“ቅድስት”

በቀሲስ ኃይለ ሚካኤል ብርሃኑ

የዐቢይ ጾም ሁለተኛ ሳምንት ቅድስት ይባላል፡፡  እንደሚታወቀው የዐቢይ ጾም ሳምንታት ሁሉ ስያሜ አላቸው፡፡ ስያሜአቸውም   የእግዚአብሔር ባሕርይ የሚገለጽባቸውና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ስለ ማዳኑ ስለተቀበለው ጸዋትወ መከራ የሚያስረዱ ናቸው፡፡ የመጀመሪያው ሳምንት ዘወረደ፣ሙሴኒ፣ሕርቃል የሚሉ መጠሪያዎች ያሉት ሲሆን ዘወረደ ማለት መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰው ሆነ፣ከሰማየ ሰማያት ወረደ ከቅድስት ድንግል ማርያም ተወለደ ሕግ መጽሐፋዊንና ሕግ ጠባይዓዊን እየፈጸመ ከኃጢአት በቀር ሁሉን እያደረገ በተለይም ለእኛ አብነት የሚሆንባቸውን ሁሉ እየሠራ ቀስ በቀስ አደገ ማለት ነው፡፡

በቃሉ ትምህርት ደዌ ነፍስን በእጁ ተአምር ደዌ ሥጋን ከሰው ልጅ እያራቀ ፍጹም አምላክ ሲሆን የሰውነትን ሥራ ሠራ፡፡ፍጹም ሰው ሲሆን የአምላክነትን ሥራ ሠራ፡፡ በመሆኑም “ዘወረደ” አምላክ ሰው በመሆን የፈጸመልንን የማዳኑን ሥራ የምንመሰክርበት ነው፡፡

ሌላው “ሙሴኒ” ብለን ሳምንቱን መጥራታችን ሊቀ ነቢያት ሙሴ እንደሚታወቀው እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ነፃ አውጥቶ ባሕር ከፍሎ ያሻገራቸው የእግዚአብሔር ሰው ነው፡፡ ሙሴን ለዚህ አገልግሎት የመረጠው ራሱ እግዚአብሔር ነው፡፡ የሙሴም መሪነት የተፈጸመው በእግዚአብሔር ኃይል በቃሉ ነው፡፡ ሙሴ እስራኤል ከግብጽ እንዳወጣ ሁሉ መድኃኒታችን ኢሱስ ክርስቶስም አዳምንና የልጅ ልጆቹን ሁሉ ከሞት ወደ ሕይወት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን ከሲኦል ወደ ገነት የመለሰ ነውና ሙሴኒ ተብሎ ተሠየመ፡፡

በሌላ መልኩ “ሕርቃል” መባሉም  ሕርቃል የሮም ንጉሥ በነበረበት ሰዓት ክርስቲያኖች ቅዱስ መስቀሉን በፋርሳውያን ተነጥቀው ስለ ነበር ክርስቲያኖችን ረድቶ መስቀሉን ከፋርሳውያን እጅ በጦርነት አሸንፎ ለክርስቲያኖች ለማስመለስ በሚያደርገው ውጊያ ላይ ክርስቲኖች የጾሙለት የመስቀሉንም መመለስ በጾም በጸሎት እግዚአብሔርን የጠየቁበት ስለሆነ ጾመ ሕርቃል ተብሎ ተሰይሟል፡፡

የዐቢይ ጾም የመጀመሪያው ሳምንት (ዘወረደ) ቀጥሎ ያለው ሁለተኛው ሳምንት ቅድስት ይባላል፡፡ ቅድስት መባሉም አምላካችን ቅዱስ እግዚአብሔር በባሕርዩ ቅዱስ መሆኑንና  እኛን ለቅድስና የጠራን መሆኑን “እኔ ቅዱስ ነኝና ቅዱሳን ሁኑ” በማለት ለክብር ያጨን መሆናችንን እያሰብን የምናመሰግንበት ሳምንት ነው፡፡ እግዚአብሔር ቅዱስ ነው ስንል የእርሱ ቅድስና ከቅዱሳን መላእክት እና ከቅዱሳን ጻድቃን፣ከቅዱሳን ሰማዕታት ይለያል፡፡ የቅዱሳኑ ሁሉ ቅድስና የጸጋ ነውና፡፡

በባሕርዩ ፍጹም ቅዱስ የሆነ ከማንም ያላገኘው ማንም ያልሰጠውና የማይወስድበት ቅዱስ እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ነው ነቢዩ ኢሳይያስ ሱራፌል በቅዳሴያቸው ያለማቋረጥ  ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ ብለው የሚያመሰግኑት መሆኑን የገለጸው፡፡ “አንዱም ለአንዱ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያለ ይጮኽ ነበር”(ኢሳ.፮፥፫)ይላል፡፡

እግዚአብሔር ቅዱስ በመሆኑ ሰውም በንጽሕና በቅድስና እንዲመስለውና እንዲያገለግለው ይፈልጋል፡፡ ሰንበት እግዚአብሔር ለምስጋና ያዘጋጃት ከሥጋ ሥራ አርፈን የነፍስ ሥራ እንሠራባት ዘንድ የተሰጠችን የተቀደሰች ቀን ናት፡፡ ይህንንም እንድናስብ  የዐቢይ ጾም ሁለተኛው ሳምንት   ቅድስት ተብሎአል፡፡

እግዚአብሔር ከሥራው ሁሉ ያረፈባትን ቀዳሚት ሰንበት ከዕለታት ሁሉ የለያትና የቀደሳት ሲሆን በዚህች ዕለት ከሥጋ ሥራ ሁሉ እንድናርፍባት ቀድሶ ሰጥቶናል ይህቺም ዕለት ከሥነ ፍጥረት ጀምሮ ትታሰብ የነበረች ቢሆንም በኦሪት ሕግ ግን በጉልህ እግዚአብሔር ለሙሴ በሲና ተራራ እስራኤል ይመሩበት ዘንድ  ከሰጠው ሕጎች መካከል አንዱዋ ሆና ተጠቅሳለች(ዘፀ.፳፥፩)፡፡

ሰንበተ ክርስቲያን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ  ዓለሙን ሁሉ ከሞት ከኩነኔ ለማዳን ሞትን በሞቱ ደምስሶ ወደ ቀደመ ክብራችን በመመለስ ቅድስት ትንሣኤውን ያየንባት ዕለት ሰንበተ ክርስቲያን (እሑድን) የተቀደሰ ሥራ በመሥራት የሰንበትን ቅድስና እያሰብን የምናከብር በመሆናችን ይህ ስያሜ ተሰጥቷል፡፡

                               ወስብሐት ለእግዚአብሔር

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *