የእግዚአብሔር ፈቃድ

ክፍል አንድ

በመ/ር ተርቢኖስ ቶሎሳ

የሰው ልጅ በአንድ ጸጋ ብቻ አይወሰንም። አንድ ጸጋ ብቻውን የእግዚአብሔርን ሰጭነት የሰውን ልጅ ተቀባይነት ቢገልጥ እንጂ ወደ መንግሥተ ሰማያት ለሚደረገው ጉዞ ዋና አይሆንም።

ይህን ለማየት በብሉይ ኪዳን ዘመን እስራኤላውያን ወደ ተስፋይቱ ምድር ያደረጉትን ጉዞ በቀላሉ መመልከት በቂ ነው። እግዚአብሔር አምላካችን “ባርነት ይብቃ” ብሎ ሙሴን በመሪነት ወደ ግብፅ ላከ።  ሙሴም ብቻውን በቂ አይደለምና “አሮን እኁከ ይኩንከ አፈ፤ አሮን ወንድምህ አፍ ይሁንህ” ብሎ ሰጠው። ከሚገጥመውም ፈተና ይታደገውና ይጠብቀው ዘንድም መልአኩን ላከለት።

ለዚህ መንገደኛ ሕዝብ ከደመና ላይ የሚወርደው መና፣ ከዐለት የሚፈልቀው ውኃ፣ ከላይ፣ ግራና ቀኝ የሚጋርደው ደመና፣ ሕዝቡን የሚያጽናኑ ሌዋውያን፣ የሚያስታርቁ ካህናት፣ ምስጋናው የማይታጣባት ደብተራ ኦሪት፣ ለኃጢአት ስርየት የሚሆነው መሥዋዕቱና የመሳሰሉት ሁሉ ከላይ የተሰጡት ጸጋዎቹ ናቸው።

በፍጻሜው ምድረ ርስትን ብቻ በሚያስገኝ በዚህ አስጨናቂ ጉዞ ውስጥ እግዚአብሔር ሙሴን ብቻ ጸጋ አድርጎ አለመስጠቱ በብዙ ሀብታት ተውባና ደምቃ ወደ ዘለዓለማዊት መንግሥቱ የምትጓዘዋ ቤተ ክርስቲያን በብዙ ጸጋ የምታገኘውን ሀብት ለማሳየት ነው።  “ያመነ የተጠመቀ ይድናል” ስለተባለች በጥምቀት ጸጋነት ብቻ ለጽድቁ እበቃለሁ አትልም። (ማር. ፲፮÷፲፮) እንዲሁም “ሥዬን የበላ፣ ደሜንም የጠጣ፣ የዘለዓለም ሕይወት አለው” ስለተባለም በሥጋውና በደሙ ብቻ እጸድቃለሁ አትልም። “በእምነት ጽደቁ” ስለተባለ ምግባር ለምኔ አትልም። ለጽድቋ እምነት፣ ክህነት(የሚናዝዝ፣ የሚያጠምቅ፣ የሚያቆርብ)፣ ጥምቀት፣ ሜሮን፣ ቁርባንና ምግባር ጸጋዎቿ እንደሆኑ ታምናለች።

በጉዞዋ ፈርዖን ይነሣባታል፤ ከኋላዋ አእላፍ ፈታኞች ይከተሏታል። ነገር ግን አይቀድሟትም። መከተላቸውም እስከ ኤርትራ ባሕር ድረስ ነውና ለተሻገረ ሕዝብ ጭንቅ አይሆኑም። በእርግጥ ከግብፅ እስከ ኤርትራ ድረስ ያለው ጉዞ ከኤርትራ እስከ ምድረ ርስት ድረስ ካለው ጉዞ ጋር ሲነጻጸር እጅጉን አስጨናቂ ነው። በዚህ ጉዞ የሙሴ ፍጹም መሪነት ጎልቶ አልተገለጠም፤ የምድሪቱም ዓቅም ገና አልተስተዋለም፣ የግብፃውያን ፉከራና ግርግርታም እስከ ባሕረ ኤርትራ ድረስ ፈጽሞ አልታጣም። የጠላት ኮቴም በቅርብ ይከተል ነበር። የፈርዖንም ተስፋ ገና አልተቋጨም፣ ከኤርትራ በኋላ ግን አዲስ ታሪክ ይጀመራል። ፈርዖንም አይጨብጥም፣ ኤርትራም፤ አታሰጥምም።

በዚህ ዐውድ ፈርዖን ዲያብሎስ ነው፡፡ ኤርትራም ሲኦል ናት።  ከኤርትራ ማዶ ማርያም እኅተ ሙሴ ለምስጋና ተሰልፋለች። እውነትም አመስጋኟ ማርያም የምትገኘው ከኤርትራ በኋላ ነውና እንደ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም “ተዐብዮ ነፍስየ ለእግዚአብሔር፤ ነፍሴ እግዚአብሔርን ታከብረዋለች” አለች። ከግብፅ እስከ ኤርትራ የተደረገው ጉዞም ከጓዳ በተዘጋጀ ስንቅ ነበር።  ከኤርትራ በኋላ ግን ውኃው ከዐለት ይፈልቃል፤ መናውም ከደመና ይወርዳል።

ነገር ግን ቤተ ክርስቲያኒቱን ክርስቶስ በቤዛነቱ ከተቤዣት በኋላ ለመንገዷ ስንቅ ይሆኗት ዘንድ ቤት ያፈራቸውን ኮርማውንና ጠቦቱን መሥዋዕት አድርጋ አታቀርብም።  ከሰማይ የወረደላትን መና (ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ የቆረሰላትን ሥጋውንና ያፈሰሰላትን ደሙን) መሥዋዕት አድርጋ ታቀርባለች አንጂ።

ተናዳፊውን እባብ አልፈው፣ የበለዓምን ርግማን ተራምደው፣ ዮርዳኖስን ተሻግረው፣ ግንቡን አፈራርሰው፣ ጠላት ደምስሰው ርስታቸውን ገንዘብ ማድረግ እንደ ሥጋ ሲታይ ለአእላፈ እስራኤል አይወጡት ተራራ ነው። በብሉይ ኪዳኑ ለነበረው ምድረ ርስት መውረስ ምክንያቱ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ሆኖም ቤተ ክርስቲያኒቱ ይህን ሁሉ ውጣ ውረድ የምታልፍ ናትና የእስራኤል ጉዞ ምድረ ርስትን በመውረስ ይደማደማል።

እግዚአብሔር አምላካችን ገዥ እና መጋቢ አምላክ ስለሆነ በባሕርይ ለሚገዛው ፍጥረት ፈቃዱን ያለ ወሰን ሰጥቷል። የምድር ወሰን ስፋት፣ የሰማይ ምጡቅ ጽናት ያለ መናወጽ የሚኖረው በፈቃዱ ተራዳኢነት ነው። የኦሪት ዘፍጥረት ጸሐፊው ሙሴ “በቀዳሚ ገብረ እግዚአብሔር ሰማየ ወምድረ፤ በመጀመሪያ እግዚአብሔር ሰማይና ምድርን ፈጠረ” ሲል የሰማይና የምድር መፈጠር የእግዚአብሔር ፈቃዱም እንደሆነ ለማጠየቅ ነው። (ዘፍ. ፩፥፩) ለዚህም ነው በፈቃዱ በስድስት ቀን የፈጠረውን ፍጥረት እስከ ዓለም ፍጻሜ በፈቃዱ ሲመግብ የሚኖረው።

የእግዚአብሔር ፈቃድ የሰው ልጅ በአዳም የሕይወት ጉዞ በኩል በገነት ይኖርለት ዘንድ ነው። “… ከእርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለህ” ብሎ አዳምን ማስጠንቀቁ በሕይወት ይኖርለት ዘንድ እንጂ አስጨናቂ ስለሆነ አይደለም። (ዘፍ. ፪÷፲፯)

ቃኤልን “ለምንት ቀተልኮ ለአቤል እኍከ፤ አቤል ወንድምህን ለምን ገደልኸው” ብሎ እግዚአብሔር መጠየቁ አቤል ይሞትበት ዘንድ ስለማይሻ ነው። አቤል በአባቱ በኩል የሞት ሞትን ትሞታለህ የሚል የሞት ዕዳ ቢተላለፍበትም ይህ ፍርድ ግን ቃኤልን ከባለ ዕዳነት አልታደገውም። በአጠቃላይ የሰው ልጅ እንደጠፋ ይቀር ዘንድ የእግዚአብሔር ፈቃድ አልነበረም። (ዘፍ. ፬፧፱)

ፈቃዱ ወደ ቀደመ ርስቱ ገነት ወደ ነበረበት ሕይወት ይመለስለት ዘንድ ነውና፣ ብዙ ምሳሌያትን አስመሰለ፤ ቁጥራቸው የበዙ ነቢያትን በኢየሩሳሌምና በሰማርያ አሰማራ፤ ሱባኤ አስቆጠረ፤ ተስፋውን አስነገረ፤ ለኦሪታውያኑ ምልክት አድርጎ ግዝረትን ሰጠ፣ አድርግ አታድርግ ብሎ ትእዛዙን አጸና፤ ኦሪትን በሕግነት፣ ካህናትን በአባትነት ሰጠ።

ይህ ሁሉ በአዲስ ኪዳን፣ ለሚፈጸመው ድኅነት ጥላ ይሆን ዘንድ እና የማዳኑን ተስፋ በልቡና ለማጽናት ነበር። የዘመኑ ፍጻሜም ሲደርስ የአዳም መዳን ፈቃዱ ነውና መጥቶ አዳነን። ” እስመ በፈቃዱ ወበሥምረተ አቡሁ መጽአ ወአድኃነነ” እንዲል ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ድርሰቱ።  አስቀድሞም “ኃጢአታችሁ እንደ አለላ ብትሆን እንደ አመዳይ ትነጻለች፤ እንደ ደምም ብትቀላ እንደ ባዘቶ ትጠራለች” እያለ በተስፋ ማጽናናቱ ይመጣ ዘንድ ያለውን ድኅነት ከደጅ እንዳለ ለማጠየቅ ነበር። (ኢሳ. ፩፧፲፰)

የሰው ልጅ መዳን አቻ የለሽ ፈቃዱ ነውና አዳምን የመሰለ ሌላ ልፍጠር ሳይል በደለኛውን አዳም የንስሓ ጊዜ ሰጥቶ ወደ ራሱ መለሰው። አድንሃለሁ እንዳለውም ሰው በመሆን ፈቃዱን ፈጸመ።  የእግዚአብሔር ፈቃድ እንደ ንጉሥ ትእዛዝ ነው፤ ረዘመ ብለው አያሳጥሩትም፤ አጠረ ብለውም አያስረዝሙትም። ፈቃዱም “ድንገት የወለደው፣ ዘመን ያወረደው” አይደለም። መታመን የእግዚአብሔር ፈቃድ ነውና።

እርሱን እኛ ባናምነውም፣ ብናምነውም መታመኑ አይለወጥም፤ አይናወጥም። “ባናምነውም እርሱ የታመነ ሆኖ ይኖራል” መባሉ ለዚህ ነው። (፪ኛጢሞ. ፪÷፲፫) ስለዚህ ፈቃዱ የጸና ነው የሚባለው ከዚህ የተነሣ ነው። የጸና ነው ማለትም ምክንያት ሳይከለክለው ይፈጽማል ማለት ነው። “እኔ አምላክ ነኝና፣ ሌላም የለምና የቀድሞውንና የጥንቱን ነገር አስቡ፡፡ እኔ እግዚአብሔር ነኝ እንደ እኔም ያለ ማንም የለም፡፡ በመጀመሪያ መጨረሻውን፣ ከጥንትም ያልተደረገውን እናገራለሁ፤ ምክሬ ትጸናለች፣ የመከርሁትንም ሁሉ አደርጋለሁ።” እንዲል (ኢሳ.  ፵፮፥፱-፲)

ከመጀመሪያ መጨረሻውን የሚናገር እርሱና ከእርሱ የሆነ ብቻ ነው። የፈቃዱ ጥንቱ መጀመሪያ ቢሆንም ፈጻሜ ፈቃድነቱ ግን የሚታወቀው መጨረሻ ነው። ስለዚህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በፍጥረት ፈቃድና ዓላማ አይለካምና ከመጀመሪያ የመጨረሻውን የሚናገር እርሱ ነው። አንዳች ሕጸጽ የሌለበትና ምክንያት የሚከለክለው ፈቃድ የለውምና “ፈቃዴን ሁሉ እፈጽማለሁ” አለ። በፈታሒነቱ ቀዳማዊ አዳም የሞት ሞትን ጽዋዕ ይጎነጭ ዘንድ ፈቃዱ ነበርና ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ።  (ሮሜ. ፭፥፲፬) አዳም ይድንም ዘንድ ፈቃዱ ነውና አንድያ ልጁን አብ ለሞት አሳልፎ ሰጠ። (ዮሐ. ፫፥፲፮)

በሰብአ ትካት ዘመን እግዚአብሔር ያን አመጸኛ ትውልድ ማጥፋት፣ ኖኅንም እስከ ልጆቹ ማዳን   ፈቃዱ ነበርና ኖኅንና ቤተሰቡን በምሕረቱ አተረፈ፤ ሰብአ ትካትን በመዓቱ ቀሰፈ። (ዘፍ. ፯፥፳፩) አብርሃምን እንደ ሰማይ ከዋክብት፣ እንደ ባሕር አሸዋ ማብዛት የማይለወጥ ፈቃዱ ነውና ይህንንም አደረገለት። ስለዚህ የእግዚአብሔር ፈቃድ ተከፍሎ የሚፈጸም፣ ተከፍሎም የማይፈጸም ነው ልንለው አንችልም።

የሰው ልጅ ፈቃድ አለው። ይህን ፈቃዱን “ነጻ ፈቃድ” ልንለው እንችላለን። ባለፈቃዱ ሰውም ፈቃዱን ይፈጽምበት ዘንድ ጊዜና ሁኔታ ያጣል።  በዚህም ተከፍሎ ያለበት ፈቃድ ሕልም ብቻ ሆኖ ይመክናል። ምክንያቱም ተፈጥሮው የምክንያት ጥገኛ ስለሆነ። ለመገለጡ እንጂ ለመኖሩ ምክንያት የሌለው እግዚአብሔር ግን የወደደውን ያደርግ ዘንድ ይቻለዋል።

“በከመ ፈቀደ ይገብር ወበከመ ሐለየ ይፌጽም፤ እንደ አሰበው ያደርጋል፣ እንደ ፈቃዱም ይፈጽማል” እንደተባለ። በሌላም ስፍራ “በምድርም የሚኖሩ ሁሉ እንደ ኢምንት ይቆጠራሉ፤ በሰማይም ሠራዊት በምድርም ላይ በሚኖሩ መካከል እንደ ፈቃዱ ያደርጋል፤ እጁንም የሚቃወማት ወይም ‘ምን ታደርጋለህ?’ የሚለው የለም” ተብሏል።  (ዳን. ፬፥፴፭) ይህን ወሰን የለሽና እንዲህ ነው ተብሎ የማይደረስበትን በጎ ፈቃዱን ነው “አባታችን ሆይ በሰማያት የምትኖር ስምህ ይቀደስ መንግሥትህ ትምጣ፣ ፈቃድህ በሰማይ እንደሆነች እንዲሁም በምድር ትሁን!”  እያልን በጸሎታችን የምንጠይቀው። (ማቴ. ፮፥፱-፲፩)

እንጀራችንን በማዕድ አቅርበን የዕለት እንጀራችንን ዛሬ ስጠን ብለን መጠየቃችን የእንጀራችን ቁልፉ በበጎ ፈቃዱ በኩል ስለሆነ ነው። እናም ያለ እርሱ ፈቃድ እንኖር ዘንድ አይቻለንምና ይህንን በጎ ፈቃዱን መነኮሳት በምናኔ ይማጸኑታል፡ ባህታውያን በበረሃ ደጅ ይጠኑታ፤ ካህናቱ በመቅደስ ይጠይቁታል፤ ምእመናንም ይናፍቁታል።  ምክንያቱም “ያለ እኔ ምንም ማድረግ አትችሉም” ተብሎ ተነግሯልና ነው። (ዮሐ. ፲፭፥፭) ስለዚህ ያለ እርሱ ፈቃድ የምንፈጽመው ጉዳይ የለንምና ሁል ጊዜ እንደ ፈቃዱ ልንኖር ተገባን። ክርስቲያን ማለት የበጎ ፈቃዱ ባለሟል ነውና፡፡

ይቆየን

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *