የኮሮና ቫይረስ እና ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት

በእንዳለ ደምስስ

በአሁኑ ወቅት ዓለምን እያስጨነቀና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ሕይወት እየቀጠፈ ያለው የኮሮና ቫይረስ ወደ ሀገራችን መግባቱን ተከትሎ የችግሩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት መንግሥት በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ለ15 ቀናት እንዲዘጉ ሲወስን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎችም በየዩኒቨርስቲዎቻቸው ሆነው አስፈላጊውን ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚቆዩ ገልጿል፡፡

ሕዝቡም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ መንግሥትና የሃይማኖት አባቶች ጥሪ በማቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም መሠረት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በዚህ በዐቢይ ጾም በየቤተ ክርስቲያኑ የምሕላ ጸሎት እስከ ትንሣኤ ድረስ እንዲደረግ ያሳሰቡ ሲሆን፣ የመጣውን መቅሰፍት መሻገር እንዲቻልም ምእመናን በምሕላ፣ በጾም፣ በጸሎት ጸንተው እንዲቆዩ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎቻቸውን እዚያው ባሉበት እንዲያቆዩ ከመንግሥት በተላላፈው ጥሪ መሠረት ተማሪዎች ራሳቸውን ከቫይረሱ ለመከላከል ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ግንዛቤ ከመፍጠር አንስቶ የተቀናጀ ሥራ መሥራት ይገባል፡፡

አብዛኛዎቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እያስተናገዱት ካለው የተማሪዎች ቁጥር አንጻር ምን እየሠሩ እንደሚገኙ ባይገልጹም የአምቦ፣ የጎንደርና የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲዎች ከተማሪዎች ጋር በመሆን ግብረ ኃይል በማቋቋም አስፈላጊውን ዝግጅት በማድረግ የመከላከሉን ሥራ ተግባራዊ በማድረግ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ተማሪዎች በየማደሪያ ክፍሎቻቸው ሆነው ሳይዘናጉ በመማር ላይ ያሉትን ትምህርቶች በመከለስ እንዲያሳልፉ፣ በርከት ብለው በአንድ ቦታ ላይ እንዳይሰባሰቡ፣ የሚመገቡባቸውን ቁሳቁሶች ንጽሕና በመጠበቅ፣ ቤተ መጻሕፍት በአንድ ጊዜ የሚያስተናግዷቸውን ተማሪዎች ቁጥር በመቀነስ፣ ተራርቀው እንዲቀመጡ በማድረግ ቫይረሱን ለመከለከል ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኙ እነዚህ ዩኒቨርስቲዎች ገልጸዋል፡፡ ሌሎች ከፍተኛ ተቋማትም የአምቦ፣ የጎንደርና የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲዎችን እንደ አርአያ በመውሰድ የበኩላቸውን ጥረት ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚገኙ የግቢ ጉባኤያት ተሳታፊ ተማሪዎችም ራሳቸውን ከመጠበቅ አልፎ ሌሎችን ተማሪዎች በማገዝ፣ ግንዛቤ በመፍጠር፣ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የምታስተላልፋቸውን መልእክቶች ተግባራዊ በማድረግ፣ የሱባኤ ወቅት በመሆኑም በምሕላ፣ በጾም፣ በጸሎት ተወስነው ወደ እግዚአብሔር መጸለይ ይጠበቅባቸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ግለሰቦች ለዚሁ በተዘጋጀው ማቆያ ስፍራ ላይ ክትትል እየተደረገላቸው እንደሚገኙ የጤና ሚኒስቴር ገልጿል፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *