“እንድታገኙ ፈጽማችሁ ሩጡ” (፩ኛቆሮ. ፱÷፳፬)

በዲ/ን ግርማ ተከተለው

ቃሉን የተናገረው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሁለት የሕይወት ገጽታ እንደ ነበረው ይታወቃል። የመጀመሪያው በክርስቶስ ከማመኑ በፊት ምሁረ ኦሪት፣ ኋላ ደግሞ የሐዲስ ኪዳን ሐዋርያነትን የተጎናጸፈ ቅዱስና ታማኝ አገልጋይ ነው። ከአሳዳጅነት ተጠርቶ ሰዎችን ለመንግሥተ ሰማይ ይበቁ ዘንድ በጽናት ያስተማረ፣ ለክርስቶስ ፍቅር ሲል ልዩ ልዩ ፀዋትወ መከራዎችን በመቀበል በሰማዕትነት ያረፈ ታላቅ የቤተ ክርስቲያናችን ሐዋርያ ነው።

ቅዱስ ጳውሎስ በጻፋቸው ፲፬ መልእክታት በሁለት ሥፍራዎች ስለ ሩጫ አስተምሯል። የመጀመሪያው፡- “መልካሙን ገድል ተጋድዬአለሁ፥ ሩጫዬን ጨርሼአለሁ፥ ሃይማኖቴን ጠብቄአለሁ…” በማለት ለመንፈስ ልጁ ለጢሞቴዎስ ጽፎለታል። (፪ኛጢሞ. ፬÷፯) በዚህ አንቀጽ ከእርሱ የሚለይበት ጊዜ መድረሱን፣ የሚያስጨንቅ ጊዜ /ዘመን/ መምጣቱንና በዚህ ጊዜም ልጁ ጢሞቴዎስ እንዴት መኖርና እንዴት ማገልገል እንዳለበት ያስረዳበት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሁሉን ታግሦ አገልግሎቱን በታማኝነት፣ በትጋት እንዲሁም የተጠራበትን ዓላማ ተረድቶ በማገልገሉም ምን ዓይነት ሽልማት እንደሚጠብቀው ነግሮታል።

ሁለተኛው፡- “በእሽቅድምድም ሥፍራ የሚሽቀዳደሙ ሁሉ እንደሚፋጠኑ አታውቁምን? ለቀደመው የሚደረግለት ዋጋ አለ፤ እንዲሁ እናንተም እንድታገኙ ፈጽማችሁ ሩጡ።” በማለት በሩጫ መስሎ መንፈሳዊ ቁም ነገርን አስተምሯል። (፩ኛቆሮ. ፱÷፳፬) ሩጫ በጥንቷ ግሪክ በስፋት ይታወቅና ይዘወተር የነበረ፤ ታላላቅ ሽልማቶችንም ያስገኝ የነበረ የስፖርት ዓይነት ነው። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ሩጫ በዚህ ዘመን የተጀመረ ሳይሆን በጥንት ዘመንም የነበረ ስፖርት መሆኑንና የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችንም በሚያውቁትና በሚገባቸው መልኩ እንዳስተማራቸው እንረዳለን። ጌታችንም በመዋዕለ ሥጋዌው የተለያዩ ምሳሌዎችን በመጠቀም በሰሚዎቹ የአኗኗር ዘይቤ አንጻር ሲያስተምር እንደነበር ይታወቃል። ለምሳሌ በዘር በመንገድ በእርሾ፤ በበግና በፍየል እየመሰለ አስተምሯል። (ማቴ. ፲፫፥፲፮፤ ፳፭፥፴፩-፴፬፤ሉቃ. ፲፪፥፲፫)

በሩጫ ውድድር እናሸንፋለን ብለው የሚሮጡ ብዙዎች ቢሆኑም የሮጠ ሁሉ ግን ሽልማት (ሜዳልያ) አያገኝም። ለምሳሌ በአንድ ጊዜ የሚሮጡ መቶ ሰዎች ቢሆኑ፣ ሦስቱ ሰዎች የሜዳልያ ተሸላሚዎች ሲሆኑ፣ ሌሎቹ ደግሞ ተሸናፊ ይሆናሉ። ሁሉም ይሮጣሉ፣ ሁሉ ግን ተሸላሚ አይሆኑም ማለት ነው። እንደዚሁ ሁሉ የክርስትናን ሕይወት ለመኖር መንፈሳዊ ሩጫን የሚጀምር ብዙ ነው፤ ነገር ግን በአግባቡና በትጋት እየወደቁና እየተነሡ ሩጠው የሚጨርሱ ጥቂቶች ናቸው፡፡ “የተጠሩ ብዙዎች፥ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና” እንዲል። (ማቴ. ፳÷፲፮)

በክርስትና ሕይወት መንፈሳዊውን ፍሬ ለማፍራትና ለሽልማት ለመብቃት ያሉትን ውጣ ውረዶች ሁሉ ታግሦና በዓላማ ሩጦ መጨረስን ይጠይቃል። በሩጫ ውጤት የሚያስመዘግቡ አትሌቶችን ስንመለከት፣ ለዚህ ስኬት የሚበቁት በብዙ ትዕግሥትና ድካም አሰልቺውን ልምምድ አልፈው ነው። ያሰኛቸውን ሁሉ አይበሉም፣ አይጠጡም። መርጠው ይበላሉ፣ መርጠው ይጠጣሉ ማለት ነው። መተኛት ቢያስፈልጋቸውም የሞቀ አልጋቸውን ትተው በጠዋት ማልደው በመነሣት ልምምድ ያደርጋሉ። ከዚህ የምንረዳው ለመሮጥ የሚያስፈልጉ ነገሮች መኖራቸውን ነው። ምግብና መጠጥ አመራረጥ፣ እንቅልፍ መተው፣ ተግቶ ልምምድ ማድረግ፣ ለሩጫ ሕግ መገዛት አስፈላጊ ከሆኑ ነገሮች ጥቂቶቹ ናቸው። በክርስትና ሕይወትም እንዲሁ ነው። የተገኘውን ሁሉ ከመብላት ይልቅ ንቆ ትቶ በመጾም፤ እንቅልፍን በመተው ተግቶ በመጸለይ፤ ከራስ ቀንሶ ለሌላ በመስጠት፤ ዓለማዊውን ሽልማት ንቆ ለእውነት በመቆም እንዲሁም ለሥጋችን ዕረፍት የሚሆኑ ጊዜን፣ ገንዘብን፣ ጉልበትን ለመንፈሳዊ አገልግሎት በማዋል ለሽልማት መብቃት ያስፈልጋል።

ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ ይህንን የቅዱስ ጳውሎስን ትምህርት አብራርቶ ባስተማረበት ድርሳኑ፤ ለሩጫ ሦስት ነገሮች ያስፈልጋሉ ይላል። አንደኛው፡- በሩጫ ጊዜ ብዙ ተመልካቾች ከመኖራቸው የተነሣ በተለይ ዙሩን በመምራት ላይ ላሉት በማጨብጨብና በመጮህ ድጋፍ ይሰጣሉ። በዚህ ጊዜ ይላል ሊቁ፣ ሯጮቹ ዘወር ብለው አጨብጫቢዎቹን መመልከት የለባቸውም። ሁለተኛ፡- ሯጮቹ መመልከትና መከተል ያለባቸው ከፊታቸው ያሉትን የቀደሟቸውን እንጂ ከኋላቸው ያሉትን መሆን የለበትም። በሦስተኛ ደረጃ፡- በዚያን ዘመን እንደ አሁኑ የሩጫ ሜዳ ኖሮ ሳይሆን ሩጫ የሚከናወነው በአትክልት ሥፍራ ነው። በዚህ ሥፍራ ደግሞ የተለያዩ ለመብላት የሚያስጎመጁ ፍራፍሬዎች አሉ። ስለዚህ ሯጩ ፍራፍሬውን ለመብላት ሩጫውን ማቆም የለበትም። ምንም እንኳ ፍራፍሬዎቹ ለመብላት የሚያስጎመጁ ቢሆኑም ለዓላማው ሲል ሽልማቱን ላለማጣት ታግሦ መሮጥ ያስፈልጋል። ሊቁ በክርስትና ሕይወትም እንዲህ ነው ይላል።

አንድ ክርስቲያን በመንፈሳዊ ሕይወቱ ብዙ ሩጫዎች አሉበት። ጾም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ ቅዳሴ፣ ምጽዋት፣ ዘወትር ቃለ እግዚአብሔርን መስማት፣ በአጠቃላይ ክርስቲያናዊ ሕይወትና ሥነ ምግባር በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ሊኖሩ የሚገቡ ሩጫዎች ናቸው። እነዚህን ተግባራት ለመፈጸም ደግሞ የምንተዋቸው ብዙ ሥጋዊ ፍላጎቶች አሉን፡፡ ነገር ግን በዚህ ሕይወት ውስጥ ያለፉ፣ ሩጫቸውን በድል ያጠናቀቁትን አብነት አድርገን የምንከተላቸው ቅዱሳን አባቶቻችንና እናቶቻችን አሉ። ለምሳሌ ጾምን ለመጾም ርኀብን መታስ ያስፈልጋል፣ በተለያዩ የሥራ ቦታዎች የሚቀርቡልንን ሥጋዊ ፍላጎቶቻችንን የሚቀሰቅሱና ለሥጋ ድሎት ብቻ የሚሆኑ ጥቅማ ጥቅሞችን መናቅ፣ መተው ያስፈልጋል። ጸሎትን ለማቅረብ ጊዜን መሥዋዕት ማድረግን፣ እንቅልፍን መተውን፣ ዘወትር ደጅ መጥናትን ይጠይቃል። ሌሎችንም መንፈሳዊ ተግባራት ለመፈጸም ብዙ ንቀን የምንተዋቸው ነገሮች መኖር አለባቸው። ካልሆነ ከጀመርነው ሩጫ ያሰናክሉንና ሽልማትን ለማግኘት፣ ገነት መንግሥተ ሰማያትየመግትን ዕድል ያሳጡናል።

በሩጫ ጊዜ ደጋፊዎችም ነቃፊዎችም እንዳሉ ሁሉ፣ የክርስትናውን ሕይወት ጉዞ ስንጀምርም እንዲሁ የሚነቅፉንና በውዳሴ ከንቱ ሊጥሉን የሚፈልጉ አያሌ አካላት ሊኖሩ ይችላሉ። በዚህ ጊዜም ጊዜያችንን በአግባቡ ለመጠቀምና ላለመውደቅ /ላለመሸነፍ/ ትኩረታችንን ማድረግ ያለብን በሩጫችን (በመንፈሳዊ ሕይወታችን) ላይ መሆን አለበት። በሐዋርያት ሕይወትም ይህ ዓይነቱ ፈተና አጋጥሞ እንደ ነበር መረዳት ይቻላል። ቅዱስ ጳውሎስና በርናባስ መንፈሳዊውን አገልግሎት (ያመኑትን ላላመኑት በሚያስተምሩበት ጊዜ) ካላመኑት አይሁዳውያን ተቃውሞ ደርሶባቸው ነበር። በሌላ ቦታ ደግሞ የሚያደርጉትን ተአምራት በመመልከት ሊያወድሷቸው /ሊያመልኳቸው/ ፈልገውም ነበር። ሁለቱም ሐዋርያት ለሁለቱም ሁኔታዎች ቦታ አልሰጡም። ምክንያቱም በደረሰባቸው ተቃውሞው ተስፋ ቢቆርጡ፤ የቀረበላቸውን ከንቱ ውዳሴና የተሰጣቸውን የማይገባቸውን ቦታ ተቀብለው ቢሆን ኖሮ ከጀመሩት ሩጫ ይሰናከሉ ነበር፤ የቀረበላቸውንም አክሊል ያሳጣቸው ነበር። ስለዚህ ሩጫችንን /መንፈሳዊ ሕይወታችንን/ ከሚያደናቅፉ ነገሮች ራሳችን መቆጠብ እና በመንፈሳዊ ሩጫችን መትጋት ያስፈልጋል፡፡

ሐዋርያው “እንድታገኙ ፈጽማችሁ ሩጡ” እንዳለን፤ ክርስቲያን ሁል ጊዜም በዓላማ የሚጓዝ፣ የጀመረውን ሩጫም /መንፈሳዊ ሕይወት/ ምንነትና የሚያስገኘውን ዋጋ በሚገባ መረዳት ይጠበቅበታል። ምንም እንኳን በዚህ ምድር መንፈሳዊ በመሆናችንና በእግዚአብሔር በመታመናችን የምናገኛቸው ብዙ ነገሮች ቢኖሩም፤ ለእኛ ለክርቲያኖች የመጨረሻ ሽልማት ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀልንን መንግሥቱን መውረስ ነውና ለዚህ የሚያበቃንን ሩጫችንን በአግባቡና በትጋት መሮጥ ይገባል።

የእግዚአብሔር ቸርነት፣ የድንግል ማርያም አማላጅነት፣ የቅዱሳን ሁሉ ተራዳኢነት አይለየን፤ አሜን!

0 replies

Leave a Reply

Want to join the discussion?
Feel free to contribute!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *