቻችን እኛንም እያስከተሉ ቅዳሜና እሑድ ጋምቤላ፣ መቱ፣ ወልቂጤ ድረስ እየሄድን ነበር የምናገለግለው፡፡ ሰንበት ትምህርት ቤቶችን በማቋቋምና ቃለ እግዚአብሔርን በማስተማር እንተጋ ነበር፡፡ ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር የቀረበ ግንኙነት በመፍጠር ውጤታማ ሥራ ለመሥራት ጥረት እናደርግ ነበር፡፡

የሰንበት ትምህርት ቤት አገልግሎትን በተመለከተም በጅማ ሐመረ ኖኅ ኪዳነ ምሕረት ሰንበት ትምህርት ቤት ሥር በሌሎች ሰንበት ትምህርት ቤቶች ውስጥ ያልተሞከረ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ክፍል በሚል ተጠሪነቱ ለሰንበት ትምህርት ቤቱ የሆነ ራሱን የቻለ ዋና ክፍል እንዲቋቋም አደረግን፡፡ በዚህ ክፍል ውስጥ ከሌሎች ወንድሞችና እኅቶች ጋር በመሆን አገልግሎት ውስጥ በስፋት በመሳተፍ ሰንበት ትምህርት ቤቱንና ግቢ ጉባኤውን የማስተሳሰርና የተቀናጀ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ ችለናል፡፡

በዚህ ዘመን በተለይ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ስማርት ስልኮች፣ ላፕ ቶፕ ኮምፒዩተሮች በቀላሉ በእያንዳንዱ ተማሪ እጅ ስለሚገኙ ተማሪዎች በስልኮቻቸው ላይ እየተጠመዱ ረጅም ሰዓት ቢጠቅማቸውም ባይጠቅማቸውም ያሳልፋሉ፡፡ ይህ ደግሞ ከዓላማቸው ወደ ኋላ እንዲሉና ለትምህርታቸውና ለአገልግሎት የሚሰጡትን ጊዜ እንዲያጡ ያደርጋቸዋል፡፡ ሐሳባቸውን ከሚከፋፍል ድርጊት መቆጠብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በግቢ ጉባኤ ውስጥ ተሳተፉም አልተሳተፉም ለመጡበት ዓላማ ታማኞች መሆን አለባቸው፡፡ ጠንክሮ መማር ያስፈልጋል፡፡

ጉባኤ ቃና፡-  በግቢ ጉባኤያት አማካይነት ከእናንተ በፊት አዳራሽና ቤተ ክርስቲያን የመሥራት እንቅስቃሴ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ሐሳቡ እንዴት መነጨ?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- ሐሳቡ እኛ ያሰብነው ሐሳብ አይደለም፡፡ ከእኛ በፊት ገብተው የነበሩ ታላላቅ ወንድሞቻችን ሐሳብ ነው፡፡ ለአገልግሎት ምቹ አልነበረም፡፡ ቅድም እንደገለጽኩት ቤተ ክርስቲያኑ በመቃኞ ነው የነበረው ያለው፣ በዚህ ላይ በጣም ትንሽ ነበር፡፡ በወቅቱ እናድሰው የሚል ሐሳብ ቢኖርም እንደ አዲስ መሥራት የተሻለ እንደሆነ ታምኖበት እኔ ሁለተኛ ዓመት ሆኜ ገንዘብ ማሰባሰብ ተጀመረ፡፡ በወቅቱ የነበሩ አንድ ኢንጂነር ቤተ ንጉሥ የሚባለው ቤተ ክርስቲያን ዲዛይን ሠርተውልን ነበር፡፡ የተሠራው ዲዛይን አነስተኛ ቢሆንም ተማሪው ብቻ ሳይሆን የአጥቢያው ምእመናንም ቁጭት ስለነበር ሁሉም የተቻለውን ጥረት ማድረግ ቀጠለ፡፡ ነገር ግን ለተወሰኑ ዓመታት ሥራው ሳይጀመር ቀረ፣ እኔም ተመረቅሁ፡፡ እኔ ዕድለኛ ሆኜም በነበረኝ ከፍተኛ ውጤት ምክንያት እዚያው ለሁለት ዓመታት እንድሠራ ስለተመደብኩ ከምረቃ በኋላ ግንባታው ተጀመረ፡፡ የሕንጻ አሠሪው ኮሚቴም አባል ነበርኩ፡፡ የደብሩ አስተዳደርና ሰበካ ጉባኤው በጣም ያከብሩንና የምናቀርበውን ሐሳብ የማድመጥ፣ ተግባራዊም ለማድረግ ወደ ኋላ የማይሉ ነበሩ፡፡ እኛም እንታዘዛቸው ነበር፡፡ ዲዛይኑን የማሠራት ኃላፊነት ተሰጥቶን ስለነበር ወደ አዲስ አበባ ከአስተዳዳሪው ጋር መጥተን ማኅበረ ቅዱሳን ሠርቶ እንዲያቀርብ አደረግን፡፡

የሚያግዙን ከአምስት ኪሎ ኢንጂነሪንግ የተመረቁ ወንድሞችም ወደ ጅማ መጡ፤ ተጨማሪም ኃይል ሆኑን፡፡ ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያኗን የሚሠራላትን ሰው አሰባሰበች ማለት እንችላለን፡፡ በሁለት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ቤተ ክርሰቲያኑ ተሠራ፡፡ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነ እንጂ የእኛ መሰባሰብ ብቻ እንዲሠራ አላደረገውም፡፡ በጣም ጥሩ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማነጽ ቻልን፡፡

ይቆየን

“ለግቢ ጉባኤ ትምህርቴ የመደበኛው ትምህርቴን ያህል ትኩረት ስሰጠው ነበር፡፡” (ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ)

ክፍል አንድ                                             

በእንዳለ ደምስስ

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ በ፲፱፻፹፯ ዓ.ም ከኮልፌ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ፲፪ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተናን ፬ ነጥብ በማምጣት በ፲፱፻፹፰-፲፱፻፺፬ ዓ.ም በጅማ ዩኒቨርስቲ የሕክምና ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ በሰባት ዓመታት የሕክምና ትምህርት ቆይታቸው ከትምህርት ክፍሉ እና ከአጠቃላይ የዩኒቨርሲቲው ተመራቂዎች በከፍተኛ ማዕረግ የሜዳልያ ተሸላሚ በመሆን የሕክምና ትምህርታቸውን አጠናቀዋል፡፡ ባስመዘገቡት ውጤት መሠረትም በዩኒቨርሲቲው ለሁለት ዓመታት በመምህርነት ተመድበው አገልግለዋል፡፡

ለሰባት ዓመታት በዩኒቨርሲቲው ትምህርታቸውን ሲከታተሉ በየዓመቱ ዩኒቨርሰቲው የሚያዘጋጃቸውን ሽልማቶች በተደጋጋሚ ለመቀበል ችለዋል፡፡ እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው በቆዩባቸው ጊዜያት በግቢ ጉባኤ ውስጥ በንቃት ከሚሳተፉ ወንድሞችና እኅቶች መካከል ነበሩ፡፡

ፕ/ር እንግዳ በሙያቸው በተለያዩ ሆስፒታሎች ውስጥ ያገለገሉና በቅዱስ ጳውሎስ ሚሊኒየም ሆስፒታል ውስጥ በሚገኘው የሕክምና ኮሌጅ ውስጥ በኃላፊነትና በመምህርነት እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ በሙያቸው ባበረከቱት አስተዋጽኦም ከተለያዩ ተቋማት ሽልማቶችን ለማግኘት የቻሉ ባለሙያ ናቸው፡፡

በዚህም መሠረት የካቲት ፲ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሕክምና ኮሌጅ የማኔጅመንት ቦርድ የዶ/ር እንግዳ አበበን መረጃዎች ከገመገመ በኋላ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰጥቷል፡፡ ፕሮፌሰር እንግዳ አበበ ገላን የሕክምና ዲግሪያቸውን (MD) ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ፣ የቀዶ ሕክምና ስፔሻሊቲ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቀዶ ሕክምና እንዲሁም የሰብ-ስፔሻሊቲ ዲግሪያቸውን በኩላሊት ንቅለ ተከላ ከቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም የሕክምና ኮሌጅ ያገኙ ሲሆን፤ የተለያዩ አጫጭር የሞያ ሥልጠናዎችን በአገር ውስጥ እና በውጭ አገር መከታተላቸውን የሕክምና ኮሌጁ አስታውቋል፡፡

ፕሮፌሰር እንግዳ አበበ ገላን በግላቸውና ከሙያ አጋሮቻቸው ጋር ከ፵ በላይ በምርምር የተደገፉ ጥናታዊ ፅሁፎችን በታወቁ አገራዊና ዓለም አቀፋዊ መጽሔቶች ላይ ለኅትመት አብቅተዋል፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሕክምና ኮሌጅ በሚገኘው የሕክምና ትምህርት ቤት ውስጥ የቀዶ ሕክምና ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

ወደ ቃለ ምልልሳችን ከመግባታችን በፊት አብረዋቸው የሚሠሩ ባለሙያዎች ስለ ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ የሰጡትን የምስክርነት ቃል በጥቂቱ እነሆ፡-

“እጅግ በጣም ታታሪ እና ትሁት ስለሆነው ፕ/ር እንግዳ አበበ ሳወራ በኩራት ነው፡፡ ወደ ቀዶ ጥገና ክፍል የሚሄድ ሁሉ ያውቀዋል፡፡ ጠዋት ታካሚዎችን ስንጎበኝ ለአንድ ቀን የተኛ ታካሚ እንኳን በእርሱ መታየት ይፈልጋል፡፡ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል የሚማሩ ተማሪዎች ሁሉ እንደ እርሱ መሆን ይፈልጋሉ፡፡ በሆስፒታል ውስጥ በሚሠሩ ሰዎች ሁሉ የተከበረ ነው፡፡ የቀዶ ጥገና ፕሮፌሰርና የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሐኪም የሆነው ፕ/ር እንግዳ አበበ ለእኛ ልዩ አርአያችን ነው፡፡” (ዶ/ር ፍራኦል)

“በእርሱ መማር መቻሌ ታላቅ ዕድል ነው፡፡ ሰው አክባሪ፣ ትሁት፣ እግዚአብሔርን የሚፈራ ሰው ነው፡፡”(ምሕረት ተዘራ)

“የተባረኩ እጆች፣ የሚደንቅ ዕውቀት ያለው ሰው ነው፡፡ ከእርሱ ጋር ቀዶ ጥገና ከገባህ የሚያሳስብህ አይኖርም፡፡”(ቶሌ ካን ያደቴ)

“በሀገራችን ካሉ ምርጥ የቀዶ ጥገና ሐኪሞች አንዱ ነው፡፡ ትህትናው፣ ዕውቀቱ እና ታማኝነቱ ሁሉም ተስማምተው ስለ እርሱ መልካምነት እንዲያወሩ አድርጎታል፡፡”(አዲስ ዓለም ገንታ)

“ፕ/ር እንግዳ እጅግ የምትደነቅ ትሁት እና ሥራ ወዳድ ሰው ነህ፡፡ አብሬህ በመሥራቴ ዕድለኛ እንደሆንኩ ይሰማኛል፡፡” (ቤላ ሮማን)

“እርሱ በጣም የሚደንቅና ታላቅ ሰብእና ያለው ሰርጀን ነው፤ በጣም ትሁት፣ ታታሪና ጠንካራ ሠራተኛ እንዲሁም ለታካሚዎች አክብሮት የሚሰጥ ሰው ነው፡፡ እርሱን በቃላት መግለጽ አይቻልም፡፡ በእርሱ በመማሬ በጣም ደስተኛ ነኝ፡፡” (አያንቱ ተስፋዬ)

ከላይ የቀረበው ምሥክርነት “Hakim 2011 Nominee” በተሰኝ ድረ ገጽ ላይ ያገኘነው መረጃ ሲሆን ከዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ ጋር በሕክምናው ዘርፍ የሠሩ እና የተማሩ ባለሙያዎች ናቸው፡፡ ለመሆኑ ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበ ማን ናቸው? በየጊዜው የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን ታሳቢ በማድረግ በምናሳትማቸው የጉባኤ ቃና መጽሔት እትሞቻችን በግቢ ጉባኤያት ውስጥ ያለፉና የሕይወት ተሞክሯቸው ሌሎችን ያስተምራል ያልናቸውን ወንድሞችና እኅቶችን በቃና እንግዳ ዓምዳችን እናቀርባለን፡ እኛም በዚህ ዝግጅታችንም የግቢ ጉባኤ ቆይታቸውን መሠረት አድርገን ከሕይወት ተሞክሯቸው ያካፍሉን ዘንድ ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ አበበን እንግዳችን አድርገናቸዋል፡፡ መልካም ቆይታ ይሁንላችሁ፡፡

ጉባኤ ቃና፡- ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ከመግባትዎ በፊት ለቤተ ክርስቲያን የነበረዎትን ቅርበት ቢገልጹልን?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- ተወልጄ ያደግሁት አዲስ አበባ ነው፡፡ ልጅ ሆኜ እንደማንኛውም ሕፃን እናቴ ወደ ቤተ ክርስቲያን ትወስደኝና ታስቆርበኝ ነበር፡፡ በዕድሜ ከፍ ስል ከሌላ ጊዜ በተለየ ሁኔታ የፍልሰታ ለማርያም ጾምን በጉጉት እጠብቀው ስለነበር ከሰፈር ጓደኞቼ ጋር ወደ ቤተ ክርስቲያን በመሄድ እቆርብ ነበር፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ስከታተልም ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን የረቡዕ ሠርክ እና እሑድ ከቅዳሴ በኋላ ልዩ ጉባኤ በየዐሥራ አምስት ቀኑ ይካሄድ ስለነበር ያለማቋረጥ እሳተፍ ነበር፡፡ በሠርክ ጉባኤም እየተገኘሁ በመማር ስለ እምነቴና ስለ ቤተ ክርስቲያን ለማወቅ ጥረት ከማድረግ ወደ ኋላ አላልኩም፡፡ በተለይም በወቅቱ ያስተምሩን የነበሩት መምህራን በዘመኑ ላለነው ወጣቶችና ኦርቶዶክሳውያን አርአያ ነበሩ ማለት ይቻላል፡፡ ስለዚህ ከልጅነቴ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንን ለማወቅና ስለ እምነቴ ለመረዳት የቻልኩትን አድርጌያለሁ ማለት እችላለሁ፡፡ ይህም በወጣትነት ዘመኔ ራሴን እንድገዛና በፈሪሃ እግዚአብሔር እንድታነጽ አድርጎኛል፡፡

ጉባኤ ቃና፡- የከፍተኛ ትምህርትን ለመከታተል ከቤተሰብ ርቆ መሄድ እንዴት ይገልጹታል?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- ከቤተሰብ መራቅ በራሱ አስፈሪ ያደርገዋል፡፡ ለአንዲት ቀን ከቤተሰብ ተለይቶ የማያውቅ ተማሪ በአንድ ጊዜ ወደተመደበበት ለመሄድ ሲታሰብ ከራስ አልፎ ቤተሰብ ውስጥ የሚፈጥረው ስጋት ቀላል አይደለም፡፡ በቤተሰብ በኩል ምክሮችና መመሪያዎች ይበዙብሃል፤ “እንዲህ አድርግ፣ እንዲህ ደግሞ አታደርግ” ትባላለህ፡፡ በዚህ ላይ ወጣትነት በራሱ አዲስ ነገር ለማየትና ለመሞከር ፍጥነት የሚታይበት ጊዜ ነው፡፡ ለተወሰኑ ቀናት አካባቢውን ለማጥናትና ለመልመድ ሲባል ቁጥብነት በተማሪው ዘንድ ይታያል፡፡

እኔ የተመደብኩት ጅማ ዩኒቨርሲቲ ነበር፡፡ እንደማንኛውም ተማሪ ፍርሃት ይኖራል፡፡ ነገር ግን ብዙ አልተቸገርኩም፡፡ ከእኛ ቀድመው ወደ ዩኒቨርሲቲው የገቡና የግቢ ጉባኤ ተሳታፊ የነበሩ ወንድሞችና እኅቶች አውቶቡስ ተራ ሄደው ነው የተቀበሉን፡፡ ቦርሳችንን ተሸክመው እየተንከባከቡ እግራችንን በሽሚያ አጥበው፣ አስመዘግበውን፣ ማደሪያ ክፍላችን ድረስ ወስደው ነው ያስገቡን፡፡ በዚህ እንክብካቤ ውስጥ ፍርሃት ይጠፋል፡፡ በጣም ደስ የሚል አቀባበል ነበር፡፡ አንዳንዶች ቶሎ ለመልመድ ቢቸገሩም በአብዛኛው ግን ቶሎ ይለምዳል፡፡ ስለዚህ እኔ አልተቸገርኩም ማለት እችላለሁ፡፡

ጉባኤ ቃና፡- ግቢ ጉባኤ ውስጥ መሳተፍ እንዴት ጀመሩ?

ዲ/ን ፕ/ር እንግዳ፡- ቀድሞ መርካቶ ቅዱስ ራጉኤል ቤተ ክርስቲያን ሠርክ ላይ ይሰጥ የነበረው የወንጌል ትምህርትና አገልግሎት በጣም ረድቶኛል፡፡ በተለይ በወቅቱ ያገለግሉ የነበሩ መምህራን እግር ሥር ቁጭ ብለን እንማር ስለነበር እኔም አንድ ቀን ወደ አገልግሎት እንደምገባና እንደ እነርሱ ባይሆንም የአቅሜን አበረክታለሁ የሚል ሕልም ነበረኝ፡፡ በወቅቱ በሚያገለግሉ ወንድሞቻችን ላይ በጣም መንፈሳዊ ቅናት እቀና ነበር፡፡ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ስገባ የነበረው ግቢ ጉባኤ በጣም ጠንካራና የተደራጀ ነበር፡፡ አስተባባሪዎቹም የሚመጣውን ተማሪ የሚንከባከቡበት መንገድ አስደሳች ስለነበር ገብተን መንፈሳዊውን ማዕድ ለመካፈል አልተቸገርንም፡፡ ቤተ ክርስቲያን መሄድ የምትፈልጉ ኑ እናሳያችሁ እያሉም ይወስዱን ስለነበር እኔም ከፍተኛ ፍላጎት ስለነበረኝ ለመግባት ችያለሁ፡፡  እኛን ለማቅረብና ግቢ ጉባኤ ውስጥ እንድንማር የሚያደርጉት ጥረት፣ በዚያውም እንደ አቅማችን በአገልግሎት እንድንሳተፍ ያበረታቱን ነበር:: የመጀመሪያ ዓመት ላይ በግቢ ጉባኤው አማካይነት ይሰጥ የነበረውን መንፈሳዊ ትምህርት በመማር ነው ያሳለፍኩት፡፡ መምህራኖቻችንም ቤተ ክርስቲያንን እንድንወድ፣ የጸሎት ሕይወት እንዲኖረን፣ ጊዜያችንን አጣጥመን ውጤታማ ሆነን እንድንወጣ ዘወትር ይመክሩን ነበር፡፡

ይቆየን

“ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤያት አርአያ የሚሆን ትውልድን በመቅረጽ የድርሻቸውን እየተወጣ ይገኛል”

                                                                                               አቶ አበበ በዳዳ

 (በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ኃላፊ)

ክፍል አንድ

በእንዳለ ደምስስ

ማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ጉባኤያትን በመምራትና የተቀናጀ አገልግሎት በመስጠት ላለፉት ፴፩ ዓመታት ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም አገልግሎቱ በተለይም ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ሀገርን በቅንነትና በታማኝነት የሚያገለግሉ የግቢ ጉባኤያት ፍሬዎችን ማፍራት ችሏል፡፡

ይህንን አገልግሎት ሲያከናውንም ለሚገጥሙት ችግሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየትና ችግሮቹንም በመፍታት አገልግሎቱን አጠናክሮ በሌሎችም ዘርፎች ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚጠቅሙ ሥራዎችን በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት አሁን ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችና መፍትሔዎች ምን እንደሚመስሉ ያብራሩልን ዘንድ በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ኃላፊ የሆኑትን አቶ አበበ በዳዳን እንግዳችን አድርገናል፡፡ አቶ አበበን ስለ ትብብራቸው እያመሰገንን ያደረግነውን ቆይታ ክፍል አንድ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ዋና ዋና ተግባራትን ቢገልጹልን?

አቶ አበበ፡- ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎቱን ከሚሰጥባቸው ማስተባበሪያዎች አንዱ የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ነው፡፡ ማስተባበሪያው በዋናነትም የተመሠረተበት መሠረታዊ ዓላማ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን መንፈሳዊ ትምህርት ለማስተማር ነው፡፡ ለኦርቶዶክሳውያን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መንፈሳዊ ትምህርት በመስጠት ብቁ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ታማኝና ቅንነትን የተላበሱ ኦርቶዶክሳውያን ባለሙያዎችን ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የሚያበረክት ማስተባበሪያ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ለማስተባበሪያው በዋናነት ከተሰጡት ኃላፊነቶች ጥቂቶቹን ስንመለከት፡-

፩. ማኅበረ ቅዱሳን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ከቤተሰባቸው ርቀው የሚገኙ በመሆናቸው በሚማሩበት አቅራቢያ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ሰብስቦ መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምርበት መዋቅር ነው፡፡ ይህንን ኃላፊነት ሲረከብ በዋናነት የተሠጡት ሥራዎች ግቢ ጉባኤያትን መመሥረት፣ ማደራጀት፣ ማስተማር፣ መከታተልና ማጽደቅ ድረስ ኃላፊነት አለበት፡፡

፪. ሁለንተናዊ ድጋፍ ለግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ማድረግ ሌላው ተግባሩ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የአቅም ማጎልበቻ ሥራዎችን የሥራ አስፈጻሚ አካላትን ከመምረጥ ጀምሮ አቅማቸውን የመገንባት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የመምራት፣ የሰዓት አጠቃቀማቸውን ለተፈለገው ዓላማ እንዲያውሉ፣ ዕቅድ የማቀድ፣ የታቀደውንም ተግባራዊ የማድረግ የመሳሰሉትን ያከናውናል፡፡ ሥልጠናዎችን ይሰጣል፣ ምክክሮችን ያደርጋል፣ ይመራል፣ ይከታተላል፣ ችግሮችንም በጋራ በመፍታት ላይ አተኩሮ ይሠራል፡፡

፫. አርአያ የሚሆኑ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን ማፍራት፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሆን ሥርዓተ ትምህርት ቀርጾ በሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ተመሳሳይ ዕውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት እንዲኖራቸው ለማድረግ ወጥ በሆነ መልክ እያስተማረ ይገኛል፡፡ ይህንን ሲያደርግ በዚህ የትምህርት ሂደት አልፈው የሚወጡ ተማሪዎች ለሌሎች አርአያ የሚሆኑ ማለትም በመደበኛ ትምህርታቸው ውጤታማ ሆነው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ደግሞ አርአያ ሆነው ለአገልግሎት የሚፋጠኑና ለሁሉም ምሳሌ የሚሆኑ ወጣቶችን ለማፍራት ይሠራል፡፡

፬. የፈጠራ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ የማበረታታት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በተለይም እንደ ጸጋቸው ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚጠቅሙ የምርምር ሥራዎችን በተለያዩ መስኮች በማካሄድ መሳተፍ እንዲችሉ፣ የኅብረተሰቡንም ችግር መቅረፍ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የተማረ የሰው ኃይል ማፍራትና ሂደቱንም የማመቻቸት ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡ ለምሳሌ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶች ውድድር፣ የጥናትና ምርምር፣ ዐውደ ጥናቶችን እንዲያቀርቡ ማበረታታትና እንዲሳተፉ ማመቻቸት፡፡

፭. ተተኪ አገልጋዮችን ማፍራት አንዱ የማስተባበሪያው ኃላፊነት ነው፡፡ የአብነት ትምህርትን በማስተማር፣ ነገ በሁለቱም በኩል ማለትም በዓለማዊም በመንፈሳዊም ትምህርታቸው እንዲሁም በአብነት ትምህርት የተዋጣላቸው አገልጋዮችን ከማፍራት አንጻር ኃላፊነት ወስዶ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

፮. ተተኪ አመራርና መምህራንን ማፍራት የግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ይጠቀሳል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ለተለየ ተልእኮ የሚዘጋጁ በመሆናቸው በደረጃ አንድ በማእከል ደረጃ፤ በደረጃ ሁለት እና ሦስት በዋናው ማእከል እና በማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች አማካይነት ይሰጣል፡፡ ይህ ሥልጠና ግቢ ውስጥ እያሉ ግቢ ጉባኤያትን በአግባቡ መምራት እንዲችሉ ማብቃት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ነው፡፡ በጎ ተጽእኖአቸው ከግቢ ጉባኤያትም ውጪ የሚንጸባረቅ እንዲሆን የማብቃት ተልእኮውን ይወጣል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ነው ነገ የሀገር መሪዎች፣ በየአካባቢያቸውና በተሠማሩበት የሥራ መስክ ተጽእኖ ፈጣሪዎች እንዲሆኑና በማኅበረሰቡ ውስጥ ገብተው አገልግሎት መስጠት የሚችሉ አገልጋዮችን ማፍራት የሚቻለው፣

ከመምህራን አንጻር ተተኪ መምህራንን ማኅበሩ ሲያሠለጥን መርሐ ግብራትን በመምራት፣ በግቢም ውስጥ ሆነ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲሰጡ ልምድም እንዲያዳብሩ ያደርጋል፡፡ ከዚያም አልፎ ከግቢ ከወጡ በኋላ በመንፈሳዊ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው ዕውቀታቸውን በማዳበር የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ተተኪ መምህራን ማድረግ፤

፯. ግቢ ጉባኤያት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ማለትም ከሰ/ት/ቤቶች፣ ከማኅበራት፣ ከሚማሩበት አጥቢያ አስተዳደር ጋር መልካም ግንኙነት መሥርተው ተቀናጅተው እንዲያገለግሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር አርአያነት ያለው ተግባር እንዲፈጽሙ ያበረታታል፣

፰. ዕቅድ ማቀድ፣ ትግበራን መከታተል ማስተባበሪያው ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል ይገኝበታል፡፡ በማስተባበሪያው የሚታቀዱ ዕቅዶችን መከታተል፣ ግቢ ጉኤያትን የሚመለከቱ መመሪያዎችን፣ ደንቦችን፣ የአሠራር ሰነዶችን አዘጋጅቶ በሚመለከተው አካል አጸድቆ ለግቢ ጉባኤያት የማሠራጨት ሥራ ይሠራል፡፡

፱. ተከታታይ ትምህርት (ኮርስ)፣ የጽዋ ማኅበር፣ የንስሓ አባቶችን ማዘጋጀትና ተማሪዎች በንስሓ ሕይወት እንዲመላለሱ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ተግባራዊነቱን መከታተል ነው፡፡

፲. በአሁኑ ወቅት ደግሞ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች በፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና የሀገር አስተዳደር ላይ ተልእኮ ኖሯቸው እንዲሳተፉ ለማድረግ ማብቃት፣

ተማሪዎች በዓለማዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የተሻለ ውጤት ማምጣት እንዲችሉ፤ ከእነዚህም ውስጥ ለተልእኮ የተመረጡት ለክህነት አገልግሎትና በሌሎችም እንዲሳተፉ፣ ንቁ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ አቅጣጫ የማሳየትና የመከታተል ሥራ ማስተባበሪያው ከሚያከናውናቸው ተግባራት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

እነዚህን ዋና ዋና ተግባራት  ከማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች፣ ከማእከላትና ከግቢ ጉባኤያት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት ምን ያህል ጥረት ያደረጋል?

አቶ አበበ፡- ሥራችንን ከዕቅድ ነው የምንጀምረው፡፡ ዕቅድ ከዋናው ማእከል ይጀምራል፤ የማስተባበሪያዎች፣ የማእከላትና የግቢ ጉባኤትም ዕቅዶች ከዋናው ማእከል ዕቅድ በመነሣት ይናበባሉ፤ አገልግሎቱንም ተቀናጅተን ዕቅዶችን መሠረት አድርገን እናከናውናለን፤ ወጥነት ያለው፣ የሚመዘን ዕቅድ እንዲኖረንም ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ የአብነት ትምህርት ማስተማር፣ ማስተባበርን በተመለከተ ያቅዳል፣ ለአብነት ትምህርት የሚያስፈልጉ ግብአቶችን፣ ደረጃዎችን፣ ማእቀፎችንና የአገልግሎት መመሪያዎችን ያዘጋጃል፡፡ ማእከላት ደግሞ በተዘጋጀው ዕቅድ መሠረት በትክክል ግቢ ጉባኤያት ላይ እንዲተገበር ያደርጋሉ፤ ክትትሎችም ይደረጋሉ፣ ይገመገማሉ፡፡

፪. መረጃም አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ መረጃ የተቀናጀ አገልግሎት ለመስጠት ወሳኝ በመሆኑ የተቀናጀ የመረጃ ፍሰት ልውውጥ እንዲኖር ጥረት ይደረጋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ተሳክቷል ለማለት ባይቻልም ከርቀት፣ ከአንዳንድ አካባቢዎች ነባራዊ ሁኔታዎች አንጻር የተሻለ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

፫. ግቢ ጉባኤያትን የማስተባበር ኃላፊነት የግቢ ጉባኤያት ድርሻ ነው፡፡ ነገር ግን በተሰጣቸው ኃላፊነት መሠረት ይሠራሉ ወይ የሚለውን ዋናው ማእከል ይከታተላል፤ ይገምግማል፣ አቅጣጫም በመስጠት የተሳሠረ አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡

፬. በዋናው ማእከል እነ በማስተባበሪያው አማካይነት መጻሕፍት፣ ልዩ ልዩ ትምህርቶችና የተለያዩ ጽሑፎች ይዘጋጃሉ፡፡ እነዚህ መረጃዎች /ውጤቶች/ መድረስ የሚችሉት ደግሞ በማእከላት አማካይነት ነው፡፡ በትክክል መድረሳቸውንም ክትትል ያደርጋል፡፡

፭. የመምህራንና የማስተማሪያ ቦታዎች እጥረት ለመቅረፍ ከማእከላት ጋር ተቀናጅተን እንሠራለን፡፡ በአሁኑ ወቅት የተጀመረው የመምህራን እጥረት በሚያገጥሙ ቦታዎች ለሚማሩ ተማሪዎች ቨርቹዋል (በኢተርኔት) አማካይነት በመገናኘት መምህራን ከዋናው ማእከል ሆነው ተማሪዎች ካሉበት የማስተማርና የማሠልጠን አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በተለይም በውጪ ሀገራት ለሚገኙ ፳፫ ግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ተደራሽ እየተደረገ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ላሉት ግቢ ጉባኤያትም መምህራን እየተላኩ ተከታታይ ትምህርቶችን፣ ሥልጠናዎችን ይሰጣሉ፡፡ ይህም ከማእከላትና ከግቢ ጉባኤያት ጋር ተቀናጅተን የምንሠራው ነው፡፡

ማስተባበሪያው ግቢ ጉባኤያትን ከመምራትና ከማስተማሩ አንጻር የሚያጋጥሙት ችግሮች ምን ምን ናቸው? ለመፍታትስ ምን ጥረቶች ይደረጋሉ?

አቶ አበበ፡- የግቢ ጉባኤያት ቁጥር በተለይም ከ፲፱፻፺፭ ዓ.ም ወዲህ በርካታ የመንግሥትና የግል ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች መቃቋምን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡

እስከ ፲፱፻፺፭ ዓ.ም ድረስ ተማሪዎችን ስናስተምር የነበረው ያለ ሥርዓተ ትምህርት (Curricullum) ነበር፡፡ ይህንን ችግር ወጥ በሆነ መልኩ ለመፍታት ከ፲፱፻፺፮ ዓ.ም ጀምሮ ሥርዓተ ትምህርት በማዘጋጀት በሁሉም ግቢ ጉባኤያት ወጥነት ያለው ትምህርት መስጠት ተጀመረ፡፡ ትምህርቱንም ለማስተማር የሰው ኃይል (መምህራን) ያስፈልጋሉ፡፡ ትልቁ ችግር የሆነው የመምህራን እጥረት ነው፡፡ አሁንም ድረስ ጎልተው ከሚታዩ ችግሮች መካከል የመምህራን እጥረት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ያሉት መምህራን የዝግጅትና የአቅም ማነስ እያጋጠመን ይገኛል፡፡ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ያሉትን መምህራን ለተጨማሪ ዕውቀት ማሠልጠን፣ ተተኪ መምህራንን ማፍራት፣ ከማኅበራትና ከሰ/ት/ቤቶች ጋር ተባብሮ በመሥራት የመምህራንን ችግር ለመቅረፍ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡

የሰው ኃይልን በተመለከተ የማእከላት መደበኛ አገልጋዮች እጥረት መኖር እንደ ችግር ሲፈትነን የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ በአብዛኛው በኢመደበኛ (በትርፍ ጊዜያቸውየሚያገለግሉ ወንድሞችና እኅቶች) የሚሸፈን በመሆኑ ከፍተቶች ይፈጠራሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ዋናው ማእከል ላይ ያለው አገልጋይ ከማእከላት አገልጋይ ጋር ለመገናኘት ሲፈለግ በምንፈልጋቸው ሰዓት ላናገኛቸው ስለምንችል የምንፈለገውን መረጃ በጊዜው ያለማግኘት ችግር ይገጥማል፡፡ በዚህም መሠረት አቅም ያላቸው አገልጋዮችን ለማግኘት ስንቸገር ቆይተናል፡፡

ሌላው እንደ ችግር የሚፈትነን በአብዛኛው የመንግሥትም ሆነ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን የሚያስመርቁት በሦስት ዓመት ነው፡፡ አንድ ተማሪ ለተተኪ መምህርነት ከደረጃ አንድ እሰከ ሦስት ያለውን በመሠልጠኑ ለሥራ በተመደበበት አካባቢ ባለው ግቢ ጉባኤ ከእርሱ በላይ ያሉትን ማለትም አምስት እና ሰባት ዓመት የሚቆዩትን ያስተባብራል፡፡ በዚህም ምክንያት ግቢ ጉባኤውን የመምራትና የማስተባበር አቅም ያጥረዋል፡፡

በወቅታዊ ሀገራዊ ግጭቶች እንዲሁም ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የትምህርት አሰጣጣችን የመዛባት ችግር ገጥሞታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአንዳንድ ግጭት ባጋጠማቸው አካባቢዎች አገልገሎት እስከ መቋረጥ የደረሰበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ተማሪዎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ በመሆናቸው በቤተሰባቸው መፈናቀል ምክንያት የትምህርት ሂደታችንን ሲያደናቅፍብን ይታያል፡፡

የተዛባውንም ትምህርት ለመስጠት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቅዳሜና እሑድ ጨምሮ የማካካሻ ትምህርት ስለሚሰጡ ለግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች የጊዜ እጥረት ስለሚገጥማቸው ተከታታይ ትምህርት ለመስጠት አዳጋች አድርጎታል፡፡

አንዳንድ ማኅበራት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ካባ ለብሰው “እኛ ነን የምናስተምራችሁ” እያሉ ከግቢ ጉባኤያት የማስኮብለልና በግዳጅ ለማስተማር የሚጥሩ አካላት አሉ፡፡ ልጆቹንም ወስደው ሳያስጨርሷቸው ይበትኗቸዋል፡፡ ይህ አካሄድ አገልግሎቱን እየፈተነ ይገኛል፡፡ በተለይም አንዳንድ ሀገረ ስብከት ውስጥ ባሉ ኃላፊዎች ደብዳቤ ጽፈው ለሚፈልጉት አካል ግቢ ጉባኤን እንዲያስተምር ፈቃድ ይሰጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ በተማሪዎችና በተምሮ ማስተማሩ ላይ መከፋፈልን እየፈጠረ ይገኛል፡፡

ግቢ ጉባኤትን እንዲያስተምር በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የተሰጠው ማኅበረ ቅዱሳን ሆኖ ሳለ እኛ ነን በማለት ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ሲመሩት እንመለከታለን፡፡ አንድ ተቋም ውስጥ የተለያዩ ግቢ ጉባኤት እንዲኖሩ የመፈለግና የመበተን ዓላማ ያላቸው አካላት አሉ፤ ይህ ደግሞ ከጀርባው የፖለቲካ ተጽእኖ እንዳለው ያመለክታል፡፡

በማስተባበሪያ ደረጃ ገቢ እያስገኘ መልሶ ለግቢ ጉባኤት አገልግሎት እንዲያውሉት የማድረግ ኃላፊነት ላይ የልምድ ማነስና የሰው ኃይል እጥረት ክፍተቶች ጎልተው ይታዩብናል፡፡ እነዚህንና ሌሎችም እንደ ተግዳሮት የሚነሡ ናቸው፡፡

ማስታወሻ፡- ከአቶ አበበ በዳዳ በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልገሎት ማስተባበሪያ ኃላፊ ጋር ያደረግነው ቆይታ አልተጠናቀቀም፡፡ በክፍል ሁለት እንመለሳለን፡፡

ይቆየን፡፡

ዕቅድ ከክንውን የተስማሙለት ግቢ ጉባኤ

በዲ/ን ቴዎድሮስ ኃይሉ

ጊዜው ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ሲሆን በወቅቱ የነበሩ ተማሪዎቹ ሰፊ የሆነ መርሐ ግብር እና የመሰበሰቢያ አዳራሽ ስለሌላቸው መርሐ ግብራቸውን ፀሐይና ዝናብ እየተፈራረቁባቸው፣ ዛሬ አዳራሹ ተሠርቶ ከሚገኝበት ቦታ በነበሩ ዛፎች ጥላ ሥር ያካሒዱ ነበር፡፡ ይህን የተቀደሰ ተግባር በደብረ ማርቆስ ከተማ የሚገኘው የማኅበረ ቅዱሳን ጽ/ቤት ያበረታታ፤ ይደግፍ ነበር፡፡ እግዚአብሔር ሲፈቅድ፤ የተማሪዎቹና የማእከሉ ጥረት ተሳክቶ ተቋሙ ከተመሠረተ ከስድስት ወር በኋላ የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ጉባኤ ተብሎ፣ በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት መዋቅር ውስጥ ታቅፎ የካቲት ፲፮ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓ.ም አገልግሎቱን በተጠናከረ መንገድ ጀመረ፡፡ በምሥረታው ዕለት በተቋሙ ከሚገኙ ፯፻፷ ተማሪዎች መካከል ፭፻፴፮ ተማሪዎች ተገኝተዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ፳፻፣ በ፳፻፩ እና በ፳፻፪ ዓ.ም ተማሪዎችን የመቀበል ዐቅሙ እያሳዳደገ በመሔዱ፣ ግቢ ጉባኤውም አገልግሎቱን አሰፋ፤ በተለይ የቴክኖሎጂ ተማሪዎችን ተቋሙ ሲቀበል የግቢ ጉባኤው አገልግሎት ይበልጥ እየጎለበት መጣ፡፡ Read more