ወቅታዊ ጉዳዮችን በማስመልከት ከማኅበረ ቅዱሳን የተሰጠ መግለጫ
የቤተ ክርስቲያናችን ስደት የሚቆመው ሁላችንም ድርሻችንን ስንወጣ ነው!!!
“ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ስለተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኳችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ፡፡” (ይሁዳ ፩፥፫)
ማኅበረ ቅዱሳን ከሦስት ዓመት በፊት ግንቦት ወር 2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከ1950ዎቹ ጀምሮ ሁለንተናዊ የአስተሳሰብ ውጊያ ሲደረግባት ቆይቷል፡፡ ይህ የአስተሳሰብ ውጊያ በጊዜ ሂደት መዋቅራዊና ስልታዊ ሆኖ ቀጥሎ ይኸው ዛሬም ቤተ ክርስቲያን ከስደት አልተመለሰችም፡፡ ይልቁንም የቤተ ክርስቲያን መከራና ስደት በዓይነቱ ተለይቶ፣ ድግግሞሹ በዝቶ፣ በመጠኑም ጨምሮ ቀጥሏል፡፡ ለዚህም ባሳለፍናቸው ሦስት ዓመታት ውስጥ በቤተ ክርስቲያንና በልጆቿ ላይ ተጠናክረው የተፈጸሙ ድርጊቶች በቂ ማሳያዎች ናቸው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች በተከታታይ ካህናት፣ መነኮሳትና ምእመናን በሃይማኖታቸው ተለይተው ተገድለዋል፣ ተሰደዋል፣ አብያተ ክርስቲያናትና ገዳማት ተቃጥለዋል፡፡ በተጨማሪም ንብረታቸውንም እንዲያጡ ተደርገዋል፡፡ የቤተ ክርስቲያን መዋቅርም እንዲናጋ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡
በአጠቃላይ በውስጥና በውጭ ባሉ የቤተ ክርስቲያን ጠላቶች ቅንጅት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት የሚፈታተኑ ተግባራት በድፍረትና በማን አለብኝነት ተፈጽመዋል፡፡ በቅርቡም የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳገቡ መደረጋቸው፣ በተመሳሳይ በዝቋላ ገዳም መናኝ አባቶች ላይ የተፈጸመው የግፍ ግድያ በቤተ ክርስቲያን ላይ የተፈጸመ መዋቅራዊ ጥቃት ማሳያ ነው፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በነነዌ ጾም መልእክታቸው ላይ እንዳስተላለፉት፡፡
“ይህንን የነነዌ ጾም ልንቀበል ዋዜማ ላይ ባለንበት በዚህ ጊዜ በቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊ ከሆኑት ገዳማት አንዱ በሆነው በዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም የሚገኙ፣ ዓለሙን ትተው በፈቃዳቸው ረኃብተኛ እና ጥማተኛ ሆነው ሀገርን በጸሎት የሚጠብቁ መነኮሳት ጫካው መኖሪያችሁ፣ ዳዋው ልብሳችሁ፣ ቅጠሉ ምግባችሁ መሆን አይችልም ተብለው የሰማዕትነት ጽዋ ተጎንጭተዋል፡፡ እነርሱ በሥጋ እየሞቱ እኛም በየቀኑ ሟቾችን እየቆጠርን በኀዘን ለመኖር የተፈረደብን ሆኗል” ብለዋል፡፡
በሀገራችን ውስጥ የሕግ የበላይነት እስካልሰፈነና ጠያቂና ተጠያቂ እስካልኖረ ድረስ ወደፊትም በባሰ ሁኔታ ሊቀጥል ይችላል፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያን ስደት ይቆም ዘንድ የቤተ ክርስቲያን ልዕልና ይከበር ዘንድ ሁላችንም የድርሻችንን ለመወጣት በያለንበትም ሆነ በጋራ በመናበብ ከሕጻን እስከ አዋቂ፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ የሥጋ ጥቅምን፣ ምድራዊ ሥልጣንና የግል ፍላጎትን አስወግደን በቤተ ክርስቲያን ጉዳይ ሁላችንም ቁርጥ መንፈሳዊ አቋም በመያዝ ለሃማኖታችን ዘብ ልንቆምና የድርሻችንን በትጋት ልንወጣ እንደሚገባ ማኅበረ ቅዱሳን እያሳሰበ ለቤተ ክርስቲያን አካላት ሁሉ ጥሪውን ያስተላልፋል፤
- የተከበራችሁ አበው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ሆይ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁ ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድሮ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ” እንዳለ በዚህ ታላቅ የፈተና ወቅት የቤተ ክርስቲያንን አንድነት ለማስጠበቅ፤ ቅዱስ ሲኖዶስ የሰጣችሁን ኃላፊነት ለመወጣት ምእመናንን አቅጣጫ በመስጠት የቀደሙ አባቶቻችሁን ፈለግ በመከተል ዛሬም በጽናት እንድትተጉ፤ ያከበረቻችሁን ቤተ ክርስቲያን በአንድነት ሆናችሁ እንድትጠብቁ በልጅነት መንፈስ በትሕትና እንጠይቃለን፡፡ በተጨማሪም የአባትነት የዋህ ልቡናችሁን በመጠቀም ያዘኑ፣ የጠቀሙ፣ የተቆረቆሩ መስለው ቀርበው የግል ፍላጎታቸውን ለመፈጸም የሚጥሩ ስለሚኖሩ ሁሉንም በጥንቃቄ እንድትመረምሩ፣፤ ቀኖች ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን በመዋጀት አንድነታችሁን እንድታጠነክሩና በቤተ ክርስቲያን ዙሪያ ለሚፈጠሩ ችግሮች በጥልቀት እንድትወያዩና እንድትመካከሩ እናሳስባለን፡፡
- ከዚህ ውጭ ቤተ ክርስቲያንን በማይጠቅማት ጉዳይ የግል ፍላጎትንና ምድራዊ ዓላማን መሠረት አድርጋችሁ ከቤተ ክርስቲያን ሕግ ቀኖና ውጭ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊን ለመተካት፣ ፓትርያርክ ለመሾምና የመሳሰሉትን ለመፈጸም የምትንቀሳቀሱ አንዳንድ አባቶች ከድርጊታችሁ እንድትታቀቡ ለማሰብ እንወዳለን፡፡ ማኅበራችን ይህንን ጉዳይ እየተከታተለ መረጃውን ለምእመናን የሚያደርስ መሆኑንም በዚሁ አጋጣሚ እንገልጻለን፡፡
- ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ መምህራነ ወንጌል፣ ካህናት ሆይ በጸሎትና በትምህርት ምእመናንን በማጽናናት፤ ከእውነት ጋር በመቆም እውነታውን በማሳየት ምእመናን ለቤተ ክርስቲያን ዘብ እንዲቆሙ በማድረግ ድርሻችሁን እንድትወጡ እናሳስባለን፡፡
- ውድ ምእመናንና የማኅበራችን አባላት የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያንን ከአሳዳጆቿ የመጠበቁ ዋነኛ ኃላፊነት በዘመኑ ባለን ብፁዓን አባቶች፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ካህናትና ምእመናን ሁላችን እጅ ላይ ወድቆአል፡፡ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ ለአባቶችና ለካህናት ትተን “እኔ አያገባኝም፣ አይመለከተኝም” ልንል አይገባም፡፡ ሁሉም በየድርሻው ቤተ ክርስቲያኑን ለመጠበቅ መትጋት አለበት፡፡ በቤተ ክርስቲያን ላይ የደረሰውን ጥፋትና ሊመጣ ያለውን ፈተና አስቀድሞ በመረዳት ቅዱስ ሲኖዶስ ቀደም ሲል በወሰነው መሠረት በየአጥቢያችን፤ በተለያየ መልኩ በመደራጀት፤ በቤተ ክርስቲያን ላይ ጥፋት ለማድረስ የሚመጡትን በመከላከል የቤተ ክርስቲያንን ስደት ለማስቆም መንፈሳዊ ግዴታችን እንድንወጣ እንጠይቃለን፡፡
- በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በልዩ ልዩ አገልግሎት እየተሳተፋችሁ ያላችሁ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ ማኅበራትና ሌሎችም ሁላችንም አንድነታችንን በመጠበቅ በጋራ አገልግሎቶችን በመፈጸም ድርሻችንን እንድንወጣ ለተግባራዊነቱ ጥሪ እናቀርባለን፡፡
- ገዳም ድረስ ገብቶ መሳሪያ ያልያዙና ራሳቸውን እንደ ሞቱ ቆጥረው እየኖሩ ያሉ መነኮሳት ላይ ግድያ የፈጸመ ማንኛውም የታጠቀ ኃይል (መደበኛም ይሁን ኢመደበኛ፣ በግልም ይሁን በቡድን፣ አማኝም ይሁን ኢአማኝ) ድርጊቱ ከሰውነት ተፈጥሮ የወጣ ነው፡፡ ምናኔንና የክህነት ክብርን በተቃረነ መልኩ ሰብእና የጎደለው ጥቃት ማድረስ ኢትዮጵያዊ ባህልም አይደለም፡፡ ጥቅም የሌለው ከንቱ ተግባር ነው፡፡ በዚህ የሚገኝ የፖለቲካ ትርፍ ይኖራል ብለን አናምንም፡፡ ጤነኛ በሆነ አእምሮ ታስቦ የተፈጸመ ነው ማለትም አይቻልም፡፡ ማስተዋል ተወስዶባቸው እውቀት ተሰውሮባቸው እንጂ ይህንን ማድረግ ቀርቶ ማሰቡም የሙት ሐሳብ ነው፡፡ ቀድሞ የሞተው ሟቹ ሳይሆን ገዳዩ ነው፡፡ በዚህ መንገድ የቤተ ክርስቲያን አማኞች ሲበዙ እንጂ ሲያንሱ በታሪክ አልታየም፡፡ ይህ ድርጊት ክርስቲያኖችን ሲያጠነክር እንጂ ሲያዳክም ታይቶ አይታወቅም፡፡ መጽሐፍ ጎርፍም መጣ፣ ነፋስም ነፈሰ፣ ያንን ቤት ገፋው፤ በዐለት ላይ ስለተመሠረተ አልወደቀም” ባለው መሠረት ቤተ ክርስቲያን በጽኑ ዐለት ላይ የተመሠረተች ስለሆነ አታሸንፏትም፡፡ ዲዮቅልጥያኖስም አላጠፋትም፤ ዲያብሎስም ዝናሩን እንዲሁ ጨረሰ፡፡ ስለዚህ አትድከሙ፤ አትሳቱም፡ እናንተ ሳትወለዱም የነበረች ቤተ ክርስቲያን እናንተም አልፋችሁም እንደ እናንተ ላሉት በስሑት መንገድ ለሚጓዙት ሁሉ እየጸለየች ትቀጥላለች፡፡ ሐሳቧም፣ ሥራዋም፣ ዓላማዋም፣ ግቧም ሰማያዊ ነውና፡፡
በመጨረሻም ማኅበረ ቅዱሳን ከቤተ ክርስቲያን ሕልውና በላይ የሚያስቀድመው የሌለ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያን የገጠማትን ፈተና ለማለፍ ከሚመለከታቸው የቤተ ክርስቲያን አካላት ጋር በመናበብ የሚጠበቅበትን መንፈሳዊ ግዴታ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን በዚሁ አጋጣሚ እያሳወቅን የሁላችንም መሰባሰብና የአገልግሎት ማእከል ቤተ ክርስቲያን በመሆኗ ከሁሉም ነገር በፊት ቅድሚያ ሰጥተን ሊመጣ ካለው አደጋ ቤተ ክርስቲያናችንን የመጠበቅ ኀላፊነት በትጋት እንወጣ ሲል ማኅበረ ቅዱሳን በአክብሮት ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ረድኤተ እግዚአብሔር አይለየን!!!
“የግቢ ጉባኤያት ተመራቂዎች ዲጂታል የምረቃ መጽሔት ዘመኑን ለዋጀ አገልግሎት አንዱ ማሳያ ነው”
በማኅበረ ቅዱሳን የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ የተዘጋጀው የግቢ ጉባኤያት ተመራቂዎች ዲጂታል የምረቃ መጽሔት ዘመኑን የዋጀ አገልግሎት ለመስጠት አንዱ ማሳያ መሆኑን የማኅበረ ቅዱሳን ዋና ጸሓፊ መ/ር ዋሲሁን በላይ ገለጹ፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ከዐሥር ወራት በላይ መረጃ በማሰባብ የዲጂታል መጽሔቱን ለማዘጋጀት ጊዜ እንደወሰደበትና በጥሩ አፈጻጸም መጠናቀቁን ሐምሌ ፲፪ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በነበረው የመጽሔት ምረቃ መርሐ ግብር ላይ ገልጸዋል፡፡ የዲጂታል የምረቃ መጽሔት ማዘጋጀት የተጀመረው ከ፳፻፲፩/፲፪ ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን ለዐራተኛ ጊዜ መዘጋጀቱንና ወደፊትም እንደሚቀጥል ጠቁመዋል፡፡
የግቢ ጉባኤያት አገልግሎት ማስተባበሪያ ኀላፊ አቶ አበበ በዳዳ በበኩላቸው ይህን የዲጂታል መጽሔት ማዘጋጀት ያስፈለገበት ዋና ዋና ምክንያቶችን ሲያብራሩም “በወረቀት መጽሔት ታትሞ ለተመራቂዎች ለማድረስ ከፍተኛ የሰው ኀይልና የገንዘብ ወጪ መጠየቁ፣ የግቢ ጉባኤያት ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣትና የወረቀት ዋጋ መናር፣ ወደ ማእከላትና ግቢ ጉባኤያት ለማዳረስ ከፍተኛ ወጪ መጠየቁ፣ …” ወደ ዲጂታል መጽሔት ዝግጅት ለመሸጋገር በምክንያትነት ካነሧቸው ምክንያቶች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡
የዲጂታል መጽሔቱን ለማዘጋጀት ሲጀመር በተማሪዎች ዘንድ በርካታ ተግዳሮቶች የነበሩ ቢሆንም ከጊዜ በኋላ ግን ተማሪዎች እየተረዱት በመምጣታቸው ቁጥራቸው ሊጨምር እንደቻለ አቶ አበበ ገልጸዋል፡፡ እንደ ችግር ካነሧቸው ውስጥም፡- ከሕገ ወጥ የኤጲስ ቆጶሳት ምርጫ ጋር ተያይዞ ያልተካተቱ ግቢ ጉባኤያት መኖራቸው፣ አስፈላጊ መረጃዎችን በተያዘለት ዕቅድ መሠረት ማእከላትና ግቢ ጉባኤያት አሰባስበው ያለመላካቸው፣ የጽሑፎች መዘግየት፣ በወረቀት እናሳትማለን እያሉ ተማሪዎቹን ልብ የሚከፍሉ አካላት መኖራቸው፣ ከቅባት አስተምህሮ ጋር ተያይዞ በተማሪዎች ላይ ይደርስ የነበረው ጫና፣ … የመሳሰሉት ጉዳዮች ይገኙባቸዋል፡፡
የዲጂታል መጽሔቱ ዝግጅት ጠንካራ ጎን በተመለከተም አቶ አበበ ሲገልጹ፡- “መጽሔቱ በየግቢ ጉባኤያቱ ተለይቶ መዘጋጀቱንና በወረቀትም ኮፒ ማድረግ እንደሚቻል፣ ሦስት ቋንቋዎችን ያካተተ መሆኑ (አማርኛ፣ አፋን ኦሮሞ እና እንግሊዝኛ)፣ የተመራቂ ተማሪዎች የምስጋና ቃል (Last words) መካተቱ፣ ክትትል ላይ ያሉ ግቢ ጉባኤያት መካተታቸው፣ በውጪ ሀገራት ያሉ ግቢ ጉባኤያት መካተት፣ ድጋፍ ሰጪዎች (Sponsers) አካላት ለመጀመሪያ ጊዜ መሳተፋቸውና ፕሮጀክቱን በታቀደለት ጊዜ ማጠናቀቅ መቻላችን ውጤታማ አድርጎናል” ብለዋል፡፡ የዲጂታል መጽሔቱን ለማዘጋጀት ሙሉ ሥራውን በኀላፊነት ወስዶ ውጤታማ አገልግሎት መፈጸም እንዲቻል የበኩሉን ድርሻ የተወጣውን የ“ተክሌ ኮንሰልቲንግ” ድርጅት ኀላፊን ኪዳኔ መብራቱንና በዚህ አገልግሎት ውስጥ የተሳተፉትን ሁሉ አመስግነዋል፡፡
የዲጂታል መጽሔቱ መታተም ከጀመረበት ጊዜ አንሥቶ አገልግሎቱን በመፈለግ የሚካተቱ ተመራቂ ተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ የጨመረ ሲሆን በ፳፻፲፩/፲፪ ዓ.ም አሥራ አንድ ሺህ ሁለት መቶ ሠለሳ፤ በ፳፻፲፫ ዓ.ም አምስት ሺህ ስምንት መቶ ሃምሳ አንድ፤ በ፳፻፲፬ ዓ.ም አሥር ሺህ ሃያ ስድስት፤ በ፳፻፲፭ ዓ.ም አሥራ ሁለት ሺህ አራት መቶ ሃምሳ አምስት ተመራቂዎች ተካ’ተዋል፡፡ የእያንዳንዱ ዓመት ተመራቂዎች ዳታም እንደ ተካተትና አንድ ተመራቂ ተማሪ አገልግሎቱን በስድሣ ብር ማግኘት እንደቻለ በምረቃው ሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል፡፡
የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎች ከምረቃ በኋላ የሚያጋጥሟቸው ፈተናዎች
በመ/ር ተመስገን ዘገዬ
ክፍል ፪
የተከበራችሁ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎቻችን በክፍል አንድ ዝግጅታችን ከምረቃ በኋላ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን በተመለከተ ሦስት ነጥቦችን ማቅረባችን ይታወሳል፡፡ እነዚህም፡- እንደተመረቁ ሥራ አለመያዝ፣ አለመረጋጋት እና መወሰን የሚሉ ነጥቦችን አይተናል፡፡ ቀጣዩቹን ነጥቦች ደግሞ በክፍል ሁለት እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
ክርስትናም በእምነት እያደጉ እየጠነከሩ የሚጓዙበት ሕይወት እንጂ ባለህበት እርገጥ ዓይነት አይደለም፡፡ አንድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተመራቂ ከትናንት ዛሬ፣ ከአምና ዘንድሮ አድጎና ጠንክሮ መገኘት አለበት፡፡ ክርስትና ቱቻ ገመድ አይደለም፡፡ ተቹ ገመድ ከሣር የሚዘጋጅ ቆርቆሮ ባልነበረበት ዘመን ለቤት መሥሪያ አገልግሎት ያገለግል ነበር፡፡ቱቻ ገመድ ውኃ ሲያገኝ በጣም ይጠብቃል፡ውኃ ሲያጣ ለመበጠስ ቀላል ነው፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች በግል ሕይወታቸው ሥጋዊውን ኑሯቸውን ከመንፈሳዊ ኑሯቸው ጋር አጣጥመው መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ብዙዎቻችን መንፈሳዊ ሥራን በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የጨረስን ይመስል ትተን እንደመጣን በሄድንበት ቦታ በዓለም ፍቅር እንደነዝዛለን፡፡ እንደ ዴማስ በሄድንበት በዓለም ተውጠን እንቀራለን፡፡ “ዴማስ የአሁኑን ዓለም ወዶ ትቶኛልና ወደ ተሰሎንቄም ሄዶአል ቄርቂስም ወደ ገላትያ ቲቶም ወደ ድልማጥያ ሄደዋል “እንዳለ ( ፪ኛ ጢሞ.፬፥፲)
መጾም መጸለይ ከትናንሽ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር በማኀበር ፡ በሰንበት ትምህርት ቤት መቀመጥ ይከብደናል፡፡ ቅዱስ ዳዊት “ወንድሞች በኀብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው፡፡እነሆም ያማረ ነው” ይላል (መዝ.133፥1) የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ከእግዚእበሔር ክብር ይልቅ የራሳችንን ክብር ይታየናል፡፡ ለሥጋችን ምቾት እንጂ ለክርስትና መስፋፋት ግዴለሾችና በእንቅልፍ ማሳለፍ እናበዛለን፡፡
ስለሆነም ከምረቃ በኋላ የምናገኘው የአካባቢና የኑሮ ለውጥ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ሊያመጣ ይችላል፡፡
ስለዚህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች በአካባቢ፣ በጓደኛ፣ በኑሮ ለውጥ ተውጠን የግል ሕይወታችን ተበላሽቶ እንዳይቀር ራሳችን መግለጽ፤ ዘወትር መጸለይ፤ ከእግዚአብሔር አለመራቅ፤ በማይመች አካሄድ አለመጠመድ፤ ከምክንያተኝነት መራቅ፤ ተስፋ አለመቁረጥ፤ ኑሮን በመርሐ ግብር መምራት፤ የምሥጢራት ተካፋይ መሆን ይገባል፡፡
ራስን መግለጽ፦ይህ ሲባል ግን እኔ የማኀበሩ አባል ነኝ፣ እኔ ሰባኪ ነኝ ማለት ሳይሆን በኑሯችን እንግለጸው ለማለት ነው፡፡ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ” ብሏል፡፡ (ማቴ .፭፥፲፮)
ክርስትና ማስመሰል ሳይሆን ሁኖ መገኘት ይፈልጋል፡፡ መንፈሳዊ ሕይወታችን ጊዜና ቦታ የሚወስነው ሳይሆን የሁል ጊዜ ኑሯችንና መታወቂያችን ነው፡፡ ምክንያቱም ክርስትና የምንተርከው ታሪክ ሳይሆን የምንኖረው ሕይወት ስለሆነ ነው፡፡ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የነበሩት “ተግባር ከቃል የበለጠ ይሰብካል“ ይላሉ፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን አንደበተ ርቱዕ የሆኑ ሰዎች አላጣችም፤ የተቸገረችው በሕይወቱ አርአያና ምሳሌ የሚሆን ሰው ግን ማግኘት በ፳፩ኛ ክፍለ ዘመን እየተቸገርን ነው፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተመራቂ ወጥ የሆነ ክርስቲያናዊ ሕይወት ሊኖረው ይገባል፡፡ ከግቢ ጉባኤው ተመረቆ ሲወጣ መንፈሳዊ አገልግሎትን የሚዘነጋ (የሚተው) ከሆነ መንፈሳዊ አገልግሎት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ገና አልገባውም ማለት ይቻላል፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ የመንፈስ ቅዱስ ልጁን ጢሞቴዎስን “ቃሉን ስበክ፣ በጊዜውም አለ ጊዜውም ጽና ፈጽመህ እየታገሥክና እያስተማርክ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም” ብሎታል፡፡ (፪ኛ ጢሞ. ፬፥፪) በነገራችን ላይ ማስተማር በዐውደ ምሕረት አትሮንስ ላይ በመሆን ማስተማር ብቻ አይደለም፡፡ በሕይወት በሥራና በተግባር ማስተማር ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች በምንሄድበት ቦታ ሁሉ፣ በቤታችን ውስጥ፣ በሠፈራችን፣ በሥራ ቦታችን ክርስትናችን በኑሯችን ሊገለጥ ይገባል፡፡ ክርስትናችን የሚነበብ መጽሐፍ መሆን አለበት ፡፡
“…በቃልና በኑሮ በፍቅርም በእምነትም፣ በንጽሕናም ለሚያምኑት ምሳሌ ሁን” (፩ኛ ጢሞ. ፬፥፲፩-፲፪) የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ከላይ በተጠቀሱት መሠረታዊ ነጥቦች ስንመዘን ምሳሌ የሚሆን ሕይወት ይኖረን ይሆን? አንዳንዶች ራስን መግለጽ ሲባል “ግብዝነት” ይመስላቸዋል፡፡ ከቤተ ክርስቲያን ተለይተው በዓለም ቀልጠው የቀሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ማንነታችን በሰዎች ዘንድ ከታወቀ ሰዎች ለእኛ ታላቅ ክብር አላቸው፡፡ ይህ ክብር የእግዚአብሔር መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ እንደ ክርስትና የሚስከብር ሌላ ምንም ነገር የለም፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች በጸሎት ሕይወት መበርታት ይኖርባቸዋል፡፡ ቅዱስ ያዕቆብ “ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች” ይላል (ያዕ. ፭÷፲፯) ማር ይስሐቅ “ዕንባሕ ከመፍሰስ እንዳያቆም ከወደድህ በጸሎት ጽሙድ ሁን” ይላል። “ጸሎት ከልዑል እግዚአብሔር ጋር የሚነጋገራት ናት” (ፍትሐ ነገሥት ንባቡና ትርጓሜው አንቀጽ ፲ ወ፬ቱ)
ጌታችንም በመከራው ሌሊት ፫ ጊዜ ጸለየ ደቀ መዛሙርቱን “ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ “አለ፡፡ (ማቴ. ፳፮÷፵፩) የዕውቀት ደጋፊዎችን ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ለጸሎት መትጋት ይኖርብናል። የዲያብሎስ አጽመ ርስት ኃጢአት እንዳይነግስብን በጸሎት ሕይወት ፍኖተ አበውን በመከተል መትጋት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች አንዱ የቤት ሥራ ነው፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተመራቂዎች ሕዋሳትን ሰብስበን በሰቂለ ኀሊና:በነቂሐ ልቡና ሁነን ወደ እግዚአብሔር መጮኽ አለብን። ከሌሊቱ ዕንቅልፍ በመቀነስ መጸለይ ብልህነት ነው ። የጸሎት መጽሐፍ፣ ምስለ ፍቁር ወልዳ በሁሉም እንቅስቃሴያችን መለየት የለባቸውም፡፡ ጥሩ የጸሎት ሕይወት ያለው ክርስቲያን አይወድቅም፣ ቢወድቅም ይነሳል፡፡
ነቢዩ “ጠላቴ ሆይ ብወድቅ እነሣለሁና በጨለማም ብቀመጥ እግዚአብሔር ብርሃን ይሆንልኛልና “እንዳለ (ሚክ. ፯፥፰) እኛም በሥራችን፣ በአገልግሎታችን መውደቅ፣ መነሣት መኖሩን መረዳት ይኖርብናል፡፡ ተስፋ መቁረጥ የለብንም፡፡
ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ለሚኒስትሮችና ለካቢኒ አባላት በሰጡት የወቅታዊ ጉዳይ ማብራሪያ አስመልክቶ ከቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ። ጥር 24 ቀን 2015 ዓ.ም.
እንደ ኦርቶዶክ ተዋሕዶ ሃይማኖት አማኝነት ስንኖር…
ካለፈው የቀጠለ…
ዲ/ን ታደለ ፈንታው (ዶ/ር)
በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት በክርስትና ሕይወታችን እንድንኖር፣እንድንለማመድ፣ገንዘብም እንድናደርግ የተፈለገው ሕይወት ውስብስብ፣ አስቸጋሪ፣ እንግዳ፣ ምናባዊ እና የማይደረስበት ሕይወትን አይደለም፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስን፣ጳውሎስን፣ዮሐንስን፣ ባስልዮስን፣ጎርጎርዮስን፣ ቄርሎስን ወይም በዘመን የከበሩ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ምስክርነት ያላቸውን ቅዱሳን አበውን እማትን አንዱን ወይም አንዷን መስተካከል፣ ማከል ሳይሆን መምሰል፣ የኑሮ ዱካቸውን፣ የሕይወት ዘይቤአቸውን በመከራ የተቀበሉትን ጽናታቸውን፣ በችግር መካከል ያለፈ ርጋታቸውን፣ በመከራ የተፈተነ ትሕትናቸውን ገንዘብ ማድረግ ነው፡፡
ሰሎሞን በርጋታ የምትመላለስ፣አምላኳን ለመፈለግ ጊዜ የማታባክንን የክርስቲያን ነፍስ እንዲህ በማለት ምክር ሲለግሣት እንመለከታለን፤«ያላወቅሽ እንደሆነ የመንጎችን ፍለጋ ተከትለሽ ውጪ»( መሓ ፩፡፰)
ስለምን መንጎች አላቸው? መንጋ ቁጥሩ በርካታ ነው፤ ዓላማ ሰንደቅ ይዞ እንደተሰለፈ ሠራዊት ነው፤ ከሩቁ ይታያል፡፡ መንጋውን የሚመራ አውራ ቀድሞ ከፊት ከፊት ይሄዳል፡፡ በፍየል መንጋ፣በከብቶች መንጋ በሌሎችም እንዲሁ ነው፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድስ ስንኳ ሊቆጥራቸው የማይችላቸው መንጎች የተመላለሱበት ቅድስት መካን ናት፡፡ እነዚህ መንጎች በሩቁ በሰውም በእግዚአብሔርም ዘንድ ይታያሉ፤ በትውልድ መካከል ያሸበርቃሉ፤ ያለ አጥር፣ ያለከልካይ፣ ያለመሪ፣ ያለአስተማሪ አልነበሩም፡፡ መንጋውን የሚመሩ፣ ከበጎቻቸው አስቀድሞ ራሳቸውን የሚሰጡ፣መከራን በበጎቻቸው ተገብተው የሚቀበሉ፤ እነርሱን ልቀቁአቸው እኔን ያዙ የሚሉ ድንቅ መሪዎች የነበሩአት አሁንም ያሏት የልዑል እግዚአብሔርን ክብር እያብለጨለጨች የምትኖር ቅድስት ናት፡፡
ምእመናንንም መንጎች አላቸው፤ መንጋ እውነተኛ የሆነውን እረኛ፤ መሪውን ተከትሎ የሚጓዝ ነውና፡፡ ስለዚህ አስቀድሞ ነቢያትን፣ በኋላም ሐዋርያትን ፣ከእነርሱ ቀጥሎ ሐዋርያነ አበውን እነርሱ የወለዱአቸው ሊቃውንትን አስነሣ የእነዚህ ሁሉ መነሣት መንጋውን በተገቢው መንገድ ለመምራት ነው፡፡
እንድንመራ የተፈለገው ሕይወት
በተግባር እንድንመራ የተፈለገው ሕይወት ቀለል ያለና ለብዙዎች ቀንበር የማይሆን የፍቅር የመተሳስብ የመረዳዳት የመከባበር የመተጋገዝ ሕይወትን ነው፡፡ ሰው አብሮት የሚኖረውን በስሜት ፣ በፍላጎት፣ በአስተሳሰብ የሚመስለውን፣ በመካከሉ የሚኖረውን፤ ጎረቤቱን ጓደኛውን የማይወድ እና የሚያገልል ከሆነ የማያውቀውን አምላኩን እንዴት እወድድሃለሁ ሊለው ይችላል? እንደምንስ መውደድ ይቻለዋል፡፡
ቅዱስ የሐንስ ወንጌላዊ ወንድሙን የሚጠላ እስካሁን በጨለማ ይኖራል፤ወንድሙን የሚወድድ በብርሃን ይኖራል፤ማሰናከያም የለበትም ወንድሙን የሚጠላ ግን በጨለማ አለ፤ በጨለማም ይመላለሳል፤ የሚሄድበትንም አያውቅም ጨለማው ዐይኖቹን አሳውሮታልና(፩ኛ ዮሐ.፪፡፫-፬) እንዳለ፡፡ ስለዚህ እንድንመራ የተጠየቅነው ሕይወት ጨለማ የተለየው ብርሃንን ማእከል ያደረገ ሕይወትን ነው፡፡ ወንጌላዊው እንዲህ በማለት ያጸናዋል፡፡ ከእርሱ የሰማናት ለእናንተም የምናወራላችሁ መልእክት እግዚአብሔር ብርሃን ነው ጨለማም በእርሱ ዘንድ ከቶ የለም የምትል ይህች ናት፡፡ (፩ኛ ዮሐ.፩፡፭)
ቀለል ያለ ሕይወት
ሌላው ቀላል ያለ ሕይወት የተባለው በመንገድ ላይ ማንም ማሰናከል የሌለበት ለማነጽ እንጂ ለማፍረስ ያይደለ፤ የሕይወት እንጂ የሞት መንገድን የማያውቅ ክርስቲያናዊ የጸሎት ሕይወት ነው፡፡ ለወንድሞቻችን ለጎረቤቶቻችን መልካም ሥራ ልንሠራላቸው፤ ወደ መልካም ሥራ እና የጸሎት ሕይወት ልንመራቸው ታዘናል፡፡
እንደ አንድ የተዋሕዶ ልጅ በጊዜ ልንነቃ፣ወገባችን ልንታጠቅ፣መብራታችንን ልናበራ በሥርዓት ልንኖር፣ በአምላካችን ፊት በኅብረት ልንቆም ታዘናል፡፡ ወንድሞች በኅብረት ቢኖሩ እነሆ መልካም ነው፤ እነሆ ያማረ ነው”እንዲል (መዝ.፻፴፫፡፩-፪) እግዚአብሔር ኃጢአታችንን፣ በደላችንን፣ ይቅር እንዲለን ልንለምነው ይገባል፡፡
የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታይ ስንሆን ብዙ ወርቅ፣ብዙ ገንዘብ ብዙ ጥሪት፣ መሬት፣ልብስ ሌላም ሌላ እንዲኖረን አይጠይቅም፤እነዚህ በጽናት እና በትዕግሥት ሆነን የአባቶቻችንን የእናቶቻችንን ዐሠረ ፍኖት ተከትለን ስንጓዝ ወደእኛ የሚመጡ እንጂ እኛ ወደ እነርሱ የምንሄድባቸው ቁም ነገር ጉዳዮች አይደሉም፡፡ አስቀድማችሁ ጽድቁንና መንግሥቱን ፈልጉ ሌላው ይጨመርላችኋል የተባለው ስለዚህ ነው፡፡
ጥንቃቄያችን
እንደ ክርስቲያን መጠንቀቅ የሚኖርብን የእግዚአብሔር የሆነውን ነገር ገንዘብ ለማድረግ በምናደርገው የዘወትር መንፈሳዊ ልምምዶች ላይ ነው፡፡ እነዚህ ልምምዶች እንድንጠነክር፣ በፈተና ተፈትነን ነጥረን እንድንወጣ፣ጸጋው እንዲበዛልን፣አእምሮአችን እንዲከፈት፣ ከእኛ በዘመን የቀደሙ አባቶቻችንና እናቶቻችን በምን አይነት መታመን እንደታመኑ የምንመለከትባቸው መነጽሮቻችን ናቸው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስን እግዚአብሔርን ለመምሰል ራስህን አስለምድ፤ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማል፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁን እና የሚመጣውን ሕይወት ተስፋ ስላለው ለነገር ሁሉ ይጠቅማል( ፩.ጢሞ.፬፡፯) በማለት ይመክራል፡፡ ነገር ግን በልምምድ ስፍራ ስንሆን ጠላት ወደ እኛ እንደሚመለከት፣ እንደሚያደባ፣ እንዲሚያታልል፣ እንደሚያባብል፣ እንደሚያስፈራራ ቢቻለው ሊያጠፋን ወደኋላ ገፍትሮ ሊጥለን እንደሚፈልግ ጠንክሮም እንደሚሠራ ማስተዋል ይገባል፡፡
ሌላው መጠንቀቅ የሚኖርብን ክርስቶስን ከሚመስል ነገር ግን ከክርስቶስ ያይደለ ሐሰተኛ አስተምህሮ ነው፡፡ ክፉ መንፈስ እና ሐሰተኛ አስተምህሮ በዓለሙ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ ተሰራጭቷል፡፡ራሳቸውን ከፍ ከፍ የሚያደርጉ ግብዞች እና ሐሰተኛ ነቢያት ተሰማርተዋል፡፡ ከተቀበልነው፣አባቶቻችን እናቶቻችን እምነት ሊያስወጡን አጥብው እየሠሩ ነው፡፡ እንደ መልካቸው ስማቸው ልዩ ልዩ ነው፡፡
እኛ ግን ዕለት ዕለት እውነተኛ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ተከታይ ሊያደርገው የሚገባውን መንፈሳዊ ሥራ ብቻ በመሥራት፣ የእኛ ወገኖች የሆኑትን ብቻ በመስማት፣ ከቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ የሚቀዳውን ትምህርት፣ ኑሮ፣ ሕይወት፣ ሥርዓት፣ልማድ፣ ወግ ፍልስፍና እና አስተሳሰብ ከፍ አድርገን ይዘን፤ ለመያዝም ጠንክረን እየሠራን በጽናት እና በጥንቃቄ ልንጓዝ ያስፈልጋል፡፡
ጥንካሬያችን
መምህራችን ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ሲያስተምረን በቃልና በኑሮ በፍቅርም ፣በእምነትም፣ በንጽሕናም፣ ለሚያምኑቱ ምሳሌ ሁን እንጂ ማንም ታናሽነትህን አይናቀው፤(፩ኛ ጢሞ.፫፡፲፪) ብሎናል፡፡በንግግር፣በግብርም የሚደረግ ፍቅራችን፣ ራስን መግዛታችንን የወጣትነት ጊዜያችንንም ፍሬያማ እና የተወደደ እንደሚያደርገው አስተውሉ፡፡
ነገር ግን እነዚህን ነገሮች በማሟላት ሂደት ውስጥ ችግር ቢገጥማችሁ፣ፈተናዎች ቢደራረቡ ጌታችን መድኃኒታችን፣ክርስቶስ ቤዛችን፣ ክርስቶስ ነጻነታችን፣ ክርስቶስ አምላካችን የበዛውን መከራ እንደተቀበለ በእምነት አስተውሉ፡፡የለበስነው ልብስ አንዳች ሌላ ነገር ሳይሆን ራሱን ክርስቶስን እንደሆነ ልብ በሉ፡፡ ይህንን ልብስ መከራ የማያጠፋው፣ ችግር የማይበግረው ሰማያዊ ልብስ እንደሆነ በፍቅር እንመልከት፡፡
ወንድሞችንና እኅቶችን ጽናት ይሰጣቸው ዘንድ፣ በእምነት ጠንክረው ይቆሙ ዘንድ፣እግሮቻቸውን የወንጌልን መጫሚያ ይጫሙ ዘንድ አንዳችን ስለሌሎቻችን ዘወትር እንጸልይ፡፡ጥበብን፣ ሰላምን፣ ትእግሥትን፣ ትሕትናን፣ ጤንነትን፣ ማስዋልን፣ ሀብትን፣ ረጅም ዕድሜን እንዲሰጠን ዘወትር በእምነት እንጠይቀው፡፡
አስቀድመን የጠቃቀስናቸውን ነገሮች በግል ሕይወታችን በቤታችን በመኝታ ክፍላችን በግቢ ጉባኤዎቻችን፣በማኅበረሰባችን፣በአገራችን ቢበዙልን የእግዚአብሔር የመንግሥቱ ወራሾች እንሆናለን፡፡ ስለዚህ ወጣትነታችንን እንደ ታላቅ ጥንካሬ ተጠቅመን ወደ እግዚአብሔር በእምነት፣ በትሕትና በፍቅር እና በየዋህነት እንቅረብ፡፡
ከእኛ ይልቅ በዕድሜ ለግላጋ የሆኑ ታናናሾቻችን ማስተማራችንን እርግጠኛ እንሁን፡፡ ቅዱስ ከሆነው ኦርቶዶክሳዊ ትውፊት ጋር ይተዋወቁ ዘንድ እንትጋ፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ ታላላቆችን እናክብር፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር ጥንቃቄ እናድርግ ከታላላቆችን መማር የሚኖርብን በጎ የሆነውነ ነገር ብቻ ነው፡፡ ክፋትን እንጥላ እናስወግደውም፡፡ እኛም ወደ አረጋዊነት የምንሄድበት ዘመን ይመጣልና አስቀድመን በኦርቶዶክሳዊ ትውፊት ያዘጋጀናቸው ወጣቶች የሚገባንን ክብር ይሰጡናል፡፡ ስለዚህ በተቻለ መጠን ሕፃናት ላይ ጊዜን ሰጥተን ዕውቀትን ለማፍሰስ እንትጋ፡፡ልጆቻችን ወንድሞቻችን የሚገባቸው ዕድሜ ላይ ሲደርሱ በካህን ቡራኬ ወደ ተቀደሰ ጋብቻ እንዲመጡ መሠረት የምንጥልበት ጊዜ የወጣትነት ጊዜ አሁን ነው፡፡
ወጣቶቻችን ጤናቸው የተጠበቀ፣ አእምሮአቸው የተጠበቀ፣ ክፋትን የማያውቅ በጎ የሆነውን ነገር ገንዘብ ለማድረግ የሚተጉ እንዲሆኑ የምንችለውን ያህል እንርዳ፡፡ ጠንካራ የሆነ ማኅበረሰብ እና ወጣትን ለመገንባት የትኩረት አቅጣጫዎቻችን ይሁኑ፡፡
ማጠቃለያ
በሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠቅ(ኤፌ.፬፡፫) በምናደርገው ፍጻሜ የሌለው ተጋድሎ የቱንም ያህ የቋንቋ፣ የአስተዳደግ የባህል ልዩነቶች ቢኖሩንም በአንድ መንፈስ በአንድ ልብ በአንድ አሳብ የክርስቶስ እንድንሆን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን አማካኝነት ተጠርተናል፡፡
ቤተ ክርስቲያን አንዲት ቅድስት፣ ኩላዊት፣ ሐዋርያዊት እና የሁላችንም መንፈሳዊ ሀብት ናት፡፡ እብሪተኞች አላዋቆች እና ሃይማኖት የሌላቸው ሰዎች እንደፈለጉ የሚያደርጓት አይደለችም፡፡ ስለዚህ መሠረታዊ የሆነው አስተሳሰባችንን በምድረ በዳ እንደደረቀችው የበለስ ዛፍ ሳይሆን በወንዝ ዳር እንደተተከለችው ዛፍ ነው፡፡
ኦርቶደክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ተከታዮች እንደመሆናችን ልዩ የአግዚአብሔር ገንዘቦች የሆንን ነን፡፡ ቤተ ክርስቲያን በሁለንተናዋ እንድታድግ አእምሯችን የፈቀደውን፣ አቅማችን የቻለውን ያህል ከማበርከት ወደኋላ አንበል፡፡
አባቶቻችንን የምንመስል፣ በተስፋ የምንጠብቅ ግዴታችንን እና መብታችንን ጠንቅቀን የምናውቅ ፣በአስተሳሰባችን ከፍ እና ላቅ ያልን ወጣቶች ሆነን ለመሥራት ዕለት ዕለት ልንተጋ ይገባል፡፡ እውነተኛ የሆነ ትጋትን እንፈልግ፤ ገንዘብም እናድርግ፡፡ በቤታችን፣ በማኅበረሰባችን፣ በግቢያችን እውነተኛ ሰላም እንድናመጣ የነገሮችን አካሂያድ በጥንቃቄ እንመርምር ፤ በእውነት ጉዳይ ደፋሮች እና ጽኑዎች እንሁን፡፡
ይቆየን!!
” ቤተ ክርስቲያን በዘርና በቋንቋ አትከፈልም ” ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሊቀጳጳስ
የብዙ ቋንቋ ተናጋሪ መሆን እድለኝነት ነው። ያለምንም. ድካም በተፈጥሮ ሂደት ካገኘነው የእናት ቋንቋችን በተጨማሪ በራስ ፍላጎትና ጥረት ተናጋሪ የሆንባቸው ቋንቋዎች የእኛን ፍላጎት ሐሳብና ጥረት የማሳየት እድል አላቸው።
ጌታችንም ቅዱሳን ሐዋርያትን ዛሬም ለምንገኘው መምህራነ ወንጌል በቅዱሳን ሐዋርያት አንጻር “ወደ ዓለም ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ”(ማር ፲፮÷፲፭) በማለት እንዳዘዘን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ዓላማዋ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ማድረስ ነውና ቋንቋ መሣሪያ ነው።
ቅዱስ ጳውሎስ “በዓለም ምናልባት ቁጥር የሌለው የቋንቋ ዓይነት ይኖራል ቋንቋም የሌለው ሕዝብ የለም፤እንግዲህ የቋንቋውን ፍች ባላውቅ ለሚናገረው እንግዳ እሆናለሁ፥ የሚናገረውም ለእኔ እንግዳ ይሆናል። እንዲሁ ደግሞ እናንተ መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ የምትፈልጉ ከሆናችሁ ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ ይላል (፩ቆሮ ፲፬÷፲-፲፪) ስለዚህ በቋንቋ ማስተማር ማንኛውም መምህር ፣ጸሓፊ፣ ተርጓሚ አብዝቶ ሊሻው የሚገባ መንፈሳዊ ስጦታ ነው።
የትኛውም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ድምር ውጤታቸው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው መታነጽያ ፣መጽደቂያ ነው። በዘፍ ፲፩÷፩ የምንመለከተው ሰዎች የተሰጡትን የቋንቋን ስጦታ በአግባቡ አለመጠቀማቸውን ነው።
በዘመነ ሐዲስ የእግዚአብሔን መንግሥት ለዓለም ሁሉ እንዲያሰሙ የተጠሩት ቅዱሳን ሐዋርያት ከሚያስፈልጋቸው ትጥቅ አንዱ ቋንቋ በመሆኑ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን ከ 15-71 ቋንቋ ገለጸላቸው።(የሐዋ•ሥራ ፪÷፩)በባቢሎን ለተገቢው አገልግሎት ያልዋለ ቋንቋ በኢየሩሳሌም በበዓለ ጰራቅሊጦስ የመለኮት ድምፅ የሆነውን ወንጌል ማስተላለፊና ምእመናንን መሰብሰቢያ ሆነ። በውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም አንድምታ መግቢያው ላይ እንደተገለጸው የግሪክን(ጽርዕ) ቋንቋ ተናጋሪው ቅዱስ ባስልዮስና የሶርያ (ሱርስት) ቋንቋ ተናጋሪው ቅዱስ ኤፍሬም በአስተርጓሚ የነበረው ውይይታቸው ያላረካው ቅዱስ ባስልዮስ ለቅዱስ ኤፍሬም ጸልዮ ቋንቋው እንዲገለጽለት በማድረግ ስለ ልዑል እግዚአብሔር ሲነጋገሩ አድረዋል።(ውዳሴና ቅዳሴ ማርያም አንድምታ)
ቅዱሳን ሐዋርያት አገልግሎታቸውን ሕዝቡ በሚያውቀው ቋንቋ በመፈጸማቸው መሰማትን አግኝተዋል።”በዕብራይስጥም ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ ከፊት ይልቅ ዝም አሉ። እርሱም አለ”ይላል (የሐዋ•ሥራ ፳፪÷፪) “የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው፤አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ ዕውቀትን መናገር ይሰጠዋል፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤”ብሏል (፩ቆሮ. ፲፪÷፬-፲)
የተለያዩ መምህራን አጫጭር ትምህርቶችን በመተርጎም የድርሻቸውን በትምህርተ ወንጌል ዓለምን ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡ ሥራዎቻቸውም ምስክሮቻቸው ናቸው ፣የቋንቋ ስጦታን በአግባቡ መጠቀም ማለት እንዲህ ነው። አሁን እየሆነ ያለው ግን አበው” ጉድ ሳይሰማ መስከረም አጠባም ” ነው፡፡
እንደ ጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ እንደ ይሁዳ የገንዘብ ቤት ቁልፍ ያዥ ለመሆን ሲሽቀዳደሙ ማየት እጅግ ያሳዝናል፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማሳ ላይ አረም በብዛት በቅሎ እየታየ ነው፡፡ ቀደምት አበውም ይህን በመንፈስ ቅዱስ ተረድተው የአረም ማጥፊያ ሥርዓት አዘጋጅተውልን አልፈዋል ፡፡
በዘመናችን ማስተዋል ጎድሏል ሕገ አበው ቦታ እያጣ በዘረኝነት ከረጢት ውስጥ መኖር እንደ መንፈሳዊነት እየተገለጸ ነው፡፡ መነኩሴ የፈለገ ችግር ቢያጋጥመው ማመልከት ያለበት ለእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ዓለምን ክዷልና ወደ ዓለማዊ ባለሥልጣን መሔድ የለበትም፡፡ ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ ስለ ነገረ ምጽአት ሲናገር “የጥፋትን ርኲሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል” ይላል(ማቴ.፳፬፥፲፭) ነገሮችን በማስተዋል ማየት ይገባል፡፡ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ስትፈተን መኖርን ገንዘቧ አድርጋለች እስከ ማለት የሚያደርስ ረዥምና ውስብስብ የፈተና ታሪክ አላት ፡፡ያለችው በዓለም ላይ ነውና፡፡
ዲያብሎስ ከእነ ጳውሎስ ሳምሣጢ ጀምሮ እነ አርዮስን፣ አቡሊናርዮስን፣ መቅዶንዮስን እና ንስጥሮስን እያስነሣ ቤተ ክርስቲያንን ሲታገላት ኖረ፡፡ይህም ከሦስተኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ እስከ አምስተኛው ምዕት ዓመት ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል፡፡ከዚያም ወዲህ ፋታ አልሰጣትም፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየሆነ ያለው ውስብስብ ፈተና የችግሩ ስፋትና ጥልቀት በሁሉም ዘንድ ያለው ዕውቅና በጣም ይለያያል፡፡
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ መጽሐፍ ” ቤተ ክርስቲያን የሁሉና በሁሉ ያለች ናት በቦታው በዘርና በቋንቋ አትከፈልም አትወሰንምና ወይም የነ ዕገሌ ናት የነ ዕገሌ ናት አይደለችም ፣አትባልም “ብለዋል (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ -ገጽ ፲፬)
-ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የቁስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ “ሰውን ብትታገልና ብትዋጋ ታሸንፈዋለህ ወይም ያሸንፍሃል ቤተ ክርስቲያንን ግን ማሸነፍ አይቻልም ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ ትዋጋለች፣ተሸንፋ ግን አታውቅም፣ዲያብሎስ ዝናሩን አራገፈ ቀስቱንም ጨረሰ። ቤተ ክርስቲያንን ግን አልጎዳትም “(የማቴዎስ ወንጌልን በተረጎመበት ምዕ.፲፮÷፲፰)
ስለዚህ “ቄስም ሆነ ዲያቆን ከሹመቱ በኃጢአት ከተሻረ በኋላ ደፍሮ ለአገልግሎት ቢገባ ከቤተ ክርስቲያን ተወግዞ ከምእመናን ይለያል እያወቀ በዚህ ድፍረቱ የተባበሩት ሁሉ ከምእመናን ይለያሉ” ይላል (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፮ ረስጠብ ፲፱ ክፍል ፬)
“አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ “ (፪ኛ.ጢሞ.፬÷፭)
በእንተ ሢመተ ኤጲስ ቆጰሳት
በመ/ር እንዳልካቸው ንዋይ
ክህነት “ተክህነ” ከሚለው የግዕዝ ግሥ የወጣ ቃል ሲሆን ትርጓሜውም አገለገለ ተሾመ መንፈሳዊ ሥልጣን ተቀበለ ማለት ነው፡፡በአጠቃላይ ዘይቤያዊ ትርጉሙ አገልግሎት ማለት ሲሆን በምሥጢር ለሹመት መመረጥን ያመለክታል፡፡
ካህን ማለትም በቁሙ ሲተረጎም ቄስ ጳጳስ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሕዝብ መሪ አስተማሪ መንፈሳዊ አባት ማለት ነው፡፡
ክህነት እግዚአብሔር ለሰው ከሰጠው ሀብት አንዱና ዋናው ነው፡፡ ክህነት ከእግዚአብሔር የሚገኝ ጸጋ መለኮታዊ ጥሪ እና ሰማያዊ ምርጫ ነው፡፡ ክህነት እንደ ምድራዊ ሹመት በዘፈቀደ የሚታደል አይደለም፡፡ እግዚአብሔር ባወቀ ተመርጠው የሚሾሙበት ጸጋ እንጂ ሁሉ ገንዘብ የሚያደርገው ሥልጣን እንዳልሆነ ወንጌላዊው ቅዱስ ማርቆስ እንዲህ አለ
‹‹ ወደ ተራራም ወጣ ራሱም የወደዳቸውን ወደርሱ ጠራ ወደ እርሱም ሄዱ ከእርሱም ጋር እንዲኖሩና ለመስበክ እንዲልካቸው ድዉዮችንም ሊፈወሱ አጋንንትንም ሊያወጡ ሥልጣን ይሆንላቸው ዘንድ አሥራ ሁለቱን አደረገ›› (ማር.፫፡፲፭ )
የመጀመርያው ሰው አዳም ከእግዚአብሔር ከተሰጡት ፯ ሀብታት በአንዱ ሀብተ ክህነት ነው፡፡ ለዚህም ነው በገነት እያለ መሥዋዕት ለእግዚአብሔር ያቀርብ እንደነበር የተጻፈው ሕጉን ትእዛዙን አፍርሶ በሰይጣን በተታለለ ጊዜ ደሙን አእዋፍ ለምግቡ ከመጣለት ፍሬ ከስንዴ ጋር ቀላቅሎ መሥዋዕት አቀረበ ፡፡
እግዚአብሔርም ዓለም የሚድነው በአንተ ደም ሳይሆን በእኔ ደም ነው ብሎታል፡፡ይህ የክህነት አገልግሎት በሦስቱ ዘመናት ማለትም በዘመነ አበው በዘመነ ኦሪት በዘመነ ወንጌል የተለየ መልክና ሥርዓት ይዞ መጥቷል፡፡
በዘመነ አበው በአበው ዘንድ የክህነቱ ሥራ እየተሠራ ኖሯል፡፡በተራራ ላይ አበው መሥዋዕት እየሰው እግዚአብሔርን እያመለኩ ኖረዋል፡፡ በዘመነ ኦሪትም በምስክሩ ድንኳን በአሮን እና በአሮን ወገኖች ይፈጸም እንደነበር ቅዱሳት መጻሕፍት ያስረዳሉ፡፡ በሐዲስ ኪዳን ግን ራሱ ክርስቶስ በሥጋ ተገልጦ በላምና በበግ የነበረው መሥዋዕት በአማናዊው በግ በክርስቶስ ተተክቶ አምላካችን በሾማቸው በ12ቱ ሐዋርያት የሐዲስ ኪዳኑ የክህነት አገልግሎት ይቀጥላል፡፡
በሐዲስ ኪዳን ካሉት የክህነት ደረጃዎች አንዱ ኤጲስ ቆጶስነት ነው፡፡
ኤጲስ ቆጳስነት የአገልግሎቱ ስም ሲሆን ባለቤቱ ኤጲስ ቆጰስ ይባላል፡፡ኤጲስ ቆጶስነት ከፍተኛው የክህነት ደረጃ ነው፡፡ ትርጉሙም የበላይ ጠባቂ መምህር ማለት ነው፡፡በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ኤጲስ ቆጰስ የሚሾመው ከቆሞሳት መካከል በትምህርቱ በትሩፋቱ ልቆ የተገኘ አባት ነው፡፡ የሚመረጠውም በሲኖዶስ ነው፡፡
ቅዱስ ጳውሎስ ለደቀ መዝሙሩ ጢሞቴዎስ ስለ ጵጵስና ሲጽፍለት ለዚህ ከፍተኛ ማዕርግ የሚመረጠው አገልጋይ ሊያሟላቸው የሚገቡ ጉዳዮችን አብሮ ጽፎለታል፡፡እንዲህ ሲል እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል … (፩.ጢሞ ፫፡፩-፯)
የማይነቀፍ
ከፍተኛው የቤተ ክርሰቲያን መዓርግ ስለሆነ የእግዚአብሔርም እንደ ራሴ ቤተ ክርስቲያንንም የሚጠብቅ ነውና ለዚህ ሹመት የሚመረጠው አገልጋይ የሚነቀፍ ጠባይ ሊኖረው አይገባም፡፡
ድንግል መነኮስ የሆነ
ቅዱስ ጳውሎስ ለልጁ ለጢሞቴዎስ ኤጲስ ቆጶስ የአንዲት ሚስት ባል እንዲሆን ጽፎለታል፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም ይህን ሲተረጉም ሐዋርያው ይህንን ትእዛዝ እንደ ግድ መስፈርት አድርጎ አላስቀመጠውም ነገር ግን ከአንድ በላይ ሚስት ያገቡትን ከዚህ ሹመት ለማገድ ነው፡፡
ይህንንም ማድረጉ በመጀመሪያዎቹ የክርስትና ጊዜያት በመሥፈርቱ ልክ የሚሆን ሰው ስላልነበረ በጊዜው ከነበሩት ሰዎች የተሻለ ቅድስናና ንጽሕና የያዙትን ለመምረጥ ነው፡፡ የድንግልና የገዳማዊ ሕይወት ከተጀመረ በኋላ ግን ከደናግል መነኮሳት መካከል ተመርጦ ይሾማል፡፡ ብሏል በቤተ ክርስቲያናችንም በ325 ዓም በኒቅያ ጉባኤ ከአገልግሎቱ ትልቅነት የተነሳ ጳጳስ ድንግላዊ እንዲሆን ተወስኗል፡፡
ልበኛ
ስለአገልግሎቱ ጥንቁቅና ንቁ መሆን አለበት ቤተ ክርሰቲያንን የሚያይበት ብዙ አይኖች ያሉት የትናንቱን የዛሬውንና የነገውን አርቆ ማየት የሚችል መሆን አለበት፡፡ ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅም አንድ ጳጳስ አንድ ጦርን ከሚመራ የጦር መኮንን በላይ ጥንቁቅ መሆን አለበት፡፡
ራሱን የሚገዛ
ራስን መግዛት ትልቁ የኦርቶዶክሳዊነት መለኪያ ነው፡፡ ሐዋርያውም በመልእክቱ የመንፈስ ቅዱስ ፍሬ በማለት ገልጾታል፡(ገላ ፭፡፳፫) ራስን መግዛት ለአንድ ምዕመን በጣም አስፈላጊ ከሆነ ለምዕመናን ጠባቂማ እጅጉን አስፈላጊ ይሆናል ፡፡ ራሱን የገዛ ዓለምን መግዛት ይችላል አዳም በገነት ሲኖር ራሱን በመግዛቱ ፍጥረታት በመላ ተገዙለት ራሱን መግዛት ቢሳነው ግን ፍጥረታት በመላ ጠላት ሁነው ተነሱበት፡፡ አምላክም ሰው የሆነው ሰውን ራሱን መግዛት ወደሚችልበት መዓርግ ለመመለስ እና ከራሱ ጋር አስታርቆ ፍጥረት ሁሉ እንዲወዳጀው ለማድረግ ነው፡፡
እንደሚገባው የሚሠራ
የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን አገልጋይ እንደመሆኑ ሊሠራ የሚገባውን ሥራ ሐዋርያት በሲኖዶስ ሠለስቱ ምዕትም በፍትሐ ነገሥት እንዲሠራ የተናገሩትን በትጋት በአግባቡ የሚሠራ መሆን ይኖርበታል፡፡ ከመዓርጉ የተነሳ ሊሠራ የማይገባውን ከማድረግ መከልከል ይኖርበታል ምክንያቱም ምዕመናን አብነት እንዳያጡ እርሱም የማይገባ ሥራ ሠርተዉ እንደተቀጡ እንደ ናዳብና አብዩድ እንዳይቀሰፍ መጠንቀቅ ይገባዋል (ዘሌ.፲፡፩)
ገንዘብ የማይወድ
የአንድ አባት ገንዘቡ ቤተ ክርስቲያንና ምዕመናን ናቸው፡፡ ጌታም ለቅዱስ ጴጥሮስ አደራ ጠብቅ ብሎ የሠጠው ገንዘብ በጎች ጠቦቶችና ግልገሎች ናቸው፡፡ማለትም ከታናሽ እስከ ታላቅ ያሉ ምዕመናንን መጠበቅ ዋናው ተግባሩ እንደሆነ ያሳያል ( ዮሐ.፳፩፡፲፭-፲፯) ከላይ በተወሰነ መልኩ ያየናቸው የአንድ ኤጲስ ቆጶስ መገለጫዎች ሲሆኑ የሚሾምበትን ሥርዓት ተመልክተን የጽሑፋችን ሐሳብ እንቋጫለን፡፡
ሥርዓተ ሢመተ ኤጲስ ቆጳሳት
ኤጲስ ቆጶስ ከ፶ ዓመት በታች እንዳይሾም ተከልክሏል ‹‹ወዘኢኮነ ሕይወቱ ሕፁፀ እም ፶ ዓመት›› ፍት.ነገ አን ፭/ ዲድ .፬
ብሉይና ሐዲስ የተማረ
የሚሾመውም በሚሾምበት ሀገር በምእመናን ምርጫና በርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ (ፓትርያርኩ) ፈቃድ ነው፡፡ካህናቱና ሕዝቡ እንዲሾምላቸው ኤጲስ ቆጶስ የሚሆነውን ቆሞስ መርጠው ሲያቀርቡ ስለ ደግነቱና ትሩፋቱ ስለንጽሕናውና ከነውር የራቀ ስለመሆኑ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ሦስት ጊዜ እየመላለሰ ማረጋጋጫ ይጠይቃቸዋል፡፡ ሕዝቡም አረጋግጠው የሚገባው ነው ብለው ሦስት ጊዜ መልስ ይሰጣሉ በሦስተኛው ሕዝቡ መልስ ሲሰጡ እጃቸዋን አንስተዉ ይገባዋል እያሉ ያጨበጭባሉ፡፡
ደግነቱ ያልታወቀ አይሾምም
ሲሾም ካህናቱም ሕዝቡም በሙሉ ተገኝተዉ እየመሰከሩለት ነው የሚሾመው ‹‹ወኩሎሙ ሰብእ ይንበሩ በእንተ ተሠይሞቱ ሕዝብኒ ወካህናት እንዘ ስምዐ ይከውኑ ሎቱ›› በአንድ ዘመን በአንድ ወንበር ሁለት ሰዎች ፓትርያርክ ሆነው አይሾሙም፡፡
-ርእሰ ሊቃነ ጳጶሳት ሲሾም ሊቃነ ጳጳሳት ኤጲስ ቆጰሳት ይገኛሉ፡፡ይህ ሹመት ያለ ኤጲስ ቆጶሳት ጉባኤ አይደረግም (ፍት.መን አን.፬ ) ሊቀ ጳጳሳቱ ወይም ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ የታመመ እንደሆነ እስከሚድን የታሠረ እንደሆነ እስከ ሚፈታ ይጠበቃል ሹመቱ ለሌላ አይሰጥም፡፡ (ፍት.መን. አን 4)
በአጠቃላይ ከብዙ በጥቂቱ ሥርዓተ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ይህን ይመስላል፡፡አሁን በአለንበት ጊዜ ግን እነዚህን ሥርዓታት ባለመከተል ከሐዋርያት ሲኖዶስ እና ከፍትሐ ነገሥት ትምህርት ውጭ ኤጲስ ቆጶሳትን ሾምን የሚሉ አካላት እየመጡ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ይህን ትምህርት በማወቅ ክፉውን ከደጉ ሃይማኖቱን ከክህደት ጽድቁን ከኃጢአት ሥርዓቱን ሥርዓት ካልሆነው በመለየት በአባቶቻችን ትምህርት መጽናት ይገባል፡፡ የእግዚአብሔር ቸርነት የወላዲተ አምላክ አማላጅነት የቅዱሳን ጸሎት ይርዳን፡፡
ምንጭ ፡ፍትሐ ነገሥትና
-ድዲስቅልያ