ዘረኝነት፤ የዘመናችን ወጣቶች ተግዳሮት
በአዱኛ ጌታቸው
ክፍልሦስት
ከዘረኝነት ጠባይ ለመራቅ ወጣቶች ምን ማድረግ አለባቸው?
ሥጋዊ ማንነትንና ክርስትናን መለየት
በማነንት ጉዳይ ብዙ ክርክሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ምድራዊው ማንነት በሰዎች መንፈስ የተገነባ ሲሆን ሰማያዊው ማንነት ደግሞ በመስቀል ላይ የተገነባ ነው ይላሉ፡፡ ምድራዊ ማንነት ሙሉ በመሉ ሰው ሠራሽ ነው ብሎ መቀበል ቢከብድም ኃላፊ ጠፊ መሆኑ ግን አያጠራጥርም፡፡ በምድራዊው ማንነት ውስጥ በተፈጥሯዊ ሂደት የምንወርሳቸው ማንነቶች ይኖራሉ፤ በጊዜ ሂደት በመማር ወይም በመላመድ የምንወርሳቸው ማንነቶች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ ጾታን፣ የቆዳ ቀለምን፤ አካላዊ ቁመና የመሳሰሉትን በተፈጥሮ የምንወርሳቸው ማንነቶች ናቸው፡፡ ቋንቋ፣ አለባበስ፣ አመጋገብ፣ በአጠቃላይ የሰዎች የአኗኗር ዘዬ ከማኅበረሰብ የሚወረሱ ማንነቶች ናቸው፡፡ ግለሰቦችን ወይም ማኅበረሰቦችን አንድ የሚያደርጋቸው ማንነት ይኖራል፤ የሚለያቸው ማንነትም ይኖራል፡፡
አንድ የሚያደርጉንም ሆነ ልዩ የሚያደርጉን ሥጋዊ ማንነቶች ከሃይማኖታችን ዓላማ ወይም እሳቤ ጋር እስካልተጋጩ ድረስ አክብሮና ተቀብሎ መኖር ሰላማዊና ጤናማ ማኅበራዊ መስተጋብር እንዲኖረን ይረዳናል፡፡ ግጭት ወይም አለመግባባት የሚፈጠረው የራስን አድንቆ የሌላውን ማንቋሸሽ ሲጀመር እንዲሁም የእኔን ማንነት ካልተቀበልክ ብሎ አካላዊና ሥነ ልቡናዊ ጫና ለማሳደር መሞከር ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ከእግዚአብሔር መንግሥት ሊለየን ይችላል፡፡ ክብር ምስጋና ይግባውና ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትወዱትን ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉ በማለት ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯቸዋል፡፡ (ማቴ. ፯፥፲፪)
በመሆኑም የሌሎች ወንድሞቻችንን ማንነት አክብረን በሰላም መኖር ክርስቲያናዊ ሥነ-ምግባር ነው፡፡ አንድ ክርስቲያን ምድራዊ ማንነት ቢኖረውም ከክርስትናው ሊበልጥበት አይገባም፡፡ ምክንያቱም ምድራዊ ማንነት በምድር የሚቀርና ጊዜያዊ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ማንነት ግን ዘለዓለማዊ ነው፡፡ በፍርድ ቀን የምንጠየቀው የምንናገረውን ቋንቋ ወይም የምንከተለውን የፖለቲካ ርዕዮተ ዓለም ወይም ደግሞ የኖርንበትን ማኅበረሰባዊ ባህል አይደለም፡፡ ስለ ሠራነው መልካም ሥራ እንጂ፡፡ ስለዚህ በዚህ ዓለም ስንኖር የማንነታችን ሚዛን ሊሆን የሚገባው ክርስትናችን ነው፡፡ ሌላው ሁሉ ተራ ነገር ነው፡፡ ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ “በዚህ በሚሞት ሰውነታችሁ ኃጢአትን አታንግሧት፣ ለምኞቱም እሺ አትበሉት፡፡ ለእግዚአብሔር ራሳችሁን መሥዋዕት አድርጉ እንጂ ሰውነታችሁን ለኃጢአት የዐመፅ የጦር መሣሪያ አታድርጉት” ይላል፡፡ (ሮሜ ፮፥፲፪)፡፡ ስለሆነም ክርስቲያን ወጣቶች ፖለቲከኞችና የጎሳ አቀንቃኝ ቡድኖች ለራሳቸው ጥቅም በሚቀይሱት የጥፋት መነገድ ተጠልፎ ላለመግባት ራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው፡፡
በወጣትነት ዘመን እንደ ዜጋ ለሀገርና ለማኅበረሰብ የሚጠቅም ሥራ መሥራት እንደ ሃይማኖት ሰው ደግሞ በመንፈሳዊ ሕይወት ለማሳደግ መትጋት እንጂ ለሥጋም ለነፍስም በማይበጅ ሐሳብ መጠመድ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡
ለሕሊና መኖር
ኢትዮጵያዊው ሊቅ ዶ/ር እጓለ ገብረ ዮሐንስ “ብፁዓን ነጹሐነ ልብ” በሚለው መጽሐፋቸው “የሃይማኖት ሰው መሆን የሚቻለው መጀመሪያ በሕሊናችን ማዘዝ ስንችል ነው” ይላሉ፡፡ ሕሊና የመፈተሸ፣ የመመርመር፣ የመምረጥ፣ የአመክንዮ ችሎታ አለው፡፡ ሕሊና የእውነት ሚዛን ነው፡፡ ሊባንዮስ የሚባል በዐራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኖረ የታወቀ ፈላስፋ ነበር፡፡ በዘመኑ የምርምር መስክ እጅግ የተራቀቁ ተማሪዎችን ስላፈራ ከነዚህ ለየትኛው የመምህርነት መንበሩን እንደሚያወርስ ቢጠይቁት “ለዮሐንስ ነበር ወደ ክርስትና ተሻገረ እንጂ” ብሎ መለሰ ይባላል፡፡
ዮሐንስ የተባለው ትልቁ የቤተ ክርስቲያችን ሊቅ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ነው፡፡ ታላቁ አባት ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ሕሊናችሁን ከፍ ከፍ አድርጉ ይላል፡፡ ሕሊናን ከፍ ከፍ ማድረግ ማለት ከተራው፣ ከሚለያየው፣ ከሚከፋፍለው አስተሳሰብ፣ ከደሴቱ ከሥርቻው ወደ ኮረብታው ወደ ተራራው ውጡ፤ ወደ ሰማይም ቀና በሉ፤ ተገቢ ቦታችሁን ዐውቃችሁ በዚያ ቁሙ፣ የእውነት ቃል የደግነት ዜና ስሙ፤ አዳምጡም፤ ማለት ነው፡፡ እኛ ሕያውያን ፍጥረታት መሆናችንን ስናስብ የሚለያየንና የሚከፋፍለን አጀንዳ ሁሉ ተራና የማይጠቅም ሐሳብ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ ኃላፊና ቁሳዊ በሆነ አጀንዳ ልቡናችን ከባዘነ ግን ከሕሊና በታች እንሆናለን፡፡
በፖለቲካው ዘርፍ በንቃት መሳተፍ
በአገራችን በማንነት ላይ የተመሠረተ ግጭት በስፋት የሚስተዋለው ክርስቲያኖች ከፖለቲካና ከውሳኔ ሰጪነት በመራቃቸው ነው፡፡ ክርስቲያን ሲባል የስም ክርስቲያን ሳይሆን ለእውነት የቆመውንና ለእውነት የሚተጋውን ማለታችን ነው፡፡ ቀደምት ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ለፍትሕና ለሰው ልጅ እኩልነት ይተጉና ፍርድ ጎደለ ደኃ ተበደለ ብለው የሚሠሩ እንደነበር በልዩ ልዩ የታሪክ መዛግብት ተጽፎ እናገኛለን፡፡ ኢትዮጵያውያን እንኳንስ ለራሳቸው ዜጋ ይቅርና ለወራሪ ጠላት እንኳ የሚራሩ እንደነበር በታሪክ መዛግብት ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡
ኢትዮጵያውያን በግብረ ገብነት እንዲታወቁ ያደረጋቸው በዋናነት እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሕዝቦች በመሆናቸው ነው፡፡ ፈጣሪውን የሚፈራ ሰው በእግዚአብሔር አምሳል ለተፈጠረው የሰው ልጅ ይራራ ዘንድ ግድ ይለዋልና፡፡ ይህ ማለት ግን ኢትዮጵያን ይመሩና ያስተዳድሩ የነበሩ ነገሥታት ሁሉ እንከን አልነበራቸውም ማለት እንዳልሆነ ልገነዘብ ይገባል፡፡ ክርስቲያኖች በፖለቲካው ቢሳተፉ ዛሬ ላይ የምናስተውላቸው መለያየቶች ባልተፈጠሩ ነበር፡፡
ምክንያቱም ዳዊት ደስታ ኦርቶዶክሳውያን እና ፖለቲካ በሚለው መጽሐፉ ከገጽ ፩፻፫ ጀምሮ እንደገለጠው ክርስቲያኖች በፖለቲካው በንቃት ቢሳተፉ ዴሚክራሲ ይሠፍናል፤ የፖለቲካ መረጋጋት ይመጣል፤ አገርን ከመፍረስና ከመበታተን መታደግ ይቻላል፤ ክርስቲያኖች በሀገራቸው በክፉ መሪዎች አንዳይሞቱና ለስደትና ለእንግልት እንዳይዳረጉ መታደግ ይቻላል፤ ክርስቲያንም ሆነ ማንኛውም ዜጋ በሀገሩ ተከብሮ በነጻነት እንዲኖር ማድረግ ይቻላል፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ለማጥፋት ሌት ተቀን የሚተጉ የውጭና የውስጥ ኃይሎችን መከላከል ይቻላል፤ ብልሹ አሠራር እንዳይኖርና ዜጎች መብትና ግዴታቸውን አውቀው እንዲኖሩ ማድረግ ይቻላል፤ ለአገራችንም ሆነ ለሕዝባችን የምንመኘውን መልካም ተግባር መፈጸም ይቻላል፤ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት በሰውነቱ ተከብሮ እንዲኖር ማድረግ ይቻላል፤ የሥጋም ሆነ የነፍስ ድህነትን ለማስወገድ ዕድል መፍጠር ይቻላል፤ ዛሬ ላይ የምናስተውለው የጎሳ ግጭት እንዳይፈጠር ማድረግ ይቻላል፤ ወዘተ፡፡ ነገር ግን አቅምና ችሎታ ያላቸው ክርስቲያኖች በራሳቸውና በውጫዊ ምክንያቶች ከፖለቲካው በመራቃቸው ከላይ የተዘረዘሩትን በጎ ተግባራት ማከናወን አልተቻለም፡፡ ዛሬም ቢሆን አልረፈድምና ወጣቶች በፖለቲካው በንቃት በመሳተፍ አገርንና ቤተ ክርስቲያንን ከአጥፊዎች ለመታደግ ግንባር ቀደም ተዋናይ መሆን አለባቸው፡፡
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
Leave a Reply
Want to join the discussion?Feel free to contribute!