“መልአክን በፊትህ እሰድዳለሁ።” (ዘፀ. ፳፫፥፳)
በመምህር ይበልጣል ጋሹ
የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ የሚያደርገው ጉዞ እንደ እንግዳና እንደ መንገደኛ ነው። ከልጅነት እስከ ዕውቀት፣ ከቤተሰብ እቅፍ ወጥቶ ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት እስኪገባ ድረስ የሚያልፍባቸው መንገዶች ብዙ ናቸው። በተለይም የዩኒቨርሲቲ ወይም የኮሌጅ ቆይታ (የግቢ ሕይወት) ለአንድ ወጣት ክርስቲያን ትልቅ የሽግግር ምዕራፍ ነው። ከቤተሰብ ቁጥጥር ተለይቶ ራሱን ችሎ የሚኖርበት፣ አዳዲስ ባሕሎችንና አስተሳሰቦችን የሚጋፈጥበት፣ እንዲሁም የነገ ሕይወቱን መሠረት የሚጥልበት ወሳኝ ወቅት ነው።
እግዚአብሔር አምላክ እስራኤል ዘሥጋን ከግብጽ ባርነት አውጥቶ ወደ ተስፋዪቱ ምድር (ከነዓን) ሲመራቸው፣ በበረሃው ጉዞ ብቻቸውን አልተዋቸውም ነበር። አስፈሪውን ምድረ በዳ አልፈው ወደ አዘጋጀላቸው ርስት እስኪገቡ ድረስ የሚመራቸውንና የሚጠብቃቸውን መልአክ ከፊታቸው ሰድዶላቸዋል።
ዛሬም እኛ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች ከዓለም ፈተና ወጥተን ወደ ተስፋይቱ መንግሥተ ሰማያት በምናደርገው መንፈሳዊ ጉዞም ሆነ በትምህርት ሕይወታችን፣ ቅዱሳን መላእክት ከፊታችን ተልከው ይጠብቁናል። ይህ ጽሑፍ የቅዱሳን መላእክትን አገልግሎትና በግቢ ሕይወታችን የእነርሱን ረድኤት እንዴት ማግኘት እንደምንችል በመጽሐፍ ቅዱስና በቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ መሠረት ይዳስሳል።
፩. የቅዱሳን መላእክት አገልግሎት
መልአክ የሚለው “ተለአከ” ከሚለው የግእዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም “መልእክተኛ፣ አገልጋይ፣ ተላላኪ” ማለት ነው። ቅዱስ ጳውሎስ ስለ መላእክት ማንነትና አገልግሎት ሲናገር “ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?” (ዕብ. ፩፥፲፬) በማለት ይገልጻቸዋል። በቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት የቅዱሳን መላእክት አገልግሎት በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይጠቃለላል፦
ሀ.እግዚአብሔርን ማመስገን፦ የቅዱሳን መላእክት ቀዳሚና ቋሚ ተግባራቸው ፈጣሪያቸውን ያለማቋረጥ ማመስገን ነው። ምግባቸውም ሆነ መጠጣቸው ምስጋና ነው። ነቢዩ ኢሳይያስ በራእዩ ሱራፌል በእግዚአብሔር ዙፋን ዙሪያ ቆመው ፊታቸውንና እግራቸውን በክንፎቻቸው ሸፍነው “ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፤ ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች” እያሉ ሲያመሰግኑ ተመልክቷል። (ኢሳ. ፮፥፪-፫)
በሐዲስ ኪዳንም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቤተልሔም በተወለደ ጊዜ ብዙ የሰማይ ሠራዊት ከመልአኩ ጋር ሆነው “ክብር ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን ሰላምም በምድር ለሰውም በጎ ፈቃድ” እያሉ ዘምረዋል። (ሉቃ. ፪፥፲፫-፲፬) ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊም በራእዩ መላእክት ሌትና ቀን ሳያርፉ እግዚአብሔርን እንደሚያመሰግኑ መስክሯል። (ራእ. ፬፥፰)
ለ.ወደ ሰው ልጆች መላክ፦ መላእክት የእግዚአብሔርን የምሥራች ቃል፣ ትእዛዝ፣ ማጽናኛና ማስጠንቀቂያ ለሰው ልጆች ለማድረስ ይላካሉ። ቅዱስ ገብርኤል ወደ ካህኑ ዘካርያስ ተልኮ የመጥምቁ ዮሐንስን መወለድ ሲያበሥር “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ፤ እንድናገርህም ይህችንም የምሥራች እንድሰብክልህ ተልኬአለሁ” ብሎታል። (ሉቃ. ፩፥፲፱) ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያምም የዓለም መድኃኒት ከእርሷ እንደሚወለድ የምሥራች ነግሯታል። (ሉቃ. ፩፥፳፮-፴፰) ከዚህም ባለፈ የእግዚአብሔርን ቁጣና ፍርድ ለማስፈጸም፣ እንደ ሰዶምና ገሞራ ያሉ ኃጢአተኛ ከተሞችን ለማጥፋትም ሆነ ጻድቁን ሎጥን ከጥፋት ለማዳን መላእክት ተልከዋል። (ዘፍ. ፲፱፥፩-፳፪)
ሐ.ማማለድና የሰው ልጆችን መጠበቅ፦ ቅዱሳን መላእክት ለሰው ልጆች ካላቸው ፍቅርና ርኅራኄ የተነሣ ስለ ሰው ልጆች ኃጢአት ወደ እግዚአብሔር ይማልዳሉ፤ የሰዎችንም ጸሎትና መባ ወደ ሰማይ ያሳርጋሉ። ነቢዩ ዘካርያስ በራእዩ የእግዚአብሔር መልአክ ስለ ኢየሩሳሌምና ስለ ይሁዳ ከተሞች “አቤቱ የሠራዊት ጌታ ሆይ እነዚህን ሰባ ዓመት የተቈጣሃቸውን ኢየሩሳሌምንና የይሁዳን ከተሞች የማትምራቸው እስከ መቼ ነው?” እያለ ሲማልድ ሰምቷል። (ዘካ. ፩፥፲፪) መልአኩ ቅዱስ ሩፋኤልም ለጦቢት ሲገለጥለት “አንተና ሣራ በጸለያችሁ ጊዜ ጸሎታችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት ያሳረግሁት እኔ ነኝ” በማለት የመላእክትን የምልጃና የጸሎት አሳራጊነት አገልግሎት አረጋግጧል። (ጦቢት ፲፪፥፲፪)
ከምልጃቸው ጎን ለጎን ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎችን ከመከራ ሥጋና ከመከራ ነፍስ ይጠብቃሉ። ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት “የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፤ ያድናቸውማል” (መዝ. ፴፬፥፯) እንዲሁም “በመንገድህ ሁሉ ይጠብቁህ ዘንድ መላእክቱን ስለ አንተ ያዝዛቸዋልና፤ እግርህም በድንጋይ እንዳትሰናከል በእጆቻቸው ያነሡሃል” (መዝ. ፺፩፥፲፩-፲፪) በማለት ዘምሯል። በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ሠለስቱ ደቂቅን ከሚነድ እሳት ያወጣቸው (ዳን. ፫፥፳፭) ነቢዩ ዳንኤልን የአንበሶችን አፍ የዘጋለት (ዳን. ፮፥፳፪) ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስንም የእስር ቤቱን ሰንሰለት በጥሶ ያወጣው (ሐዋ. ፲፪፥፯) የእግዚአብሔር መልአክ ነው።
፪. በግቢ ሕይወታችን መላእክት ሊራዱን የሚችሉት እንዴት ነው?
የግቢ ሕይወት እንደ ምድረ በዳ ጉዞ ብዙ ፈተናዎች አሉት። የትምህርት ጫናው፣ የኢኮኖሚ እጥረቱ፣ ከቤተሰብ መራቁ የሚፈጥረው ብቸኝነት፣ እንዲሁም በዙሪያችን ያሉ የተለያዩ ዓለማዊ አመለካከቶችና የኃጢአት መስሕቦች በቀላሉ ሊያንገዳግዱን ይችላሉ። በዚህ ወቅት ቅዱሳን መላእክት ከጎናችን ሆነው እንዲራዱንና ከውድቀት እንዲጠብቁን ከእኛ የሚጠበቁ ሦስት መሠረታዊ ነገሮች አሉ፦
ሀ. የእግዚአብሔርን ፈቃድ ስንፈጽም: እግዚአብሔር መልአኩን የሚልከው በመንገዱ ለሚሄዱና ፈቃዱን ለሚፈጽሙ ልጆቹ ነው። የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም ማለት በመንፈሳዊ ሕይወታችን መበርታት ብቻ ሳይሆን፣ ወደ ዩኒቨርሲቲ የመጣንበትን ዋና ዓላማ (ትምህርታችንን)በታማኝነትና በትጋት መወጣትም ጭምር ነው። ቅዱስ ጳውሎስ “ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደምታደርጉ የምታደርጉትን ሁሉ በትጋት አድርጉት” (ቆላ. ፫፥፳፫) እንዳለ በትምህርታችን ስንተጋ፣ በጸሎትና በቅዳሴ ስንበረታ፣ በግቢ ጉባኤ አገልግሎት ስንሳተፍና እርስ በርሳችን ስንዋደድ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እየፈጸምን ነው። ቅዱሳን መላእክት ደግሞ የእግዚአብሔር ፈቃድ በሚፈጸምበት ቦታ ይገኛሉ፤ በትምህርታችን ማስተዋልንና ጥበብን እንድናገኝ ይራዱናል፣ የፈተና ወቅት ሲመጣም ፍርሃትን አርቀው ያጽናኑናል።
ለ. ከክፉ ሥራ ስንርቅ:- እግዚአብሔር ለእስራኤል መልአኩን እንደሚልክላቸው ቃል ከገባላቸው በኋላ ወዲያውኑ አክሎ የሰጣቸው ጥብቅ ማስጠንቀቂያ አለ፦ “በፊቱ ተጠንቀቅ፤ ቃሉንም አድምጥ፤ ስሜም በእርሱ ስለ ሆነ ኃጢአት ብትሠራ ይቅር አይልምና አታስመርረው” (ዘፀ. ፳፫፥፳፩) ቅዱሳን መላእክት በተፈጥሯቸው ንጹሓንና ቅዱሳን ስለሆኑ ኃጢአትን፣ ርኩሰትንና ክፉ ሥራን ይጸየፋሉ። በኃጢአት ስንመላለስ ጠባቂ መልአካችንን እናሳዝነዋለን፤ ከእኛም እንዲርቅ እናደርገዋለን።
በግቢ ሕይወት ውስጥ “ማን ያየኛል?”በሚል ስሜት ወደ ሱስ፣ ወደ ዝሙት፣ ወደ ኩረጃ፣ ወደ ሐሜትና ወደ ክፉ ጓደኝነት የሚገቡ ተማሪዎች ብዙ ናቸው። ነገር ግን ሰው ባያየንም የእግዚአብሔር ዐይንና ጠባቂ መልአካችን ሁልጊዜ ከእኛ ጋር ናቸው። ስለዚህ የመላእክት ጥበቃ እንዳይለየን ከፈለግን ከክፉ ሥራና ከክፉ ጓደኝነት በመራቅ ሰውነታችንን በንጽሕና መጠበቅ ይኖርብናል።
ሐ. መልአኩ የሚነግረንን ምክርና የምሥራች ቃል ስንሰማ (ስንታዘዝ)፦ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የበለዓም ታሪክ (ዘኍ. ፳፪) ለእኛ ትልቅ ትምህርት ይሰጠናል። በለዓም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመርገም በተጓዘ ጊዜ የእግዚአብሔር መልአክ የተመዘዘ ሰይፍ ይዞ በመንገዱ ላይ ቆመ። በለዓም ግን በገንዘብና በክብር ፍቅር ዐይኑ ታውሮ ስለነበር መልአኩን አላየውም፤ አህያዪቱ እንኳ መልአኩን አይታ ስትቆም እርሱ ግን ይመታት ነበር። በመጨረሻም እግዚአብሔር የበለዓምን ዐይን ሲከፍትለት መልአኩን አየ፤ መልአኩም “እነሆ መንገድህ በፊቴ ጠማማ ሆኖአልና ልቋቋምህ ወጥቻለሁ… ነገር ግን እኔ የምነግርህን ቃል ብቻ ተናገር” (ዘኍ. ፳፪፥፴፪-፴፭) አለው።
ዛሬም በግቢ ሕይወታችን ውስጥ ወደ ጥፋት መንገድ ስንሄድ፣ ከሃይማኖታችንና ከሥነ ምግባራችን ስንወጣ መልአኩ በኅሊናችን፣ በንስሓ አባታችን፣ በመንፈሳዊ ወንድሞቻችንና እኅቶቻችን፣ እንዲሁም በግቢ ጉባኤ ትምህርት አማካኝነት የማስጠንቀቂያና የምሥራች ቃሉን ይነግረናል። የመልአኩን ድምፅ ሰምተን ከጠማማ መንገዳችን ስንመለስና የእግዚአብሔርን ቃል ስንታዘዝ መንገዳችን ሁሉ ይቀናል፤ ወዳዘጋጀልን የስኬትና የድኅነት ስፍራም በሰላም ያደርሰናል።
ውድ የግቢ ጉባኤ ተማሪዎች! በዩኒቨርሲቲ ቆይታችን ብቻችንን አይደለንም። የእግዚአብሔር ዐይን ይመለከተናል፤ የቅዱሳን መላእክት እጆችም ይደግፉናል። እኛ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እየፈጸምን፣ ከኃጢአት እየራቅንና የመላእክት ተራዳኢነትን አምነን መንፈሳዊ ምክር እየሰማን መገኘት ይኖርብናል። እንዲህ ሆነን ከተገኘን ጌታችን በቃሉ እንዳለው መልአኩ በመንገዳችን ሁሉ ይጠብቀናል፤ የትምህርት ዘመናችን በስኬት አጠናቀን ወደ ቤተሰቦቻችንና ወደ ሀገራችን በሰላም እንድንመለስ፣ በመጨረሻም ወዳዘጋጀልን ሰማያዊት ርስት (መንግሥተ ሰማያት) እንድንገባ ይረዳናል።
የቅዱሳን መላእክት ጥበቃና ምልጃ በግቢ ቆይታችን ሁሉ ከእኛ ጋር ይሁን!
ስብሐት ለእግዚአብሔር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር አሜን።

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!