የአዲስ አበባ ማእከል በግቢ ጉባኤያት ያስተማራቸውን ተማሪዎች አስመረቀ

በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አበባ ማእከል ከመደበኛ ትምህርታቸው በተጨማሪ የቅድሰት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ትምህርት ተከታትለው ያጠናቀቁ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፮፻ የግቢ ጉባኤያት ተማሪዎችን ሐምሌ ፲፬ ቀን ፳፻፲፭ ዓ.ም በጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽርሐ ተዋሕዶ አዳራሽ በድምቀት አስመረቀ፡፡

መርሐ ግብሩ በጸሎተ ወንጌል የተጀመረ ሲሆን ማኅበረ ቅዱሳንን በመወከል ከሥራ አመራር ጀምሮ በልዩ ልዩ ማስተባበሪያዎች ለረጅም ዓመታት በማገልግል የሚታወቁት በአሁኑ ወቅት የሕብረት ባንክ ም/ፕሬዚዳንት የሆኑት በኩረ ትጕሃን አንዱዓለም ኃይሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡ በመልእክታቸውም፡- “መመረቃችሁ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ የምትጀምሩበትና ሥራ ለመቀጠርና በጋራ ሆናችሁ ሥራ የምትፈጥሩበት ጊዜ ላይ ደርሳችኋል፡፡ የምታገኟቸውን ዕድሎች መጠቀም፣ ራሳችሁን ማሳደግና በሙያችሁ ብቃት ያላችሁ (  Profesional) ሁኑ፤ ከሁሉም በላይ ግን ፈቃደ እግዚአብሔርን አስቀድሙ” በማለት ከሕይወት ተሞክሯቸው ተነሥተው ለተመራቂዎች ምክርና መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

የመርሐ ግብሩ አካል ከነበሩት ውስጥ አንዱ የዕለቱ ትምህርት ወንጌል ሲሆን በመ/ር ኢዮብ ይመኑ “ሌላ ሸክም አላሸክማችሁም፤ ነገር ግን እስክመጣ ድረስ ያላችሁን ጠብቁ” (ራእ.፪፥፳፭) በሚል ርእስ ለተመራቂዎች ለወደፊት ሕይታቸው ሥንቅና መመሪያ የሚሆን ትምህርት ሰጥተዋል፡፡

በማኅበረ ቅዱሳን የአዲስ አባባ ማእከል ጸሐፊ የሆኑት አቶ ካሣሁን ኃይሌ በኩላቸው ባስተላለፉት መልእክትም “በየጊዜው ማኅበራችሁ ማኅበረ ቅዱሳን እናንተን በማስተማር፣ በመምከር፣ የሕይወት አቅጣጫዎችን በመጠቆም፤ የታተሙ መጻሕፍትን እና ጽሑፎችን በማዳረስ መንፈሳዊ ምግብ እንድትመገቡ ሲያደርግ ቆይቷል፤ እንዲሁም በመደበኛው ትምህርታችሁ እንድትበረቱ ሐሳብ በመስጠት፣ በመደገፍ ንስሓ ገብታችሁ የምሥጢራት ተካፋይ እንድትሆኑ በማድረግ በሕይወታችሁ ላይ ለውጥ አምጥታችኋል” ብለዋል፡፡

አቶ ካሳሁን ከተመራቂዎች የሚጠበቅባቸውን ሲገልጹም “በምትሄዱበት ሁሉ በመንፈሳዊ ሕይወት ራሳችሁን እያነጻችሁ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ባስታጠቀቻችሁ መንፈሳዊ ትጥቅ ሌሎችን በማጽናት በተለይም በልዩ ልዩ ጭንቀት ውስጥ ያለውንና መድረሻ አጥቶ የሚባዝነውን ትውልድ ትታደጉ ዘንድ መትጋት ይጠበቅባችኋል፡፡” ሲሉ የአደራ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

በተመራቂዎች የቀረቡት የበገናና እና የያሬዳዊ ወረብ፣ እንዲሁም የልዩ ፍላጎት ተመራቂዎች ያቀረቧቸው መንፈሳዊ ዝማሬዎች የመርሐ ግብሩ ልዩ ድምቀት ነበሩ፡፡ በምረቃ መርሐ ግብሩም ላይ ተመራቂዎች፣ የተመራቂ ቤተሰቦች፣ የማኅበረ ቅዱሳን ማስተባበሪያ ኃላፊዎች፣ የግቢ ጉባኤያት መምህራንና የተመራቂዎቹ የንስሓ አባቶች የተገኙ ሲሆን ለተመራቂዎች የአደራ መስቀል በካህናት አባቶች ተባርኮ ተበርክቶላቸዋል፡፡

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *