ስለ ማኅበረ ቅዱሳን መሠረታዊ መረጃዎች
የማኅበሩ ስያሜ
አንዳንድ ሰዎች የማኅበሩ አባላት ለራሳቸው ያወጡት አስመስለው የሚነግሯቸው ሰዎች አሉና ስያሜውም ግራ ያጋባቸዋል፡፡ ነገር ግን የማኅበሩ ስያሜ እኩያኑ ማኅበሩን ለማጥላላት ከሚናገሩት በእጅጉ የተለየ ነው፡፡ ማኅበረ ሚካኤል «የሚካኤሎች ስብስብ»፣ ማኅበረ ማርያምም «የማርያሞች ስብስብ» እንዳልሆነ ማኅበረ ቅዱሳንም «የቅዱሳን ሰብስብ» አይደለም፡፡ ወይም ማኅበረ ጊዮርጊስን የመሠረቱ ሰዎች ራሳቸውን «ጊዮርጊሶች»ነን እንደማይሉት፤ እንዳልሆኑትም፣ ማኅበረ ቅዱሳንም ቅዱሳን ነን የሚሉ ሰዎች ስብስብ አይደለም፡፡ ይልቁንም ማኅበረ ማካኤል የሊቀ መላእክት የቅዱስ ሚካኤል አማላጅነት፣ ተራዳኢነት የሚታሰብበት ማኅበር እንደሆነው ሁሉ ማኅበረ ቅዱሳንም የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርተ ሃይማኖትና ሥርዐት ከመጠበቅና ከማስተማር በተጨማሪ በቤተ ክርስቲያኒቱ ትምህርተ ሃይማኖት መሠረት የቅዱሳን ጻድቃንና ሰማዕታት እንዲሁም የቅዱሳን መላእክት ክብራቸው፤ ገድላቸውና ትሩፋታቸው፣ አማላጅነታቸውና በረከታቸው የሚታሰቡበት ማኅበር ነው፡፡ ምእመናን በቅዱሳን አማላጅነትና ረድኤት እየታገዙ ለመንግሥተ ሰማያት እንዲበቁ ማስተማርም ቀዳሚ ተግባሩ ነው፡፡
በአጠቃላይ ማኅበረ ቅዱሳን እግዚአብሔር ያከበራቸው የነቢያት፣ የሐዋርያት፣ የጻድቃንና የሰማዕታት በአጠቃላይ የቅዱሳን ገድል፣ ትሩፋትና አማላጅነት የሚዘከርበት በመሆኑ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳን›› የሚል ስያሜውን አግኝቷል፡፡
የማኅበሩ ርእይ
ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓለም አቀፍ የወንጌል አገልግሎቷ ተስፋፍቶ፣ በመልካም አስተዳደር ምሳሌ ሆና በፈተና ጊዜ ሁሉ በማንነቷ የጸናች እና ልዕልናዋን በሁለንተናው የምታስጠብቅ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ማየት ነው፡፡
የማኅበሩ ተልእኮ
ማኅበሩ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ውጤት የሆኑትን የተለያዩ ትምህርተ ሃይማኖት ማስፋፊያ ዘዴዎችን በመጠቀም ግቢ ጉባኤያትና ምእመናን የወንጌልን ትምህርት፣ ሥርዓት፣ ትውፊት እንዲያውቁና እንዲጠብቁ፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር እንዲጠናከርና አቅሙ እንዲያድግ ማድረግና በየዘመኑ የሚከሰቱ ተለዋዋጭ ሃይማኖታዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ችግሮችን በመቃኘት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሐዋርያዊ አገልግሎት ማጠናከር፡፡
የማኅበሩ አስፈላጊነት
የቤተ ክርስቲያቱ መዋቅር ያልሸፈናቸውን ክፍተቶች በመሙላት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚገባውን የዘመኑን ትውልድ ከመንፈሳዊነትና ከቅድስት ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ጋር በማዋሐድና ከአበው በማቀራረብ ቤተ ክርስቲያን የምትጠብቅበትን ድርሻ እንዲወጣ ለማድረግ የማኅበረ ቅዱሳን አገልግሎት አስፈላጊ ነው፡፡
የማኅበሩ ዓላማዎች
ማኅበሩ ከዚህ ቀጥሎ የተዘረዘሩት ዐበይት ዓላማች አሉት፡፡
- በከፍተኛ ትምህርት ተቋማ ውስጥ የሚማሩ ወጣቶችን በማኅበሩ ሥር አደራጅቶ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን እምነት፣ ሥርዓት እና ትውፊት እንዲማሩ እና የአባቶች ተተኪ እንዲሆኑ ማድረግ፣
- የቤተ ክርስቲያን እምነትና ሥርዓት ሳይለወጥ ተጠብቆ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ይቻል ዘንድ ለዘመኑ ትውልድ ትምህርተ ሃይማኖት እንዲዳረስ ማድረግ፣
- ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አካላት ጋር በመነጋገርና በማስፈቀድ ትምህርተ ወንጌልን በተለያዩ ዘዴዎች በመጽሔት፣ በጋዜጣ፣ በበራሪ ጽሑፎች፣ በካሴት እና በመሳሰሉት እንዲስፋፋ ማድረግ፣
- የተማረው የኅብረተሰብ ክፍል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በገንዘቡ፣ በዕውቀቱና በጉልበቱ እንዲያገለግል አስፈላጊውን ሁሉ ማመቻቸት፣
- ስለ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥናት የሚያደርጉ ሰዎችን በተለይ ወጣት ምሁራንን ማበረታታትና በሚቻለው ሁሉ መርዳት
የማኅበሩ አቋም
በማንኛውም የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውስጥ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት የለውም፡፡
አመሠራረት /ማኅበረ ቅዱሳን እንዴትስ ተመሠረተ?/
ዘመኑ የኮምዩኒዝም ርዕዮተ ዓለምና አስተሳሰብ የሰፈነበት፤ ስመ እግዚአብሔርን መጥራት አስቸጋሪ የሆነበትና ወደ ቤተ እግዚአብሔር መሔድ እንደ ኋላቀርነት የሚቆጠርበት ዘመን ነበር 1977 ዓ.ም፡፡ በተለይም በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱ በሚገኙ ተማሪዎች ዘንድ ቃለ እግዚአብሔርን በግልጽ መነጋገርም ሆነ መስማት የማይታሰብበት ወቅት ነበር፡፡ ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለይም በንጉሠ ነገሥት ዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥት በዩኒቨርሲቲና ኮሌጆች እንዲያስተምሩ ከምዕራባውያኑ ሀገሮች መጥተው የነበሩ ሚሲዮናውያን የኑፋቄ ትምህርታቸውን ያሠራጩ የነበረውም በእነዚሁ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ነበር፡፡ በዚህ ሁኔታ ትውልዱ በየአቅጣጫው በሚሲዮናውያኑ የኑፋቄ ትምህርት እንዲሁም በኮምዩኒዝም ርዕዮተ ዓለምና አስተሳሰብ እየተነጠቀ ከኦርቶዶከሳዊት ተዋሕዶ እምነት የኮበለለበት ዘመን ነበር፡፡
በዚህ ጊዜ ነው፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ ዋናው ግቢ ከፍተኛ ትምህርታቸውን ይከታተሉ የነበሩ አምስት ወጣቶች ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ በቅዱስ ገብርኤል ስም ተሰባስበው ጽዋ መጠጣት የጀመሩት፡፡ በመቀጠልም በየሳምንቱ እሑድ በመንበረ ፓትርያርክ ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ቤተ ክርስቲያን ግቢ በመጠለያ ሥር እየተሰባሰቡ በተደራጀ መልክ ባይሆንም መንፈሳዊ ትምህርት ይማሩ ጀመር፡፡ ከዚያም በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ተምሮ ማስተማር ሰንበት ትምህርት ቤት አዳራሽ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን መንፈሳዊ ትምህርት መማር ቀጠሉ፡፡
እንዲህ የተጀመረው መንፈሳዊ እንቅስቃሴ በሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሚገኙ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ዘንድ በተለያዩ አጋጣሚዎችና ሁኔታዎች በፈቃደ እግዚአብሔር መስፋፋት ቀጠለ፡፡
በ1977 ዓ.ም በነበረው የመንግሥት ሠፈራ ፕሮግራም በሀገሪቱ ውስጥ ያሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በሙሉ በመንደር ምሥረታና መልሶ ማቋቋም ዘመቻ ወደ ጋምቤላ፣ መተከል እና ፓዌ እንዲዘምቱ ሲደረግ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ቃለ እግዚአብሔርን በመማር፣ በማኅበር ጸሎት በማድረግ እና ስለቤ ተክርስቲያን ጉዳይ በመወያየት ጊዜውን ተጠቀሙበት፡፡
ከዘመቻው መልስ በ1978 ዓ.ም አገልግሎቱን በማጠናከር ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስድስት ኪሎ፣ አምስት ኪሎ፣ አራት ኪሎ ግቢዎች እስከ አርባ የሚደርሱ ተማሪዎች በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ተምሮ ማስተማር አዳራሽ እየተገኙ ትምህርተ ወንጌል መማር ጀመሩ፡፡
በ1980 ዓ.ም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አራት ኪሎ ግቢ ትምህርታቸውን ሊከታተሉ ከገቡት መካከል እስከ ሃምሣ የሚደርሱ ተማሪዎች በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት ተሰብስበው ይማሩ ጀመር፡፡ በዚሁ ዓመት በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የሚማሩ ተማሪዎችም ተመሳሳይ መንፈሳዊ መርሐ ግብር ጀምረው ነበር፡፡
በዩኒቨርሲቲ መደበኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው በ1980 ዓ.ም ከተመረቁት ተማሪዎች ውስጥ በግቢ ቆይታቸው በቤተ ክርስቲያን ተሰባስበው መንፈሳዊ ትምህርት ሲማሩ የነበሩት የቤተክርስቲያን ልጆችም በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም ተምሮ ማስተማር ማኅበር አዳራሽ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮሰ ካልዕና ሌሎችም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በተገኙበት ለመጀመሪያ ጊዜ ተመረቁ፡፡
ከብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ጋር በተደረገው ግንኙነት መሠረት በዚሁ ዓመት ከተመረቁት መካከል ዐሥራ ሁለት ተመራቂዎች በዝዋይ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ካህናት ማሠልጠኛ ገብተው በክረምቱ ወራት፤ ትምህርተ ሃይማኖት፣ ሥርዓተ እምነት፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ፣ ትውፊት እንዲሁም የስብከት ዘዴ ሲማሩ ከረሙ፡፡
ከክረምቱ ሥልጠና በኋላ የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕን አባታዊ ምክርና መመሪያ ሳይዘነጉ «ማኅበረ ማርያም» በሚል ስያሜ የጽዋ ማኅበር በመመሥረት በአዲስ አበባና በዙሪያው በሚገኙ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በዓውደ ምሕረትና ሌሎች መርሐ ግብሮች ቃለ እግዚአብሔርን በማስተማር በየወሩ እየተገናኙም ስለአገልግሎታቸው መወያየት ቀጠሉ፡፡ በዓመቱ መጨረሻም በዝዋይ ተገኝተው ሪፖርት አድርገዋል፡፡
በ1981 ዓ.ም ክረምት ለሁለተኛ ዙር ሥልጠና በምስካዬ ኅዙናን መድኃኔዓለም ተምሮ ማስተማር ማኅበር እና በግቢ ገብርኤል ዓምደ ሃይማኖት አዳራሾች ይማሩ ከነበሩት መካከል ዐሥራ ሁለት ተማሪዎች ተወክለው በዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ በአቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ አማካኝነት ሥልጠና ተሰጥቷቸዋል፡፡
መንፈሳዊ እንቅስቃሴው እየተጠናከረ ቀጥሎ በተለይም በ1982 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ፋኩልቲዎች፤ በጥቁር አንበሳ ሕክምና ፋኩልቲ፣ በልደታ ሕንፃ ኮሌጅ፣ በደብረ ዘይት እንስሳት ሕክምና ፋኩልቲ እንዲሁም በጅማ ጤና ሳይንስ፣ በዓለማያ ዩኒቨርሲቲ፣ በወቅቱ በአሥመራ ዩኒቨርሲቲ ወዘተ ተስፋፋ፡፡ በዓመቱ የክረምት ወራት ከየዩኒቨርሲቲ እና ኮሌጆቹ የተውጣጡ አርባ አምስት ተማሪዎች ዝዋይ ካህናት ማሠልጠኛ ገብተው ሥልጠና ወስደዋል፡፡ በሥልጠናው በአዲስ አበባ አድባራትና ገዳማት ከሚገኙ ሰንበት ትምህርት ቤቶች የተውጣጡ አርባ የሚደርሱ ተማሪዎችም ተሳትፈዋል፡፡
በ1983 ዓ.ም በወቅቱ በነበረው መንግሥት በሁሉም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚማሩ ተማሪዎች በሙሉ ወታደራዊ ሥልጠና እንዲወስዱ ሲታዘዝ፤ በሀገሪቱ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የሚማሩ አሥራ አንድ ሺሕ ያህል ተማሪዎች በብላቴ አየር ወለድ ማሠልጠኛ እንዲገቡ ተደረገ፡፡ ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ በዩኒቨርሲቲና ኮሌጆቹ ግቢዎች ተጀምሮ ቀስ በቀስ የተስፋፋው መንፈሳዊ እንቅስቃሴም የበለጠ የሰፋበትና የተጠናከረበት ጊዜ ሆነ፡፡
በወቅቱ እነዚህ ተማሪዎች ማታ ማታ እየተሰበሰቡ በአንድነት ከሚያደርጉት ጸሎት እና ከሚማሩት የቤተ ክርስቲያን ትምህርት በተጨማሪ፤ በአካባቢው ወደሚገኘው ብላቴ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን እየተደበቁም እያስፈቀዱም በመሔድ ምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ይሳተፉ ነበር፡፡
የወታደራዊ ሥልጠናው የሁለት ወር ቆይታ በመንግሥት ለውጥ ምክንያት ሊበተን ግድ ሲሆን፤ ተማሪዎቹ ይህ መንፈሳዊ አንድነት እንዴት መቀጠል እንዳለበት ተነጋገሩ፡፡ ከብዙ ውይይት በኋላም ፈቃደ እግዚአብሔር ሆኖ በየዩኒቨርሲቲና ኮሌጆቻቸው ሲመለሱ በቅዱስ ሚካኤል ስም ተሰባስበው ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል በመስማማት ቃል ገብተው ተለያዩ፡፡
በዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ ዕረፍት ዓመታዊ መታሰቢያ ላይ የተገኙ ደቀመዛሙርትና መምህራን ሐምሌ 22 ቀን 1983 ዓ.ም፤ በወቅቱ የሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣ የገዳሙና የካህናት ማሠልጠኛው የበላይ ጠባቂ በነበሩበት በብፁዕ ዶ/ር አቡነ ገብርኤል ሰብሳቢነት ጉባኤ አድርገው «የዝዋይ ደቀ መዛሙርትና መምህራን ማኅበር» በሚል ስያሜ ማኅበር ተመሠረተ፡፡
ከዚህ ቀደም በ1981 ዓ.ም በምስካየ ኅዙናን መድኃኔዓለም ገዳም በተምሮ ማስተማር ማኅበር እና በመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓምደ ሃይማኖት ሰንበት ትምህርት ቤት የሚማሩ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች ጉባኤ አንድነት በመፍጠር የተጠናከረ እንቅስቃሴ ባያደርግም «ማኅበረ እስጢፋኖስ» የሚባል ማኅበር መሥርተው ነበር፡፡ ከዚያ በኋላም ቢሆን እንቅስቃሴአቸው የተጠናከረ ባይሆንም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ፋኩልቲ ተማሪዎች «ማኅበረ ሥላሴ» በሚል ስያሜ፤ በሌሎችም ፋኩልቲዎችና ኮሌጆች ግቢዎች የሚገኙ ተማሪዎች በተለያዩ ቅዱሳን ስም በሰየሟቸው ጽዋ ማኅበራት ተሰባስበው ነበር፡፡
ሆኖም በቅዱሳኑ ስም የተለያዩ ማኅበራትን መሥርተው የተሰባሰቡት አባላት፤ ዓላማቸው፣ አገልግሎታቸውም ሆነ ታሪካቸው አንድ በመሆኑ በአንድ ማኅበር ቢሰባሰቡ የሚሰጡት አገልግሎት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ተገነዘቡ፡፡ “ለምን አንድ ስያሜ ይዘን በአንድነት አንንቀሳቀስም?” የሚል ሐሳብ በውስጣቸው እየተነሣ በተለያዩ አጋጣሚዎች በጉዳዩ ሲወያዩበት ቆይቷል፡፡
በዝዋይ ለተመሠረተው ማኅበር ስያሜ ለመስጠት አዲስ አበባ በብፁዕ አቡነ ገብርኤል ቤት በዚሁ ዓመት በየካቲትና መጋቢት ወራት በተካኼደው ስብሰባ ላይ ሐሳቡ ቀርቦ ውይይት ተደረገበት፡፡ በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ገብርኤል “ሁላችሁም የያዛችሁት አገልግሎት የቅዱሳን ክብር የሚገለጽበት ነው፡፡ ስለዚህ የማኅበራችሁም ስም ‘ማኅበረ ቅዱሳን’ ይባል፡፡” በማለት ባቀረቡት ሐሳብ መሠረት፤ የ«ማኅበረ ማርያም»፣ «ማኅበረ ሚካኤል» እና «የዝዋይ ደቀ መዛሙርትና መምህራን ማኅበር» ተዋሕደው የሁሉም ማኅበራት የጋራ የሆነው ማኅበረ ቅዱሳን ተመሠረተ፡፡
አባላቱም መንፈሳዊ አገልግሎታቸው የቅድስት ቤተክርስቲያንን ሥርዓትና መዋቅር ጠብቆ በቤተክርስቲያን አስተዳደር ዕውቅና ማግኘት እንዳለበት አምነው፤ «በጠቅላይ ቤትክህነት በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር ሆነን እናገልግል» በማለት መተዳደሪያ ደንባቸውን ይዘው ወደ መምሪያው ጽ/ቤት ቀረቡ፡፡ በዚህ ዓይነት ማኅበረ ቅዱሳን ለመጀመሪያ ጊዜ በቤተ ክርስቲያኒቷ መዋቅር ዕውቅና አግኝቶ ግንቦት 2 ቀን 1984 ዓ.ም በጠቅላይ ቤተክህነት በሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር መደራጀቱ ይፋ ሆነ፡፡ እነሆ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በሰ/ት/ቤቶች ማደራጃ መምሪያ ሥር አገልግሎቱን እየፈጸመ ይገኛል፡፡