“የክርስቶስ መስቀል ከተቀበረበት ስለ መውጣቱ”

በቀሲስ ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ለማዳን የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀል በአይሁድ ክፋት ተቀብሮ ለሦስት መቶ አመታት ያህል ቆሻሻ እየተደፋበት ኖረ፡፡ በዚህ የአይሁድ የክፋት ሥራ በኢየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች በነገሩ እያዘኑ ቢኖሩም ከተቀበረበት ለማውጣት ግን አቅም አልነበራቸውም፡፡ ነገር ግን ከተቀበረበት ለማውጣት የሚያስችል መብትም ሆነ ሥልጣን ባያገኙም የተቀበረበትን ሥፍራ ግን ለይተው ያውቁት ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እስራኤልን ከሮም ቅኝ አገዛዝ ነጻ ለማውጣት ከስድሳ ስድስት(፷፮)  እስከ ሰብአ (፸) ዓ.ም ባደረጉት እንቅስቃሴ ጥጦስ የተባለው የሮም ንጉሥ ዘምቶ ኢየሩሳሌምን በሰብኣ(፸) ዓ.ም ደመሰሳት፡፡ ትልቁን የአይሁድ ቤተ መቅደስንም አቃጠለው፡፡ እስራኤላውያንም በመላው ዓለም ተበተኑ፡፡

ከዚህ በኋላ ክርስቲያኖች የተቀበረውን ቅዱስ መስቀል አስፈልገው ለማውጣት ቀርቶ በሃይማታቸውም ነጻነት ሊኖራቸው አልቻለም፡፡ ስለ ክርስትናቸውም ተሰዳጆች ሆኑ፡፡ በዚህም ምክንያት ቅዱስ መስቀሉ ለአይሁድ ያለ ማንም ከልካይ ለሦስት መቶ ዓመት ያህል የቆሻሻ መጣያ ሆኖ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን አይሁድ ተቀብሮና ተደፍኖ ይቀራል ያሉት የአምላካችን የልዑል እግዚአብሔር ኃይሉና ጥበቡ የሚገለጥበት፣ ድውያን የሚፈወሱበት፣ ሐዘንተኞች የሚጽናኑበት፣ የክርስቲያች መመኪያ የሆነው ቅዱስ  መስቀሉ በተአምራት ከተቀበረበት እንዲወጣ ፈቃዱ ስለሆነ ለዚህ ምክንያት የሚሆኑትን ንጉሥ ቆስጠንጢኖስንና ቅድስት ዕሌኒን ጊዜው ሲደርስ እግዚአብሔር አስነሣ፡፡

የታላቁ ቆስጠንጢኖስ እናት ንግሥት ዕሌኒ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ መስቀል በኢየሩሳሌም ተቀብሮ ለብዙ ዘመናት መኖሩን ትሰማ ስለ ነበር፤ ያንን በክፉዎች አይሁድ ተቀብሮ የሚኖረውን ቅዱስ መስቀል ከተቀበረበት አስቆፍራ ለማውጣት ስለት ተሳለች፡፡  ‹‹ልጇ ቆስጠንጢኖስ ከአሕዛባዊው ንጉሥ ከቁንስጣ የወለደችው ነውና ልጄ ክርስቲያን ቢሆንልኝ ከቁስጥንጥንያ ኢየሩሳሌም ሄጄ የክርስቶስን ቅዱስ መስቀል ከተቀበረበት አስቆፍሬ አወጣዋለሁ›› ብላ ስእለት ተስላ ነበር፡፡

ነገር ግን ታሪኩን ጠይቃ እንደሰማችው መሬት ውስጥ የተቀበረውን ቅዱስ መስቀል ስፍራውን እንዴት አገኘዋለሁ የሚል አሳብ ሁልጊዜ ያስጨንቃት ስለነበር፡፡ እናቱን ስለሚያስጨንቃት ስለ መስቀሉ ነገር ለቆስጠንጢኖስ አንድ ታላቅ ተአምር ተፈጸመለት፡፡  እሱም በሦስት መቶ አሥራ ሁለት (፫፻፲፪) ዓ.ም ቆስጠንጢኖስ ከጠላቱ ከመክስምያኖስ ጋር በሚልቪያን ብሪጅ የጦር ሜዳ ላይ ከመሰለፉ በፊት ሊዋጋ እየተዘጋጀ ሳለ እንዴት አድርጎ ጠላቱን ተዋግቶ ማቸነፍ እንዳለበት ሲያወጣ ሲያወርድ አንድ በከዋክብትና በብርሃን የተሞላ መስቀል ከሰማይ ወደ ንጉሡ ቀረበ፡፡ በዚህ ብርሃን በተሞላ መስቀል ላይም ‹‹በዝንቱ ትእምርተ መስቀል ትመውዕ ፀረከ፤ በዚህ የመስቀል ምልክት ጠላትህን ታቸንፋለህ›› የሚል እጅግ የሚያበራ ጽሑፍ በሰማይ ላይ ተመለከተ፡፡

ቆስጠንጢኖስ ይህንን በራዕይ እንዳየ ወዲያውኑ መስቀሉ እግዚአብሔር በቸርነቱ የሰጠው ኃይል መሆኑን ተገንዝቦ በክርስቶስ በማመን ተጠመቀ፡፡ ምክንያቱም እናቱ ከልጅነቱ ጀምሮ ስለ ክርስትና ሃይማኖት ብዙ ነገር ስታስተምረው ቆይታለችና ለማመንና ክርስቲያን ለመሆን ብዙም አልተቸገረም፡፡ ያን እዚአብሔር ያሳየውን ጠላቶቹን ድል የሚያደርግበትን የመስቀል ምልክት በሰንደቅ ዓላማው ላይ በየጦር ሠራዊቱ ደረትና ልብስ፣ በየፈረሱ አንገትና በየመሣሪያው ሁሉ በጋሻቸው፣ በጦራቸው እንዲያደርጉ አዋጅ አስነገረ፡፡ የወርቅ መስቀል አስቀርጾም ከሠራዊቱ ፊት አስይዞ ዘመተ፡፡

ከዚያ  በኋላ  ክተት  ሠራዊት  ምታ  ነጋሪት  ብሎ  ዘመተባቸው፡፡  በውጊያው  ሰዓት በዲዮቅልጥያኖስና በመክሲምያኖስ ላይ አድረው ደም ያፈሱ የነበሩት አጋንንት በመስቀል ፊት መቆም አልቻሉምና ድል ሆኑ፡፡ ቆስጠንጢኖስም በመስቀሉ ምልክት ምክንያት ኃይለ አግዚአብሔርን ገንዘብ ስላደረገ እየተከተለ አጥፍቷቸዋል (ቆላ ፪፥፲፭)፡፡ ንጉሥ መክስምያኖስም በጦርነቱ በመገደሉ ቆጠንጢኖስ የእርሱን ቦታ ጠቅልሎ በመያዝ የሮማ ግዛት ብቸኛ ቄሳር አውግስጦስ ተባለ፡፡ ንጉሥ ቆስጠንጢኖስ ያ ወደ ጦር ሜዳ ለመሄድ ሲዘጋጅ ያየው የመስቀል ምልክትና ያስገኘለት ድል የክርስትናን ሃይማት የበለጠ እንዲወደድና እንዲያስፋፋ ብሎም ንጉሡ አይቀር ባመነበት በክርስትናው እንዲጠነክር፣ ክርስቲያኖችንም አብዝቶ እንዲወድ አድርጎታል፡፡ እንዲያውም ከዚያ በኋላ የቆስጠንጢኖስ የጦር ሠራዊት የሚለየውና መታወቂያ ምልክቱ መስቀል ሆነ፡፡

ይህንን ፈለግ የተከተሉት አባቶቻችንም መስቀልን በሚለብሱት ልብስ  ላይ  በመጥለፍ፣ በቤታቸው ጉልላት ላይ በማድረግ፣ በፈረሳቸው መጣብር ላይ በማስጌጥ፤ በጦራቸው ጫፍ በመሰካት፣ በአንገታቸው ማተብ በማንጠልጠልና በሰውነታቸው ላይ በመነቀስ የሕይወታቸው

መሠረት የደኅንነታቸው ዋልታ መሆኑን መስክረዋል፡፡ እንደነ ቅዱስ ላልይበላ ያሉ አባቶቻችን መስቀሉን በአስደናቂ ሁናቴ የቤተክርስቲያን መሠረትና ጉልላት አድርገው በሁለመናቸው አክብረውት በዘመናቸው ሁሉ ተመላለሱ፡፡ በመስቀሉ ኃይልም ደዌ ጸንቶባቸው የነበሩ ጤናቸውን አግኝተዋል፡፡ እውር የነበሩ አይተዋል፡፡ ልምሾም የነበሩ ተራምደዋል፡፡ በመሆኑም አባቶቻችን የክርስቶስን መስቀል የሚያፈቅሩት ሰይጣን ድል የሆነበት፤ የጠብ ግድግዳ የፈረሰበት ሰላማችን መሆኑን ስለተረዱ ነው፡፡ ምክንያቱም መስቀል ሰይጣን እራስ እራሱን የተቀጠቀጠበትና የተሸነፈበትን ሥልጣኑን የተገፈፈበት የክርሰቶስ ዙፋን ነውና፡፡

መስቀል  ሰይጣን በተንኮሉ በሰው ልጆች ላይ ያመጣው ሞት የሻረበት በመሆኑና ሰይጣን በሰው ልጆች ላይ የነበረውን የገዢነት ሥልጣኑን ያጣበት ስለሆነ አጥብቆ ይፈራዋል፡፡ ስለዚህም አባቶች መስቀሉን ከፊት ከኋላ ደጀን አድርገው ሰይጣን ያደረባቸውን ሠራዊቶች ድል አድርገዋል፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያም በአድዋ ላይ የሆነው ይኸው ነው፡፡ በመስቀሉ ኃይል ተማምነዋልና የመስቀል ምልክት (መስቀል) አናቱ ላይ (ከጫፉ ላይ) ባለው ጦርና ጎራዴ ብቻ እሳት የሚተፋ መትረየስ የታጠቁ የፋሽስት ኢጣሊያን ሠራዊት ማረኩ፡፡

የመስቀሉ ጠላት የሆነው ካቶሊካዊው ወራሪ በዘመናዊ የጦር መሳሪያ የኢትዮጵያን ዳር ድንበር በኃይል ሰባብሮ ወደ ውስጥ በመግባት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ምሽግ ለማድረግ ቢሞክርም አባቶቻችን እግዚአብሔርን ተማምነው የመስቀሉን ምልክት አድርገው የተኮሱት የመድፍ ጥይት ዘመናዊ በሆነው በጠላት መድፍ አፍ ውስጥ ገብቶ የሠራውን ምሽግ ንዶታል፡፡ ስለዚህ ምን ጊዜም ቢሆን ጠላት የሚንቀው መስቀል ለእኛ ኃይላችን፣ መመኪያችን፣ ሰላማችን፣ ማቸነፊያችን ነውና እናከብረዋለን፡፡

ወደቀደመ ነገራችን እንመለስና በመስቀሉ ኃይል በተገኘው ድል መሠረት ቆስጠንጢኖስ ጠንካራ ክርስቲያን ስለሆነ በግዛቱ ሁሉ ጣኦት አምልኮ አከተመለት፡፡ ይመለኩ የነበሩ ጣኦታት እንዲፈርሱ እነዚህ አላውያን ነገሥታት አንጸዋቸው የነበሩት አብያተ ጣኦታት እንዲዘጉና እንዲቃጠሉ ከንጉሡ ቆስጠንጢኖስ ትእዛዝ ወጣ፡፡ ዘመነ ሰማዕታት እየተባለ የሚጠራውምክርስቲያኖች ይገጠማቸው የነበረ የከፋ እንግልትና መከራ እንዲቆም ተደረገ፡፡ በነ ዲዮቅልጥኖስና መክስምኖስ ዘመን ፈርሰው፣ተቃጥለውና ተዘግተው የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት ተከፈቱ፣ የክርስቲያኖች የስቃይና የእንግልት ሕይወት በሰላም ተቀየረ፡፡ ምክንያቱም ታላቁ ቆስጠንጢኖስ የሮም ንጉሠ ነገሥት ከሆነ በኋላ ከሦስት መቶ(፫፻) ዓመታት በላይ ክርስቲያኖች አጥተውት የነበረውን ነጻነትና መብት መለሰላቸው፡፡ ለክርስቲያኖች ክብርና ሰላም እንዲሆንላቸውም አዋጅ አወጀ፡፡

ንግሥት ዕሌኒ ስእለቷ ስለሰመረላትና የልጇ የንጉሥ ቆስጠንጢኖስም ነገር ከጠበቀችው በላይ በሃይማኖቱ ጠንካራና ክርስቲያኖችን ወዳድ ስለሆነ እጅግ ተደሰተች፡፡ በተፈጠረላት ምቹ ሁኔታ የገባችውን ስእለቷን ለመፈጸም ተነሣች፡፡

ንግሥት ዕሌኒ ባገኘችው መልካም አጋጣሚ ለመጠቀም በሦስት መቶ ሃያ ስድስት(፫፻፳፮) ዓ.ም ሠራዊት አስከትላ የጌታችንን ቅዱስ መስቀሉን ከተቀበረበት ቦታ ፈልጋ ለማስወጣት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደች፡፡ በቦታውም በደረሰች ጊዜ መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ያውቁት የነበሩት ክርስቲያኖች በሰብአ (፸) ዓ.ም በጥጦስ ወረራ ከኢየሩሳሌም ተሰድደው ስለነበር መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ በቀላሉ ልታገኘው አልቻለችም ነበር፡፡ ስለሆነም መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ እንዲያሳዩአት ታሪክ የሚያውቁ የአካባቢው የአይሁድ ሽማግሌዎችን እየጠየቀች ነገር ግን በቶሎ የሚነግራት ብታጣም ስታፈላልግ ቆይታ ከብዙ ድካም በኋላ አንድ የአይሁድ ሽማግሌ (አረጋዊ) ኪራኮስ የሚባለውን በተጠቆመችው መሠረት አገኘችውና መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ እንዲነግራት በብዙ ጥበብ ተጠቅማ ጠየቀችው፡፡

እርሱም ‹‹አባቶቻችን ሲናገሩ እንደሰማነው ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን በቀበሩበት ቦታ ገቦታ በሚባለው ይኸውም ጎሎጎልታ ነው የከበረ መስቀሉን አባቶቻችን በዚያ ቀበሩት ሲሉ ሰማን፡፡ የከበረ የክርስቶስን መስቀል አይሁድ ከቀበሩት በኋላ የኢየሩሳሌምን ሰዎች ሁሉንም ሕዝብ ትልቁንም ታናሹንም ቤታቸውን የሚጠርጉ ሁሉ የቤታቸውን ጥራጊ ጉድፋቸውን በጌታ ኢየሱስ መቃብር ዕፀ መስቀሉን በቀበሩበት ጎልጎታ በሚባል ቦታ ወስደው በዚያ እንዲጥሉ አዘዟቸው ይሉ ነበር›› አላት፡፡ ዕሌኒ ንሥትም አረጋዊ ኪራኮስን የጌታችንየክርስቶስ መስቀል ከተቀበረ ምን ያህል ዓመት ይሆናል? አለቸው፡፡ ኪራኮስም ቅድስት ዕሌኒን እመቤቴ ሆይ አንቺ ወደዚህ እስከ ደረስሽበት ጊዜ ሦስት መቶ(፫፻) ዓመት ሆነው፡፡ ሰዎችም ሁሉ በላዩ የሚጥሉት የየቤት ጥረጊያቸውና ጉድፋቸው ታላቅ ኮረብታ እስኪሆን ድረስ የኢየሩሳሌም ሰዎችም ሁሉ የሚጥሉት ጉድፍ በሰው ክንድ አምስት መቶ ያህል ከፍ ከፍ አለ እመቤቴ ሆይ የጌታ ክርስቶስ የመስቀሉ ነገር እንዲህ ነው አላት፡፡

ንግሥት ዕሌኒም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል የተቀበረበትን ሥፍራ ስለሰማች እጅግ ደስ አላት፡፡ ስትናፍቀው የነበረውን መስቀሉ የተቀበረበትን አካባቢ (ሥፍራ) የሚያመላክት

ፍንጭ ስላገኘች እግዚአብሔርን እያመሰገነች እንዲህ ስትል ጸለየት ‹‹እኔ ከሩቅ ሀገር የከበረ መስቀልህን ለመፈለግ መጥቻለሁና ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ለሚጠሉኝ ጠላቶቼ አጋንንትና አንተን ለሰቀሉ ፈጽሞ የከበረ መስቀልህንም ለቀበሩ ዐመፀኞች አይሁድ መሳቂያና መዘባበቻ አታድርገኝ›› ብላ ጸለየች፡፡ እንዲህም ወደ ልዑል አምላክ ስትጸልይና ስትለምን ወዲያውኑ ‹‹በከበረ ደሜ የተቀደሰ መስቀሌ በመንግሥትሽ ወራት ዕሌኒ ሆይ ይገኝልሻል፣ ይገኝልሻል፣ ይገኝልሻል የሚል ቃል ሦስት ጊዜ ከሰማይ ሰማች አገልጋዬ ዕሌኒ ሆይ ከጥቂት ወራቶች በኋላ የፈለግሽውን ታገኚአለሽና ፈጽሞ ደስ ይበልሽ›› አላት፡፡

ከዚያም በኋላ መስቀሉ የተቀበረበትን ትክክለኛ ቦታ ለይቶ ለማወቅ የቆሻሻው ጥርቅም እንደ ተራራ ገዝፎ ስለነበር አስቸጋሪ ስለሆነባት እንዴት አድርጋ የክርሰቶስ መስቀል የተቀበረበትን ሌሎች ከጎኑ ካሉት ተራሮች መለየት እንደምትችል ከአረጋዊው ኪራኮስ በተነገራትና እገዚአብሔርን በጸሎት ጠይቃ ባገኘችው መልስ መሠረት ካህናቱና ሕዝቡን ሰብስባ በእንጨት ደመራ አስደምራ ጸሎትና ምህላ ካስደረሰች በኋላ ዕጣኑን ጨምራ ደመራውን በእሳት ለኮሰችው፡፡

በመሆኑም በእሳት ከተለኮሰው ደመራ የሚወጣው ጢስ ወደ ላይ ወጥቶ ወደታች ወደ ጎልጎታ በመመለስ መስቀሉ የተቀበረበት ቦታ ላይ በመተከል ያለበትን ቦታ በጣት ጠቅሶ እንደማሳየት ያህል አመለከተ፡፡ ንግሥት ዕሌኒም እሊህን ምልክቶችና እውነት የሆኑ ሥራዎችን ባየችና በተመለከተች ጊዜ ድምጿን ከፍ አድርጋ እንዲህ እያለች ዘመረች፡፡‹‹እውነት በእውነት ያለሐሰት የጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ በላዩ የከበረ ደሙ የፈሰሰበት መስቀሉ የተቀበረበት ቦታው ይህ ነው›› እያለች በደስታ እግዚአብሔርን አመሰገነች፡፡

ከዚህ በኋላ ንግሥት ዕሌኒ ለአገልጋዮቿና ለሠራዊቶቿ የክብር ባለቤት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት ዕፀ መስቀሉ ለተቀበረበት ቦታ ምልክቱ ይህ ነው አለቻቸው፡፡ በመሆኑም ንግሥት ዕሌኒ የጢሱን ስግደት ተመልክታ ጢሱ ያረፈበት ቦታ ቅዱስ መስቀሉ የተቀበረበት እንደሆነ በማመን ቅዱስ መስቀሉ ከዚህ ቦታ አለ ብሎ ሲጠቁመን ነው በማለት ሳትጠራጠር በመስከረም ወር በዐሥራ ሰባተኛው ቀን የጌታችን ክርስቶስ ዕፀ መስቀል በውስጡ የተቀበረበት እስከሚገኝ እጅግ ጥልቅ አድርገው ምድሩን ይቆፍሩ ዘንድ ሠራዊቶቿና ሕዝቡን ሁሉ አዘዘቻቸው፡፡

ከዚህ በኋላ ጭፍሮቿና ሁሉም የአይሁድ ሕዝብ መስቀሉን ለማግኘት መስከረም ዐሥራ ሰባት ቀን መቆፈር ጀመሩ፡፡ አስቀድመውም በላዩ የተጣለና የተደፋ እንደ ኮረብታ ሆኖ መጠኑ በሰው ክንድ አምስት መቶ የሆነው የአይሁድን ጉድፋቸውንና ጥራጊያቸውን አነሡ፡፡ ከዚያም ቀጥለው በሰው ክንድ ዘጠና ዘጠኝ ያህል ወደታች አጥልቀው በቆፈሩ ጊዜ ጠንካሮች የሆኑ የተጣመሙ ደንጊያዎችን አስቀድሞ አገኙ፡፡ እንዚያንም ደንጊያዎች ባነሱ ጊዜ ከጥልቁ ጉድጓድ ውስጥ ታላቅ ብርሃን  ወጣ  እንደ  ፀሐይም  አንፀባረቀ፡፡  በዚያንም  ጊዜሁለት  መስቀሎችን  አግኝተው አወጧቸው፡፡ ቀጥሎም የጠነከሩና የጠመሙ ደንጊያዎችን አወጡ፡፡ ከዚህም በኋላ ከአምስት ችንካሮች ጋር ሌላ መስቀልን አገኙ እሱም ጌታችን የተሰቀለበት ቅዱስ መስቀሉ ነው፡፡

እሊህም ችንካሮች፡- ሳዶር፣ አላዶር፣ ዳናት፣ አዴራ ሮዳስ የሚባሉ ናቸው፡፡ ሰፍነጉን ራሱን የመቱበት ሽመሉን፣ ከለሜዳውን የክብር ባለቤት ጌታ ኢየሱስን የገረፉበትንና ያሰቃዩበትን ዕቃዎች ሁሉን ከቅዱስ መስቀሉ ጋር አገኙ፡፡ ይህም የሆነው ቁፋሮው መስከረም ፲፯ ተጀምሮበመጋቢት ወር በ፲ኛው ቀን ነው፡፡ ይህም ማለት በሦስት መቶ ሃያ ሰባት (፫፻፳፯) ዓ.ም በመጋቢት ፲ ቀን ቅዱስ መስቀሉ ከተቀበረበት ቦታ ወጣ ማለት ነው፡፡

ይሁን እንጂ ወዲያውኑ ቆፍረው እንዳወጡት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ጋር ሁለቱ ወንበዴዎች የተሰቀሉባቸውንም መስቀሎች አብረው ስላገኙ ቅዱስ መስቀሉን መለየት አልቻሉም፡፡ በእርግጥ ታሪኩ እንደሚነግረን ከተገኙት ሦስት መስቀሎች መካከል አንደኛው መስቀል ልክ ከጉድጓዱ ሲያወጡት ቦግ ብሎ ብርሃን ፈነጠቀበትና አካባቢውን ሁሉ ብርሃን አጥለቀለቀው በማለት ያስረዱናል፡፡

ይሁን እንጂ በቅዱስ መስቀሉ ላይ የብርሃን ምልክት ቢታይም በእውነት ክርስቶስ የተሰቀለበትን መስቀል  ሁለቱ  ወንበዴዎች  ከተሰቀሉባቸው መስቀሎች ለመለየትና ለማረጋገጥይቻል  ዘንድ የኢየሩሳሌም ጳጳስ የሆኑት አቡነ መቃርዮስ ሦስቱንም መስቀሎች በተራ እንዲያስቀምጡአቸውና አንድ የሞተ ሰው አስክሬን እንዲያመጡ አዘዙ፡፡ የሞተውን ሰው አስከሬንም በአንደኛው መስቀልና በሁለተኛው መስቀል ላይ አደረጉት የሞተው ሰው አልተነሣም፡፡ በሦስተኛው መስቀል ላይ ቢያስቀምጡት ግን ያ የሞተ ሰው አፈፍ ብሎ ተነሣና ለክርስቶስ መስቀል ምስጋና አቀረበ፡፡ በቅዱስ መስቀሉ ሌሎችም ድንቆች ተአምራቶች ተፈጸሙ፡፡ ዕውሮችን አብርቷል፣ ድውያን

ፈውሷል፣ ጎባጦችን አቅንቷል፣ በነዚህና መሰል ገቢረ ተአምራቶች ክርስቶስ የተሰቀለበትና የከበረ ደሙ የፈሰሰበት ቅዱስ መስቀሉ ከሌሎች ተለይቶ ታውቋል፡፡

በዚያም የነበሩ ሰዎች ሁሉ እጆቹንና እግሮቹን ለሕማም በዕፀ መስቀል ላይ የዘረጋ እግዚአብሔርን አመስግነዋል፡፡ ሕዝቡ ሁሉ በተገለጡት ተአምራቶችና በክርስቶስ መስቀል በተፈጸሙት ተአምራቶች ደስታቸው እጅግ ጥልቅ ስለነበር በእንባ ጭምር የደስታ ስሜታቸውን አንፀባርቀዋል፡፡ ቅድስት ዕሌኒም በዚህ ጊዜ አሳቧና ምኞቷ ስለተፈጸመላትና በቅዱስ መስቀሉ የተደረጉትን ተአምራቶች በዐይኖቿ ማየት በመቻሏ ደስታዋ ወደር አልነበረውም፡፡ እግዚአብሔርንም በብዙው አመሰገነች፡፡ ለጌታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ መስቀልም ሰገደች፡፡ ጭፍሮቿም ሆኑ የተሰበሰቡ የኢየሩሳሌም ሕዝቦች ሁሉ ለቅዱስ መስቀሉ በታላቅ አክብሮት ሰገዱ፡፡ መስቀሉንም እየዳሰሱ ተሳለሙት፣ ሕሙማንም እየዳሰሱትተፈወሱ፣ የኢየሩሳሌሙ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ መቃርዮስም እጅግ ደስ ብሏቸው ፈጣሪያችንን አመሰገኑ፡፡

ቀኑ መሽቶ ጨለማ በሆነ ጊዜም ብፁዕ አቡነ መቃርዮስና ንግሥት ዕሌኒ ሠራዊቱና ሕዝቡ ሁሉ በሰልፍ የችቦ መብራት ይዘው እየዘመሩ ቅዱስ መስቀሉን ወስደው በአንድ የጸሎት ቤት አስቀመጡት፡፡ ከዚህ በኋላ ንግሥት ዕሌኒ እንዲህ ስትል ካህናቱን አዘዘቻቸው ‹‹የከበረ ዕፀ መስቀልን ከወርቅ በተሠራ ግምጃ አጎናጽፉት ብሩህ በሆነ ልብስም ጠቅልሉት በሰማያዊ ዕንቊ ሸፍናችሁም ከወርቅ ዐልጋ ላይ አውጡት ከወርቅ ሣጥንም ውስጥ አስገቡት አለቻቸው›› እነርሱም እንደታዘዙት አድርገው ቅዱስ መስቀሉን በክብር አኖሩት፡፡ ቅድስት ዕሌኒ በመስቀሉ መገኘት ደስ እየተሰኘችና እግዚአብሔርን እያመሰገነች በቅዱስ መስቀሉ ስም በኢየሩሳሌምና በሮሜ አገር ቤተክርስቲያንን አንፃለች፡፡ በኢየሩሳሌምም አስቀድማ በከበረ መስቀል ስም ታላቅ ቤተ ክርስቲያን አንጻለች፡፡ ቀጥላም በእመቤታችን ስም ብዙ አብያተ ክርስቲያናትን አነጸች፡፡ ንግሥት ዕሌኒ ያሠራቻቸውን አብያተ ክርስቲያናት በወርቅ፣ በብር፣ በዕንቊ መርገድ፣ ጳዝዮን በሚባሉ ዕንቊዎች፣ አስጌጠቻቸው፡፡

ቅድስት ዕሌኒ ለከበረው ለክርስቶስ መስቀል እጅግ የሚያምር ቤተ ክርስቲያን ካሳነጸች በኋላ በቅዱስ መስቀሉ ስም ታላቅ በዓልን በማድረግ ለድሆችና ለምስኪኖች፣ ለባልቴቶችና ለሙት ልጆች ታላቅ ምሳን አዘጋጀች፡፡ ስለጌታችን ክርስቶስ መስቀልም ስለ ክብሩ መኳንንቶችን መሳፍንቶችንና የሀገር ሰዎችን ሁሉ ጠራቻቸው፡፡ ብዙ ላሞችንና ሰንጋዎችን፣ በጎችንና ፍየሎችን አሳረደች፡፡ በዚያች ዕለትም የታረዱት የቁጥራቸው መጠን ላሞች ዘጠኝ ሺህ፣ በጎች

ሰባ ሺህ፣ ፍየሎች ሰባ ሺህ፣ ዶሮዎች ዘጠኝ ሺህ ናቸው፡፡ በዚህ መልኩ በዓልን አድርጋ በቅዱስ መስቀሉ ስም ብዙዎችን መገበች፡፡

ንግሥት ዕሌኒ እንዲህ ባው መልካም ሥራ ከኖረች በኋላ በሦስት መቶ ሃያ ስምንት (፫፻፳፰) ዓ.ም በክብር አርፋለች፡፡ ታላቁ ቆስጠንጢኖስም በሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት(፫፻፴፯) ዓ.ም ግንቦት ሃያ ሁለት (፳፪) ቀን የጰራቅሊጦስ ዕለት በኀምሳ አራት (፶፬) ዓመቱ በነገሠ በሠላሳ አንድ (፴፩) ዓመቱ በክብር ዐረፈ፡፡ በመሆኑም እናትና ልጅ በሠሩት ክርስቲያናዊና ሐዋርያዊ ተግባር ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስታስታውሳቸው ትኖራለች፡፡ ቅዱስ መስቀሉ የተገኘበትንም መጋቢት ፲ ቀን ስብሐተ እግዚአብሔር በማድረስ የመስቀሉን ኃይል እየመሰከረች አክብራ ትውላለች፡፡

ከቅዱስ መስቀሉ ረድኤት በረከት ያሳትፈን አሜን፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *