” ቤተ ክርስቲያን በዘርና በቋንቋ አትከፈልም ” ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ሊቀጳጳስ

የብዙ ቋንቋ ተናጋሪ መሆን እድለኝነት ነው። ያለምንም. ድካም በተፈጥሮ ሂደት ካገኘነው የእናት ቋንቋችን በተጨማሪ በራስ ፍላጎትና ጥረት ተናጋሪ የሆንባቸው ቋንቋዎች የእኛን ፍላጎት ሐሳብና ጥረት የማሳየት እድል አላቸው።
ጌታችንም ቅዱሳን ሐዋርያትን ዛሬም ለምንገኘው መምህራነ ወንጌል በቅዱሳን ሐዋርያት አንጻር “ወደ ዓለም ሂዱ ወንጌልንም ለፍጥረት ሁሉ ስበኩ”(ማር ፲፮÷፲፭) በማለት እንዳዘዘን የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተቀዳሚ ዓላማዋ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ማድረስ ነውና ቋንቋ መሣሪያ ነው።
ቅዱስ ጳውሎስ “በዓለም ምናልባት ቁጥር የሌለው የቋንቋ ዓይነት ይኖራል ቋንቋም የሌለው ሕዝብ የለም፤እንግዲህ የቋንቋውን ፍች ባላውቅ ለሚናገረው እንግዳ እሆናለሁ፥ የሚናገረውም ለእኔ እንግዳ ይሆናል። እንዲሁ ደግሞ እናንተ መንፈሳዊ ስጦታን በብርቱ የምትፈልጉ ከሆናችሁ ቤተ ክርስቲያንን ለማነጽ እንዲበዛላችሁ ፈልጉ ይላል (፩ቆሮ ፲፬÷፲-፲፪) ስለዚህ በቋንቋ ማስተማር ማንኛውም መምህር ፣ጸሓፊ፣ ተርጓሚ አብዝቶ ሊሻው የሚገባ መንፈሳዊ ስጦታ ነው።
የትኛውም የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች ድምር ውጤታቸው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው መታነጽያ ፣መጽደቂያ ነው። በዘፍ ፲፩÷፩ የምንመለከተው ሰዎች የተሰጡትን የቋንቋን ስጦታ በአግባቡ አለመጠቀማቸውን ነው።
በዘመነ ሐዲስ የእግዚአብሔን መንግሥት ለዓለም ሁሉ እንዲያሰሙ የተጠሩት ቅዱሳን ሐዋርያት ከሚያስፈልጋቸው ትጥቅ አንዱ ቋንቋ በመሆኑ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን የልደት ቀን ከ 15-71 ቋንቋ ገለጸላቸው።(የሐዋ•ሥራ ፪÷፩)በባቢሎን ለተገቢው አገልግሎት ያልዋለ ቋንቋ በኢየሩሳሌም በበዓለ ጰራቅሊጦስ የመለኮት ድምፅ የሆነውን ወንጌል ማስተላለፊና ምእመናንን መሰብሰቢያ ሆነ። በውዳሴ ማርያምና ቅዳሴ ማርያም አንድምታ መግቢያው ላይ እንደተገለጸው የግሪክን(ጽርዕ) ቋንቋ ተናጋሪው ቅዱስ ባስልዮስና የሶርያ (ሱርስት) ቋንቋ ተናጋሪው ቅዱስ ኤፍሬም በአስተርጓሚ የነበረው ውይይታቸው ያላረካው ቅዱስ ባስልዮስ ለቅዱስ ኤፍሬም ጸልዮ ቋንቋው እንዲገለጽለት በማድረግ ስለ ልዑል እግዚአብሔር ሲነጋገሩ አድረዋል።(ውዳሴና ቅዳሴ ማርያም አንድምታ)
ቅዱሳን ሐዋርያት አገልግሎታቸውን ሕዝቡ በሚያውቀው ቋንቋ በመፈጸማቸው መሰማትን አግኝተዋል።”በዕብራይስጥም ቋንቋ ሲናገር በሰሙ ጊዜ ከፊት ይልቅ ዝም አሉ። እርሱም አለ”ይላል (የሐዋ•ሥራ ፳፪÷፪) “የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው፤አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ ዕውቀትን መናገር ይሰጠዋል፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤”ብሏል (፩ቆሮ. ፲፪÷፬-፲)
የተለያዩ መምህራን አጫጭር ትምህርቶችን በመተርጎም የድርሻቸውን በትምህርተ ወንጌል ዓለምን ለማዳረስ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፡ ሥራዎቻቸውም ምስክሮቻቸው ናቸው ፣የቋንቋ ስጦታን በአግባቡ መጠቀም ማለት እንዲህ ነው። አሁን እየሆነ ያለው ግን አበው” ጉድ ሳይሰማ መስከረም አጠባም ” ነው፡፡

እንደ ጴጥሮስ የመንግሥተ ሰማያት ቁልፍ ለማግኘት ከመሞከር ይልቅ እንደ ይሁዳ የገንዘብ ቤት ቁልፍ ያዥ ለመሆን ሲሽቀዳደሙ ማየት እጅግ ያሳዝናል፡፡ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ማሳ ላይ አረም በብዛት በቅሎ እየታየ ነው፡፡ ቀደምት አበውም ይህን በመንፈስ ቅዱስ ተረድተው የአረም ማጥፊያ ሥርዓት አዘጋጅተውልን አልፈዋል ፡፡
በዘመናችን ማስተዋል ጎድሏል ሕገ አበው ቦታ እያጣ በዘረኝነት ከረጢት ውስጥ መኖር እንደ መንፈሳዊነት እየተገለጸ ነው፡፡ መነኩሴ የፈለገ ችግር ቢያጋጥመው ማመልከት ያለበት ለእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም ዓለምን ክዷልና ወደ ዓለማዊ ባለሥልጣን መሔድ የለበትም፡፡ ጌታችን ለደቀ መዛሙርቱ ስለ ነገረ ምጽአት ሲናገር “የጥፋትን ርኲሰት በተቀደሰችው ስፍራ ቆሞ ስታዩ አንባቢው ያስተውል” ይላል(ማቴ.፳፬፥፲፭) ነገሮችን በማስተዋል ማየት ይገባል፡፡ ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ስትፈተን መኖርን ገንዘቧ አድርጋለች እስከ ማለት የሚያደርስ ረዥምና ውስብስብ የፈተና ታሪክ አላት ፡፡ያለችው በዓለም ላይ ነውና፡፡
ዲያብሎስ ከእነ ጳውሎስ ሳምሣጢ ጀምሮ እነ አርዮስን፣ አቡሊናርዮስን፣ መቅዶንዮስን እና ንስጥሮስን እያስነሣ ቤተ ክርስቲያንን ሲታገላት ኖረ፡፡ይህም ከሦስተኛው ምዕተ ዓመት ጀምሮ እስከ አምስተኛው ምዕት ዓመት ብዙ ዋጋ አስከፍሏታል፡፡ከዚያም ወዲህ ፋታ አልሰጣትም፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እየሆነ ያለው ውስብስብ ፈተና የችግሩ ስፋትና ጥልቀት በሁሉም ዘንድ ያለው ዕውቅና በጣም ይለያያል፡፡
ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ መጽሐፍ ” ቤተ ክርስቲያን የሁሉና በሁሉ ያለች ናት በቦታው በዘርና በቋንቋ አትከፈልም አትወሰንምና ወይም የነ ዕገሌ ናት የነ ዕገሌ ናት አይደለችም ፣አትባልም “ብለዋል (የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክ -ገጽ ፲፬)
-ሊቁ ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የቁስጥንጥንያው ሊቀ ጳጳስ “ሰውን ብትታገልና ብትዋጋ ታሸንፈዋለህ ወይም ያሸንፍሃል ቤተ ክርስቲያንን ግን ማሸነፍ አይቻልም ቤተ ክርስቲያን ሁል ጊዜ ትዋጋለች፣ተሸንፋ ግን አታውቅም፣ዲያብሎስ ዝናሩን አራገፈ ቀስቱንም ጨረሰ። ቤተ ክርስቲያንን ግን አልጎዳትም “(የማቴዎስ ወንጌልን በተረጎመበት ምዕ.፲፮÷፲፰)
ስለዚህ “ቄስም ሆነ ዲያቆን ከሹመቱ በኃጢአት ከተሻረ በኋላ ደፍሮ ለአገልግሎት ቢገባ ከቤተ ክርስቲያን ተወግዞ ከምእመናን ይለያል እያወቀ በዚህ ድፍረቱ የተባበሩት ሁሉ ከምእመናን ይለያሉ” ይላል (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፮ ረስጠብ ፲፱ ክፍል ፬)
“አንተ ግን ነገርን ሁሉ በልክ አድርግ “ (፪ኛ.ጢሞ.፬÷፭)

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *