ከጎፋና ባስኬቶ ሀገረ ስብከት ጥያቄ አስተባባሪ ኮሚቴ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ላይ በዛሬው ዕለት መግለጫ ተሰጥቷል፡፡
ከጉራጌ ሀገረ ስብከት ጽሕፈት ቤት ወቅታዊ ጉዳዮችን በተመለከተ የተሰጠ መግለጫ
ማኅበረ ቅዱሳን በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መግለጫ ሰጠ።
የግቢ ጉባኤያት ሴሚናር በአቀባበል መርሐ ግብር ተጀመረ
ማኅበረ ቅዱሳን ፲፪ኛው የግቢ ጉባኤያት ሴሚናር ላይ ለመሳተፍ ለሚመጡ የማእከላትና የግቢ ጉባኤያት ተወካዮች አቀባበል እያደረገ ይገኛል፡፡
የአቀባበል ሥርዓቱም በሕጽበተ እግር የተጀመረ ሲሆን በማኅበረ ቅዱሳን ሕንጻ ፫ኛ ወለል ላይ በመከናወን ላይ ነው፡፡ በዚህ ሴሚናር ላይ ፫፻ የማእከላትና የግቢ ጉባኤያት ተወካየች የሚሳተፉ ሲሆን ጉባኤው ለሁለት ቀናት ከሐምሌ ፳፫-፳፬ ቀን ፳፻፲፬ ዓ.ም እንደሚካሄድ የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ገልጿል፡፡
ከአቀባበል ሥነ ሥርዓቱ በኋላም ጉባኤው በእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክትይቀጥላል፡፡
ሂደቱን እየተከታተልን የምናቀርብ ይሆናል፡፡
ትጉኀኑ የግቢ ጉባኤያት ፍሬዎች …
ወቅቱ ክረምት እንደመሆኑ መጠን ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደግሞ እንደየደረጃው ሲያስተምሯቸው የነበሩ ተማሪዎችን የሚያስመርቁበት ጊዜ ነው፡፡ ትምህርት ቤቶችም ለተማሪዎቻቸው ዓመቱን ሙሉ የደከሙበትን ውጤት አብስረው ተማሪዎቻቸውን የሚያሰናብቱበት፣ እነርሱም ለሚቀጥለው ዓመት ዝግጅት የሚያደረጉበት ጊዜ ነው፡፡
ኦርቶዶክሳውያን ተመራቂ ተማሪዎች በማኅበረ ቅዱሳን ግቢ ጉባኤያት አማካይነት ከትምህርታቸው ጎን ለጎን የቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት በመማር በሁለት ወገን የተሳሉ ስለት ሆነው በመውጣት ሀገራቸውንና ቤተ ክርስቲያናቸውን በቅንነትና በታማኝነት ለማገልገል ዝግጅት የሚጀምሩበትም ነው-ወቅቱ፡፡
ከእነዚህ ተማሪዎች መካከል ደግሞ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከትምህርት ክፍላቸው ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የዋንጫና ሜዳልያ ተሸላሚ የሚሆኑት ቁጥራቸው ከፍተኛ ነው፡፡ በየዓመቱም ከፍተኛ ውጤት በማመምጣት የተሸለሙትን ዋንጫና ሜዳልያ “እግዚአብሔር ረድቶን ውጤታማ እንድንሆንና ቤተ ክርስቲያናችንን እንድናውቃት፣ በሃይማኖታችንም እንድንጸና ያስተማረን ማኅበረ ቅዱሳን ነውና ለውጤታማነታችን ድርሻው ከፍተኛ ነው” በማለት ሽልማቶቻቸውን ለማኅበረ ቅዱሳን ማበርከታቸው የተለመደ ነው፡፡
እንደተለመደው በ፳፻፲፬ ዓ.ም በየከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችም ዋንጫውንና ሜዳልያውን ለመውሰድ ችለዋል፡፡
ከእነዚህም ውስጥ፡- ከነቀምት፣ ከደብረ ማርቆስ፣ ከሐዋሳ፣ ሐረር፣ መቱ፣ ዋቸሞ፣ ሻምቡ፣ አሰላ፣ … እና ከሌሎችም ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በከፍተኛ ውጤት በመመረቅ ተሸላሚዎች መሆናቸውን መረጃዎች እየደረሱን ይገኛሉ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ከተመሠረተበት ከ፲፱፻፹፬ ዓ.ም ጀምሮ እስከ አሁን ከሰባት መቶ ሺህ በላይ ተማሪዎችን በግቢ ጉባኤያት ውስጥ በማስተማር እንዳስመረቀ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ወደ ቤተሰቦቻቸው በመሔድ ላይ ይገኛሉ
የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያይዞ ሊፈጠር የሚችለውን አደጋ ለመቀነስና ለመታደግ ወደየቤተሰቦቻቸው እንዲሔዱ በወሰነው መሠረት በርካታ ዩኒቨርስቲዎች ተማሪዎቻቸውን በመሸኘት ላይ ይገኛሉ፡፡
የትራንስፖርት አቅርቦቱ የሳይንስና የከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር የተቀናጀ ሥራ በመሥራትና በማመቻቸት ለተማሪዎቹ እንደሚቀርብ የተገለጸ ሲሆን ላልተወሰነ ጊዜ ከቤተሰቦቻቸው ጋር በሚቆዩበት ወቅት ትምህርታቸውን እያጠኑ እንዲቆዩ ተነግሯቸዋል፡፡
የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችም ስለ ቫይረሱ ስርጭት በቂ ግንዛቤ ይዘው ወደየቤተሰቦቻቸው በመሔድ ቤተሰብን የማሳወቅና የመንከባከብ ኃላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም ወቅቱ የሱባኤ ወቅት በመሆኑ በጾም በጸሎት እየበረቱ፣ ራሳቸውንም እየጠበቁ ሌሎችን ስለ ቫይረሱና ሊደረጉ ስለሚገባቸው ጥንቃቄዎች በማስተማር፣ በመርዳትና በመንከባከብ ክርስቲያናዊ ግዴታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ወቅታዊውን የኮሮና በሽታ አስመልክቶ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የተሰጠ መግለጫ
መጋቢት 16 ቀን 2012 ዓ.ም
በአሁኑ ጊዜ በዓለም ላይ እንደ ሰደድ እሳት እየተቀጣጠለ የሰው ልጆችን ሕይወት በሞት እየቀጠፈ ያለው ተላላፊ በሽታ በአገራችን ኢትዮጵያም ከፍተኛ ስጋት እየሆነ መምጣቱ ታምኖበት ወረርሽኙም ለመቋቋም ከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ እንደምንገኝ ይታወቃል፡፡
በመሆኑም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም ባሉባት ሕዝባዊ ኃላፊነት የተነሳ ለዚሁ የመከላከል ሥራ ራሱን የቻለ የተስፋ ግብረ ኃይል በማቋቋም ኅብረተሰቡ ከበሽታው እንዲጠበቅ ለማድረግ በከፍተኛ እንቅስቃሴ ላይ ትገኛለች፡፡ በቀጣይም ከበሽታው ራስን በተገቢው መንገድ መጠበቅ እንዲቻል ቋሚ ሲኖዶስ በዛሬው ዕለት ባደረገው ስብሰባ በጉዳዩ በሰፊው በመነጋገር በጊዜያዊነት መዘጋት በሚገባቸው የሥራ ክፍሎች ላይ የሚከተለውን ወስኗል፡፡
- ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጀምሮ ሙሉ በሙሉ የተዘጉ መምሪያዎች
ሀ. የመንበረ ፓትርያርክ ቅርሳቅርስ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር
- ጉብኝት
- የንባብ አገልግሎት
- በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር ከአዲስ አበባ እስከ አህጉረ ስብከት ያሉ
ሀ. መንፈሳዊ ዩኒቨርስቲዎች
ለ. መንፈሳዊ ኮሌጆች
ሐ. ሥልጠና ያልጀመሩ የካህናት ማሰልጠኛዎች
መ. መዋዕለ ሕፃናት
ረ. የአብነት ትምህርት ቤቶች ላልተወሰነ ጊዜ የመማር ማስተማሩ ሥራ ቁሞ ደቀ መዛሙርቱና ተማሪዎቻቸው የተማሩትን እየቀጸሉና እያጠኑ እንዲቆዩ፡-
- በከፊል እንዲዘጉ የተደረጉ፡-
ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት እስከ መላው አህጉረ ስብከት ጽ/ቤቶች ለአስቸኳይ ሥራ ከሚፈለጉና ተለይተው እንዲቆዩ ከሚደረጉ ሠራተኞች በስተቀር መላው ሠራተኞች በየቤታቸው ሥራቸውን እንዲያከናውኑና ሲፈለጉና ጥሪ ሲደረግላቸው ከሚመጡ በስተቀር በቤታቸው እንዲቆዩ፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ሕዝባችንን ከሕማም ሞት፣ ሀገራችንን ከልዩ ልዩ መቅሰፍትና ደዌ ይጠብቅልን፡፡
ብፀዕ አቡነ ያሬድ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን
መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የአርሲ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ
በስመ አብ ወወልድ ወንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፡፡ አሜን
በመላው ዓለም የተስፋፋውን የኮሮና ወረርሽኝ ለመግታት ከኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ
ቤተ ክርስቲያን የተሰጠ መግለጫ
በሀገራችን በኢትየጵያ በገጠር፣ በከተማና በመላው ዓለም ለምትገኙ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን በሙሉ!
ወቅታዊ የሰው ልጅ ሥጋት በመሆን በመላው ዓለም በፍጥነት በተስፋፋው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት ዓለም አቀፍ ሥጋት ስለተከሰተ መንግሥታት ሀገርን ከጥፋት፣ ሕዝቡን ከሞት ለመጠበቅ አዋጆችን እያወጡ ይገኛሉ፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ሕይወት ለመታደግ እምነትና ቀኖናን ጠብቆ ሃይማኖታዊ መመሪያ የመስጠት ሐዋርያዊ ኃላፊነት አለባት፡፡
ስለዚህ ቀሚ ሲኖዶስ የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መሠረተ እምነትንና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን ጠብቆ ለሁሉም ካህናትና ለሕዝበ እግዚአብሔር ደኅንነት ሲባል የሚከተሉትን መመሪያዎች አስተላልፏል፡-
- በሰሙነ ሕማማት እንደምናደርገው የእርስ በርስ መሳሳም ቀርቶ ራስን ዝቅ በማድረግ እጅ መንሳት ወይም በእማሄ ሰላምታ በማቅረብ እንዲፈጸም፣
- ወረርሽኙ በሰዎች መሰባሰብ የሚስፋፋ ስለሆነ ማናቸውም መንፈሳዊ ጉባኤያት፣ የትምህርት ክፍለ ጊዜያት፣ ወደ ገዳማትና አድባራት የሚደረጉ ጉዞዎች እና ምእመናን የሚሳተፉባቸው ታላላቅ መርሐ ግብሮች ለጊዜው እንዲቋረጡ፣
- ወደ ቤተ ክርስቲያን ሲገባም ሆነ አስፈላጊ በሆነበት በጊዜ ሁሉ እጆቻችንን በመታጠብና ዘርዘር ብሎ በመቆም ሥርዓተ አምልኮ እንዲፈጸም፣
- ዓመታዊ የንግሥ ክብረ በዓላት በቅደሴና በማኅሌት ታስበው ክብረ በዓላቱ በሌላ ጊዜ እንዲከበሩ፣
- የጉንፋን ምልክት ያለባቸው ለሌሎች እንዳያስተላልፉ በቤታቸው በጥንቃቄ ተለይተው በጸሎትና በሕክምና እንዲቆዩ፣ ከቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ አገልግሎትም በልዩ ሁኔታ እንዲያገኙ፣
- በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ የተቋቋመው ግብረ ኃይል የተስፋ ልዑክ በመሆን እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ድረስ ተደራጅቶ ተልእኮውን በአስቸኳይ እንዲጀምር፣
- ሥርዓተ ቅዳሴን በተመለከተ፡-
- በቤተ መቅደስ ቀዳስያን በሆኑት ልዑካን ብቻ ሥርዓተ ቅዳሴው እንዲፈጸምና ሌሎች አገልጋዮች በቅድስቱ ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያገለግሉ፣
- በዕለቱ ለሚቆርቡ ምእመናን አረጋውያን፣ ለወጣቶችና ለሕፃናት የፈረቃ ተራ በማዘጋጀት ቆራቢዎች ብቻ ወደ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ገብተው ዘርዘር ብለው በመቆም እንዲያስቀድሱ፣
- ሌሎች ምእመናን በአጸደ ቤተ ክርስቲያን ቢያንስ ሁለት የትልልቅ ሰው እርምጃ ያህል በመራራቅ ቆመው እንዲያስቀድሱ፣
- የቅዳሴ ጠበል በየግል መጠቀሚያ ምእመናን በየቆሙበት ቦታ በጥንቃቄ እንዲሰጥ፣
- ሌሎች ከቅዳሴ ጋር የተያያዙ ዝርዝር የአፈጻጸም ጉዳዮችን ግብረ ኃይሉ አዘጋጅቶ በቅዱስ ሲኖዶስ በማጸደቅ ለአህጉረ ስብከት በሚልከው መመሪያ መሠረት ተግባራዊ እንዲደረግ፣
- ከሥርዓተ ቅዳሴ በተጨማሪ እንደ ስብሐተ ነግሕ፣ ሰዓታት፣ ቁመተ ማኅሌት፣ ጥምቀተ ክስትና፣ ጸሎተ ፍትሐት፣ የመሳሰሉ አገልግሎቶች ለሥርዓቱ በሚያስፈልገው ቁጥር ብቻ እና ውሱን ሊቃውንት በተራ እንዲፈጸም፣
- ወረርሽኙ ከዓለም እንዲጠፋ ካህናት ብቻ በቤተ መቅደስ፣ በዐውደ ምሕረትና በአፀደ ቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ጸሎተ እጣን በማድረስ ማዕጠንት እንዲፈጽሙ፣
- በማኅበራዊ ግንኙነት በደስታ፣ በሐዘን፣ በእድር፣ በሥርዓተ ቀብር አፈፃፀምና በመሳሰሉት መሰባሰቦች በሽታው እንዳይሰራጭ አገልግሎቱ በውስን የሰው ቁጥር በጥንቃቄ እንዲፈጸም፣
- ምእመናን ራሳቸውን እየጠበቁ በቫይረሱ የተጠቁና አገግመው የወጡ ወገኖችን፣ እንዲሁም በውጭ ሀገር ዜጎች ላይ ከሃይማኖትና ከምግባር የወጣ መገለልና ጥቃት እንዳይደርስባቸው በክርስቲያናዊ ፍቅርና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት እንክብካቤ እንዲደረግላቸው፣
- ለነዳያንና ለተቸገሩ ወገኖች አስፈላጊው ማኅበራዊ እና ቁሳዊ እገዛ በሁሉም አጥቢያዎች እንዲደረግ፣
- ቤተ ክርስቲያንን ከማይወክሉና ቀኖናዊ ካልሆኑ አሳሳች መረጃዎች በመቆጠብ ሊቃውንት፣ ካህናት፣ መምህራን፣ ሰባክያን፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶች ከቅዱስ ሲኖዶስ የሚሰጡ መመሪያዎችን በየአጥቢያችሁና አስፈላጊ በሆኑ ቦታዎች ሁሉ እንድትፈጽሙ እና እንድታስፈጽሙ ተወስኗል፣
በአጠቃላይ በሽታው እስካሁን ለተያዙት፣ በጊዜያዊ ማቆያ ለሚገኙት በሙሉ እግዚአብሔር አምላካችን ምሕረቱን እንዲሰጥልን እንጸልያለን፣
በመላው ዓለም ዜጎቻቸውን በበሽታው ለተነጠቁ ሁሉ መጽናናቱን እንዲሰጥልን ያረፉትንም እንዲምርልን እግዚአብሔርን በጸሎት እንጠይቃለን፣
በመላው ዓለም የምትገኙ ወገኖቻችን የራሳችሁንና የሌሎች ሕይወት ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ እንዲሁም የበሽታው ሥርጭት እንዲቆም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ኃላፊነታችሁን እንድትወጡ እያሳሰብን የተሰጡት መመሪያዎች ወረርሽኙ እስኪጠፋ ድረስ የጸኑ እንዲሆኑ በጥብቅ እናስታውቃለን፡፡
ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱና በይቅርታው ብዛት ዓለማችንን ከጥፋት የሰውን ልጅ ሁሉ ከመከራ ሞት ይጠብቅልን፡፡ አሜን፡፡
ወስብሐተ ለእግዚአብሔር!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ
ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት
መጋቢት 14 ቀን 2012 ዓ/ም አዲስ አበባ
የኮሮና ቫይረስ እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት
በእንዳለ ደምስስ
በአሁኑ ወቅት ዓለምን እያስጨነቀና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራችን መግባቱን ተከትሎ የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለ15 ቀናት እንዲዘጉ ሲወስን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችም በየዩኒቨርስቲዎቻቸው ሆነው አስፈላጊውን ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚቆዩ ገልጿል፡፡
ሕዝቡም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መንግሥትና የሃይማኖት አባቶች ጥሪ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም መሠረት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በዚህ በዐቢይ ጾም በየቤተ ክርስቲያኑ የምሕላ ጸሎት እስከ ትንሣኤ ድረስ እንዲደረግ ያሳሰቡ ሲሆን፣ የመጣውን መቅሰፍት መሻገር እንዲቻልም ምእመናን በምሕላ፣ በጾም፣ በጸሎት ጸንተው እንዲቆዩ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን እዚያው ባሉበት እንዲያቆዩ ከመንግሥት በተላላፈው ጥሪ መሠረት ተማሪዎች ራሳቸውን ከቫይረሱ ለመከላከል ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ግንዛቤ ከመፍጠር አንስቶ የተቀናጀ ሥራ መሥራት ይገባል፡፡
አብዛኛዎቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እያስተናገዱት ካለው የተማሪዎች ቁጥር አንጻር ምን እየሠሩ እንደሚገኙ ባይገልጹም የአምቦ፣ የጎንደርና የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲዎች ከተማሪዎች ጋር በመሆን ግብረ ኃይል በማቋቋም አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ የመከላከሉን ሥራ ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎች በየማደሪያ ክፍሎቻቸው ሆነው ሳይዘናጉ በመማር ላይ ያሉትን ትምህርቶች በመከለስ እንዲያሳልፉ፣ በርከት ብለው በአንድ ቦታ ላይ እንዳይሰባሰቡ፣ የሚመገቡባቸውን ቁሳቁሶች ንጽሕና በመጠበቅ፣ ቤተ መጻሕፍት በአንድ ጊዜ የሚያስተናግዷቸውን ተማሪዎች ቁጥር በመቀነስ፣ ተራርቀው እንዲቀመጡ በማድረግ ቫይረሱን ለመከለከል ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ እነዚህ ዩኒቨርስቲዎች ገልጸዋል፡፡ ሌሎች ከፍተኛ ተቋማትም የአምቦ፣ የጎንደርና የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲዎችን እንደ አርአያ በመውሰድ የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ የግቢ ጉባኤያት ተሳታፊ ተማሪዎችም ራሳቸውን ከመጠበቅ አልፎ ሌሎችን ተማሪዎች በማገዝ፣ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፋቸውን መልእክቶች ተግባራዊ በማድረግ፣ የሱባኤ ወቅት በመሆኑም በምሕላ፣ በጾም፣ በጸሎት ተወስነው ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ግለሰቦች ለዚሁ በተዘጋጀው ማቆያ ስፍራ ላይ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኙ የጤና ሚኒስቴር ገልጿል፡፡