ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል

ሚካኤል የሚለው ስም አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ በተሰኘው መዝገበ ቃላት መጽሐፋቸው ሲገልጹ ቃሉ የዕብራይስጥ ሲሆን፤ ሚ ማለት “መኑ” ፥ ካ ማለት “ከመ” ማለት ሲሆን፥ ኤል ማለት ደግሞ “አምላክ” ማለት ነው። በዚህም መሠረት ቅዱስ ሚካኤል የስሙ ትርጓሜ “መኑ ከመ አምላክ፥ ማን እንደ እግዚአብሔር” ማለት ነው።

በሥነ ፍጥረት ትምህርት እግዚአብሔር ሳጥናኤልን ቅሩበ እግዚአብሔር፣ ለእግዚአብሔር የቀረበ አድርጎ እንደ ሾመው ቅዱሳት መጻሕፍት ይመሰክራሉ፡፡ ነገር ግን ሳጥናኤል ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ክብር ትቶ አምላክነትን በመሻቱ በትዕቢቱ ምክንያት ሥልጣኑ ተገፍፎ ወደ ምድር ጥሎታል፡፡ በቦታውም ቅዱስ ሚካኤልን ሾሞታል፡፡ የቅዱስ ሚካልን ሲመት ምክንያት በማድረግም ዕለቱን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ኅዳር ፲፪ ቀን በየዓመቱ በድምቀት ታከብረዋለች፡፡ (መጽሐፈ አክሲማሮስ)

ይህም ብቻ አይደለም፤ እስራኤላውያን በግብፅ በባርነት ቀንበር ተይዘው ለ፪፲፭ በስቃይ ሲኖሩ ያለቀሱት ዕንባ መንበረ ጸባዖት ደርሶ ከግብፅ ወደ ምድረ ርስት ይገቡ ዘንድ እግዚአብሔር ሊቀ ነቢያት ሙሴን አሥነስቶ ባሕረ ኤርትራን ከፍሎ አሻግሮ፣ ለዐርባ ዘመናት ሲጓዙ ቀን በደመና ሌሊቱን በብርሃን እየመራ ያደረሳቸው ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ይህንን ቀን መታሰቢያ አድርጋ የምታከብርበት ዕለት ነው፡፡

ቅዱስ ሚካኤል ለኢያሱ ወልደ ነዌ በሰው አምሳል ተገልጦ “የተመዘዘ ሰይፍ በእጁ የያዘ ሰው በፊቱ ቆሞ አየ፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ ‘ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ?’ አለው፡፡ እርሱም ‘እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ነኝ፤ አሁንም ወደ አንተ መጥቻለሁ’ አለ፡፡ ኢያሱም ወደ ምድር በግንባሩ ተደፍቶ ሰገደ” በማለት እግዚአብሔር የቅዱስ ሚካኤልን ክብር ገልጧል፡፡ (ኢያ. ፭፥፲፫-፲፬)

የቅዱስ ሚካኤል ሹመት በነገደ መላእክት ላይ ብቻ አይደለም፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆኑት ላይ ጭምር ነው፡፡ ሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል፣ ለእኛ ለሰዎች አማላጅ ሲሆን ለቅዱሳን፣ ፃድቃን ሰማዕታት ደግሞ አጋዣቸው ነው፤ በሕይወታቸውና በተጋድሏቸውም እስከ መጨረሻው ይረዳቸዋል፡፡

ይህንንም በቤተ ክርስቲያናችን በመጽሐፈ ስንክሳር እና ድርሳነ ሚካኤል ኅዳር ፲፪ ቀን እንደተጻፈው መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ዱራታዎስንና ሚስቱ ቴዎብስታን ከዲያብሎስ ፈተና የታደገበት ዕለት ነው፡፡

ዱራታዎስና ቴዎብስታ ሁልጊዜ ያለማቋረጥ የዚህን የከበረ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን የበዓሉን መታሰቢያ ያደርጉ ነበር፡፡ ነገር ግን በሀገር ውስጥ ችግር በሆነ ጊዜ ገንዘባቸው አለቀ፡፡ ለቅዱስ ሚካኤልም ለበዓሉ መታሰቢያ የሚያደርጉትን እስኪያጡ ድረስ ቸገራቸው፡፡ ዱራታዎስም የእርሱንና የሚስቱን ልብስ ሸጦ ለመልአኩ በዓል መታሰቢያ ያደርገው ዘንድ ይዞ ወጥቶ ሄደ፡፡ የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤልም በታላቅ መኮንን አምሳል ለዱራታዎስ ተገለጠለትና ወደ ባለ ጸጎች ሄዶ በእርሱ ዋስትና በአንድ ዲናር አንድ በግ፣ ሁለተኛም ወደ ባለ ስንዴ ዘንድ ሄዶ በእርሱ ዋስትና ስንዴን እንዲወስድ፣ ዳግመኛም ወደ ዓሣ አጥማጅ ዘንድ ሄዶ አንድ ዓሣ እንዲወስድ፣ ነገር ግን ወደ ቤቱ ሳይርስ የዓሣውን ሆድ እንዳይቀድ አዘዘው፡፡ ዱራታዎስም እንደታዘዘው አደረገ፡፡ ወደ ቤቱም በተመለሰ ጊዜ ቤቱ ሁሉ በበረከት ተመልቶ አገኘው፡፡ እርሱም እጅግ ተደስቶ የዚህን የክቡር መልአክ የመታሰቢያውን በዓል አደረገ፡፡ ጦም አዳሪዎችንና ድኆችንም ጠርቶ አጠገባቸው፡፡

ከዚህም በኋላ ለዱራታዎስና ለሚስቱ ቴዎብስታ ቅዱስ ሚካኤል ለሁለተኛ ጊዜ ተገለጠላቸው፡፡ ዱራታዎስንም የዓሣውን ሆድ እንዲሰነጥቅ አዘዘው፡፡ በሰነጠቀውም ጊዜ ፫፻ (ሦስት መቶ) የወርቅ ዲናር በዓሣው ሆድ ውስጥ ተገኘ፡፡ ቅዱስ ሚካኤል ዱራታዎስንና ሚስቱን ቴዎብስታን እንዲህ አላቸው፡- “ከዚህ ዲናር ወስዳችሁ ለባለ በጉ፣ ለባለ ዓሣውና ለባለ ስንዴው ዕዳችሁን ክፈሉ፡፡ የቀረውም ለፍላጎታችሁ ይሁናችሁ እግዚአብሔር አስቧችኋልና በጎ ሥራችሁን፣ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን አስቦ በዚህ ዓለም አሳመረላችሁ፣ በኋለኛውም መንግሥተ ሰማያትን አዘጋጅቶላችኋል” አላቸው፡፡

እነርሱም ይህን ነገር ሲሰሙ ደነገጡ፤ የከበረ ገናናው መልአክም “ከመከራችሁ ሁሉ ያዳንኳችሁ የመላእክት አለቃ እኔ ሚካኤል ነኝ፤ መሥዋዕታችሁንና ምጽዋታችሁን ወደ እግዚአብሔር ፊት ያሳረግሁ እኔ ነኝ፡፡ አሁንም በዚህ ዓለም ከበጎ ነገር እንድታጡ አላደርጋችሁም” አላቸው፡፡ ይህንንም ከነገራቸው በኋላ ወደ ሰማያት ወጣ፤ እነርሱም በፍርሃትና በክብር ሰገዱለት፡፡”

የመላእክት አለቃ ቅዱስ ሚካኤል ከበዓሉ በረከት ረድኤት ይክፈለን፤ ጥበቃውና አማላጅነቱ አይለየን፡፡ አሜን፡፡

ምንጭ፡ድርሳነ ቅዱስ ሚካኤል፣ ስንክሳር ዘወርኃ ኅዳር፣ መጽሐፈ አክሲማሮስ፣ መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *