“ማኅበረ ቅዱሳን በግቢ ጉባኤያት አርአያ የሚሆን ትውልድን በመቅረጽ የድርሻቸውን እየተወጣ ይገኛል”

                                                                                               አቶ አበበ በዳዳ

 (በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ኃላፊ)

ክፍል አንድ

በእንዳለ ደምስስ

ማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ጉባኤያትን በመምራትና የተቀናጀ አገልግሎት በመስጠት ላለፉት ፴፩ ዓመታት ጥረቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ በዚህም አገልግሎቱ በተለይም ራሳቸውን፣ ቤተሰባቸውን፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ሀገርን በቅንነትና በታማኝነት የሚያገለግሉ የግቢ ጉባኤያት ፍሬዎችን ማፍራት ችሏል፡፡

ይህንን አገልግሎት ሲያከናውንም ለሚገጥሙት ችግሮች ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመወያየትና ችግሮቹንም በመፍታት አገልግሎቱን አጠናክሮ በሌሎችም ዘርፎች ለቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚጠቅሙ ሥራዎችን በማበርከት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም መሠረት የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት አሁን ያለበትን ነባራዊ ሁኔታ፣ የሚያጋጥሙ ችግሮችና መፍትሔዎች ምን እንደሚመስሉ ያብራሩልን ዘንድ በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ኃላፊ የሆኑትን አቶ አበበ በዳዳን እንግዳችን አድርገናል፡፡ አቶ አበበን ስለ ትብብራቸው እያመሰገንን ያደረግነውን ቆይታ ክፍል አንድ እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡

የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ዋና ዋና ተግባራትን ቢገልጹልን?

አቶ አበበ፡- ማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎቱን ከሚሰጥባቸው ማስተባበሪያዎች አንዱ የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ነው፡፡ ማስተባበሪያው በዋናነትም የተመሠረተበት መሠረታዊ ዓላማ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን መንፈሳዊ ትምህርት ለማስተማር ነው፡፡ ለኦርቶዶክሳውያን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች መንፈሳዊ ትምህርት በመስጠት ብቁ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ታማኝና ቅንነትን የተላበሱ ኦርቶዶክሳውያን ባለሙያዎችን ለሀገርና ለቤተ ክርስቲያን የሚያበረክት ማስተባበሪያ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ለማስተባበሪያው በዋናነት ከተሰጡት ኃላፊነቶች ጥቂቶቹን ስንመለከት፡-

፩. ማኅበረ ቅዱሳን በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያሉ ኦርቶዶክሳውያን ተማሪዎች ከቤተሰባቸው ርቀው የሚገኙ በመሆናቸው በሚማሩበት አቅራቢያ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ሰብስቦ መንፈሳዊ ትምህርት የሚያስተምርበት መዋቅር ነው፡፡ ይህንን ኃላፊነት ሲረከብ በዋናነት የተሠጡት ሥራዎች ግቢ ጉባኤያትን መመሥረት፣ ማደራጀት፣ ማስተማር፣ መከታተልና ማጽደቅ ድረስ ኃላፊነት አለበት፡፡

፪. ሁለንተናዊ ድጋፍ ለግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ማድረግ ሌላው ተግባሩ ነው፡፡ በዚህም መሠረት የአቅም ማጎልበቻ ሥራዎችን የሥራ አስፈጻሚ አካላትን ከመምረጥ ጀምሮ አቅማቸውን የመገንባት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የመምራት፣ የሰዓት አጠቃቀማቸውን ለተፈለገው ዓላማ እንዲያውሉ፣ ዕቅድ የማቀድ፣ የታቀደውንም ተግባራዊ የማድረግ የመሳሰሉትን ያከናውናል፡፡ ሥልጠናዎችን ይሰጣል፣ ምክክሮችን ያደርጋል፣ ይመራል፣ ይከታተላል፣ ችግሮችንም በጋራ በመፍታት ላይ አተኩሮ ይሠራል፡፡

፫. አርአያ የሚሆኑ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን ማፍራት፡፡ ማኅበረ ቅዱሳን ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሆን ሥርዓተ ትምህርት ቀርጾ በሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ተመሳሳይ ዕውቀት፣ ክህሎትና አመለካከት እንዲኖራቸው ለማድረግ ወጥ በሆነ መልክ እያስተማረ ይገኛል፡፡ ይህንን ሲያደርግ በዚህ የትምህርት ሂደት አልፈው የሚወጡ ተማሪዎች ለሌሎች አርአያ የሚሆኑ ማለትም በመደበኛ ትምህርታቸው ውጤታማ ሆነው በመንፈሳዊ ሕይወታቸው ደግሞ አርአያ ሆነው ለአገልግሎት የሚፋጠኑና ለሁሉም ምሳሌ የሚሆኑ ወጣቶችን ለማፍራት ይሠራል፡፡

፬. የፈጠራ ሥራ ላይ እንዲሳተፉ የማበረታታት አገልግሎት ይሰጣል፡፡ በተለይም እንደ ጸጋቸው ለቤተ ክርስቲያንና ለሀገር የሚጠቅሙ የምርምር ሥራዎችን በተለያዩ መስኮች በማካሄድ መሳተፍ እንዲችሉ፣ የኅብረተሰቡንም ችግር መቅረፍ የሚችሉ የፈጠራ ሥራዎችን በመሥራት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የተማረ የሰው ኃይል ማፍራትና ሂደቱንም የማመቻቸት ኃላፊነቱን ይወጣል፡፡ ለምሳሌ የተለያዩ የፈጠራ ውጤቶች ውድድር፣ የጥናትና ምርምር፣ ዐውደ ጥናቶችን እንዲያቀርቡ ማበረታታትና እንዲሳተፉ ማመቻቸት፡፡

፭. ተተኪ አገልጋዮችን ማፍራት አንዱ የማስተባበሪያው ኃላፊነት ነው፡፡ የአብነት ትምህርትን በማስተማር፣ ነገ በሁለቱም በኩል ማለትም በዓለማዊም በመንፈሳዊም ትምህርታቸው እንዲሁም በአብነት ትምህርት የተዋጣላቸው አገልጋዮችን ከማፍራት አንጻር ኃላፊነት ወስዶ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡

፮. ተተኪ አመራርና መምህራንን ማፍራት የግቢ ጉባኤያት ማስተባበሪያ ከሚያከናውናቸው ተግባራት መካከል ይጠቀሳል፡፡ እነዚህ ተማሪዎች ለተለየ ተልእኮ የሚዘጋጁ በመሆናቸው በደረጃ አንድ በማእከል ደረጃ፤ በደረጃ ሁለት እና ሦስት በዋናው ማእከል እና በማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች አማካይነት ይሰጣል፡፡ ይህ ሥልጠና ግቢ ውስጥ እያሉ ግቢ ጉባኤያትን በአግባቡ መምራት እንዲችሉ ማብቃት ላይ ያተኮረ ሥልጠና ነው፡፡ በጎ ተጽእኖአቸው ከግቢ ጉባኤያትም ውጪ የሚንጸባረቅ እንዲሆን የማብቃት ተልእኮውን ይወጣል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ነው ነገ የሀገር መሪዎች፣ በየአካባቢያቸውና በተሠማሩበት የሥራ መስክ ተጽእኖ ፈጣሪዎች እንዲሆኑና በማኅበረሰቡ ውስጥ ገብተው አገልግሎት መስጠት የሚችሉ አገልጋዮችን ማፍራት የሚቻለው፣

ከመምህራን አንጻር ተተኪ መምህራንን ማኅበሩ ሲያሠለጥን መርሐ ግብራትን በመምራት፣ በግቢም ውስጥ ሆነ በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት የስብከተ ወንጌል አገልግሎት እንዲሰጡ ልምድም እንዲያዳብሩ ያደርጋል፡፡ ከዚያም አልፎ ከግቢ ከወጡ በኋላ በመንፈሳዊ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ገብተው ዕውቀታቸውን በማዳበር የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችና ተተኪ መምህራን ማድረግ፤

፯. ግቢ ጉባኤያት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር ማለትም ከሰ/ት/ቤቶች፣ ከማኅበራት፣ ከሚማሩበት አጥቢያ አስተዳደር ጋር መልካም ግንኙነት መሥርተው ተቀናጅተው እንዲያገለግሉ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር አርአያነት ያለው ተግባር እንዲፈጽሙ ያበረታታል፣

፰. ዕቅድ ማቀድ፣ ትግበራን መከታተል ማስተባበሪያው ከሚሠራቸው ሥራዎች መካከል ይገኝበታል፡፡ በማስተባበሪያው የሚታቀዱ ዕቅዶችን መከታተል፣ ግቢ ጉኤያትን የሚመለከቱ መመሪያዎችን፣ ደንቦችን፣ የአሠራር ሰነዶችን አዘጋጅቶ በሚመለከተው አካል አጸድቆ ለግቢ ጉባኤያት የማሠራጨት ሥራ ይሠራል፡፡

፱. ተከታታይ ትምህርት (ኮርስ)፣ የጽዋ ማኅበር፣ የንስሓ አባቶችን ማዘጋጀትና ተማሪዎች በንስሓ ሕይወት እንዲመላለሱ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ተግባራዊነቱን መከታተል ነው፡፡

፲. በአሁኑ ወቅት ደግሞ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች በፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ ኢኮኖሚያዊና የሀገር አስተዳደር ላይ ተልእኮ ኖሯቸው እንዲሳተፉ ለማድረግ ማብቃት፣

ተማሪዎች በዓለማዊም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የተሻለ ውጤት ማምጣት እንዲችሉ፤ ከእነዚህም ውስጥ ለተልእኮ የተመረጡት ለክህነት አገልግሎትና በሌሎችም እንዲሳተፉ፣ ንቁ ተሳታፊዎች እንዲሆኑ አቅጣጫ የማሳየትና የመከታተል ሥራ ማስተባበሪያው ከሚያከናውናቸው ተግባራት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

እነዚህን ዋና ዋና ተግባራት  ከማስተባበሪያ ጽ/ቤቶች፣ ከማእከላትና ከግቢ ጉባኤያት ጋር ተቀናጅቶ ለመሥራት ምን ያህል ጥረት ያደረጋል?

አቶ አበበ፡- ሥራችንን ከዕቅድ ነው የምንጀምረው፡፡ ዕቅድ ከዋናው ማእከል ይጀምራል፤ የማስተባበሪያዎች፣ የማእከላትና የግቢ ጉባኤትም ዕቅዶች ከዋናው ማእከል ዕቅድ በመነሣት ይናበባሉ፤ አገልግሎቱንም ተቀናጅተን ዕቅዶችን መሠረት አድርገን እናከናውናለን፤ ወጥነት ያለው፣ የሚመዘን ዕቅድ እንዲኖረንም ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ የአብነት ትምህርት ማስተማር፣ ማስተባበርን በተመለከተ ያቅዳል፣ ለአብነት ትምህርት የሚያስፈልጉ ግብአቶችን፣ ደረጃዎችን፣ ማእቀፎችንና የአገልግሎት መመሪያዎችን ያዘጋጃል፡፡ ማእከላት ደግሞ በተዘጋጀው ዕቅድ መሠረት በትክክል ግቢ ጉባኤያት ላይ እንዲተገበር ያደርጋሉ፤ ክትትሎችም ይደረጋሉ፣ ይገመገማሉ፡፡

፪. መረጃም አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡ መረጃ የተቀናጀ አገልግሎት ለመስጠት ወሳኝ በመሆኑ የተቀናጀ የመረጃ ፍሰት ልውውጥ እንዲኖር ጥረት ይደረጋል፡፡ ሙሉ ለሙሉ ተሳክቷል ለማለት ባይቻልም ከርቀት፣ ከአንዳንድ አካባቢዎች ነባራዊ ሁኔታዎች አንጻር የተሻለ ሥራ ሲሠራ ቆይቷል፡፡

፫. ግቢ ጉባኤያትን የማስተባበር ኃላፊነት የግቢ ጉባኤያት ድርሻ ነው፡፡ ነገር ግን በተሰጣቸው ኃላፊነት መሠረት ይሠራሉ ወይ የሚለውን ዋናው ማእከል ይከታተላል፤ ይገምግማል፣ አቅጣጫም በመስጠት የተሳሠረ አገልግሎት እንዲሰጥ ይደረጋል፡፡

፬. በዋናው ማእከል እነ በማስተባበሪያው አማካይነት መጻሕፍት፣ ልዩ ልዩ ትምህርቶችና የተለያዩ ጽሑፎች ይዘጋጃሉ፡፡ እነዚህ መረጃዎች /ውጤቶች/ መድረስ የሚችሉት ደግሞ በማእከላት አማካይነት ነው፡፡ በትክክል መድረሳቸውንም ክትትል ያደርጋል፡፡

፭. የመምህራንና የማስተማሪያ ቦታዎች እጥረት ለመቅረፍ ከማእከላት ጋር ተቀናጅተን እንሠራለን፡፡ በአሁኑ ወቅት የተጀመረው የመምህራን እጥረት በሚያገጥሙ ቦታዎች ለሚማሩ ተማሪዎች ቨርቹዋል (በኢተርኔት) አማካይነት በመገናኘት መምህራን ከዋናው ማእከል ሆነው ተማሪዎች ካሉበት የማስተማርና የማሠልጠን አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል፡፡ በተለይም በውጪ ሀገራት ለሚገኙ ፳፫ ግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ተደራሽ እየተደረገ ነው፡፡ በሀገር ውስጥ ላሉት ግቢ ጉባኤያትም መምህራን እየተላኩ ተከታታይ ትምህርቶችን፣ ሥልጠናዎችን ይሰጣሉ፡፡ ይህም ከማእከላትና ከግቢ ጉባኤያት ጋር ተቀናጅተን የምንሠራው ነው፡፡

ማስተባበሪያው ግቢ ጉባኤያትን ከመምራትና ከማስተማሩ አንጻር የሚያጋጥሙት ችግሮች ምን ምን ናቸው? ለመፍታትስ ምን ጥረቶች ይደረጋሉ?

አቶ አበበ፡- የግቢ ጉባኤያት ቁጥር በተለይም ከ፲፱፻፺፭ ዓ.ም ወዲህ በርካታ የመንግሥትና የግል ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች መቃቋምን ተከትሎ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡

እስከ ፲፱፻፺፭ ዓ.ም ድረስ ተማሪዎችን ስናስተምር የነበረው ያለ ሥርዓተ ትምህርት (Curricullum) ነበር፡፡ ይህንን ችግር ወጥ በሆነ መልኩ ለመፍታት ከ፲፱፻፺፮ ዓ.ም ጀምሮ ሥርዓተ ትምህርት በማዘጋጀት በሁሉም ግቢ ጉባኤያት ወጥነት ያለው ትምህርት መስጠት ተጀመረ፡፡ ትምህርቱንም ለማስተማር የሰው ኃይል (መምህራን) ያስፈልጋሉ፡፡ ትልቁ ችግር የሆነው የመምህራን እጥረት ነው፡፡ አሁንም ድረስ ጎልተው ከሚታዩ ችግሮች መካከል የመምህራን እጥረት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ያሉት መምህራን የዝግጅትና የአቅም ማነስ እያጋጠመን ይገኛል፡፡ ይህንንም ችግር ለመቅረፍ ያሉትን መምህራን ለተጨማሪ ዕውቀት ማሠልጠን፣ ተተኪ መምህራንን ማፍራት፣ ከማኅበራትና ከሰ/ት/ቤቶች ጋር ተባብሮ በመሥራት የመምህራንን ችግር ለመቅረፍ ጥረት ሲደረግ ቆይቷል፡፡

የሰው ኃይልን በተመለከተ የማእከላት መደበኛ አገልጋዮች እጥረት መኖር እንደ ችግር ሲፈትነን የቆየ ጉዳይ ነው፡፡ በአብዛኛው በኢመደበኛ (በትርፍ ጊዜያቸውየሚያገለግሉ ወንድሞችና እኅቶች) የሚሸፈን በመሆኑ ከፍተቶች ይፈጠራሉ፡፡ ሌላው ደግሞ ዋናው ማእከል ላይ ያለው አገልጋይ ከማእከላት አገልጋይ ጋር ለመገናኘት ሲፈለግ በምንፈልጋቸው ሰዓት ላናገኛቸው ስለምንችል የምንፈለገውን መረጃ በጊዜው ያለማግኘት ችግር ይገጥማል፡፡ በዚህም መሠረት አቅም ያላቸው አገልጋዮችን ለማግኘት ስንቸገር ቆይተናል፡፡

ሌላው እንደ ችግር የሚፈትነን በአብዛኛው የመንግሥትም ሆነ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችን የሚያስመርቁት በሦስት ዓመት ነው፡፡ አንድ ተማሪ ለተተኪ መምህርነት ከደረጃ አንድ እሰከ ሦስት ያለውን በመሠልጠኑ ለሥራ በተመደበበት አካባቢ ባለው ግቢ ጉባኤ ከእርሱ በላይ ያሉትን ማለትም አምስት እና ሰባት ዓመት የሚቆዩትን ያስተባብራል፡፡ በዚህም ምክንያት ግቢ ጉባኤውን የመምራትና የማስተባበር አቅም ያጥረዋል፡፡

በወቅታዊ ሀገራዊ ግጭቶች እንዲሁም ከኮቪድ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ የትምህርት አሰጣጣችን የመዛባት ችግር ገጥሞታል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ በአንዳንድ ግጭት ባጋጠማቸው አካባቢዎች አገልገሎት እስከ መቋረጥ የደረሰበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ተማሪዎች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚመጡ በመሆናቸው በቤተሰባቸው መፈናቀል ምክንያት የትምህርት ሂደታችንን ሲያደናቅፍብን ይታያል፡፡

የተዛባውንም ትምህርት ለመስጠት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቅዳሜና እሑድ ጨምሮ የማካካሻ ትምህርት ስለሚሰጡ ለግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች የጊዜ እጥረት ስለሚገጥማቸው ተከታታይ ትምህርት ለመስጠት አዳጋች አድርጎታል፡፡

አንዳንድ ማኅበራት የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ካባ ለብሰው “እኛ ነን የምናስተምራችሁ” እያሉ ከግቢ ጉባኤያት የማስኮብለልና በግዳጅ ለማስተማር የሚጥሩ አካላት አሉ፡፡ ልጆቹንም ወስደው ሳያስጨርሷቸው ይበትኗቸዋል፡፡ ይህ አካሄድ አገልግሎቱን እየፈተነ ይገኛል፡፡ በተለይም አንዳንድ ሀገረ ስብከት ውስጥ ባሉ ኃላፊዎች ደብዳቤ ጽፈው ለሚፈልጉት አካል ግቢ ጉባኤን እንዲያስተምር ፈቃድ ይሰጣሉ፡፡ ይህ ደግሞ በተማሪዎችና በተምሮ ማስተማሩ ላይ መከፋፈልን እየፈጠረ ይገኛል፡፡

ግቢ ጉባኤትን እንዲያስተምር በቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ የተሰጠው ማኅበረ ቅዱሳን ሆኖ ሳለ እኛ ነን በማለት ወደ አልተፈለገ አቅጣጫ ሲመሩት እንመለከታለን፡፡ አንድ ተቋም ውስጥ የተለያዩ ግቢ ጉባኤት እንዲኖሩ የመፈለግና የመበተን ዓላማ ያላቸው አካላት አሉ፤ ይህ ደግሞ ከጀርባው የፖለቲካ ተጽእኖ እንዳለው ያመለክታል፡፡

በማስተባበሪያ ደረጃ ገቢ እያስገኘ መልሶ ለግቢ ጉባኤት አገልግሎት እንዲያውሉት የማድረግ ኃላፊነት ላይ የልምድ ማነስና የሰው ኃይል እጥረት ክፍተቶች ጎልተው ይታዩብናል፡፡ እነዚህንና ሌሎችም እንደ ተግዳሮት የሚነሡ ናቸው፡፡

ማስታወሻ፡- ከአቶ አበበ በዳዳ በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልገሎት ማስተባበሪያ ኃላፊ ጋር ያደረግነው ቆይታ አልተጠናቀቀም፡፡ በክፍል ሁለት እንመለሳለን፡፡

ይቆየን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *