‹‹በጊዜውም አለጊዜውም ጽና» (፪ኛ ጢሞ. ፬፥፪)
በዲ/ን ፍቃደሥላሴ ወ/ሰንበት
ክርስትና የጽናት ጉዞ ነው፡፡ «በጊዜውም አለጊዜውም ጽና» ይህ ቃል ለተማሪዎች፣ ለግቢ ጉባኤ አገልጋዮች፣ ለወጣቶች፣ ለቤተሰብ አባላት፣ ለሥራ ዓለም ሰዎችና በእምነት ጉዞ ላይ ላሉ ሁሉ የተሰጠ መንፈሳዊ ጥሪ ነው።
አንድን ሰው በመንፈሳዊ ጉዞው የሚገልጸው በመጀመሪያ ያሳየው ትጋት ብቻ አይደለም፤ በመንገዱ ላይ መሰናክል ሲገጥመው የሚያሳየው ጽናትም ነው።
መጀመር ቀላል ሊሆን ይችላል፤ መቀጠል ግን ጽናትን ይፈልጋል። በደስታ ጊዜ ማገልገል ቀላል ነው፤ በኀዘን ጊዜ ማገልገል ግን የእምነት ፈተና ነው። በተሟላ ሁኔታ መጸለይ ቀላል ነው፤ በችግርና በድካም መካከል ጸሎትን አለመተው ግን የጽናት ምልክት ነው። “በእግዚአብሔር የሚጸና አይደክምም እርሱ ያጸናችሁ ዘንድ ተከተሉት ሁሉን የሚችል ጌታ እግዚአብሐየር ብቻ ነው ከእርሱም በቀር ሌላ አዳኝ የለም” (ሲራክ ፳፬ ፥፳፬)
፩.«በጊዜውም አለጊዜውም ጽና» ሲል ምን ማለቱ ነው?
ውድ የግቢ ጉባኤ ልጆች ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሲነግረው በሰው ዓይን ለአገልግሎት የሚመች ጊዜ አለ፤ የማይመች ጊዜም አለ ብሏል። ሰዎች ሲያበረታቱን፣ ሲያመሰግኑንና ሲደግፉን ማገልገል ይቀላል። ግን ሰዎች ሲቃወሙን፣ ዝቅ ሲያደርጉን፣ ሲሳለቁብን የተቃዋሚዎቻችን ተቃውሞ መቋቋም ያቅተናል። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙረቱ ኋላም ለእኛ የተናገረውን እንዴትስ መፈጸም ይቻለናል። በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ የሚጸና ግን እርሱ ይድናል ሲል ተናግሯል። (ማቴ. ፲፥፪፳)
ክርስቶስ መስቀሉን ተሸክሞ መንገዱን ከፈተ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የድኅነታችንን ሥራ በመስቀል ፈጸመ። መስቀሉ ለዓለም የፍቅር፣ የመታዘዝና የድል ምልክት ነው። ጌታ ራሱ፦ «ማንም ከኋላዬ ሊመጣ ቢወድ ራሱን ይካድ፤ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ» አለ (ማር. ፰፥፴፬) እዚህ ላይ ጌታ የሚጠይቀን ምንድን ነው?
አንደኛ፦ ራስን መካድ ይህ ማለት ራስን መጥላት ወይም የሰውነትን ክብር ማጣት አይደለም። የራሳችንን ፈቃድ ከእግዚአብሔር ፈቃድ በላይ አለማድረግ ነው። የሥጋ ፍላጎታችን ከእውነት ጋር ሲጋጭ፣ የግል ጥቅማችን አምላካችንን ከመውደድ ጋር ሲጋጭ፣ የእኛ ፈቃድ ከጌታ ትእዛዝ ጋር ሲጋጭ የጌታን ፈቃድ መምረጥ ነው።
ሁለተኛ፦ መስቀሉን መሸከም ነው። ይህ ማለት የሚያጋጥመንን ክፉ ነገር ሁሉ በዝምታ መቀበል ማለት አይደለም። በእምነት ምክንያት የሚመጣን ችግር በትዕግሥት መቋቋም፣ በእውነት ላይ አለመደራደር፣ አንተን ተስፋ የሚያደረጉ አያፍሩም (መዝ ፳፭፤፫) እንዲል በጌታ ላይ ተስፋ አድርገን በሃይማኖታችን ምክንያት የሚያገኘን መከራ ሁሉ ሳይሰቀቁ መቀበልና በጽናት መቆየት ነው።
ሦስተኛ፦ ክርስቶስን መከተል ነው። መስቀሉን ብቻ መሸከም አይደለም፤ መስቀሉን የተሸከመው ጌታን መከተል ነው። የክርስቲያን ጽናት መሠረቱ የራሱ ጉልበት ሳይሆን የክርስቶስ ጸጋ ነው።
፫. በክርስቲያኖች ጉዞ ውስጥ የዲያቢሎስ ፈተና
ጥንተ ጠላታችን የሆነው ዲያብሎስ እኛ የሰው ልጆችን ከመፈተን መቼም ባይቦዝንም ሐዋርያው ከእኛ የንጽሕና ጉድለት እንደሆነ እንዲህ ያስተምራል፦ «በንጽሕና ጉድለታችሁ ምክንያት ሰይጣን እንዳይፈትናችሁ» (፩ቆሮ. ፯፥፭) በፍቅረ ነዋይ በኩል እንደሚፈትነን ሲነግረን «ባለጠጋ ለመሆን የሚፈልጉ በፈተናና በዲያብሎስ ወጥመድ ይወድቃሉ» (፩ጢሞ. ፮፥፱) ይላል። በሌላ ቦታም እንዲህ ይላል፦
«ምድራዊ ሰውነቶቻችሁንም ከዝሙትና ከርኩሰት፣ ከጥፋትና ከክፉ ምኞት፣ ጣዖት ጣዖት ማምለክ ከሆነው ከቅሚያም ግደሉ» (ቆላ. ፫፥፭)። በእነዚህ ነገሮች ውስጥ የዲያብሎስን ፈቃድ ስለምንፈጽም ነው። ስለዚህ ዲያብሎስ ማንንም ሰው በኃጢአቱ ሲያገኘው በራሱ ሥልጣን ሥር ሰውመሆኑን ያረጋግጣል። ቢያመነዝር፣ በቅንጦት ሕይወት ቢጠመድ፣ የሌላውን ንብረት በግፍ ቢወስድ፣ የዲያብሎስ ድርሻ ይሆናል። ንጹሕ የሆነ፣ ራሱን የሚገዛ፣ መሐሪ የሆነ ሰው ግን የክርስቶስ ድርሻ ነው። ነገርግን የክርስቶስን አገልጋይ ዲያብሎስ የራሱ አድርጎ መውሰድ አይችልም፤ ከዚያ በፊት በኃጢአት ውስጥ ወድቆ ካገኘው በስተቀር፤ በዚያ ጊዜም እንኳን በቀጥታ አይወስደውም፤ እንደ ራሱ የሆነ ሰው አሳልፈው እንዲሰጡት ይጠይቃል። ስለዚህ ዳዊት፦«ፍርድንና ጽድቅን ፈጸምሁ» ሲል ራሱን ለማስመስገን ሳይሆን ለመከላከል ነው፤ የሐዋርያት ትምህርትም ለምን ሰው ለሰይጣን እንደሚሰጥ ምሳሌ ይሆነናል። የአባቱን ሚስት የወሰደውን ሰው በዚያ የኃጢአት ሥራ ምክንያት ለሰይጣን አሳልፌ ሰጠሁት ይላል ሐዋርያው (፩ኛ ቆሮ. ፭፥፬-፭) ስለዚህ የዲያብሎስን ሥራ ባይሠራ ኖሮ አሳልፎ አይሰጥም ነበር።
ስለዚህ ነቢዩ ለግፈኞች አሳልፎ እንዳይሰጥ መጠየቁ ተገቢ ነው፤ እርሱ የዲያብሎስን ሥራ ሳይሆን የክርስቶስን ሥራ እንደሠራ ይመሰክራልና። ሰው የዲያብሎስን ፈቃድና የሥጋ ምኞትን ሲከተል ለጠላት አሳልፎ ይሰጣል፤ የእግዚአብሔርን ሕግና ፍትሕ ሲጠብቅ ግን በክርስቶስ ጸጋ ሥር ይኖራል።
፬. በጊዜውም አለጊዜውም ለመጽናት ምን እናድርግ
፬.፩ በቃለ እግዚአብሔር እንኑር
«ቃልህ ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው።» (መዝ. ፻፲፰፥፻፭) እንዲል ቃለ እግዚአብሔር በጨለማ ውስጥ የሚመራ መብራት ነው። አምብሮስ ይህንን ሲያብራራ መብራት ለምን ያስፈልጋል? በዓለም ጨለማ ውስጥ ብዙ ጉድጓዶችና ድንጋያማ መንገዶች አሉ፤ መብራቱ ከሌለን የምንረግጠውን ቦታ ማወቅ አንችልም። ብርሃን ባለበት መንገድ ላይ ሰው እግሩን የት እንደሚያኖረው ያውቃል። የሕይወት ጨለማ ሲከበን፤ የምንወስነውን ነገር ሳናውቅ ስንቀርና የሰዎች ምክር ሲያደናግረን ቃሉ ይመራናል። ስለዚህ ነቢዩ የሚያሳየንን መብራት ከፊታችን እናድርግ፤ እግራችንንም በዚያ እንምራ። ይህ መብራት ቃለ እግዚአብሔር ነው። (አምብሮስ መዝሙረ ዳዊት ፻፲፰ ማብራርያ)
በጉባኤ ውስጥ ቃሉን ሰምቶ ብቻ የሚደሰት፣ ከጉባኤው ሲወጣ ግን የሰማውን የሚረሳ ሰው መብራቱን በቤቱ ውስጥ ያጠፋ ሰው ነው። በጉባኤ ብቻ ብርሃን መሆን አይበቃም፤ በቤት፣ በትምህርት፣ በሥራና በግንኙነት ውስጥም ቃሉ መብራታችን መሆን አለበት። በግቢ ጉባኤ የምትማሩት ቃለ እግዚአብሔር በግቢው ውስጥ ብቻ እንዲቀር አትፍቀዱ። ከጉባኤ ወጥታችሁ ወደ ማኅበራዊ ሕይወት ስትመለሱ የምታደርጉትንም ጭምር ነው እንጂ ይህ ቃል ሕይወታችሁ ሊመራው ይገባል። በኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ስትሆኑ ሐሰትን እንዳትመርጡ፤ በፍቅር ግንኙነት ስትፈተኑ ንጽሕናን እንዳትተዉ፤ በሥራ ፍለጋ ስትጨነቁ በእምነታችሁ እንዳትደራደሩ። ቃሉ ለእግራችሁ መብራት ይሁን። ከእግዚአብሔር ቃል የተለየ ሰው በፈተና ጊዜ መውጫ መንገድ ይጠፋበታል። (አምብሮስ መዝሙረ ዳዊት ፻፲፰ ማብራርያ)
፬.፪. በትዕግሥት እንጽና
አምብሮስ የጽናትን ጉዳይ በተለይ ከኢዮብ ታሪክ ጋር ያያይዛል። ኢዮብ ልጆቹን አጣ፤ ሀብቱን አጣ፤ ሥጋው በከባድ ቁስል ተመታ። ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት አልተወም።
ይህ ሊቅ የኢዮብን ፈተና በሦስት መንገድ ያብራራል፦ የሀብቱ መጥፋት የትዕግሥት ፈተና ነበር። የልጆቹ መጥፋት የልብ ኀዘን ፈተና ነበር። የሥጋው ቁስል የሥጋ ሥቃይ ፈተና ነበር።
ነገር ግን እነዚህ ሁሉ የኢዮብን እምነት ለመግለጥ የሆኑ ፈተናዎች ነበሩ። አምብሮስ የኢዮብን ቃል ያስታውሰናል፦ «እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔርም ወሰደ፤ የእግዚአብሔር ስም የተባረከ ይሁን» (ኢዮብ ፩፥፳፩)።
እግዚአብሔር ኢዮብ ሀብቱን እንዲያጣ በፈቀደበት ፈተና ውስጥ የኢዮብ ትዕግሥት ተገለጠ። አትሌት ለውድድር እንደሚዘጋጅ፣ በፈተናም የጽናት ብርታት ድል በማድረጉና በማሸነፉ እንደሚገለጥ ሁሉ ከኢዮብ የምንማረው ይህ ነው።
በተጨማሪም አምብሮስ ጻድቅ ሰው በፈተና ጊዜ እግዚአብሔርን አይተውም፤ እንዲያውም በእምነቱ ለመፈተን ይዘጋጃል። የእግዚአብሔርን ፍርድ ለመጠበቅ በልቡ የወሰነ ሰው ፈተናን አይፈራም ይላል፡፡
አንድ ሰው በሥራ ሊደክም ይችላል፤ በመከራ ሊሰለች ይችላል፤ በሰዎች በደል ሊጎዳ ይችላል። ነገር ግን ተስፋ ከሌለው ትዕግሥት እስከ መጨረሻ አይቆይም። ትዕግሥት በእምነት ይጸናል፤ እምነትም ሥሩ ተስፋ ነው። ሰው ለክርስቶስ ስም መከራን ለመቀበል የሚያበረታው ይህ ተስፋ ነው። ተስፋ የሌለው ትዕግሥት ይደክማል፤ ተስፋ ያለው ትዕግሥት ግን በፈተና ውስጥ ይጸናል።
ወጣቶች ሆይ፤ በግቢ ጉባኤ ስታገለግሉ አንዳንድ ጊዜ የምግብ እጥረት፣ የመኖሪያ ችግር፣ የትምህርትና የትራንስፖርት ወጪ፣ የጤና ችግርና የሰዎች ተቃውሞ ሊያጋጥማችሁ ይችላል። በዚህ ጊዜ ኢዮብን አስታውሱ። ኢዮብ ሀብቱን ሲያጣ እምነቱን አላጣም፤ ልጆቹን ሲያጣ ተስፋውን አልተወም፤ በሥጋው ሲሰቃይ አምላኩን አልካደም። ስለዚህ የኢኮኖሚ ችግራችሁ እምነታችሁን እንዳይሸጥ፤ የሰው ጫና እውነትን እንዳያስተዋችሁ፤ የሥጋ ሕመም ጸሎታችሁን እንዳያስቆም ተጠንቀቁ፡፡
፬.፫ መከራ መስቀሉን አስበን እንከተለው
አምብሮስ የመስቀሉን ትርጉም ሲያብራራ፦ መስቀልን መሸከም ማለት ኃጢአትን ለመግደል ሥጋዊ ምኞትን መስቀል ላይ መስቀል እንደሆነ ያስተምራል። የክርስቶስ መስቀል ኃጢአትን ይገድላል፤ ፍርሃትና ሥጋዊ ምኞትን ይሰብራል፤ ከዚህ ፍርሃት በኋላ ፍቅር ይከተላል።
ከክርስቶስ ጋር የተቀበረ ፍቅር ከክርስቶስ አይለይም፤ ከእርሱም ጋር ይነሳል። መስቀሉን ተሸክመን ክርስቶስን እንከተለው፤ ኃጢአትን እንዳንሠራ በክርስቶስም እንድንኖር።
ተወዳጆች ሆይ መስቀል ማለት በአንገታችን የምናንጠለጥለው ምልክት ብቻ አይደለም። መስቀል ማለት በሕይወታችን ውስጥ ኃጢአትን መቃወም፣ ሥጋዊ ምኞትን መግደል፣ በክርስቶስ ፍቅር መኖር ነው። አንድ ሰው አገልግሎት እየሰጠ ሊሆን ይችላል፤ በውስጡ ግን በስውር ለኃጢአት እየተገዛ ከሆነ መስቀሉን በትክክል አልተሸከመም። መስቀል ተሸክሞ መከተል ማለት በሰው ፊት ብቻ መልካም መምሰል ሳይሆን ማንም በማያየን ቦታ ጭምር በንጽሕናና በቅድስና መኖር ነው።
በመቀጠልም ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው የፈጸማቸው ሥራዎቹና ተአምራቱ ሁሉ ታላላቅና አምካላዊ ናቸው። ከሁሉም ግን በመስቀሉ የፈጸመው ሥራ ክቡርና ታላቅ ነው። በመስቀሉ ክርስቶስ ሞትን ጣለው፤ በአዳምና በሔዋን መተላለፍ ምክንያት በሰው ልጆች ላይ ሠልጥኖ የነበረውን የሞት ፍርድ አስወገደ፤ ሲዖል ተመዘበረች፤ ትንሣዔም ተሰጠችን፤ ዓለምንና ሞትን እንደ ኢምንት ነገር የምንቆጥርበት ጸጋ ተቀበልን፤ ወደ ቀድሞ ርስታችን ለመመለስ ጎዳናው እንደገና ተቃናልን፤ የገነት ደጅ ተከፈተ፤ የእኛን ሥጋ ተዋህዶ በአብ ቀኝ ተቀመጠ፤ እኛም በመስቀሉ የእግዚአብሔር ልጅነት ሥልጣን አገኘን፤ የርስቱ ወራሾችም ሆንን፤ በመስቀሉ ሁሉም ነገር ተከናወነልን፡፡
፬.፬. በትሕትና መጽናት
አምብሮስ ስለ ትሕትና ሲናገር ከክርስቶስ መስቀል ጋር ያያይዘዋል። ክርስቶስ ራሱን አዋረደ፤ እስከ መስቀልም ድረስ ታዘዘ። በዚህም ትሕትና ቤተ ክርስቲያንን መሠረተ።
ተወዳጆች ሆይ አንዳንድ ጊዜ በአገልግሎት ውስጥ ሰዎች ሊያከብሩን፣ ሊያመሰግኑን፣ የኃላፊነት ቦታ ሊሰጡን እንፈልጋለን። ነገር ግን አምብሮስ የሚያስተምረን የክርስቶስ መንገድ የትሕትና መንገድ መሆኑን ነው።
አምብሮስ የሰው ልብ በክብር፣ በዝናና በሥልጣን ሊኮራ እንደሚችል ይገልጻል። ነገር ግን አገልጋይ መፈለግ ያለበት የሰው ምስጋና ሳይሆን የክርስቶስን ትሕትና ነው።
በጉባኤ ውስጥ የተሻለ ቦታ ባታገኙ፣ ሰዎች ባያደንቋችሁ፣ የምትሠሩት ሥራ በሌላ ሰው ስም ቢጠራ፣ አትበሳጩ። አገልግሎታችሁን በትሕትና ቀጥሉ። የክርስቶስ መንገድ በዓለም ዘንድ የሚታወቅ ክብር ሳይሆን በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጸና ታማኝነት ነው።
ልጄ ሆይ! ወደ እግዚአብሔር የሚያደርሰውን መንገድ ምረጣት። እርሷ ምንም እንኳ በሰዎች ዘንድ የታወቀች ባትሆንም፣ እግዚአብሔር ግን ያውቃታል። በሰው ፊት ሞኝ የሆኑት በእግዚአብሔር ፊት ጥበበኞች ናቸውና። የዚህ ዓለም ክፋትና የክፉዎች መንገድ ግን እንደ ጉም የሚጠፋ፣ ዛሬ ታይቶ ነገ የማይገኝ ከንቱነት ነው።” (የበረሃ አባቶች)
፬.፭ ጸሎት ከሕይወታችን ጋር መያያዝ አለበት
አምብሮስ «ጸሎቴ በፊትህ ትቅረብ» (መዝ ፻፲፰፥፻፰፱) የሚለውን ቃል ያብራራል
መልካም ሕይወት ለጸሎት ክንፍ ይሆናል። ይህም ማለት ጸሎት በአፍ ብቻ የሚነገር አይደለም፤ በሥራችንም ይገለጣል። አምብሮስ በግልጽ አቀራረብ የሚያስተምረው፦
መልካም ሥራችሁን ከፍ ካደረጋችሁ ጸሎታችሁንም ከፍ አደረጋችሁ። ሐሰትን ከተዋችሁ፣ እውነትን ከተከተላችሁ፣ ንጽሕናን ከጠበቃችሁ ከክርስቶስ ጋር ቀረባችሁ። ጸሎት በኃጢአት ይከብዳል፤ በንጹሕ ልብ ግን ወደ እግዚአብሔር ይቀርባል ይላል፡፡ (አምብሮስ መዝሙረ ዳዊት ፻፲፰ ማብራርያ)
ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለ ጸሎት መዝሙር አራት ማብራራያው ላይ እንዲህ ይላል፡-ጸሎት የሚሰማው በዚህ መንገድ ነው፡፡ “የመጀመሪያው በእርግጥ አንድን ነገር ለመቀበል ብቁ መሆን፤ ሁለተኛው በእግዚአብሔር ሕጎች መሠረት መጸለይ፤ ሦስተኛው መጽናት (አለመታከት)፤ አራተኛው ምድራዊ የሆነን ነገር አለመጠየቅ፤ አምስተኛው ለእውነተኛ ጥቅማችን የሚሆኑትን ነገሮች መፈለግ፤ ስድስተኛው ከእኛ በኩል የሚጠበቀውን ሁሉ ማበርከት። ከእግዚአብሔር ጋር እንደሚነጋገር ሰው ሆኖ ከእግዚአብሔር ጋር መነጋገርን የተማረ ሰው፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ መልአክ ይሆናል” ይላል፡፡ (የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ማብራርያ)
«አምላክ የሚመለከተው የአነጋገርን ውበት ወይም የቃላትን ፍሰት ሳይሆን የነፍስን ንጽሕናና ቅንነት ነው፤ በአእምሮአችን የመጣውን እንኳ ብንናገር ልመናችን ተሰምቶልን እንመለሳለን።
ነገሩ ምን ያህል ቀላል እንደሆነ አያችሁት? በሰዎች ዘንድ ከሆነ፣ ለታላቅ ሰው አቤቱታ የሚያቀርብ ሰው የንግግር ችሎታ ሊኖረው፣ የዚያን ታላቅ ሰው አጃቢዎች ሁሉ ለማስደሰት መጣጣር እና ተቀባይነት ለማግኘት ሲል ለብዙ ዝርዝር ነገሮች መጨነቅ ያስፈልገዋል። በእግዚአብሔር ዘንድ ግን በተቃራኒው፣ ከንቁና ከተረጋጋ መንፈስ ውጭ ምንም የሚያስፈልግ ነገር የለም፤ ወደ አምላክ ለመቅረብ ምንም የሚከለክል እንቅፋት የለም። “እኔ የቅርብ አምላክ ነኝ እንጂ የሩቅ አምላክ አይደለሁም” ማለቱን አስቡ።
ነገርግን ሩቅ ሆነን መገኘታችን የእኛ ድክመት ነው፤ እርሱ ግን ሁልጊዜም አጠገባችን ነው። የንግግር ችሎታ አያስፈልገንም ማለት ብቻም ሳይሆን ድምፅ ማውጣት እንኳ ላይጠበቅብን ይችላል! ማለት በልባችን እንኳ ብናሳውቅ እንደሚገባ ብንጠራው፣ መሻታችንን ይፈጽማል። ሐናም የተሰማችው በዚህ መንገድ ነበር፤ ሰዎችን የሚያስፈራራ ምንም አይነት ወታደር አጠገቡ የለም፤ ተገቢውን የጸሎት ጊዜ የሚያቋርጥ ምንም ዓይነት ዘበኛ የለም፤ “አሁን ለመቅረብ ጥሩ ጊዜ አይደለም፣ በኋላ ተመለስ” የሚል ማንም የለም። ይልቁንስ፣ በማዕድ ጊዜ፣ በአስቸጋሪ ጊዜ ቢሆን፣ እንዲሁም በገበያ ስፍራ፣ በጉዞ ላይ፣ በባሕር ላይ፣ ወይም በዳኛ ፊት በሚገኝ ችሎት ውስጥ ሆነን እንደሚገባ ብንጠራው፣ ልመናችን ከመቀበል የሚያግደው ምንም ነገር የለም። “ጠላቴ አጠገቤ ነውና ወደ ፊት ቀርቤ ለመጸለይ እፈራለሁ” ለማለትም ምንም ምክንያት የላችሁም፤ ምክንያቱም እርሱ ጠላትን አይፈራም፣ ጸሎታችሁንም አያቋርጥም። ይልቁንስ ያለ ምንም አስቸጋሪ እንቅፋት ሁልጊዜም ያለማቋረጥ ከእርሱ ጋር መነጋገር እንችላለን።
እኛን የሚያስተዋውቁ በር ጠባቂዎች፣ አስተዳዳሪዎች ወይም ወዳጆች አያስፈልጉንም። ይልቁንስ በራሳችን ስንቀርብ በተለይም የነገሩን እርዳታ ከማንም ሳንፈልግ በሚሆንበት ጊዜ የበለጠ ይሰማናል።
የእግዚአብሔር ጥበብና አቅም በተለየ ሁኔታ የሚገለጸው መከራዎችን በማራቅ ብቻ ሳይሆን፣ መከራዎቹ የምንሻገርበት ብርታት በመስጠት ነው።
እናንተም “በመከራ ውስጥ እንዴት ሰፊ ቦታ ሊኖር ይችላል?” ብላችሁ ትጠይቁ ይሆናል። ሦስቱ ወጣቶች በእሳት ውስጥ ተጥለው ነበር፤ ዳንኤል በአንበሶች ጉድጓድ ውስጥ ተጥሎ ነበር፤እርሱ እሳቱን አላጠፋውም፣ ነገር ግን እሳቱ እንዳይበላቸው አደረገ፤ አንበሶቹንም አልገደላቸውም፣ ነገር ግን በዚያው ሁኔታ ውስጥ እርሱን (ዳንኤልን) ከአደጋ ጠበቀው።
ነፍስ በፈተናዎች መደራረብ በሚጨነቅበት ጊዜ፣ ከሁከትና ከብዙ ሕመሞች ነፃ ስትወጣ፣ ያኔ ከሁሉ በላይ ብርታትን ታገኛለች። በብልጽግናና በደስታ፣ ባልተገሩ ምኞቶች ሰለባ የሆኑ በገንዘብ፣ በሥጋዊ ፍላጎትና በሌሎች መሰል ከንቱ ነገሮች ምክንያት መንፈሳቸው ይጨነቃል። በመከራ በሚያዙበት ጊዜ ግን፣ ከእነዚያ ሁሉ ነገሮች ነፃ ይወጣሉ፤ በዚህ ጊዜ ረፍት ያገኛሉ።
«ነገር ግን ከመከራ አያሌ ሰፊ ቦታ (እፎይታ) እንደሚገኝ ከሐዋርያት ትምህርት ደግሞ ለመማር፣ ራሱ ጳውሎስ የመከራን ፍሬ ሲናገር አዳምጡ፦ “መከራ ትዕግሥትን ያመጣል፤ ትዕግሥት ፈተናን ማለፍን [ምስክርነትን]፤ ፈተናን ማለፍ ደግሞ ተስፋን፤ ተስፋ ደግሞ አያፍርም” ይላል። (ሮሜ ፭፥፫) ታላቅ ትዕግሥት ካለውና ሁሉንም ነገር በቀላሉ መሸከም ከሚችል ሰው በላይ በሰላም የሚኖር ማን አለ? ፈተናን ካለፈና ከጸና ሰው በላይ ጠንካራ ማን ሊሆን ይችላል? ከዚያ ከሚገኘው እርካታ ጋር የሚወዳደርስ ምን አለ? አስተውሉ እርሱ ከዚህ የሚወጡ ሦስት ደስታዎችን ይዘረዝራል፦ትዕግሥት፣ ፈተናን ማለፍ(ጽናት) እና የወደፊት በረከቶች ተስፋ ናቸው።
እግዚአብሔርን ሁልጊዜ ረዳትና ደጋፊ አድርጎ ማግኘት በሁሉም አጋጣሚዎችና ሁኔታዎች ሁሉ ከእኛ ጎን መሆኑ ነው። ተመልከቱ! ይህን የሚያደርገው አንድ ጊዜ፣ ሁለት ጊዜ ወይም ሦስት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ወደ እርሱ የምንጠራው ከሆነ ሁልጊዜ እንደሆነ ይናገራል። እንደገና ደግሞ የእግዚአብሔርን ፈጣን ሰሚነት አስተውል። ከዚህ በላይ፦ «በጠራሁህ ጊዜ የጽድቄ አምላክ ሰማኝ» እንዳለ ሁሉ እዚህም ላይ፦ «ወደ እርሱ በጮኹሁ ጊዜ ይሰማኛል» ይላል።
ታዲያ «ብዙ ሰዎች ጸልየው የማይሰሙት ለምንድን ነው?» ብለህ ትጠይቅ ይሆናል። የማይጠቅም (ተገቢ ያልሆነ) ጥያቄ ስለሚያቀርቡ ነው። በዚህ ዓይነት ሁኔታ ላይ አለመሰማት ከመሰማት ይበልጥ ጥቅም አለው። ስለዚህ ተገቢ ያልሆነውን ለምነን እንኳ ብንሰማ ደስተኞች አንሆንም ነበር፤ ባንሰማ እንኳ በዚህ ምክንያት ይልቁንም እግዚአብሔርን እናመሰግናለን። በሌላ አነጋገር ተገቢ ያልሆነ ነገር በምንለምንበት ጊዜ ባለማግኘታችን ይበልጥ እንጠቀማለን፤ በሌላ በኩል ደግሞ አቀራረባችን ግዴለሽ በሆነ ጊዜ እግዚአብሔር መልሱን በማዘግየት ይበልጥ እንድንማጸነው ያደርገናል፤ ይህም ቀላል ያልሆነ መንፈሳዊ ጥቅም አለው፡፡
ቅዱስ መጽሐፍ፦ «እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ» (ማቴ. ፯:፲፩) እንዳለ ታስታውሳለህ፤ መስጠት ምን እንደሆነ መቼ መስጠት እንዳለበትና ምን መስጠት እንደሚገባው የሚያውቀው አምላካችንማ እንዴት አብልጦ አይሰጥም! ባንሰማ እንኳ አንታክት፤ አንበሳጭ ወይም አንደንዝዝ፤ ይልቁንም በጸሎትና በምልጃ እንጽና። እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር የሚያደርገው ለበጎ ነውና።
ስብሐት ለእግዚአብሕር ወለወላዲቱ ድንግል ወለመስቀሉ ክቡር

Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!